የጥናት ርዕስ 25
መዝሙር 96 የአምላክ መጽሐፍ ውድ ሀብት ነው
ያዕቆብ ሊሞት ሲል ከተናገረው ትንቢት የምናገኘው ትምህርት—ክፍል 2
“ለእያንዳንዳቸውም የሚገባቸውን በረከት ሰጣቸው።”—ዘፍ. 49:28
ዓላማ
ያዕቆብ ሊሞት ሲል ስለ ስምንት ወንዶች ልጆቹ ከተናገረው ትንቢት የምናገኛቸው ተግባራዊ ትምህርቶች።
1. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
የያዕቆብ ወንዶች ልጆች በዙሪያው ተሰብስበው አረጋዊ አባታቸው ሲባርካቸው በጥሞና እያዳመጡ ነው። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ያዕቆብ ለሮቤል፣ ለስምዖን፣ ለሌዊና ለይሁዳ የተናገራቸው ቃላት ልጆቹን አስገርመዋቸው መሆን አለበት። በመሆኑም ለቀሪዎቹ ስምንት ልጆቹ ምን እንደሚላቸው ለመስማት ጓጉተው እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ያዕቆብ ለዛብሎን፣ ለይሳኮር፣ ለዳን፣ ለጋድ፣ ለአሴር፣ ለንፍታሌም፣ ለዮሴፍና ለቢንያም ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።a
ዛብሎን
2. ያዕቆብ ዛብሎንን ምን ብሎ ባርኮታል? በረከቱ ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው? (ዘፍጥረት 49:13) (ሣጥኑንም ተመልከት።)
2 ዘፍጥረት 49:13ን አንብብ። ያዕቆብ የዛብሎን ዘሮች መኖሪያቸው በተስፋይቱ ምድር ሰሜናዊ ክፍል ባለው ባሕር ዳርቻ አካባቢ እንደሚሆን ጠቁሟል። ከ200 ዓመት በኋላ ዛብሎናውያን በገሊላ ባሕርና በሜድትራንያን ባሕር መካከል ርስት ወርሰዋል። ሙሴ “ዛብሎን ሆይ፣ በመውጣትህ ደስ ይበልህ” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ዘዳ. 33:18) ሙሴ የተናገረው ነገር፣ ዛብሎናውያን በሁለት ባሕሮች መካከል መኖራቸው የንግድ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ የዛብሎን ዘሮች ደስተኛ ለመሆን የሚያበቃ ምክንያት ነበራቸው።
3. ደስተኛ ለመሆን ምን ይረዳናል?
3 ምን ትምህርት እናገኛለን? የምንኖረው የትም ይሁን የት ወይም ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ደስተኛ ለመሆን የሚያበቃ ምክንያት አለን። ደስተኛ ሆነን መቀጠል ከፈለግን ባለን ነገር መርካት ይኖርብናል። (መዝ. 16:6፤ 24:5) አንዳንድ ጊዜ፣ ባሉን መልካም ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በሌሉን ነገሮች ላይ ማተኮር ይቀናን ይሆናል። እንግዲያው ያላችሁበት ሁኔታ ያለውን መልካም ጎን ለማስተዋል ጥረት አድርጉ።—ገላ. 6:4
ይሳኮር
4. ያዕቆብ ይሳኮርን ምን ብሎ ባርኮታል? ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው? (ዘፍጥረት 49:14, 15) (ሣጥኑንም ተመልከት።)
4 ዘፍጥረት 49:14, 15ን አንብብ። ያዕቆብ ይሳኮርን ጠንካራ ሠራተኛ በመሆኑ አመስግኖታል፤ እንዲሁም ከባድ ጭነት መሸከም ከሚችል አጥንተ ብርቱ አህያ ጋር አመሳስሎታል። ከዚህም በተጨማሪ ያዕቆብ፣ የይሳኮር ምድር አስደሳች እንደሚሆን ተናግሯል። ከያዕቆብ ትንቢት ጋር በሚስማማ መልኩ የይሳኮር ዘሮች በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ የሚገኝ ለምና ፍሬያማ መሬት ወርሰዋል። (ኢያሱ 19:22) የይሳኮር ዘሮች ምድራቸውን ለማልማት በርትተው እንደሠሩ ምንም ጥያቄ የለውም። ግን ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ለመርዳትም ጠንክረው ይሠሩ ነበር። (1 ነገ. 4:7, 17) የይሳኮር ነገድ፣ የእስራኤል ብሔር ከጠላቶቹ ጋር በሚዋጋበት ወቅት ለመዝመት ፈቃደኛ ነበር። ለምሳሌ በመስፍኑ ባርቅና በነቢዪቱ ዲቦራ ዘመን ይህን አድርጓል።—መሳ. 5:15
5. ጠንካራ ሠራተኞች ለመሆን ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
