በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት እና የኋላ ታሪካቸው ጥናት
ጥናት ቁጥር 1—ተስፋይቱን ምድር መጎብኘት
የምድሪቱ ክልሎች፣ ተፈጥሯዊ ገጽታዎች፣ ተራሮችና ሸለቆዎች፣ ወንዞችና ሐይቆች፣ የአየር ንብረት፣ አፈር እንዲሁም ልዩ ልዩ ተክሎች
የጥንቷን ተስፋይቱ ምድር ድንበር የከለለው ይሖዋ አምላክ ነው። (ዘፀ. 23:31፤ ዘኁ. 34:1-12፤ ኢያሱ 1:4) ለብዙ መቶ ዘመናት ይህ አካባቢ የፓለስቲና ምድር እየተባለ ይጠራ የነበረ ሲሆን ይህን ስያሜ ያገኘው ፓለስቲና ከሚለው የላቲን ቃልና ፓለስቲን ከሚለው የግሪክኛ ቃል ነው። ግሪክኛው ቃል ፔሌሼት ከተሰኘው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ነው። በዕብራስይጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ፔሌሼት የሚለው ቃል “ፍልስጤም” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን የአምላክ ሕዝብ ጠላት የነበሩትን የፍልስጤማውያንን ክልል ያመለክታል። (ዘፀ. 15:14) ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህችን ምድር ታማኝ ለነበረው ለአብርሃምና ለዘሮቹ ለማውረስ ተስፋ ሰጥቶ ስለነበረ “ተስፋይቱ ምድር” የሚለው ስያሜ ይበልጥ ተስማሚ ነው። (ዘፍጥረት 15:18፤ ዘዳግም 9:27, 28፤ ዕብራውያን 11:9) ይህ ቦታ ልዩ ልዩ መልክዓ ምድራዊ ገጽታዎች አሉት፤ አጠቃላይ ስፋቱ አነስተኛ ቢሆንም በመላው ምድር የሚገኙ የተለያዩ የተፈጥሮ ገጽታዎችን የያዘ መሆኑ አስደናቂ ነው። ይሖዋ ተስፋ በሰጠው መሠረት ለጥንት ምሥክሮቹ እንዲህ ያለ የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት ውብ ምድር ሊያወርሳቸው ከቻለ ወደፊትም ቢሆን ሕይወታቸውን ለእሱ የወሰኑ አምላኪዎቹን መላዋን ምድር የሚያካልል ገነት በማውረስ እንደሚባርካቸው ጥርጥር የለውም፤ ይህ ገነት በተራሮች፣ በሸለቆዎች፣ በወንዞችና በሐይቆች የተሞላ ይሆናል። አሁን በዓይነ ሕሊናችን ተስፋይቱን ምድር ስንጎበኝ፣ ምድሪቱ ያሏትን የተለያዩ መልክዓ ምድራዊ ገጽታዎች በትኩረት እንከታተል።a
የቆዳ ስፋት
2 አምላክ በዘኁልቁ 34:1-12 ላይ የምድሪቱን ወሰን በተመለከተ ከተናገረው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ተስፋይቱ ምድር ሾጣጣ ቅርጽ አላት። ከሰሜን ወደ ደቡብ ርዝመቷ 480 ኪሎ ሜትር ገደማ ሲሆን የጎን ስፋቷ ደግሞ በአማካይ 56 ኪሎ ሜትር ነበር። መላዋን ተስፋይቱ ምድር በወታደራዊ ኃይል መያዝ የተቻለው በዳዊትና በሰለሞን የግዛት ዘመን ነበር፤ በዚያ ዘመን እነዚህ ነገሥታት በምድሪቱ የሚኖሩ ብዙ ሕዝቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ችለው ነበር። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን የሰፈሩበት ክልል ከዳን እስከ ቤርሳቤህ እየተባለ በጥቅሉ የተገለጸ ሲሆን ይህ ቦታ ከሰሜን እስከ ደቡብ 240 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት የሚሸፍን ነበር። (1 ነገ. 4:25) አገሪቱ ከቀርሜሎስ ተራራ እስከ ገሊላ ባሕር ድረስ ያላት የጎን ስፋት 51 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው፤ በደቡብ በኩል ደግሞ የሜድትራንያን የባሕር ዳርቻ ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ከሚታጠፍበት ቦታ ማለትም ከጋዛ እስከ ሙት ባሕር ድረስ ያለው አካባቢ የጎን ስፋቱ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ ነው። ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያለው እስራኤላውያን የሰፈሩበት ይህ ቦታ ስፋቱ 15,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ገደማ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባሉ (በመጀመሪያ ቃል ከተገባው የተስፋይቱ ምድር ወሰን ውጭ በሆኑ) ቦታዎችም ሰፍረው ነበር፤ በመሆኑም እስራኤላውያን የሰፈሩበት ክልል በአጠቃላይ 26,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆናል።
በተስፋይቱ ምድር ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች
3 ተስፋይቱን ምድር ስንጎበኝ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ገጽታዎችን እንቃኛለን። ከታች የቀረበው ዝርዝር መግለጫ በዚህ ጥናት ላይ የሚገኘውን ካርታ ለመረዳት የሚያስችል ሲሆን በካርታው ላይ የቦታዎቹን ወሰን በተቻለ መጠን በትክክል ለማስቀመጥ ጥረት ተደርጓል።
መልክዓ ምድራዊ ክልሎች
A. የታላቁ ባሕር ዳርቻ—ኢያሱ 15:12
B. ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉ ሜዳዎች
1. የአሴር ሜዳ—መሳ. 5:17
2. ባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኝ የዶር መሬት—ኢያሱ 12:23
3. የሳሮን የግጦሽ መሬቶች—1 ዜና 5:16
4. የፍልስጤም ሜዳ—ዘፍ. 21:32፤ ዘፀ. 13:17
5. ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚዘልቀው ማዕከላዊ ሸለቆ
ሀ. የመጊዶ ሜዳ (ኤዝድራኢሎን)—2 ዜና 35:22
ለ. የኢይዝራኤል ሸለቆ—መሳ. 6:33
C. ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉት ተራራማ ክልሎች
1. የገሊላ ኮረብታዎች—ኢያሱ 20:7፤ ኢሳ. 9:1
2. የቀርሜሎስ ኮረብታዎች—1 ነገ. 18:19, 20, 42
3. የሰማርያ ኮረብታዎች—ኤር. 31:5፤ አሞጽ 3:9
5. ኮረብታማው የይሁዳ አገር—ኢያሱ 11:21
6. የይሁዳ ምድረ በዳ (የሺሞን)—መሳ. 1:16፤ 1 ሳሙ. 23:19
