የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ሚያዝያ ገጽ 14-19
  • እርስ በርስ መቀራረባችን ይበጀናል!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እርስ በርስ መቀራረባችን ይበጀናል!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እርስ በርስ ይበልጥ መቀራረብ ያለብን ለምንድን ነው?
  • አንዳችሁ ሌላውን አክብሩ
  • ‘በመካከላችሁ መከፋፈል አይኑር’
  • ‘በተግባርና በእውነት ተዋደዱ’
  • ይሖዋ እጅግ ይወድሃል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ‘ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀናል!’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ አጣጥም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ሚያዝያ ገጽ 14-19

የጥናት ርዕስ 16

መዝሙር 87 ኑ! እረፍት አግኙ

እርስ በርስ መቀራረባችን ይበጀናል!

“እነሆ፣ ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!”—መዝ. 133:1

ዓላማ

እርስ በርስ ይበልጥ መቀራረብ የምንችለው እንዴት ነው? ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ጓደኝነት መመሥረታችንስ የትኞቹን በረከቶች ያስገኝልናል?

1-2. ይሖዋ ለየትኛው ነገር ትኩረት ይሰጣል? ምን እንድናደርግስ ይፈልጋል?

ይሖዋ ሌሎች ሰዎችን ለምንይዝበት መንገድ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል። ኢየሱስ ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን መውደድ እንዳለብን አስተምሯል። (ማቴ. 22:37-39) ይህም እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎችም ጭምር ደግነት ማሳየትን ያካትታል። እንዲህ ያለ ደግነት ስናሳይ ይሖዋ አምላክን እንመስላለን፤ “እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።”—ማቴ. 5:45

2 ይሖዋ ሁሉንም የሰው ልጆች የሚወድ ቢሆንም በተለይ ትክክል የሆነውን ነገር ለሚያደርጉ ሰዎች የተለየ ፍቅር አለው። (ዮሐ. 14:21) እኛም እሱን እንድንመስለው ይፈልጋል። ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን “የጠለቀ ፍቅር” እንዲኖረን እንዲሁም ከልብ እንድንወዳቸው አሳስቦናል። (1 ጴጥ. 4:8፤ ሮም 12:10) እንዲህ ያለው ፍቅር ለምንወዳቸው የቤተሰባችን አባላት ወይም ለጓደኞቻችን ካለን ፍቅር ጋር ይመሳሰላል።

3. ስለ ፍቅር ምን መዘንጋት አይኖርብንም?

3 እንደ ተክል ሁሉ ፍቅርም እንዲያድግ እንክብካቤ ያስፈልገዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ” በማለት ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል። (ዕብ. 13:1) ይሖዋ ለሌሎች ያለንን ፍቅር ማሳደጋችንን እንድንቀጥል ይፈልጋል። ይህ ርዕስ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ይበልጥ መቀራረብ ያለብን ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይህን በቀጣይነት ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

እርስ በርስ ይበልጥ መቀራረብ ያለብን ለምንድን ነው?

4. በመዝሙር 133:1 ላይ እንደተጠቀሰው አንድነት ላለው የወንድማማች ማኅበራችን ያለንን አድናቆት ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

4 መዝሙር 133:1⁠ን አንብብ። መዝሙራዊው ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ያለን እውነተኛ ወዳጅነት “መልካም” እና ‘ደስ የሚያሰኝ’ እንደሆነ ገልጿል፤ እኛም በዚህ ሐሳብ እንስማማለን። ሆኖም አንድ ሰው በየቀኑ የሚያየውን ግርማ ሞገስ የተላበሰ ዛፍ ላያስተውለው እንደሚችል ሁሉ እኛም ክርስቲያናዊ አንድነታችን ያለውን ውበት አቅልለን ልንመለከተው እንችላለን። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ብዙ ጊዜ፣ ምናልባትም በሳምንት ውስጥ በተደጋጋሚ እናገኛቸዋለን። ታዲያ ለእነሱ ያለንን አድናቆት ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? እያንዳንዳቸው ለጉባኤውም ሆነ ለእኛ ምን ያህል ውድ እንደሆኑ ጊዜ ወስደን ካሰብን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር ያድጋል።

ሥዕሎች፦ 1. አንዲት እህት አንድን የሚያምር ዛፍ ስታደንቅ። 2. በኋላም በክልል ስብሰባ ላይ ከሌላ እህት ጋር ስትተቃቀፍ። በስብሰባው ላይ የተገኙ ሌሎች ክርስቲያኖችም በደስታ እርስ በርስ እየተጨዋወቱ ነው።

ክርስቲያናዊ አንድነታችን ያለውን ውበት ፈጽሞ አቅልለህ አትመልከት (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)


5. ፍቅር የሰፈነበት የወንድማማች ማኅበራችን በሌሎች ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?