5 ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ የይሳኮር ነገድ በትጋት ያከናወነውን ሥራ ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው ሁሉ እኛም በእሱ አገልግሎት በትጋት የምናከናውነውን ሥራ ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (መክ. 2:24) ጉባኤውን ለመንከባከብ በትጋት የሚሠሩትን ወንድሞች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (1 ጢሞ. 3:1) እነዚህ ወንድሞች ቃል በቃል በጦርነት ባይካፈሉም የአምላክን ሕዝቦች ከመንፈሳዊ አደጋ ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። (1 ቆሮ. 5:1, 5፤ ይሁዳ 17-23) ከዚህም ሌላ ጉባኤውን የሚያጠናክሩ አበረታች ንግግሮችን ለመዘጋጀትና ለማቅረብ በርትተው ይሠራሉ።—1 ጢሞ. 5:17
ዳን
6. የዳን ነገድ ምን ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር? (ዘፍጥረት 49:17, 18) (ሣጥኑንም ተመልከት።)
6 ዘፍጥረት 49:17, 18ን አንብብ። ያዕቆብ ዳንን፣ እንደ ጦር ፈረስና እንደ ጋላቢው ካሉ ከእሱ እጅግ የሚበልጡ ጠላቶቹ ጋር ለመፋለም ዝግጁ ከሆነ እባብ ጋር አመሳስሎታል። ዳን በእስራኤል ጠላቶች ላይ በድፍረት ጥቃት ይሰነዝራል። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት የዳን ነገድ “የኋላ ደጀን በመሆን” ብሔሩን ከአደጋ ይጠብቅ ነበር። (ዘኁ. 10:25) ዳናውያን የሚያከናውኑትን ሥራ መላው ብሔር በግልጽ ባይመለከተውም እንኳ የተሰጣቸው ኃላፊነት በጣም ወሳኝ ነበር።
7. የተሰጠንን ማንኛውንም ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነት በተመለከተ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?
7 ምን ትምህርት እናገኛለን? ያከናወናችሁትን ሥራ ሌሎች እንዳላስተዋሉት ተሰምቷችሁ ያውቃል? ምናልባትም በስብሰባ አዳራሽ ጽዳት ወይም ጥገና ተካፍላችሁ፣ በወረዳ ወይም በክልል ስብሰባ ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆናችሁ አሊያም ደግሞ ሌላ ኃላፊነት ተወጥታችሁ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ልትመሰገኑ ይገባችኋል። ይሖዋ እሱን ለማገልገል ስትሉ የምታከናውኑትን ማንኛውንም ሥራ እንደሚያስተውልና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ምንጊዜም አስታውሱ። በተለይም ከሌሎች አድናቆት ጠብቃችሁ ሳይሆን ለእሱ ባላችሁ ልባዊ ፍቅር ተነሳስታችሁ ስታገለግሉት በጣም ይደሰታል።—ማቴ. 6:1-4
ጋድ
8. በተስፋይቱ ምድር ውስጥ የጋድ ነገድ ለጥቃት ተጋላጭ የነበረው ለምንድን ነው? (ዘፍጥረት 49:19) (ሣጥኑንም ተመልከት።)
8 ዘፍጥረት 49:19ን አንብብ። ያዕቆብ ጋድን የወራሪዎች ቡድን አደጋ እንዲሚጥልበት ትንቢት ተናግሯል። ከ200 ዓመታት በኋላ የጋድ ነገድ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ መሬት ወረሰ። ይህ መሬት ከጠላት ብሔራት ጋር ይዋሰን ነበር። ይህም ነገዱን ለጥቃት ተጋላጭ አድርጎታል። ሆኖም ጋዳውያን በዚያ አካባቢ ለከብቶቻቸው አመቺ የግጦሽ መሬት ስለነበረ እዚያ ለመኖር መርጠዋል። (ዘኁ. 32:1, 5) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ጋዳውያን ደፋሮች ነበሩ። ከዚህም በላይ ይሖዋ በርስትነት የሰጣቸውን መሬት ከየትኛውም የወራሪዎች ቡድን ለመከላከል እንደሚረዳቸው ተማምነው ነበር። እንዲያውም ሌሎቹ ነገዶች ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያለውን የተስፋይቱን ምድር በተቆጣጠሩበት ወቅት እነሱን ለመርዳት ወታደሮቻቸውን ልከዋል። እነዚህ ወታደሮች ለዓመታት እዚያ ቆይተዋል። (ዘኁ. 32:16-19) ወንዶቹ ቢሄዱም ይሖዋ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን እንደሚጠብቅላቸው ተማምነው ነበር። ይሖዋ ለድፍረታቸውና ላሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ባርኳቸዋል።—ኢያሱ 22:1-4
9. በይሖዋ መታመናችን በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች የሚነካው እንዴት ነው?
