-
“ከእናንተ አንድም ሰው አይጠፋም”‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
-
-
ምዕራፍ 26
“ከእናንተ አንድም ሰው አይጠፋም”
ጳውሎስ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጠመው፤ ይህ አጋጣሚ የጳውሎስን ጠንካራ እምነትና ለሰዎች ያለውን ፍቅር አሳይቷል
በሐዋርያት ሥራ 27:1 እስከ 28:10 ላይ የተመሠረተ
1, 2. ጳውሎስ የትኛው ጉዞ ይጠብቀዋል? የትኞቹ ጉዳዮችስ አሳስበውት ሊሆን ይችላል?
ጳውሎስ አገረ ገዢው ፊስጦስ የተናገራቸውን ቃላት በአእምሮው እያውጠነጠነ ነው። “ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” ብሎታል፤ ይህ ውሳኔ ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን እንደሚወስነው ያውቃል። ጳውሎስ ሁለት ዓመት ሙሉ እስር ቤት ውስጥ አሳልፏል፤ ወደ ሮም የሚያደርገው ረጅም ጉዞ ቢያንስ ለውጥ ይሆንለታል። (ሥራ 25:12) ይሁን እንጂ ጳውሎስ በባሕር ላይ ሲጓዝ ያጋጠሙት በርካታ ነገሮችም ወደ አእምሮው መምጣታቸው አይቀርም፤ ንጹሕ አየር እየተነፈሱና የተንጣለለውን አድማስ እያዩ ከመጓዝ ባለፈ አስቸጋሪ ሁኔታዎችም ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ ያውቃል። በመጨረሻም ቄሳር ፊት መቅረብ እንደማይቀርለት ሲያስብ ልቡ መስጋቱ አይቀርም።
2 ጳውሎስ “በባሕር ላይ ለሚያጋጥም አደጋ” እንግዳ አይደለም፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞታል እንዲሁም አንድ ሌሊትና አንድ ቀን በባሕር ላይ አሳልፏል። (2 ቆሮ. 11:25, 26) ከዚህም ሌላ አሁን የሚያደርገው ጉዞ ነፃ ሰው ሆኖ ካደረጋቸው ሚስዮናዊ ጉዞዎች ፈጽሞ የተለየ ነው። አሁን የሚጓዘው እስረኛ ሆኖ ነው፤ ጉዞው ደግሞ እንዲህ የዋዛ አይደለም። ከቂሳርያ እስከ ሮም ያለው ርቀት ከ3,000 ኪሎ ሜትር በላይ ነው። በሰላም ጉዞውን አጠናቅቆ ካሰበበት ይደርስ ይሆን? እሺ፣ መድረሱንስ ይድረስ፤ እዚያስ ምን ይጠብቀው ይሆን? የሞት ፍርድ? ጳውሎስ ይግባኝ ያለው በወቅቱ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ከሁሉ በላይ ኃያል ለሆነው መንግሥት እንደሆነ እናስታውስ።
3. ጳውሎስ ምን ለማድረግ ቆርጦ ነበር? በዚህ ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?
3 ስለ ጳውሎስ እስካሁን ካነበብከው አንጻር ከፊቱ የሚጠብቀውን እያሰበ ተስፋው የሚጨልምበት ወይም በጭንቀት የሚዋጥ ዓይነት ሰው ይመስልሃል? በጭራሽ! እርግጥ ጳውሎስ ከፊቱ መከራ እንደሚጠብቀው ያውቃል፤ ምን ዓይነት ችግሮች የሚለውን ግን በዝርዝር አያውቅም። ታዲያ ከቁጥጥሩ ውጭ ስለሆኑ ጉዳዮች በመጨነቅ ከአገልግሎቱ የሚያገኘውን ደስታ የሚያጣበት ምን ምክንያት አለ? (ማቴ. 6:27, 34) ጳውሎስ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ያውቃል፤ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሰዎች፣ ለገዢዎችም ጭምር የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብክ ተልእኮ ተሰጥቶታል። (ሥራ 9:15) የመጣው ቢመጣ የተሰጠውን ተልእኮ ዳር ለማድረስ ቆርጧል። የእኛስ ቁርጥ አቋም ይህ አይደል? እንግዲያው በዚህ ታሪካዊ ጉዞ ላይ ጳውሎስ ምን እንዳጋጠመው እስቲ እንመልከት፤ ከእሱ ምሳሌ ለሕይወታችን የሚጠቅም ምን ትምህርት እናገኝ ይሆን?