8. የፋራን ምድረ በዳ—ዘፍ. 21:21፤ ዘኁ. 13:1-3
D. ታላቁ አረባ (ስምጥ ሸለቆ)—2 ሳሙ. 2:29፤ ኤር. 52:7
1. የሁላ ረባዳ ቦታ
2. በገሊላ ባሕር ዙሪያ የሚገኝ ክልል—ማቴ. 14:34፤ ዮሐ. 6:1
3. የዮርዳኖስ ሸለቆ አውራጃ (ጎር)—1 ነገ. 7:46፤ 2 ዜና 4:17፤ ሉቃስ 3:3
4. ጨው (ሙት) ባሕር (የአረባ ባሕር)—ዘኁ. 34:3፤ ዘዳ. 4:49፤ ኢያሱ 3:16
5. አረባ (ከጨው ባሕር በስተ ደቡብ)—ዘዳ. 2:8
E. ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያሉ ተራሮችና አምባዎች—ኢያሱ 13:9, 16, 17, 21፤ 20:8
1. የባሳን ምድር—1 ዜና 5:11፤ መዝ. 68:15
2. የጊልያድ ምድር—ኢያሱ 22:9
3. የአሞንና የሞዓብ ምድር—ኢያሱ 13:25፤ 1 ዜና 19:2፤ ዘዳ. 1:5
4. የኤዶም አምባ—ዘኁ. 21:4፤ መሳ. 11:18
F. የሊባኖስ ተራሮች—ኢያሱ 13:5
A. የታላቁ ባሕር ዳርቻ
4 ጉብኝታችንን ከምዕራብ ስንጀምር ውብ በሆነውና ሰማያዊ ቀለም ባለው የሜድትራንያን ባሕር አጠገብ ያለውን የባሕር ዳርቻ እንመለከታለን። በባሕሩ ዳርቻ ሰፊ ቦታ የሚሸፍኑ ትላልቅ የአሸዋ ክምሮች በመኖራቸው ከቀርሜሎስ ተራራ በታች ያለው ጥሩ ተፈጥሯዊ ወደብ፣ በኢዮጴ የሚገኘው ብቻ ነው፤ ከቀርሜሎስ በስተ ሰሜን ግን ብዙ ጥሩ የተፈጥሮ ወደቦች አሉ። በዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ፊንቄያውያን በባሕር ላይ ጉዞ ዝነኞች ሆነው ነበር። ፀሐያማ በሆነው በዚህ የባሕር ዳርቻ ዓመታዊው የሙቀት መጠን በአማካይ 19 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ስለሆነ አየሩ ተስማሚና ደስ የሚል ነው፤ በበጋ ግን በጣም ሞቃት ሲሆን ጋዛ ውስጥ የቀኑ የሙቀት መጠን በአማካይ 34 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል።
B-1 የአሴር ሜዳ
5 በባሕሩ ዳርቻ የሚገኘው ይህ ሜዳ ከቀርሜሎስ ተራራ በስተ ሰሜን 40 ኪሎ ሜትር ድረስ ይዘልቃል። የዚህ ሜዳ ከፍተኛው የጎን ስፋት 13 ኪሎ ሜትር ገደማ ሲሆን ለአሴር ነገድ በተመደበው ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው። (ኢያሱ 19:24-30) መሬቱ ለምና ጥሩ ምርት የሚሰጥ ስለነበረ ለሰለሞን ቤተ መንግሥት የሚሆን ቀለብ ከዚህ አካባቢ ይመጣ ነበር።—ዘፍ. 49:20፤ 1 ነገ. 4:7, 16
B-2 ባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኝ የዶር መሬት
6 ይህ መሬት የቀርሜሎስን የተራራ ሰንሰለት 32 ኪሎ ሜትር ያህል ያዋስነዋል። የመሬቱ የጎን ስፋት 4 ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ነው። በቀርሜሎስ የተራራ ሰንሰለትና በሜድትራንያን ባሕር መካከል የሚገኝ የባሕር ዳርቻ ነው። በዚህ መሬት ደቡባዊ ክፍል የዶር የወደብ ከተማ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ በስተ ደቡብ ደግሞ የአሸዋ ክምሮች ይገኛሉ። ከዶር ከተማ በስተ ጀርባ ባሉት ኮረብታዎች የሚመረተው ምርጥ እህል በሰለሞን ቤተ መንግሥት ለሚካሄዱ ድግሶች ይቀርብ ነበር። በዚህ ክልል የሚኖር አንድ አስተዳዳሪ ከሰለሞን ሴት ልጆች አንዷን አግብቶ ነበር።—1 ነገ. 4:7, 11
B-3 የሳሮን የግጦሽ መሬቶች
7 ይህ ቦታ በዚያ በሚበቅሉት አበቦች ውበት በሰፊው ይታወቅ ነበር፤ በመሆኑም ነቢዩ ኢሳይያስ ባየው ትንቢታዊ ራእይ ላይ እስራኤላውያን ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ምድራቸው የሚኖረውን ልምላሜና ውበት ለማመልከት ሳሮን መጠቀሱ ተገቢ ነው። (ኢሳ. 35:2) ሳሮን ለምና ውኃ በደንብ የሚያገኝ ምድር ነው። የጎን ስፋቱ ከ16 እስከ 19 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ሜዳማ አካባቢ ሲሆን ከዶር መሬት በስተ ደቡብ አቅጣጫ 64 ኪሎ ሜትር ያህል ይዘልቃል። በዕብራውያን ዘመን በሳሮን ሰሜናዊ ክፍል የባሉጥ ዛፎች የሚበቅሉባቸው ደኖች ነበሩ። ብዙ መንጎች እህሉ ከታጨደ በኋላ እዚያ ተሰማርተው ይግጡ ነበር። ይህ አካባቢ የሳሮን የግጦሽ መሬቶች ተብሎ ይጠራ የነበረው በዚህ ምክንያት ነው። በንጉሥ ዳዊት ዘመን የንጉሡ መንጎች የሚሰማሩት በሳሮን ነበር። (1 ዜና 27:29) በዛሬው ጊዜ በዚህ አካባቢ የብርቱካን ዝርያ የሆኑ ዛፎች በብዛት ይገኛሉ።
B-4 የፍልስጤም ሜዳ
8 ይህ ቦታ የሚገኘው ከሳሮን የግጦሽ መሬቶች በስተ ደቡብ ነው፤ በባሕሩ ዳርቻ 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝማኔ የሚሸፍን ሲሆን ወደ መሃል አገር እስከ 24 ኪሎ ሜትር ድረስ ይገባል። (1 ነገ. 4:21) በባሕር ዳርቻው ላይ የሚገኘው የአሸዋ ክምር አንዳንድ ጊዜ እስከ 6 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ መሃል አገር ይዘልቃል። የዚህ ሜዳ ከፍታ ልክ እንደ ደረጃ እየጨመረ ይሄዳል፤ ከ30 ሜትር ጀምሮ ከፍ እያለ በመሄድ በስተ ደቡብ ከጋዛ በስተ ጀርባ ያለው አካባቢ ሲደርስ ከፍታው 200 ሜትር ይሆናል። አፈሩ ለም ነው፤ ይሁን እንጂ ዝናብ በበቂ ሁኔታ የማያገኝና ድርቅ የሚያጠቃው አካባቢ ነው።
B-5 ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚዘልቀው ማዕከላዊ ሸለቆ
9 ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚዘልቀው ማዕከላዊ ሸለቆ ሁለት ክፍሎች አሉት፤ አንደኛው በስተ ምዕራብ በኩል የሚገኘው የመጊዶ ሜዳ ወይም ኤዝድራኢሎን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በስተ ምሥራቅ የሚገኘው የኢይዝራኤል ሸለቆ ነው። (2 ዜና 35:22፤ መሳ. 6:33) ጠቅላላው ማዕከላዊ ሸለቆ ከዮርዳኖስ ስምጥ ሸለቆ ወደ ሜድትራንያን የባሕር ዳርቻ በቀላሉ ለመጓዝ የሚያስችል አገር አቋራጭ መንገድ ያለው ሲሆን ጠቃሚ የንግድ መስመር ሆኖ ነበር። የመጊዶ ሜዳ፣ በቀርሜሎስ ተራራና በገሊላ ኮረብታዎች መካከል ባለው ጠባብ ቦታ በኩል አልፎ ወደ አሴር ሜዳ፣ ከዚያም ወደ ሜድትራንያን በሚገባው የቂሶን ደረቅ ወንዝ ይጥለቀለቅ ነበር። ይህ ትንሽ ወንዝ በበጋ ወራት ቢደርቅም በሌሎች ወቅቶች ሞልቶ ይፈስሳል።—መሳ. 5:21