9 ምን ትምህርት እናገኛለን? በተፈታታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ይሖዋን ለማገልገል ምንጊዜም በእሱ መታመን ይኖርብናል። (መዝ. 37:3) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለመካፈል፣ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ለማገልገል ወይም ሌሎች ኃላፊነቶችን ለመወጣት ሲሉ መሥዋዕቶችን በመክፈል በይሖዋ እንደሚታመኑ ያሳያሉ። ይህን የሚያደርጉት ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚንከባከባቸው እርግጠኞች ስለሆኑ ነው።—መዝ. 23:1
አሴር
10. አሴራውያን ምን ሳያደርጉ ቀርተዋል? (ዘፍጥረት 49:20) (ሣጥኑንም ተመልከት።)
10 ዘፍጥረት 49:20ን አንብብ። ያዕቆብ የአሴር ነገድ ባለጸጋ እንደሚሆን ተንብዮ ነበር፤ የሆነውም ይኸው ነው። የአሴር ነገድ ርስት እስራኤል ውስጥ ካሉት እጅግ ለም ቦታዎች አንዳንዶቹን ያካትት ነበር። (ዘዳ. 33:24) በተጨማሪም ርስታቸው ሜድትራንያን ባሕርን የሚያዋስን ከመሆኑም ሌላ በብልጽግናው የሚታወቀውን የፊንቄያውያን የንግድ ማዕከል የሆነውን የሲዶና ወደብ ያካትት ነበር። ይሁንና አሴራውያን ከነአናውያንን ከምድሪቱ ሳያባርሩ ቀርተዋል። (መሳ. 1:31, 32) የከነአናውያን መጥፎ ተጽዕኖ ከአሴር ብልጽግና ጋር ተደምሮ አሴራውያን ለንጹሕ አምልኮ የነበራቸው ቅንዓት እንዲቀዘቅዝ አድርጎ ሊሆን ይችላል። መስፍኑ ባርቅ፣ እስራኤላውያን ከከነአናውያን ጋር እንዲዋጉ ጥሪ ሲያቀርብ የአሴር ነገድ ምላሽ አልሰጠም። በዚህም የተነሳ የአሴር ነገድ “በመጊዶ ውኃዎች አጠገብ” በተገኘው ተአምራዊ ድል የመካፈል መብት አጥቷል። (መሳ. 5:19-21) አሴራውያን ባርቅና ዲቦራ በመንፈስ ተመርተው በዘመሩት የድል መዝሙር ውስጥ ያለውን “አሴር በባሕር ዳርቻ ላይ ሥራ ፈቶ ተቀምጧል” የሚለውን ስንኝ ሲሰሙ ተሸማቀው መሆን አለበት።—መሳ. 5:17
11. ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ያለብን ለምንድን ነው?
