የጥናት ርዕስ 17
መዝሙር 99 እልፍ አእላፋት ወንድሞች
መቼም ቢሆን ብቻችንን አይደለንም
“እረዳሃለሁ።”—ኢሳ. 41:10
ዓላማ
ይሖዋ የሚንከባከበን በየትኞቹ አራት መንገዶች እንደሆነ እንመለከታለን።
1-2. (ሀ) ፈተናዎችን የምንጋፈጠው ብቻችንን አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
ከባድ መከራ ሲያጋጥመን በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ውስጥ ብቻችንን ትንሽዬ ጀልባ ላይ እንዳለን ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ይሁንና ፈተናዎችን የምንጋፈጠው ብቻችንን አይደለም። የሚወደን የሰማዩ አባታችን ያለንበትን መከራ ያያል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ፈተናውን እንድንቋቋም እንደሚረዳን ቃል ገብቶልናል። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን “እረዳሃለሁ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል።—ኢሳ. 41:10
2 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ይሖዋ በሚከተሉት አራት መንገዶች የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን፦ (1) ይመራናል፤ (2) የሚያስፈልገንን ነገር ያሟላልናል፤ (3) ይጠብቀናል፤ እንዲሁም (4) ያጽናናናል። ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ ምንም ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመን መቼም ቢሆን እንደማይረሳን ቃል ገብቶልናል። ፈጽሞ አይተወንም። ስለዚህ መቼም ቢሆን ብቻችንን አይደለንም።
ይሖዋ ይመራናል
3-4. ይሖዋ የሚመራን እንዴት ነው? (መዝሙር 48:14)
3 መዝሙር 48:14ን አንብብ። ይሖዋ ራሳችንን እንድንመራ አይጠብቅብንም። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹን የሚመራቸው እንዴት ነው? እንዲህ የሚያደርግበት አንዱ መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (መዝ. 119:105) በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ አማካኝነት ይሖዋ ጥሩ ውሳኔዎችን እንድናደርግና ግሩም ባሕርያትን እንድናዳብር ይረዳናል፤ ይህም በአሁኑ ጊዜ ይበልጥ ደስተኛ እንድንሆን፣ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል።a ለምሳሌ ቂምን እንድንተው፣ በሁሉም ነገር ሐቀኛ እንድንሆን እንዲሁም ሌሎችን አጥብቀን ከልብ እንድንወድ ያስተምረናል። (መዝ. 37:8፤ ዕብ. 13:18፤ 1 ጴጥ. 1:22) እንዲህ ያሉትን ግሩም ባሕርያት ስናንጸባርቅ ጥሩ ወላጆች፣ ጥሩ የትዳር አጋሮች እንዲሁም ጥሩ ጓደኞች እንሆናለን።
4 በተጨማሪም ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ፈተና ያጋጠማቸውና እንደ እኛው ዓይነት ስሜት የተሰማቸው ሰዎች ታሪክ እንዲቀመጥልን አድርጓል። (1 ቆሮ. 10:13፤ ያዕ. 5:17) እነዚህን እውነተኛ ታሪኮች ስናነብና ያገኘነውን ትምህርት በሥራ ላይ ስናውል ቢያንስ ሁለት ጥቅሞችን እናገኛለን። አንደኛ፣ ብቻችንን እንዳልሆንን እንገነዘባለን፤ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማቸውና ችግሩን በጽናት መቋቋም የቻሉ ሌሎች ሰዎችም አሉ። (1 ጴጥ. 5:9) ሁለተኛ፣ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች እንዴት መቋቋም እንደምንችል እንማራለን።—ሮም 15:4
5. ይሖዋ እኛን በሕይወት መንገድ ላይ ለመምራት በእነማን ይጠቀማል?
