የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 መጋቢት ገጽ 26-31
  • የይሖዋ እጅ መቼም ቢሆን አጭር አይደለም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋ እጅ መቼም ቢሆን አጭር አይደለም
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከሙሴ እና ከእስራኤላውያን የምናገኘው ትምህርት
  • የገንዘብ ችግር ሲያጋጥመን
  • ወደፊት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ስለምናሟላበት መንገድ ዕቅድ ስናወጣ
  • ታማኝ ሰዎች ከተናገሯቸው የስንብት ቃላት ተማሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ይሖዋ “ሕያው አምላክ” እንደሆነ አስታውስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 መጋቢት ገጽ 26-31

የጥናት ርዕስ 13

መዝሙር 4 “ይሖዋ እረኛዬ ነው”

የይሖዋ እጅ መቼም ቢሆን አጭር አይደለም

“ለመሆኑ የይሖዋ እጅ አጭር ነው?”—ዘኁ. 11:23

ዓላማ

ይሖዋ በቁሳዊ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚያሟላልን መተማመን እንዲሁም ይህን እምነታችንን ማጠናከር።

1. ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ አውጥቶ እየመራ ሲወስዳቸው በይሖዋ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው?

የዕብራውያን መጽሐፍ ግሩም የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ይዘረዝራል፤ ከእነዚህ ውስጥ ጎልቶ የሚጠቀሰው ሙሴ ነው። (ዕብ. 3:2-5፤ 11:23-25) እስራኤላውያንን ከግብፅ እየመራ ሲያወጣ እምነት አሳይቷል። በፈርዖንና በሠራዊቱ አልተሸበረም። በይሖዋ ተማምኖ ሕዝቡን ቀይ ባሕርን አሻገረ፤ በኋላም እየመራ ወደ ምድረ በዳ ወሰዳቸው። (ዕብ. 11:27-29) አብዛኞቹ እስራኤላውያን ይሖዋ ለእነሱ የሚያስፈልገውን ማቅረብ መቻሉን ተጠራጥረው ነበር። ሙሴ ግን በአምላክ ላይ ያለውን እምነት አላጣም። ደግሞም እንደ እምነቱ ሆኖለታል፤ አምላክ በዚያ ጠፍ ምድረ በዳ ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን ምግብና ውኃ በተአምር አቅርቧል።a—ዘፀ. 15:22-25፤ መዝ. 78:23-25

2. አምላክ ሙሴን “ለመሆኑ የይሖዋ እጅ አጭር ነው?” ብሎ የጠየቀው ለምንድን ነው? (ዘኁልቁ 11:21-23)

2 ይሖዋ እስራኤላውያንን በተአምር ከታደገ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ግን የሙሴ እምነት ተፈተነ፤ ሙሴ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ሥጋ ማቅረብ መቻሉን ተጠራጠረ። ይሖዋ በዚያ ወና ምድር በሚሊዮኖች የሚቆጠረውን ያን ሁሉ ሕዝብ ሊያጠግብ የሚችል ሥጋ ማግኘት ይችላል ብሎ ማሰብ ሙሴን ከበደው። ስለዚህ ይሖዋ “ለመሆኑ የይሖዋ እጅ አጭር ነው?” በማለት ጠየቀው። (ዘኁልቁ 11:21-23⁠ን አንብብ።) እዚህ ላይ “የይሖዋ እጅ” የሚለው አገላለጽ የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ይኸውም በሥራ ላይ የዋለ ኃይሉን ያመለክታል። በሌላ አባባል ይሖዋ ‘እውነት አደርገዋለሁ ያልኩትን ነገር ማድረግ እንደሚሳነኝ ታስባለህ?’ በማለት የጠየቀው ያህል ነበር።

3. ሙሴና እስራኤላውያን ያጋጠማቸው ነገር የእኛንም ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ የሚያስፈልጋችሁን ቁሳዊ ነገር እንደሚያቀርብ ተጠራጥረህ ታውቃለህ? ይህ ጥርጣሬ ኖረህም አልኖረህ በዚህ ርዕስ ላይ ከምንመረምረው ታሪክ የምትማረው ቁም ነገር አለ። አምላክ ለእነሱ የሚያስፈልገውን ነገር ማቅረብ መቻሉን የተጠራጠሩትን የሙሴንና የእስራኤላውያንን ታሪክ እንመለከታለን። የይሖዋ እጅ መቼም አጭር እንዳልሆነ ያለንን እምነት ለማጠናከር የሚረዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እናያለን።

ከሙሴ እና ከእስራኤላውያን የምናገኘው ትምህርት

4. ብዙ እስራኤላውያን ይሖዋ ለእነሱ የሚያስፈልገውን ማቅረብ መቻሉን መጠራጠር የጀመሩት ለምን ሊሆን ይችላል?

