ምዕራፍ 7
‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች የሚያነቃቁ’ ስብሰባዎች
ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ የይሖዋ ሕዝቦች በተደራጀ መልኩ አንድ ላይ ሲሰበሰቡ ቆይተዋል። በጥንቷ እስራኤል ሁሉም ወንዶች ሦስቱን ታላላቅ በዓላት ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ ነበር። (ዘዳ. 16:16) በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ክርስቲያኖች አዘውትረው የመሰብሰብ ልማድ የነበራቸው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚሰበሰቡት በግለሰቦች ቤት ነበር። (ፊልሞና 1, 2) በዛሬው ጊዜም የጉባኤ፣ የወረዳና የክልል ስብሰባዎችን እናደርጋለን። የአምላክ አገልጋዮች አንድ ላይ የሚሰበሰቡት ለምንድን ነው? ዋናው ምክንያት የአምልኳችን አቢይ ክፍል ስለሆነ ነው።—መዝ. 95:6፤ ቆላ. 3:16
2 በስብሰባዎች ላይ መገኘት ተሰብሳቢዎቹንም ይጠቅማል። እስራኤላውያን በየዓመቱ የሚከበረውን የዳስ በዓል ሰባተኛ ዓመት በተመለከተ የሚከተለው መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር፦ “ስለ አምላካችሁ ስለ ይሖዋ ይሰሙና ይማሩ እንዲሁም እሱን ይፈሩ ዘንድ ብሎም የዚህን ሕግ ቃላት በሙሉ በጥንቃቄ እንዲፈጽሙ ሕዝቡን ማለትም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችንና በከተሞችህ ውስጥ የሚኖረውን የባዕድ አገር ሰው ሰብስብ።” (ዘዳ. 31:12) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አብረን ከምንሰበሰብባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ‘ከይሖዋ ለመማር’ ነው። (ኢሳ. 54:13) ከዚህም ሌላ ስብሰባዎች እርስ በርስ መተዋወቅ፣ መጽናናትና መበረታታት የምንችልበት አጋጣሚ ይሰጡናል።
የጉባኤ ስብሰባዎች
3 በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ አንድ ላይ ተሰብስበው የነበሩት ደቀ መዛሙርት፣ የሐዋርያትን ትምህርት በትጋት ይከታተሉ ነበር፤ “በየዕለቱም በአንድ ልብ ሆነው በቤተ መቅደሱ አዘውትረው ይገኙ ነበር።” (ሥራ 2:42, 46) ከጊዜ በኋላም ክርስቲያኖች ለአምልኮ ሲሰበሰቡ በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ጽሑፎችን ያነቡ ነበር፤ ከእነዚህ መካከል ሐዋርያትና ሌሎች ደቀ መዛሙርት የጻፏቸው ደብዳቤዎች ይገኙበታል። (1 ቆሮ. 1:1, 2፤ ቆላ. 4:16፤ 1 ተሰ. 1:1፤ ያዕ. 1:1) በተጨማሪም በጉባኤ ደረጃ አንድ ላይ ይጸልያሉ። (ሥራ 4:24-29፤ 20:36) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ፣ ተሰብሳቢዎቹ ሚስዮናውያን በአገልግሎት ላይ ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች ያዳምጣሉ። (ሥራ 11:5-18፤ 14:27, 28) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶችና በመንፈስ መሪነት በተጻፉ ትንቢቶች ፍጻሜም ላይ ይወያዩ ነበር። እንዲሁም በስብሰባው ላይ ስለ ክርስቲያናዊ አኗኗርና ለአምላክ ያደሩ ስለመሆን ትምህርት ይሰጥ ነበር። ከዚህም ሌላ ሁሉም ቀናተኛ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች እንዲሆኑ ማበረታቻ ይሰጣቸው ነበር።—ሮም 10:9, 10፤ 1 ቆሮ. 11:23-26፤ 15:58፤ ኤፌ. 5:1-33
አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ዘወትር በመሰብሰብ ተጨማሪ ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልገናል
