የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?
    ንቁ!—2015 | ሐምሌ
    • ደስተኛ ያልሆነ አንድ ሰው በሥራ ቦታው ሆኖ ስለወደፊቱ ጊዜ ሲያስብ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

      ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?

      ወጣት ሳለህ ምን ግቦች ነበሩህ? ትዳር ለመመሥረት፣ በአንድ ዓይነት ሙያ የተካንክ ለመሆን ወይም በሚያስደስትህ የሥራ ዘርፍ ለመሰማራት አስበህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሕይወታችን ሁልጊዜ እኛ እንዳሰብነው አይሆንም። የሚያጋጥሙን ያልተጠበቁ ሁኔታዎች የሕይወታችንን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ሊቀይሩት ይችላሉ። አንያ፣ ዴሊና እና ግሪጎሪ ያጋጠማቸው ይህ ነው።

      አንያ፣ ዴሊና እና ግሪጎሪ
      • በጀርመን የምትኖረው አንያ ካንሰር እንዳለባት ያወቀችው በ21 ዓመቷ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከቤት መውጣት አትችልም።

      • በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ዴሊናም ዲስቶኒያ ኒውሮመስኩላር ዲስኦርደር ተብሎ በሚጠራ በሽታ ትሠቃያለች።

      • የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ሦስት ወንድሞቿን የመንከባከብ ኃላፊነትም አለባት። በካናዳ የሚኖረው ግሪጎሪ ደግሞ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ይሠቃያል።

      አንያ፣ ዴሊናና ግሪጎሪ የደረሱባቸው ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንዲቆጣጠሯቸው አልፈቀዱም። ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው?

      አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል” ይላል። (ምሳሌ 24:10) መልእክቱ ግልጽ ነው፦ አመለካከት ለውጥ ያመጣል። አሉታዊ አመለካከት መያዝ ያለንን ጥቂት አቅም እንኳ ያሟጥጥብናል፤ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ግን ሕይወታችንን በተቻለ መጠን እኛ በምንፈልገው መንገድ ለመምራት የሚያስችል ኃይል እንድናገኝ ይረዳናል።

      ይህ እውነት መሆኑ በአንያ፣ በዴሊናና በግሪጎሪ ላይ የታየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

  • ተፈታታኙ ነገር፦ ሊለወጡ የማይችሉ ሁኔታዎች
    ንቁ!—2015 | ሐምሌ
    • አንያ ከጓደኞቿ ጋር በቪዲዮ እየተያየች ስታወራ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?

      ተፈታታኙ ነገር፦ ሊለወጡ የማይችሉ ሁኔታዎች

      ሥር የሰደደ በሽታ ይዞህ ወይም ከትዳር ጓደኛህ ጋር ተፋትተህ አሊያም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ሊለወጡ የማይችሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ ያለህበት ሁኔታ እንዲለወጥ ከመመኘት በቀር ምንም ማድረግ እንደማትችል ይሰማህ ይሆናል። ታዲያ ሕይወትህን በተቻለ መጠን አንተ በምትፈልገው መንገድ መምራት የምትችለው እንዴት ነው?

      የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ጳውሎስ

      በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቀናተኛ ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለገለው ሐዋርያው ጳውሎስ ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዞ ነበር። ይሁን እንጂ ፍትሕ በጎደለው መንገድ ታሰረ፤ ከዚያም ለሁለት ዓመት ያህል አንድ ቤት ውስጥ በወታደር እየተጠበቀ እንዲኖር በመደረጉ ጉዞውን መቀጠል አልቻለም። ጳውሎስ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ከመዋጥ ይልቅ ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ ትኩረት አድርጓል። ሊጠይቁት ለመጡት ሰዎች ሁሉ መንፈሳዊ እርዳታና መጽናኛ ይሰጥ ነበር። በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን በርካታ ደብዳቤዎች የጻፈውም በዚያ እያለ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 28:30, 31

      አንያ ያደረገችው ነገር

      ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አንያ ከቤት መውጣት አትችልም። “ካንሰር እንዳለብኝ ማወቄ መላ ሕይወቴን ቀይሮታል። ለተላላፊ በሽታ እንዳልጋለጥ ስለምፈራ ሰብዓዊ ሥራ የማልሠራ ከመሆኑም ሌላ ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ተገድቧል” ብላለች። ታዲያ አንያ ሊለወጡ የማይችሉ ሁኔታዎችን መቋቋም የቻለችው እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “በየዕለቱ በማደርጋቸው ነገሮች ላይ ማስተካከያ ማድረጌ በጣም ረድቶኛል። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከለየሁ በኋላ አቅሜን ያገናዘበ ፕሮግራም አወጣለሁ። ይህም ሕይወቴን መቆጣጠር እንደቻልኩ እንዲሰማኝ አድርጓል።”

      “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬአለሁ።”—በፊልጵስዩስ 4:11 ላይ የሚገኘው ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ

      ምን ማድረግ ትችላለህ?

      በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠሙህን ሁኔታዎች ልትለውጣቸው እንደማትችል ከተሰማህ የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ ሞክር፦

      • ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ አተኩር። ለምሳሌ ያህል፣ የጤንነትህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የተመካው በአንተ ላይ ባይሆንም አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን በመመገብና በቂ እንቅልፍ በመተኛት ጤንነትህን ተንከባከብ።

      • በሕይወትህ ውስጥ ምን ማከናወን እንደምትፈልግ በግልጽ አስቀምጥ። ደረጃ በደረጃ ግብህ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን መንገዶች ፈልግ። ከዚያም በየቀኑ የተወሰነ ጊዜ መድበህ ወደ ግብህ ለመድረስ የሚረዳህን ነገር አከናውን።

      • ትናንሽ ቢሆኑም እንኳ ሕይወትህን መቆጣጠር እንደቻልክ እንዲሰማህ የሚያደርጉ ነገሮችን ለማከናወን ሞክር። የመመገቢያ ጠረጴዛ ማጽዳት ወይም ዕቃዎችን ማጠብ ትችላለህ። እንዲሁም ጥሩ አለባበስ ይኑርህ። ጠዋት ላይ ሥራህን ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በማከናወን ጀምር።

      • ያለህበት ሁኔታ ያስገኘልህን ጥቅሞች ለማስተዋል ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ያጋጠመህ ሁኔታ ችግሮችን መቋቋም የሚቻልባቸውን መንገዶች ይበልጥ እንድትገነዘብ ረድቶሃል? ታዲያ በዚህ ተጠቅመህ ሌሎችን መርዳት ትችል ይሆን?

      ዋናው ነጥብ፦ የሚያጋጥሙህን ሁኔታዎች መቆጣጠር ባትችልም ሁኔታዎቹን የምታስተናግድበት መንገድ ግን በአንተ ቁጥጥር ሥር ነው።

  • ተፈታታኙ ነገር፦ አሉታዊ ስሜቶች
    ንቁ!—2015 | ሐምሌ
    • ግሪጎሪ ተፈጥሮን ሲያደንቅ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?

      ተፈታታኙ ነገር፦ አሉታዊ ስሜቶች

      እንደ ሐዘን፣ ቁጣ ወይም ምሬት ያሉ ከባድ ስሜቶችን መቋቋም አዳጋች ሆኖብሃል? እነዚህ ስሜቶች ልታከናውናቸው የሚገቡ ነገሮችን ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ ወይም አቅም እንድታጣ አድርገውህ ይሆናል። ታዲያ ምን ልታደርግ ትችላለህ?a

      የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ዳዊት

      ንጉሥ ዳዊት ጭንቀትንና ሐዘንን ጨምሮ የተለያዩ ስሜቶች ተፈራርቀውበታል። ታዲያ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲቀጥል የረዳው ምንድን ነው? ዳዊት ያስጨነቁትን ነገሮች ለአምላክ ይተው ነበር። (1 ሳሙኤል 24:12, 15) በተጨማሪም ስሜቶቹን በጽሑፍ ያሰፍር እንዲሁም የእምነት ሰው እንደመሆኑ መጠን አዘውትሮ ይጸልይ ነበር።b

