የመታሰቢያውን በዓል የምናስተዋውቅበት ዘመቻ መጋቢት 1 ይጀምራል
1. ሰዎችን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ መጋበዝ የምንጀምረው መቼ ነው? በዚህ ዓመት ዘመቻው የሚቆይበት ጊዜ የተራዘመው ለምንድን ነው?
1 በየዓመቱ ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል ከእኛ ጋር እንዲያከብሩ ለመጋበዝ የምናደርገው ዘመቻ በዚህ ዓመት ዓርብ፣ መጋቢት 1 ይጀምራል። የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው መጋቢት 26 ሲሆን ይህ ዘመቻ ከዚህ በፊት ከነበሩት ረዘም ያለ ይሆናል። ይህ ደግሞ ብዙ ሰዎች የመጋበዣ ወረቀቱ እንዲደርሳቸው ያደርጋል፤ በተለይ ሰፊ ክልል ባላቸው ጉባኤዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በዓሉ ላይ እንዲገኙ ጥሩ አጋጣሚ ይከፍታል።
2. የመጋበዣ ወረቀቱን ለመውሰድም ሆነ ክልሎችን ለመሸፈን ምን ዝግጅት ይደረጋል?
2 በሚገባ ተደራጁ፦ ሽማግሌዎች የጉባኤው ክልል እንዴት መሸፈን እንዳለበት መመሪያ ይሰጣሉ፤ ይህም ቤታቸው ለማይገኙ ሰዎች የመጋበዣ ወረቀቱን መተው እንደሚኖርብንና እንደማይኖርብን የሚሰጠውን መመሪያ ይጨምራል። ከቤት ወደ ቤት አገልግለን የመጋበዣ ወረቀቱ ከተረፈን በአደባባይ ምሥክርነት ልናሰራጨው እንችላለን። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ፣ አድራሻ የታተመባቸው የመጋበዣ ወረቀቶች መጽሔት በሚቀመጥበት ቦታ ላይ መኖራቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል፤ ሆኖም ሁሉም መጋበዣ ወረቀት በአንድ ጊዜ መውጣት የለበትም። በአንድ ጊዜ መውሰድ ያለብን የመጋበዣ ወረቀት መጠን በአንድ ሳምንት ውስጥ የምንጠቀምበትን ያህል ብቻ መሆን አለበት።
3. የመጋበዣ ወረቀቱን ስናሰራጭ ምን ነገር መርሳት የለብንም?
3 ምን እንላለን? መግቢያችን አጭር መሆኑ የተሻለ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ለብዙ ሰዎች የመጋበዣ ወረቀቱን ለማሰራጨት ያስችለናል። እንደ ክልላችን ሁኔታ ልንለውጠው የምንችል የመግቢያ ሐሳብ በገጽ 4 ላይ ይገኛል። እርግጥ ነው፣ የቤቱ ባለቤት ወዳጃዊ ስሜት ካሳየን ወይም ጥያቄ ካለው ከቤቱ ተቻኩለን መውጣት አይኖርብንም። ቅዳሜና እሁድ በምናደርገው የማሰራጨት ዘመቻ ላይ ሁኔታው አመቺ እንደሆነ ከተሰማን መጽሔቶችንም ማበርከት እንችላለን። መጋቢት 2 ትኩረት የምናደርገው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ በመጋበዝ ላይ ሳይሆን የመጋበዣ ወረቀቱን በማሰራጨት ላይ ነው።
4. በዘመቻው በቅንዓት መካፈል ያለብን ለምንድን ነው?
4 በመታሰቢያው በዓል ላይ ብዙ ሰዎች ከእኛ ጋር እንደሚገኙ ተስፋ እናደርጋለን። በዚያ የሚቀርበው ንግግር ኢየሱስ በእርግጥ ማን እንደሆነ ጥሩ አድርጎ ያብራራል። (1 ቆሮ. 11:26) እንዲሁም የእሱ ሞት ለእኛ ምን ጥቅም እንዳስገኘ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ሮም 6:23) በተጨማሪም ኢየሱስን ማስታወስ ያለብን ለምን እንደሆነ ያብራራል። (ዮሐ. 17:3) እንግዲያው በዘመቻው በቅንዓት እንካፈል!