5 ይሖዋ በእምነት አጋሮቻችን አማካኝነትም ይመራናል።b ለምሳሌ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች እኛን ለማበረታታት ሲሉ በየተወሰነ ጊዜው ጉባኤዎችን ይጎበኛሉ። የሚያቀርቧቸው ንግግሮች እምነታችንን ያጠናክሩልናል፤ እንዲሁም ውድ የሆነውን አንድነታችንን ለመጠበቅ ይረዱናል። (ሥራ 15:40–16:5) የጉባኤ ሽማግሌዎችም ለእያንዳንዱ አስፋፊ ልባዊ ትኩረት ይሰጣሉ። (1 ጴጥ. 5:2, 3) ወላጆች ልጆቻቸውን በመንፈሳዊ ይመሯቸዋል፤ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታና ጠቃሚ ልማዶችን እንዲያዳብሩ ይረዷቸዋል። (ምሳሌ 22:6) በተጨማሪም የጎለመሱ እህቶች ጥሩ ምሳሌ በመሆን እንዲሁም ተግባራዊ ምክርና ማበረታቻ በመስጠት ወጣት እህቶችን ይረዳሉ።—ቲቶ 2:3-5
6. ከይሖዋ አመራር ለመጠቀም ምን ማድረግ ይኖርብናል?
6 ይሖዋ የሚያስፈልገንን አመራር በመስጠት የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል። ታዲያ እኛ እሱ ለሚሰጠን አመራር አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ 3:5, 6 “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ” ይላል። እንዲህ ካደረግን ‘እሱ ጎዳናችንን ቀና ያደርገዋል’፤ ማለትም ከተለያዩ ችግሮች እንድንጠበቅና ደስተኛ ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ፍቅራዊ ምክር ስለሚሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን!—መዝ. 32:8
ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ያሟላልናል
7. ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር የሚያሟላልን እንዴት ነው? (ፊልጵስዩስ 4:19)
7 ፊልጵስዩስ 4:19ን አንብብ። ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ከመምራት በተጨማሪ የሚያስፈልገንን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ይባርክልናል። (ማቴ. 6:33፤ 2 ተሰ. 3:12) ስለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች ማሰባችን የሚጠበቅ ነገር ቢሆንም ይሖዋ ስለ እነዚህ ነገሮች ከልክ በላይ እንዳንጨነቅ መክሮናል። (ማቴ. 6:25) ለምን? ምክንያቱም አባታችን ታማኝ አገልጋዮቹ በሚቸገሩበት ጊዜ ፈጽሞ አይተዋቸውም። (ማቴ. 6:8፤ ዕብ. 13:5) የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያሟላልን በገባው ቃል መተማመን እንችላለን።
8. ይሖዋ ለዳዊት ምን አድርጎለታል?
8 ይሖዋ ዳዊትን የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ዳዊት ስደተኛ ሆኖ ባሳለፋቸው አስቸጋሪ ዓመታት እሱም ሆነ ሰዎቹ ሕይወታቸውን ለማቆየት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ይሖዋ አሟልቶላቸዋል። ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ይሖዋ የተንከባከበው እንዴት እንደሆነ መለስ ብሎ ሲያስብ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በአንድ ወቅት ወጣት ነበርኩ፤ አሁን ግን አርጅቻለሁ፤ ይሁንና ጻድቅ ሰው ሲጣል፣ ልጆቹም ምግብ ሲለምኑ አላየሁም።” (መዝ. 37:25) አንተም ብትሆን በሕይወት ዘመንህ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሲያሟላላቸው ተመልክተህ መሆን አለበት።
9. በዛሬው ጊዜ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ይሖዋ ለሕዝቦቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያሟላላቸው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
9 አደጋ በሚከሰትበት ጊዜም ይሖዋ ለሕዝቦቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያሟላላቸዋል። ለምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ረሃብ በተከሰተበት ወቅት በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖች ለተቸገሩ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እርዳታ ልከዋል። (ሥራ 11:27-30፤ ሮም 15:25, 26) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም ተመሳሳይ የልግስና መንፈስ ያሳያሉ። አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ጉዳት ለደረሰባቸው ክርስቲያኖች እንደ ምግብ፣ ውኃ፣ ልብስና መድኃኒት ያሉ መሠረታዊ ነገሮችን እንዲልኩ ሕዝቦቹን ያነሳሳቸዋል። የግንባታ ቡድኖች በአደጋው የተጎዱ ቤቶችንና የስብሰባ አዳራሾችን ይጠግናሉ። በተጨማሪም የይሖዋ አገልጋዮች ንብረታቸውንም ሆነ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ክርስቲያኖች ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ለመስጠት ፈጣኖች ናቸው።c
በአደጋ ጊዜ ይሖዋ የሚያጽናናን እንዴት ነው? (አንቀጽ 9ን ተመልከት)e
10-11. ከቦሪስ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?
