የጥናት ርዕስ 30
መዝሙር 97 የአምላክ ቃል ሕይወት ነው
ከመሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አሁንም መማር ትችላለህ?
“ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች የምታውቁና በተማራችሁት እውነት ጸንታችሁ የቆማችሁ ብትሆኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ እናንተን ከማሳሰብ ወደኋላ አልልም።”—2 ጴጥ. 1:12
ዓላማ
መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ከተማርን ዓመታት ቢያልፉም ትምህርቶቹ አሁንም የሚጠቅሙን እንዴት ነው?
1. እውነትን ስትሰማ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የጠቀሙህ እንዴት ነው?
መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ሕይወታችንን ለውጠውታል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ስናውቅ የእሱ ወዳጅ ለመሆን የመጀመሪያውን እርምጃ ወሰድን። (ኢሳ. 42:8) ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ስንማር ‘በሞት የተለዩን ቤተሰቦቻችን እየተሠቃዩ ይሆን?’ ብለን መጨነቃችንን አቆምን። (መክ. 9:10) በተጨማሪም አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ ቃል እንደገባ ስናውቅ ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጨነቅ አቆምን። በሕይወት የምንኖረው ለአጭር ጊዜ፣ ማለትም ለ70 ወይም ለ80 ዓመት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም እንደሆነ እርግጠኞች ሆንን።—መዝ. 37:29፤ 90:10
2. ሁለተኛ ጴጥሮስ 1:12, 13 የጎለመሱ ክርስቲያኖችም እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች ጥቅም ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያሳየው እንዴት ነው?
2 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች ፈጽሞ አቅልለን ልንመለከታቸው አይገባም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ሁለተኛውን ደብዳቤውን የጻፈላቸው ክርስቲያኖች ‘በእውነት ጸንተው የቆሙ’ ነበሩ። (2 ጴጥሮስ 1:12, 13ን አንብብ።) አሁን ግን ጉባኤው መንፈሳዊ አደጋ ተደቅኖበታል፤ ከአደጋዎቹ መካከል የሐሰት አስተማሪዎችና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ይገኙበታል። (2 ጴጥ. 2:1-3) ጴጥሮስ ወንድሞቹና እህቶቹ እነዚህን አደጋዎች መቋቋም እንዲችሉ ሊያጠናክራቸው ፈልጎ ነበር። በመሆኑም ቀደም ሲል የተማሯቸውን አንዳንድ ትምህርቶች አስታወሳቸው። እነዚህ ትምህርቶች እስከ መጨረሻው ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ ይረዷቸዋል።
3. ሁሉም ክርስቲያኖች መሠረታዊ በሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ማሰላሰላቸውን መቀጠል ያለባቸው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
3 በመንፈሳዊ እየጎለመስን ስንሄድ መሠረታዊ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አዳዲስ ትምህርቶችን ማግኘት እንችል ይሆናል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላት አንዲት እናትና ወጣት ልጇ ተመሳሳይ ግብዓት ተጠቅመው ምግብ ሊያበስሉ ይችላሉ። ሆኖም እናትየዋ በጊዜ ሂደት እነዚያኑ ግብዓቶች በተሻለ መንገድ በመጠቀም አዳዲስ ምግቦችን መሥራት ተምራለች። በተመሳሳይም ለረጅም ጊዜ ይሖዋን ያገለገሉ ክርስቲያኖችና አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን የሚመለከቱበት መንገድ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ከተጠመቅንበት ጊዜ ወዲህ ያለንበት ሁኔታም ሆነ የአገልግሎት መብታችን ተቀይሮ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። ከረጅም ጊዜ በፊት የተማርናቸውን ትምህርቶች አሁን ካለንበት ሁኔታ አንጻር ስናያቸው አዳዲስና ተግባራዊ ትምህርቶች ልናገኝ እንችላለን። የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከሦስት መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ምን ሊማሩ እንደሚችሉ እስቲ እንመልከት።
ይሖዋ ፈጣሪ ነው
4. ይሖዋ ፈጣሪ መሆኑን ማወቃችን የጠቀመን እንዴት ነው?
