የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ኅዳር ገጽ 8-9
  • መኪና መንዳቴን ማቆም ይኖርብኝ ይሆን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መኪና መንዳቴን ማቆም ይኖርብኝ ይሆን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አነዳድህን ገምግም
  • በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመራ
  • መኪና ስታሽከረክር ራስህን ከአደጋ ትጠብቃለህ?
    ንቁ!—2002
  • ጠንቃቃ ሾፌር ነህን?
    ንቁ!—1996
  • የመኪና አደጋ እንዳይደርስ መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2011
  • አደጋ በማያስከትል መንገድ ማሽከርከር የምትችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2009
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ኅዳር ገጽ 8-9
አንድ አረጋዊ ወንድም መስኮት አጠገብ ተቀምጦ ደጅ ያለውን መኪናውን ይመለከታል። በእጁ የመኪናውን ቁልፍ ይዞ እያሰላሰለ ነው።

መኪና መንዳቴን ማቆም ይኖርብኝ ይሆን?

ለበርካታ አሥርተ ዓመታት መኪና ሲነዳ የኖረን አንድ አረጋዊ ሰው ለማሰብ ሞክር። የፈለገበት ቦታ መሄድ ስለሚችል መንዳቱን ይወደዋል። ሆኖም ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ሁኔታው ስላሳሰባቸው መንዳቱን ቢያቆም ደስ ይላቸዋል። እሱ ግን ያስጨነቃቸው ነገር ምን እንደሆነ አልገባውም።

አንተም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ መንዳትህን መቀጠል ይኖርብህ እንደሆነ ለመወሰን ምን ይረዳሃል?

በአንዳንድ አገሮች ከተወሰነ ዕድሜ በላይ ያሉ አሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃዳቸውን ለማደስ የሐኪም ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ክርስቲያኖች፣ ባለሥልጣናት ያወጧቸውን ሕጎች መታዘዝ ይኖርባቸዋል። (ሮም 13:1) ሆኖም የምትኖረው የትም ይሁን የት የመንዳት ችሎታህን ራስህ መገምገም የምትችልባቸው መንገዶች አሉ።

አነዳድህን ገምግም

ስለ አረጋውያን የሚያጠና አንድ ድርጅት አረጋውያን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳቸውን እንዲጠይቁ ያበረታታል፦

  • የመንገድ ዳር ምልክቶችን ማንበብ ወይም በምሽት ማየት ይከብደኛል?

  • አንገቴን አዙሬ ስፖኪዮ ወይም የኋላ መስታወቱን ማየት ያስቸግረኛል?

  • ለሁኔታዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ይከብደኛል? ለምሳሌ እግሬን ከነዳጁ ላይ አንስቼ ፍሬን ቶሎ መያዝ ያቅተኛል?

  • በጣም ቀስ ብዬ ከመንዳቴ የተነሳ የትራፊክ ፍሰቱን አስተጓጉላለሁ?

  • ከአደጋ ለጥቂት የተረፍኩባቸው ጊዜያት አሉ? ወይም ደግሞ የቆመ ነገር በመግጨቴ ምክንያት መኪናዬ ተጫጭሯል?

  • በአነዳዴ ምክንያት ትራፊክ ፖሊስ አስቁሞኝ ያውቃል?

  • እየነዳሁ እንቅልፍ ወስዶኝ ያውቃል?

  • በአነዳዴ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መድኃኒት እየወሰድኩ ነው?

  • የቤተሰቤ አባላት ወይም ጓደኞቼ አነዳዴ እንደሚያሳስባቸው ነግረውኝ ያውቃሉ?

ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱ ወይም ለሁለቱ “አዎ” የሚል መልስ ከሰጠህ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ልታስብበት ይገባል። ለምሳሌ የምትነዳበትን ጊዜ ለመቀነስ ትወስን ይሆናል፤ በተለይ ምሽት ላይ። አነዳድህን በየጊዜው ገምግም። የቤተሰብህን አባላት ወይም ጓደኞችህን ስለ አነዳድህ አስተያየት እንዲሰጡህ መጠየቅ ትችላለህ። ምናልባትም አነዳድህን ለማሻሻል የሚረዳ ኮርስ ልትወስድ ትችላለህ። ሆኖም አብዛኞቹን ጥያቄዎች “አዎ” ብለህ ከመለስክ መንዳትህን ማቆምህ የተሻለ ሊሆን ይችላል።a

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመራ

የመንዳት ችሎታችን እየቀነሰ መሆኑ ላይታወቀን ይችላል። እንዲሁም መንዳት ማቆም የሚለው ጉዳይ ለማሰብ እንኳ ሊከብደን ይችላል። ታዲያ ሁኔታህን በሐቀኝነት ለመመርመርና ጥበብ የታከለበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? እስቲ ሁለቱን እንመልከት።