10 ይሖዋ በአሁኑ ወቅት እሱን ለማያመልኩ ሰዎችም የሚያስፈልጋቸውን ነገር በልግስና ያሟላላቸዋል። እኛም በተመሳሳይ፣ እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች ደግነት ማሳየት የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች እንፈልጋለን። (ገላ. 6:10) እንዲህ ማድረጋችን ብዙውን ጊዜ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል። የቦሪስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በዩክሬን የሚኖረው ቦሪስ የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ነበር። ቦሪስ የይሖዋ ምሥክር ባይሆንም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ተማሪዎችን ሁልጊዜ በደግነት ይይዛቸው እንዲሁም ለእምነታቸው አክብሮት ያሳይ ነበር። ቦሪስ በሚኖርበት አካባቢ ጦርነት በተነሳበት ወቅት የተሻለ ሰላም ወዳለበት የአገሪቱ ክፍል ለመሸሽ ወሰነ። በዚህ ጊዜ ወንድሞቻችን ረዱት። በኋላም ቦሪስ በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኘ። ቦሪስ ያሳለፈውን ነገር አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ለየት ያለ ትኩረት ሰጥተውኛል፤ እንዲሁም ተንከባክበውኛል። ከልብ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።”
11 እኛም የእምነት አጋሮቻችን ሆኑም አልሆኑ ለተቸገሩ ሰዎች ፍቅር በማሳየት መሐሪ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን መምሰል እንችላለን። (ሉቃስ 6:31, 36) ለሰዎች ፍቅር ለማሳየት የምናደርገው ጥረት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን እንደሚያነሳሳቸው ተስፋ እናደርጋለን። (1 ጴጥ. 2:12) ይሁንና ውጤቱ ምንም ሆነ ምን፣ በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ ማጣጣማችን አይቀርም።—ሥራ 20:35
ይሖዋ ይጠብቀናል
12. ይሖዋ ለሕዝቦቹ በቡድን ደረጃ ምን ዓይነት ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብቷል? (መዝሙር 91:1, 2, 14)
12 መዝሙር 91:1, 2, 14ን አንብብ። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ እንደሚያደርግልን ቃል ገብቶልናል። ሰይጣን እውነተኛውን አምልኮ እንዲበክል አይፈቅድለትም። (ዮሐ. 17:15) ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ደግሞ ይሖዋ ለሕዝቦቹ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ጥበቃም እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብቷል። ይህን ቃሉን እንደሚፈጽም ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።—ራእይ 7:9, 14
13. ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?
