የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ለሕይወት ዓላማ አገኘች
ኢየሱስ በጎቹን እንደሚያውቃቸው ተናግሯል። (ዮሐንስ 10:14) አንድ ሰው ጥሩ ልብ እና ለሰላም እንዲሁም ለጽድቅ ፍቅር ያለው ከሆነ ወደ ኢየሱስ ተከታዮች ይሳባል። አንዲት የቤልጅግ ሴት ከሕይወቷ ዓላማ እንዳገኘች ሁሉ እንዲህ ያለ ግለሰብም ለሕይወቱ ዓላማ ያገኛል። የእርሷ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፦
በመንፈስ ጭንቀት እየተሠቃየሁና ሕይወቴን ለማጥፋት እያሰብኩ ሳለ የይሖዋ ምሥክሮች በሬን አንኳኩ። ምሥክሮቹ በመከራ ለታመሰው ዓለም ያቀረቧቸው መፍትሔዎች አስደሰቱኝ፤ በዚህ ውስጥ አምላክ ድርሻ አለው የሚለው ሐሳብ ግን አልተስማማሁበትም ነበር። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማየው ግብዝነት ስላስጠላኝ ወደዚያ መሄድ ያቆምኩት ከስምንት ዓመት በፊት ነበር። ነገር ግን ምሥክሮቹ የነገሩኝ ነገር እውነት እንደሆነና ዞሮ ዞሮ ካለ አምላክ መኖር በጣም አስቸጋሪ መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል።
“ያሳዝናል፤ ጥቂት ጉብኝቶችን ካደረጉልኝ በኋላ ከምሥክሮቹ ጋር የነበረኝ ግንኙነት ተቀረጠ። በጣም እበሳጭ ነበር። በቀን ሁለት ፓኬት ሲጋራ አጨስ ነበር፤ የዕፅም እንኳ ሳይቀር ሱሰኛ ሆንኩ። ከሞተው አያቴ ጋር ለመነጋገር በመፈለግ አልፎ አልፎ በመናፍስትነት ሥራ ውስጥ እካፈል ነበር። ከዚህም የተነሳ የአጋንንት ጥቃት ያጋጥመኝ ስለነበር በምሽት ብቻዬን መሆን እንዴት እፈራ ነበር! ይህ ሁኔታ ለወራት ቀጠለ። በመሸ ቁጥር ለብቻዬ የመሆን ሐሳብ በጣም ያስፈራኝ ነበር።
“አንድ ቀን ሁልጊዜ ከምሄድበት የተለየ መንገድ ይዤ በእግሬ ስጓዝ አንድ ትልቅ ሕንፃ ወደሚሠራበት ቦታ ደረስኩ። ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ነበሩ። እየተጠጋሁ ስሄድ በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ስረዳ በጣም ተገረምኩ። ምሥክሮቹ በቤቴ ያደረጉልኝ ጉብኝት አስታወስኩና መላው ዓለም እንደነዚህ ሕዝቦች መኖር ቢችል እንዴት ግሩም ነበር ብዬ አሰብኩ።
“ምሥክሮቹ እንደገና ወደ ቤቴ እንዲመጡ ስለፈለግሁ በአዳራሹ ሥራ ከነበሩት ጥቂቶቹን አነጋገርኳቸው። ወደ አምላክ ጸለይኩ፤ ከአሥር ቀናት በኋላ በመጀመሪያው አነጋግሮኝ የነበረው ሰው ወደ ቤቴ መጣ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን እንድቀጥል ሐሳብ አቀረበልኝ፤ በደስታ ተስማማሁ። ብዙም ሳይቆይ ወደ መንግሥት አዳራሽ ስብሰባዎች ጋበዘኝ። ግብዣውን ተቀበልኩ። እንደዚህ ዓይነት ነገር ፈጽሞ አይቼ አላውቅም! እርስ በርሳቸው የሚዋደዱና ደስተኛ ሕዝቦች ለረጅም ጊዜ ስፈልግ ነበር። ይኸው በመጨረሻ እዚህ አገኘኋቸው!
“ከዚያ ወዲህ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ተገኘሁ። ከሦስት ሳምንት በኋላ የነበረብኝን የማጨስ ልማድ አቆምኩ። የኮከብ ቆጠራ መጻሕፍቶቼን እና ሰይጣናዊ ሙዚቃ ቅጂዎችን አውጥቼ ጣልኳቸው፤ ከዚያ በኋላ ከአጋንንት መዳፍ እንደወጣሁ ይሰማኝ ነበር። ሕይውቴን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አስተካከልኩና ከሦስት ወር በኋላ የምሥራቹን መስበክ ጀመርኩ። ከስድስት ወር በኋላ ተጠመቅሁ። ከተጠመቅሁ ከሁለት ቀን በኋላ የረዳት አቅኚነትን ጀመርኩ።
“ላደረገልኝ መልካም ነገሮች ሁሉ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። በመጨረሻም ሕይወቴ ዓላማ ያለው ሆነ። አዎን፣ የይሖዋ ስም መጠጊያ እና መከታ ያገኘሁበት የጸና ግንብ ነው። (ምሳሌ 18:10) መዝሙር 84፡10ን ሲጽፍ መዝሙራዊው የነበረውን ዓይነት ስሜት ይሰማኛል፦ “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኀጥአን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ።”
ይህች ገር ልብ ያላት ሴት ትርጉም ያለው ሕይወት አገኘች። ይሖዋን በጥሩ ልብ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው እንደርሷ ትርጉም ያለው ለሕይወቱ ሊያገኝ ይችላል።