4 “ሁሉን ነገር የሠራው . . . አምላክ ነው።” (ዕብ. 3:4) ፕላኔታችንን እና በውስጧ ያሉትን ፍጥረታት የሠራው በጥበቡና በኃይሉ ተወዳዳሪ የሌለው ፈጣሪ መሆኑን እናውቃለን። የሠራን እሱ ስለሆነ ጠንቅቆ ያውቀናል። ከዚህም በተጨማሪ ያስብልናል። ለእኛ የሚበጀንን ያውቃል። ይህን ቀላል እውነት ማለትም ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደሆነ ማወቃችን በእጅጉ ጠቅሞናል፤ ሕይወታችን ትርጉምና ዓላማ እንዲኖረው አድርጓል።
5. ትሕትና እንድናዳብር የሚረዳን የትኛው እውነት ነው? (ኢሳይያስ 45:9-12)
5 ይሖዋ ፈጣሪ ነው የሚለው እውነት ትሕትና ያስተምረናል። ኢዮብ በራሱና በሌሎች ሰዎች ላይ ከልክ በላይ ባተኮረ ጊዜ ይሖዋ፣ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ መሆኑን አስታውሶታል። (ኢዮብ 38:1-4) ይህም ኢዮብ የአምላክ መንገድ ከሰዎች መንገድ እጅግ የላቀ እንደሆነ እንዲገነዘብ ረድቶታል። ከጊዜ በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ “ሸክላ፣ ሠሪውን ‘የምትሠራው ምንድን ነው?’ ይለዋል?” በማለት ጽፏል።—ኢሳይያስ 45:9-12ን አንብብ።
6. ፈጣሪያችን ይሖዋ ባለው ታላቅነት ላይ ማሰላሰላችን እንዴት ሊጠቅመን ይችላል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
6 አንድ ክርስቲያን ተሞክሮ እያዳበረ ሲሄድ መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋና ወደ ቃሉ ዘወር ከማለት ይልቅ ከልክ በላይ በራሱ አመለካከት መተማመን ሊጀምር ይችላል። (ኢዮብ 37:23, 24) ሆኖም ፈጣሪው ባለው ወደር የለሽ ጥበብና ታላቅነት ላይ ቢያሰላስል ምን ውጤት ይኖረዋል? (ኢሳ. 40:22፤ 55:8, 9) ይህ መሠረታዊ እውነት ትሑት ሆኖ እንዲቀጥልና ለራሱ አመለካከት ተገቢውን ቦታ እንዲሰጥ ይረዳዋል።
ለራሳችን አመለካከት ተገቢውን ቦታ እንድንሰጥ ምን ይረዳናል? (አንቀጽ 6ን ተመልከት)d
7. ራሄላ አንድን ድርጅታዊ ማስተካከያ ለመቀበል የረዳት ምንድን ነው?
7 በስሎቬንያ የምትኖረው ራሄላ ስለ ፈጣሪዋ ማሰላሰሏ ድርጅታዊ ማስተካከያዎችን ለመቀበል እንደረዳት ገልጻለች። እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች፦ “አመራር የሚሰጡ ወንድሞች የሚያደርጉትን ውሳኔ መቀበል ቀላል የማይሆንልኝ ጊዜ አለ። ለምሳሌ የ2023 የበላይ አካሉ ሪፖርት ቁጥር 8ን ከተመለከትኩ በኋላም ጺሙን ያሳደገ ወንድም ንግግር ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይ ደንግጬ ነበር። ስለዚህ ይህን ለውጥ ለመልመድ እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ።” ራሄላ ይሖዋ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ድርጅቱን በትክክለኛው መንገድ የመምራት ችሎታ እንዳለው አስታወሰች። አንተም አንድን አዲስ ግንዛቤ ወይም አዲስ መመሪያ መቀበል ከከበደህ፣ ትሑት በመሆን ፈጣሪያችን ባለው ወደር የለሽ ጥበብና ኃይል ላይ ለምን አታሰላስልም?—ሮም 11:33-36
አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት
8. አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ማወቃችን የጠቀመን እንዴት ነው?