4 በዘመናችንም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚደረጉት በሐዋርያት ዘመን ይደረጉ በነበረበት መንገድ ነው። በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን፦ “አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።” አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ምንጊዜም በመንፈሳዊ ጠንካሮች ለመሆንና ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ዘወትር በመሰብሰብ ተጨማሪ ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልገናል። (ሮም 1:11, 12) የምንኖረው ጠማማና ወልጋዳ በሆነ ትውልድ መካከል ነው። ሆኖም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ዓለማዊ ምኞቶችን ከመከተልና ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ ከመኖር ለመራቅ ጥረት እናደርጋለን። (ፊልጵ. 2:15, 16፤ ቲቶ 2:12-14) ታዲያ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ከመሆን የተሻለ ምን ነገር ይኖራል? (መዝ. 84:10) ደግሞስ የአምላክን ቃል ከማጥናትና ቃሉ ሲብራራ ከመስማት ይበልጥ የሚጠቅም ነገር እናገኛለን? ለእኛ ጥቅም ሲባል የተደረጉትን የተለያዩ ስብሰባዎች እስቲ እንመልከት።
የሳምንቱ መጨረሻ ስብሰባ
5 በሳምንቱ መጨረሻ በሚደረገው ስብሰባ የመጀመሪያ ክፍል ላይ በዋነኝነት እንግዶችን ታሳቢ ያደረገ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ይቀርባል፤ ምናልባትም ከእንግዶቹ መካከል አንዳንዶቹ በስብሰባችን ላይ የተገኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ይህ የሕዝብ ንግግር የእንግዶችንም ሆነ የጉባኤውን አስፋፊዎች መንፈሳዊ ፍላጎት በማሟላት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።—ሥራ 18:4፤ 19:9, 10
6 ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱና ሌሎች ደቀ መዛሙርት በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ከሚያደርጓቸው የሕዝብ ስብሰባዎች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ስብሰባዎችን ያደርጉ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ እስከዛሬ ድረስ በምድር ላይ ከኖሩት የሕዝብ ተናጋሪዎች ሁሉ የላቀ ችሎታ እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። “ማንም ሰው እንደዚህ ተናግሮ አያውቅም” ተብሎለታል። (ዮሐ. 7:46) ኢየሱስ እንደ ባለሥልጣን ይናገር ነበር፤ አድማጮቹም በዚህ ተደንቀዋል። (ማቴ. 7:28, 29) እሱ ያስተማረውን ትምህርት የተቀበሉ ሁሉ ብዙ ጥቅም አግኝተዋል። (ማቴ. 13:16, 17) ሐዋርያትም ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ተከትለዋል። በሐዋርያት ሥራ 2:14-36 ላይ ጴጥሮስ በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ስለሰጠው ስሜት ቀስቃሽ ንግግር የሚገልጽ ዘገባ እናገኛለን። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ከሰሙት ንግግር የተነሳ እርምጃ ለመውሰድ ተገፋፍተዋል። ከጊዜ በኋላም ጳውሎስ በአቴና የሰጠውን ንግግር ያዳመጡ አንዳንድ ግለሰቦች አማኞች ሆነዋል።—ሥራ 17:22-34
7 በዛሬው ጊዜም ቢሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በጉባኤ ከሚደረጉ ሳምንታዊ የሕዝብ ንግግሮች እንዲሁም በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ከሚቀርቡ የሕዝብ ንግግሮች ጥቅም ማግኘት ችለዋል። እንዲህ ያሉ ንግግሮች ክርስቲያናዊ ትምህርቶችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ዘወትር ንቁ እንድንሆን የሚረዱን ከመሆኑም ሌላ በአገልግሎት እንድንጸና ያበረታቱናል። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ጨምሮ ሁሉንም ሰዎች ወደ ስብሰባ በመጋበዝ መሠረታዊ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲያውቁ ልንረዳቸው እንችላለን።
