የጥናት ርዕስ 26
መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት
የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
“ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከመረዳት ችሎታችን በላይ ነው።”—ኢዮብ 37:23
ዓላማ
ልካችንን በማወቅ የማናውቀው ነገር እንዳለ አምነን መቀበላችን፣ በምናውቀው ነገር ላይ ማተኮራችን እንዲሁም በይሖዋ መታመናችን የሚረዳን እንዴት ነው?
1. ይሖዋ ምን ዓይነት ችሎታ ሰጥቶናል? ለምንስ?
ይሖዋ የፈጠረን የማሰብ፣ እውቀት የመቅሰም፣ የማስተዋልና ጥበብ የማንጸባረቅ ችሎታ እንዲኖረን አድርጎ ነው። ለመሆኑ እንዲህ አድርጎ የፈጠረን ለምንድን ነው? ‘ስለ አምላክ እውቀት እንድንቀስም’ እና የማሰብ ችሎታችንን ተጠቅመን እንድናገለግለው ስለሚፈልግ ነው።—ምሳሌ 2:1-5፤ ሮም 12:1
2. (ሀ) ምን ገደብ አለብን? (ኢዮብ 37:23, 24) (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ልካችንን በማወቅ ያለብንን ገደብ አምነን መቀበላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
2 የመማር ችሎታ ቢኖረንም የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ። (ኢዮብ 37:23, 24ን አንብብ።) ኢዮብን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይሖዋ ያቀረበለት ጥያቄዎች የማያውቃቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ አስገንዝበውታል። ይህ ሁኔታ ትሑት እንዲሆንና አመለካከቱን እንዲያስተካክል ረድቶታል። (ኢዮብ 42:3-6) እኛም ልካችንን በማወቅ፣ የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ከተገነዘብን እንጠቀማለን። በዚህ መልኩ ልካችንን የምናውቅ ከሆነ ይሖዋ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚያስፈልገንን መረጃ እንደሚሰጠን እንተማመናለን።—ምሳሌ 2:6
ልክ እንደ ኢዮብ፣ የማናውቃቸው ነገሮች እንዳሉ አምነን መቀበላችን ይጠቅመናል (አንቀጽ 2ን ተመልከት)
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የማናውቃቸውን አንዳንድ ነገሮች እንዲሁም እነዚህን ነገሮች አለማወቃችን የሚያስከትልብንን ተፈታታኝ ሁኔታ እንመለከታለን። በተጨማሪም አንዳንድ ነገሮችን አለማወቃችን ጥሩ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመረምራለን። እነዚህን ነጥቦች መመርመራችን “እውቀቱ ፍጹም የሆነው” ይሖዋ ማወቅ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚነግረን ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።—ኢዮብ 37:16
መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ አናውቅም
4. በማቴዎስ 24:36 መሠረት ምን አናውቅም?
4 ማቴዎስ 24:36ን አንብብ። የዚህ ሥርዓት መጨረሻ መቼ እንደሚመጣ አናውቅም። ኢየሱስም እንኳ ምድር ላይ ሳለ “ስለዚያ ቀንና ሰዓት” አያውቅም ነበር።a ኢየሱስ፣ አንዳንድ ነገሮች መቼ እንደሚከናወኑ “የመወሰን ሥልጣን ያለው” ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ለሐዋርያቱ ነግሯቸዋል። (ሥራ 1:6, 7) ይሖዋ የዚህ ሥርዓት መጨረሻ መቼ እንደሆነ ወስኗል፤ እኛ ግን ያንን ቀን የማወቅ ሥልጣን አልተሰጠንም።
5. መጨረሻው የሚመጣበትን ቀን አለማወቃችን ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል?
5 ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ አንጻር፣ መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ ምን ያህል መጠበቅ እንዳለብን አናውቅም። በመሆኑም ትዕግሥት ልናጣ ወይም ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ በተለይም የይሖዋን ቀን ስንጠብቅ የቆየነው ረዘም ላለ ጊዜ ከሆነ እንዲህ ቢሰማን አያስገርምም። አሊያም ደግሞ መጨረሻው እስካሁን ባለመምጣቱ የተነሳ የቤተሰባችን አባላት ወይም ሌሎች ሰዎች የሚያደርሱብንን ፌዝ በጽናት መቋቋም ሊከብደን ይችላል። (2 ጴጥ. 3:3, 4) መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ቀን ብናውቅ በትዕግሥት መጠበቅና የሚደርስብንን ፌዝ መቋቋም ይበልጥ ቀላል እንደሚሆንልን ሊሰማን ይችላል።
6. መጨረሻው የሚመጣበትን ቀን አለማወቃችን ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?