8 አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት ያልቻሉ አንዳንዶች በአምላክ ላይ ተቆጥተዋል፤ ወይም አምላክ የለም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። (ምሳሌ 19:3) አንተ ግን የመከራ መንስኤ ይሖዋ ሳይሆን የወረስነው ኃጢአትና አለፍጽምና መሆኑን ተምረሃል። በተጨማሪም ይሖዋ እስካሁን የታገሠው ለምን እንደሆነ ተምረሃል። እንዲህ ያደረገው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲያውቁትና መከራን በዘላቂነት ስለሚያስወግድበት መንገድ እንዲማሩ ብሎ ነው። (2 ጴጥ. 3:9, 15) እነዚህ እውነቶች አጽናንተውሃል፤ እንዲሁም ወደ እሱ ይበልጥ እንድትቀርብ ረድተውሃል።
9. ይሖዋ መከራ እንዲደርስ የፈቀደበትን ምክንያት ማስታወሳችን የሚጠቅመን መቼ ነው?
9 ይሖዋ መከራን እስኪያስወግድ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ እንዳለብን እንገነዘባለን። ይሁንና በእኛ ወይም በምንወዳቸው ሰዎች ላይ መከራ፣ ግፍ ወይም ሐዘን ሲደርስ ይሖዋ ቶሎ እርምጃ አለመውሰዱ ያሳስበን ይሆናል። (ዕን. 1:2, 3) በዚህ ጊዜ፣ ይሖዋ ጻድቃን መከራ እንዲደርስባቸው የፈቀደው ለምን እንደሆነ ማሰላሰላችን ጥበብ ነው።a (መዝ. 34:19) በተጨማሪም መከራን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ባለው ዓላማ ላይ ማሰላሰል እንችላለን።
10. አን የእናቷ ሞት ያስከተለባትን ሐዘን ለመቋቋም የረዳት ምንድን ነው?
10 ስለ መከራ እውነቱን ማወቃችን እንድንጸና ሊረዳን ይችላል። በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በምትገኘው በማዮት ደሴት ላይ የምትኖረው አን እንዲህ ብላለች፦ “ከተወሰኑ ዓመታት በፊት እናቴ በሞት ስትለየኝ በጣም አዝኜ ነበር። ሆኖም ለመከራ ተጠያቂው ይሖዋ እንዳልሆነ ዘወትር ለማሰብ እሞክራለሁ። ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት መከራ ለማስወገድና በሞት ያጣናቸውን ሰዎች ለማስነሳት ይጓጓል። በእነዚህ እውነቶች ላይ ማሰላሰሌ የአእምሮ ሰላም አስገኝቶልኛል፤ የሚሰማኝ ሰላም አንዳንዴ እኔንም ያስገርመኛል።”
11. ይሖዋ መከራ እንዲደርስ የፈቀደበትን ምክንያት ማወቃችን መስበካችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን እንዴት ነው?
11 ይሖዋ መከራ እንዲደርስ የፈቀደበትን ምክንያት ማወቃችን መስበካችንን እንድንቀጥል ሊያነሳሳን ይችላል። ጴጥሮስ የይሖዋ ትዕግሥት ንስሐ ለሚገቡ ሰዎች መዳን እንደሚያስገኝ ከገለጸ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል!” (2 ጴጥ. 3:11) ‘ለአምላክ ያደርን መሆናችንን ከሚያሳዩት ተግባሮች’ መካከል የስብከቱ ሥራችን ይገኝበታል። እንደ አባታችን እኛም ሰዎችን እንወዳለን። ጽድቅ በሰፈነበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ እንፈልጋለን። ይሖዋ ታጋሽ በመሆን በክልልህ ውስጥ ያሉ ሰዎች እሱን ማገልገል የሚችሉበት አጋጣሚ እየሰጣቸው ነው። ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራትና መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ስለ እሱ እንዲማሩ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—1 ቆሮ. 3:9
የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ ነው
12. የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ መሆኑን ማወቃችን የጠቀመን እንዴት ነው?
12 መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ሰዎች ምን ዓይነት ባሕርይ እንደሚኖራቸው በትክክል ይገልጻል። (2 ጢሞ. 3:1-5) ይህ ትንቢት እየተፈጸመ እንዳለ ለማወቅ ዙሪያችንን መመልከት በቂ ነው። የሰዎች ባሕርይ እየተባባሰ መሄዱን ስናይ የአምላክ ቃል እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ይበልጥ እርግጠኞች እንሆናለን።—2 ጢሞ. 3:13-15
13. ኢየሱስ በሉቃስ 12:15-21 ላይ በተናገረው ምሳሌ መሠረት ራሳችንን ምን ብለን ልንጠይቅ ይገባል?
13 የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደሆነ ማወቃችን የጥድፊያ ስሜት እንዲኖረን ይረዳናል። ኢየሱስ በሉቃስ 12:15-21 ላይ የተናገረው ምሳሌ ስለ ጥድፊያ ስሜት ምን ትምህርት እንደሚሰጠን እንመልከት። (ጥቅሱን አንብብ።) ሀብታሙ ሰው ‘ማስተዋል የጎደለው’ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? ሰውየው ባለጸጋ ስለነበረ ሳይሆን ለትክክለኛው ነገር ቅድሚያ ስላልሰጠ ነው። ‘ለራሱ ሀብት ቢያከማችም በአምላክ ዘንድ ግን ሀብታም አልነበረም።’ ጉዳዩን በጣም አጣዳፊ ያደረገው ምንድን ነው? አምላክ ሰውየውን “በዚህች ሌሊት ሕይወትህን ይፈልጓታል” ብሎታል። እኛም ወደዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየተቃረብን ስንሄድ ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ግቦቼ የጥድፊያ ስሜት እንዳለኝ ያሳያሉ? ልጆቼን እንዲያወጡ የማበረታታቸው ግቦችስ? ጉልበቴን፣ ጊዜዬንና ገንዘቤን በዋነኝነት የምጠቀምበት ለራሴ ሀብት ለማከማቸት ነው ወይስ በሰማይ ሀብት ለማከማቸት?’
14. የሚኪ ተሞክሮ እንደሚያሳየው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደምንኖር በሚያሳየው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ላይ ማሰላሰላችን ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው?
14 በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደምንኖር ስለሚያሳዩት ማስረጃዎች ስናስብ ለሕይወት ያለን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ሊቀየር ይችላል። ሚኪ የተባለች እህት ያጋጠማት ይኸው ነው። እንዲህ ብላለች፦ “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ባጠናቀቅኩበት ወቅት ስለ እንስሳት የማጥናት ፍላጎት ነበረኝ። በሌላ በኩል ደግሞ የዘወትር አቅኚ የመሆንና ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ የማገልገል ግብ ነበረኝ። የጎለመሱ ጓደኞቼ ያንን ሥራ እየሠራሁ መንፈሳዊ ግቦቼ ላይ በእርግጥ መድረስ እችል እንደሆነ ቆም ብዬ እንዳስብበት አበረታቱኝ። ይህ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚያበቃ አስታወሱኝ። በሌላ በኩል ደግሞ በአዲሱ ዓለም ለዘላለም ስለ እንስሳት የፈለግኩትን ያህል ማጥናት እችላለሁ። ስለዚህ ጥሩ ሙያ የሚያስተምር አጭር ኮርስ ለመውሰድ ወሰንኩ። ይህም በዘወትር አቅኚነት ለማገልገል የሚያስችል ሥራ እንድቀጠር ረድቶኛል። በኋላ ላይ ደግሞ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ ኢኳዶር መሄድ ችያለሁ።” ሚኪና ባለቤቷ በአሁኑ ጊዜ በዚያች አገር በወረዳ ሥራ እየተካፈሉ ነው።
15. ሰዎች ለምሥራቹ የሚሰጡት ምላሽ ሊቀየር የሚችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
15 ሰዎች መጀመሪያ ላይ ምሥራቹን ለመቀበል ፈቃደኞች ባይሆኑ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ሰዎች ሊቀየሩ ይችላሉ። የኢየሱስ ወንድም የሆነውን የያዕቆብን ምሳሌ እንመልከት። ያዕቆብ ኢየሱስን ከልጅነቱ ጀምሮ ያውቀዋል፤ እንዲሁም የመሲሕነት ተልእኮውን ሲወጣና ከሌሎች ሰዎች ሁሉ በላቀ መንገድ ሲያስተምር ተመልክቷል። ሆኖም ለበርካታ ዓመታት ያዕቆብ የኢየሱስ ተከታይ አልሆነም። ያዕቆብ ደቀ መዝሙር የሆነው ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ነው። እንዲያውም ቀናተኛ ደቀ መዝሙር ሆኗል!b (ዮሐ. 7:5፤ ገላ. 2:9) ለምሥራቹ ፍላጎት ላላሳዩ ዘመዶቻችን መስበካችንን መቀጠላችን እንዲሁም የመንግሥቱን መልእክት ላልተቀበሉ ሰዎች ደጋግመን መስበካችን አስፈላጊ ነው። የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደሆነ አስታውስ፤ በመሆኑም የስብከቱ ሥራችን አጣዳፊ ነው። ዛሬ የምንነግራቸው ነገር ከጊዜ በኋላ፣ ምናልባትም ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ ልባቸውን ሊነካው ይችላል።c
