-
በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ክቡር የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓትመጠበቂያ ግንብ—2006 | ጥቅምት 15
-
-
በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ክቡር የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት
“በቃና ከተማ ሰርግ ነበር፤ . . . ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ተጠርተው ነበር።”—ዮሐንስ 2:1, 2
1. ኢየሱስ በቃና እንደነበረ የሚገልጸው ዘገባ ምን ያስገነዝበናል?
ኢየሱስም ሆነ እናቱ ማርያም እንዲሁም አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚፈጸሙ ክቡር የሆኑ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ደስታ እንደሚያስገኙ ያውቁ ነበር። እንዲያውም ክርስቶስ በአንድ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጀመሪያውን ተአምር በመፈጸም ዝግጅቱ ለየት ያለና አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል። (ዮሐንስ 2:1-11) አንተም፣ ተጋብተው ይሖዋን በደስታ ማምለክ በሚፈልጉ ክርስቲያኖች ሠርግ ላይ ተገኝተህ በሥነ ሥርዓቱ ተደስተህ ይሆናል። ወይም አንተ ራስህ ሠርግህ እንደዚህ ዓይነት እንዲሆን ትመኝ አሊያም የአንድ ወዳጅህ የሠርግ ዝግጅት የተሳካ እንዲሆን ልትረዳው ትፈልግ ይሆናል። እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳህ ይችላል?
2. መጽሐፍ ቅዱስ የሠርግ ሥነ ሥርዓትን አስመልክቶ ምን መረጃ ይዟል?
2 ክርስቲያኖች አንድ ወንድና አንዲት ሴት ትዳር ለመመሥረት በሚፈልጉበት ወቅት አምላክ በመንፈሱ አነሳሽነት ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው ይገነዘባሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያኖች ሠርግ ምን ሊመስል እንደሚገባ የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ አይሰጥም። ይህም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም የሰዎች ባሕልና መንግሥት የሚያወጣው ሕግ ከቦታ ቦታ እንዲሁም ከዘመን ዘመን የተለያየ ሊሆን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ዛሬ እንደምንመለከተው ዓይነት የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አልነበረም። በሠርጉ ዕለት ሙሽራው፣ ሙሽራዋን ወደ ራሱ ቤት አሊያም ወደ አባቱ ቤት ይወስዳታል። (ዘፍጥረት 24:67፤ ኢሳይያስ 61:10፤ ማቴዎስ 1:24) ሙሽራው በይፋ የሚወስደው ይህ እርምጃ እንደ ሠርግ ይቆጠራል፤ ዛሬ በአብዛኞቹ ሠርጎች ላይ የምናየው ዓይነት ሥነ ሥርዓት አልነበረም።
3. ኢየሱስ በቃና ለየትኛው ዝግጅት አስተዋጽኦ አድርጓል?
3 በእስራኤላውያን ዘንድ እንደ ሠርግ የሚቆጠረው ይህ ድርጊት ነበር። ከዚያ በኋላ በዮሐንስ 2:1 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ዓይነት ድግስ ይደረግ ይሆናል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን ጥቅስ “በቃና ከተማ ሰርግ ነበር” ብለው ተርጉመውታል። ሆኖም በኩረ ጽሑፉ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ቃል በሌሎች ቦታዎች ‘የሰርግ ድግስ’ ወይም ‘የሰርግ ግብዣ’ ተብሎ ይበልጥ ተስማሚ በሆነ መንገድ ተተርጉሟል።a (ማቴዎስ 22:2-10፤ 25:10፤ ሉቃስ 14:8 የ1980 ትርጉም) ከዘገባው በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ከአይሁዳውያን ሠርግ ጋር በተያያዘ ተዘጋጅቶ በነበረ አንድ ድግስ ላይ የተገኘ ሲሆን ግብዣው የበለጠ አስደሳች እንዲሆንም አስተዋጽኦ አድርጓል። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ የነበረ ሠርግ የሚያካትታቸው ነገሮች በዛሬው ጊዜ ከተለመደው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የተለዩ እንደሆኑ ልብ ልንል ይገባል።
4. አንዳንድ ክርስቲያኖች የጋብቻቸው ሥነ ሥርዓት ምን ዓይነት እንዲሆን ይመርጡ ይሆናል? ለምንስ?
4 በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ ለማግባት የሚፈልጉ ክርስቲያኖች አንዳንድ ሕጋዊ ደንቦችን ማሟላት ይኖርባቸዋል። ተጋቢዎቹ እነዚህን ደንቦች ካሟሉ በኋላ ሕጋዊ ተቀባይነት ባለው በማንኛውም መንገድ መጋባት ይችላሉ። ይህም መንግሥት የማጋባት ሥልጣን በሰጠው አንድ ዳኛ፣ ሹም አሊያም ሃይማኖታዊ ተወካይ አማካኝነት የሚፈጸም ቀለል ያለ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች በዚህ መንገድ ለመጋባት የሚመርጡ ሲሆን በሠርጋቸው ላይ ጥቂት ዘመዶቻቸው ወይም ክርስቲያን ወዳጆቻቸው ሕጋዊ ምሥክር ሆነው እንዲገኙ አሊያም በዚህ አስደሳች ወቅት ተገኝተው የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ ለመጋበዝ ይፈልጉ ይሆናል። (ኤርምያስ 33:11፤ ዮሐንስ 3:29) ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ሰፊ እቅድ የሚያስፈልገውና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ትልቅ የሠርግ ድግስ ከማዘጋጀት ይልቅ ለቅርብ ወዳጆቻቸው አነስ ያለ ግብዣ ያደርጉ ይሆናል። በዚህ ረገድ የግል ምርጫችን ምንም ይሁን ምን፣ ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከእኛ የተለየ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል።—ሮሜ 14:3, 4
5. በርካታ ክርስቲያኖች የጋብቻ ንግግር እንዲደረግላቸው የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ንግግሩስ ምን ይዟል?
5 አብዛኞቹ ክርስቲያን ተጋቢዎች በሠርጋቸው ዕለት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር እንዲደረግላቸው ይፈልጋሉ።b የጋብቻ መሥራች ይሖዋ መሆኑን እንዲሁም ትዳር ስኬታማና አስደሳች እንዲሆን የሚረዳ ምክር በቃሉ ውስጥ እንዳሰፈረ ይገነዘባሉ። (ዘፍጥረት 2:22-24፤ ማርቆስ 10:6-9፤ ኤፌሶን 5:22-33) ከዚህም በላይ አብዛኞቹ ተጋቢዎች ክርስቲያን ወዳጆቻቸውና ዘመዶቻቸው በዚህ ዕለት የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ሆኖም ከሕግ ጋር በተያያዙ ሁኔታዎችና ሥነ ሥርዓቶች እንዲሁም በአካባቢው ልማድ ረገድ ያሉትን በርካታ ልዩነቶች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል? ይህ የጥናት ርዕስ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉትን ሁኔታዎች ይመረምራል። አንዳንዶቹ አንተ ከምታውቃቸው ወይም በአካባቢህ ከሚከናወኑት ሥርዓቶች በጣም የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ቢሆን ግን በዚህ ርዕስ ውስጥ ለአምላክ አገልጋዮች አስፈላጊ የሆኑና በብዙ ቦታዎች የሚሠሩ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ወይም ሁኔታዎችን ልታስተውል ትችላለህ።
ጋብቻ ክቡር እንዲሆን ሕጋዊ መሆን አለበት
6, 7. ከጋብቻ ጋር ለተያያዙ ሕግ ነክ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
6 የጋብቻ መሥራች ይሖዋ ቢሆንም ሰብዓዊ መንግሥታት ተጋቢዎቹ የሚወስዱትን እርምጃ በተወሰነ መልኩ የመቆጣጠር ሥልጣን አላቸው። ይህ መሆኑም ተገቢ ነው። ኢየሱስ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” ብሏል። (ማርቆስ 12:17) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።”—ሮሜ 13:1፤ ቲቶ 3:1
7 በብዙ አገሮች ውስጥ አንድ ሰው ለማግባት የሚያስፈልገውን መሥፈርት ያሟላ መሆን አለመሆኑን የሚወስነው ቄሳር ማለትም መንግሥት ሥልጣን የሰጠው አካል ነው። በዚህም የተነሳ በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ለማግባት ነጻ የሆኑ ሁለት ክርስቲያኖች ለመጋባት ሲወስኑ ጋብቻን በተመለከተ የወጣውን የአገራቸውን ሕግ ያከብራሉ። ይህም ፈቃድ ማግኘትን፣ ጋብቻ ለማስፈጸም መንግሥት ሥልጣን በሰጠው አካል አማካኝነት መጋባትንና ምናልባትም ይህ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ጋብቻውን ማስመዝገብን ይጨምር ይሆናል። አውግስጦስ ቄሳር ሕዝቡ “እንዲመዘገብ” ባዘዘ ወቅት ማርያምና ዮሴፍ ትእዛዙን አክብረው “ለመመዝገብ” ወደ ቤተልሔም ሄደዋል።—ሉቃስ 2:1-5
8. የይሖዋ ምሥክሮች የትኛውን ልማድ አይከተሉም? ለምንስ?