10 የኢይዝራኤል ሸለቆ በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ በኩል እስከ ዮርዳኖስ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ሸለቋማ መተላለፊያ የሆነው የኢይዝራኤል ሜዳ 3.2 ኪሎ ሜትር ገደማ የጎን ስፋት ያለው ሲሆን ወደ 19 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርቀት ይሸፍናል። ሸለቆው ከ90 ሜትር ከፍታ ተነስቶ ዝቅ እያለ በመሄድ ቤትሼን አካባቢ ሲደርስ ከባሕር ወለል በታች 120 ሜትር ገደማ ይሆናል። ማዕከላዊ ሸለቆው በጠቅላላ በጣም ለም ሲሆን በተለይ የኢይዝራኤል አካባቢ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ቦታዎች ሁሉ እጅግ ለም ነው። ኢይዝራኤል ማለት “አምላክ ዘር ይዘራል” ማለት ነው። (ሆሴዕ 2:22) ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ይህ አውራጃ በጣም ውብ እንደሆነ ይገልጻሉ። (ዘፍ. 49:15) መጊዶም ሆነ ኢይዝራኤል በእስራኤልና በአጎራባች ብሔራት መካከል በተደረጉ ጦርነቶች ላይ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ቦታዎች ነበሩ፤ ባርቅ፣ ጌድዮን፣ ንጉሥ ሳኦልና ኢዩ ጦርነት ያካሄዱት በዚህ አካባቢ ነበር።—መሳ. 5:19-21፤ 7:12፤ 1 ሳሙ. 29:1፤ 31:1, 7፤ 2 ነገ. 9:27
C-1 የገሊላ ኮረብታዎች
11 ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ስምና መንግሥት የመመሥከር ሥራውን በአብዛኛው ያካሄደው በገሊላ ኮረብታዎች ደቡባዊ ክፍል (እና በገሊላ ባሕር ዙሪያ) ነበር። (ማቴ. 4:15-17፤ ማር. 3:7) አሥራ አንዱን ታማኝ ሐዋርያት ጨምሮ አብዛኞቹ የኢየሱስ ተከታዮች የገሊላ ሰዎች ነበሩ። (ሥራ 2:7) ይህ አውራጃ አንዳንድ ጊዜ ታችኛው ገሊላ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን አካባቢው በጣም ደስ ይላል፤ የኮረብታዎቹ ከፍታ ከ600 ሜትር አይበልጥም። አካባቢው በዓመት ውስጥ ለበርካታ ወራት ዝናብ የሚያገኝ በመሆኑ በረሃማ አይደለም። በጸደይ ወቅት ኮረብታዎቹ በአበቦች የሚያሸበርቁ ሲሆን እያንዳንዱ ረባዳ ቦታም በእህል ሰብል ይሞላል። በትናንሽ አምባዎች ላይ ለግብርና የሚመች ለም አፈር ያለ ሲሆን ኮረብታዎቹ ደግሞ ወይራ ዛፎችና ወይን ለማብቀል ተስማሚ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት እንደ ናዝሬት፣ ቃና እና ናይን ያሉ ከተሞች የሚገኙት በዚህ አካባቢ ነው። (ማቴ. 2:22, 23፤ ዮሐ. 2:1፤ ሉቃስ 7:11) ኢየሱስ ለማስተማር የተጠቀመባቸው በርካታ ምሳሌዎች በዚህ አካባቢ ካለው ሁኔታ በመነሳት የተናገራቸው እንደሆኑ መረዳት ይቻላል።—ማቴ. 6:25-32፤ 9:37, 38
12 በሰሜናዊው ክፍል ወይም በላይኛው ገሊላ የሚገኙት ኮረብታዎች ከ1,100 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ሲሆን የሊባኖስ ተራሮች ግርጌ ናቸው ሊባል ይችላል። ላይኛው ገሊላ ርቆ የሚገኝ ሲሆን ነፋስ የሚበዛበትና ከባድ ዝናብ የሚጥልበት አካባቢ ነው። በጥንት ዘመን በምዕራብ አቅጣጫ ያሉት ሸንተረሮች ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈኑ ነበሩ። ይህ ክልል ለንፍታሌም ነገድ በዕጣ ደርሶት ነበር።—ኢያሱ 20:7
C-2 የቀርሜሎስ ኮረብታዎች
13 ግርማ ሞገስ የተላበሰው የቀርሜሎስ ተራራ በአንድ በኩል ወደ ሜድትራንያን ባሕር ገብቶ ይታያል። ቀርሜሎስ፣ 48 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ከባሕሩ በላይ እስከ 545 ሜትር ከፍ እያለ የሚሄድ ኮረብታማ ሰንሰለት ነው። ከሰማርያ ኮረብታዎች ጀምሮ እስከ ሜድትራንያን ይደርሳል፤ ወደ ባሕሩ ገባ ብሎ የሚገኘው ክፍል፣ በስተ ሰሜን ምዕራብ ጫፍ ላይ ወጣ ብሎ የሚታይ ተረተር ያለው ሲሆን ግርማውና ውበቱ በጣም ይማርካል። (መኃ. 7:5) ቀርሜሎስ ማለት “የፍራፍሬ እርሻ” ማለት ሲሆን ቃሉ በስፋት በሚታወቁት የወይን እርሻዎቹ እንዲሁም በፍራፍሬና በወይራ ዛፎች ያጌጠውን ይህን ለም ባሕረ ገብ መሬት በትክክል ይገልጻል። ኢሳይያስ 35:2 እስራኤላውያን ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ምድራቸው የሚኖረውን ልምላሜ ሲገልጽ ‘የቀርሜሎስን ግርማ ይለብሳል’ ይላል። ኤልያስ የባአልን ካህናት የተገዳደረውና የይሖዋ ታላቅነት ማስረጃ የሆነው “የይሖዋ እሳት” የወረደው በዚህ ቦታ ነው፤ እንዲሁም ኤልያስ፣ የእስራኤል የድርቅ ዘመን በተአምራዊ መንገድ እንዲያበቃ ያደረገው ዝናብ መምጣቱን የሚጠቁም ትንሽ ደመና እንደታየ የተናገረው በቀርሜሎስ አናት ላይ ሆኖ ነበር።—1 ነገ. 18:17-46
C-3 የሰማርያ ኮረብታዎች
14 የዚህ ክልል ደቡባዊ ክፍል ይበልጥ ኮረብታማ ሲሆን በምሥራቅ በኩል ከፍታው እስከ 900 ሜትር ይደርሳል። (1 ሳሙ. 1:1) ይህ አካባቢ፣ በስተ ደቡብ ካለው ከይሁዳ ይልቅ ከፍተኛና ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ ዝናብ ያገኛል። በዚህ ክልል የሰፈሩት የዮሴፍ ታናሽ ልጅ የሆነው የኤፍሬም ዝርያዎች ነበሩ። የዮሴፍ ታላቅ ልጅ ለሆነው ለምናሴ ነገድ እኩሌታ በዕጣ የተመደበው የዚህ ክልል ሰሜናዊ ክፍል በኮረብታዎች የተከበቡ ሸለቆዎችና ትናንሽ ሜዳዎች የሚገኙበት ነው። ኮረብታማው መሬት እምብዛም ለም ባይሆንም በኮረብታው ጎን ታች ታቹን እርከን በመሥራት የወይን አትክልቶችና የወይራ ዛፎችን ማልማት ተችሏል። (ኤር. 31:5) ይሁን እንጂ ሰፋፊ የሆኑት ሸለቆዎች የጥራጥሬ እህል ለማብቀልም ሆነ በአጠቃላይ የግብርና ሥራ ለማከናወን አመቺ ነበሩ። በጥንት ዘመን በዚህ ክልል ብዙ ከተሞች ተበታትነው ይገኙ ነበር። በሰሜናዊው መንግሥት ዘመን የምናሴ ነገድ፣ በተከታታይ ዋና ከተማ ሆነው ላገለገሉት ሦስት ከተሞች ማለትም ለሴኬም፣ ለቲርጻና ለሰማርያ ቀለብ ያቀርብ ነበር፤ በኋላም ጠቅላላው ክልል በዋና ከተማዋ ስም ሰማርያ ተብሎ መጠራት ጀመረ።—1 ነገ. 12:25፤ 15:33፤ 16:24
