የጥናት ርዕስ 40
መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች
ይሖዋ ‘እጅግ ሐሴት የምናደርግበት አምላክ’ ነው
“እጅግ ሐሴት ወደማደርግበት አምላክ እመጣለሁ።”—መዝ. 43:4
ዓላማ
ደስታችንን ሊሰርቅብን የሚችለው ምን እንደሆነና ደስታችንን ብናጣ መልሰን ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1-2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙዎች በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
በምንኖርበት ዓለም ሰዎች ደስታ ለማግኘት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ነገር ግን ዘላቂ ደስታ ማግኘት አልቻሉም። ብዙዎች በሐዘንና በባዶነት ስሜት ተውጠዋል። የይሖዋ ሕዝቦችም እንዲህ ያለ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ስለሆነ ‘ለመቋቋም የሚያስቸግሩ’ ሁኔታዎችና ስሜቶች ሊያጋጥሙን ይችላሉ።—2 ጢሞ. 3:1
2 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ደስታችንን ሊሰርቁብን የሚችሉት ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁም ደስታችንን ብናጣ መልሰን ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን የእውነተኛ ደስታና ሐሴት ምንጭ ማን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል።
የእውነተኛ ደስታና ሐሴት ምንጭ
3. ፍጥረት ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
3 ይሖዋ ምንጊዜም ደስተኛ ነው። እኛም ደስተኛ እንድንሆንና ሐሴት እንድናደርግ ይፈልጋል። ደስታው በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ ተንጸባርቋል፤ ለምሳሌ ውብ የሆነችው ፕላኔታችን፣ የምናያቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቀለማት፣ የእንስሳት ጨዋታ እንዲሁም የምንመገባቸው የተትረፈረፉ ጣፋጭ ምግቦች ይህን የሚያሳዩ ናቸው። በእርግጥም አምላክ ይወደናል፤ በሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆንም ይፈልጋል።
Baby elephant: Image © Romi Gamit/Shutterstock; penguin chicks: Vladimir Seliverstov/500px via Getty Images; baby goats: Rita Kochmarjova/stock.adobe.com; two dolphins: georgeclerk/E+ via Getty Images
የእንስሳት ጨዋታ ይሖዋ ደስተኛ እንደሆነ ያሳያል (አንቀጽ 3ን ተመልከት)
4. (ሀ) ይሖዋ በዓለም ላይ ያለውን መከራ እየተመለከተም ደስተኛ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ስጦታ ሰጥቶናል? (መዝሙር 16:11)
4 ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ቢሆንም በዓለም ላይ ያለውን ሐዘንና መከራ ይመለከታል። (1 ጢሞ. 1:11) ይሁንና ይህ ሁኔታ ደስታውን እንዲቀንስበት አይፈቅድም። ሁሉም መከራ ጊዜያዊ እንደሆነ ያውቃል፤ እንዲያውም መከራ የሚያበቃበትን ጊዜ እሱ ራሱ ወስኗል። ማንኛውንም ሐዘንና መከራ የሚያስወግድበት ጊዜ እስኪደርስ በትዕግሥት እየጠበቀ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን ይሖዋ የሚያጋጥመንን ችግር ይመለከታል፤ ሊረዳንም ይፈልጋል። ታዲያ የሚረዳን እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ደስታን ስጦታ አድርጎ ሰጥቶናል። (መዝሙር 16:11ን አንብብ።) ይህን ስጦታ ለልጁ ለኢየሱስ የሰጠው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
5-6. ኢየሱስ ደስተኛ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ የኢየሱስን ያህል ደስተኛ የለም። ለምን? ሁለት ምክንያቶችን እናንሳ። (1) እሱ “የማይታየው አምላክ አምሳል” ነው፤ ሁሉንም የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃል። (ቆላ. 1:15፤ 1 ጢሞ. 6:15) (2) ኢየሱስ የደስታ ምንጭ ከሆነው ከአባቱ ጋር ከየትኛውም ፍጥረት የበለጠ ብዙ ጊዜ አሳልፏል።