11 ምን ትምህርት እናገኛለን? ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት እንፈልጋለን። እንዲህ ለማድረግ፣ ዓለም ለቁሳዊ ነገሮች ያለው አመለካከት እንዳይጋባብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። (ምሳሌ 18:11) ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት እናደርጋለን። (መክ. 7:12፤ ዕብ. 13:5) የማያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች ለማሳደድ የምናደርገው ጥረት ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት እንዲቀንስብን አንፈቅድም። ከዚህ ይልቅ፣ ከሁሉ የተሻለውን የተደላደለና አስተማማኝ ሕይወት ወደፊት እንደምናገኝ በመተማመን በአሁኑ ወቅት ከጊዜያችንና ከጉልበታችን ምርጡን ለይሖዋ ለመስጠት ጥረት እናደርጋለን።—መዝ. 4:8
ንፍታሌም
12. ስለ ንፍታሌም የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ሊሆን ይችላል? (ዘፍጥረት 49:21) (ሣጥኑንም ተመልከት።)
12 ዘፍጥረት 49:21ን አንብብ። ያዕቆብ የተናገረው “ያማሩ ቃላት” የሚለው አገላለጽ ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ይናገር የነበረበትን መንገድ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ውጤታማ አስተማሪ በመሆኑ የሚታወቀው ኢየሱስ በንፍታሌም ክልል ውስጥ የምትገኘውን ቅፍርናሆምን ‘የራሱ ከተማ’ አድርጓት ነበር። (ማቴ. 4:13፤ 9:1፤ ዮሐ. 7:46) ኢሳይያስ ኢየሱስን አስመልክቶ ትንቢት ሲናገር የዛብሎንና የንፍታሌም ሰዎች “ታላቅ ብርሃን” እንደሚያዩ ገልጿል። (ኢሳ. 9:1, 2) ኢየሱስ “ለሁሉም ዓይነት ሰው ብርሃን የሚሰጠው እውነተኛው ብርሃን” መሆኑን ባስተማረው ትምህርት አሳይቷል።—ዮሐ. 1:9
13. በንግግራችን ይሖዋን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?
13 ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ የምንናገረውን ነገርና የምንናገርበትን መንገድ በቁም ነገር ይመለከተዋል። ይሖዋን የሚያስደስቱ “ያማሩ ቃላት” መናገር የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ እውነቱን እንናገራለን። (መዝ. 15:1, 2) ለማመስገን ፈጣኖች በመሆን እንዲሁም ከመተቸትና ከማማረር በመቆጠብ በንግግራችን ሌሎችን ማነጽ እንችላለን። (ኤፌ. 4:29) በተጨማሪም ከሌሎች ጋር ጭውውት የመጀመር ክህሎታችንን ለማሳደግ ግብ ማውጣት እንችላለን፤ ይህም ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ሊከፍትልን ይችላል።
ዮሴፍ
14. ያዕቆብ ስለ ዮሴፍ የተናገረው ትንቢት እንዴት ፍጻሜውን እንዳገኘ አብራራ። (ዘፍጥረት 49:22, 26) (ሣጥኑንም ተመልከት።)
14 ዘፍጥረት 49:22, 26ን አንብብ። ያዕቆብ በዮሴፍ በጣም እንደሚኮራበት ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ ዮሴፍን ‘ከወንድሞቹ መካከል ነጥሎ በማውጣት’ ለልዩ ዓላማ መርጦታል። ያዕቆብ ዮሴፍን “ፍሬያማ የሆነ ዛፍ ቀንበጥ” በማለት ጠርቶታል። ዛፉ ያዕቆብን የሚያመለክት ሲሆን ዮሴፍ ደግሞ የዛፉ ቀንበጥ ነው። ዮሴፍ የያዕቆብ ተወዳጅ ሚስት የነበረችው የራሔል የበኩር ልጅ ነው። ያዕቆብ፣ ከሚስቱ ከሊያ የወለደው የበኩር ልጁ ሮቤል ያጣውን ሁለት ድርሻ ዮሴፍ እንደሚያገኝ ተናግሯል። (ዘፍ. 48:5, 6፤ 1 ዜና 5:1, 2) የዮሴፍ ልጆች የሆኑት የኤፍሬምና የምናሴ ዘሮች እንደ ሁለት ነገድ ተቆጥረው ርስት በወረሱበት ጊዜ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል።—ዘፍ. 49:25፤ ኢያሱ 14:4
15. ዮሴፍ ግፍ ሲፈጸምበት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?