4 እስቲ አውዱን እንመልከት። ከግብፅ የወጡት እስራኤላውያን እንዲሁም እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎችን ያቀፈው “እጅግ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” ወደ ተስፋይቱ ምድር እየተጓዙ ነው። ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ላይ መጓዝ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። (ዘፀ. 12:38፤ ዘዳ. 8:15) ድብልቁ ሕዝብ መና መብላት ሰለቸው፤ በርካታ እስራኤላውያንም እንደ እነሱ ስለተሰማቸው አብረዋቸው ማጉረምረም ጀመሩ። (ዘኁ. 11:4-6) ሕዝቡ በግብፅ ይበሉ የነበሩትን ምግብ መናፈቅ ጀመሩ። የሕዝቡ ጥያቄ ሙሴን አስጨነቀው፤ ለእነሱ የሚያስፈልገውን ማቅረብ የእሱ ኃላፊነት እንደሆነ የተሰማው ይመስላል።—ዘኁ. 11:13, 14

5-6. የድብልቁ ሕዝብ መንፈስ ወደ ብዙ እስራኤላውያን መጋባቱ ምን ያስተምረናል?

5 እስራኤላውያን ምስጋና ቢስ የሆኑት ከድብልቁ ሕዝብ ተጋብቶባቸው ሳይሆን አይቀርም። እኛም ካልተጠነቀቅን የምስጋና ቢስነት መንፈስ ሊጋባብንና ይሖዋ በሚሰጠን ነገር እርካታ ልናጣ እንችላለን። ቀድሞ የነበረንን ነገር መናፈቅ ወይም እኛ የምንመኛቸው ነገሮች ባሏቸው ሰዎች መቅናት ከጀመርን ይህ መንፈስ ሊያድርብን ይችላል። የኑሯችን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ባለን የምንረካ ከሆነ ግን ደስተኞች መሆን እንችላለን።

6 እስራኤላውያን የተትረፈረፉ ቁሳዊ ነገሮችን የሚያገኙት ወደ አዲሱ መኖሪያቸው ሲደርሱ እንደሆነ አምላክ የሰጣቸውን ማረጋገጫ ማስታወስ ነበረባቸው። አምላክ የገባላቸው ቃል ፍጻሜውን የሚያገኘው በተስፋይቱ ምድር እንጂ ምድረ በዳ ላይ በሚጓዙበት ወቅት አይደለም። እኛም በተመሳሳይ በዚህ ሥርዓት ባላገኘናቸው ነገሮች ላይ ማተኮር የለብንም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በአዲስ ሥርዓት ውስጥ ሊሰጠን ቃል ስለገባቸው ነገሮች ማሰባችን የተሻለ ነው። በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር በሚረዱን ጥቅሶች ላይ ማሰላሰላችንም ይጠቅመናል።

7. የይሖዋ እጅ አጭር አለመሆኑን መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

7 ይሁንና አምላክ “ለመሆኑ የይሖዋ እጅ አጭር ነው?” በማለት ሙሴን የጠየቀው ለምንድን ነው? ይሖዋ ሙሴን ሊያስገነዝበው የፈለገው እውነታ ያለ ይመስላል። ይህም እጁ ብርቱ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የትም ሊደርስ የሚችል መሆኑን ጭምር ነው። እስራኤላውያን ጭልጥ ባለ ምድረ በዳ መሃል ቢሆኑም ይሖዋ እነሱን የሚያጠግብ ሥጋ ማምጣት አይሳነውም። አምላክ “በኃያል እጅና በተዘረጋ ክንድ” ምንም እንደማይሳነው አሳይቷቸዋል። (መዝ. 136:11, 12) እኛም ከባድ ሁኔታ ውስጥ በምንገባበት ጊዜ የይሖዋ እጅ እኛ ያለንበት ቦታ መድረስ መቻሉን ፈጽሞ ልንጠራጠር አይገባም።—መዝ. 138:6, 7

8. ብዙ እስራኤላውያን ምድረ በዳ ላይ የሠሩትን ስህተት እንዳንደግም ምን ይረዳናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