15 ሙሴ ስለ ዮሴፍ የተናገረው በረከት በእርግጥም በዚህ ምድር ላይ ተፈጽሟል። “ስለ ዮሴፍ እንዲህ አለ፦ ‘ይሖዋ ከሰማይ በሚወርዱ ምርጥ ነገሮች፣ በጤዛ . . . ምድሩን ይባርክ፤ እንዲሁም ፀሐይ በምታስገኛቸው ምርጥ ነገሮች፣ በየወሩ በሚገኝ ምርጥ ፍሬ፣ ጥንታዊ ከሆኑ ተራሮች በሚገኙ ምርጥ ነገሮች፣ ጸንተው ከሚኖሩት ኮረብቶች በሚገኙ ምርጥ ነገሮች።’” (ዘዳ. 33:13-15) አዎ፣ ይህ ምድር ደስ የሚል ነበር። ተራሮቹ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈኑ ነበሩ፤ ሸለቆዎቹ ምርታማ ነበሩ፤ እንዲሁም የበለጸጉና ብዙ ሕዝብ ያለባቸው በርካታ ከተሞች በዚህ አካባቢ ይገኙ ነበር። (1 ነገ. 12:25፤ 2 ዜና 15:8) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ በሰማርያ ምድር የሰበከ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱም እንደዚሁ አድርገዋል፤ በመሆኑም በዚህ ቦታ ብዙ ተከታዮችን አፍርተዋል።—ዮሐ. 4:4-10፤ ሥራ 1:8፤ 8:1, 14
C-4 ሸፌላ
16 ሸፌላ የሚለው ስም “ዝቅተኛ ስፍራ” ማለት ነው፤ ይሁንና የዚህ ቦታ ደቡባዊ ክፍል እስከ 450 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያለው ኮረብታማ አካባቢ ሲሆን ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የሚሄዱ ብዙ ሸለቆዎች አሉት። (2 ዜና 26:10) በባሕር ዳርቻ ላይ ከሚገኘው የፍልስጤም ሜዳ አንስቶ በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ የመሬቱ ከፍታ እየጨመረ ይሄዳል፤ በመሆኑም ይህ አካባቢ እንደ ዝቅተኛ ስፍራ የተቆጠረው በምሥራቅ በኩል ራቅ ብለው ከሚገኙት ከፍ ያሉ የይሁዳ ኮረብታዎች አንጻር ሲታይ ነው። (ኢያሱ 12:8) በሾላ ዛፎች ተሸፍነው የነበሩት የሸፌላ ኮረብታዎች በአሁኑ ጊዜ የወይን አትክልትና የወይራ ዛፎች ያበቅላሉ። (1 ነገ. 10:27) በዚህ ክልል ብዙ ከተሞች ይገኙ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይህ አካባቢ፣ እስራኤልን ከፍልስጤማውያን ወይም በባሕሩ ዳር ካለው ሜዳ በኩል መጥተው ወደ ይሁዳ ለመግባት ከሚሞክሩ ሌሎች ወራሪ ሠራዊቶች የሚለይ ቦታ ሆኖ አገልግሏል።—2 ነገ. 12:17፤ አብ. 19
C-5 ኮረብታማው የይሁዳ አገር
17 ይህ ክልል 80 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 32 ኪሎ ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን ከባሕር ወለል በላይ ከ600 እስከ 1,000 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያለው ዓለታማ አካባቢ ነው። በጥንት ዘመን በዚህ አካባቢ ሳንቃ ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ ዛፎች በብዛት ይገኙ ነበር፤ በተለይም በምዕራብ በኩል ኮረብታዎቹና ሸለቆዎቹ በእህል ማሳዎች፣ በወይራ ዛፎችና በወይን አትክልት እርሻዎች የተሸፈኑ ነበሩ። ለመላ አገሪቱ የሚሆን ምርጥ እህል፣ ዘይትና ወይን በብዛት የሚመረተው በዚህ አውራጃ ነበር። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለው አካባቢ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ብዙ የደን መራቆት የደረሰበት በመሆኑ ያኔ የነበረውን ልምላሜ አጥቷል። በክረምት ወቅት እንደ ቤተልሔም ባሉት በከፍታ ቦታ የሚገኙ ስፍራዎች ላይ አንዳንድ ጊዜ በረዶ ይጥላል። በጥንት ዘመን ይሁዳ ለከተሞችና ለምሽጎች ጥሩ ቦታ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር የነበረ ሲሆን በችግር ጊዜ ሕዝቡ ከወራሪዎች ጥቃት ለመዳን ወደነዚህ ተራሮች መሸሽ ይችል ነበር።—2 ዜና 27:4
18 በይሁዳና በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራት ኢየሩሳሌም ስትሆን በምሽጓ ስም ጽዮን ተብላም ትጠራ ነበር። (መዝ. 48:1, 2) ኢየሩሳሌም መጀመሪያ ላይ የሄኖምና የቄድሮን ሸለቆ ከሚገናኙበት ቦታ በላይ በሚገኝ ከፍታ ስፍራ ላይ የነበረች ኢያቡስ የምትባል የከነዓናውያን ከተማ ነበረች። ዳዊት ማርኮ ከያዛትና ዋና ከተማ ካደረጋት በኋላ ወደ ሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ የሰፋች ሲሆን የኋላ ኋላም ታይሮፕያን ሸለቆንም የምትሸፍን ሆነች። ከጊዜ በኋላ የሄኖም ሸለቆ ገሃነም ተብሎ መጠራት ጀመረ። አይሁዳውያን በዚያ ስፍራ ለጣዖት አምልኮ መሥዋዕት ያቀርቡ ስለነበረ ቦታው ርኩስ ተደርጎ መታየት የጀመረ ሲሆን የቆሻሻና የወንጀለኞች አስከሬን መጣያ ቦታ ሆነ። (2 ነገ. 23:10፤ ኤር. 7:31-33) በመሆኑም በዚያ የሚነድደው እሳት ሙሉ በሙሉ መጥፋትን የሚያመለክት ምሳሌ ሆነ። (ማቴ. 10:28፤ ማር. 9:47, 48) ኢየሩሳሌም ከቄድሮን ሸለቆ በስተ ምዕራብ ከሚገኘው ከሰሊሆም ኩሬ የተወሰነ ውኃ ታገኝ የነበረ ሲሆን ሕዝቅያስ ይህን ኩሬ ለመጠበቅ ሲል ቅጥር በመገንባት ኩሬው የከተማዋ ክፍል እንዲሆን አድርጎ ነበር።—ኢሳ. 22:11፤ 2 ዜና 32:2-5
C-6 የይሁዳ ምድረ በዳ (የሺሞን)