8 ሁለት ክርስቲያኖች ሕጋዊ በሆነና ተቀባይነት ባለው መንገድ ትዳር ሲመሠርቱ ይህ ጥምረት በአምላክ ፊት የጸና ይሆናል። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች የተለያዩ ሕጋዊ ሥነ ሥርዓቶችን በመፈጸም የጋብቻ ሥርዓቱን አይደግሙትም፤ እንዲሁም 25ኛ ወይም 50ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን ሲያከብሩ በድጋሚ የጋብቻ መሐላ አይፈጽሙም። (ማቴዎስ 5:37) (አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ቄስ ተጋቢዎቹን በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ካላጋባቸው ወይም ባልና ሚስት መሆናቸውን በይፋ ካላሳወቀ በስተቀር ጋብቻው ተቀባይነት እንደማይኖረው በመናገር በመንግሥት ሕግ የጸደቀውን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አይቀበሉም።) በበርካታ አገሮች ውስጥ አንድ የይሖዋ ምሥክር የጋብቻ ሥነ ሥርዓት እንዲያስፈጽም መንግሥት ሥልጣን ይሰጠዋል። ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ የማጋባት ሥልጣን የተሰጠው ሰው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የጋብቻ ንግግር ካቀረበ በኋላ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን ሊያከናውን ይችላል። የመንግሥት አዳራሽ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው እውነተኛ አምልኮ የሚያካሂዱበት ቦታ ሲሆን ይሖዋ ያቋቋመውን የጋብቻ ዝግጅት በተመለከተ ንግግር ለማቅረብ ተስማሚ የሆነ ቦታ ነው።
9. (ሀ) በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚጋቡ ክርስቲያኖች ምን ሊወስኑ ይችላሉ? (ለ) ከሠርጉ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ሽማግሌዎች ምን ኃላፊነት አለባቸው?
9 በሌሎች አገሮች ደግሞ ተጋቢዎቹ እንደ ማዘጋጃ ቤት ባለ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ወይም በክብር መዝገብ ሹም ፊት (የማጋባት ሥልጣን የተሰጠው አካል) እንዲጋቡ ሕጉ ይደነግጋል። አብዛኛውን ጊዜ ክርስቲያኖች ይህንን ሕጋዊ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ በዚያው ዕለት ወይም በማግሥቱ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የጋብቻ ንግግር እንዲደረግላቸው ይፈልጋሉ። (እነዚህ ክርስቲያኖች ከዚያ በኋላ በአምላክም ሆነ በሰው ፊት እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ዘንድ ባልና ሚስት በመሆናቸው በሕግ በተፈራረሙበት ቀንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር በሚቀርብበት ቀን መካከል ረዘም ያለ ጊዜ እንዲያልፍ አያደርጉም።) በማዘጋጃ ቤት ወይም በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚጋቡ ክርስቲያኖች በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ንግግር እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ከሆነ አስቀድመው የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ አባላት ከሆኑት ሽማግሌዎች ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሽማግሌዎች ተጋቢዎቹ ጥሩ ስም ያላቸው መሆኑን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ሠርጉ የሚከናወንበት ሰዓት በአዳራሹ ከሚደረጉ መደበኛ ስብሰባዎችና ሌሎች ፕሮግራሞች ጋር የማይጋጭ መሆኑን ማጣራት ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 14:33, 40) ከዚህም በላይ ተጋቢዎቹ የመንግሥት አዳራሹን ለጋብቻቸው ሥነ ሥርዓት ለማዘጋጀት ከጠየቁ ሽማግሌዎቹ ይህንንም ይመለከታሉ፤ አዳራሹ ለዚህ ዓላማ ጥቅም ላይ እንደሚውል ማስታወቂያ መንገር ያስፈልግ እንደሆነም ይወስናሉ።
10. ጥንዶቹ በሕግ ተጋብተው ከሆነ የጋብቻ ንግግሩ ምን መልክ ይኖረዋል?
10 የጋብቻ ንግግሩን የሚያቀርበው ሽማግሌ ንግግሩ ወዳጃዊ ስሜት የሚንጸባረቅበት፣ በመንፈሳዊ የሚያጠናክርና ክብር ያለው እንዲሆን ለማድረግ ይጥራል። ተጋቢዎቹ ከላይ እንደተገለጸው አስቀድመው በሕግ ፊት ተጋብተው ከሆነ፣ በቄሳር ሕግ መሠረት ባልና ሚስት መሆናቸውን ንግግሩን የሚያቀርበው ሽማግሌ በግልጽ ይናገራል። በሕግ ፊት በተጋቡበት ወቅት የጋብቻ መሐላ ካልፈጸሙ ንግግሩ በሚቀርብበት ጊዜ ይህንን ለማድረግ ይፈልጉ ይሆናል።c በሌላ በኩል ደግሞ አዲሶቹ ተጋቢዎች በሕግ ፊት ሲጋቡ መሐላ የፈጸሙ ቢሆንም በይሖዋና በጉባኤው ፊት እንደገና የጋብቻ መሐላ መፈጸም ከፈለጉ፣ ቀደም ብለው ‘እንደተጣመሩ’ በሚያሳይ መንገድ መሐላውን ማድረግ ይችላሉ።—ማቴዎስ 19:6፤ 22:21
11. በአንዳንድ ቦታዎች ጋብቻ የሚከናወነው እንዴት ነው? ይህስ በጋብቻ ንግግሩ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?
11 በአንዳንድ ቦታዎች ሕጉ፣ ተጋቢዎቹ መንግሥት የማጋባት ሥልጣን በሰጠው አካል ፊትም ሆነ በሌላ በማንኛውም ዓይነት ሥርዓት እንዲጋቡ አይጠብቅባቸው ይሆናል። ጋብቻው የሚፈጸመው ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀውን ቅጽ ሞልተው ሥልጣን ለተሰጠው አካል ሲያቀርቡ ነው። ከዚያም ይህ ቅጽ በመዝገብ ቤት ይቀመጣል። በዚህ ቅጽ ላይ የተመዘገበው ዕለት የጋብቻቸው ቀን ስለሚሆን ከዚያ በኋላ እንደ ባልና ሚስት ይቆጠራሉ። ከላይ እንደተገለጸው በዚህ መንገድ የተጋቡ ጥንዶች ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የጋብቻ ንግግር በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ እንዲደረግላቸው ይፈልጉ ይሆናል። ንግግሩን እንዲያቀርብ የተመረጠው በመንፈሳዊ የጎለመሰ ወንድም፣ ጥንዶቹ ጋብቻቸው ስለተመዘገበ ባልና ሚስት መሆናቸውን በሥርዓቱ ላይ ለተገኙት በሙሉ ይገልጻል። የጋብቻ መሐላ የሚፈጽሙ ከሆነ አንቀጽ 10ና የግርጌ ማስታወሻው ላይ የሰፈረውን መመሪያ ይከተላሉ። በመንግሥት አዳራሹ የተገኙት ሰዎች የተጋቢዎቹ ደስታ ተካፋይ ከመሆናቸውም በላይ በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርቶ ከሚቀርበው ምክር ይጠቀማሉ።—ማሕልየ መሓልይ 3:11
ባሕላዊ ጋብቻና በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈጸም ጋብቻ
12. ባሕላዊ ጋብቻ ምንድን ነው? እንዲህ ያለው ጋብቻ ከተፈጸመ በኋላ ምን ማድረጉ የተሻለ ነው?
12 በአንዳንድ አገሮች ጋብቻ የሚፈጸመው በባሕላዊ ሥርዓት (ወይም በጎሳው ልማድ) መሠረት ነው። ይህ ዓይነቱ ጋብቻ ሁለት ሰዎች ሳይጋቡ አብረው ከሚኖሩበት ሁኔታ የተለየ ነው፤ እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች ተቀባይነት ቢኖረውም ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ ጋብቻ እንደሆነ ተደርጎ የማይቆጠረውን ልማድ (common-law marriage) የሚያመለክትም አይደለም።d እዚህ ላይ የተገለጸው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ባለው የጎሳው ወይም የአካባቢው ባሕል መሠረት የሚከናወን ጋብቻ ነው። ይህም ጥሎሽ መቀበልን ወይም መስጠትን ይጨምር ይሆናል፤ በዚህ መልኩ ጥንዶቹ በሕጉም ሆነ በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ባልና ሚስት ይሆናሉ። መንግሥት እንደዚህ ያለውን ባሕላዊ ጋብቻ ተቀባይነት ያለው፣ ሕጋዊና የጸና እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። አብዛኛውን ጊዜ ከዚህ ዓይነቱ ሥርዓት በኋላ ይህንን ባሕላዊ ጋብቻ ማስመዝገብ ይቻላል፤ ባልና ሚስቱ እንዲህ ሲያደርጉ ሕጋዊ የጋብቻ የምሥክር ወረቀት ይሰጣቸዋል። ጋብቻቸው መመዝገቡ፣ ለባልና ሚስቱ ወይም ከጊዜ በኋላ ባሏ ቢሞት ለሚስትየው እንዲሁም ወደፊት ለሚወለዱ ልጆች ጥበቃ ይሆናል። ጉባኤው እንዲህ ባለ ባሕላዊ መንገድ የሚጋቡ ሰዎች በተቻለ ፍጥነት ጋብቻቸውን እንዲያስመዘግቡ ያሳስባቸዋል። በሙሴ ሕግ ሥር ሰዎች ሲጋቡ እንዲሁም ልጆች ሲወለዱ ይመዘገብ እንደነበረ ማወቁ ትኩረት የሚስብ ነው።—ማቴዎስ 1:1-16
13. ባሕላዊ ጋብቻ ከተፈጸመ በኋላ የጋብቻ ንግግር የሚቀርብ ከሆነ ምን ማድረጉ ተገቢ ነው?
