በቅርብ አስቀምጡት
እነዚህን ብሮሹሮች እየተጠቀማችሁባቸው ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው?
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እምብዛም እውቀት የሌላቸው በተለይ ደግሞ ከክርስትና ሃይማኖት ውጪ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ
እንዴት ማበርከት እንችላለን? “በዚህ ጥቅስ (ወይም ቅዱስ መጽሐፍ) ላይ ስለሚገኝ አንድ ሐሳብ ምን አስተያየት እንዳለዎት ብናውቅ ደስ ይለናል። [መዝሙር 37:11ን አንብብ፤ ጥቅሱ በክፍል 11 ላይ ተጠቅሷል።] ይህ ትንቢት ሲፈጸም በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ የሚኖር ይመስልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] የትኛውም ዓይነት ባሕልና እምነት ያላቸው ሰዎች እንዲህ ያሉ ተስፋዎችንና ማጽናኛዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ይችላሉ።” ገጽ 3 ላይ ያለውን የመግቢያ ሐሳብ ካነበብክ በኋላ ብሮሹሩን አበርክት።
የሚከተለውን ሐሳብ ልትሠራበት ትችላለህ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት የምታስጠናው ከክርስትና ሃይማኖት ውጪ ያለ ጥናት ካለህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ የሆነ ግንዛቤ እንዲያገኝ በጥናቱ መጀመሪያ ወይም መጨረሻ ላይ ጥቂት ደቂቃዎችን ወስደህ ከብሮሹሩ አንድ ክፍል አወያየው።
ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እምብዛም እውቀት የሌላቸው የተማሩ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ
እንዴት ማበርከት እንችላለን? 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ። ከዚያም እንዲህ በል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ በሚገልጸው በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ? ወይስ እንዲሁ ጥሩ መጽሐፍ ብቻ እንደሆነ ይሰማዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ብዙ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የራሳቸው የሆነ አስተያየት ቢኖራቸውም በትክክል መጽሐፍ ቅዱስን የመረመሩ ሰዎች ግን በጣም ጥቂት ናቸው። [ገጽ 3 መጀመሪያ ላይ የሚገኘውን ተሞክሮ አንብብለት።] ይህ ግሩም ብሮሹር መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ ያለብን ለምን እንደሆነ የተለያየ ባሕል፣ የኑሮ ደረጃና እምነት ላላቸው ሰዎች አጥጋቢ ምክንያት ያቀርባል።”
የሚከተለውን ሐሳብ ልትሠራበት ትችላለህ፦ የቤቱ ባለቤት ብሮሹሩን ከተቀበለ እንዲህ በል፦ “ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ምንም ጥቅም እንደሌለው አድርገው እንዲያስቡ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ ሃይማኖቶች ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለሚያስተምራቸው ትምህርቶች የተሳሳተ መልእክት ስለሚያስተላልፉ ነው። በሚቀጥለው ጊዜ ስመጣ ለዚህ ምሳሌ የሚሆን ነገር ልነግርዎት እችላለሁ።” ተመልሰህ ስትሄድ ከገጽ 4-5 ላይ ከሚገኙት ሐሳቦች አንዳንዶቹን አብራችሁ ተመልከቱ።
የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ!