6 ኢየሱስ አባቱ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ስለሚያደርግ ምንጊዜም ደስተኛ ነው። (ምሳሌ 8:30, 31፤ ዮሐ. 8:29) በተከተለው የታማኝነት ጎዳና የተነሳ ይሖዋ ይደሰትበታል።—ማቴ. 3:17
7. እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
7 እኛም የደስታ ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ በመቅረብ እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንችላለን። ስለ ይሖዋ በመማር የበለጠ ጊዜ ባሳለፍን እንዲሁም እሱን ለመምሰል ጥረት ባደረግን ቁጥር ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችንና የእሱን ሞገስ እንዳገኘን ማወቃችንም ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል።a (መዝ. 33:12) ይሁንና አልፎ አልፎ ወይም ረዘም ላለ ጊዜ ደስታችንን ብናጣስ? ይህ የይሖዋን ሞገስ እንዳጣን የሚያሳይ ነው? በጭራሽ! ፍጹማን ባለመሆናችን አልፎ አልፎ ሕመም፣ ሐዘን እንዲሁም የመንፈስ ጭንቀት ሊያጋጥመን ይችላል። ይሖዋ ይህን ይረዳል። (መዝ. 103:14) ደስታችንን ሊሰርቁን የሚችሉት ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁም ደስታችንን መልሰን ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
ምንም ነገር ደስታችሁን እንዲሰርቃችሁ አትፍቀዱ
8. የሕይወት ውጣ ውረድ ምን ተጽዕኖ ያደርግብናል?
8 አንደኛው ሌባ፦ የሕይወት ውጣ ውረድ። በስደት፣ በተፈጥሮ አደጋ፣ በድህነት፣ በሕመም ወይም በእርጅና ምክንያት ሕይወትህ ከባድ ሆኖብሃል? እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥሙን በቀላሉ ደስታችንን ልናጣ እንችላለን፤ በተለይ ችግሩ ከቁጥጥራችን ውጭ ከሆነ ሁኔታው ይበልጥ ሊከብደን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የልብ ሐዘን . . . መንፈስን ይደቁሳል” በማለት እውነታውን በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 15:13) በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወንድሙንና ሁለቱንም ወላጆቹን በሞት ያጣ ባቢስ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ብቻዬን እንደሆንኩና ረዳት እንደሌለኝ ተሰማኝ። ብዙ ኃላፊነት ስለተደራረበብኝ ወንድሜና ወላጆቼ ከመሞታቸው በፊት ከእነሱ ጋር በቂ ጊዜ ማሳለፍ ባለመቻሌ በሐዘን የምዋጥባቸው ጊዜያት ነበሩ።” በእርግጥም የሕይወት ውጣ ውረድ በአካልም ሆነ በስሜት እንድንዝል ሊያደርገን ይችላል።
9. ደስታችንን መልሰን ለማግኘት ምን ሊረዳን ይችላል? (ኤርምያስ 29:4-7, 10)
9 ደስታችንን መልሰን ለማግኘት ምን ይረዳናል? እውነታውን አምነን በመቀበልና አመስጋኞች በመሆን ደስታችንን መልሰን ማግኘት እንችላለን። ዓለም ደስተኛ መሆን የምንችለው ሕይወታችን አልጋ በአልጋ ከሆነ ብቻ እንደሆነ እንድናስብ ይፈልጋል። ይሁንና ይህ እውነት አይደለም። ለምሳሌ ይሖዋ ወደ ባቢሎን በግዞት የተወሰዱትን አይሁዳውያን በባዕድ አገር ያሉ ምርኮኞች መሆናቸውን አምነው እንዲቀበሉና ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም አቅማቸው የፈቀደውን እንዲያደርጉ አዟቸዋል። (ኤርምያስ 29:4-7, 10ን አንብብ።) ነጥቡ ምንድን ነው? ያለህበትን ሁኔታ አምነህ ተቀበል፤ እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ ላገኘሃቸው መልካም ነገሮች አመስጋኝ ሁን። ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚረዳህ አስታውስ። (መዝ. 63:7፤ 146:5) በደረሰባት አደጋ ምክንያት ሽባ የሆነችው ኤፊ እንዲህ ብላለች፦ “ከይሖዋ፣ ከቤተሰቦቼ እንዲሁም ከጉባኤው ብዙ እርዳታና ድጋፍ አግኝቻለሁ። ስለዚህ ተስፋ ብቆርጥ ምስጋና ቢስነት እንደሚሆንብኝ ተሰማኝ። ይሖዋና ጉባኤው ላደረጉልኝ ከፍተኛ እርዳታ አመስጋኝነቴን ማሳየት እፈልጋለሁ።”