13 በዚህ ዓይነት ባሕላዊ ሥርዓት የተጣመሩት ተጋቢዎች ይህ ሕጋዊ ጋብቻ ሲከናወን ባልና ሚስት ይሆናሉ። ከላይ እንደተገለጸው እንደዚህ ባለው ሕጋዊ መንገድ የተጋቡ ክርስቲያኖች በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የጋብቻ ንግግር ተደርጎላቸው የጋብቻ መሐላ ለመፈጸም ይፈልጉ ይሆናል። እንዲህ የሚደረግ ከሆነ ንግግሩን የሚያቀርበው ወንድም እነዚህ ሰዎች በቄሳር ሕግ መሠረት ቀደም ሲል እንደተጋቡ ይገልጻል። እንዲህ ያለው የጋብቻ ንግግርም የሚቀርበው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሕግ ተቀባይነት ያለው ባሕላዊ ወይም የጎሳ ጋብቻ የሚፈጸመውም ሆነ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ንግግር የሚቀርበው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እነዚህ ሁለት ክንውኖች በተቻለ መጠን በአንድ ቀን ቢደረጉ ይመረጣል። ካልሆነ ግን ቀኑ ብዙም ባይራራቅ ጥሩ ነው፤ ይህ መሆኑ የክርስቲያኖች ጋብቻ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተከበረ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።
14. ባሕላዊውንም ሆነ በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚደረገውን ጋብቻ መፈጸም በሚቻልባቸው አገሮች አንድ ክርስቲያን ምን ሊያደርግ ይችላል?
14 ባሕላዊ ጋብቻ እንደ ሕጋዊ ጋብቻ በሚቆጠርባቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ በክብር መዝገብ ሹም ፊት ጋብቻን ለመፈጸም የሚያስችል ተጨማሪ ዝግጅትም አለ። በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈጸመው ጋብቻ ብዙውን ጊዜ የሚከናወነው የመንግሥት ተወካይ በተገኘበት ሲሆን ተጋቢዎቹ የጋብቻ መሐላ ይፈጽማሉ፤ እንዲሁም በክብር መዝገብ ላይ ይፈርማሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች በባሕላዊ ሥርዓት ከመጋባት ይልቅ በዚህ መንገድ ለመጋባት ይመርጣሉ። ሁለቱም የጋብቻ ሥርዓቶች ከሕግ አንጻር ተቀባይነት ያላቸው እስከሆኑ ድረስ ሁለቱንም በአንድነት ለመፈጸም የሚያስገድድ ሕግ የለም። የጋብቻ ንግግርንና መሐላን በተመለከተ በአንቀጽ 9 እና 10 ላይ የቀረበው ሐሳብ እዚህ ላይም ይሠራል። ዋናው ነገር ጥንዶቹ በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ክቡር በሆነ መንገድ መጋባታቸው ነው።—ሉቃስ 20:25፤ 1 ጴጥሮስ 2:13, 14
ጋብቻችሁ ክቡር እንደሆነ ይቀጥል
15, 16. ጋብቻው ክብር ያለው እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
15 አንድ የፋርስ ንጉሥ በትዳሩ ውስጥ ችግር በገጠመው ወቅት ምሙካ የተባለው የንጉሡ ዋና አማካሪ ‘ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን እንዲያከብሩ’ የሚረዳ ጠቃሚ ምክር ሰጠ። (አስቴር 1:20) የክርስቲያኖችን ትዳር በተመለከተ ማንኛውም ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲህ ያለ አዋጅ ማስነገር አያስፈልገውም፤ ምክንያቱም ሚስቶች ባሎቻቸውን ማክበር ይፈልጋሉ። በተመሳሳይም ክርስቲያን ባሎች ሚስቶቻቸውን ያከብሯቸዋል እንዲሁም ያመሰግኗቸዋል። (ምሳሌ 31:11, 30፤ 1 ጴጥሮስ 3:7) ትዳራችንን ለማክበር ተጋብተን ረጅም ዓመት መቆየት አያስፈልገንም። እንዲህ ያለው አክብሮት ገና ከመጀመሪያው ይኸውም ጋብቻው ከተፈጸመበት ቀን አንስቶ መታየት ይኖርበታል።
16 የሠርጉ ቀን ክብር ያለው እንዲሆን ማድረግ የሚገባቸው ባልና ሚስቱ ብቻ አይደሉም። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ የጋብቻ ንግግር የሚያቀርብ ከሆነ ይህም ክብር ባለው መንገድ ሊደረግ ይገባል። ተናጋሪው ፊቱን ወደ ተጋቢዎቹ አዙሮ በእነርሱ ላይ ያተኮረ ንግግር ማቅረብ ይኖርበታል። ተናጋሪው ለተጋቢዎቹ አክብሮት በማሳየት በንግግሩ ላይ ቀልድ ወይም በአካባቢው የተለመደ ተረት አይናገርም። ተጋቢዎቹንም ሆነ አድማጮቹን ሊያሳፍሩ የሚችሉ ስለ ተጋቢዎቹ የግል ሁኔታ የሚገልጹ ሐሳቦች መሰንዘር አይኖርበትም። ከዚህ ይልቅ የጋብቻ መሥራች የሆነውን አምላክና እርሱ የሰጠውን የላቀ ምክር ጎላ አድርጎ በመግለጽ ንግግሩን ሞቅ ባለና በሚያንጽ መንገድ ሊያቀርበው ይገባል። በእርግጥም ሽማግሌው የጋብቻ ንግግሩን በሚያስከብር መንገድ ማቅረቡ የጋብቻው ሥነ ሥርዓት ለይሖዋ አምላክ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።
17. የክርስቲያኖች ሠርግ በሕጉ መሠረት የሚከናወነው ለምንድን ነው?
17 በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ ሕጋዊ ጋብቻን በተመለከተ በርካታ ነጥቦችን ሳታስተውል አልቀረህም። አንዳንዶቹ ነጥቦች አንተ በምትኖርበት አካባቢ አይሠሩ ይሆናል። ያም ቢሆን ግን የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጓቸው የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ለአገራቸው ሕግ ማለትም ቄሳር ለሚያወጣቸው ደንቦች አክብሮት እንዳለን የሚያሳዩ መሆናቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። (ሉቃስ 20:25) ጳውሎስ “ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን፣ . . . ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ” በማለት አሳስቧል። (ሮሜ 13:7) በእርግጥም ክርስቲያኖች አምላክ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ላስቀመጠው ዝግጅት አክብሮት እንዳላቸው ከሠርጉ ቀን ጀምሮ ማሳየታቸው ተገቢ ነው።
18. አንዳንዶች ከጋብቻቸው ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ለማድረግ የሚመርጡት የትኛው ዝግጅት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል? ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሐሳብ የምናገኘው ከየት ነው?
18 አብዛኛውን ጊዜ በክርስቲያኖች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ግብዣ ወይም ድግስ ይኖራል። ኢየሱስ እንዲህ ባለ ግብዣ ላይ ተገኝቶ እንደነበረ አስታውስ። እንዲህ ዓይነት ግብዣ የሚዘጋጅ ከሆነ፣ ዝግጅቱ ለአምላክ ክብር የሚያመጣና ተጋቢዎቹንም ሆነ ክርስቲያን ጉባኤን የሚያስመሰግን እንዲሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው ምክር የሚረዳን እንዴት ነው? የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው።e
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
b በይሖዋ ምሥክሮች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ “በአምላክ ፊት ክብር ያለው ጋብቻ” የሚል ርዕስ ያለው የ30 ደቂቃ የጋብቻ ንግግር ይቀርባል። ንግግሩ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? ከሚለው መጽሐፍና ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች ላይ የተወሰዱ ጠቃሚ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ይዟል። እንዲህ ያለው ንግግር ለተጋቢዎቹም ሆነ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለሚገኙት ሁሉ ጠቃሚ ነው።
c የአገሩ ሕግ ከዚህ የተለየ መመሪያ እስከሌለው ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን የሚያስከብረውን የሚከተለውን የጋብቻ መሐላ ይጠቀማሉ። ሙሽራው እንዲህ ይላል:- “እኔ [የሙሽራው ስም] ሁለታችንም በአምላክ የጋብቻ ሥርዓት ሥር በዚች ምድር ላይ በሕይወት አብረን እስከኖርን ድረስ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ለክርስቲያን ባሎች በተሰጠው መለኮታዊ ሕግ መሠረት አንቺን [የሙሽራዋ ስም] ልወድሽና ልንከባከብሽ ሚስቴ አድርጌ ወስጄሻለሁ።” ሙሽራዋ እንዲህ ትላለች:- “እኔ [የሙሽራዋ ስም] ሁለታችንም በአምላክ የጋብቻ ሥርዓት ሥር በዚች ምድር ላይ በሕይወት አብረን እስከኖርን ድረስ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ለክርስቲያን ሚስቶች በተሰጠው መለኮታዊ ሕግ መሠረት አንተን [የሙሽራው ስም] ልወድህ፣ ልንከባከብህና በጥልቅ ላከብርህ ባሌ አድርጌ ወስጄሃለሁ።”
d የግንቦት 1, 1962 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 287 (እንግሊዝኛ) እንደዚህ ስላለው ጋብቻ ሐሳብ ይሰጣል።
e በተጨማሪም “የሠርጋችሁ ቀን የሚያስደስትና የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ” የሚለውን በገጽ 28 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• ከጋብቻ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ሕጉም ሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች ለሚሰጡት መመሪያ ትኩረት መስጠት የሚገባን ለምንድን ነው?
• ሁለት ክርስቲያኖች በክብር መዝገብ ሹም ፊት ከተጋቡ ከዚያ ብዙም ሳይቆዩ ምን ለማድረግ ሊወስኑ ይችላሉ?