13 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ምን ዓይነት ጥበቃ ያደርግልናል? በቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንድንችል ይረዳናል። (ዕብ. 5:14) በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕይወታችንን ስንመራ ራሳችንን ከመንፈሳዊም ሆነ ከአካላዊ ጉዳት እንጠብቃለን። (መዝ. 91:4) በተጨማሪም ይሖዋ በጉባኤው አማካኝነት ጥበቃ ያደርግልናል። (ኢሳ. 32:1, 2) ይሖዋን በሚወዱና እሱ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚመሩ ሰዎች በመከበባችን የሚያስፈልገንን ማበረታቻ እናገኛለን፤ እንዲሁም መጥፎ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ይኖረናል።—ምሳሌ 13:20
14. (ሀ) ይሖዋ አንዳንድ ፈተናዎች እንዲደርሱብን የሚፈቅደው ለምንድን ነው? (ለ) መዝሙር 9:10 ምን ዋስትና ይሰጠናል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
14 ይሖዋ በጥንት ዘመን አገልጋዮቹ አካላዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የጠበቃቸው ጊዜ አለ። ሆኖም ይህን ያደረገው ሁልጊዜ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ “ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሊያጋጥሙን ይችላሉ። (መክ. 9:11) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑ እንዲረጋገጥ ሲል በታሪክ ዘመናት ሁሉ አገልጋዮቹ ስደት እንዲደርስባቸው አልፎ ተርፎም ሞትን እንዲጋፈጡ ፈቅዷል። (ኢዮብ 2:4-6፤ ማቴ. 23:34) በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ የሚደርሱብንን ፈተናዎች ላያስወግድልን ቢችልም እንኳ እሱን የሚወዱትን ሰዎች መቼም ቢሆን እንደማይተዋቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።d—መዝ. 9:10
ይሖዋ ያጽናናናል
15. በጸሎት፣ በአምላክ ቃልና በእምነት አጋሮቻችን አማካኝነት ማጽናኛ የምናገኘው እንዴት ነው? (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4)
15 ሁለተኛ ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ። አልፎ አልፎ ከባድ ሐዘን፣ ጭንቀት ወይም ውጥረት ያጋጥመናል። ምናልባትም በአሁኑ ወቅት፣ ባጋጠመህ አስጨናቂ ሁኔታ የተነሳ ብቸኝነት እየተሰማህ ሊሆን ይችላል። ይህን ስሜትህን ማን ይረዳልሃል? ይሖዋ ይረዳልሃል። እሱ ሥቃያችን ይሰማዋል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን “በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።” እንዴት? ለይሖዋ ምልጃ ስናቀርብ ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያስተላለፈልንን መልእክት በምናነብበት ጊዜም ማጽናኛ እናገኛለን። ይሖዋ በዚህ ውድ ስጦታ አማካኝነት ፍቅሩን ይገልጽልናል፤ ጥበበኞች እንድንሆን ይረዳናል፤ እንዲሁም ተስፋ ይሰጠናል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞቻችን ጋር የምናሳልፈው አስደሳች ጊዜና የምናገኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማበረታቻም ያጽናናናል።
16. ከናታንና ከፒሪሲላ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
16 ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ማጽናኛና ማበረታቻ የሚሰጠን እንዴት እንደሆነ ለማየት በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩትን የናታንን እና የፕሪሲላን ተሞክሮ እንመልከት። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ለመዛወር ወሰኑ። ናታን “ይሖዋ ጥረታችንን እንደሚባርክልን ተማምነን ነበር” ብሏል። ሆኖም ወደ አዲሱ ምድባቸው ከሄዱ በኋላ ያልተጠበቀ የጤና እክልና የኢኮኖሚ ችግር አጋጠማቸው። በኋላም ቀደም ሲል ወደሚኖሩበት አካባቢ ለመመለስ ተገደዱ። ያኔም ቢሆን የኢኮኖሚ ችግራቸው አልተቀረፈም። ናታን እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ በጠበቅነው መንገድ ያልባረከን ለምን እንደሆነ ግራ ገባኝ። እንዲያውም ‘ያጠፋሁት ነገር ይኖር ይሆን?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።” ከጊዜ በኋላ ግን ናታንና ፕሪሲላ አምላክ በችግራቸው ጊዜ እንዳልተዋቸው መገንዘብ ጀመሩ። ናታን እንዲህ ብሏል፦ “በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስ ማበረታቻና መመሪያ እንደሚሰጠን ጥበበኛ ወዳጅ ሆኖልን ነበር። በፈተናው ላይ ከማተኮር ይልቅ ይሖዋ ፈተናውን እንድንቋቋም የረዳን እንዴት እንደሆነ ማሰባችን ወደፊት የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በእምነት ለመጋፈጥ አዘጋጅቶናል።”
17. ሄልጋ የተባለች እህት ማጽናኛ ያገኘችው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ማጽናኛ ሊሰጡን ይችላሉ። እንዴት? በሃንጋሪ የምትኖረውን የሄልጋን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ከተለያዩ ችግሮች ጋር ስትታገል ስለኖረች በጭንቀትና በዋጋ ቢስነት ስሜት ተውጣ ነበር። ሆኖም ያሳለፈችውን ሕይወት መለስ ብላ ስታስብ ይሖዋ በጉባኤው አማካኝነት እንዳጽናናት አስተውላለች። እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “በሥራ፣ ልጄን በማስታመም ወይም በሌሎች ችግሮች የተነሳ አቅሜ በሚሟጠጥበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ይረዳኝ ነበር። ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ይሖዋ እኔን ለማጽናናት የገባውን ቃል ያልጠበቀበት አንድም ቀን የለም። ሌሎች በሚናገሯቸው ደግነት፣ አሳቢነትና አድናቆት የሚንጸባረቅባቸው ሐሳቦች አማካኝነት ያበረታታኛል። ልክ በሚያስፈልገኝ ጊዜ የጽሑፍ መልእክት ወይም ፖስት ካርድ ይደርሰኛል፤ ወይም ደግሞ ወንድሞቼ ያመሰግኑኛል።”
ይሖዋ ሌሎችን ለማጽናናት ሊጠቀምብህ የሚችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 17ን ተመልከት)
18. ሌሎችን ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?