“ነፋሱ ከፊት ለፊታችን ይነፍስ” ነበር (የሐዋርያት ሥራ 27:1-7ሀ)
4. ጳውሎስ ጉዞ የጀመረው በምን ዓይነት መርከብ ነው? እነማንስ አብረውት ነበሩ?
4 ጳውሎስና የተወሰኑ እስረኞች ዩልዮስ በሚባል የጦር መኮንን ኃላፊነት እንዲጓዙ ተወሰነ፤ እሱም ወደ ቂሳርያ በመጣ የንግድ መርከብ ለመሳፈር አሰበ። መርከቡ የመጣው በትንሿ እስያ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ላይ ካለው የአድራሚጢስ ወደብ ነው፤ አድራሚጢስ በሌዝቮስ ደሴት ላይ ካለችው የሚጢሊኒ ከተማ ማዶ የሚገኝ ወደብ ነው። መርከቡ በመጀመሪያ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ከዚያም ወደ ምዕራብ የሚጓዝ ሲሆን ዕቃ ለማራገፍና ለመጫን አንዳንድ ቦታዎች ላይ ይቆማል። እንዲህ ዓይነቶቹ መርከቦች የመንገደኞችን ምቾት ለመጠበቅ ታስበው የተሠሩ አይደሉም፤ በተለይ ደግሞ ለእስረኞች ፈጽሞ አይመቹም። (“የባሕር ጉዞና የንግድ መስመሮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ጥሩነቱ፣ በመንገደኞቹ መካከል ያለው ክርስቲያን ጳውሎስ ብቻ አይደለም። ቢያንስ ሁለት የእምነት ባልንጀሮቹ አብረውት ስላሉ ብቻውን ከወንጀለኞች ጋር ለመጓዝ አልተገደደም፤ አርስጥሮኮስና ሉቃስ ከጎኑ ነበሩ። እንደሚታወቀው፣ ይህን ዘገባ የጻፈው ሉቃስ ነው። እነዚህ ሁለት ታማኝ ወዳጆቹ የጉዟቸውን ወጪ የሸፈኑት ራሳቸው ናቸው? ወይስ እንደ ጳውሎስ አገልጋዮች ተቆጥረው በነፃ ተጓዙ? ዘገባው የሚገልጸው ነገር የለም።—ሥራ 27:1, 2
5. ጳውሎስ በሲዶና ከእነማን ጋር የመገናኘት አጋጣሚ አግኝቷል? ከዚህስ ምን ትምህርት እናገኛለን?
5 በስተ ሰሜን 110 ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ በማግስቱ መርከቡ በሶርያ የባሕር ዳርቻ የምትገኘው ሲዶና ላይ ቆመ። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ዩልዮስ ጳውሎስን የያዘው ከሌሎቹ ወንጀለኞች በተለየ መንገድ ነው፤ ይህን ያደረገው ጳውሎስ፣ ጥፋተኛ መሆኑ ያልተረጋገጠ የሮም ዜጋ ስለሆነ ይመስላል። (ሥራ 22:27, 28፤ 26:31, 32) ጳውሎስ ከመርከብ ወርዶ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ጋ እንዲሄድ ዩልዮስ ፈቀደለት። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ለረጅም ጊዜ የታሰረውን ይህን ሐዋርያ የመንከባከብ አጋጣሚ በማግኘታቸው ምንኛ ተደስተው ይሆን! አንተስ እንደዚህ ዓይነት እንግዳ ተቀባይነት ማሳየት የምትችልበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን? በዚህ መንገድ ፍቅር ስታሳይ አንተም በምላሹ ትታነጻለህ።—ሥራ 27:3
6-8. ከሲዶና እስከ ቀኒዶስ ያለው የጳውሎስ ጉዞ ምን ይመስል ነበር? መስበክ የሚችልባቸው ምን አጋጣሚዎችስ ተከፍተውለት ነበር?