8 በሕዝብ ንግግር ላይ የሚቀርቡት ርዕሰ ጉዳዮች የተለያዩ ናቸው። ንግግሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረተ ትምህርቶችና ትንቢቶች እንዲሁም ከቤተሰብ ሕይወት፣ ከትዳር ሕይወት፣ ወጣቶችን ከሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎችና ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሰፍረው የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምክሮች ይዳስሳሉ። አንዳንዶቹ ንግግሮች አስደናቂ በሆኑት የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ያተኩራሉ። ሌሎች ንግግሮች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ያሳዩትን ለሌሎች አርዓያ የሚሆን እምነት፣ ድፍረትና ንጹሕ አቋም ጎላ አድርገው በመግለጽ ከዚያ በምናገኘው ትምህርት ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።
9 ከሕዝብ ንግግሮች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት በጥሞና ማዳመጥ እንዲሁም ተናጋሪው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ሲያነብና ሲያብራራ አውጥቶ መከታተል ያስፈልጋል። (ሉቃስ 8:18) በዚህ መንገድ የሚብራሩትን ሐሳቦች ስንመረምር የተማርነውን አጥብቀን ለመያዝና በሥራ ላይ ለማዋል ቁርጥ ውሳኔ እናደርጋለን።—1 ተሰ. 5:21
10 በቂ ተናጋሪዎች የሚገኙ ከሆነ ጉባኤው በየሳምንቱ የሕዝብ ንግግር ይኖረዋል። አብዛኞቹ ጉባኤዎች በየሳምንቱ ንግግር እንዲቀርብ የሚያደርጉት ቅርብ ካሉ ጉባኤዎች ተናጋሪዎችን በመጋበዝ ነው። በአካባቢው የተናጋሪዎች እጥረት ካለ እነዚህ ንግግሮች ሁኔታው በፈቀደ መጠን በየተወሰነ ጊዜው እንዲቀርቡ ዝግጅት ይደረጋል።
11 በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረገው ስብሰባ ሁለተኛ ክፍል በመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም ላይ በሚወጡ ርዕሶች ላይ ተመሥርቶ በጥያቄና መልስ የሚካሄድ ውይይት ነው። ይሖዋ በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል።
12 አብዛኛውን ጊዜ የጥናት ርዕሶቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያብራሩ ትምህርቶችን ይዘው ይወጣሉ። እነዚህ ርዕሶች ክርስቲያኖች “የዓለምን መንፈስ” እና ብልሹ ሥነ ምግባርን ለመከላከል የሚያስችል ጥንካሬ እንዲኖራቸው ይረዳሉ። (1 ቆሮ. 2:12) በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡት ርዕሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶችና ትንቢቶች ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ብርሃን ይፈነጥቃሉ፤ በመሆኑም ሁሉም ክርስቲያኖች በየጊዜው ከሚገለጠው እውነት ጋር እንዲተዋወቁና ከጻድቃን መንገድ እንዳይወጡ ይረዷቸዋል። (መዝ. 97:11፤ ምሳሌ 4:18) በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ መገኘታችንና ተሳትፎ ማድረጋችን ይሖዋ ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣልን በሰጠን ተስፋ እንድንደሰት ይረዳናል። (ሮም 12:12፤ 2 ጴጥ. 3:13) ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አብረን መሰብሰባችን የመንፈስ ፍሬ እንድናፈራ እንዲሁም ይሖዋን በቅንዓት ለማገልገል ያለንን ፍላጎት እንድናጠናክር ይረዳናል። (ገላ. 5:22, 23) በተጨማሪም ፈተናዎችን በጽናት እንድንቋቋም እንዲሁም “ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን መልካም መሠረት” በመገንባት ‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀን መያዝ እንድንችል’ ብርታት ይሰጠናል።—1 ጢሞ. 6:19፤ 1 ጴጥ. 1:6, 7