10. ችግሮች ቢያጋጥሙንም እንኳ ደስተኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
10 በሕይወታችን ውስጥ ችግር ቢያጋጥመንም ወይም በእኛም ሆነ በቤተሰባችን ላይ መጥፎ ነገር ቢደርስም እንኳ ደስተኞች ሆነን መቀጠል እንችላለን።b (መዝ. 126:5) ለምን? ምክንያቱም ደስታችን ባለንበት ሁኔታ ላይ የተመካ አይደለም። አቅኚ የሆነችው ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “ችግሮች ቢያጋጥሙንም ደስተኛ እንሆናለን ሲባል ስሜታችንን እናፍናለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የገባልንን ቃል እናስታውሳለን ማለት ነው። አባታችን ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል።” በአሁኑ ወቅት ነገሮች ምንም ያህል ከባድ ቢሆኑ ሁሉም ችግሮቻችን ጊዜያዊ እንደሆኑ አስታውስ። በባሕር ዳርቻ አሸዋ ላይ እንዳለ ኮቴ ምንም ርዝራዥ ሳይተዉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታጥበው ይሄዳሉ።
11. የሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ የሚያበረታታህ እንዴት ነው?
11 የሚደርሱብን መከራዎች በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳጣን የሚያሳዩ እንደሆነ ከተሰማንስ? በጣም ከባድ ችግር ያጋጠማቸውን ሌሎች የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ማስታወሳችን ይጠቅመናል። የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስ “በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት” ምሥራቹን እንዲሰብክ ኢየሱስ ራሱ መርጦታል። (ሥራ 9:15) እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው! ይሁንና የጳውሎስ ሕይወት አልጋ በአልጋ አልነበረም። (2 ቆሮ. 11:23-27) ጳውሎስ ያጋጠመው የማያባራ ፈተና በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳጣ የሚያሳይ ነው? በፍጹም! እንዲያውም መጽናቱ የይሖዋ በረከት እንዳልተለየው የሚያሳይ ነው። (ሮም 5:3-5) እስቲ አሁን ደግሞ አንተ ስላለህበት ሁኔታ አስብ። ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥሙህም እስካሁን ድረስ በታማኝነት ጸንተሃል። ስለዚህ አንተም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
12. የጠበቅናቸው ነገሮች ሳይሆኑ ሲቀሩ ደስታችን ሊሰረቅ የሚችለው እንዴት ነው?
12 ሁለተኛው ሌባ፦ የጠበቅናቸው ነገሮች ሳይሆኑ ሲቀሩ። (ምሳሌ 13:12) ለይሖዋ ያለን ፍቅርና አመስጋኝነት ከእሱ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ግቦችን እንድናወጣ ያነሳሳናል። ነገር ግን ያወጣናቸው ግቦች ሁኔታችንን ያላገናዘቡ ከሆኑ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። (ምሳሌ 17:22) ሆሊ የተባለች አንዲት አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት መማር፣ በውጭ አገር ማገልገል ወይም በራማፖ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ መሳተፍ እፈልግ ነበር። ሆኖም ያለሁበት ሁኔታ ስለተቀየረ እነዚህ ግቦች ላይ መድረስ አልቻልኩም። በጣም አዘንኩ። አንድን ነገር ማድረግ እየፈለጋችሁ ማድረግ አለመቻል በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ነው።” ብዙዎች ይህን ስሜት ይጋሩታል።
13. ያለንበት ሁኔታ ማከናወን የምንችለውን ነገር ከገደበብን የትኞቹን ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች ማውጣት እንችላለን?