• የጋብቻ ንግግር የሚቀርበው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጥንት እስራኤላውያን ሠርግ ላይ ሙሽራው ሙሽራይቱን ወደ ራሱ ወይም ወደ አባቱ ቤት ይወስዳት ነበር
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች በባሕላዊ ሥርዓት ከተጋቡ በኋላ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የጋብቻ ንግግር እንዲደረግላቸው ይፈልጉ ይሆናል
-
-
እምነትህ በአኗኗርህ በግልጽ ይታይመጠበቂያ ግንብ—2006 | ጥቅምት 15
-
-
እምነትህ በአኗኗርህ በግልጽ ይታይ
“ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው።”—ያዕቆብ 2:17
1. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለእምነትም ሆነ ለሥራ ትኩረት የሰጡት ለምን ነበር?
በጥቅሉ ሲታይ የጥንት ክርስቲያኖች እምነታቸውን በአኗኗራቸው በግልጽ ያሳዩ ነበር። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ [አትሁኑ]” በማለት ሁሉንም ክርስቲያኖች አሳስቧል። አክሎም “ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው” ብሏል። (ያዕቆብ 1:22፤ 2:26) ይህንን ደብዳቤ ከጻፈ ከ35 ዓመታት ገደማ በኋላም እንኳ በርካታ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ተገቢ በሆኑ ሥራዎች ማሳየታቸውን ቀጥለው ነበር። የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶች እንዲህ አላደረጉም። ኢየሱስ በሰምርኔስ ያለውን ጉባኤ ቢያመሰግነውም በሰርዴስ ባለው ጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን ብዙዎቹን ክርስቲያኖች “ሥራህን ዐውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል” ብሏቸዋል።—ራእይ 2:8-11፤ 3:1
2. ክርስቲያኖች እምነታቸውን በተመለከተ ራሳቸውን ምን ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል?
2 በዚህም የተነሳ ኢየሱስ የሰርዴስ ክርስቲያኖች ለክርስቲያናዊው እውነት የነበራቸውን የመጀመሪያ ፍቅር በሥራ እንዲገልጹና በመንፈሳዊ ንቁ እንዲሆኑ አበረታቷቸዋል፤ ይህ ምክር ለሰርዴስ ጉባኤ ብቻ ሳይሆን ከጊዜ በኋላ እነዚህን ቃላት ለሚያነቡ ሁሉ ይሠራል። (ራእይ 3:2, 3) እያንዳንዳችን እንዲህ በማለት ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን:- ‘እኔስ ስለ ተግባሬ ምን ማለት እችላለሁ? ከስብከቱ ሥራም ሆነ ከጉባኤ ስብሰባዎች ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ በሌላቸው ጉዳዮችም ጭምር የማደርጋቸው ነገሮች እምነቴን በሥራ ለማሳየት የምችለውን ያህል እየጣርኩ መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ?’ (ሉቃስ 16:10) ይህንን ማድረግ የምንችልባቸው የተለያዩ የሕይወት ዘርፎች ቢኖሩም በዚህ ርዕስ ሥር አንዱን ይኸውም ግብዣን እንመልከት፤ አብዛኛውን ጊዜ ከክርስቲያኖች ሠርግ ጋር በተያያዘ የሚዘጋጁት ግብዣዎችም በዚህ ርዕስ ውስጥ ይካተታሉ።
አነስ ያሉ ግብዣዎች
3. መጽሐፍ ቅዱስ ግብዣን በተመለከተ ምን ይላል?
3 አብዛኞቻችን ደስተኛ የሆኑ ክርስቲያኖች በሚያደርጉት ግብዣ ላይ ስንጠራ ደስ ይለናል። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹም ደስ እንዲላቸው የሚፈልግ “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ሰሎሞን የሚከተለውን ሐቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲያሰፍር ያደረገውም እርሱ ነው:- “ለሰው፣ ከፀሓይ በታች ከመብላት፣ ከመጠጣትና ከመደሰት ሌላ የተሻለ ነገር ስለሌለ፣ በሕይወት ደስ መሰኘት መልካም ነው አልሁ።” (መክብብ 3:1, 4, 13፤ 8:15) ቤተሰብ አንድ ላይ ተሰባስቦ ሲመገብ ወይም እውነተኛ አምላኪዎች በሚሰባሰቡበት አነስተኛ ግብዣ ላይ እንዲህ ያለ ደስታ ይገኛል።—ኢዮብ 1:4, 5, 18፤ ሉቃስ 10:38-42፤ 14:12-14
4. ግብዣ የሚያዘጋጅ ግለሰብ ሊያስብበት የሚገባው ጉዳይ የትኛው ነው?
4 እንዲህ ያለ ግብዣ እያዘጋጀህ ከሆነና ሥነ ሥርዓቱን በተመለከተ ኃላፊነቱን የምትወስደው አንተ ከሆንክ ዝግጅቱን በጥንቃቄ ልታስብበት ይገባል። የጋበዝካቸው ወንድሞች ጥቂት በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ነው። (ሮሜ 12:13) ‘ከሰማይ በሆነችው ጥበብ’ ለመመራትና “ሁሉም በአግባብ” እንዲከናወን ለማድረግ እንደምትፈልግ ግልጽ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:40፤ ያዕቆብ 3:17) ሐዋርያው ጳውሎስ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። . . . መሰናክል አትሁኑ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:31, 32) በዚህ ረገድ ትኩረት ልናደርግባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? እነዚህን ጉዳዮች አስቀድሞ መመርመሩ አንተም ሆንክ የጋበዝካቸው እንግዶች እምነታችሁን በተግባር እንድታሳዩ ይረዳችኋል።—ሮሜ 12:2
ግብዣው ምን ዓይነት ሊሆን ይችላል?
5. ጋባዡ የአልኮል መጠጥ ማቅረብን ወይም ሙዚቃን በተመለከተ በጥንቃቄ ማሰብ የሚገባው ለምንድን ነው?
5 በርካታ ጋባዦች የአልኮል መጠጥ ማቅረብ ያስፈልጋቸው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን አስፈልጓቸዋል። ግብዣው አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ የአልኮል መጠጥ የግድ አስፈላጊ አይደለም። ኢየሱስ በአንድ ወቅት ዳቦና ዓሣ በመባረክ ወደ እርሱ የመጡ ብዙ ሰዎችን እንደመገበ አስታውስ። ክርስቶስ በተአምራዊ መንገድ የወይን ጠጅ ማቅረብ እንደሚችልም እናውቃለን፤ ሆኖም ዘገባው እንዲህ እንዳደረገ አይገልጽም። (ማቴዎስ 14:14-21) አንተ ግን በግብዣህ ላይ የአልኮል መጠጥ ለማቅረብ ከወሰንክ በልክ አድርገው፤ የአልኮል መጠጥ የማይፈልጉ ሰዎችን ለማስደሰት ደግሞ ሌሎች አማራጮች እንዲኖሩ አድርግ። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3, 8፤ 5:23፤ 1 ጴጥሮስ 4:3) ማንም ሰው ቢሆን ‘እንደ እባብ ሊናደፍ’ የሚችለውን የአልኮል መጠጥ እንዲወስድ ግፊት እንደተደረገበት እንዲሰማው ከማድረግ ተቆጠብ። (ምሳሌ 23:29-32) ሙዚቃን ወይም ዘፈንን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? በግብዣው ላይ ሙዚቃ የሚኖር ከሆነ የሙዚቃውን ምትም ሆነ ግጥሙን ግምት ውስጥ በማስገባት ዘፈኖቹን በጥንቃቄ እንደምትመርጥ ጥርጥር የለውም። (ቈላስይስ 3:8፤ ያዕቆብ 1:21) በርካታ ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ጣዕመ ዜማዎች በማጫወት ወይም እነዚህን መዝሙሮች በአንድ ላይ በመዘመር አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ እንደሚቻል ተገንዝበዋል። (ኤፌሶን 5:19, 20) ከዚህም በላይ የሙዚቃው ድምፅ በጣም ከፍ ብሎ አስደሳች ጭውውት ለማድረግ እንቅፋት እንዳይፈጥር ወይም ጎረቤት እንዳይረብሽ መጠኑን መቆጣጠር ያስፈልጋል።—ማቴዎስ 7:12
6. አንድ ጋባዥ በግብዣው ላይ በሚደረገው ጭውውት ወይም በሌሎች ጉዳዮች ረገድ እምነቱ ሕያው እንደሆነ ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?
6 ክርስቲያኖች በግብዣ ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስተው ሊጫወቱ፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አንድ ጽሑፍ ሊያነቡ ወይም አስደሳች ተሞክሮዎችን ሊያወሩ ይችላሉ። ውይይቱ መሥመሩን ከሳተ ጋባዡ በዘዴ ሊያስተካክለው ይችላል። ከዚህም በላይ ጭውውቱን አንድ ሰው ብቻ እንዳይቆጣጠረው ንቁ ሆኖ መከታተል ይኖርበታል። ጋባዡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደተፈጠረ ከተሰማው ጥበብ በተሞላበት መንገድ የውይይቱን አቅጣጫ ማስለወጥ ይችል ይሆናል፤ ምናልባትም ትናንሽ ልጆች እንዲናገሩ በማድረግ ወይም ተጋባዦቹ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሚገፋፋ ርዕስ በማንሳት ሌሎችም በጨዋታው እንዲካፈሉ ማድረግ ይችላል። ግብዣው እንደዚህ ዓይነት መልክ ሲኖረው ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ደስ ይላቸዋል። ግብዣውን ያዘጋጀኸው አንተ እንደመሆንህ መጠን ሁኔታዎችን በጥበብና በዘዴ የምትመራ ከሆነ ‘ምክንያታዊነትህ’ በቦታው በተገኙ ሁሉ ዘንድ ይታወቃል። (ፊልጵስዩስ 4:5 NW) ተጋባዦቹም በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች የሚታይ ሕያው እምነት እንዳለህ መገንዘብ ይችላሉ።
የጋብቻ ሥነ ሥርዓትና ድግሱ
7. ሠርግንና ከዚያ ጋር የተያያዙ ግብዣዎችን የማዘጋጀቱ ጉዳይ ሊታሰብበት የሚገባው ለምንድን ነው?