13 መንፈሳዊ ምግብ እንድንመገብ ከተደረገው ከዚህ ዝግጅት የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ከስብሰባው በፊት በግለሰብ ደረጃ አሊያም በቤተሰብ መዘጋጀት፣ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥተን ማንበብ እንዲሁም በስብሰባው ወቅት በራሳችን አባባል ሐሳብ መስጠት ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን እውነት ወደ ልባችን እንዲሰርጽ ያደርጋል፤ አድማጮችም እምነታችንን ስንገልጽ በመስማት ይጠቀማሉ። ሌሎች የሚሰጡትን ሐሳብ በጥሞና ማዳመጣችን በየሳምንቱ ከሚሰጠው ትምህርት ብዙ ጥቅም እንድናገኝ ይረዳናል።
የሳምንቱ መሃል ስብሰባ
14 ጉባኤው በየሳምንቱ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን የተባለውን ስብሰባ ያደርጋል። ይህ ስብሰባ ብቁ የአምላክ አገልጋዮች እንድንሆን ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ሦስት ክፍሎች አሉት። (2 ቆሮ. 3:5, 6) የስብሰባው ፕሮግራምና የሚቀርቡት ትምህርቶች ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ በተባለው ወርሃዊ ጽሑፍ ላይ ይወጣሉ። በተጨማሪም የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ አገልግሎት ላይ የምንጠቀምባቸውን የውይይት ናሙናዎች ይዞ ይወጣል።
15 ‘ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት’ የተባለው የዚህ ስብሰባ የመጀመሪያ ክፍል የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን መቼትና አውድ እንድናውቅ እንዲሁም ከዘገባዎቹ የምናገኘውን ትምህርት እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደምንችል እንድንገነዘብ ይረዳናል። በዚህ ክፍል ሥር በሳምንቱ ውስጥ እንድናነባቸው በተመደቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ላይ የተመሠረተ ንግግር፣ ንባብና ውይይት ተካትቷል። የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ዘገባዎቹን በሚገባ መረዳት እንድንችል የሚያግዙ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ ካርታዎችና ሰንጠረዦች አሉት። እንዲህ ባለ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት መመርመራችን ለግል ሕይወታችንም ሆነ ሌሎችን ለማስተማር ይጠቅመናል፤ ይህ ደግሞ “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ” እንድንሆን ያስችለናል።—2 ጢሞ. 3:16, 17
16 ‘በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ተጣጣር’ የሚለው ሁለተኛው የስብሰባው ክፍል ሁላችንም ለአገልግሎት ልምምድ የምናደርግበት አጋጣሚ ይሰጠናል፤ እንዲሁም የመስበክና የማስተማር ችሎታችንን እንድናሻሽል ይረዳናል። ከተማሪ ክፍሎች በተጨማሪ የውይይት ናሙና ቪዲዮዎች ይቀርባሉ። ይህ የስብሰባው ክፍል “የተማሩ ሰዎችን አንደበት” እንድናገኝ ያስችለናል፤ ይህም “ለደከመው ትክክለኛውን ቃል በመናገር እንዴት መልስ መስጠት” እንደምንችል በሚገባ እንድናውቅ ይረዳናል።—ኢሳ. 50:4
17 ‘ክርስቲያናዊ ሕይወት’ የሚለው የዚህ ስብሰባ ሦስተኛ ክፍል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። (መዝ. 119:105) በዚህ ክፍል ሥር ሰፋ ያለ ጊዜ የሚይዘው የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው። የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልክ እንደ መጠበቂያ ግንብ ጥናት በጥያቄና መልስ በሚደረግ ውይይት ይሸፈናል።