8 ይሖዋ እንደተናገረው ሥጋ ሰጣቸው፤ የድርጭት መንጋ አምጥቶ ከመረላቸው። እስራኤላውያን ግን አምላክን ለዚህ ተአምር አላመሰገኑም። እንዲያውም ብዙዎች ስግብግብነት ተጠናወታቸው። ቀን ከሌት ድርጭት ሲሰበስቡ ቆዩ። ይሖዋ ‘ሲስገበገቡ በነበሩት ሰዎች’ ተቆጣ፤ በመሆኑም ቀጣቸው። (ዘኁ. 11:31-34) እኛም ከዚህ ታሪክ ትምህርት እናገኛለን። ስግብግብነት እንዳያሸንፈን መጠንቀቅ አለብን። ሀብታምም ሆንን ድሃ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባው ‘በሰማይ ለምናከማቸው ሀብት’ ነው፤ ይህን የምናደርገው ደግሞ ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ተግተን በመሥራት ነው። (ማቴ. 6:19, 20፤ ሉቃስ 16:9) እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

እስራኤላውያን ምድረ በዳ ላይ በምሽት ብዛት ያለው ድርጭት ሲሰበስቡ።

ብዙዎች ምድረ በዳ ላይ ምን ዓይነት መንፈስ አሳይተዋል? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)


9. ከአምላክ ከምናገኘው ድጋፍ ጋር በተያያዘ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

9 ይሖዋ ዛሬም አገልጋዮቹን ለመርዳት እጁን ይዘረጋል። ይህ ሲባል ግን ፈጽሞ አንቸገርም ወይም አንራብም ማለት አይደለም።b ይሁንና ይሖዋ ሁሌም ከጎናችን ይሆናል። የሚያጋጥሙንን የተለያዩ ችግሮች ማለፍ እንድንችል አቅም ይሰጠናል። ይሖዋ በተዘረጋ እጅ የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች እንደሚያሟላልን ያለንን እምነት ማሳየት የምንችልባቸውን ሁለት ሁኔታዎች እንደ ምሳሌ እንመልከት፦ (1) የገንዘብ ችግር ሲያጋጥመን እና (2) ወደፊት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ስለምናሟላበት መንገድ ዕቅድ ስናወጣ።

የገንዘብ ችግር ሲያጋጥመን

10. ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ምን ችግር ሊያጋጥመን ይችላል?

10 ይህ ሥርዓት ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ሲሄድ የኢኮኖሚው ሁኔታ እየተባባሰ እንደሚመጣ እንጠብቃለን። የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም አዲስ የሚነሳ ወረርሽኝ ያልጠበቅነው ወጪ ሊያስከትልብን አሊያም ሥራችንን፣ ንብረታችንን ወይም ቤታችንን እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል። ባለንበት አካባቢ አዲስ ሥራ ማፈላለግ አሊያም ሥራ ፍለጋ ወደ ሌላ አካባቢ ቤተሰባችንን ይዘን መሄድ ሊያስፈልገን ይችላል። ታዲያ በይሖዋ እጅ እንደምንተማመን የሚያሳዩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ምን ይረዳናል?

11. የገንዘብ ችግርን ለመቋቋም ምን ሊረዳህ ይችላል? (ሉቃስ 12:29-31)

11 በዋነኝነት ልትወስደው የሚገባው ውጤታማ እርምጃ ያሳሰበህን ነገር ለይሖዋ መንገር ነው። (ምሳሌ 16:3) ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ ጠይቀው፤ ስላለህበት ሁኔታ ከልክ በላይ ‘እንዳትጨነቅ’ ልብህን እንዲያረጋጋው ለምነው። (ሉቃስ 12:29-31⁠ን አንብብ።) ለኑሮ የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች ካሉህ በዚያ ረክተህ ለመኖር እንዲረዳህ ጠይቀው። (1 ጢሞ. 6:7, 8) የገንዘብ ችግር ላጋጠማቸው ሰዎች ጠቃሚ ምክር የያዙ ሐሳቦች ለማግኘት በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርግ። ብዙዎች የኢኮኖሚ ችግሮችን መወጣት ስለሚቻልበት መንገድ jw.org ላይ ያገኟቸው ሐሳቦች በጣም ጠቅመዋቸዋል።

12. አንድ ክርስቲያን ቤተሰቡን የሚጠቅም ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የትኞቹን ጥያቄዎች ራሱን መጠየቅ ይችላል?