19 የሺሞን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለይሁዳ ምድረ በዳ የተሰጠ ስም ሲሆን “በረሃ” ማለት ነው። (1 ሳሙ. 23:19 የግርጌ ማስታወሻ) ይህ ስያሜ ምንኛ ገላጭና ተስማሚ ነው! በምሥራቅ በኩል አባጣ ጎርባጣ የሆኑ እንዲሁም የኖራ ድንጋዮች ያሉባቸው በረሃማ የይሁዳ ኮረብታዎች በዚህ ምድረ በዳ ይገኛሉ፤ ኮረብታዎቹ ወደ ሙት ባሕር እየተቃረቡ ሲሄዱ በየ24 ኪሎ ሜትሩ ከፍታቸው ከ900 ሜትር በላይ ዝቅ እያለ ይሄዳል፤ በሙት ባሕር አቅራቢያ ሹል ጫፍ ያላቸው ገደሎች ይታያሉ። በየሺሞን ከተሞች የሌሉ ሲሆን ጥቂት የሰፈራ መንደሮች ብቻ ይገኛሉ። ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል የሸሸው ወደዚህ ምድረ በዳ ሲሆን አጥማቂው ዮሐንስም የሰበከው በዚህ ምድረ በዳና በዮርዳኖስ መካከል ባለው አካባቢ ነበር፤ እንዲሁም ኢየሱስ ለ40 ቀናት በጾመበት ጊዜ ብቻውን ሆኖ የቆየው በዚህ ክልል ነበር።b—1 ሳሙ. 23:14፤ ማቴ. 3:1፤ ሉቃስ 4:1
C-7 ኔጌብ
20 ኔጌብ ከይሁዳ ኮረብታዎች በስተ ደቡብ የሚገኝ ሲሆን አብርሃምና ይስሐቅ ለብዙ ዓመታት በዚህ አካባቢ ኖረዋል። (ዘፍ. 13:1-3፤ 24:62) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን አካባቢ ደቡባዊ ክፍል “የጺን ምድረ በዳ” በማለት ይጠቅሰዋል። (ኢያሱ 15:1) ከፊል በረሃማ የሆነው ኔጌብ በሰሜን በኩል ካለው ከቤርሳቤህ አውራጃ አንስቶ በደቡብ በኩል እስካለው እስከ ቃዴስ በርኔ ይዘልቃል። (ዘፍ. 21:31፤ ዘኁ. 13:1-3, 26፤ 32:8) ይህ ምድር፣ ከይሁዳ ኮረብታዎች ተነስቶ ወደ ታች ዝቅ እያለ የሚሄድ ሲሆን ሸንተረሮቹ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የተዘረጉ ናቸው፤ ይህም ፍልሰትንና ከደቡብ አቅጣጫ የሚመጣን ወረራ ይከላከላል። ይህ ምድር በኔጌብ ምሥራቃዊ ክፍል ካሉት ኮረብታዎች አንስቶ ከፍታው ዝቅ እያለ በመሄድ በስተ ምዕራብ ባሕሩ ዳርቻ አካባቢ ሲደርስ በረሃማ ሜዳ ይሆናል። በጋ ሲመጣ፣ ደረቅ ወንዝ ባለባቸው ሸለቆዎች አጠገብ ካሉ አካባቢዎች በቀር ምድሩ ደረቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጉድጓድ በመቆፈር ውኃ ማግኘት ይቻላል። (ዘፍ. 21:30, 31) በአሁኑ ጊዜ የእስራኤል መንግሥት የኔጌብን አንዳንድ ክፍሎች በመስኖ እያለማቸው ነው። “የግብፅ ወንዝ” የኔጌብ ደቡባዊ ምዕራብ ክፍልና የተስፋይቱ ምድር ደቡባዊ ክፍል የድንበር ምልክት ሆኖ ያገለግላል።—ዘፍ. 15:18
C-8 የፋራን ምድረ በዳ
21 ከኔጌብ በስተ ደቡብ ከጺን ምድረ በዳ ጋር የሚገናኘው ቦታ የፋራን ምድረ በዳ ተብሎ ይጠራል። እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲሄዱ ይህን ምድረ በዳ ያቋረጡ ሲሆን ሙሴ 12ቱን ሰላዮች የላከው ከፋራን ምድረ በዳ ነበር።—ዘኁ. 12:16–13:3
D. ታላቁ አረባ (ስምጥ ሸለቆ)
22 በምድር ላይ ካሉት ለየት ያለ የመሬት አቀማመጥ ያላቸው ቦታዎች አንዱ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ተስፋይቱን ምድር ከሰሜን እስከ ደቡብ የሚያቋርጠው የስምጥ ሸለቆው ክፍል “አረባ” ተብሎ ይጠራል። (ኢያሱ 18:18) በላይኛው የምድር ንጣፍ ላይ የተፈጠረው ይህ ክፍተት በ2 ሳሙኤል 2:29 ላይ ሸለቆ ተብሎም ተጠርቷል። ከስምጥ ሸለቆው በስተ ሰሜን የሄርሞን ተራራ ይገኛል። (ኢያሱ 12:1) ስምጥ ሸለቆው ከሄርሞን ግርጌ ተነስቶ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ታች እያቆለቆለ በመሄድ ሙት ባሕር ጋ ሲደርስ ከፍታው ከባሕር ወለል በታች 800 ሜትር ያህል ይሆናል። አረባ፣ ከሙት ባሕር ደቡባዊ ጫፍ ተነስቶ ከፍ እያለ በመሄድ በሙት ባሕርና በአቃባ ባሕረ ሰላጤ መካከል ያለ ቦታ ጋ ሲደርስ ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ ከ200 ሜትር በላይ ይሆናል። ከዚያም ለብ ያለ ውኃ ወዳለበት የቀይ ባሕር ምሥራቃዊ ክፍል እስኪደርስ ድረስ እያቆለቆለ ይሄዳል። በዚህ ጥናት ላይ የሚገኙት ካርታዎች፣ የስምጥ ሸለቆው በአካባቢው ካሉ ቦታዎች ጋር ያለውን ተዛማጅነት ያሳያሉ።
D-1 የሁላ ረባዳ ቦታ
23 ስምጥ ሸለቆው ከሄርሞን ተራራ ግርጌ ጀምሮ ከ490 ሜትር በላይ ወደ ታች በማቆልቆል በባሕር ወለል ላይ ወደሚገኘው የሁላ ክልል ዥው ብሎ ይወርዳል። ይህ አውራጃ ውኃ በደንብ የሚያገኝ ሲሆን በሞቃታማዎቹ የበጋ ወራትም ጭምር ልምላሜውን አያጣም። የዳን ነገድ የሰፈረባት የዳን ከተማ የምትገኘው በዚህ አካባቢ ሲሆን ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ አሥሩ የእስራኤል ነገዶች ለብቻቸው ተገንጥለው መኖር እስከጀመሩበት ጊዜ ድረስ የጣዖት አምልኮ ማዕከል ሆና አገልግላለች። (መሳ. 18:29-31፤ 2 ነገ. 10:29) ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ ያረጋገጠላቸው በጥንቷ የዳን ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው በቂሳርያ ፊልጵስዩስ ሲሆን ከስድስት ቀናት በኋላ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ የተለወጠው በአቅራቢያው ባለው የሄርሞን ተራራ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። ስምጥ ሸለቆው ከሁላ አንስቶ የገሊላ ባሕር ጋ እስኪደርስ ድረስ ወደ ታች እያቆለቆለ ይሄዳል፤ ይህ ቦታ ከባሕር ወለል በታች 210 ሜትር ገደማ ላይ ይገኛል።—ማቴ. 16:13-20፤ 17:1-9
D-2 በገሊላ ባሕር ዙሪያ የሚገኝ ክልል