13 ደስታችንን መልሰን ለማግኘት ምን ይረዳናል? ይሖዋ ከአቅማችን በላይ እንደማይጠብቅብን አስታውስ። ዋጋማነታችንን የሚመዝነው በእሱ አገልግሎት ውስጥ ባከናወንናቸው ነገሮች ላይ ተመሥርቶ አይደለም። ይሖዋ ልካችንን እንድናውቅና ታማኞች እንድንሆን ይፈልጋል። (ሚክ. 6:8፤ 1 ቆሮ. 4:2) ከምናከናውነው ነገር በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለውስጣዊ ማንነታችን ነው። ይሖዋ ከሚጠብቅብን በላይ ከራሳችን ብንጠብቅ ምክንያታዊ ይሆናል?c በጭራሽ! ስለዚህ ያለህበት ሁኔታ ለይሖዋ የምታቀርበውን አገልግሎት ከገደበብህ ማከናወን በምትችለው ነገር ላይ አተኩር። ወጣቶችን ማሠልጠን ወይም አረጋውያንን መደገፍ ትችል ይሆን? አንድን ሰው በአካል፣ በስልክ ወይም በጽሑፍ መልእክት ለማበረታታት ግብ ማውጣት ትችል ይሆን? እንዲህ ያሉ ጠቃሚና ሁኔታህን ያገናዘቡ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ ይሖዋ ደስታ በመስጠት ይባርክሃል! በጣም በቅርቡ ደግሞ፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ አስበህ በማታውቀው መንገድ ይሖዋን ማገልገል የምትችልባቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው አጋጣሚዎች እንደሚከፈቱልህ አስታውስ! ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሆሊ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ቁጭ ብዬ እንዲህ በማለት አስባለሁ፦ ‘ገና ለዘላለም እኖራለሁ። በይሖዋ እርዳታ በአዲሱ ዓለም አንዳንዶቹ ግቦቼ ላይ መድረስ እችላለሁ።’”
14. ደስታችንን ሊሰርቅብን የሚችለው ሌላው ነገር ምንድን ነው?
14 ሦስተኛው ሌባ፦ ራስን ማስደሰት። አንዳንዶች እውነተኛ ደስታና እርካታ የሚገኘው ራስን በማስደሰት ነው የሚለውን ሐሳብ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያራምዳሉ። ሰዎች ለትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ፣ ለጉዞ ወይም ዕቃ ለመሸመት ከልክ ያለፈ ትኩረት እንዲሰጡ ይበረታታሉ። በእነዚህ ነገሮች መደሰት ስህተት የለውም። ይሖዋ የፈጠረን ውብ ነገሮችን እንድናደንቅ አድርጎ ነው። ይሁንና ብዙዎች፣ ደስታ ያመጣልናል ብለው ያሰቡት ነገር መልሶ ደስታቸውን ሲሰርቀው ተመልክተዋል። ኤቫ የተባለች አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ሕይወታችሁ ራሳችሁን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ከሆነ ምንም ነገር አይበቃችሁም።” ራሳችንን ማስደሰት የኋላ ኋላ ለሐዘንና ለባዶነት ስሜት ሊዳርገን ይችላል።
15. ከንጉሥ ሰለሞን ምን ትምህርት እናገኛለን?