7 ደስታ ከሚያስገኙ ልዩ አጋጣሚዎች አንዱ የክርስቲያኖች ሠርግ ነው። ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን ጨምሮ የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች እንደዚህ ባሉት አስደሳች የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶችና ከዚያም ጋር ተያይዞ በሚዘጋጀው ግብዣ ላይ ተገኝተዋል። (ዘፍጥረት 29:21, 22፤ ዮሐንስ 2:1, 2) ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተሞክሮ እንደታየው ከሠርግ ጋር የተያያዙ ግብዣዎች፣ ማስተዋልና ክርስቲያናዊ ሚዛናዊነት እንዲንጸባረቅባቸው ከተፈለገ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ ያለው ግብዣ አንድ ክርስቲያን እምነቱን በተግባር ማሳየት እንዲችል አጋጣሚ የሚከፍትለት የሕይወት ዘርፍ ነው።
8, 9. በብዙ ሠርጎች ላይ የሚታዩት ነገሮች በ1 ዮሐንስ 2:16, 17 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?
8 የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች የማያውቁና ለእነዚህ መመሪያዎች ግድ የሌላቸው በርካታ ሰዎች፣ በሠርግ ወቅት ከተለመደው ወጣ ያለ ድርጊት መፈጸም እንደሚቻል ወይም ደግሞ እንዲህ ያለ ድርጊት ቢፈጸም ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸዋል። አውሮፓ ውስጥ በሚታተም መጽሔት ላይ አንዲት ሚስት ሠርጓ “የነገሥታት ቤተሰብ” የሚያደርጉት ዓይነት እንደነበረ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- ‘እኛ በአራት ፈረሶች በሚጎተት ሠረገላ እንጓዝ የነበረ ሲሆን ከኋላችን 12 ሠረገላዎችና ሙዚቃ የሚጫወተውን ቡድን የያዘ አንድ ሌላ ሠረገላ ይከተሉን ነበር። ከዚያም በግሩም ሁኔታ የተሠራ ምግብ በላን፤ ሙዚቃውም ቢሆን አስደሳች ነበር፤ ሁሉም ነገር ፍጹም ድንቅ ነበር። ልክ እንደ ተመኘሁት በዕለቱ ንግሥት ሆኜ ነበር።’
9 የየአገሩ ባሕል የተለያየ ሊሆን ቢችልም ከላይ የተገለጸው አስተያየት ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት የጻፈውን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው:- “በዓለም ያለው ሁሉ:- የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም።” የጎለመሱ ክርስቲያን ተጋቢዎች “የነገሥታት ቤተሰብ” የሚያደርጉት ዓይነት ሠርግና ድል ያለ ድግስ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ይመስልሃል? ከዚህ በተቃራኒ ለሠርጋቸው እቅድ ሲያወጡ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለውን ምክር እንዳሰቡበት ማሳየት ይኖርባቸዋል።—1 ዮሐንስ 2:16, 17
10. (ሀ) ምክንያታዊነት የተንጸባረቀበት ሠርግ ለመደገስ እቅድ ማውጣት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ተጋቢዎቹ የሚጋብዟቸውን ሰዎች በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ የሚኖርባቸው እንዴት ነው?
10 ክርስቲያን ተጋቢዎች እውነታውን ግምት ውስጥ ማስገባትና ምክንያታዊ መሆን ይፈልጋሉ፤ በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳቸው ይችላል። የሠርጋቸው ቀን ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ቢሆንም ይህ ዕለት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሁለት ክርስቲያኖች የትዳር ሕይወታቸውን አንድ ብለው የሚጀምሩበት ቀን እንደሆነ ያውቃሉ። ትልቅ የሠርግ ድግስ የማዘጋጀት ግዴታ የለባቸውም። ግብዣ ለማዘጋጀት ከመረጡ ደግሞ ወጪውን ማስላትና ግብዣው ምን ዓይነት እንደሚሆን አስቀድመው ማሰብ ይፈልጋሉ። (ሉቃስ 14:28) እነዚህ ክርስቲያኖች ተጋብተው በሚኖሩበት ወቅት በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ባልየው ራስ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:22, 23) ስለዚህ የሠርጉን ግብዣ በተመለከተ በዋነኝነት ኃላፊነት የሚኖርበት ሙሽራው ነው። በእርግጥ በግብዣው ላይ ማንን መጥራት እንደሚፈልጉ ወይም አቅማቸው የሚፈቅደው ምን ያህል ሰዎችን ለመጋበዝ እንደሆነ ከእጮኛው ጋር ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይወያያል። ሙሽሮቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በሙሉ መጋበዝ አይችሉ ይሆናል፤ እንዲህ ማድረጉም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ አንዳንድ ውሳኔዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ አቅማቸውን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። ተጋቢዎቹ አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በሠርጋቸው ላይ መጋበዝ ባይችሉ እነዚህ ክርስቲያኖች ሁኔታውን በመረዳት እንደማይቀየሟቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይገባል።—መክብብ 7:9 NW
የድግሱ አሳዳሪ
11. በሠርግ ግብዣ ላይ አሳዳሪው ምን ድርሻ ይኖረዋል?
11 ተጋቢዎቹ ሠርጋቸውን አስመልክተው ግብዣ ለማድረግ ከመረጡ ሥነ ሥርዓቱ ክብር የተላበሰ እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዓመታት ኢየሱስ በቃና ከተገኘበት ግብዣ ጋር በተያያዘ የተገለጸውን አንድ አሠራር ሲከተሉ ቆይተዋል። በቃናው ሠርግ ላይ “የድግሱ ኀላፊ” ወይም አሳዳሪ የነበረ ሲሆን ይህ ሰው ኃላፊነት የሚሰማው የእምነት ባልንጀራቸው ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐንስ 2:9, 10) በተመሳሳይም ብልህ የሆነ ሙሽራ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ይህንን ኃላፊነት የሚሸፍንለት በመንፈሳዊ የጎለመሰ አንድ ክርስቲያን ወንድም ሊመርጥ ይችላል። አሳዳሪው የሙሽራውን ፍላጎትና ምርጫ ካረጋገጠ በኋላ ከግብዣው በፊትም ሆነ በግብዣው ወቅት መከናወን ያለባቸውን ነገሮች ያደርጋል።
12. የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ሙሽራው ሊያስብበት የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው?
12 በአንቀጽ 5 ላይ በተመለከትነው መሠረት አንዳንድ ተጋቢዎች በሠርጋቸው ላይ የአልኮል መጠጥ እንዳይቀርብ ይወስኑ ይሆናል፤ ይህም አንዳንዶች ከልክ በላይ ጠጥተው ሥነ ሥርዓቱን አስደሳችና ስኬታማ እንዳይሆን እንዳያደርጉት ጥበቃ ይሆናል። (ሮሜ 13:13፤ 1 ቆሮንቶስ 5:11) ሆኖም የአልኮል መጠጥ እንዲቀርብ ከወሰኑ ሙሽራው መጠጡ በልክ እንዲቀርብ ማድረግ ይኖርበታል። ኢየሱስ በቃና በተገኘበት ሠርግ ላይ ወይን የነበረ ከመሆኑም በላይ እርሱም ምርጥ ወይን እንዲቀርብ አስተዋጽኦ አድርጓል። የድግሱ ኃላፊ “ሰው ሁሉ በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ እንግዶቹም ብዙ ከጠጡ [“ከሰከሩ፣” የ1954 ትርጉም] በኋላ መናኛውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈይተሃል” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዮሐንስ 2:10) ኢየሱስ ራሱ ስካርን ስለሚያወግዝ ሰዎች እንዲሰክሩ የሚያበረታታ ምንም ነገር እንዳላደረገ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 12:45, 46) የድግሱ አሳዳሪ ስለ ወይን ጠጁ ጥራት የሰነዘረው ሐሳብ በሌሎች የሠርግ ድግሶች ላይ አንዳንድ ተጋባዦች መስከራቸውን እንደተመለከተ የሚያሳይ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:15፤ 1 ተሰሎንቄ 5:7) ስለዚህ ሙሽራውም ሆነ አሳዳሪ የመሆን ኃላፊነት የተሰጠው እምነት የሚጣልበት ክርስቲያን “በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና” የሚለውን ግልጽ መመሪያ በግብዣው ላይ የተገኙ ሁሉ ተግባራዊ ማድረጋቸውን መከታተል ይኖርባቸዋል።—ኤፌሶን 5:18፤ ምሳሌ 20:1፤ ሆሴዕ 4:11
13. ተጋቢዎቹ በሠርጉ ግብዣ ላይ ሙዚቃ እንዲኖር ካደረጉ ስለ የትኛው ጉዳይ ሊያስቡ ይገባል? ለምንስ?