24 የገሊላ ባሕርና በዙሪያው ያለው አካባቢ በጣም ያምራል።c በዚህ ክልል ከኢየሱስ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ብዙ ነገሮች የተከናወኑ መሆኑ ስለ አካባቢው የማወቅ ጉጉታችንን ይጨምረዋል። (ማቴ. 4:23) ባሕሩ፣ የጌንሴሬጥ ሐይቅ ወይም ኪኔሬት እንዲሁም የጥብርያዶስ ባሕር ተብሎም ተጠርቷል። (ሉቃስ 5:1፤ ኢያሱ 13:27፤ ዮሐ. 21:1) ሐይቁ የልብ ቅርጽ ያለው ሲሆን 21 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 11 ኪሎ ሜትር የጎን ስፋት (ሰፊ የሆነው የሐይቁ ክፍል ሲለካ) አለው፤ ውኃው በአካባቢው ለሚኖረው ሕዝብ ሁሉ ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጥ ነበር። ሐይቁ በሁሉም ጎኖቹ ማለት ይቻላል በኮረብታዎች የታጠረ ነው። ይህ ሐይቅ ከባሕር ወለል በታች 210 ሜትር ገደማ ላይ የሚገኝ በመሆኑ አየሩ በክረምት ወቅትም እንኳ ሞቅ ያለና ተስማሚ ነው፤ ሞቃታማ የሆነው የበጋ ወቅት ደግሞ ለረጅም ጊዜ ይቆያል። በኢየሱስ ዘመን ይህ ክልል ዓሣ በማስገር ሥራ በጣም የታወቀ ነበር፤ በተጨማሪም እንደ ኮራዚን፣ ቤተ ሳይዳ፣ ቅፍርናሆምና ጥብርያዶስ ያሉት ሞቅ ደመቅ ያሉ ከተሞች የሚገኙት በባሕሩ ዳርቻ ወይም በአቅራቢያው ነበር። ሰላማዊ የነበረው ሐይቅ በድንገት በማዕበል ሊናጥ ይችላል። (ሉቃስ 8:23) የሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያለው የጌንሴሬጥ ትንሽ ሜዳ ከሐይቁ በስተ ሰሜን ምዕራብ ይገኛል። አፈሩ በጣም ለም ሲሆን በተስፋይቱ ምድር የሚታወቁትን ሁሉንም ዓይነት ሰብሎች ያበቅላል ለማለት ይቻላል። በጸደይ ወራት በልምላሜ የሚያጌጡት ተረተሮች፣ በእስራኤል ምድር ከሚገኝ ከየትኛውም ቦታ የበለጠ ውበት አላቸው።d
D-3 የዮርዳኖስ ሸለቆ አውራጃ (ጎር)
25 ይህ ወደ ታች እያቆለቆለ የሚሄድ ሸለቆ “አረባ” ተብሎም ተጠርቷል። (ዘዳ. 3:17) በዛሬው ጊዜ ያሉት አረቦች ጎር ብለው የሚጠሩት ሲሆን ትርጉሙም “ዝቅተኛ ስፍራ” ማለት ነው። ሸለቆው የሚጀምረው ከገሊላ ባሕር ሲሆን በአጠቃላይ ሲታይ ሰፋ ያለ ነው፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የጎን ስፋቱ 19 ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆናል። የዮርዳኖስ ወንዝ ከሸለቋማው ሜዳ 46 ሜትር ገደማ ዝቅ ብሎ የሚገኝ ሲሆን ከ105 ኪሎ ሜትር ርቀት በኋላ ወደሚገኘው ሙት ባሕር ይገባል፤ እርግጥ፣ ወንዙ የሚጓዘው እየተጠማዘዘ ስለሆነ በአጠቃላይ 320 ኪሎ ሜትር ይጓዛል።e ወንዙ 27 የፏፏቴ መውረጃ ገደሎችን እየዘለለ ሄዶ ሙት ባሕር ጋ በሚደርስበት ጊዜ ከ180 ሜትር ርቀት ላይ ወደ ታች ይወረወራል። ታችኛው የዮርዳኖስ ክፍል ዳርና ዳሩ በዛፎችና በቁጥቋጦዎች የተሞላ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ታማሪስክ፣ ኦሊያንደር እና ሪጋ የተባሉት ዛፎች በብዛት ይገኙበታል፤ በጥንት ዘመን እነዚህ ጥሻዎች የአንበሶችና የግልገሎቻቸው መደበቂያ ነበሩ። ይህ ስፍራ በዛሬው ጊዜ ዞር በመባል የሚታወቅ ሲሆን በጸደይ ወራት በከፊል ውኃ ይተኛበታል። (ኤር. 49:19) እንደ ዱር ባለው በዚህ ጠባብ መሬት ዳርና ዳር ቃታራ የሚባል ለመኖሪያነት ተስማሚ ያልሆነ አካባቢ አለ፤ ይህ ባድማ አካባቢ፣ እስከ ጎር ሜዳዎች ድረስ በትናንሽ አምባዎችና ሸንተረሮች የተሞላ ነው። በጎር ወይም በአረባ ሰሜናዊ ክፍል ያሉት ሜዳዎች ለእርሻ ተስማሚ ናቸው። በሙት ባሕር አቅጣጫ፣ በደቡባዊው ክፍል የሚገኘው የአረባ አምባም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ደረቅ ቢሆንም በአንድ ወቅት በርካታ የተምር ዓይነቶችና በሞቃታማ ክልል የሚገኙ በርካታ የፍራፍሬ ዓይነቶች ያበቅል እንደነበረ ይነገራል። ኢያሪኮ ጥንትም ሆነ ዛሬ በዮርዳኖስ ሸለቆ ውስጥ የምትገኝ በጣም ታዋቂ ከተማ ነች።—ኢያሱ 6:2, 20፤ ማር. 10:46
D-4 ጨው (ሙት) ባሕር
26 ይህ በምድር ገጽ ላይ ካሉት አስደናቂ የውኃ አካላት አንዱ ነው። በባሕሩ ውስጥ ምንም ዓይነት ዓሣ ባለመኖሩና በዳርቻው ላይ የሚበቅሉ ብዙ ተክሎች ባለመኖራቸው ሙት ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። ባሕሩ የሚገኘው በአረባ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ጨው ባሕር ወይም የአረባ ባሕር ብሎ ይጠራዋል። (ዘፍ. 14:3፤ ኢያሱ 12:3) ባሕሩ ከሰሜን እስከ ደቡብ 75 ኪሎ ሜትር ገደማ ሲሆን የጎን ስፋቱ 15 ኪሎ ሜትር ነው። ጨው ባሕር ከሜድትራንያን ባሕር 400 ሜትር ዝቅ ብሎ የሚገኝ በመሆኑ በምድር ላይ ካሉት ሁሉ እጅግ ዝቅተኛው ስፍራ ነው ሊባል ይችላል። በስተ ሰሜን በኩል 400 ሜትር ያህል ጥልቀት አለው። ባሕሩ በሁለቱም ወገን ባዶና ጠፍ በሆኑ ኮረብታዎችና ገደሎች የታጠረ ነው። ንጹሕ ውኃ ከዮርዳኖስ ወንዝ ወደ ባሕሩ የሚገባ ቢሆንም የገባው ውኃ በትነት ካልሆነ በቀር ከባሕሩ የሚወጣበት መንገድ የለም፤ በትነት የሚወጣው ውኃ ወደ ባሕሩ ከሚገባው ውኃ አይተናነስም። እዚያው ታምቆ የሚቀረው ውኃ 25 በመቶ ያህሉ የሟሟ ጠጣር ነገር (በአብዛኛው ጨው) ስለሆነ ለዓሦች መርዛማ ከመሆኑም ሌላ የሰው ዓይን ውስጥ ከገባ ያሳምማል። በሙት ባሕር ዙሪያ ያለውን አካባቢ የሚጎበኙ ሰዎች የምድሩን ባድማነት እንዲሁም በአካባቢው ላይ የደረሰውን ውድመትና ጥፋት ሲመለከቱ በጣም ይገረማሉ። የሙታን ስፍራ ነው ሊባል ይችላል። መላው ክልል በአንድ ወቅት “ልክ እንደ ይሖዋ የአትክልት ስፍራ፣ . . . ውኃ የጠገበ” የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የሙት ባሕር ዙሪያ በአብዛኛው “ባድማ” ሲሆን ላለፉት ወደ 4,000 የሚጠጉ ዓመታት እንዲህ ሆኖ ቆይቷል፤ ይህም በዚያ ስፍራ በሰዶምና በገሞራ ላይ ደርሶ ለነበረው የማይለወጠው የይሖዋ ፍርድ አስደናቂ ምሥክር ይሆናል።—ዘፍ. 13:10፤ 19:27-29፤ ሶፎ. 2:9
D-5 አረባ (ከጨው ባሕር በስተ ደቡብ)