18 ሌሎችን በማጽናናት አምላካችንን መምሰል የምንችልበት ልዩ አጋጣሚ አለን። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በትዕግሥት ልናዳምጣቸው፣ በሚያጽናኑ ቃላት ልናነጋግራቸው እንዲሁም ተግባራዊ እርዳታ ልንሰጣቸው እንችላለን። (ምሳሌ 3:27) በአሁኑ ወቅት ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎችን ጨምሮ በመከራ ውስጥ ያሉትን በሙሉ ለማጽናናት ጥረት እናደርጋለን። ጎረቤቶቻችን ሐዘን፣ ሕመም ወይም ጭንቀት ሲያጋጥማቸው ሄደን እንጠይቃቸዋለን፤ እናዳምጣቸዋለን፤ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያበረታቱ ሐሳቦችን እናሳያቸዋለን። “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ስንመስል የእምነት አጋሮቻችን ፈተናዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ ከመርዳት ባለፈ አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ንጹሕ አምልኮን እንዲቀበሉ ልናነሳሳቸው እንችላለን።—ማቴ. 5:16
ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን ነው
19. ይሖዋ የትኞቹን ነገሮች ያደርግልናል? እሱን መምሰል የምንችለውስ እንዴት ነው?
19 ይሖዋ ለሚወዱት ሰዎች ሁሉ በጣም ያስብላቸዋል። በመከራ ውስጥ ስንሆን አይተወንም። አንድ አባት ልጁን በፍቅር እንደሚንከባከብ ሁሉ ይሖዋም ታማኝ አገልጋዮቹን ይንከባከባቸዋል። ይመራናል፤ የሚያስፈልገንን ነገር ያሟላልናል፤ ይጠብቀናል፤ እንዲሁም ያጽናናናል። እኛም በመከራ ውስጥ ያሉትን በመደገፍና በማበረታታት አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን መምሰል እንችላለን። የተለያዩ ፈተናዎችና ልብ የሚሰብሩ ችግሮች ሊያጋጥሙን ቢችሉም ይሖዋ ከጎናችን እንደማይለይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ምክንያቱም “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ” በማለት ቃል ገብቶልናል። (ኢሳ. 41:10) ይህ ምንኛ የሚያበረታታ ነው! በእርግጥም መቼም ቢሆን ብቻችንን አይደለንም።
መዝሙር 100 እንግዳ ተቀባይ ሁኑ
a በሚያዝያ 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ አድርጉ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b በየካቲት 2024 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ምንጊዜም የይሖዋን አመራር ተከተሉ” የሚለውን ርዕስ ከአንቀጽ 11-14ን ተመልከት።
c jw.org ላይ ባለው መፈለጊያ ውስጥ “የአደጋ ጊዜ እርዳታ” ብለህ በመጻፍ የቅርብ ጊዜ ምሳሌዎችን ማግኘት ትችላለህ።
d በየካቲት 2017 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ በማላዊ የሚኖሩ ወንድሞች የተፈጥሮ አደጋ ከደረሰ በኋላ ቁሳዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ሲደረግላቸው።