6 መርከቡ ከሲዶና ተነስቶ ጉዞውን በመቀጠል ኪልቅያን አልፎ ሄደ፤ ኪልቅያ የምትገኘው ጳውሎስ ባደገባት በጠርሴስ አቅራቢያ ነው። ሉቃስ ሌላ ቦታ ላይ እንደቆሙ አልጠቀሰም፤ በእርግጥ “ነፋሱ ከፊት ለፊታችን ይነፍስ [ነበር]” ማለቱ አደገኛ ሁኔታ አጋጥሟቸው እንደነበር ይጠቁማል። (ሥራ 27:4, 5) እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢኖርም ጳውሎስ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን ይሰብክ እንደነበር መገመት እንችላለን። ለመርከበኞቹ፣ ለወታደሮቹ እንዲሁም እንደ እሱ እስረኛ ለሆኑትም ሆነ ለሌሎቹ ተሳፋሪዎች መሥክሮላቸው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም፤ መርከቡ በቆመባቸው ወደቦች ላይ ለሚያገኛቸውም ቢሆን መስበኩ አይቀርም። እኛስ ለመስበክ የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በሚገባ እንጠቀምባቸዋለን?
7 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መርከቡ በትንሿ እስያ ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ላይ ወደሚገኘው የሚራ ወደብ ደረሰ። በዚያም ጳውሎስና ሌሎቹ ሰዎች ወደ ጉዟቸው መጨረሻ ይኸውም ወደ ሮም የሚያደርሳቸው ሌላ መርከብ መቀየር ያስፈልጋቸው ነበር። (ሥራ 27:6) በዚያ ዘመን ለሮም አብዛኛውን ስንዴ የምታቀርበው ግብፅ ነበረች፤ እህል የጫኑ የግብፅ መርከቦች ሚራ ወደብ ላይ ይቆሙ ነበር። ዩልዮስ እንዲህ ዓይነት መርከብ አገኘና ወታደሮቹና እስረኞቹ እንዲሳፈሩ አደረገ። ይህ መርከብ ከመጀመሪያው በጣም የሚተልቅ ሳይሆን አይቀርም። መርከቡ ብዙ ዋጋ የሚያወጣ ስንዴ ጭኗል፤ በዚያ ላይ ደግሞ መርከበኞቹን፣ ወታደሮቹን፣ እስረኞቹንና ወደ ሮም የሚሄዱ ሌሎች ሰዎችን ጨምሮ በድምሩ 276 ሰዎችን አሳፍሯል። መርከብ ሲቀይሩ የጳውሎስ የአገልግሎት ክልል እንደሰፋ ግልጽ ነው፤ ደግሞም ጳውሎስ ይህ ሁኔታ የፈጠረውን አጋጣሚ እንደሚጠቀምበት የታወቀ ነው።
8 ቀጥሎ የቆሙት፣ በትንሿ እስያ ደቡብ ምዕራብ ጫፍ ላይ በምትገኘው በቀኒዶስ ነው። ነፋሱ ለጉዞ ተስማሚ ቢሆን ኖሮ ይህ የአንድ ቀን ጉዞ ነበር። ይሁንና ሉቃስ “ለብዙ ቀናት በዝግታ ተጉዘን በስንት ችግር ቀኒዶስ ደረስን” ሲል ጽፏል። (ሥራ 27:7ሀ) የአየሩ ሁኔታ ለጉዞ አስቸጋሪ እየሆነባቸው መጣ። (“አስቸጋሪ የሆነው የሜድትራንያን ነፋስ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ኃይለኛው ነፋስና ማዕበሉ መርከቡን ከዚያም ከዚህም ሲያላጋው ተሳፋሪዎቹ እንዴት እንደሚንገላቱ አስበው።
‘አውሎ ነፋሱ ክፉኛ አንገላታን’ (የሐዋርያት ሥራ 27:7ለ-26)
9, 10. በቀርጤስ አካባቢ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጠሩ?