18 በየወሩ አዲስ የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ሲወጣ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ወይም እሱን የሚረዳው ሽማግሌ ክፍሎቹን በሚገባ በማጤን ፕሮግራም ያወጣል። በእያንዳንዱ ሳምንት፣ ጥሩ የማስተማር ችሎታ ያለውና ከሽማግሌዎች አካል ድጋፍ ያገኘ አንድ ሽማግሌ የስብሰባው ሊቀ መንበር ሆኖ ያገለግላል። ሊቀ መንበሩ ካሉት ኃላፊነቶች መካከል ስብሰባው በሰዓቱ ተጀምሮ እንዲያልቅ ማድረግ እንዲሁም ክፍል ያቀረቡ ተማሪዎችን ማመስገንና ለእነሱ ምክር መስጠት ይገኙበታል።
19 ለክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ በየጊዜው ስንዘጋጅ እንዲሁም በስብሰባው ላይ ስንገኝና ተሳትፎ ስናደርግ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀታችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግንዛቤያችን፣ ምሥራቹን ለመስበክ ያለን ልበ ሙሉነት እንዲሁም ደቀ መዛሙርት የማድረግ ችሎታችን እያደገ ይሄዳል። በስብሰባው ላይ የሚገኙ ያልተጠመቁ ሰዎችም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ከሚያሳልፉት አስደሳች ጊዜም ሆነ ከሚያዳምጧቸው በመንፈሳዊ የሚያንጹ ክፍሎች ጥቅም ያገኛሉ። ለዚህም ሆነ ለሌሎች ስብሰባዎች ለመዘጋጀት በዎችታወር ላይብረሪ፣ በጄደብልዩ ላይብረሪ (JW Library®)፣ በመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት (በቋንቋችን የሚገኝ ከሆነ) እንዲሁም በስብሰባ አዳራሽ በሚገኘው ቤተ መጻሕፍት መጠቀም እንችላለን። በስብሰባ አዳራሽ የሚገኘው ቤተ መጻሕፍት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ የተለያዩ ጽሑፎች፣ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (በአማርኛ አይገኝም) ወይም የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች እንዲሁም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ ጥቅስ ማውጫ (ኮንኮርዳንስ)፣ መዝገበ ቃላትና ሌሎች ጠቃሚ የማመሳከሪያ ጽሑፎች ይኖሩታል። ማንኛውም ሰው ከስብሰባ ሰዓት ውጭ ይህን ቤተ መጻሕፍት መጠቀም ይችላል።
የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች
20 አስፋፊዎች ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በሳምንቱ ውስጥ በተለያዩ ቀናት ለጥቂት ደቂቃዎች የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ያደርጋሉ። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ስብሰባዎች የሚደረጉት በግል መኖሪያ ቤቶች ወይም አመቺ በሆኑ ሌሎች ቦታዎች ነው። የስብሰባ አዳራሹንም ለዚህ ዓላማ መጠቀም ይቻላል። አስፋፊዎች አነስ ባሉ ቡድኖች ተከፋፍለው በጉባኤው ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች የስምሪት ስብስባ ማድረጋቸው ወደ ስምሪት ስብሰባቸውም ሆነ ወደ ክልላቸው መሄድ ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። በተጨማሪም አስፋፊዎቹን ለመመደብ የሚውለው ጊዜ አጭር ይሆናል፤ በመሆኑም አስፋፊዎች ቶሎ ወደ ክልላቸው መሄድ ይችላሉ። የቡድን የበላይ ተመልካቹም በቡድኑ ውስጥ ላሉት አስፋፊዎች በደንብ ትኩረት መስጠት እንዲችል ይረዳዋል። ቡድኖቹ ለየብቻቸው መሰብሰባቸው ጥቅም ቢኖረውም ከአንድ በላይ ቡድኖች አብረው እንዲሰበሰቡ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችም ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በሳምንቱ መሃል አገልግሎት የሚወጡት አስፋፊዎች ጥቂት ከሆኑ ቡድኖቹን መቀላቀል