ሰዎችን ስናስተምር ውጤታማ ለመሆን ዝግጅት አስፈላጊ ነው
ኢየሱስ ቢያንስ በሁለት አጋጣሚዎች የዘላለም ሕይወትን በተመለከተ ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፤ ይሁንና በሁለቱም ጊዜያት መልስ የሰጠው ጥያቄውን ያቀረቡትን ግለሰቦች ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። (ሉቃስ 10:25-28፤ 18:18-20) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የምንጠቀምበትን ጽሑፍ በሚገባ ብናውቀውም የምናስተምረውን ሰው በአእምሯችን ይዘን መዘጋጀት ይኖርብናል። ተማሪው ለመረዳት ወይም ለማመን የሚከብዱት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? የትኞቹን ጥቅሶች አብረን ማንበብ ይኖርብናል? ምን ያህል አንቀጾችን ብናጠና ይሻላል? የምናስተምረው ሰው ትምህርቱን መረዳት እንዲችል ምሳሌ፣ የማብራሪያ ሐሳብ ወይም ጥያቄዎችን ማዘጋጀት ሊያስፈልገን ይችላል። በተጨማሪም የእውነት ዘር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ እንዲያድግ የሚያደርገው ይሖዋ እንደመሆኑ መጠን ለጥናቱ የምናደርገውን ዝግጅት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የምናስተምረውን ሰው እንዲሁም እሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት እንዲባርክልን ይሖዋን በጸሎት መጠየቅ አለብን።—1 ቆሮ. 3:6፤ ያዕ. 1:5