የጥናት ርዕስ 24
መዝሙር 98 ቅዱሳን መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው
ያዕቆብ ሊሞት ሲል ከተናገረው ትንቢት የምናገኘው ትምህርት—ክፍል 1
“በኋለኞቹ ቀናት ምን እንደሚያጋጥማችሁ እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ።”—ዘፍ. 49:1
ዓላማ
ያዕቆብ ሊሞት ሲል ስለ ሮቤል፣ ስለ ስምዖን፣ ስለ ሌዊ እና ስለ ይሁዳ ከተናገራቸው ትንቢቶች የምናገኛቸው ተግባራዊ ትምህርቶች።
1-2. ያዕቆብ በሕይወቱ ማብቂያ ላይ ምን አደረገ? ለምንስ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ያዕቆብ ቤተሰቡን ይዞ ከከነአን ወደ ግብፅ ከተጓዘ 17 ዓመታት አልፈዋል። (ዘፍ. 47:28) በዚያ ጊዜ፣ ከሚወደው ልጁ ከዮሴፍ ጋር እንደገና በመገናኘቱ እንዲሁም መላው ቤተሰቡ አንድ ላይ በመሰባሰቡ በጣም ተደስቶ ነበር። አሁን ግን ያዕቆብ መሞቻው እንደቀረበ ተሰምቶታል። ስለዚህ ወሳኝ የሆነ የቤተሰብ ስብሰባ ጠራ።—ዘፍ. 49:28
2 በዚያ ዘመን፣ ሊሞት የተቃረበ አንድ የቤተሰብ ራስ ቤተሰቡን አንድ ላይ ሰብስቦ የመጨረሻ መመሪያ መስጠቱ የተለመደ ነበር። (ኢሳ. 38:1) በዚያ ስብሰባ ላይ፣ እሱ ከሞተ በኋላ የቤተሰቡ ራስ የሚሆነው ማን እንደሆነም ሊናገር ይችላል።
መሞቻው የተቃረበው ያዕቆብ ስለ 12 ወንዶች ልጆቹ ትንቢት ሲናገር (አንቀጽ 1-2ን ተመልከት)
3. በዘፍጥረት 49:1, 2 መሠረት ያዕቆብ የተናገራቸው ቃላት ልዩ ትርጉም አላቸው የምንለው ለምንድን ነው?
3 ዘፍጥረት 49:1, 2ን አንብብ። ነገር ግን ይህ ስብሰባ ተራ የቤተሰብ ስብሰባ አልነበረም። ያዕቆብ ነቢይ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዩን በመንፈሱ በመምራት ወደፊት በዘሮቹ ላይ የሚደርሱ ታላላቅ ክንውኖችን እንዲናገር አነሳስቶታል። በመሆኑም ያዕቆብ ሊሞት ሲል ለልጆቹ የተናገረው ሐሳብ ትንቢት ነበር።
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን? (“የያዕቆብ ቤተሰብ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
4 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ያዕቆብ ለአራት ልጆቹ ማለትም ለሮቤል፣ ለስምዖን፣ ለሌዊና ለይሁዳ የተናገራቸውን ነገሮች እንመረምራለን። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ደግሞ ያዕቆብ ለቀሪዎቹ ስምንት ወንዶች ልጆቹ የተናገረውን ሐሳብ እንመለከታለን። ቀጥሎ እንደምናየው፣ ያዕቆብ የተናገረው ስለ ልጆቹ ብቻ ሳይሆን የጥንቷን የእስራኤል ብሔር ስለመሠረቱት ስለ ዘሮቻቸውም ጭምር ነው። የእስራኤልን ብሔር ታሪክ መመርመራችን የያዕቆብ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል። እንዲሁም ያዕቆብ የተናገራቸውን ቃላት በመመርመር የሰማዩን አባታችንን ይሖዋን ለማስደሰት የሚረዱንን ጠቃሚ ትምህርቶች እናገኛለን።
ሮቤል
5. ሮቤል ምን አገኛለሁ ብሎ ጠብቆ ሊሆን ይችላል?