13 እንደ ሌሎች ግብዣዎች ሁሉ በሠርግ ግብዣ ላይም ሙዚቃ የሚኖር ከሆነ የድምፁ መጠን ሰዎች መጨዋወት እንዳይችሉ የሚከለክል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “ምሽቱ እየገፋ በሚሄድበት ጊዜ ጭውውቱ ሞቅ ሲል ወይም ጭፈራ ሲጀመር አንዳንድ ጊዜ የሙዚቃው ድምፅ ይጨመራል። ለስለስ ብሎ ይሰማ የነበረው ሙዚቃ በጣም ከመጮኹ የተነሳ መነጋገር አስቸጋሪ ይሆናል። የሠርግ ግብዣ አስደሳች ጭውውት ለማድረግ አጋጣሚ ይከፍታል። ከሙዚቃው ጩኸት የተነሳ እንዲህ ማድረግ ባይቻል ምንኛ ያሳዝናል!” ሙዚቀኞቹ ተቀጣሪ ይሁኑም አይሁኑ የሙዚቃውን ዓይነትና የድምፁን መጠን የመቆጣጠሩ ኃላፊነት ለእነርሱ መሰጠት አይኖርበትም፤ ከዚህ ይልቅ ሙሽራውና እርሱ የመረጠው አሳዳሪ ኃላፊነት ተሰምቷቸው አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ “በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” ሲል ጽፏል። (ቈላስይስ 3:17) ከሠርጉ ግብዣ በኋላ ተጋባዦቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በሠርጉ ላይ የነበረው ሙዚቃ ተጋቢዎቹ ሁሉን በኢየሱስ ስም እንዳደረጉት የሚያሳይ እንደነበረ ሊሰማቸው ይገባል።
14. አንድ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ጥሩ ትዝታ ጥሎ የሚያልፈው ዝግጅቱ ምን ዓይነት ከሆነ ነው?
14 አዎን፣ ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት ሠርግ አስደሳች ትዝታ ይኖረዋል። በትዳር ውስጥ 30 ዓመታት ያሳለፉት አዳም እና ኢዲታ አንድን ሠርግ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “ክርስቲያናዊ የሆነ መንፈስ ነበረው። ይሖዋን የሚያወድሱ መዝሙሮች እንዲሁም ሌሎች ግሩም መዝናኛዎች ነበሩ። ዋናውን ቦታ የያዘው ጭፈራና ሙዚቃ አልነበረም። ሠርጉ አስደሳችና የሚያንጽ ከመሆኑም በላይ ሁሉም ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ነበር።” በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ሙሽራውና ሙሽራዋ እምነታቸውን በሥራ ለማሳየት ሊያደርጓቸው የሚችሏቸው ብዙ ነገሮች አሉ።
የሠርግ ስጦታዎች
15. የሠርግ ስጦታዎችን በተመለከተ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል?
15 በብዙ አገሮች ውስጥ የሙሽሮቹ ወዳጆችና ዘመዶች ለአዲሶቹ ተጋቢዎች ስጦታ መስጠታቸው የተለመደ ነው። እንዲህ ለማድረግ ከወሰንክ ስለ የትኛው ጉዳይ ማሰብ ይኖርብሃል? ሐዋርያው ዮሐንስ ‘የኑሮ ትምክሕትን’ በተመለከተ የሰጠውን ሐሳብ አስታውስ። እንዲህ ያለውን ትምክሕት ወይም የይታይልኝ መንፈስ ያያያዘው እምነታቸውን በተግባር ከሚያሳዩ ክርስቲያኖች ጋር ሳይሆን ‘ከሚያልፈው ዓለም’ ጋር ነው። (1 ዮሐንስ 2:16, 17) ሁኔታውን ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት ከሰጠው ሐሳብ አንጻር ካየነው፣ አዲሶቹ ተጋቢዎች እያንዳንዱን ስጦታ ማን እንዳመጣላቸው በሕዝብ ፊት መናገር ይኖርባቸዋል? በመቄዶንያና በአካይያ የነበሩት ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም የነበሩትን ወንድሞቻቸውን ለመርዳት መዋጮ አድርገው ነበር፤ ሆኖም መዋጮውን ያደረጉት ሰዎች ስም በሕዝብ ፊት እንደተነገረ የሚጠቁም ሐሳብ አናገኝም። (ሮሜ 15:26) ስጦታ የሚሰጡ ብዙ ክርስቲያኖች አላስፈላጊ ትኩረት ወደ ራሳቸው ከመሳብ ይልቅ ስማቸው ባይጠቀስ ይመርጣሉ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:1-4 ላይ የሰጠውን ምክር ተመልከት።
16. አዲሶቹ ተጋቢዎች ከሠርግ ስጦታዎች ጋር በተያያዘ የሌሎችን ስሜት ላለመጉዳት ሊጠነቀቁ የሚችሉት እንዴት ነው?
16 እያንዳንዱን ስጦታ ማን እንዳመጣው መግለጹ ሰዎች የትኛው ስጦታ የተሻለ ወይም ውድ እንደሆነ እንዲያስቡ ስለሚያደርግ እርስ በርስ ‘የመጎነታተል [‘የመፎካከር፣’ NW]’ መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል። አዲስ የተጋቡ አስተዋይ ክርስቲያኖች ስጦታዎቹን ያመጡላቸውን ሰዎች ስም በሕዝብ ፊት ከማስነገር ይቆጠባሉ። ስጦታዎቹን የሰጡትን ሰዎች ስም መናገር ይህን ማድረግ ያልቻሉ ተጋባዦችን ሊያሳቅቅ ይችላል። (ገላትያ 5:26፤ 6:10) እርግጥ ሙሽራውና ሙሽራይቱ ስጦታዎቹን ማን እንዳመጣላቸው ማወቃቸው ምንም ስህተት የለውም። ምናልባትም ከስጦታው ጋር የሚያያዘውን ካርድ በማንበብ የሰጪውን ማንነት ማወቅ ይችሉ ይሆናል፤ ሆኖም ይህ በሕዝብ ፊት መነበብ አያስፈልገውም። ሁላችንም የሠርግ ስጦታ በምንገዛበት፣ በምንሰጥበት እንዲሁም በምንቀበልበት ጊዜ እንደዚህ በመሳሰሉት የግል ጉዳዮች እንኳ እምነታችንን በሥራ መግለጽ የምንችልበት አጋጣሚ እናገኛለን።a
17. ክርስቲያኖች በእምነትና በሥራ ረገድ ምን ግብ ሊኖራቸው ይገባል?
17 እምነታችንን በተግባር መግለጽ በሥነ ምግባር ረገድ ንጹሕ ከመሆን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት እንዲሁም በስብከቱ ሥራ ከመካፈል የበለጠ ነገርን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ሁላችንም በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ሕያው እምነት ይኑረን። አዎን፣ ከላይ የተወያየንባቸውን የሕይወት ዘርፎች ጨምሮ እምነታችንን “ፍጹም” በሆነ መንገድ በተግባር መግለጽ እንችላለን።—ራእይ 3:2
18. ከክርስቲያኖች ሠርግና ግብዣዎች ጋር በተያያዘ በዮሐንስ 13:17 ላይ ያለውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ግሩም ምሳሌ ከተወ በኋላ “እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 13:4-17) በዛሬው ጊዜ በምንኖርበት አካባቢ የሌሎችን፣ ለምሳሌ የእንግዶቻችንን እግር ማጠብ አስፈላጊ ወይም የተለመደ ነገር ላይሆን ይችላል። ሆኖም በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደተመለከትነው እምነታችንን ፍቅርና አሳቢነት በተንጸባረቀባቸው መንገዶች ማሳየት የምንችልባቸው ሌሎች የሕይወት ዘርፎች አሉ። ግብዣዎችና የክርስቲያኖች ሠርግም በዚህ ውስጥ ይካተታሉ። እኛ ራሳችን የምናገባ ብንሆን ወይም እምነታቸውን በሥራ ለማሳየት በሚፈልጉ ክርስቲያኖች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አሊያም ከዚያ በኋላ በሚደረገው አስደሳች የሆነ ክርስቲያናዊ ግብዣ ላይ ተጋብዘን ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረግ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሠርግንና ከሠርግ ጋር በተያያዘ የሚዘጋጀውን ግብዣ በተመለከተ “የሠርጋችሁ ቀን የሚያስደስትና የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ” በሚለው በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ተጨማሪ ነጥቦች ማግኘት ይቻላል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ግብዣ በምታዘጋጅበት ወቅት፣
• በጋብቻው ሥነ ሥርዓት ወይም በግብዣው ላይ፣
• የሠርግ ስጦታ ስትሰጥ ወይም ስትቀበል
እምነትህን በተግባር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥቂት ሰዎችን በምትጋብዝበት ጊዜም እንኳ ‘ከሰማይ በሆነችው ጥበብ’ ተመራ
-
-
የሠርጋችሁ ቀን የሚያስደስትና የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግመጠበቂያ ግንብ—2006 | ጥቅምት 15
-
-
የሠርጋችሁ ቀን የሚያስደስትና የሚያስከብር እንዲሆን ማድረግ
ስድሳ ለሚያክሉ ዓመታት በጋብቻ የቆዩት ጎርደን እንዲህ ይላሉ:- “የሠርጌ ቀን በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከምሰጣቸውና በጣም ከተደሰትኩባቸው ቀናት አንዱ ነበር።” እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሠርጋቸው ቀን ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለምንድን ነው? ይህ ቀን በጥልቅ ለሚወዷቸው ሁለት አካላት ማለትም ለይሖዋ እና ለትዳር ጓደኛቸው ቅዱስ ቃል ኪዳን የሚገቡበት ዕለት ነው። (ማቴዎስ 22:37፤ ኤፌሶን 5:22-29) በእርግጥም ለማግባት የሚያስቡ ወንድና ሴት የሠርጋቸው ቀን አስደሳች እንዲሁም የጋብቻ መሥራች ለሆነው አምላክ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን ይፈልጋሉ።—ዘፍጥረት 2:18-24፤ ማቴዎስ 19:5, 6
ሙሽራው ይህ አስደሳች ወቅት ይበልጥ ክብር ያለው እንዲሆን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ሙሽራዋስ ለባሏና ለይሖዋ አክብሮት እንዳላት እንዴት ማሳየት ትችላለች? በዝግጅቱ ላይ የሚገኙ ተጋባዦችስ የሠርጉ ቀን ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መመልከት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከማስገኘቱም በላይ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋል አስደሳች በሆነው በዚህ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉትን ችግሮች ለመቀነስ ይረዳል።
ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ማን ነው?
