ከመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች የተሟላ ጥቅም ማግኘት
1. የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች የሚረዱን እንዴት ነው?
1 ውጤታማ የሆኑ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች አገልግሎት ከመውጣታችን በፊት ጥሩ ማበረታቻና ጠቃሚ ትምህርት ይሰጡናል። እነዚህ ስብሰባዎች ከሌሎች አስፋፊዎች ጋር አብረን በማገልገል እርስ በርስ እንድንደጋገፍና ጥሩ ሥልጠና እንድናገኝ ይረዱናል። (ምሳሌ 27:17፤ መክ. 4:9, 10) ታዲያ ከእነዚህ ስብሰባዎች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን?
2. ስብሰባውን የሚመራው ወንድም በውይይቱ ወቅት ሊያነሳቸው የሚችሉ አንዳንድ ሐሳቦች ምንድን ናቸው?
2 ስብሰባውን የሚመራው ወንድም:- በዚህ ስብሰባ ላይ ምን ነገር መቅረብ እንዳለበት የሚገልጽ ዝርዝር ሐሳቦችን የያዘ መመሪያ አስቀድሞ አይዘጋጅም። ስብሰባውን የምትመራ ከሆነ ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብሃል። የዕለት ጥቅሱ ከአገልግሎት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ከሆነ በውይይታችሁ ላይ ልታካትተው የምትችል ቢሆንም ሁልጊዜ የዕለት ጥቅሱን ሐሳብ ብቻ አታቅርብ። በዚያን ቀን ለማገልገል የተሰበሰቡት ወንድሞች ሊጠቀሙበት የሚችሉትን ተግባራዊ ሐሳብ ልታካፍላቸው የምትችለው እንዴት እንደሆነ አስብ። ለምሳሌ ያህል፣ በመግቢያዎች ላይ መወያየት ወይም በሠርቶ ማሳያ እንዲቀርቡ ማድረግ ትችል ይሆናል። ከማመራመር ወይም ከአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ አሊያም በቅርቡ ከተወሰደ የአገልግሎት ስብሰባ ክፍል ላይ ያገኘሃቸውን አንዳንድ ነጥቦች መከለስ ትችል ይሆናል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ በመስክ ሊያጋጥሙ በሚችሉ ሁኔታዎች ላይ ወይም አብዛኞቹ አስፋፊዎች ተመላልሶ መጠየቅ የሚያደርጉ ከሆነ እንዴት የሰዎችን ፍላጎት ማሳደግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር እንደሚችሉ ልትወያዩ ትችላላችሁ። የሚቀርበው ነገር ምንም ይሁን ምን በጋለ ስሜትና በሚያበረታታ መንፈስ አቅርበው።
3. ስብሰባው መካሄድ ያለበት ለስንት ደቂቃ ነው? በዚህ ጊዜስ ምን ምን ነገሮች ሊደረጉ ይገባል?
3 አንዳንዶች እንደሚዘገዩ ብታውቅም ስብሰባውን በሰዓቱ ጀምር። በምትመድብበት ጊዜ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ተጠቀም፤ የአገልግሎት ክልል የሚፈልጉ ካሉም ስጣቸው። ስብሰባው ከ10 እስከ 15 ደቂቃ መብለጥ የለበትም፤ ከጉባኤ ስብሰባ ቀጥሎ የሚካሄድ ከሆነ ደግሞ ጊዜው ከዚህ ሊያጥርም ይችላል። ስብሰባውን ከመደምደምህ በፊት ሁሉም፣ ከማን ጋር እንደተመደቡና የሚያገለግሉበት ክልል የት እንደሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ስብሰባው በጸሎት መደምደም አለበት።
4. ከመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚዎች ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
4 የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላላችሁ:- ልክ እንደ ጉባኤ ስብሰባ ሁሉ በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ላይም በሰዓቱ በመገኘት ለይሖዋ አክብሮት እንዳለንና ለሌሎች እንደምናስብ እናሳያለን። በሚደረገው ውይይት ላይ ተሳትፎ አድርጉ። ስምሪቱን የሚመራው ወንድም ከሌሎች ጋር እንድታገለግሉ ሊመድባችሁ ወይም ከስብሰባው በፊት ከሌላ ሰው ጋር ለማገልገል ቀጠሮ ይዛችሁ ሊሆን ይችላል። አስቀድማችሁ ቀጠሮ ከያዛችሁ፣ ሁልጊዜ ከቅርብ ጓደኞቻችሁ ጋር ብቻ ከማገልገል ይልቅ ከተለያዩ አስፋፊዎች ጋር በማገልገል ‘ፍቅራችሁን ለማስፋት’ ጣሩ። (2 ቆሮ. 6:11-13 NW) ስብሰባው ካለቀ በኋላ አብሯችሁ የተመደበውን ሰው መለወጥ አይኖርባችሁም፤ እንዲሁም ከስምሪት ስብሰባው ቶሎ ወጥታችሁ ወደ ክልላችሁ ሂዱ።
5. የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ዓላማ ምንድን ነው?
5 የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችና የጉባኤ ስብሰባዎች ዓላማ ተመሳሳይ ነው። ሁሉም ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ’ ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። (ዕብ. 10:24, 25) ከእነዚህ ስብሰባዎች ለመጠቀም ጥረት የምናደርግ ከሆነ ‘መልካም ሥራ’ የሆነውን አገልግሎታችንን ለመፈጸም የሚያስችል እርዳታ እናገኛለን!