5 ያዕቆብ በመጀመሪያ የተናገረው ለሮቤል ነው፤ “አንተ የበኩር ልጄ ነህ” አለው። (ዘፍ. 49:3) ሮቤል የበኩር ልጅ እንደመሆኑ መጠን ከአባቱ ንብረቶች ሁለት ድርሻ እንደሚያገኝ ጠብቆ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም አባቱ ከሞተ በኋላ የዚያ ቤተሰብ ራስ እንደሚሆን እንዲሁም ይህ መብት ለዘሮቹ እንደሚተላለፍ ጠብቆ ሊሆን ይችላል።
6. ሮቤል የብኩርና መብቱን ያጣው ለምንድን ነው? (ዘፍጥረት 49:3, 4)
6 ይሁን እንጂ ሮቤል የብኩርና መብቱን አጥቷል። (1 ዜና 5:1) ለምን? ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ የያዕቆብ ቁባት ከሆነችው ከባላ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽሞ ነበር። ባላ የያዕቆብ ሚስት የነበረችው የሟቿ የራሔል አገልጋይ ነበረች፤ ያዕቆብ ራሔልን በጣም ይወዳት ነበር። (ዘፍ. 35:19, 22) ሮቤል የያዕቆብ ሌላኛዋ ሚስት የሆነችው የሊያ ልጅ ነበር። ሮቤል ከባላ ጋር የተኛው በፍትወት ስሜት ተገፋፍቶ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ይህን ያደረገው፣ አባቱ ባላን ጠልቶ እናቱን ይበልጥ እንዲወዳት አስቦ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ ያደረገው ነገር ይሖዋንም ሆነ አባቱን በጣም የሚያሳዝን ነበር።—ዘፍጥረት 49:3, 4ን አንብብ።
7. የሮቤልና የዘሮቹ ታሪክ ምን ይመስላል? (“ያዕቆብ ሊሞት ሲል የተናገረው ትንቢት” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
7 ያዕቆብ ሮቤልን “የበላይ አትሆንም” ብሎታል። እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ከሮቤል ዘሮች መካከል ንጉሥ፣ ካህን ወይም ነቢይ የሆነ አንድም ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። ያም ቢሆን ያዕቆብ የልጅነት መብቱን አልከለከለውም፤ የሮቤል ዘሮችም በእስራኤል ውስጥ አንድ ነገድ ሆነዋል። (ኢያሱ 12:6) ሮቤል በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ ግሩም ባሕርያትን አንጸባርቋል፤ እንዲሁም ከዚያ በኋላ የፆታ ብልግና እንደፈጸመ የሚያሳይ ዘገባ አናገኝም።—ዘፍ. 37:20-22፤ 42:37
8. ከሮቤል ታሪክ ምን እንማራለን?
8 ምን ትምህርት እናገኛለን? ራሳችንን ለመግዛትና ከፆታ ብልግና ለመሸሽ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ኃጢአት ለመፈጸም ስንፈተን ድርጊታችን ይሖዋን፣ ቤተሰቦቻችንንና ሌሎችን የሚጎዳው እንዴት እንደሆነ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል። በተጨማሪም “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ [እንደሚያጭድ]” ማስታወስ ይኖርብናል። (ገላ. 6:7) በሌላ በኩል ደግሞ የሮቤል ታሪክ የይሖዋን ምሕረት ያስታውሰናል። ምንም እንኳ ይሖዋ የሠራናቸው ስህተቶች ከሚያስከትሉብን መዘዝ ባይከልለንም ንስሐ ከገባንና ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥረት ካደረግን ይሖዋ ጥረታችንን ይባርክልናል።
ስምዖን እና ሌዊ
9. ያዕቆብ ስምዖንንና ሌዊን ጠንከር ባሉ ቃላት የተናገራቸው ለምንድን ነው? (ዘፍጥረት 49:5-7)
9 ዘፍጥረት 49:5-7ን አንብብ። ቀጥሎም ያዕቆብ ጠንከር ባሉ ቃላት ስምዖንንና ሌዊን አነጋግሯቸዋል። ከዓመታት በፊት የያዕቆብ ልጅ ዲና፣ ሴኬም በተባለ ከነአናዊ ተደፍራ ነበር። እንደሚጠበቀው፣ ሁሉም የያዕቆብ ልጆች በእህታቸው ላይ በደረሰው ነገር በጣም ተበሳጭተው ነበር። ስምዖንና ሌዊ ግን የጭካኔ እርምጃ ወሰዱ። ስምዖንና ሌዊ፣ ሴኬምና የከተማዋ ሰዎች ለመገረዝ ከተስማሙ ከእነሱ ጋር ሰላም እንደሚያወርዱ ቃል በመግባት አታለሏቸው። ሰዎቹም በሐሳባቸው ተስማሙ። ሰዎቹ ገና በግርዘቱ ቆስለው እያሉ “ስምዖንና ሌዊ ማንም ሳይጠረጥራቸው ሰይፋቸውን ይዘው ወደ ከተማዋ በመግባት ወንዶቹን ሁሉ ገደሉ።”—ዘፍ. 34:25-29
10. ያዕቆብ ስለ ስምዖንና ስለ ሌዊ የተናገራቸው ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው? (“ያዕቆብ ሊሞት ሲል የተናገረው ትንቢት” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
10 ያዕቆብ ሁለቱ ልጆቹ በፈጸሙት የጭካኔ ድርጊት በጣም ተረብሾ ነበር። በመላዋ እስራኤል ተበትነውና ተሰራጭተው እንደሚኖሩ ትንቢት ተናገረ። እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት የእስራኤል ብሔር ከ200 ዓመት በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገባ ተፈጽመዋል። የስምዖን ነገድ የወረሰው በይሁዳ ነገድ ርስት መካከል ተሰበጣጥረው የሚገኙ ቦታዎችን ነው። (ኢያሱ 19:1) የሌዊ ርስት ደግሞ በእስራኤል ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ 48 ከተሞችን የሚያካትት ነበር።—ኢያሱ 21:41
11. የስምዖንና የሌዊ ነገዶች ምን ጥሩ ነገር አከናውነዋል?