በበርካታ አገሮች የማጋባት ሥልጣን የተሰጠው አንድ የይሖዋ ምሥክር የጋብቻው ውል ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲፈጸም ያደርግ ይሆናል። ጋብቻው በክብር መዝገብ ሹም ፊት መፈጸም ባለበት አገርም እንኳ ተጋቢዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር እንዲደረግላቸው ይፈልጉ ይሆናል። በዚህ ንግግር ላይ ሙሽራው አምላክ የሰጠውን የቤተሰብ ራስ የመሆን ኃላፊነት እንዲያስብበት ይጠየቃል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በመሆኑም ሙሽራው በሠርጉ ወቅት ለሚከናወኑት ነገሮች ሁሉ ተቀዳሚውን ኃላፊነት ይወስዳል። እርግጥ ነው፣ ለጋብቻ ሥነ ሥርዓቱም ሆነ ከዚያ በኋላ ሊደረግ ለሚችለው ማንኛውም ግብዣ የሚያስፈልገው ዝግጅት ብዙውን ጊዜ አስቀድሞ ይደረጋል። እነዚህን ነገሮች ማዘጋጀት ለሙሽራው አስቸጋሪ የሚሆንበት ለምን ሊሆን ይችላል?
ለዚህ አንደኛው ምክንያት፣ ሙሽራዋ ወይም የሙሽራዋም ሆነ የሙሽራው ዘመዶች የሠርጉን ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ስለሚፈልጉ ይሆናል። ሮዶልፎ የተባለ በርካታ ሙሽሮችን ያጋባ ሰው እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አንዳንድ ጊዜ፣ በተለይ ደግሞ ሠርጉን ለመደገስ ዘመዶች የሚረዱት ከሆነ ሙሽራው እነርሱ የሚያደርጉበትን ከፍተኛ ግፊት መቋቋም ይኖርበታል። በጋብቻ ሥነ ሥርዓቱም ሆነ በግብዣው ላይ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች በተመለከተ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩ ይሆናል። ይህ ደግሞ በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ሙሽራው በሥነ ሥርዓቱ ላይ ያለውን ኃላፊነት መጋፋት ይሆናል።”
ከ35 ዓመታት በላይ የተለያዩ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶችን ያከናወነው ማክስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ሙሽራው የሠርጉን ዝግጅትም ሆነ በድግሱ ላይ መከናወን ያለበትን ነገር በተመለከተ ሐሳብ ለመስጠት አጋጣሚ እንደማያገኝና ቅድሚያውን በመውሰድ የምትወስነው ሙሽራዋ እንደሆነች መመልከት ችያለሁ።” በተመሳሳይም በርካታ ሙሽሮችን ያጋባው ዴቪድ እንዲህ በማለት ሐሳብ ይሰጣል:- “ሙሽራው አመራር የመስጠት ልምድ አይኖረው ይሆናል፤ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ በሠርጉ ዝግጅት ላይ በቂ ተሳትፎ አያደርግም።” ታዲያ ሙሽራው ኃላፊነቱን በተሳካ መንገድ መወጣት የሚችለው እንዴት ነው?
በግልጽ መነጋገር ደስታን ይጨምራል
ሙሽራው በሠርጉ ዝግጅት ውስጥ ያለውን ኃላፊነት በተሳካ መንገድ ለመወጣት እንዲችል በግልጽ የመነጋገር ችሎታ ሊኖረው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 15:22) ሆኖም ሙሽራው የሠርጉን ዝግጅት አስመልክቶ ከሙሽራዋና ከቤተሰብ አባላት እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ግሩም ምክሮችን ሊሰጡ ከሚችሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ቀደም ብሎ መወያየቱ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ሊቀንስ ይችላል።
በእርግጥም እጮኛሞቹ በመጀመሪያ ስለ ዝግጅቱም ሆነ ስለ ሌሎች ነገሮች መወያየታቸው አስፈላጊ ነው። ለምን? የተለያየ ባሕል ያላቸው ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ደስታ የሞላበት የትዳር ሕይወት ያሳለፉት አይቫንና ባለቤቱ ዴልዊን የሰጧቸውን አንዳንድ ሐሳቦች እንመልከት። የሠርጋቸውን ዝግጅት በማስታወስ አይቫን እንዲህ ይላል:- “በሠርጌ ቀን ሁሉም ጓደኞቼ የሚገኙበት ድግስ እንደሚደረግ፣ የሠርግ ኬክ እንደሚኖር፣ ሙሽራዋ ነጭ ቬሎ እንደምትለብስና የመሳሰሉትን ዝግጅቶች ጨምሮ በግልጽ የተቀመጡ እቅዶች ነበሩኝ። በሌላ በኩል ዴልዊን የምትፈልገው አነስ ያለ፣ የሠርግ ኬክ የሌለበትና ያልተንዛዛ ሠርግ ነበር። እንዲያውም የሙሽራ ቀሚስ ከመልበስ ይልቅ ሌላ ልብስ ብትለብስ ትመርጥ ነበር።”
እነዚህ እጮኛሞች በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት ምን አደረጉ? ደግነትና ሐቀኝነት የተንጸባረቀበት ውይይት በማድረግ ልዩነታቸውን ሊፈቱት ችለዋል። (ምሳሌ 12:18) አይቫን እንዲህ ይላል:- “የሚያዝያ 15, 1984 መጠበቂያ ግንብን (እንግሊዝኛ) የመሰሉ ስለ ሠርግ የሚናገሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አጠናን።a እነዚህ ጽሑፎች የሠርጋችንን ወቅት በተመለከተ መንፈሳዊ አመለካከት እንዲኖረን ረድተውናል። አስተዳደጋችን የተለያየ በመሆኑ በግል ምርጫዎቻችን ረገድ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሁለታችንም አመለካከታችንን ማስተካከል አስፈልጎናል።”
አሬትና ፔኒ የተባሉ ባልና ሚስትም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። አሬት ስለ ሠርጋቸው ቀን እንዲህ ይላል:- “እኔና ፔኒ በሠርጉ ቀን ማድረግ የምንፈልጋቸውን ነገሮች በተመለከተ ባለን ልዩነት ላይ ተወያየን፤ ይህ ደግሞ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ አስችሎናል። በሠርጋችን ቀን የይሖዋ በረከት እንዳይለየን ጸለይን። ወላጆቻችንም ሆኑ በጉባኤያችን የሚገኙ የጎለመሱ ባለትዳሮች ምክር እንዲሰጡኝ ጠየቅኩ። የሰጡኝ ምክር እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ሠርጋችን አስደሳች ሊሆን ችሏል።”
የሚያስከብር አለባበስና አጋጌጥ
ሙሽራውም ሆነ ሙሽራዋ በሠርጋቸው ቀን አምረው ለመታየት እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። (መዝሙር 45:8-15) ለሠርጉ ተገቢ የሆነ ልብስ ማግኘት ጊዜ፣ ጥረትና ገንዘብ ይጠይቅባቸዋል። ተጋቢዎቹ የሚያምር ሆኖም የሚያስከብር ልብስ እንዲመርጡ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዷቸው ይችላሉ?
እስቲ ሙሽራዋ ለሠርጉ ቀን የምትለብሰውን ልብስ እንደ ምሳሌ እንመልከት። እርግጥ ነው፣ በዚህ ረገድ የሚደረገው ምርጫ ከሰው ወደ ሰው እንዲሁም ከአገር ወደ አገር የሚለያይ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ግን በየትም ቦታ ይሠራል። ሴቶች “በጨዋነትና ራስን በመግዛት ተገቢ የሆነ ልብስ [እንዲለብሱ]” ተመክረዋል። ይህ ደግሞ የሠርጋቸውን ቀን ጨምሮ ክርስቲያን ሴቶች ሁልጊዜ ሊሠሩበት የሚገባ ምክር ነው። እንዲያውም ሠርግ አስደሳች እንዲሆን “ዋጋቸው ውድ በሆኑ ልብሶች” ማጌጥ የግድ አስፈላጊ አይደለም። (1 ጢሞቴዎስ 2:9፤ 1 ጴጥሮስ 3:3, 4) ይህ ምክር በሥራ ሲውል ምንኛ ደስ ያሰኛል!