15 ራስን ማስደሰት የሚያስከትለውን አሳዛኝ ውጤት ከንጉሥ ሰለሞን ታሪክ መማር እንችላለን። ሰለሞን የግል ፍላጎቶቹን በማርካት ለምሳሌ ጥሩ ምግብ በመመገብ፣ ጥሩ ሙዚቃ በመስማት እንዲሁም በዘመኑ ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችላቸውን ነገሮች ሁሉ በማድረግ ደስታ ለማግኘት ሞክሯል። ቢሆንም ግን እነዚህ ነገሮች ሊያረኩት አልቻሉም። እንዲህ ብሏል፦ “ዓይን አይቶ አይጠግብም፤ ጆሮም ሰምቶ አይሞላም።” (መክ. 1:8፤ 2:1-11) ዓለም ስለ እውነተኛ ደስታ ያለው አመለካከት ከሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሲታዩ ዋጋ ያላቸው ይመስላሉ፤ ግን ምንም ነገር መግዛት አይችሉም።
16. ለሌሎች መስጠት ደስታችንን መልሰን ለማግኘት የሚረዳን እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
16 ደስታችንን መልሰን ለማግኘት ምን ይረዳናል? ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ሲል ተናግሯል። (ሥራ 20:35) አሌኮስ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ለሌሎች ትናንሽ ነገሮችን ለማድረግ ጥረት አደርጋለሁ። ለሌሎች መስጠቴ በራሴ ላይ ትኩረት እንዳላደርግ ይረዳኛል፤ ይህ ደግሞ ደስተኛ ያደርገኛል።” አንተስ ለሌሎች ምን ማድረግ ትችላለህ? ችግር ያጋጠመው ሰው ስታይ ለማበረታታት ጥረት አድርግ። ችግሮቹን ልትቀርፍለት አትችል ይሆናል፤ ነገር ግን በአዘኔታ ስሜት በማዳመጥ፣ ርኅራኄ በማሳየት እንዲሁም ሸክሙን በይሖዋ ላይ እንዲጥል በማስታወስ ልታጽናናው ትችላለህ። (መዝ. 55:22፤ 68:19) ይሖዋ እንዳልተወው በመንገርም ልታበረታታው ትችላለህ። (መዝ. 37:28፤ ኢሳ. 59:1) ምናልባትም ተግባራዊ እርዳታ ልታደርግለት ትችል ይሆናል፤ ለምሳሌ ምግብ ልታዘጋጅለት ወይም አብረኸው ወክ ልታደርግ ትችላለህ። አገልግሎትም ልትጋብዘው ትችላለህ፤ ይህም መንፈሱን ያነቃቃለታል። በይሖዋ እጅ ላይ ያለ መሣሪያ ለመሆን ራስህን አቅርብ። ከራሳችን ይልቅ በሌሎች ላይ ትኩረት ማድረጋችን እውነተኛ ደስታ ያስገኝልናል!—ምሳሌ 11:25
አንተ በምትፈልጋቸው ነገሮች ላይ ሳይሆን ሌሎች በሚያስፈልጓቸው ነገሮች ላይ ትኩረት አድርግ (አንቀጽ 16ን ተመልከት)d
17. እውነተኛ ደስታ ማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (መዝሙር 43:4)
17 ወደ ሰማዩ አባታችን መቅረባችንን ከቀጠልን እውነተኛ ደስታ እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ‘እጅግ ሐሴት የምናደርግበት’ አምላክ እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 43:4ን አንብብ።) ስለዚህ በሕይወታችን ውስጥ ምንም ዓይነት ከባድ ሁኔታ ቢገጥመን አንጨነቅም። እንግዲያው የማይነጥፍ የደስታ ምንጭ በሆነው በይሖዋ ላይ ትኩረት ማድረጋችንን እንቀጥል!—መዝ. 144:15
መዝሙር 155 የዘላለም ደስታ
a “ከይሖዋ ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b ለምሳሌ ያህል፣ በ2023 የበላይ አካሉ ሪፖርት ቁጥር 5 ላይ የወጣውን የዴኒስና የአይሪና ክሪስተንሰንን ቃለ መጠይቅ jw.org ላይ ተመልከት።
c ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌ 15, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ በመሆን ደስታ ማግኘት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት ለራሷ ብዙ ነገሮችን ትገዛለች፤ ይበልጥ ያስደሰታት ግን ማበረታቻ ለሚያስፈልጋት አንዲት አረጋዊት እህት አበባ መግዛቷ ነው።