9 የመርከቡ አዛዥ ከቀኒዶስ ተነስቶ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ጉዞውን ለመቀጠል አቅዶ ነበር፤ ይሁንና በቦታው የነበረው ሉቃስ እንደዘገበው ‘ነፋሱ እንደ ልብ ለመጓዝ አልፈቀደላቸውም።’ (ሥራ 27:7ለ) መርከቡ ከየብስ እየራቀ ሲሄድ በባሕሩ ዳርቻ ካለው ለጉዞ ተስማሚ ሞገድ ራቀ፤ ከሰሜን ምዕራብ የመጣው ኃይለኛ ነፋስ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ገፋው፤ ምናልባትም በፍጥነት እየነዳ ወስዶት ሊሆን ይችላል። እንደምታስታውሰው፣ ቀደም ሲል የተሳፈሩበት መርከብ ኃይለኛውን ነፋስ ያለፈው የቆጵሮስ ደሴትን ተገን አድርጎ ነው፤ አሁን ደግሞ ለዚህኛው መርከብ የቀርጤስ ደሴት ተገን ሆነለት። መርከቡ በቀርጤስ ምሥራቃዊ ዳርቻ የምትገኘውን ስልሞናን ካለፈ በኋላ ሁኔታው በመጠኑ ተሻሻለ። ምን ተገኘ? መርከቡ ከደሴቱ በስተ ደቡብ በኩል ስላለ የብሱ ኃይለኛውን ነፋስ አበረደለት። ተሳፋሪዎቹ በዚህ ጊዜ የተሰማቸውን እፎይታ መገመት ይቻላል! መርከበኞቹ ግን ባሕር ላይ እስካሉ ድረስ መረጋጋት እንደማይችሉ ያውቃሉ፤ ክረምት እየቀረበ በመሆኑ ከፊታቸው አሳሳቢ ሁኔታ ተደቅኗል።
10 ሉቃስ “[የቀርጤስን የባሕር] ዳርቻ ይዘን በብዙ ችግር በመጓዝ . . . ‘መልካም ወደብ’ ወደተባለ ስፍራ ደረስን” ሲል ዘግቧል። ደሴቱ ከለላ ሆኖላቸውም እንኳ መርከቡን መቆጣጠር በጣም አዳጋች ነበር። በመጨረሻ ግን መልሕቃቸውን መጣል የሚችሉበት ቦታ አገኙ፤ ይህ ወደብ የባሕሩ ዳርቻ ወደ ሰሜን እጥፍ የሚልበት ቦታ ላይ እንደሚገኝ ይገመታል። ለመሆኑ በዚህ ቦታ ምን ያህል ጊዜ ቆዩ? ሉቃስ “ረጅም ጊዜ” መቆየታቸውን ገልጿል፤ ሆኖም ለጉዞ አመቺ የሆነው ጊዜ እየተሟጠጠባቸው ነው። በመስከረም/በጥቅምት ወር በባሕር ላይ መጓዝ የባሰ አደገኛ ይሆናል።—ሥራ 27:8, 9
11. ጳውሎስ አብረውት ለሚጓዙት ሰዎች ምን ምክር ሰጠ? ይሁንና ሰዎቹ ምን ለማድረግ ወሰኑ?