ወይም ሁሉም ቡድኖች በስብሰባ አዳራሹ ወይም አመቺ በሆነ ሌላ ቦታ አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ማድረግ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እንዲህ መደረጉ አስፋፊዎች የአገልግሎት ጓደኛ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም ጉባኤው ዓለማዊ በዓላት ባሉባቸው ቀናት የስምሪት ስብሰባውን በስብሰባ አዳራሹ ማድረጉን አመቺ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። ከመጠበቂያ ግንብ ጥናት በኋላም ጉባኤው ሁሉም ቡድኖች አንድ ላይ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንዲያደርጉ ሊመርጥ ይችላል።
21 የመስክ አገልግሎት ቡድኖቹ የስምሪት ስብሰባ የሚያደርጉት በተናጠል ከሆነ በዋነኝነት ስብሰባውን የመምራት ኃላፊነት የሚኖርበት የቡድን የበላይ ተመልካቹ ነው። አልፎ አልፎ የቡድን የበላይ ተመልካቹ፣ ረዳቱ ወይም ብቃት ያለው ሌላ ወንድም የስምሪት ስብሰባውን እንዲመራ ሊመድብ ይችላል። ስብሰባውን የሚመራው ወንድም ለመስክ አገልግሎት የሚጠቅምና ተግባራዊ የሚሆን ሐሳብ ለማቅረብ መዘጋጀት አለበት። ምደባው ካለቀ በኋላ ከመካከላቸው አንዱ ይጸልያል። ከዚያም ቡድኑ ወዲያውኑ ወደ አገልግሎት ክልሉ መሄድ ይኖርበታል። የስምሪት ስብሰባ ከአምስት እስከ ሰባት ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ አለበት፤ የስምሪት ስብሰባው ከጉባኤ ስብሰባ በኋላ የሚደረግ ከሆነ ደግሞ ከዚያም ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማለቅ ይኖርበታል። ስብሰባው አገልግሎት የሚወጡትን አስፋፊዎች በሚያበረታታና በሚጠቅም መንገድ መቅረብ የሚኖርበት ከመሆኑም ሌላ አስፋፊዎች ከአገልግሎት ጋር የተያያዘ መመሪያ ሊያገኙበት ይገባል። አዲሶች ወይም እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሌሎች አስፋፊዎች ሥልጠና እንዲያገኙ ልምድ ካላቸው አስፋፊዎች ጋር ማገልገል ይችላሉ።
ለአዳዲስ ወይም ለትናንሽ ጉባኤዎች የሚደረጉ የስብሰባ ዝግጅቶች
22 ደቀ መዛሙርት የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር በጨመረ መጠን የጉባኤዎችም ቁጥር ይጨምራል። በአብዛኛው አዲስ ጉባኤ እንዲቋቋም ማመልከቻ የሚልከው የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ትናንሽ ቡድኖች በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጉባኤ ሥር መሆናቸው የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
23 አንዳንድ ጊዜ ትናንሽ ጉባኤዎች እህቶች ብቻ የሚገኙባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ አንዲት እህት በጉባኤው ውስጥ ስትጸልይ ወይም ስብሰባ ስትመራ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ በማክበር ራሷን ትሸፍናለች። (1 ቆሮ. 11:3-16) አብዛኛውን ጊዜ ወደ አድማጮች ዞራ በመቀመጥ ስብሰባውን ትመራለች። እህቶች በስብሰባ ላይ ንግግር አያቀርቡም። ከዚህ ይልቅ ድርጅቱ ያዘጋጀውን ጽሑፍ ካነበቡ በኋላ በዚያ ላይ ሐሳብ ይሰጣሉ፤ አሊያም ለለውጥ ያህል ትምህርቱን በውይይት ወይም በሠርቶ ማሳያ መልክ ያቀርቡታል። ቅርንጫፍ ቢሮው በጉባኤው ውስጥ ያለች አንዲት እህት ከቢሮው ጋር የደብዳቤ ልውውጥ እንድታደርግና ስብሰባዎችን እንድትመራ ይመድባል። ብቃት ያላቸው ወንድሞች ሲገኙ ደግሞ እነዚህን ኃላፊነቶች እነሱ እንዲወጡ ይደረጋል።
የወረዳ ስብሰባዎች
