የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ሚያዝያ ገጽ 8-13
  • ‘ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀናል!’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀናል!’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ወደ አምላክ መቅረብ” ደስታ ያስገኛል
  • “ወደ አምላክ መቅረብ” ዓላማ ያለው ሕይወትና ተስፋ ያስገኛል
  • ‘ወደ አምላክ መቅረባችንን’ መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
  • በምንሰናከልበት ጊዜም “ወደ አምላክ መቅረብ” እንችላለን
  • ለዘላለም “ወደ አምላክ መቅረብ”
  • እርስ በርስ መቀራረባችን ይበጀናል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ይሖዋ “ሕያው አምላክ” እንደሆነ አስታውስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ጥርጣሬን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ሚያዝያ ገጽ 8-13

የጥናት ርዕስ 15

መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ

‘ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀናል!’

“እኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል።”—መዝ. 73:28

ዓላማ

ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

1-2. (ሀ) ከአንድ ሰው ጋር የቅርብ ጓደኝነት መመሥረት ምን ዓይነት ጥረት ይጠይቃል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

የቅርብ ጓደኛ አለህ? ከእሱ ጋር ጓደኝነት የመሠረትከው እንዴት ነው? አብረኸው ጊዜ እንዳሳለፍክ ምንም ጥያቄ የለውም። ስላጋጠሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲሁም ስለሚወዳቸውና ስለሚጠላቸው ነገሮች አወቅክ። መኮረጅ የምትፈልጋቸው ግሩም ባሕርያት እንዳሉትም ተገነዘብክ። እንዲሁም ለእሱ ፍቅር አዳበርክ።

2 ከአንድ ሰው ጋር የቅርብ ጓደኝነት መመሥረት ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ አምላክ ጋር የቀረበ ወዳጅነት ከመመሥረት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ወደ አምላካችን ይበልጥ መቅረብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም እንዲህ ማድረጋችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን እንመለከታለን። በመጀመሪያ፣ ከሁሉ የተሻለ ወዳጃችን ወደሆነው ወደ ይሖዋ መቅረባችን የሚበጀን ለምን እንደሆነ እንመልከት።

3. ወደ ይሖዋ መቅረብ በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

3 ወደ ይሖዋ መቅረብ ይበጀናል ወይም ይጠቅመናል ቢባል እንደምትስማማ ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ወደ ይሖዋ መቅረባችን ምን ያህል እንደሚጠቅመን ማሰላሰላችን ወደ እሱ መቅረባችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል። (መዝ. 63:6-8) ለምሳሌ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቂ እረፍት ማግኘት እንዲሁም በቂ ውኃ መጠጣት እንደሚጠቅመን እናውቃለን። ይሁንና ብዙ ሰዎች ስለ እነዚህ ጉዳዮች እምብዛም ስለማያስቡ ጤንነታቸውን ችላ ይላሉ። ሆኖም እነዚህ ልማዶች ምን ያህል እንደሚጠቅሙን ይበልጥ ባሰብን መጠን ልማዶቹን ይዘን የመቀጠላችን አጋጣሚ ይጨምራል። በተመሳሳይም ወደ ይሖዋ መቅረባችን እንደሚጠቅመን እናውቃለን። ሆኖም እንዲህ ማድረጋችን በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ ማሰላሰላችን ወደ ወዳጃችን ይበልጥ መቅረባችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል።—መዝ. 119:27-30

4. የመዝሙር 73:28 ጸሐፊ ምን ብሏል?

4 መዝሙር 73:28⁠ን አንብብ። የመዝሙር 73 ጸሐፊ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሙዚቀኛ ሆኖ እንዲያገለግል የተሾመ ሌዋዊ ነበር። ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግል እንደቆየ ምንም ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን “ወደ አምላክ መቅረብ” እንደሚበጅ ራሱንም ሆነ ሌሎችን ማስታወስ አስፈልጎታል። ወደ አምላክ መቅረብ የትኞቹን ጥቅሞች ያስገኛል?

“ወደ አምላክ መቅረብ” ደስታ ያስገኛል

5. (ሀ) ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረባችን ደስታ የሚያስገኝልን ለምንድን ነው? (ለ) በምሳሌ 2:6-16 መሠረት የይሖዋ ጥበብ በግለሰብ ደረጃ የሚጠቅምህና የሚጠብቅህ እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

5 ወደ ይሖዋ ይበልጥ በቀረብን መጠን ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። (መዝ. 65:4) ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር በሥራ ላይ ማዋላችን ይጠቅመናል። እንዲህ ያለው ጥበብ ከመጥፎ ተጽዕኖዎችና ከባድ ስህተቶችን ከመሥራት ይጠብቀናል። (ምሳሌ 2:6-16⁠ን አንብብ።) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብን የሚያገኝ፣ ጥልቅ ግንዛቤንም የራሱ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው” ማለቱ ተገቢ ነው።—ምሳሌ 3:13

6. መዝሙራዊው ደስታውን ያጣው ለምንድን ነው?

6 እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ወዳጆችም ቢሆኑ አልፎ አልፎ ሐዘን ይሰማቸዋል። የመዝሙር 73 ጸሐፊ አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲቆጣጠረው በፈቀደበት ወቅት ደስታውን አጥቶ ነበር። ስለ አምላክም ሆነ ስለ መሥፈርቶቹ ግድ የሌላቸው መጥፎ ሰዎች የተደላደለ ሕይወት እንደሚመሩ ስለተሰማው ቀንቶና ተበሳጭቶ ነበር። ዓመፀኛና ትዕቢተኛ የሆኑ ሰዎች ሀብታምና ጤናማ እንደሆኑ አልፎ ተርፎም ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንደሚመሩ በማሰብ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሶ ነበር። (መዝ. 73:3-7, 12) መዝሙራዊው ባየው ነገር በጣም ከመረበሹ የተነሳ ይሖዋን ለማገልገል ያደረገው ጥረት ከንቱ እንደሆነ ተሰማው። በሐዘን ተውጦ “በእርግጥም ልቤን ያነጻሁት፣ ንጹሕ መሆኔንም ለማሳየት እጄን የታጠብኩት በከንቱ ነው” በማለት ተናግሯል።—መዝ. 73:13

7. ሐዘን በሚሰማን ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 መዝሙራዊው፣ የተሰማው ሐዘን እንዲያሽመደምደው አልፈቀደም። እርምጃ ወሰደ። “ወደ ታላቁ የአምላክ መቅደስ” ገባ፤ በዚያም ይሖዋ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ረዳው። (መዝ. 73:17-19) በምናዝንበት ጊዜ የቅርብ ወዳጃችን የሆነው ይሖዋ ስሜታችንን ያውቃል። አመራር እንዲሰጠን ከጸለይን እንዲሁም በቃሉና በጉባኤው አማካኝነት የሚሰጠንን እርዳታ ከተቀበልን ሐዘንን ለመቋቋም የሚያስችል ውስጣዊ ጥንካሬ እናገኛለን። በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜም እንኳ ይሖዋ ያጽናናናል፤ እንዲሁም ያረጋጋናል።—መዝ. 94:19a

አንድ ሌዋዊ በመዳብ መሠዊያውና በቤተ መቅደሱ በረንዳ መካከል ቆሞ።

መዝሙር 73⁠ን የጻፈው ሌዋዊ ‘በታላቁ የአምላክ መቅደስ’ ውስጥ ቆሞ (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)


“ወደ አምላክ መቅረብ” ዓላማ ያለው ሕይወትና ተስፋ ያስገኛል

8. ወደ አምላክ መቅረብ በየትኞቹ መንገዶች ይጠቅመናል?

8 ወደ አምላክ መቅረብ በሌሎች ሁለት አስፈላጊ መንገዶችም ይጠቅመናል። አንደኛ፣ ሕይወታችን ዓላማ እንዲኖረው ይረዳናል። ሁለተኛ፣ ለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ ይሰጠናል። (ኤር. 29:11) እስቲ እነዚህን ጥቅሞች በዝርዝር እንመልከት።

9. ወደ ይሖዋ መቅረብ ሕይወታችን ዓላማ እንዲኖረው የሚያደርገው እንዴት ነው?