11 ጳውሎስ በሜድትራንያን ባሕር ላይ የመጓዝ ልምድ ስላለው አንዳንድ መንገደኞች ምክር ጠይቀውት ሊሆን ይችላል። እሱም መርከቡ ጉዞ መቀጠል እንደሌለበት ሐሳብ አቀረበ። ጉዞ ከቀጠለ ግን “ከፍተኛ ጉዳትና ጥፋት” ሊደርስ ምናልባትም የሰው ሕይወት ሊጠፋ ይችላል። ይሁን እንጂ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት ጉዟቸውን መቀጠል ፈለጉ፤ ምናልባትም ይበልጥ አስተማማኝ ቦታ በአፋጣኝ ማግኘት እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ይሆናል። ሰዎቹ ዩልዮስን አሳመኑት፤ አብዛኞቹ መንገደኞችም እንደ ምንም ብለው ፊንቄ ወደብ ለመድረስ መረጡ። አሁን ካሉበት ራቅ ብላ በቀርጤስ የባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ፊንቄ ክረምቱን ማሳለፍ የሚችሉበት ትልቅና የተሻለ ወደብ ሳይኖራት አይቀርም። ለጉዞ ተስማሚ የሚመስል የደቡብ ነፋስ በቀስታ ሲነፍስ ደግሞ ተነስተው ጉዞ ጀመሩ።—ሥራ 27:10-13
12. መርከቡ ቀርጤስን ለቆ ከሄደ በኋላ ምን አደጋዎች አጋጠሙት? መርከበኞቹ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ምን አደረጉ?
12 ብዙም ሳይቆይ ግን ሌላ ጣጣ መጣ፦ ከሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ “ኃይለኛ አውሎ ነፋስ” መጣባቸው። ከመልካም ወደብ 65 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኝ ‘ቄዳ የተባለች ትንሽ ደሴት’ ለተወሰነ ጊዜ ተገን ሆነችላቸው። አውሎ ነፋሱ ግን አሁንም መርከቡን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ገፍቶ ሊወስደው ይችላል፤ መርከቡ በአፍሪካ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ከሚገኝ የአሸዋ ቁልል ጋር የመላተም አደጋ ተደቅኖበት ነበር። መርከበኞቹ ይህ እንዳይደርስባቸው ስለፈሩ መርከቡ ከኋላ የሚጎትታትን ትንሽ ጀልባ ስበው ወደ መርከቡ አስገቧት። ጀልባዋ በውኃ ስለተሞላች ሳይሆን አይቀርም ይህ የሆነላቸው በስንት መከራ ነው። ከዚያም መርከቡ የተሠራባቸው ጣውላዎች እንዳይበታተኑ ከሥር በኩል ዙሪያውን በገመድ ወይም በሰንሰለት በማሰር አጠናከሩት። ገመዶቹን በመፍታት ሸራውን ዝቅ ካደረጉ በኋላ ነፋሱን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ማዕበሉን ሰንጥቆ እንዲያልፍ ለማድረግ ይታገሉ ጀመር። ሁኔታው ምን ያህል አስፈሪ እንደሚሆን አስበው! ይህ ሁሉ ተደርጎም ጉዞው የዋዛ አልነበረም፤ ሉቃስ “አውሎ ነፋሱ ክፉኛ እያንገላታን [ነበር]” ብሏል። በሦስተኛው ቀን ለመርከቡ የሚያገለግሉትን ዕቃዎች ወደ ባሕሩ ወረወሩ፤ እንዲህ ያደረጉት መርከቡ መንሳፈፍ እንዲቀለው ብለው ሳይሆን አይቀርም።—ሥራ 27:14-19
13. ጳውሎስ በተሳፈረበት መርከብ ላይ ሁኔታው ምን ይመስል ነበር?
13 ተሳፋሪዎቹ በፍርሃት ተውጠው መሆን አለበት። ጳውሎስና ጓደኞቹ ግን አልተሸበሩም። ቀደም ሲል ጌታ፣ በሮም እንደሚመሠክርለት ለጳውሎስ ማረጋገጫ ሰጥቶታል፤ (ሥራ 19:21፤ 23:11) በኋላ ደግሞ አንድ መልአክ ይህንኑ ተስፋ ደግሞለታል። ይሁንና ኃይለኛው ውሽንፍር ለሁለት ሳምንት ሌት ተቀን አንገላታቸው። ዝናቡ ሊያባራ አልቻለም፤ ደመናው ደግሞ ጥቅጥቅ ከማለቱ የተነሳ ፀሐይና ከዋክብት አልታይ አሉ፤ በመሆኑም የመርከቡ መሪ የት ቦታ እንዳሉ ወይም ወዴት እያመሩ እንደሆነ የሚጠቁሙ ነገሮች ማየት አልቻለም። በዚህ ሁሉ መሃል እህል መቅመስ ጨርሶ የማይታሰብ ነው። ብርዱ፣ ዝናቡ፣ ባሕሩ የሚፈጥረው የማጥወልወል ስሜት፣ በዚያ ላይ ፍርሃት ቀስፎ ይዞት ምግብ የሚያሰኘው ሰው ይኖራል?