24 በአንድ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ጉባኤዎች በዓመት ሁለት ጊዜ የአንድ ቀን የወረዳ ስብሰባ እንዲያደርጉ ዝግጅት ይደረጋል። እነዚህ አስደሳች ወቅቶች ስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ ለሌሎች ክርስቲያናዊ ፍቅር በማሳየት ረገድ ‘ልባቸውን ወለል አድርገው የሚከፍቱበት’ አጋጣሚ ይሰጧቸዋል። (2 ቆሮ. 6:11-13) የይሖዋ ድርጅት ለመንጋው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት የስብሰባዎቹን ጭብጥ ይመርጣል፤ እንዲሁም በስብሰባዎቹ ላይ የሚቀርቡ የተለያዩ ክፍሎችን ያዘጋጃል። ትምህርቱ በንግግሮች፣ በሠርቶ ማሳያዎች፣ በመነባንቦችና በቃለ መጠይቆች እንዲሁም በሠርቶ ማሳያ መልክ በሚቀርቡ ተሞክሮዎች አማካኝነት ይቀርባል። እንዲህ ዓይነቱ ወቅታዊ ትምህርት በስብሰባው ላይ የተገኙትን ሁሉ ይገነባል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በጥምቀት ማሳየት የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ።
የክልል ስብሰባዎች
25 በዓመት አንድ ጊዜ፣ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ጉባኤዎችን ያቀፈ የክልል ስብሰባ ይደረጋል። ይህ ስብሰባ ብዙውን ጊዜ የሚቆየው ለሦስት ቀናት ነው። አነስ ያሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በሥራቸው የሚገኙ ጉባኤዎች በሙሉ አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ማድረግ ሊመርጡ ይችላሉ። ከሁኔታዎች ወይም ድርጅቱ ከሚሰጠው መመሪያ አንጻር ለእነዚህ ስብሰባዎች የሚደረገው ዝግጅት ከአገር አገር ሊለያይ ይችላል። አልፎ አልፎ ደግሞ በአንዳንድ አገሮች ብሔራት አቀፍ ወይም ልዩ የክልል ስብሰባዎች የሚደረጉ ሲሆን ከተለያዩ አገሮች የመጡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ሊገኙ ይችላሉ። ባለፉት ዓመታት በርካታ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጓቸው ትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ አግኝተዋል።
26 የክልል ስብሰባዎች የይሖዋ ሕዝቦች አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን በማምለክ የሚያሳልፏቸው አስደሳች ወቅቶች ናቸው። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ተጨማሪ የእውነት እውቀት የሚገለጥበት ጊዜም አለ። በአንዳንድ የክልል ስብሰባዎች ላይ በግልና በጉባኤ የምናጠናቸው ወይም በመስክ አገልግሎት ላይ የምንጠቀምባቸው አዳዲስ ጽሑፎች ይወጣሉ። ከዚህም ሌላ በክልል ስብሰባዎች ላይ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል። የክልል ስብሰባዎች ለመንፈሳዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። እነዚህ ስብሰባዎች የይሖዋ ሕዝቦች ዓለም አቀፍ የወንድማማች ኅብረት ያላቸው ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች እንደሆኑና የኢየሱስ ክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ለይቶ የሚያሳውቀው ምልክት እንዳላቸው የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።—ዮሐ. 13:35
27 የይሖዋ ሕዝቦች በሚያደርጓቸው የጉባኤ፣ የወረዳና የክልል ስብሰባዎች ላይ መገኘታችን የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያናዊ እምነታችንን ሊያዳክሙ ከሚችሉ ዓለማዊ ተጽዕኖዎች ጥበቃ እናገኛለን። እነዚህ ስብሰባዎች ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ ያመጣሉ። (መዝ. 35:18፤ ምሳሌ 14:28) በዚህ የፍጻሜ ዘመን ይሖዋ ራሳቸውን ለእሱ የወሰኑ ሕዝቦቹ በመንፈሳዊ የሚታደሱባቸውን እነዚህን ዝግጅቶች በማድረጉ ልናመሰግነው ይገባል።
የጌታ ራት
28 በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በዓመት አንድ ጊዜ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል ወይም የጌታ ራትን ለማክበር ይሰበሰባሉ። (1 ቆሮ. 11:20, 23, 24) የይሖዋ ሕዝቦች በዓመት ውስጥ ከሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጡት ለዚህ ስብሰባ ነው። የመታሰቢያውን በዓል እንድናከብር ቀጥተኛ ትእዛዝ ተሰጥቶናል።—ሉቃስ 22:19