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዴቪድ እንዲህ ይላል:- “ብዙ ባልና ሚስት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተል ጥረት የሚያደርጉ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ሆኖም የሙሽራዋና የሚዜዎቿ ልብስ ጡት እስከሚያሳይ ድረስ ደረቱ በጣም የተገለጠጠ ወይም ስስ ሆኖ ሰውነትን በግልጽ የሚያሳይ በመሆኑ ልከኛ ያልሆነ አለባበስ የታየባቸው ጊዜያት አሉ።” አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ሽማግሌ ቀደም ብሎ ከሙሽራውና ከሙሽሪት ጋር በሚገናኝበት ጊዜ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይችላል። ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? በዚያን ጊዜ ሊለብሱት ያሰቡት ልብስ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሊሆን የሚችል ልከኛ ልብስ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል። እርግጥ የልብሱ ዓይነት ሁልጊዜ ለስብሰባ ከምንለብሰው ልብስ ሊለይ እንዲሁም በአካባቢው ያለውን ባሕል የሚያንጸባርቅ ሊሆን ቢችልም ላቅ ካሉት ክርስቲያናዊ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ልከኛ መሆን አለበት። በዓለም የሚገኙ አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕግ ጥብቅ እንደሆነ አድርገው ቢመለከቱትም እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ዓለም በሚፈልገው መንገድ እነርሱን ለመቅረጽ የሚያደርገውን ጥረት በመቋቋማቸው ደስተኞች ናቸው።—ሮሜ 12:2፤ 1 ጴጥሮስ 4:4
ፔኒ እንዲህ ትላለች:- “እኔና አሬት ለምንለብሰው ልብስ ወይም ለድግሱ ትልቅ ቦታ ከመስጠት ይልቅ ትኩረት ያደረግነው መንፈሳዊ በሆነው የዝግጅቱ ክፍል ላይ ነበር። ይህ ደግሞ በዕለቱ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ነው። በሠርጌ ቀን ከተከናወኑት ሁኔታዎች መካከል ልዩ ቦታ ሰጥቼ የማስታውሰው፣ የለበስኩትን ልብስ ወይም የበላሁትን ምግብ ሳይሆን አብረውን ከነበሩ ሰዎች ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜ እንዲሁም የምወደውን ሰው በማግባቴ የተሰማኝን ደስታ ነው።” ክርስቲያን ተጋቢዎች ለሠርጋቸው እቅድ ሲያወጡ እነዚህን ነገሮች በአእምሯቸው መያዝ ይገባቸዋል።
የመንግሥት አዳራሹ—ክብር ያለው ቦታ
በርካታ ክርስቲያን ተጋቢዎች የሠርጋቸው ሥነ ሥርዓት ከተቻለ በመንግሥት አዳራሽ እንዲከናወን ይፈልጋሉ። ይህንን ቦታ የሚመርጡት ለምንድን ነው? አንድ ባልና ሚስት ይህን ቦታ የመረጡበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ይናገራሉ:- “ጋብቻ የይሖዋ ቅዱስ ዝግጅት መሆኑን ተገንዝበን ነበር። የአምልኮ ቦታችን በሆነው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ መጋባታችን ይሖዋ ገና ከጅምሩ የትዳራችን ክፍል መሆን እንዳለበት እንድናስታውስ አድርጎናል። የሠርጉ ሥነ ሥርዓት በሌላ ቦታ ከሚሆን ይልቅ በመንግሥት አዳራሽ መሆኑ ያለው ሌላ ጥቅም ደግሞ፣ በሠርጉ ላይ የተጋበዙት የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ዘመዶቻችን ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ለእኛ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማየት የሚያስችላቸው መሆኑ ነው።”
የመንግሥት አዳራሹን ኃላፊነት ወስደው የሚከታተሉ የጉባኤው ሽማግሌዎች ሠርጉ በዚያ እንዲካሄድ ከፈቀዱ ተጋቢዎቹ ወንድና ሴት፣ የሚያደርጉትን ዝግጅት በተመለከተ ቀደም ብለው ሽማግሌዎቹን ማማከር ያስፈልጋቸዋል። ሙሽራውና ሙሽራዋ በሠርጋቸው ዕለት ለተጋበዙት እንግዶች ተገቢውን አክብሮት የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ሰዓት አክብሮ ለመገኘት ቁርጥ አቋም መውሰድ ነው። እንዲሁም ሁሉም ነገር በሚያስከብር ሁኔታ የሚከናወን መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።b (1 ቆሮንቶስ 14:40) በመሆኑም በዓለም እንደሚታዩት አብዛኞቹ ሠርጎች የማይገቡ ነገሮችን ከማድረግ ይቆጠባሉ።—1 ዮሐንስ 2:15, 16
ተጋባዦቹም ይሖዋ ለጋብቻ ያለው ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ማሳየት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ትልቅ የሠርግ ድግስ የማዘጋጀት ውድድር ያለ ይመስል ሠርጉ ከሌሎች ክርስቲያኖች ሠርግ ልቆ እንዲገኝ መጠበቅ የለባቸውም። ከዚህም በላይ የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርቶ የሚቀርበውን ንግግር ለማዳመጥ በመንግሥት አዳራሹ መገኘት ከዚያ በኋላ በሚደረገው ግብዣ ወይም ድግስ ላይ ከመገኘት ይልቅ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን ይገነዘባሉ። አንድ ክርስቲያን ካለው ጊዜ ወይም ከሁኔታዎች አንጻር መገኘት የሚችለው በአንዱ ቦታ ላይ ብቻ ከሆነ በመንግሥት አዳራሹ ቢገኝ ይመረጣል። ዊልያም የተባለ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “ተጋባዦች ከመንግሥት አዳራሽ በማይረባ ምክንያት ቀርተው በኋላ በድግሱ ላይ የሚገኙ ከሆነ ቅዱስ ለሆነው ለዚህ ሥነ ሥርዓት አድናቆት እንደሚጎድላቸው ያሳያል። ድግሱ ላይ ባንጠራም እንኳ በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታችን በጋብቻቸው መደሰታችንን ለሙሽሮቹ ለመግለጽ ከማስቻሉም በላይ በመንግሥት አዳራሹ ለተገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላልሆኑ ዘመዶች ጥሩ ምሥክርነት ይሰጣል።”
ከሠርጉ ቀን ባሻገር የሚዘልቅ ደስታ
የሠርግ ድግስ፣ የንግዱ ዓለም ትርፍ የሚያገኝበት መስክ ሆኗል። አንድ በቅርቡ የወጣ ሪፖርት በዩናይትድ ስቴትስ መካከለኛ የሚባለው ሠርግ “22,000 የአሜሪካ ዶላር ወይም አንድ አሜሪካዊ [በዓመት] በአማካይ ከሚያገኘው ገቢ ግማሹን” እንደሚያስወጣ ገልጿል። የንግዱ ዓለም የሚያሰራጨው ፕሮፖጋንዳ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው አዲስ ተጋቢዎች ወይም ቤተሰቦቻቸው ለዚያች አንድ ቀን ሲሉ ለዓመታት ሊወጡት በማይችሉት ከባድ ዕዳ ውስጥ ይዘፈቃሉ። ሆኖም ትዳርን በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ መጀመር የጥበብ መንገድ ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የማያውቁ ወይም ችላ የሚሉ ተጋቢዎች እንዲህ ያለ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሠርግ ለመደገስ ይመርጡ ይሆናል፤ ሆኖም በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ ሁኔታው የተለየ ነው።
በርካታ ክርስቲያን ተጋቢዎች መጠነኛና አቅማቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ሠርግ በማዘጋጀታቸው እንዲሁም በዝግጅቱ መንፈሳዊ ክፍል ላይ ይበልጥ በማተኮራቸው፣ ራሳቸውን ለአምላክ ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን መጠቀም ችለዋል። (ማቴዎስ 6:33) ትዳር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 17 ዓመታት ያሳለፉትን የሎይድና የአሊጅዛንድራን ምሳሌ እንመልከት። ሎይድ እንዲህ ይላል:- “አንዳንዶች የሠርጋችንን ዝግጅት አነስ ያለ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውት ሊሆን ቢችልም እኔና አሊጅዛንድራ ግን እጅግ ተደስተንበታል። የሠርጋችን ቀን በገንዘብ ረገድ ከፍተኛ ጫና እንዲፈጥርብን ከመፍቀድ ይልቅ ይሖዋ፣ ሁለት ሰዎች ከፍተኛ ደስታ እንዲያገኙ ያደረገውን ዝግጅት እንደምናደንቅ በሚያሳይ መንገድ አሳልፈነዋል።”
አሊጅዛንድራም እንዲህ ትላለች:- “ከመጋባታችን በፊት አቅኚ ስለነበርኩ ከአቅማችን በላይ የሆነ ሠርግ ለመደገስ ብዬ ይህን ልዩ መብት መተው አልፈለግኩም። የሠርጋችን ዕለት በጣም ልዩ ነበር። ይሁን እንጂ አብረን የምናሳልፈው ሕይወት ገና መጀመሩ ነበር። ለማግባት በሚደረገው ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዳናደርግ የተሰጠንን ምክር የሠራንበት ከመሆኑም በላይ ተጋብተን በሚኖረን ሕይወት የይሖዋን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው። ይህ ደግሞ የይሖዋን በረከት እንዳስገኘልን ምንም ጥርጥር የለውም።”c
እውነት ነው፣ የሠርጋችሁ ቀን ልዩ የሆነ ጊዜ ነው። በዚያን ቀን የሚኖራችሁ አመለካከትና የምታደርጓቸው ነገሮች በትዳር የምታሳልፉት ሕይወት ምን እንደሚመስል ይጠቁማሉ። ስለዚህ መመሪያ ለማግኘት በይሖዋ ታመኑ። (ምሳሌ 3:5, 6) የሠርጋችሁን ቀን በተመለከተ መንፈሳዊው ነገር ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝ አድርጉ። አምላክ የሰጣችሁን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ እርስ በርሳችሁ ተደጋገፉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ለትዳራችሁ ጠንካራ መሠረት መጣል ትችላላችሁ፤ ይሖዋም ስለሚባርካችሁ ከሠርጋችሁ ቀን ባሻገር የሚዘልቅ ደስታ ይኖራችኋል።—ምሳሌ 18:22
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የመጋቢት 2002 ንቁ! ተመልከት።
b ሙሽሮቹ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የሚካሄደውን ሥነ ሥርዓት ፎቶግራፍ የሚያነሳ ወይም ቪዲዮ የሚቀርጽ ሰው ለማዘጋጀት ካሰቡ የሠርጉን ክብር የሚቀንስ ምንም ነገር የማይደረግ መሆኑን በቅድሚያ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለመጋባት ያሰቡ አንድ ወንድና ሴት ሠርጉን በተመለከተ በግልጽ ሆኖም በአክብሮት መወያየት ይኖርባቸዋል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሠርጋችሁ ቀን መንፈሳዊው ነገር ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝ አድርጉ
-