14, 15. (ሀ) ጳውሎስ አብረውት ለሚጓዙት ሰዎች ቀደም ሲል የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ የጠቀሰው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ሕይወታቸው እንደሚተርፍ ከተናገረው የተስፋ መልእክት ምን ትምህርት እናገኛለን?
14 በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ጳውሎስ ተነስቶ በመካከላቸው ቆመ። ቀደም ሲል ምን ብሏቸው እንደነበር ጠቀሰ፤ እርግጥ እንዲህ ያለው ‘እኔ’ኮ ነግሬያችሁ ነበር’ በሚል መንፈስ አይደለም። ይልቁንም የደረሰባቸው ነገር፣ እሱ የተናገረው ሐሳብ ጥበብ ያዘለ እንደነበረ በግልጽ ያሳያል። በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “አሁንም ቢሆን አይዟችሁ! ምክንያቱም መርከቡ ብቻ እንጂ ከእናንተ አንድም ሰው አይጠፋም።” (ሥራ 27:21, 22) ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ ምንኛ ተጽናንተው ይሆን! ጳውሎስም ቢሆን ለሰዎቹ የሚናገረው ይህን የመሰለ የተስፋ መልእክት ከይሖዋ በማግኘቱ እጅግ ተደስቶ መሆን አለበት። ይሖዋ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት እንደሚያሳስበው ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። ሁሉም ሰው በእሱ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ይሖዋ . . . ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥ. 3:9) እንግዲያው እኛም የይሖዋን የተስፋ መልእክት በተቻለ መጠን ለብዙዎች ለማድረስ ጥረት ማድረጋችን ምንኛ አጣዳፊ ነው! ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት አደጋ ላይ ነው።
15 ጳውሎስ በመርከቡ ላይ ለነበሩ በርካታ ሰዎች ‘አምላክ ስለሰጠው ተስፋ’ ሳይመሠክርላቸው አልቀረም። (ሥራ 26:6፤ ቆላ. 1:5) የመርከብ መሰበር አደጋ ተደቅኖባቸው ባለበት በዚህ ወቅት ደግሞ ዛሬን የመትረፍ ተስፋቸውን የሚያለመልምላቸው አሳማኝ ማስረጃ ሊነግራቸው ነው። ሐዋርያው እንዲህ አለ፦ “ንብረቱ የሆንኩለት አምላክ የላከው መልአክ ትናንት ሌሊት አጠገቤ ቆሞ ‘ጳውሎስ ሆይ፣ አትፍራ። ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል፤ አምላክ ለአንተ ሲል ከአንተ ጋር የሚጓዙት ሰዎች ሁሉ እንዲተርፉ ያደርጋል’ ብሎኛል።” ከዚያም እንዲህ ሲል አሳሰባቸው፦ “ስለዚህ እናንተ ሰዎች፣ አይዟችሁ! ምክንያቱም ይህ የተነገረኝ ነገር በትክክል እንደሚፈጸም በአምላክ ላይ እምነት አለኝ። ይሁን እንጂ ከአንዲት ደሴት ዳርቻ ጋር መላተማችን የግድ ነው።”—ሥራ 27:23-26
“ሁሉም በደህና ወደ የብስ ደረሱ” (የሐዋርያት ሥራ 27:27-44)
“በሁሉ ፊት አምላክን አመሰገነ።”—የሐዋርያት ሥራ 27:35
16, 17. (ሀ) ጳውሎስ የጸለየው የትኛውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? (ለ) ጳውሎስ የተናገረው ነገር የተፈጸመው እንዴት ነው?