5 ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባችን ላይ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች በመካከላችን ያለው ፍቅር በጣም ያስደንቃቸዋል። ይህን በማየታቸው ብቻ እውነትን እንዳገኙ እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13:35) አንድ ተሞክሮ እንመልከት። ቻይትራ የተባለች አንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና ነበር። የቀረበላትን ግብዣ ተቀብላ በክልል ስብሰባ ላይ ተገኘች። የመጀመሪያውን ቀን በአካል ከተሰበሰበች በኋላ አስጠኚዋን እንዲህ አለቻት፦ “ወላጆቼ አንድም ቀን አቅፈውኝ አያውቁም። በእናንተ ስብሰባ ላይ ግን በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 52 ሰዎች አቀፉኝ! በዚህ መንፈሳዊ ቤተሰብ አማካኝነት የይሖዋን ፍቅር ማጣጣም ችያለሁ። እኔም የዚህ ቤተሰብ ክፍል መሆን እፈልጋለሁ።” ቻይትራ እድገት አድርጋ በ2024 ተጠመቀች። በእርግጥም አዲሶች በመካከላችን ያለውን ፍቅር ጨምሮ መልካም ሥራችንን ሲያዩ ብዙውን ጊዜ ይሖዋን ለማገልገል ይነሳሳሉ።—ማቴ. 5:16

6. ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር መቀራረባችን ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?

6 ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር መቀራረባችን ጥበቃ ሊሆንልን ይችላል። ጳውሎስ የእምነት አጋሮቹን እንዲህ በማለት አሳስቧቸዋል፦ “ከእናንተ መካከል አንዳችሁም ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል እንዳትደነድኑ . . . በየዕለቱ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ።” (ዕብ. 3:13) ተስፋ ከመቁረጣችን የተነሳ እግራችን ከጽድቅ መንገድ መውጣት ከጀመረ ይሖዋ አንድ የእምነት አጋራችን ሁኔታችንን አስተውሎ የሚያስፈልገንን እርዳታ እንዲሰጠን ሊያነሳሳው ይችላል። (መዝ. 73:2, 17, 23) እንዲህ ያለው ማበረታቻ በጣም ይጠቅመናል።

7. በፍቅርና በአንድነት መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? (ቆላስይስ 3:13, 14)

7 አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት በሚያደርጉ ሰዎች ስለተከበብን ብዙ በረከቶችን አግኝተናል። (1 ዮሐ. 4:11) ለምሳሌ ፍቅር ‘እርስ በርስ መቻቻላችንን እንድንቀጥል’ ያነሳሳናል፤ ይህ ደግሞ ለክርስቲያናዊ አንድነታችን አስተዋጽኦ ያበረክታል። (ቆላስይስ 3:13, 14⁠ን አንብብ፤ ኤፌ. 4:2-6) በመሆኑም በስብሰባዎቻችን ላይ ሌላ የትም ቦታ የማይገኝ ደስ የሚል መንፈስ አለ።

አንዳችሁ ሌላውን አክብሩ

8. ይሖዋ አንድነት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው?

8 ዓለም አቀፋዊ አንድነታችን ተአምር ነው። ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ይሖዋ እንዲህ ያለ አንድነት እንዲኖረን አድርጓል። (1 ቆሮ. 12:25) መጽሐፍ ቅዱስ ‘እርስ በርስ እንድንዋደድ ከአምላክ እንደተማርን’ ይናገራል። (1 ተሰ. 4:9) በሌላ አባባል፣ እርስ በርስ ለመቀራረብ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይነግረናል። ይሖዋ የሚያስተምረንን ነገር በጥንቃቄ በመመርመርና በሥራ ላይ በማዋል ‘ከአምላክ መማር’ እንችላለን። (ዕብ. 4:12፤ ያዕ. 1:25) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ።

9. አንዳችን ሌላውን ከማክበር ጋር በተያያዘ ከሮም 12:9-13 ምን እንማራለን?