11 የስምዖንና የሌዊ ዘሮች የአባቶቻቸውን ስህተት አልደገሙም። የሌዊ ነገድ ለንጹሕ አምልኮ አስደናቂ ታማኝነት አሳይቷል። ሙሴ በሲና ተራራ ሕጉን ከይሖዋ በተቀበለበት ወቅት በርካታ እስራኤላውያን በጥጃ አምልኮ ተካፍለው ነበር። ሌዋውያን ግን ከሙሴ ጎን በመቆም ጣዖት አምላኪዎቹን አስወግደዋል። (ዘፀ. 32:26-29) ይሖዋ የሌዊን ነገድ ለይቶ በመምረጥ ውድ የሆነውን የክህነት መብት ሰጥቶታል። (ዘፀ. 40:12-15፤ ዘኁ. 3:11, 12) በኋላም እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር በተቆጣጠሩበት ወቅት ስምዖናውያን የይሖዋን ዓላማ ለመፈጸም ከይሁዳ ነገድ ጋር አብረው በድፍረት ተዋግተዋል።—መሳ. 1:3, 17
12. ከስምዖንና ከሌዊ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
12 ምን ትምህርት እናገኛለን? ቁጣ ውሳኔያችሁንና ድርጊታችሁን እንዲቆጣጠረው አትፍቀዱ። እናንተም ሆናችሁ የምትወዷቸው ሰዎች ግፍ ሲፈጸምባችሁ መበሳጨታችሁ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። (መዝ. 4:4) ነገር ግን በመረረ ቁጣ ተነሳስተን የምንናገራቸውና የምናደርጋቸው ነገሮች ይሖዋን እንደሚያሳዝኑት ማስታወስ ይኖርብናል። (ያዕ. 1:20) በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤ ውጭ በደል ሲፈጸምብን ጉዳዩን መያዝ ያለብን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። እንዲህ በማድረግ፣ ቁጣን አለመቆጣጠር ከሚያስከትለው ጉዳት እንጠበቃለን። (ሮም 12:17, 19፤ 1 ጴጥ. 3:9) ከእነሱ ታሪክ የምናገኘው ሌላም ትምህርት አለ። ወላጆቻችሁ ይሖዋን የሚያስደስት ነገር ባያደርጉም እንኳ የእነሱን ምሳሌ ላለመከተል መምረጥ እንደምትችሉ አስታውሱ። ይሖዋን ማስደሰትና የእሱን በረከት ማግኘት እንደማትችሉ ሊሰማችሁ አይገባም። ይሖዋ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥረት ስታደርጉ ይረዳችኋል፤ እንዲሁም ይባርካችኋል።
ይሁዳ
13. ይሁዳ የእሱ ተራ ሲደርስ አባቱ የሚናገረው ነገር ያስጨነቀው ለምን ሊሆን ይችላል?