16 መርከቡ አስፈሪ በሆኑት ሁለት ሳምንታት ውስጥ 870 ኪሎ ሜትር ገደማ በነፋስ እየተገፋ ሄዷል፤ አሁን ግን መርከበኞቹ የሆነ ለውጥ አስተዋሉ፤ ምናልባትም ውኃ ከመሬት ጋር ሲላተም የሚፈጥረውን ድምፅ ሰምተው ሊሆን ይችላል። ከፊት ለፊታቸው የብስ ካለም ወደዚያ ለማምራት አሰቡ፤ ስለዚህ ከኋላ ያሉትን መልሕቆች በመጣል መርከቡ ካሉበት ቦታ እየተገፋ እንዳይሄድ፣ የፊተኛው ክፍልም ወደ የብሱ አቅጣጫ እንዲሆን ለማድረግ ሞከሩ። በዚህ ጊዜ መርከበኞቹ መርከቡን ጥለው ለማምለጥ ሞክረው ነበር፤ ወታደሮቹ ግን እንዳይሄዱ ከለከሏቸው። ጳውሎስ መኮንኑንና ወታደሮቹን “እነዚህ ሰዎች መርከቡን ጥለው ከሄዱ ልትድኑ አትችሉም” አላቸው። መርከቡ ትንሽ ከተረጋጋ በኋላ ጳውሎስ ምግብ እንዲበሉ አበረታታቸው፤ ሁሉም እንደሚተርፉም በድጋሚ ነገራቸው። ከዚያም “በሁሉ ፊት አምላክን አመሰገነ።” (ሥራ 27:31, 35) ጳውሎስ ያቀረበው ይህ የምስጋና ጸሎት ለሉቃስም ሆነ ለአርስጥሮኮስ እንዲሁም ዛሬ ላሉ ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ ይሆናል። አንተስ በሌሎች ሰዎች ፊት የምታቀርበው ጸሎት ሰሚዎቹን የሚያበረታታና የሚያጽናና ነው?
17 ጳውሎስ ከጸለየ በኋላ “ሁሉም ተበረታተው ምግብ እየወሰዱ ይበሉ ጀመር።” (ሥራ 27:36) ከዚያም የተጫነውን ስንዴ ወደ ባሕሩ በመጣል መርከቡ ቀለል እንዲል አደረጉ፤ ይህም ወደ ባሕሩ ዳርቻ እየተጠጋ ሲመጣ መሬት ሳይነካ ከፍ ብሎ ለመንሳፈፍ ያስችለዋል። ጎህ ሲቀድ መርከበኞቹ መልሕቆቹን ቆርጠው ጣሉ፣ ከበስተ ኋላ ያሉትን መቅዘፊያዎች ገመዶች ፈቱ እንዲሁም የፊተኛውን ሸራ ከፍ አደረጉ፤ እንዲህ ያደረጉት መርከቡን ባሕሩ ዳር በሚያቆሙበት ጊዜ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው ነው። ወደ ዳርቻው እያመሩ ሳለ ግን የመርከቡ ፊተኛ ክፍል የአሸዋ ቁልል ውስጥ ተቀረቀረ፤ ኃይለኛው ማዕበል ደግሞ የኋለኛውን ክፍል እየመታ ይሰባብረው ጀመር። አንዳንዶቹ ወታደሮች እስረኞቹ እንዳያመልጡ ሲሉ ሁሉንም ለመግደል አሰቡ፤ ዩልዮስ ግን ይህን እንዳያደርጉ ከለከላቸው። ሁሉም እየዋኙ ወይም በሆነ ነገር ላይ ተንሳፈው ወደ ባሕሩ ዳርቻ እንዲሄዱ አዘዘ። በመጨረሻ ጳውሎስ የተናገረው ነገር ተፈጸመ፤ 276ቱም መንገደኞች በሕይወት ተረፉ። አዎ፣ “ሁሉም በደህና ወደ የብስ ደረሱ።” ሆኖም የት ነው ያሉት?—ሥራ 27:44
“የተለየ ደግነት” (የሐዋርያት ሥራ 28:1-10)
18-20. የማልታ ነዋሪዎች “የተለየ ደግነት” ያሳዩት እንዴት ነው? አምላክ በጳውሎስ አማካኝነት ምን ተአምር ፈጸመ?