      ግሪጎሪ ያደረገው ነገር

      በመክፈቻው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው ግሪጎሪ በመንፈስ ጭንቀት ይሠቃያል። “ነገሮችን በጣም አጋንኜ በመመልከት ከልክ በላይ እጨነቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህ ስሜት ከቁጥጥሬ ውጭ ሆኖ ነበር” ብሏል። ታዲያ ግሪጎሪ ሚዛኑን መጠበቅ የቻለው እንዴት ነው? “ባለቤቴና ጓደኞቼ በደግነት ያደረጉልኝን እርዳታ መቀበሌ ሚዛኔን ለመጠበቅ ረድቶኛል። በተጨማሪም የባለሙያ እርዳታ ያገኘሁ ሲሆን ስላለሁበት ሁኔታ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አደረግኩ። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቼ ላይ አንዳንድ ለውጦች ሳደርግ ነገሮችን በቁጥጥሬ ሥር ማድረግ እንደቻልኩ ይሰማኝ ጀመር፤ አሁን ስሜቴ እኔን አይቆጣጠረኝም። እርግጥ አልፎ አልፎ የጭንቀት ስሜት ያድርብኛል፤ ያም ቢሆን ጭንቀት እንዲሰማኝ የሚያደርጉትን ሁኔታዎችና ይህን ስሜት መቋቋም የምችልበትን መንገድ በተመለከተ ከበፊቱ የተሻለ ግንዛቤ አለኝ።”

      “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው።”—ምሳሌ 17:22

      ምን ማድረግ ትችላለህ?

      ያደረብህን አሉታዊ ስሜት መቆጣጠር እንዳቃተህ ከተሰማህ የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ ሞክር፦

      • የሚሰሙህን ስሜቶች በማስታወሻህ ላይ አስፍር።

      • ስሜትህን ለቅርብ ዘመድህ ወይም ጓደኛህ በግልጽ ተናገር።

      • የሚሰሙህ ስሜቶች ትክክል ናቸው ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘እንዲህ ያለ አሉታዊ ስሜት እንዲያድርብኝ የሚያደርግ አሳማኝ ምክንያት አለኝ?’

      • እንደ ጭንቀት፣ ንዴት ወይም ቂም ያሉ አሉታዊ ስሜቶች እስክትዝል ድረስ እንዲቆጣጠሩህ አትፍቀድ። ከዚህ ይልቅ ኃይልህን ትርጉም ያለው ነገር ለማከናወን ተጠቀምበት።c

      ዋናው ነጥብ፦ ብዙውን ጊዜ አሉታዊ ስሜት እንዲያድርብን የሚያደርገው ያጋጠመን ሁኔታ ሳይሆን ለተፈጠረው ሁኔታ ያለን አመለካከት ነው።

      a አንዳንድ አሉታዊ ስሜቶች የባለሙያ እርዳታ በሚሹ የጤና ችግሮች ሳቢያ የሚከሰቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ንቁ! አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም። እያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት፣ ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ መመዘን ይኖርበታል።

      b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ መዝሙሮች ዳዊት በጽሑፍ ያሰፈራቸው የራሱ ጸሎቶች ናቸው።

      c ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌ 1, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ጭንቀትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ተከታታይ ርዕስ ተመልከት።

  • ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?
    ንቁ!—2015 | ሐምሌ
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?

      ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?

      ጀልባውን ተረጋግቶ እየቀዘፈ ያለ ሰው

      “ኑሮ እንዳያያዙ ነው” የሚል አባባል አለ። በዛሬው ጊዜ ሁሉም ነገር የተመቻቸለት አንድም ሰው የለም። ሕይወትህን መቆጣጠር ችለሃል የሚባለው ያለህበትን ሁኔታ አምነህ የምትቀበልና ሁኔታህ የሚፈቅድልህን ያህል ብቻ የምታደርግ ከሆነ ነው። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነህም ሕይወትህን በተወሰነ መጠን መቆጣጠር ከቻልክ ጥሩ ነው። ሁኔታዎችህ እያደር ከተሻሻሉ ደግሞ እሰየው ነው። ይበልጥ አስደሳች የሆነው ግን ወደፊት የሚጠብቅህ ነገር ነው።

      መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰው ሕይወቱን በሚፈልገው መንገድ መምራት የሚችልበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጽ ተስፋ ይዟል። በዚያን ጊዜ ሰዎች ተስፋ አስቆራጭ ከሆኑ ሁኔታዎች፣ በየዕለቱ ከሚደርሱባቸው ጫናዎችና ከአሉታዊ ስሜቶች ነፃ ሆነው አርኪ ሕይወት ይመራሉ። (ኢሳይያስ 65:21, 22) መጽሐፍ ቅዱስ ‘እውነተኛው ሕይወት’ በማለት የሚጠራው ይህንን ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:19

      “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። እነሱ በሠሩት ቤት ሌላ ሰው አይኖርም፤ እነሱ የተከሉትንም ሌላ ሰው አይበላውም። የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፤ የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።” —ኢሳይያስ 65:21, 22

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