9 ወደ ይሖዋ መቅረብ ሕይወታችን ዓላማ እንዲኖረው ያደርጋል። አምላክ መኖሩን የማያምኑ ብዙ ሰዎች፣ ሕይወት ምንም ትርጉም እንደሌለውና የሰው ዘር ውሎ አድሮ እንደሚጠፋ ያስባሉ። እኛ ግን የአምላክን ቃል በማጥናታችን አምላክ “መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን” እርግጠኞች ነን። (ዕብ. 11:6) ከተፈጠርንበት ዓላማ ጋር ተስማምተን በመኖራችን ማለትም የሰማዩን አባታችንን ይሖዋን በማገልገላችን በዛሬው ጊዜም እንኳ ደስተኛ ሕይወት መምራት ችለናል።—ዘዳ. 10:12, 13

10. መዝሙር 37:29 ይሖዋን ተስፋ ስለሚያደርጉ ሰዎች ምን ይናገራል?

10 ብዙ ሰዎች ከአሁኑ ሕይወት ውጭ ሌላ ምንም ተስፋ የላቸውም። ሕይወታቸው ያተኮረው ሥራ በመሄድ፣ ቤተሰብ በመመሥረት፣ ልጆች በመውለድና ለጡረታ ጊዜያቸው ገንዘብ በማጠራቀም ላይ ብቻ ነው። አምላክ በሕይወታቸው ውስጥ ቦታ የለውም። የይሖዋ አገልጋዮች ግን ተስፋቸውን የሚጥሉት በእሱ ላይ ነው። (መዝ. 25:3-5፤ 1 ጢሞ. 6:17) ወዳጃችን የሆነውን አምላክ እናምነዋለን፤ እንዲሁም የሰጠን ተስፋ እንደሚፈጸም እናምናለን። የወደፊት ተስፋችን በገነት ውስጥ እሱን ለዘላለም ማገልገልን ያካትታል።—መዝሙር 37:29⁠ን አንብብ።

11. ወደ ይሖዋ መቅረባችን ምን ያስገኝልናል? ይሖዋስ ወደ እሱ ስንቀርብ ምን ይሰማዋል?

11 ወደ አምላክ መቅረብ በሌሎች በርካታ መንገዶችም ይጠቅመናል። ለምሳሌ ይሖዋ ወዳጆቹ ንስሐ እስከገቡ ድረስ ኃጢአታቸውን ይቅር እንደሚላቸው ቃል ገብቷል። (ኢሳ. 1:18) በመሆኑም ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ኃጢአቶች የተነሳ በሕሊና ወቀሳ እየተሠቃየን መኖር አያስፈልገንም። (መዝ. 32:1-5) ይሖዋን የማስደሰት ልዩ መብትም አግኝተናል። (ምሳሌ 23:15) ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት የሚያስገኛቸው ሌሎች በረከቶችም ወደ አእምሮህ መጥተው መሆን አለበት። ይሁንና ወደ አምላክ መቅረብህን መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው?

‘ወደ አምላክ መቅረባችንን’ መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

12. ወደ አምላክ ይበልጥ ለመቅረብ እስካሁን ምን አድርገሃል?

12 የተጠመቅክ ክርስቲያን ከሆንክ እስካሁንም ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ብዙ እርምጃዎችን ወስደሃል። ይሖዋ አምላክንና ክርስቶስ ኢየሱስን በተመለከተ ብዙ እውነቶችን ተምረሃል፤ ቀደም ሲል ከሠራሃቸው ኃጢአቶች ንስሐ ገብተሃል፤ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት አዳብረሃል፤ እንዲሁም ምግባርህ ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት አድርገሃል። ይሁንና ወደ አምላክ ይበልጥ መቅረብ ከፈለግን እነዚህን ነገሮች ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል።—ቆላ. 2:6

13. ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረባችንን ለመቀጠል የሚረዱን የትኞቹ ሦስት ነገሮች ናቸው?