9 የአምላክ ቃል እርስ በርስ እንድንቀራረብ የሚያስተምረን እንዴት ነው? ጳውሎስ በሮም 12:9-13 ላይ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ምን እንዳለ ልብ በል። (ጥቅሱን አንብብ።) በተለይ “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ” የሚለው ሐሳብ ትኩረታችንን ይስበዋል። ይህ ምን ማለት ነው? ይቅር ባይ በመሆን፣ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት፣ በልግስና በመስጠት እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ወንድሞቻችንን ‘ከልብ ለመውደድ’ ቀዳሚ መሆን ይኖርብናል። (ኤፌ. 4:32) ወንድሞችህ ወይም እህቶችህ ወደ አንተ ለመቅረብ ጥረት እስኪያደርጉ መጠበቅ አያስፈልግህም። በዚህ ረገድ አንተ ‘ቀዳሚ መሆን’ ትችላለህ። ደግሞም ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል።—ሥራ 20:35

10. አንዳችን ሌላውን በማክበር ረገድ ታታሪ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 ጳውሎስ አንዳችን ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ መሆን እንዳለብን ከተናገረ በኋላ “ታታሪዎች ሁኑ እንጂ አትስነፉ” የሚል ምክር መስጠቱ ትኩረት የሚስብ ነው። ታታሪ የሆነ ሰው በሥራው ቀናተኛና ትጉ ነው። አንድ ሥራ ሲሰጠው ኃላፊነቱን በትጋት ይወጣል። ምሳሌ 3:27, 28 “ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል” የሚል ምክር ይሰጠናል። በመሆኑም አንድ ሰው ተቸግሮ ካየን እሱን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን እናደርጋለን። ዛሬ ነገ አንልም፤ ወይም ደግሞ ሌላ ሰው ይረዳዋል ብለን አናስብም።—1 ዮሐ. 3:17, 18

አንድ ወጣት ወንድም መሰላል ላይ ቆሞ ከአንድ አረጋዊ ወንድም ጣሪያ ላይ ቅጠሎችን ሲያጸዳ።

እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመርዳት ቅድሚያውን መውሰድ ይኖርብናል (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)


11. እርስ በርስ ለመቀራረብ ምን ይረዳናል?

11 ለሌሎች አክብሮት ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ሲበድሉን እነሱን ይቅር ለማለት ፈጣኖች በመሆን ነው። ኤፌሶን 4:26 “ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ” ይላል። ለምን? ቁጥር 27 እንዲህ ካደረግን ‘ዲያብሎስ አጋጣሚ እንደሚያገኝ’ ይናገራል። ይሖዋ እርስ በርስ ይቅር መባባል እንዳለብን በቃሉ አማካኝነት በተደጋጋሚ ነግሮናል። ቆላስይስ 3:13 “በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጠናል። ከሌሎች ጋር ለመቀራረብ ከሚረዱን ውጤታማ ዘዴዎች መካከል አንዱ ስህተቶቻቸውንና የሚያደርሱብንን በደል ችላ ብሎ ማለፍ ነው። እንዲህ ስናደርግ “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን። (ኤፌ. 4:3) በአጭር አነጋገር፣ ሌሎችን ይቅር ማለት ለአንድነትና ለሰላም ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

12. ይሖዋ ይቅር ባይ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

12 እርግጥ ነው፣ ስሜታችንን የጎዱትን ሰዎች ይቅር ማለት ሊከብደን ይችላል። ሆኖም በአምላክ መንፈስ እርዳታ ይቅር ማለት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” እንዲሁም “ታታሪዎች ሁኑ” የሚል ምክር ከሰጠ በኋላ “በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ” ይላል። በመንፈስ የሚቃጠል ሰው መንፈስ ቅዱስ ቅንዓትና ግለት እንዲኖረው ያነሳሳዋል። ስለዚህ የአምላክ መንፈስ እርስ በርሳችን ከልብ እንድንዋደድና አንዳችን ሌላውን በነፃ ይቅር እንድንል ይረዳናል። በመሆኑም ይሖዋ እንዲረዳን አጥብቀን ልንለምነው ይገባል።—ሉቃስ 11:13

‘በመካከላችሁ መከፋፈል አይኑር’

13. በመካከላችን መከፋፈል ሊፈጠር የሚችለው እንዴት ነው?

13 ጉባኤው የተለያየ አስተዳደግና ባሕል ካላቸው “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” የተውጣጣ ነው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) በመሆኑም በአለባበስና አጋጌጥ፣ በሕክምና፣ በመዝናኛ ወይም በሌሎች ጉዳዮች ረገድ የምናደርገው ምርጫ ይለያያል። ካልተጠነቀቅን እነዚህ ልዩነቶች ክፍፍል ሊፈጥሩ ይችላሉ። (ሮም 14:4፤ 1 ቆሮ. 1:10) ‘እርስ በርስ እንድንዋደድ ከአምላክ ስለተማርን’ የግል ምርጫችንን በሌሎች ላይ እንዳንጭን መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ፊልጵ. 2:3

14. ሁልጊዜ ምን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል? ለምንስ?