6 እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይሖዋ መጨረሻው የሚመጣበትን ቀን ያልነገረን መሆኑ እሱን የምናገለግለው ስለምንወደውና ስለምንተማመንበት መሆኑን ማሳየት የምንችልበት አጋጣሚ ይሰጠናል። እምነታችን ቀነ ገደብ ያለው ይመስል አንድን ቀን በአእምሯችን ይዘን ይሖዋን አናገለግልም። ‘የይሖዋ ቀን’ የሚመጣው መቼ ነው በሚለው ላይ ከማተኮር ይልቅ ያ ቀን ምን ያስገኝልናል በሚለው ላይ ማተኮራችን ጠቃሚ ይሆናል። እንዲህ ካደረግን ለአምላክ ማደራችንንና እሱን ለማስደሰት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችንን መቀጠል እንችላለን።—2 ጴጥ. 3:11, 12
7. ምን እናውቃለን?
7 በምናውቀው ነገር ላይ ማተኮራችን ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ የመጨረሻዎቹ ቀናት በ1914 እንደጀመሩ እናውቃለን። ይሖዋ ያንን ዓመት ለማስላት የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ሰጥቶናል፤ በተጨማሪም ከዚያ ዓመት በኋላ የሚከሰቱትን ነገሮች በዝርዝር ገልጾልናል። በመሆኑም “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቅርብ” እንደሆነ እርግጠኞች ነን። (ሶፎ. 1:14) ይሖዋ የትኛውን ሥራ እንድንሠራ እንደሚፈልግም እናውቃለን፤ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች እንድንሰብክ ይፈልጋል። (ማቴ. 24:14) ይህ መልእክት በ240 ገደማ አገሮች ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች እየተሰበከ ነው። በዚህ ወሳኝ ሥራ በቅንዓት ለመካፈል “ስለዚያ ቀንና ሰዓት” ማወቅ አያስፈልገንም።
ይሖዋ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ አናውቅም
8. ‘የእውነተኛው አምላክ ሥራ’ የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? (መክብብ 11:5)
8 “የእውነተኛውን አምላክ ሥራ” የማናውቅበት ጊዜ አለ። (መክብብ 11:5ን አንብብ።) ‘የእውነተኛው አምላክ ሥራ’ የሚለው አገላለጽ ይሖዋ ፈቃዱን ለማስፈጸም ሲል የሚያከናውነውን ወይም እንዲከናወን የሚፈቅደውን ነገር ያመለክታል። ይሖዋ አንድ ነገር እንዲፈጸም የፈቀደው ለምን እንደሆነ ወይም ለእኛ ሲል እርምጃ የሚወስደው እንዴት እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። (መዝ. 37:5) አንድ ሕፃን በእርጉዝ ሴት ማህፀን ውስጥ የሚያድገው እንዴት እንደሆነ እንደማናውቅ ግልጽ ነው፤ ሳይንቲስቶችም እንኳ ይህን ሙሉ በሙሉ አይረዱትም። በተመሳሳይም የአምላክን ሥራ መረዳት አንችልም።
9. ይሖዋ እኛን ለመርዳት እርምጃ የሚወስደው እንዴት እንደሆነ አለማወቃችን የትኞቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያስከትልብን ይችላል?
