‘ስለ አምላክ መንግሥት የተሟላ ምሥክርነት መስጠት’
1. ሚያዝያ 28 ከሚጀምር ሳምንት አንስቶ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ የምናጠናው ምንድን ነው?
1 ‘ስለ አምላክ መንግሥት የተሟላ ምሥክርነት መስጠት’ የተባለውን መጽሐፍ ሚያዝያ 28 ከሚጀምር ሳምንት አንስቶ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ እናጠናለን። ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው አንባቢው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸውን ስሜት ቀስቃሽ ትረካ እያጣጣመ እንዲያነብ ለመርዳት ታስቦ ነው። የተሟላ ምሥክርነት መስጠት የተባለው መጽሐፍ እያንዳንዱን ምዕራፍ ቁጥር በቁጥር የሚያብራራ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከሰፈሩት ዘገባዎች ትምህርት እንድናገኝና የተማርነውን ነገር እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደምንችል እንድንገነዘብ ይረዳናል።—ሮም 15:4
2. የተሟላ ምሥክርነት መስጠት የተባለው መጽሐፍ ያሉትን አንዳንድ ገጽታዎች ጥቀስ።
2 መጽሐፉ ያሉት ገጽታዎች፦ በገጽ 2 ላይ የሚገኘው የመጽሐፉ መግቢያ፣ የበላይ አካሉ ይህን መጽሐፍ እንዴት እንድንጠቀምበት እንደሚፈልግ የገለጸበትን ፍቅር የሚንጸባረቅበት ደብዳቤ ይዟል። ከምዕራፍ 2 ጀምሮ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የሚገኘው አጭር መግለጫ፣ ምዕራፉ የሚያተኩርበትን ዋና ሐሳብ ይገልጻል፤ ጥቅሱ ደግሞ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የትኛው ክፍል እንደሚብራራ ይጠቁማል። ብዙዎቹ ምዕራፎች፣ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ስለተጠቀሱ ሰዎች፣ ቦታዎች ወይም ክስተቶች ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን የያዙ ሣጥኖች አሏቸው። በየገጾቹ ላይ ያሉት ሰፋፊ ኅዳጎች ማስታወሻ ለመጻፍ ያስችሉናል። በጥንቃቄ ታስቦባቸው የተሠሩትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን ታሪኮች የሚያሳዩት በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት ማራኪ ሥዕሎች በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል ይረዱናል፤ በተጨማሪም በመጨረሻው ገጽ ላይ የሚገኘው የሥዕል ማውጫ በሥዕሎቹ ላይ የሚታየው ምን እንደሆነ ያብራራል። የሽፋኖቹ የውስጠኛ ገጽ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የእምነት ባልንጀሮቻችን ምሥራቹን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ሲያሰራጩ የሄዱባቸውን መንገዶች በዓይነ ሕሊናችን እንድስል የሚረዱ ካርታዎችን ይዘዋል።—ሥራ 1:8
3. የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ማጥናታችን ለየትኞቹ ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ያስገኝልናል?
3 ወሳኝ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት፦ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን መመርመራችን ከክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ወሳኝ ጥያቄዎች ግልጽ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ እውነተኞቹን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ለይቶ የሚያሳውቀው የትኛው ሥራና መልእክት ነው? ይህን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ የሚመራው ማን ነው? የሚመራውስ እንዴት ነው? ስደትና ተቃውሞ ለአገልግሎታችን የሚጠቅም ምን አጋጣሚ ይከፍታሉ? መንፈስ ቅዱስ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ምን ሚና ይጫወታል?
4. ይህንን መጽሐፍ ስናጠና የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 ከዚህ መጽሐፍ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ጽሑፉን ቀደም ብላችሁ አጥኑት፤ እንዲሁም በጉባኤ በሚጠናበት ወቅት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንድትችሉ በደንብ ተዘጋጁ። በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ያገኛችሁትን ትምህርት በአገልግሎት ላይ ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ አሰላስሉ። ይህንን አስደሳች መጽሐፍ ማጥናታችን ስለ አምላክ መንግሥት የተሟላ ምሥክርነት ለመስጠት እንዲያንቀሳቅሰን እንመኛለን!—ሥራ 28:23