ልክህን የምታውቅ ሁን። (ምሳሌ 11:2) በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ የማየትና የመስማት ችሎታችን እንዲሁም ጡንቻችንና ቅልጥፍናችን ይዳከማል። ለምሳሌ አብዛኞቹ ሰዎች ከተወሰነ ዕድሜ በኋላ በአንዳንድ ስፖርታዊ ጨዋታዎች መካፈል ያቆማሉ፤ ምክንያቱም ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ በቀላሉ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል ያውቃሉ። ከመንዳት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ልኩን የሚያውቅ ሰው ለራሱ ደህንነት በማሰብ የሆነ ጊዜ ላይ መንዳቱን ለማቆም ሊወስን ይችላል። (ምሳሌ 22:3) እንዲሁም አንዳንዶች ስለ አነዳዱ ስጋት ካላቸው ልኩን የሚያውቅ ሰው ምክራቸውን ይቀበላል።—ከ2 ሳሙኤል 21:15-17 ጋር አወዳድር።

ከደም ዕዳ ራስህን ጠብቅ። (ዘዳ. 22:8) መኪና በተገቢው መንገድ ካልተነዳ ከባድ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። የመንዳት ችሎታው ቢቀንስም መንዳቱን የሚቀጥል ሰው የራሱንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። ለሞት የሚዳርግ አደጋ ካስከተለ ደግሞ በደም ዕዳ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል።

‘መንዳቴን ማቆም ይኖርብኝ ይሆን?’ የሚለው ከባድ ውሳኔ ከፊትህ ከተደቀነ ሁኔታው ክብርህን ሊነካ እንደሚችል ወይም ዋጋማነትህን እንደሚቀንሰው አታስብ። ይሖዋ ይወድሃል፤ እንዲሁም ልክህን በማወቅህ፣ ትሑት በመሆንህና ለሌሎች ደህንነት በማሰብህ ይደሰትብሃል። ደግሞም እንደሚያጽናናህና እንደሚደግፍህ ቃል ገብቷል። (ኢሳ. 46:4) ፈጽሞ አይተውህም። ስለዚህ ‘መኪና መንዳቴን ማቆም ይኖርብኝ ይሆን?’ የሚለውን ለመወሰን የሚያስችል ጥበብና ማስተዋል እንዲሰጥህ ጠይቀው።

ሌሎች እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?

ብዙውን ጊዜ፣ አረጋውያንን ስለ አነዳዳቸው ሌሎች ከሚያነጋግሯቸው ይልቅ ቤተሰቦቻቸው ቢያነጋግሯቸው የተሻለ ይሆናል። ወይም ደግሞ አረጋዊ ጓደኛ ካለህ ሌሎች ሰዎች ስለ አነዳዱ ያሳሰባቸውን ነገር ሲናገሩ ትሰማ ይሆናል። የሚሰጡትን አስተያየት በቁም ነገር ተመልከተው። ምናልባትም አብረኸው ሆነህ ሲነዳ ማየት ትችላለህ። አስፈላጊ ከሆነ ስለ አነዳዱ አነጋግረው። እሱን በምታነጋግርበት ጊዜ ራስህን በእሱ ቦታ ለማስቀመጥ ጥረት አድርግ። በደግነት ሆኖም በግልጽ አነጋግረው። ዕድሜው ላይ ብዙ አታተኩር፤ በዋነኝነት ልታነጋግረው የሚገባው ስለ አነዳድ ችሎታው ነው። “ጥሩ አሽከርካሪ አይደለህም” ከማለት ይልቅ “ስትነዳ አደጋ እንዳይደርስብህ እሰጋለሁ” ብትለው የተሻለ ይሆናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አስታውሰው፤ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ እንደምትተማመንበት ግለጽለት።

ሁላችንም አንድ አረጋዊ ሰው መንዳቱን ለማቆም ሲገደድ ምን እንደሚሰማው ለመረዳት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ነፃነቱን እንዳጣና የሌሎች ጥገኛ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ታዲያ እንዴት ልትረዳው ትችላለህ? ደግነት አሳየው፤ እንዲሁም ተግባራዊ እርዳታ አድርግለት። (ምሳሌ 17:17) የሆነ ቦታ እንድትወስደው እስኪጠይቅህ ድረስ አትጠብቅ፤ ምክንያቱም ሸክም እንደሆነብህ ሊሰማው ይችላል። ምናልባትም እንደ ስብሰባ፣ የመስክ አገልግሎት፣ ገበያ እና የሕክምና ቀጠሮ ወዳሉ አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች የሚወስደው ሰው እንዳያጣ ልታመቻችለት ትችላለህ። በዚህ መልኩ እሱን መርዳትና ከእሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስደስትህ አረጋግጥለት።—ሮም 1:11, 12

a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥቅምት 2002 ንቁ! ላይ የወጣውን “መኪና ስታሽከረክር ራስህን ከአደጋ ትጠብቃለህ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