9 ይሖዋ እኛን ለመርዳት እርምጃ የሚወስደው እንዴት እንደሆነ አለማወቃችን አንዳንድ ውሳኔዎችን ከማድረግ ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። አገልግሎታችንን ለማስፋት ስንል መሥዋዕት ለመክፈል እናመነታ ይሆናል፤ ለምሳሌ አኗኗራችንን ከማቅለል ወይም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ከመዛወር ወደኋላ ልንል እንችላለን። ወይም ደግሞ የይሖዋን ሞገስ እንዳጣን እንዲሰማን የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ፤ ለምሳሌ ቲኦክራሲያዊ ግቦቻችን ላይ መድረስ ካልቻልን፣ በአገልግሎት በትጋት ብንካፈልም ይህ ነው የሚባል ውጤት ካላገኘን አሊያም በቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ላይ ስንካፈል እንቅፋት ካጋጠመን እንደዚህ ሊሰማን ይችላል።
10. ይሖዋ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ አለማወቃችን የትኞቹን ወሳኝ ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል?
10 እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይሖዋ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ አለማወቃችን እንደ ትሕትናና ልክን ማወቅ ያሉ ወሳኝ ባሕርያትን እንድናዳብር ይረዳናል። የይሖዋ ሐሳብና መንገድ ከእኛ እጅግ የላቀ እንደሆነ እንገነዘባለን። (ኢሳ. 55:8, 9) በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መተማመንን እንማራለን፤ እንዲሁም ስኬት ለማግኘት የእሱን እርዳታ እንጠይቃለን። በአገልግሎት ወይም በቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ጥሩ ውጤት ስናገኝ ክብሩ ወደ ይሖዋ እንዲሄድ እናደርጋለን። (መዝ. 127:1፤ 1 ቆሮ. 3:7) ነገሮች በጠበቅነው መንገድ ባይሄዱ እንኳ ይሖዋ ሁሉንም ነገር እንደሚቆጣጠር ማስታወስ ይኖርብናል። (ኢሳ. 26:12) እኛ የሚጠበቅብንን እናደርጋለን፤ ይሖዋም የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ እንተማመናለን። በጥንት ዘመን ያደርግ እንደነበረው በተአምራዊ መንገድ ባይሆንም እንኳ የሚያስፈልገንን መመሪያ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን።—ሥራ 16:6-10
11. የትኞቹን ወሳኝ ነገሮች እናውቃለን?
11 በምናውቃቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ይጠቅመናል። ለምሳሌ ይሖዋ ምንጊዜም አፍቃሪ፣ ፍትሐዊና ጥበበኛ እንደሆነ እናውቃለን። ለእሱም ሆነ ለእምነት አጋሮቻችን የምናደርገውን ነገር ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እናውቃለን። በተጨማሪም ይሖዋ ለእሱ ታማኝ ለሆኑት ምንጊዜም ወሮታ እንደሚከፍል እናውቃለን።—ዕብ. 11:6
ነገ ምን እንደሚሆን አናውቅም
12. በያዕቆብ 4:13, 14 መሠረት ምን አናውቅም?
12 ያዕቆብ 4:13, 14ን አንብብ። አንድ መሠረታዊ እውነት አለ፦ ሕይወታችን ነገ ምን እንደሚሆን አናውቅም። በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስንኖር “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ያጋጥሙናል። (መክ. 9:11) በዚህም የተነሳ፣ ዕቅዶቻችን መሳካታቸውን ሌላው ቀርቶ በሕይወት ኖረን ያሰብነውን ነገር ማሳካት መቻላችንን እንኳ አናውቅም።
13. ወደፊት የሚሆነውን ነገር አለማወቃችን ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል?
13 ሕይወታችን ምን እንደሚሆን አለማወቃችን ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። እንዴት? ወደፊት ሊፈጠር የሚችለው ነገር ሊያስጨንቀን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ደስታችንን ያሳጣናል። ድንገተኛ አደጋዎች ወይም ያልተጠበቁ ክስተቶች እንድናዝንና እንድንበሳጭ ሊያደርጉን ይችላሉ። የጠበቅነው ነገር ሳይፈጸም ሲቀር ደግሞ ስሜታችን ሊጎዳና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን።—ምሳሌ 13:12
14. ደስታችን የተመካው በምን ላይ ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
14 የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጽናት ስንቋቋም፣ ምንም ይድረስብን ምን የሰማዩን አባታችንን የምናገለግለው በራስ ወዳድነት ተነሳስተን ሳይሆን በፍቅር ተነሳስተን እንደሆነ እናሳያለን። ይሖዋ ምንም ዓይነት መከራ እንዳይደርስብን እንደማይከላከልልን እንዲሁም ወደፊት የሚያጋጥሙንን ነገሮች አስቀድሞ እንዳልወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ያሳያሉ። ይሖዋ የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ ባናውቅም ደስተኛ መሆን እንደምንችል ያውቃል። ከዚህ ይልቅ ደስታችን የተመካው የእሱን አመራር በመፈለጋችንና መመሪያውን በመታዘዛችን ላይ ነው። (ኤር. 10:23) ውሳኔ ስናደርግ የእሱን መመሪያ ከፈለግን “ይሖዋ ከፈቀደ በሕይወት እንኖራለን፤ ደግሞም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” እያልን ነው ሊባል ይችላል።—ያዕ. 4:15
የይሖዋን አመራር መፈለግና እሱን መታዘዝ አስተማማኝ ጥበቃ ይሆንልናል (አንቀጽ 14-15ን ተመልከት)b
15. ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን እናውቃለን?
15 እያንዳንዱ ቀን ምን ይዞ እንደሚመጣ ባናውቅም ይሖዋ በሰማይም ይሁን በምድር የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጠን ቃል እንደገባልን እናውቃለን። ይሖዋ ሊዋሽ እንደማይችልና የገባውን ቃል ከመፈጸም ምንም ነገር ሊያግደው እንደማይችል እናውቃለን። (ቲቶ 1:2) “ከመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ገና ያልተከናወኑትንም ነገሮች ከረጅም ጊዜ በፊት [አስቀድሞ መናገር]” የሚችለው እሱ ብቻ ነው። በጥንት ዘመን የተናገረው ነገር ተፈጽሞ ነበር፤ ወደፊትም ቢሆን መፈጸሙ አይቀርም። (ኢሳ. 46:10) ይሖዋ እኛን ከመውደድ ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ በእርግጠኝነት እናውቃለን። (ሮም 8:35-39) ምንም ነገር ቢያጋጥመን ለመጽናት የሚያስችለንን ጥበብ፣ ማጽናኛና ኃይል ይሰጠናል። ይሖዋ እንደሚረዳንና እንደሚባርከን መተማመን እንችላለን።—ኤር. 17:7, 8
ይሖዋ ምን ያህል እንደሚያውቀን ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም
16. በመዝሙር 139:1-6 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ እኛ ሙሉ በሙሉ ልንረዳው የማንችል ምን ዓይነት እውቀት አለው?
16 መዝሙር 139:1-6ን አንብብ። ፈጣሪያችን እንዴት እንደተሠራን እንዲሁም አካላዊ፣ ስሜታዊና አእምሯዊ ማንነታችንን ምን እንደቀረጸው ያውቃል። እሱ ምንጊዜም በትኩረት ይከታተለናል። ምን እንዳልን ብቻ ሳይሆን ምን ማለት እንደፈለግን እንዲሁም ምን እንዳደረግን ብቻ ሳይሆን ለማድረግ የተነሳሳንበትንም ምክንያት ያውቃል። ንጉሥ ዳዊት እንደገለጸው ይሖዋ ዙሪያችንን ከብቦ ይንከባከበናል፤ እንዲሁም እጁ እኛን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እንዲሁም ሁሉን ቻይ የሆነው የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንደዚህ በቅርበት የሚከታተለን መሆኑ ምንኛ የሚያስገርም ነው! ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለው እውቀት ለእኔ እጅግ አስደናቂ ነው። ከመረዳት አቅሜ በላይ ነው።”—መዝ. 139:6 ግርጌ
17. ይሖዋ ጠንቅቆ እንደሚያውቀን መቀበል የሚከብደን ለምን ሊሆን ይችላል?
17 በአስተዳደጋችን፣ በባሕላችን ወይም በቀድሞ እምነታችን የተነሳ ይሖዋን ለእኛ ትኩረት የሚሰጥ አፍቃሪ አባት አድርጎ መመልከት ይከብደን ይሆናል። ወይም ደግሞ ቀደም ሲል በሠራነው ከባድ ስህተት የተነሳ ይሖዋ እኛን ፈጽሞ ማወቅ እንደማይፈልግ እንዲሁም ከእኛ በጣም የራቀ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። ዳዊትም እንኳ እንዲህ የተሰማው ጊዜ ነበር። (መዝ. 38:18, 21) በሌላ በኩል ደግሞ የሚመራውን የሕይወት ጎዳና አስተካከሎ በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ለመመራት እየታገለ ያለ አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፦ ‘አምላክ በደንብ የሚያውቀኝ ከሆነ ይሄ ተፈጥሮዬ እንደሆነ እያወቀ እንዴት እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንዳደርግ ይጠይቀኛል?’
18. ይሖዋ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ እንደሚያውቀን መቀበላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
18 ይሖዋ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ እንደሚያውቀን እንዲሁም እኛ እንኳ ያላየነውን መልካም ነገር እንደሚያይልን በጊዜ ሂደት እየተገነዘብን ልንሄድ እንችላለን። ድክመታችንን እንዲሁም ለስሜታችንና ለምግባራችን መንስኤ የሆነውን ነገር ቢያውቅም ይወደናል። (ሮም 7:15) ይሖዋ እምቅ አቅማችንን እንደሚመለከት ሙሉ በሙሉ ሲገባን ደስተኞች ሆነን እሱን በታማኝነት ማገልገል እንደምንችል ይበልጥ እንተማመናለን።
ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ውስጥ በሚጠብቀን አስደሳች ጊዜ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር ይረዳናል፤ ይህም በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስንኖር የሚያጋጥመንን ስጋት ለመጋፈጥ ያስችለናል (አንቀጽ 18-19ን ተመልከት)c
19. ስለ ይሖዋ ምን ነገር በእርግጠኝነት እናውቃለን?
19 ይሖዋ ፍቅር እንደሆነ እናውቃለን። ይህን ፈጽሞ አንጠራጠርም። (1 ዮሐ. 4:8) የጽድቅ መሥፈርቶቹ ለእኛ ያለውን ፍቅር እንደሚያሳዩ እንዲሁም ምንጊዜም ለእኛ የሚጠቅመንን እንደሚያስብ እናውቃለን። ይሖዋ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ እንደሚፈልግ እናውቃለን። ለዚህም ሲል የቤዛውን ዝግጅት አድርጎልናል። የቤዛው ስጦታ ፍጽምና ቢጎድለንም እንኳ እንደሚሳካልን ዋስትና ይሰጠናል። (ሮም 7:24, 25) በተጨማሪም ‘አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ እንደሆነ፣ ደግሞም ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅ’ እናውቃለን። (1 ዮሐ. 3:19, 20) ይሖዋ ከእኛ ጋር በተያያዘ ሁሉንም ነገር ይመለከታል፤ እንዲሁም ፈቃዱን በመፈጸም ረገድ እንደሚሳካልን ይተማመናል።
20. ለአላስፈላጊ ጭንቀት እንዳንዳረግ ምን ይረዳናል?
20 ይሖዋ በእርግጥ የሚያስፈልገንን አንዳች መረጃ አልነፈገንም። ልካችንን በማወቅ ይህን ሐቅ አምነን ከተቀበልን መቆጣጠር ስለማንችለው ነገር በማውጠንጠን ራሳችንን ለአላስፈላጊ ጭንቀት አንዳርግም፤ እንዲሁም ወሳኝ በሆነው ነገር ላይ ማተኮር እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ ‘እውቀቱ ፍጹም በሆነው’ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደምንተማመን እናሳያለን። (ኢዮብ 36:4) በአሁኑ ጊዜ ስለ አንዳንድ ነገሮች ያለን ግንዛቤ ውስን ቢሆንም ይሖዋ ለዘላለም አዳዲስ ነገሮችን እንደሚያስተምረን እርግጠኞች ነን፤ ደግሞም ስለ እሱ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ።—መክ. 3:11
መዝሙር 104 የአምላክ ስጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስ
b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ አባትና ልጅ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ቤተሰባቸው ዝግጁ እንዲሆን የአደጋ ጊዜ ቦርሳ ሲያዘጋጁ።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ብዙ ችግሮችን እየተጋፈጠ ያለ አንድ ወንድም በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚጠብቀውን አስደሳች ጊዜ አሻግሮ ሲመለከት።