13 ያዕቆብ ቀጥሎ ያነጋገረው ይሁዳን ነው። ይሁዳ አባቱ ለታላላቅ ወንድሞቹ የተናገረውን ነገር ከሰማ በኋላ ትንሽ ተጨንቆ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም እሱም ከባድ ስህተቶችን ሠርቷል። ከወንድሞቹ ጋር በመሆን የሴኬም ከተማን ዘርፏል። (ዘፍ. 34:27) ዮሴፍን ለባርነት በመሸጥና አባቱን በመዋሸት ከወንድሞቹ ጋር ተባብሯል። (ዘፍ. 37:31-33) በኋላ ላይ ደግሞ ምራቱ ትዕማር ዝሙት አዳሪ እንደሆነች በማሰብ አብሯት ተኝቶ ነበር።—ዘፍ. 38:15-18
14. ይሁዳ ምን ጥሩ ነገሮችን አድርጓል? (ዘፍጥረት 49:8, 9)
14 ያም ቢሆን ያዕቆብ በመንፈስ መሪነት ይሁዳን ከመባረክና ከማመስገን ውጭ የተናገረው ሌላ ነገር አልነበረም። (ዘፍጥረት 49:8, 9ን አንብብ።) ይሁዳ በዕድሜ ለገፋው አባቱ ስሜት በጣም እንደሚያስብ አሳይቷል። እንዲሁም ለታናሽ ወንድሙ ለቢንያም ርኅራኄ አሳይቷል።—ዘፍ. 44:18, 30-34
15. የይሁዳ በረከት የተፈጸመው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
15 ያዕቆብ፣ ይሁዳ በወንድሞቹ መካከል መሪ እንደሚሆን ተናግሯል። ነገር ግን ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። ይሁዳ የመሪነት ሚና እንደተጫወተ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸው ከ200 ዓመት ገደማ በኋላ ነው፤ እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ ምድረ በዳውን አቋርጠው ወደ ተስፋይቱ ምድር በሄዱበት ጊዜ የይሁዳ ነገድ ከፊት ከፊት ይጓዝ ነበር። (ዘኁ. 10:14) ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ተስፋይቱን ምድር በተቆጣጠሩበት ወቅት ከከነአናውያን ጋር ለመዋጋት ይሁዳ ቀድሞ ወጥቷል። (መሳ. 1:1, 2) በተጨማሪም የይሁዳ ዘር የሆነው ዳዊት በዚያ ነገድ ውስጥ በተከታታይ ከተነሱት ነገሥታት መካከል የመጀመሪያው ነበር። ይህ ብቻ ግን አይደለም።
16. በዘፍጥረት 49:10 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (“ያዕቆብ ሊሞት ሲል የተናገረው ትንቢት” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
16 ያዕቆብ የሰው ዘር ዘላለማዊ ገዢ ከይሁዳ ነገድ እንደሚወጣ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 49:10ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) ይህ ገዢ፣ ያዕቆብ “ሴሎ” በማለት የጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አንድ መልአክ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ይሖዋ [አምላክ] የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል” ብሏል። (ሉቃስ 1:32, 33) ኢየሱስ “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ” ተብሎም ተጠርቷል።—ራእይ 5:5
17. ሌሎችን በምንመለከትበት መንገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
17 ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሁዳ አንዳንድ ከባድ ስህተቶችን ቢሠራም ይሖዋ ባርኮታል። ሆኖም የይሁዳ ወንድሞች፣ ይሖዋ ይሁዳን በዚህ መልኩ የባረከው ምን አይቶበት እንደሆነ ግራ ገብቷቸው ይሆን? ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ የይሁዳን መልካም ጎን ተመልክቷል፤ ለዚህም ባርኮታል። እኛስ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? አንድ የእምነት አጋራችን ለየት ያለ መብት ቢያገኝ መጀመሪያ ላይ በደካማ ጎኑ ላይ ለማተኮር እንፈተን ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ በወንድማችን መልካም ባሕርያት እንደተደሰተ ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ የሚያተኩረው በሕዝቦቹ መልካም ጎን ላይ ነው። እኛም ይሖዋን ለመምሰል ጥረት እናድርግ።
18. ታጋሽ መሆን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
18 ከይሁዳ የምናገኘው ሌላኛው ትምህርት የትዕግሥትን አስፈላጊነት ነው። ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን ይጠብቃል። ሆኖም ይህን የሚያደርገው እኛ በጠበቅነው መንገድ ወይም ባሰብነው ጊዜ ላይሆን ይችላል። የይሁዳ ዘሮች የአምላክን ሕዝቦች ወዲያውኑ መምራት አልጀመሩም። ይሖዋ ሌዋዊውን ሙሴን፣ ኤፍሬማዊውን ኢያሱን፣ ቢንያማዊውን ንጉሥ ሳኦልን እንዲሁም ሌሎችን በሾመበት ወቅት የእነሱን አመራር በታማኝነት ደግፈዋል። እኛም በመካከላችን ሆኖ አመራር እንዲሰጥ ይሖዋ የመረጠውን ማንኛውንም ሰው መደገፍ ይኖርብናል።—ዕብ. 6:12
19. ያዕቆብ ሊሞት ሲል ከተናገረው ትንቢት ስለ ይሖዋ ምን ትምህርት አግኝተናል?
19 ያዕቆብ ሊሞት ሲል ከተናገረው ትንቢት እስካሁን ምን ትምህርት አግኝተናል? “አምላክ የሚያየው ሰው በሚያይበት መንገድ [እንዳልሆነ]” ግልጽ ነው። (1 ሳሙ. 16:7) ይሖዋ በጣም ታጋሽና ይቅር ባይ ነው። መጥፎ ምግባርን በቸልታ ባያልፍም ከሕዝቦቹ ፍጽምናን አይጠብቅም። በአንድ ወቅት ከባድ ስህተት የፈጸሙ ሰዎችም እንኳ ከልብ ንስሐ እስከገቡና ትክክል የሆነውን ነገር ወደ ማድረግ እስካዘነበሉ ድረስ ይባርካቸዋል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ያዕቆብ ለቀሪዎቹ ስምንት ልጆቹ የተናገረውን ነገር እንመረምራለን።
መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን