የጥናት ርዕስ 39
መዝሙር 54 “መንገዱ ይህ ነው”
“ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ
“ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች ሆኑ።”—ሥራ 13:48
ዓላማ
ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑና በስብሰባዎቻችን ላይ እንዲገኙ መጋበዝ ያለብን መቼ ነው?
1. የተለያዩ ሰዎች ለምሥራቹ ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ? (የሐዋርያት ሥራ 13:47, 48፤ 16:14, 15)
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን ልክ እንደሰሙ እውነትን ተቀብለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 13:47, 48፤ 16:14, 15ን አንብብ።) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ምሥራቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰሙ በጣም ይደሰታሉ። የመንግሥቱን መልእክት መጀመሪያ ላይ ሲሰሙ ፍላጎት ያልነበራቸው ሰዎች እንኳ በኋላ ላይ ልባቸውን ወለል አድርገው ከፍተው ሊቀበሉት ይችላሉ። ታዲያ በአገልግሎታችን ላይ “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ስናገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
2. ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራችን ከግብርና ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
2 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራችን ከግብርና ጋር ይመሳሰላል። አንድ ገበሬ የአንድ ዛፍ ፍሬ መድረሱን ካየ እርሻው ውስጥ እየዘራ ወይም እየኮተኮተ ቢሆንም እንኳ የደረሱትን ፍሬዎች ለመሰብሰብ ቅድሚያ ይሰጣል። በተመሳሳይም፣ መልእክታችንን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ሰው ካገኘን በተቻለ ፍጥነት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን ልንረዳው እንፈልጋለን። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ምሥራቹን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆኑ ሰዎችን ፍላጎት መኮትኮታችንን እንቀጥላለን። (ዮሐ. 4:35, 36) አስተዋይ መሆናችን ለአድማጮቻችን የተሻለውን አቀራረብ ለመምረጥ ይረዳናል። ለምሥራቹ በጎ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ስናገኝ በመጀመሪያው ውይይታችን ወቅት ምን ማድረግ እንደምንችል እስቲ እንመልከት። እንዲህ ያሉ ሰዎች እድገት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነም እንመለከታለን።
ሰዎች ለመልእክቱ በጎ ምላሽ ሲሰጡ
3. በአገልግሎት ላይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስናገኝ ምን ማድረግ እንችላለን? (1 ቆሮንቶስ 9:26)
3 በአገልግሎት ላይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስናገኝ ወዲያውኑ ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ ልንረዳቸው እንፈልጋለን። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን በመጀመሪያው ውይይት ወቅት ጥናት እንዲጀምሩና በስብሰባ ላይ እንዲገኙ ከመጋበዝ ወደኋላ ማለት የለብንም።—1 ቆሮንቶስ 9:26ን አንብብ።
4. ሰዎችን ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር እንደሚቻል የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
4 ጥናት እንዲጀምሩ መጋበዝ። በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው አንዳንድ ሰዎች ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ዝግጁ ናቸው። ለምሳሌ በካናዳ የምትኖር አንዲት ወጣት ሐሙስ ቀን ላይ ወደ አንድ የጽሑፍ ጋሪ ቀርባ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ወሰደች። ጋሪው ጋ የነበረችው እህት፣ ወጣቷ ብሮሹሩን መውሰድ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ማጥናት እንደምትችል ነገረቻት። ወጣቷ ፍላጎት አሳየች፤ ከዚያም ስልክ ተለዋወጡ። በዚያው ቀን ወጣቷ ለእህት የጽሑፍ መልእክት በመላክ መቼ ጥናቱን መጀመር እንደሚችሉ ጠየቀቻት። እህትም ቅዳሜ ወይም እሁድ መምጣት እንደምትችል ነገረቻት። በዚህ ጊዜ ወጣቷ “ነገ ብንገናኝስ? ነገ ነፃ ነኝ” አለቻት። በመሆኑም ዓርብ ዕለት ጥናት ጀመረች። ወጣቷ በዚያው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኘች። ፈጣን እድገት ማድረጓንም ቀጠለች።
5. አስተዋይ መሆናችን ሰዎች ጥናት እንዲጀምሩ ስንጋብዝ የሚረዳን እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
5 እርግጥ ነው፣ መልእክታችንን የሚሰሙ ሰዎች በሙሉ እንደዚህች ወጣት ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ ብለን አንጠብቅም። ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በተያያዘ ፍላጎታቸውን መኮትኮት ሊኖርብን ይችላል። በመጀመሪያ፣ የግለሰቡን ትኩረት የሚስብ ርዕሰ ጉዳይ መርጠን ውይይት መጀመር ሊያስፈልገን ይችላል። ያም ቢሆን፣ አዎንታዊ አመለካከት ከያዝን እንዲሁም ለግለሰቡ አሳቢነት ማሳየታችንን ከቀጠልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥናት ማስጀመር እንችል ይሆናል። ሰዎች ጥናት እንዲጀምሩ ለመጋበዝ ምን ማለት እንችላለን? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር ረገድ ውጤታማ ለሆኑ የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች ይህ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
ለእነዚህ ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይበልጥ አጓጊ እንዲሆንላቸው ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 5ን ተመልከት)a
6. ፍላጎት ካሳየ ሰው ጋር ውይይት መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
6 ጥናት ስለማስጀመር ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አስፋፊዎችና አቅኚዎች በአንዳንድ አገሮች “ጥናት፣” “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት” ወይም “አስተምርሃለሁ” እንደሚሉት ያሉ አገላለጾችን አለመጠቀም የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ ይልቅ “መወያየት፣” “መነጋገር” ወይም “መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር” እንደሚሉት ያሉ አገላለጾችን መጠቀም የተሻለ እንደሆነ ጠቁመዋል። ሰዎቹ ውይይቱን ለመቀጠል እንዲነሳሱ እንዲህ ማለት እንችላለን፦ “መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ለሚያሳስቡን ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል” ወይም “መጽሐፍ ቅዱስ የሃይማኖት መጽሐፍ ብቻ አይደለም፤ ለሕይወታችን የሚጠቅም ምክር ይዞልናል።” ቀጥሎም እንዲህ ልንል እንችላለን፦ “ብዙ ጊዜ አይወስድም፤ በ10 ወይም በ15 ደቂቃ ውስጥ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ይቻላል።” ግዴታ ውስጥ እንደገቡ እንዳይሰማቸው “ቀጠሮ” ወይም “በየሳምንቱ” የሚሉትን ቃላት አለመጠቀም ጥሩ ሊሆን ይችላል።
7. አንዳንዶች እውነትን እንዳገኙ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘቡት መቼ ነው? (1 ቆሮንቶስ 14:23-25)
7 ስብሰባ እንዲመጡ መጋበዝ። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው፣ በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እውነትን እንዳገኙ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘቡት በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ በተገኙበት ወቅት ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:23-25ን አንብብ።) ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አብዛኞቹ አዳዲስ ሰዎች በስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመሩ በኋላ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት ያደርጋሉ። ታዲያ ልንጋብዛቸው የሚገባው መቼ ነው? ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ላይ እንዲህ ያለ ግብዣ ይዟል። ሆኖም እነሱን ለመጋበዝ እዚያ ምዕራፍ ላይ እስክንደርስ መጠበቅ አያስፈልገንም። ልክ የመጀመሪያውን ውይይት ስናደርግ በሳምንቱ መጨረሻ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ልንጋብዛቸው እንችላለን። ምናልባትም የሕዝብ ንግግሩን ርዕስ ወይም በዚያ ሳምንት በሚጠናው መጠበቂያ ግንብ ላይ ያለ አንድ ሐሳብ ልንጠቅስላቸው እንችላለን።
8. አንድ ሰው በስብሰባ ላይ እንዲገኝ ስንጋብዝ ስለ ስብሰባችን ምን ልንነግረው እንችላለን? (ኢሳይያስ 54:13)
8 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ወደ ስብሰባዎቻችን ስንጋብዝ ስብሰባዎቻችን እነሱ ከሚያውቋቸው ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች የሚለዩት እንዴት እንደሆነ ልናብራራላቸው ይገባል። አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ በተገኘችበት ወቅት አስጠኚዋን “ጥናቱን የሚመራው ሰው የሁሉንም ሰው ስም ያውቃል ማለት ነው?” ብላ ጠየቀቻት። እህትም የቤተሰባችንን አባላት ስም እንደምናውቀው ሁሉ፣ ሁላችንም በጉባኤያችን ያሉ ወንድሞችና እህቶችን ስም ለማወቅ ጥረት እንደምናደርግ ገለጸችላት። ጥናቷ ይህ በእሷ ቤተ ክርስቲያን ካለው ሁኔታ ጨርሶ የተለየ እንደሆነ ተናገረች። የስብሰባዎቻችን ዓላማም ብዙዎች ከሚያውቋቸው ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች የተለየ ነው። (ኢሳይያስ 54:13ን አንብብ።) የምንሰበሰበው ይሖዋን ለማምለክ፣ ከእሱ ለመማርና እርስ በርስ ለመበረታታት ነው። (ዕብ. 2:12፤ 10:24, 25) በመሆኑም ስብሰባዎቻችን ሥርዓታማና ትምህርት ሰጪ ናቸው እንጂ የተለየ የአምልኮ ሥርዓት የሚፈጸምባቸው ቦታዎች አይደሉም። (1 ቆሮ. 14:40) ወደ ስብሰባ አዳራሻችን የምንመጣው ለመማር ስለሆነ አዳራሹ በቂ ብርሃን አለው። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኞች ስለሆንን የትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ የሚደግፍ ሐሳብ አንናገርም። ጩኸትና ክርክርም የለም። ተማሪው ወደ ስብሰባ ከመምጣቱ በፊት በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የተባለውን ቪዲዮ ብናሳየው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ካደረግን ስብሰባዎቻችን ምን እንደሚመስሉ ማወቅ ይችላል።
9-10. አንድ ሰው በስብሰባ ላይ እንዲገኝ ስንጋብዝ ፍርሃት እንዳይሰማው ምን ልንነግረው እንችላለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
9 አንዳንዶች በስብሰባችን ላይ ለመገኘት የሚያመነቱት ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ እንደምንጠይቃቸው ስለሚሰማቸው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እንግዶች ሲመጡ ደስ እንደሚለን እንዲሁም እምነታቸውን እንዲቀይሩ ወይም በስብሰባው ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጫና እንደማናደርግባቸው ልናረጋግጥላቸው እንችላለን። ትናንሽ ልጆች ያሏቸውን ጨምሮ ቤተሰቦችም መገኘት ይችላሉ። በስብሰባዎቻችን ላይ ልጆች ከወላጆቻቸው ተነጥለው ትምህርት አይሰጣቸውም። ከዚህ ይልቅ፣ ወላጆችና ልጆች አብረው ተቀምጠው አንድ ላይ ይማራሉ። በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸው ከማን ጋር እንደሆኑና ምን እንደሚማሩ ማወቅ ይችላሉ። (ዘዳ. 31:12) ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም፤ እንዲሁም ገንዘብ አንሰበስብም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” በማለት የሰጠውን መመሪያ እንከተላለን። (ማቴ. 10:8) በተጨማሪም በስብሰባው ላይ ለመገኘት ውድ ልብስ መልበስ እንደማይጠበቅበት ለግለሰቡ ልንነግረው እንችላለን። አምላክ የሚያየው የሰዎችን ውጫዊ ገጽታ ሳይሆን ልብን ነው።—1 ሳሙ. 16:7
10 ግለሰቡ በስብሰባ ላይ ከተገኘ እንግድነት እንዳይሰማው አድርጉ። ከሽማግሌዎችና ከሌሎች አስፋፊዎች ጋር አስተዋውቁት። ባይተዋርነት ካልተሰማው በድጋሚ ለመምጣት ሊነሳሳ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ ካልመጣ በስብሰባው ወቅት የእናንተን መጽሐፍ ቅዱስ አሳዩት፤ እንዲሁም ንግግሩን ወይም ጥናቱን እንዲከታተል እርዱት።
አንድ ሰው ቶሎ በስብሰባ ላይ መገኘት ከጀመረ ብዙ ጥቅም ያገኛል (አንቀጽ 9-10ን ተመልከት)
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከተጀመረ በኋላ
11. ለምናስጠናው ግለሰብ ጊዜና ፕሮግራም አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
11 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ ምን ማስታወስ ይኖርብናል? የግለሰቡ ጊዜ ውድ እንደሆነ ተገንዘቡ፤ እንዲሁም ፕሮግራሙን አክብሩለት። ለምሳሌ ቀጠሮ ከሰጣችሁት በሰዓቱ ድረሱ፤ በአካባቢያችሁ ያሉ ሰዎች ሰዓት አክባሪ ባይሆኑም እንኳ ይህን ማድረጋችሁ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ ስታስጠኑት የጥናት ፕሮግራሙን አጭር ማድረጋችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ተሞክሮ ያላቸው አንዳንድ አስፋፊዎች፣ ግለሰቡ ተጨማሪ ነገር መማር ቢፈልግም እንኳ ጥናቱን በሰዓቱ መጨረስ ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህም ሌላ ብዙ አታውሩ። ጥናታችሁ ሐሳቡንና ስሜቱን እንዲገልጽ ጊዜ ስጡት።—ምሳሌ 10:19
12. ጥናት ካስጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ግባችን ምን ሊሆን ይገባል?
12 ከመጀመሪያ አንስቶ ግባችሁ ጥናቶቻችሁ ይሖዋንና ኢየሱስን እንዲያውቁና ለእነሱ ፍቅር እንዲያዳብሩ መርዳት መሆን አለበት። ይህን የምታደርጉት ጥናቱ በእናንተ ወይም እናንተ ባላችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ ሳይሆን በአምላክ ቃል ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ነው። (ሥራ 10:25, 26) ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎችን በሚያስተምርበት ጊዜ በዋነኝነት ያተኮረው ይሖዋ እሱን ለማወቅና ለመውደድ እንዲረዳን ሲል በላከልን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነበር። (1 ቆሮ. 2:1, 2) በተጨማሪም ጳውሎስ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በወርቅ፣ በብርና በከበሩ ድንጋዮች የተመሰሉ ግሩም ባሕርያትን እንዲያዳብሩ መርዳት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል። (1 ቆሮ. 3:11-15) እንዲህ ካሉት ግሩም ባሕርያት መካከል እምነት፣ ጥበብ፣ ጥልቅ ግንዛቤና ይሖዋን መፍራት ይገኙበታል። (መዝ. 19:9, 10፤ ምሳሌ 3:13-15፤ 1 ጴጥ. 1:7) ጥናቶቻችሁ ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩና አፍቃሪ ከሆነው ሰማያዊ አባታቸው ጋር በግለሰብ ደረጃ ዝምድና እንዲመሠርቱ በመርዳት የጳውሎስን ምሳሌ ተከተሉ።—2 ቆሮ. 1:24
13. ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ስንረዳ ትዕግሥት ማሳየትና ስሜታቸውን መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 ትዕግሥት በማሳየትና የጥናቶቻችሁን ስሜት በመረዳት የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ። ግለሰቡን ሊያሸማቅቀው የሚችል ጥያቄ ከመጠየቅ ተቆጠቡ። ጥናታችሁ ለመረዳት የከበደው ነጥብ ካለ ነጥቡን አልፋችሁት ሌላ ጊዜ ልትመለሱበት ትችላላችሁ። ዝግጁ ከመሆኑ በፊት አንድን ትምህርት እንዲቀበል ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ እውነት በልቡ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ጊዜ ስጡት። (ዮሐ. 16:12፤ ቆላ. 2:6, 7) መጽሐፍ ቅዱስ የምናፈርሳቸውን የሐሰት ትምህርቶች ከምሽግ ጋር ያመሳስላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5ን አንብብ።) የጥናታችሁን ምሽግ ከማፍረሳችሁ በፊት በመጀመሪያ ይሖዋን ምሽጉ እንዲያደርግ እርዱት።—መዝ. 91:9 ግርጌ
እውነት በጥናታችሁ ልብ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ጊዜ ስጡት (አንቀጽ 13ን ተመልከት)
አዲሶች በስብሰባ ላይ ሲገኙ
14. አዲሶች በስብሰባችን ላይ ሲገኙ እንዴት ልንይዛቸው ይገባል?
14 አዲሶች ባሕላቸው፣ የኑሮ ደረጃቸው ወይም ዘራቸው ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ እንድንይዛቸው ይጠብቅብናል። (ያዕ. 2:1-4, 9) ታዲያ በስብሰባችን ላይ ለሚገኙ ሰዎች ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
15-16. አዲሶች በስብሰባዎቻችን ላይ ሲገኙ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
15 አንዳንድ ሰዎች ወደ ስብሰባዎቻችን የሚመጡት የማወቅ ጉጉት ስላደረባቸው ወይም ደግሞ በሌላ አካባቢ የሚኖር ሰው በስብሰባ ላይ እንዲገኙ ስላበረታታቸው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ወደ አምልኮ ቦታችን የሚመጡ እንዲህ ያሉ ሰዎችን ከማነጋገር ወደኋላ ማለት የለብንም። ጥሩ አቀባበል አድርጉላቸው፤ ግን እንዳታስጨንቋቸው ተጠንቀቁ። አብረዋችሁ እንዲቀመጡ ጋብዟቸው። መጽሐፍ ቅዱስንና የሚጠኑትን ጽሑፎች አብረዋችሁ እንዲከታተሉ እርዷቸው፤ ወይም ደግሞ የራሳቸውን ቅጂ ስጧቸው። ከዚህም ሌላ ለስሜታቸው ትኩረት ስጡ። ወደ ስብሰባ አዳራሽ የመጣ አንድ ሰው አቀባበል ላደረገለት ወንድም የአዘቦት ልብስ ለብሶ በመምጣቱ ነፃነት እንዳልተሰማው ነገረው። ወንድምም የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሰዎች የተለዩ እንዳልሆኑ በመግለጽ ሰውየውን አረጋጋው። ከጊዜ በኋላ ሰውየው እድገት አድርጎ ተጠመቀ። ይሁንና ያ ወንድም የሰጠውን ምላሽ ፈጽሞ አይረሳውም። ሆኖም ጥንቃቄ ልናደርግበት የሚገባ አንድ ነገር አለ፤ አዲሶችን ከስብሰባ በፊት ወይም በኋላ ስታነጋግሩ አሳቢነት ልታሳዩአቸው ቢገባም በግል ጉዳያቸው ውስጥ ጣልቃ እንዳትገቡ ወይም የሚያሸማቅቅ ጥያቄ እንዳትጠይቋቸው ተጠንቀቁ።—1 ጴጥ. 4:15
16 እንግዶቻችን በስብሰባ ላይ ሲገኙ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። እርስ በርስ ስንጨዋወት፣ ሐሳብ ስንሰጥ ወይም ክፍል ስናቀርብ የይሖዋ ምሥክር ስላልሆኑ ሰዎች ወይም ስለሚያምኑበት ነገር በምንናገርበት ጊዜ አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። ሊያሰናክላቸው ወይም እንደ ስድብ ሊቆጠር የሚችል አገላለጽ አትጠቀሙ። (ቲቶ 2:8፤ 3:2) ለምሳሌ ሌላ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች የሚያምኑበትን ነገር በፍጹም አናንቋሽሽም። (2 ቆሮ. 6:3) በተለይ የሕዝብ ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞች ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በተጨማሪም አብዛኞቹ ሰዎች የማይረዷቸውን አገላለጾችና ሐሳቦች በማብራራት እንግዶችን ከግምት እንደሚያስገቡ ያሳያሉ።
17. “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ያላቸውን ሰዎች በአገልግሎት ላይ ስናገኝ ግባችን ምንድን ነው?
17 ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራችን ይበልጥ አጣዳፊ ይሆናል። እኛም “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ [ያላቸውን]” ሰዎች መፈለጋችንን እንቀጥላለን። (ሥራ 13:48) እንዲህ ያሉ ሰዎችን ስናገኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ወይም በስብሰባ ላይ እንዲገኙ ከመጋበዝ ወደኋላ ማለት አይኖርብንም። እንዲህ ካደረግን ‘ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ’ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ ልንረዳቸው እንችላለን።—ማቴ. 7:14
መዝሙር 64 በመከሩ ሥራ በደስታ መካፈል
a የሥዕሉ መግለጫ፦ ሁለት ወንድሞች በረንዳው ላይ ዘና ብሎ ለተቀመጠ ጡረታ የወጣ ወታደር ሲመሠክሩ፤ ሁለት እህቶች በሥራ ለተወጠረች እናት አጠር ያለ ምሥክርነት ሲሰጡ።