27 የስምጥ ሸለቆው የመጨረሻ ክፍል የሆነው ይህ ቦታ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እስከ 160 ኪሎ ሜትር ይዘልቃል። ይህ ክልል ሙሉ በሙሉ በረሃማ ነው ማለት ይቻላል። ዝናብ የሚጥለው ከስንት ጊዜ አንዴ ሲሆን ፀሐይዋ በጣም ታቃጥላለች። መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ክልል “አረባ” ብሎ ይጠራዋል። (ዘዳ. 2:8) ይህ ክልል፣ መሃል አካባቢ ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ 200 ሜትር ገደማ ይሆናል፤ ከዚያም በቀይ ባሕር ምሥራቃዊ ክፍል ወደሚገኘው ወደ አቃባ ባሕረ ሰላጤ እስኪደርስ ድረስ መሬቱ በደቡብ አቅጣጫ እያቆለቆለ ይሄዳል። ሰለሞን ብዙ መርከቦች ያሠራው በዚህ ማለትም በዔጽዮንጋብር ወደብ ነበር። (1 ነገ. 9:26) በአብዛኞቹ የይሁዳ ነገሥታት ዘመን ይህ የአረባ ክፍል በኤዶም መንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበር።
E. ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያሉ ተራሮችና አምባዎች
28 “ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ” ያለው አካባቢ ከስምጥ ሸለቆው አንስቶ ከፍታው በፍጥነት እየጨመረ ይሄዳል፤ በዚህ የተነሳ በርከት ያሉ አምባዎች በዚህ አካባቢ ይታያሉ። (ኢያሱ 18:7፤ 13:9-12፤ 20:8) በስተ ሰሜን፣ ከጊልያድ ምድር ከፊሉን ጨምሮ ለምናሴ ነገድ የተሰጠው የባሳን ምድር (E-1) ይገኛል። (ኢያሱ 13:29-31) ይህ አካባቢ ለከብቶችና ለግብርና ምቹ የሆነ፣ ከባሕር ወለል በላይ በአማካይ 600 ሜትር ላይ የሚገኝ ልምላሜ የሞላበት አምባ ምድር ነው። (መዝ. 22:12፤ ሕዝ. 39:18፤ ኢሳ. 2:13፤ ዘካ. 11:2) በኢየሱስ ዘመን ከዚህ አካባቢ ብዙ እህል ይላክ የነበረ ሲሆን ዛሬም ቢሆን ምርታማ ነው። ከዚህ አካባቢ በስተ ደቡብ ደግሞ የጊልያድ ምድር (E-2) ይገኛል፤ የዚህ ቦታ ታችኛው ክፍል ለጋድ ነገድ ተመድቦ ነበር። (ኢያሱ 13:24, 25) ይህ ተራራማ ክልል ከፍታው 1,000 ሜትር ይደርሳል፤ በክረምት ጥሩ ዝናብ የሚያገኝ፣ በበጋ ደግሞ ብዙ ጤዛ ያለው አካባቢ ሲሆን ለቀንድ ከብቶች ተስማሚ የሆነ ቦታ ነው። በተለይም በበለሳን ምርቱ የታወቀ ነበር። በዛሬው ጊዜ ምርጥ በሆነው የወይን ምርቱ ይታወቃል። (ዘኁ. 32:1፤ ዘፍ. 37:25፤ ኤር. 46:11) ዳዊት ከአቢሴሎም ሸሽቶ የሄደው ወደ ጊልያድ ምድር ከመሆኑም ሌላ በምዕራባዊው ክፍል፣ ኢየሱስ ”ዲካፖሊስ በተባለው ክልል” ሰብኳል።—2 ሳሙ. 17:26-29፤ ማር. 7:31
29 ‘የአሞናውያን ምድር’ (E-3) የሚገኘው ከጊልያድ በስተደቡብ ነው፤ የዚህ ክልል ግማሹ ክፍል ለጋድ ነገድ ተሰጥቶ ነበር። (ኢያሱ 13:24, 25፤ መሳ. 11:12-28) የዚህ አምባ ከፍታ ቀስ እያለ የሚጨምር በመሆኑ ለበጎች ግጦሽ እጅግ ተስማሚ ነው። (ሕዝ. 25:5) ከዚያም ወደ ደቡብ አቅጣጫ መጓዛችንን ስንቀጥል ‘የሞዓብን ምድር’ እናገኛለን። (ዘዳ. 1:5) ሞዓባውያን በበግ እረኝነት በጣም ታዋቂ የነበሩ ሲሆን እስከ ዛሬም ድረስ የአካባቢው ዋና መተዳደሪያ በግ እርባታ ነው። (2 ነገ. 3:4) ከሙት ባሕር በስተ ደቡብ ምሥራቅ በኩል ደግሞ የኤዶም አምባ (E-4) ይገኛል። እንደ ፔትራ ያሉት የኤዶማውያን ታላላቅ የንግድ ከተሞች ፍርስራሾች እስከ ዛሬም ድረስ ይታያሉ።—ዘፍ. 36:19-21፤ አብ. 1-4
30 ከእነዚህ ኮረብታዎችና አምባዎች በስተ ምሥራቅ ሰፊ ዓለታማ ምድረ በዳ ይገኛል፤ በተስፋይቱ ምድርና በሜሶጶጣሚያ መካከል የሚገኘው ይህ ምድረ በዳ ለጉዞ አመቺ ባለመሆኑ ነጋዴዎች በስተ ሰሜን አቅጣጫ ዙሪያ ጥምጥም ብዙ ኪሎ ሜትሮች መሄድ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ምድረ በዳ በስተ ደቡብ በኩል ከታላቁ አረቢያ በረሃ የአሸዋ ክምሮች ጋር ይገናኛል።
F. የሊባኖስ ተራሮች
31 በተስፋይቱ ምድር መልክዓ ምድር ላይ ጎላ ብለው የሚታዩት የሊባኖስ ተራሮች ናቸው። እነዚህ ተራሮች፣ ትይዩ የሆኑ ሁለት የተራሮች ሰንሰለቶች ናቸው። የላይኛው ገሊላ ከፍታ ቦታዎች የሚነሱት ከሊባኖስ ኮረብታ ግርጌዎች ነው። በብዙ ቦታዎች ላይ እነዚህ ኮረብታዎች እስከ ባሕሩ ዳርቻ ይደርሳሉ። በዚህ የተራራ ሰንሰለት ላይ ከፍተኛው ቦታ ከባሕር ወለል በላይ 3,000 ሜትር ገደማ ላይ ይገኛል። ከሊባኖስ የተራራ ሰንሰለት ትይዩ የሚገኘው ውብ የሆነው የሄርሞን ተራራ፣ ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ 2,814 ሜትር ገደማ ይሆናል። ከሄርሞን ተራራ ላይ እየቀለጠ የሚወርደው በረዶ ለዮርዳኖስ ወንዝ ዋና የውኃ ምንጭ ሲሆን በጸደይ ማብቂያ ላይ ላለው ደረቅ ወቅት የጤዛ ምንጭ ነው። (መዝ. 133:3) የሊባኖስ ተራሮች በተለይ የሚታወቁት ትላልቅ በሆኑት የአርዘ ሊባኖስ ዛፎቻቸው ነው፤ ሰለሞን ቤተ መቅደሱን የገነባው በእነዚህ ዛፎች እንጨት ተጠቅሞ ነው። (1 ነገ. 5:6-10) በዛሬው ጊዜ የቀሩት ጥቂት የአርዘ ሊባኖስ ዛፎች ቢሆኑም በተራሮቹ የታችኛው ክፍል ግን እንደ ጥንቱ ዘመን ሁሉ አሁንም የወይን አትክልት ስፍራዎች፣ የወይራ ዛፎችና የፍራፍሬ ተክሎች ይገኛሉ።—ሆሴዕ 14:5-7
32 የተስፋይቱን ምድር ጉብኝታችንን ስናጠቃልል በምሥራቅ በኩል ባለው አስፈሪ ምድረ በዳና በታላቁ ባሕር መካከል የምትገኘው ይህች ምድር በእስራኤላውያን ዘመን ምን ያህል ውብ እንደነበረች በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንችላለን። በእርግጥም ‘ወተትና ማር የምታፈስ እጅግ በጣም ጥሩ ምድር’ ነበረች። (ዘኁ. 14:7, 8፤ 13:23) ሙሴ ይህችን ምድር እንዲህ በማለት ገልጿታል፦ “አምላክህ ይሖዋ መልካም ወደሆነች ምድር ሊያስገባህ ነው፤ ይህች ምድር ጅረቶች ያሏት፣ በሸለቋማ ሜዳዋና በተራራማ አካባቢዋ ምንጮች የሚፈልቁባትና ውኃዎች የሚንዶለዶሉባት፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ወይን፣ በለስና ሮማን የሚበቅልባት፣ የወይራ ዘይትና ማር የሚገኝባት፣ የምግብ እጥረት የሌለባት፣ ምንም ነገር የማታጣባት፣ ብረት ያለባቸው ድንጋዮች የሚገኙባት እንዲሁም ከተራሮቿ መዳብ ቆፍረህ የምታወጣባት ምድር ናት። በልተህ በምትጠግብበት ጊዜ ስለሰጠህ ስለ መልካሚቱ ምድር አምላክህን ይሖዋን አመስግነው።” (ዘዳ. 8:7-10) ይሖዋ መላዋን ምድር ልክ በተስፋይቱ ምድር አምሳል ክብር የተጎናጸፈች ገነት ለማድረግ ዓላማ ያለው በመሆኑ በእርግጥም በአሁኑ ጊዜ ያሉ ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ሁሉ ምስጋና ሊያቀርቡለት ይገባል።—መዝ. 104:10-24