13 ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረባችንን ለመቀጠል ምን ይረዳናል? (1) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንንና ማጥናታችንን መቀጠል ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ግባችን ስለ አምላክ መሠረታዊ እውቀት ማግኘት ብቻ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእኛ ያለውን ፈቃድ ለማስተዋልና በቃሉ ውስጥ በሰጠን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመመራት ጥረት ልናደርግ ይገባል። (ኤፌ. 5:15-17) (2) አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር በሚያሳዩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ማስረጃዎች ላይ በማሰላሰል እምነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል። (3) ይሖዋን የሚያሳዝኑ ድርጊቶችን መጥላታችንንና እነዚህን ድርጊቶች ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ከመመሥረት መቆጠባችንን መቀጠል ይኖርብናል።—መዝ. 1:1፤ 101:3

14. በ1 ቆሮንቶስ 10:31 መሠረት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ይሖዋን ለማስደሰት የትኞቹን ነገሮች ማድረግ እንችላለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 አንደኛ ቆሮንቶስ 10:31⁠ን አንብብ። ይሖዋን የሚያስደስቱ ነገሮችን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። ይህም በአገልግሎት ከመካፈልና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችንም ይሖዋን የሚያስደስቱ ነገሮችን ማድረግ ይኖርብናል። ለምሳሌ በሁሉም ነገር ሐቀኛ ስንሆንና ያለንን ነገር ለሌሎች ስናካፍል ይሖዋን እናስደስተዋለን። (2 ቆሮ. 8:21፤ 9:7) ይሖዋ፣ እሱ በስጦታ የሰጠንን ሕይወታችንን ከፍ አድርገን እንድንመለከተውም ይፈልጋል። ከአመጋገብና ከመጠጥ ልማዳችን ጋር በተያያዘ ሚዛናዊ በመሆን እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ጤንነታችንን በመንከባከብ የሕይወት ምንጭ ወደሆነው አምላክ ይበልጥ መቅረብ እንችላለን። ትናንሽ በሚመስሉ ጉዳዮችም ጭምር ይሖዋን ለማስደሰት የምናደርገው እያንዳንዱ ጥረት በእሱ ዘንድ ተወዳጅ ያደርገናል።—ሉቃስ 16:10

ሥዕሎች፦ ይሖዋን ማስደሰት የምንችልባቸው መንገዶች። 1. ተጠንቅቆ ማሽከርከር፦ መኪና እየነዳ ያለ ወንድም ቀይ መብራት ላይ ሲቆም። 2. ራሳችንን መንከባከብ፦ አንድ ወንድም ደጅ ላይ በፍጥነት ሲራመድ። 3. ጤናማ ምግብ መመገብ፦ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ የተቀመጡ የተለያዩ ጤናማ ምግቦች። 4. እንግዳ ተቀባይ መሆን፦ አንዲት እህት እጇ በጀሶ ለታሰረ አረጋዊት እህት አበባና ምግብ ስታመጣላት።

ይሖዋን ማስደሰት ከምንችልባቸው መንገዶች መካከል ተጠንቅቆ ማሽከርከር፣ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግና ጤናማ ምግብ በመመገብ ራሳችንን መንከባከብ እንዲሁም እንግዳ ተቀባይ መሆን ይገኙበታል (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)


15. ይሖዋ ሌሎችን እንዴት እንድንይዝ ይጠብቅብናል?

15 ይሖዋ ለጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ላልሆኑ ሰዎች ደግነት ያሳያል። (ማቴ. 5:45) እኛም ለሌሎች ተመሳሳይ አሳቢነት እንድናሳይ ይጠብቅብናል። ለምሳሌ ‘ስለ ማንም ክፉ ነገር እንዳንናገር፣ ጠበኞች እንዳንሆን እንዲሁም ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንድናንጸባርቅ’ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። (ቲቶ 3:2) በመሆኑም ሰዎች እምነታችንን ስለማይጋሩ ብቻ አንንቃቸውም። (2 ጢሞ. 2:23-25) ለሁሉም ሰዎች ምንጊዜም ደግነትና አሳቢነት በማሳየት ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንችላለን።

በምንሰናከልበት ጊዜም “ወደ አምላክ መቅረብ” እንችላለን

16. የመዝሙር 73 ጸሐፊ ይሖዋን ለተወሰነ ጊዜ ካገለገለ በኋላ ምን ተሰምቶት ነበር?