14 በጉባኤ ውስጥ ክፍፍል እንዳይፈጠር መከላከል የምንችልበት ሌላው መንገድ ሁልጊዜ ለሌሎች የእረፍት ምንጭ ለመሆንና ወንድሞቻችንን ለማነጽ ጥረት በማድረግ ነው። (1 ተሰ. 5:11) ቀዝቅዘው ወይም ተወግደው የነበሩ ብዙ ሰዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ጉባኤው ተመልሰዋል። ለእነዚህ ክርስቲያኖች ሞቅ ያለ አቀባበል እናደርግላቸዋለን! (2 ቆሮ. 2:8) አንዲት እህት ለአሥር ዓመት ያህል ቀዝቅዛ ከቆየች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ ስትገኝ የነበረውን ሁኔታ ስትገልጽ “ሁሉም እጄን እየጨበጡ በፈገግታ ተቀበሉኝ” ብላለች። (ሥራ 3:19) ታዲያ ደግነት የሚንጸባረቅባቸው እነዚህ ቀላል ድርጊቶች በእሷ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድረዋል? እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እጄን ይዞ ደስታ ወደማገኝበት መንገድ እንደመለሰኝ ተሰማኝ።” ወንድሞቻችንን ለማነጽ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ክርስቶስ ‘ለደከማቸውና ሸክም ለከበዳቸው’ እረፍት ለመስጠት ሊጠቀምብን ይችላል።—ማቴ. 11:28, 29

15. አንድነትን ማስፈን የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 አንድነት ማስፈን የምንችልበት ሌላው መንገድ በአነጋገራችን ነው። ኢዮብ 12:11 እንዲህ ይላል፦ “ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ ሁሉ፣ ጆሮስ ቃላትን አያመዛዝንም?” አንድ ባለሙያ ሰው ምግብ ሲያበስል ምግቡን ለሌሎች ከማቅረቡ በፊት ጣፋጭ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሚቀምሰው ሁሉ እኛም አንድ ነገር ከመናገራችን በፊት ስለምንናገረው ነገር ቆም ብለን በጥንቃቄ ማሰብ ይኖርብናል። (መዝ. 141:3) ምንጊዜም ግባችን ልንናገር ያሰብነው ነገር የሚያንጽ፣ መንፈስን የሚያድስና ‘ሰሚዎቹን የሚጠቅም’ እንዲሆን ነው።—ኤፌ. 4:29

አንድ ወንድም ያበሰለውን ምግብ ለእንግዶቹ ከማቅረቡ በፊት ሲቀምሰው።

አንድ ነገር ከመናገርህ በፊት ቆም ብለህ አስብ (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)


16. አነጋገራቸው የሚያበረታታ እንዲሆን ለየት ያለ ጥረት ማድረግ ያለባቸው በተለይ እነማን ናቸው?

16 በተለይ ባሎችና ወላጆች አነጋገራቸው የሚያንጽ እንዲሆን ለየት ያለ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ቆላ. 3:19, 21፤ ቲቶ 2:4) ሽማግሌዎችም የይሖዋ መንጋ እረኞች እንደመሆናቸው መጠን የመጽናኛና የእረፍት ምንጭ ሊሆኑ ይገባል። (ኢሳ. 32:1, 2፤ ገላ. 6:1) የምሳሌ መጽሐፍ “በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ [ቃል] ምንኛ መልካም ነው!” ይላል።—ምሳሌ 15:23

‘በተግባርና በእውነት ተዋደዱ’

17. ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር ከልብ የመነጨ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

17 ሐዋርያው ዮሐንስ “በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 3:18) ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር ከልብ የመነጨ እንዲሆን እንፈልጋለን። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ይበልጥ ጊዜ ባሳለፍን መጠን ይበልጥ እንቀራረባለን፤ በመካከላችን ያለው ፍቅርም ይጠናከራል። እንግዲያው በስብሰባዎችና በአገልግሎት ላይ ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ የምትችልበት አጋጣሚ ፍጠር። ሌሎችን ቤታቸው ሄደህ ለመጠየቅ ጊዜ መድብ። እንዲህ ስናደርግ ‘እርስ በርስ እንድንዋደድ ከአምላክ እንደተማርን’ እናሳያለን። (1 ተሰ. 4:9) እንዲሁም “ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት በሕይወታችን እናያለን።—መዝ. 133:1

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • እርስ በርስ መቀራረባችን የሚጠቅመን ለምንድን ነው?

  • ሌሎችን ለማክበር ቀዳሚ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

  • አንድነትን ማስፈን የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