12 አንዳንዶች ከቤተሰባቸው ተለይተው መኖርን የሚጠይቅ የሥራ አጋጣሚ ለመቀበል ተፈትነዋል። ይህ ግን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል። ሥራ ስትመርጥ ከገንዘብ አንጻር የሚያስገኝልህን ጥቅም ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊነትህ ረገድ የሚያስከፍልህን ነገርም ግምት ውስጥ አስገባ። (ሉቃስ 14:28) ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ከትዳር ጓደኛዬ ተለይቼ መኖሬ በትዳሬ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል? ርቄ መሄዴ የስብሰባና የአገልግሎት ልማዴን እንዲሁም ከወንድሞች ጋር የማሳልፈውን ጊዜ የሚነካብኝ እንዴት ነው?’ ልጆች ካሉህ ደግሞ ልታነሳው የሚገባ ሌላ አስፈላጊ ጥያቄም አለ፦ ‘ከልጆቼ ጋር በአካል አብሬያቸው ካልሆንኩ “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ላሳድጋቸው የምችለው እንዴት ነው?’ (ኤፌ. 6:4) ውሳኔ ስታደርግ በአምላክ አስተሳሰብ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማያደርጉ የቤተሰብ አባላት ወይም ወዳጆች አመለካከት አትመራ።c በምዕራብ እስያ የሚኖረው ቶኒ በርካታ የውጭ አገር የሥራ ዕድሎች አግኝቶ ነበር። በጉዳዩ ላይ ከጸለየበትና ከባለቤቱ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ግን የሥራ ዕድሎቹን ላለመቀበል ወሰነ። ከዚህ ይልቅ የቤተሰባቸውን ወጪዎች መቀነስ ስለሚችሉበት መንገድ ከባለቤቱ ጋር ተማከረ። ቶኒ ያደረገውን ውሳኔ መለስ ብሎ ሲያስብ እንዲህ ብሏል፦ “በርካታ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ የመርዳት መብት አግኝቻለሁ። ልጆቻችን እውነትን እንዲወዱ አድርገን ማሳደግም ችለናል። ማቴዎስ 6:33 ላይ ባለው ምክር ሕይወታችንን ከመራን ይሖዋ ምንጊዜም የሚያስፈልገንን እንደሚሰጠን ቤተሰባችን ተምሯል።”

ወደፊት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ስለምናሟላበት መንገድ ዕቅድ ስናወጣ

13. በእርጅናችን ዘመን የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላት እንድንችል ከአሁኑ ምን ምክንያታዊ እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?

13 በእርጅናችን ዘመን የሚያስፈልገንን ነገር ማሟላት ስለምንችልበት መንገድ ዕቅድ ስናወጣም በይሖዋ እጅ ላይ ያለን እምነት ሊፈተን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት የምንጠቀምበት ቁሳዊ ነገር እንዲኖረን ከአሁኑ ተግተን እንድንሠራ ያበረታታናል። (ምሳሌ 6:6-11) አቅማችን በፈቀደው መጠን ለወደፊቱ ጊዜ ተቀማጭ ገንዘብ መቆጠብ ምክንያታዊ ነው። እውነት ነው፣ ገንዘብ በመጠኑም ቢሆን ጥበቃ ያስገኛል። (መክ. 7:12) ሆኖም ገንዘብ ለማስቀመጥ የምናደርገው ጥረት በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያውን ሊይዝ አይገባም።

14. ወደፊት የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ስለማሟላት ስናስብ ዕብራውያን 13:5⁠ን ከግምት ማስገባት ያለብን ለምንድን ነው?

14 ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ . . . ሀብታም” ሳንሆን ቁሳዊ ነገሮችን ማከማቸት ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:16-21) ነገ የሚያመጣውን ማንም አያውቅም። (ምሳሌ 23:4, 5፤ ያዕ. 4:13-15) የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናችን ብቻ ሊገጥመን የሚችል ተፈታታኝ ሁኔታም አለ። ኢየሱስ እንደተናገረው የእሱ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ስንል ካስፈለገ ንብረታችንን ሁሉ ‘ለመተው’ ዝግጁ መሆን አለብን። (ሉቃስ 14:33 ግርጌ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ የነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት እጦት ሲገጥማቸው ሁኔታውን በደስታ ተቀብለውታል። (ዕብ. 10:34) ዛሬ ያሉ ብዙ ወንድሞችም ለአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ድጋፍ ላለመስጠት ሲሉ ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት አድርገዋል። (ራእይ 13:16, 17) እንዲህ ያለ አቋም ለመውሰድ የረዳቸው ምንድን ነው? ይሖዋ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት በገባው ቃል ላይ ሙሉ እምነት ማሳደራቸው ነው። (ዕብራውያን 13:5⁠ን አንብብ።) እንግዲያው ለወደፊቱ ጊዜ ጥሩ ዕቅድ ማውጣታችን ተገቢ ነው፤ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን ደግሞ ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚደግፈን መተማመን አለብን።

15. ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ምን ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 በአንዳንድ ባሕሎች የተጋቡ ጥንዶች ለመውለድ የሚወስኑበት ዋነኛ ምክንያት በእርጅና ዘመናቸው የሚጦሯቸው ልጆች ለማግኘት በማሰብ ነው። ልጆችን የሚመለከቷቸው እንደ ጡረታ ዋስትና አድርገው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች፣ ልጆቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት እንዳለባቸው ይናገራል። (2 ቆሮ. 12:14) እርግጥ ነው፣ ወላጆች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ እገዛ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፤ ደግሞም ብዙ ልጆች ወላጆቻቸውን በደስታ ይረዳሉ። (1 ጢሞ. 5:4) ይሁንና ክርስቲያን ወላጆች፣ ነገ ላይ እጥፍ ድርብ ደስታ የሚያስገኝላቸው በእርጅናቸው ዘመን የሚጦሯቸው ልጆች ማፍራታቸው ሳይሆን ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ ልጆች ማሳደጋቸው እንደሆነ ይገነዘባሉ።—3 ዮሐ. 4

አንድ ባልና ሚስት ከልጃቸውና ከባለቤቷ ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ደስ ብሏቸው እያወሩ ነው። ልጃቸውና ባለቤቷ የግንባታ ቦታ ላይ የሚለበሰው ዓይነት ከርቀት የሚታይ አንጸባራቂ ሰደርያ አድርገዋል።

መንፈሳዊ የሆኑ ባልና ሚስት ስለ ወደፊት ሕይወታቸው ዕቅድ ሲያወጡ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ግምት ውስጥ ያስገባሉ (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)d


16. ወላጆች፣ ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ ለማዘጋጀት ምን ማድረግ ይችላሉ? (ኤፌሶን 4:28)

16 ልጆቻችሁን ራሳቸውን ችለው ለሚኖሩበት ጊዜ ስታዘጋጇቸው በይሖዋ በመታመን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሁኗቸው። ገና ከትንሽነታቸው አንስቶ ተግቶ መሥራት ያለውን ዋጋ አሳዩአቸው። (ምሳሌ 29:21፤ ኤፌሶን 4:28⁠ን አንብብ።) እያደጉ ሲሄዱ በትምህርታቸው ጠንክረው እንዲሠሩ እርዷቸው። ልጆቻችሁ ምን ትምህርት እንደሚከታተሉ የሚወስኑበት ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዷቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ምርምር አድርጉ። ይህም ልጆቻችሁ ወደፊት ሥራ ሲይዙ ራሳቸውን ለማስተዳደርና በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ የሚረዳቸውን ትምህርት ለመምረጥ ያስችላቸዋል።

17. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች እሱ በቁሳዊ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው ፈጽሞ አይጠራጠሩም። ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተጠጋን ስንሄድ በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ይበልጥ እንደሚፈተን እንጠብቃለን። ቁርጥ ውሳኔያችን ግን ይህ ነው፦ የመጣው ቢመጣ ይሖዋ ኃይሉን ተጠቅሞ በቁሳዊ እንደሚንከባከበን እንተማመን። ኃያል እጁና የተዘረጋው ክንዱ እኛ ያለንበት ለመድረስ ፈጽሞ አጭር እንደማይሆን እርግጠኞች እንሁን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ሙሴና እስራኤላውያን ከገጠማቸው ነገር ምን ትምህርቶች እናገኛለን?

  • የገንዘብ ችግር ሲያጋጥመን በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

  • ወደፊት የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ስለምናሟላበት መንገድ ዕቅድ ስናወጣ ምን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን?

መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ

a በጥቅምት 2023 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

b በመስከረም 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

c በሚያዝያ 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚችል የለም” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ መንፈሳዊ የሆኑ ባልና ሚስት ከልጃቸው ጋር ተደዋውለው እያወሩ ነው። ይህች ልጃቸው ከባለቤቷ ጋር በስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ላይ እየተካፈለች ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