29 የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ቀን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው የፋሲካ በዓል ከሚከበርበት ቀን ጋር ተመሳሳይ ነው። (ዘፀ. 12:2, 6፤ ማቴ. 26:17, 20, 26) ፋሲካ እስራኤላውያን በ1513 ዓ.ዓ. ከግብፅ ነፃ የወጡበትን ቀን የሚያከብሩበት ዓመታዊ በዓል ነበር። በዚያን ጊዜ ይሖዋ የመጀመሪያው የጨረቃ ወር 14ኛ ቀን፣ እስራኤላውያን የፋሲካን በግ የሚበሉበትና ከግብፅ ባርነት ነፃ የሚወጡበት ቀን እንዲሆን ወሰነ። (ዘፀ. 12:1-51) በዓሉ የሚውልበት ዕለት የሚሰላው በጸደይ ወራት የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ እኩል በሚሆንበት ቀን አካባቢ በኢየሩሳሌም አዲስ ጨረቃ ከታየችበት ዕለት አንስቶ 13 ቀን በመቁጠር ነው። አብዛኛውን ጊዜ የመታሰቢያው በዓል የሚውለው በጸደይ ወራት የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ እኩል የሚሆንበትን ዕለት ተከትሎ የመጀመሪያዋ ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት ቀን ነው።
30 የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበትን መንገድ አስመልክቶ ኢየሱስ ራሱ የተናገረው ሐሳብ በማቴዎስ 26:26-28 ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ይህ በዓል ሚስጥራዊ ትርጉም ያለው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ሳይሆን በሰማይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ አብረው እንዲገዙ የተጠሩ ሰዎች ተካፋይ የሚሆኑበት ምሳሌያዊ ራት ነው። (ሉቃስ 22:28-30) ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሌሎች ክርስቲያኖችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሁሉ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ባይካፈሉም በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ይበረታታሉ። በበዓሉ ላይ መገኘታቸው ይሖዋ አምላክ ለመላው የሰው ዘር ጥቅም ሲል በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ላደረገው ዝግጅት አድናቆት እንዳላቸው ያሳያል። የመታሰቢያው በዓል ከመከበሩ በፊት፣ ሰዎች ይህን ዝግጅት በጉጉት እንዲጠባበቁና መጽሐፍ ቅዱስ የማጥናት ፍላጎታቸው ይበልጥ እንዲነሳሳ የሚያደርግ ልዩ የሕዝብ ንግግር ይቀርባል።
31 የይሖዋ ምሥክሮች “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች [ለመነቃቃት]” የሚያስችሏቸውን ስብሰባዎች በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ዕብ. 10:24) ታማኝና ልባም ባሪያ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲህ ያሉ ስብሰባዎችን በትጋት ያዘጋጃል። የይሖዋ አገልጋዮችም ሆኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች፣ አዘውትረው እንዲሰበሰቡ ከሚያስችሏቸው እንዲህ ያሉ ዝግጅቶች በሚገባ እንዲጠቀሙ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል። የአምላክ አገልጋዮች፣ ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ለሚያደርጋቸው ዝግጅቶች ልባዊ አድናቆት ማሳየታቸው አንድነት እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለይሖዋ ውዳሴና ክብር ለማምጣት ያስችላቸዋል።—መዝ. 111:1