15 በተጨማሪም ያዕቆብ ስለ ዮሴፍ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ቀስተኞች [ቀስታቸውን] ወረወሩበት፤ ለእሱም ጥላቻ አደረባቸው።” (ዘፍ. 49:23) እነዚህ ቀስተኞች፣ በምቀኝነት ተነሳስተው ግፍ የፈጸሙበትንና ለብዙ መከራ የዳረጉትን ወንድሞቹን ያመለክታሉ። ያም ቢሆን ዮሴፍ በወንድሞቹ ላይ ቂም አልያዘባቸውም፤ በይሖዋም ላይ አልተመረረም። ያዕቆብ እንደገለጸው “[ዮሴፍ] ቀስቱ ከቦታው ንቅንቅ አላለም፤ እጆቹም ብርቱና ቀልጣፋ ናቸው።” (ዘፍ. 49:24) ዮሴፍ ባጋጠሙት ፈተናዎች ሁሉ በይሖዋ ታምኗል። በተጨማሪም ወንድሞቹን ይቅር ማለት ብቻ ሳይሆን በደግነት ይዟቸዋል። (ዘፍ. 47:11, 12) ዮሴፍ፣ ያጋጠሙት ፈተናዎች እንዲያጠሩት ፈቅዷል። (መዝ. 105:17-19) በመሆኑም ይሖዋ አስደናቂ በሆነ መንገድ ሊጠቀምበት ችሏል።
16. ለፈተናዎች ምላሽ በምንሰጥበት መንገድ ዮሴፍን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
16 ምን ትምህርት እናገኛለን? ፈተናዎች ከይሖዋም ሆነ ከእምነት አጋሮቻችን እንዲያርቁን ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። ይሖዋ የሚደርሱብንን የእምነት ፈተናዎች እኛን ለማሠልጠን ሊጠቀምባቸው እንደሚችል አስታውሱ። (ዕብ. 12:7 ግርጌ) እንዲህ ያለው ሥልጠና፣ እንደ ምሕረትና ይቅር ባይነት ያሉትን ክርስቲያናዊ ባሕርያት እንድናዳብርና እንድናሻሽል ሊረዳን ይችላል። (ዕብ. 12:11) ይሖዋ ልክ ለዮሴፍ እንዳደረገው እኛንም ለጽናታችን ወሮታ ይከፍለናል።
ቢንያም
17. ያዕቆብ ስለ ቢንያም የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ዘፍጥረት 49:27) (ሣጥኑንም ተመልከት።)
17 ዘፍጥረት 49:27ን አንብብ። ያዕቆብ፣ ቢንያማውያን ልክ እንደ ተኩላ ኃያል ተዋጊዎች እንደሚሆኑ ትንቢት ተናግሯል። (መሳ. 20:15, 16፤ 1 ዜና 12:2) በእስራኤል መንግሥት ታሪክ ውስጥ ገና “ጠዋት ላይ” ቢንያማዊው ሳኦል የእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ ሆኖ ተሹሞ ነበር። ሳኦል ከፍልስጤማውያን ጋር ባደረገው ፍልሚያ ኃያል ተዋጊ መሆኑን አሳይቷል። (1 ሳሙ. 9:15-17, 21) በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ “ምሽት ላይ” ደግሞ ቢንያማውያን የሆኑት ንግሥት አስቴርና ጠቅላይ ሚኒስትር መርዶክዮስ እስራኤላውያንን በፋርስ መንግሥት ከመጥፋት ታድገዋቸዋል።—አስ. 2:5-7፤ 8:3፤ 10:3
18. የቢንያማውያንን ታማኝነት መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
18 ምን ትምህርት እናገኛለን? ቢንያማውያን የእነሱ ወገን የሆነው ሳኦል ንጉሥ በመሆኑ በጣም ተደስተው እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ይሁንና ይሖዋ ንግሥናውን ከይሁዳ ነገድ ወደሆነው ወደ ዳዊት ባስተላለፈበት ወቅት ቢንያማውያን ውሎ አድሮ ለውጡን ደግፈዋል። (2 ሳሙ. 3:17-19) ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ሌሎቹ ነገዶች ሲያምጹ ቢንያማውያን በታማኝነት ከይሁዳ ነገድና ይሖዋ ከሾመው ንጉሥ ጎን ቆመዋል። (1 ነገ. 11:31, 32፤ 12:19, 21) እኛም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹን ለመምራት እየተጠቀመባቸው ያሉትን ወንድሞች በታማኝነት መደገፍ ይኖርብናል።—1 ተሰ. 5:12
19. ያዕቆብ ሊሞት ሲል ከተናገረው ትንቢት ምን ጥቅም እናገኛለን?
19 በእርግጥም፣ ያዕቆብ ሊሞት ሲል ከተናገረው ትንቢት ብዙ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘበትን መንገድ መመርመራችን በይሖዋ ትንቢታዊ ቃል ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። በተጨማሪም የያዕቆብ ልጆች ስለተሰጣቸው በረከት ማጥናታችን ይሖዋን ማስደሰት የምንችልበትን መንገድ ይበልጥ ለመገንዘብ ይረዳናል።
መዝሙር 128 እስከ መጨረሻው መጽናት
a ያዕቆብ ሮቤልን፣ ስምዖንን፣ ሌዊንና ይሁዳን ከትልቁ ወደ ትንሹ ከባረከ በኋላ የቀሩትን ልጆቹን የባረከው በዕድሜ ቅደም ተከተል አይደለም።