አማኝ ባልሆኑ ዘመዶቻችን ላይ ተስፋ እንዳንቆርጥ ምን ሊያነሳሳን ይችላል? (አንቀጽ 15ን ተመልከት)e
ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ምንጊዜም አመስጋኝ ሁን
16. ከይሖዋ ማሳሰቢያዎች የተጠቀምከው እንዴት ነው? (“ሌሎችን ለመርዳት ተጠቀምባቸው” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
16 ከምናገኘው መንፈሳዊ ምግብ ውስጥ አንዳንዱ የሚዘጋጀው መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ሰምተው ለማያውቁ ሰዎች ነው። ለምሳሌ በየሳምንቱ የሚቀርቡልን የሕዝብ ንግግሮች፣ jw.org ላይ የሚገኙ አንዳንድ ርዕሶችና ቪዲዮዎች እንዲሁም ለሕዝብ የሚሰራጩ መጽሔቶቻችን በዋነኝነት የሚዘጋጁት የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ሰዎች ነው። ያም ቢሆን እነዚህ ትምህርቶች ለእኛም ማሳሰቢያ ይሆኑልናል። ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ያሳድጉልናል፤ በቃሉ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል፤ እንዲሁም መሠረታዊ እውነቶችን ለሌሎች ስናስተምር ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ይረዱናል።—መዝ. 19:7
17. በመሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ላይ ማሰላሰል የሚኖርብን በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው?
17 እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ያለን ግንዛቤ ሲጠራ እንደሰታለን። ሆኖም መጀመሪያውኑ ወደ እውነት እንድንመጣ ላነሳሱን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችም በጣም አመስጋኝ ነን። ለይሖዋ ድርጅት መመሪያ ከመገዛት ይልቅ በራሳችን አመለካከት ለመመራት ስንፈተን ድርጅቱን እየመራ ያለው በኃይሉና በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለው ፈጣሪያችን መሆኑን ማስታወሳችን ትሑት እንድንሆን ይረዳናል። በእኛ ወይም በምንወዳቸው ሰዎች ላይ መከራ ሲደርስ ታጋሾች መሆንና ይሖዋ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ማሰላሰል ይኖርብናል። በተጨማሪም ጊዜያችንንና ገንዘባችንን የምንጠቀመው እንዴት እንደሆነ ስንወስን፣ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደሆነና የጥድፊያ ስሜት ሊኖረን እንደሚገባ ማስታወስ ይኖርብናል። እንግዲያው ከይሖዋ ማሳሰቢያዎች ጥንካሬ፣ ማበረታቻና ጥበብ ማግኘታችንን እንቀጥል።
መዝሙር 95 ብርሃኑ እየደመቀ ነው
a በግንቦት 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 21-25 ላይ የሚገኘውን “መከራና ሥቃይ ሁሉ በቅርቡ ይወገዳል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c በግንቦት 2024 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-13 ላይ የሚገኘውን “ይሖዋ ወደፊት ስለሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ምን እናውቃለን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ሽማግሌ ያቀረበው ሐሳብ በሽማግሌዎች አካል ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ሽማግሌው በኋላ ላይ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ሲመለከት ለራሱ አመለካከት ተገቢውን ቦታ ለመስጠት ይነሳሳል።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት የይሖዋ ምሥክር በግል ጥናቷ ላይ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ መሆኑን የሚያሳየውን ማስረጃ ትመረምራለች። ይህም ለእህቷ ደውላ እንድትመሠክርላት ያነሳሳታል።