የትምህርት ደረጃቸው አነስተኛ ወይም የማንበብ ችሎታቸው ውስን የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ
እንዴት ማበርከት እንችላለን? “የአምላክ ወዳጅ መሆን የሚቻል ይመስልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው፤ ከዚያም ያዕቆብ 2:23ን አንብብ።] ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ልክ እንደ አብርሃም የአምላክ ወዳጅ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ እኛን ለመርዳት ተብሎ ነው።”
የሚከተለውን ሐሳብ ልትሠራበት ትችላለህ፦ በመጀመሪያው ቀን ላይ ወይም ተመልሰህ ስትሄድ ክፍል 1ን በሙሉ ወይም በከፊል በማወያየት መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማጥናት እንደሚቻል አሳየው።
የምትወዱት ሰው ሲሞት
የሚወዷቸውን ዘመዶቻቸውን በሞት ያጡ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ። ይህ ደግሞ ሃይማኖተኛ ወይም ለሃይማኖት እምብዛም ፍላጎት የሌላቸውን ሰዎች ይጨምራል።
እንዴት ማበርከት እንችላለን? “የሚወዷቸውን ዘመዶቻቸውን በሞት ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽናኛ ያገኙበትን ይህን ብሮሹር ለሰዎች እያስተዋወቅን ነበር። የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ እንዳላቸው ጠይቀው ያውቃሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው፤ ከዚያም ዮሐንስ 5:28, 29ን አብራችሁ አንብቡ። የብሮሹሩን ገጽ 27 አን. 3 ማውጣት ትችላለህ።] የዚህን ብሮሹር አንድ ቅጂ ልሰጥዎት እችላለሁ።”
የሚከተለውን ሐሳብ ልትሠራበት ትችላለህ፦ የሚከተለውን ጥያቄ መጠየቅ ትችላለህ፦ “የሚወደውን ዘመዱን በሞት ያጣ ሰው ለማጽናናት ሞክረው ያውቃሉ?” ከዚያም በገጽ 20 ላይ የሚገኘውን “ሌሎች እንዴት መርዳት ይችላሉ?” የሚለውን ንዑስ ርዕስና ምሳሌ 17:17ን ልትጠቅስለት ትችላለህ።
የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች
በትምህርት ቤታቸው ስለ ዝግመተ ለውጥ የሚማሩ ክርስቲያን ወጣቶችን አልፎ ተርፎም በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ፣ በአምላክ መኖር የሚጠራጠሩና አምላክ የለሽ የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ (ይህ ብሮሹር ከቤት ወደ ቤት ለማበርከት ተብሎ የተዘጋጀ አይደለም።)
በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑና አምላክ የለሽ የሆኑ ሰዎች ሲያጋጥሙህ እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን? “ሁሉም የሳይንስ መማሪያ መጻሕፍት ማለት ይቻላል ስለ ዝግመተ ለውጥ ያስተምራሉ። ዝግመተ ለውጥን የሚመለከቱት በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ እንዳለ ትምህርት አድርገው ነው? ወይስ የተረጋገጠ ሐቅ እንደሆነ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] በእውቀት ላይ የተመሠረተ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንድንችል በቅድሚያ ጉዳዩን ከሁለቱም ወገን መስማት ይኖርብናል ቢባል እንደሚስማሙ እርግጠኛ ነኝ። ይህ ብሮሹር ብዙ ሰዎች ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው ብለው እንዲያምኑ ያደረጓቸውን አንዳንድ ማስረጃዎች ያቀርባል።”
የሚከተለውን ሐሳብ ልትሠራበት ትችላለህ፦ ተማሪ ከሆንክ ብሮሹሩን ዴስክህ ላይ አስቀምጠው፤ ከዚያም ከክፍልህ ተማሪዎች መካከል ትኩረቱ የተሳበ ተማሪ እንዳለ ለማስተዋል ሞክር።
የሙታን መናፍስት—ሊረዱህ ወይም ሊጎዱህ ይችላሉ? ደግሞስ በእርግጥ አሉ?
መናፍስታዊ ድርጊቶች በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ
እንዴት ማበርከት እንችላለን? “ብዙ ሰዎች ከሙታን ጋር እንደተገናኙ ሲናገሩ ይሰማል። አንዳንዶቹ ደግሞ የሞቱ ዘመዶቻቸውን ድምፅ በመስማታቸው ፍርሃት እንዳደረባቸው ይናገራሉ። ይህ ነገር እውነት ነው ብለው ያምናሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው፤ ከዚያም መክብብ 9:5, 10ን አብራችሁ አንብቡ።] መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወት ይቀጥላል እንደማይል አስተዋሉ? ታዲያ ሰዎች ከሙታን ጋር እንደተገናኙ የሚናገሩት ለምንድን ነው? ይህ ብሮሹር ይህን ጉዳይ ያብራራል። በተጨማሪም ወደፊት ስለተዘጋጀው አስደናቂ ተስፋ ይገልጻል።
የሚከተለውን ሐሳብ ልትሠራበት ትችላለህ፦ የቤቱ ባለቤት ለተናገርከው የመግቢያ ሐሳብ ፍላጎት ካሳየ ብሮሹሩን አበርክትና በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ያዝ። ተመልሰህ ስትሄድ ከገጽ 13-18 ላይ የሚገኙትን ነጥቦች ተወያዩባቸው።