16 ይሁንና እውነት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ከቆየህ በኋላ ‘የይሖዋ ፍቅር የሚገባኝ ሰው አይደለሁም’ የሚል ስሜት ቢያድርብህስ? ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የመዝሙር 73 ጸሐፊም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እግሮቼ ከመንገድ ሊወጡ ተቃርበው ነበር፤ አዳልጦኝ ልወድቅ ምንም አልቀረኝም።” (መዝ. 73:2) ‘እንደተመረረ፣ ማመዛዘን እንዳልቻለና በይሖዋ ፊት ማሰብ እንደማይችል እንስሳ እንደሆነ’ እሱ ራሱ በሐቀኝነት ተናግሯል። (መዝ. 73:21, 22) ታዲያ በዚህ ስህተቱ የተነሳ የይሖዋ ፍቅር እንደማይገባውና ምንም ተስፋ እንደሌለው ተሰምቶታል?

17. (ሀ) መዝሙራዊው ቅስሙ በተሰበረበት ጊዜም እንኳ ምን አድርጓል? (ለ) እኛስ ከእሱ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

17 መዝሙራዊው ይሖዋ እንደተወው ተሰምቶት የነበረ ቢሆን እንኳ ይህ ስሜት ለረጅም ጊዜ የቆየ አይመስልም። ቅስሙ በተሰበረበት ጊዜም እንኳ ወደ አምላክ መቅረብ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል፤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አሁን ግን ሁልጊዜ ከአንተ ጋር ነኝ፤ አንተም ቀኝ እጄን ይዘሃል። በምክርህ ትመራኛለህ፤ በኋላም ክብር ታጎናጽፈኛለህ።” (መዝ. 73:23, 24) እኛም በምንደክምበት ወይም ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ ዓለት የሆነው ይሖዋ እንዲያጠናክረን መለመን ይኖርብናል። (መዝ. 73:26፤ 94:18) ለተወሰነ ጊዜ ያህል እግራችን ከመንገድ ቢወጣም እንኳ ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ እንደሆነ በመተማመን ወደ እሱ መመለስ እንችላለን። (መዝ. 86:5) በተለይ በሐዘን በምንዋጥበት ጊዜ ወደ አምላካችን ይበልጥ መቅረብ ይኖርብናል።—መዝ. 103:13, 14

ሥዕሎች፦ 1. ተስፋ የቆረጠ አንድ ወንድም አልጋ ላይ ተቀምጦ። 2. በኋላ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ አንድን ባልና ሚስት ሰላም እያለ ፈገግ ሲል።

በመንፈሳዊ እንደደከምን ሲሰማን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ በመካፈል ወደ ይሖዋ መቅረብ ይኖርብናል (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)


ለዘላለም “ወደ አምላክ መቅረብ”

18. ለዘላለም ወደ ይሖዋ መቅረብ እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው?

18 ለዘላለም ወደ ይሖዋ መቅረብና እሱን ይበልጥ ማወቅ እንችላለን፤ በዚህ ረገድ የተቀመጠ ገደብ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ መንገድ፣ ጥበብና እውቀት “የማይደረስበት” እንደሆነ ይናገራል።—ሮም 11:33

19. የመዝሙር መጽሐፍ ምን ዋስትና ይሰጠናል?

19 መዝሙር 79:13 እንዲህ ይላል፦ “እኛ ሕዝቦችህ፣ በመስክህ ያሰማራኸን መንጋ፣ ለዘላለም ምስጋና እናቀርብልሃለን፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ውዳሴህን እናሰማለን።” አንተም ወደ ይሖዋ መቅረብህን ስትቀጥል እሱ ለዘላለም እንደሚባርክህ እርግጠኛ መሆን እንዲሁም በልበ ሙሉነት “አምላክ . . . ለዘላለም የልቤ ዓለትና ድርሻዬ ነው” ማለት ትችላለህ።—መዝ. 73:26

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • “ወደ አምላክ መቅረብ” በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው?

  • “ወደ አምላክ መቅረብ” የሚጠቅመን በየትኞቹ መንገዶች ነው?

  • ‘ወደ አምላክ መቅረባችንን’ መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 32 ከይሖዋ ጎን ቁም!

a ለረጅም ጊዜ በዘለቀ የጭንቀት ወይም የሐዘን ስሜት የሚሠቃዩ አንዳንድ ሰዎች የሕክምና እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ ቁጥር 1 2023⁠ን ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