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 332-3
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 335፤ ነሐሴ 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ፣ ገጽ 6
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 336
d ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 737-40፤ ጥር 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ፣ ገጽ 24፤ ኅዳር 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ፣ ገጽ 24
e ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 334
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
በተስፋይቱ ምድር ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች
(እና አጎራባች ቦታዎች)
ማይል 0 10 20 30 40 50 60
ኪ.ሜ. 0 20 40 60 80
(ስለሚከተሉት መስመሮች ለማወቅ ቀጥሎ ያለውን ገጽ ተመልከት፦ V—V፣ W—W፣ X—X፣ Y—Y እና Z—Z)
መፍቻ
ሜድትራንያን ባሕር
A የታላቁ ባሕር ዳርቻ
ኢዮጴ
B-1 የአሴር ሜዳ
B-2 ባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኝ የዶር መሬት
ዶር
B-3 የሳሮን የግጦሽ መሬቶች
B-4 የፍልስጤም ሜዳ
አሽዶድ
አስቀሎን
ኤቅሮን
ጌት
ጋዛ
B-5 ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚዘልቀው ማዕከላዊ ሸለቆ (የመጊዶ ሜዳ፣
የኢይዝራኤል ሸለቆ)
ቤትሼን
C-1 የገሊላ ኮረብታዎች
ቃና
ናይን
ናዝሬት
ጢሮስ
C-2 የቀርሜሎስ ኮረብታዎች
C-3 የሰማርያ ኮረብታዎች
ቤቴል
ኢያሪኮ
ሰማርያ
ቲርጻ
ሴኬም
C-4 ሸፌላ
ለኪሶ
C-5 ኮረብታማው የይሁዳ አገር
ቤተልሔም
ጌባ
ኬብሮን
ኢየሩሳሌም
C-6 የይሁዳ ምድረ በዳ (የሺሞን)
C-7 ኔጌብ
ቤርሳቤህ
ቃዴስበርኔ
የግብፅ ወንዝ
C-8 የፋራን ምድረ በዳ
D-1 የሁላ ረባዳ ቦታ
ዳን
ቂሳርያ ፊልጵስዩስ
D-2 በገሊላ ባሕር ዙሪያ የሚገኝ ክልል
ቤተሳይዳ
ቅፍርናሆም
ኮራዚን
የገሊላ ባሕር
ጥብርያዶስ
D-3 የዮርዳኖስ ሸለቆ አውራጃ (ጎር)
ዮርዳኖስ ወንዝ
D-4 የጨው (ሙት) ባሕር (የአረባ ባሕር)
ጨው ባሕር
D-5 አረባ (ከጨው ባሕር በስተ ደቡብ)
ዔጽዮንጋብር
ቀይ ባሕር
E-1 የባሳን ምድር
ደማስቆ
ኤድራይ
E-2 የጊልያድ ምድር
ራባ
ራሞትጊልያድ
የያቦቅ ሸለቆ
E-3 የአሞንና የሞዓብ ምድር
ሃሽቦን
ቂርሃረሰት
መደባ
አርኖን ሸለቆ
ዘረድ ሸለቆ
E-4 የኤዶም አምባ
ፔትራ
F የሊባኖስ ተራሮች
ሲዶና
የሊባኖስ ተራሮች
ሄርሞን ተራራ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ተስፋይቱን ምድር የሚከፍሉ መስመሮች
(ቦታዎቹን በትክክል ለማወቅ በስተ ግራ በኩል ያለውን ካርታ ተመልከት)
በኤፍሬም በኩል ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የሚያቋርጠው መስመር (V—V)
ሜድትራንያን ባሕር
B-3 የሳሮን የግጦሽ መሬቶች
C-3 የሰማርያ ኮረብታዎች
D-3 አረባ ወይም የዮርዳኖስ ሸለቆ (ጎር)
ቃታራ
ዞር
E-2 የጊልያድ ምድር
ማይል 0 5 10
ኪ.ሜ. 0 8 16
በስተ ግራ፦ ሜትር በስተ ቀኝ፦ ጫማ
+900 +3,000
+600 +2,000
+300 +1,000
0 (የባሕር ወለል) 0
−300 −1,000
−600 −2,000
በይሁዳ በኩል ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ የሚያቋርጠው መስመር (W—W)
ሜድትራንያን ባሕር
B-4 የአሸዋ ክምሮች
የፍልስጤም ሜዳ
C-4 ሸፌላ
C-5 ኮረብታማው የይሁዳ አገር
ኢየሩሳሌም
C-6 የይሁዳ ምድረ በዳ
D-4 ስምጥ ሸለቆ
E-3 የአሞንና የሞዓብ ምድር
ማይል 0 5 10
ኪ.ሜ. 0 8 16
በስተ ግራ፦ ሜትር በስተ ቀኝ፦ ጫማ
+900 +3,000
+600 +2,000
+300 +1,000
0 (የባሕር ወለል) 0
−300 −1,000
−600 −2,000
በይሁዳ በኩል ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የሚያቋርጠው መስመር (X—X)
ሜድትራንያን ባሕር
B-4 የአሸዋ ክምሮች
የፍልስጤም ሜዳ
C-4 ሸፌላ
C-5 ኮረብታማው የይሁዳ አገር
C-6 የይሁዳ ምድረ በዳ
D-4 ስምጥ ሸለቆ
ጨው ባሕር
E-3 የአሞንና የሞዓብ ምድር
ማይል 0 5 10
ኪ.ሜ. 0 8 16
በስተ ግራ፦ ሜትር በስተ ቀኝ፦ ጫማ
+900 +3,000
+600 +2,000
+300 +1,000
0 (የባሕር ወለል) 0
−300 −1,000
−600 −2,000
ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉትን ተራሮች ከደቡብ እስከ ሰሜን የሚያቋርጠው መስመር (Y—Y)
C-7 ኔጌብ
C-5 ኮረብታማው የይሁዳ አገር
C-3 የሰማርያ ኮረብታዎች
B-5 የኢይዝራኤል ሸለቆ
C-1 የገሊላ ኮረብታዎች
F
(የባሕር ወለል)
ማይል 0 5 10 20
ኪ.ሜ. 0 8 16 32
በስተ ግራ፦ ሜትር በስተ ቀኝ፦ ጫማ
+900 +3,000
+600 +2,000
+300 +1,000
0 (የባሕር ወለል) 0
በአረባ ወይም በስምጥ ሸለቆው በኩል ከደቡብ እስከ ሰሜን የሚያቋርጠው መስመር (Z—Z)
D-5
D-4 ጨው ባሕር
D-3 አረባ ወይም የዮርዳኖስ ሸለቆ (ጎር)
D-2 የገሊላ ባሕር
D-1 የሁላ ረባዳ ቦታ
F
ማይል 0 5 10 20
ኪ.ሜ. 0 8 16 32
በስተ ግራ፦ ሜትር በስተ ቀኝ፦ ጫማ
+900 +3,000
+600 +2,000
+300 +1,000
0 (የባሕር ወለል) 0
−300 −1,000
−600 −2,000