18 ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ከሲሲሊ በስተ ደቡብ ማልታ በተባለች ደሴት ላይ እንደሚገኙ ተገነዘቡ። (“ማልታ የምትገኘው የት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ባዕድ ቋንቋ የሚናገሩት የደሴቲቱ ነዋሪዎች “የተለየ ደግነት” አሳዩአቸው። (ሥራ 28:2) የማልታ ሰዎች በውኃ ርሰውና በብርድ እየተንቀጠቀጡ ለመጡት እንግዶች እሳት አነደዱላቸው። ብርዱና ዝናቡ ባያቆምም እሳቱ ሞቅ አደረጋቸው። በተጨማሪም አንድ ተአምር እንዲፈጸም ምክንያት ሆነ።
19 ጳውሎስ ሰዎቹን ለማገዝ ሲል ጭራሮ ሰብስቦ እሳቱ ውስጥ ጨመረው። በዚህ ጊዜ አንዲት መርዛማ እፉኝት እጁ ላይ ተጣበቀችና ነደፈችው። የማልታ ሰዎች ይህ ነገር መለኮታዊ ቅጣት እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።a
20 ጳውሎስ ሲነደፍ ያዩት የአካባቢው ነዋሪዎች “ሰውነቱ ያብጣል” ብለው አስበው ነበር። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው እዚህ ቦታ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል “የሕክምና ቃል” ነው። ጸሐፊው “የተወደደው ሐኪም ሉቃስ” በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ቃል መጠቀሙ አያስገርምም። (ሥራ 28:6፤ ቆላ. 4:14) ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ መርዛማዋን እባብ ከእጁ ላይ አራገፋት፤ አንዳች ጉዳትም አልደረሰበትም።
21. (ሀ) ሉቃስ ባሰፈረው በዚህ ዘገባ ላይ ሙያዊ ትክክለኛነትን የሚጠይቁ ምን ነገሮች ገልጿል? (ለ) ጳውሎስ ምን ተአምራት ፈጽሟል? ይህስ በማልታ ነዋሪዎች ላይ ምን ስሜት አሳድሯል?
21 ፑፕልዮስ የሚባል ሀብታም ባለርስት በዚህ አካባቢ ይኖር ነበር። በሮም የተሾመው የማልታ ዋና አስተዳዳሪ እሱ ሳይሆን አይቀርም። ሉቃስ ይህን ግለሰብ “የደሴቲቱ አስተዳዳሪ” ብሎታል፤ በማልታ ቋንቋ በተቀረጹ ሁለት ጽሑፎች ላይ ይኸው የማዕረግ ስም ተገኝቷል። ፑፕልዮስ ጳውሎስንና ጓደኞቹን ለሦስት ቀናት በእንግድነት ተቀበላቸው። ይሁንና የፑፕልዮስ አባት ታሞ ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን ሉቃስ በሽታውን በትክክል ገልጾታል። ሰውየው “ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ተኝቶ ነበር” በማለት የበሽታውን ምልክቶች በትክክለኛው የሕክምና አገላለጽ አስፍሮታል። ጳውሎስ ከጸለየለትና እጁን ከጫነበት በኋላ ሰውየው ተፈወሰ። የአካባቢው ነዋሪዎች በዚህ ተአምር በጣም ስለተደነቁ ጳውሎስ እንዲፈውሳቸው ሌሎች በሽተኞችን ይዘው መጡ፤ ከዚህም ሌላ ጳውሎስንና ጓደኞቹን በሚያስፈልጓቸው ነገሮች ለማገዝ ስጦታ አመጡላቸው።—ሥራ 28:7-10
22. (ሀ) አንድ ፕሮፌሰር፣ ወደ ሮም የተደረገውን ጉዞ በተመለከተ ሉቃስ ስለጻፈው ዘገባ ምን ብለዋል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?
22 ጳውሎስ ስላደረገው ጉዞ እስካሁን የተመለከትነው ዘገባ ሐቁን በትክክል አስፍሯል። አንድ ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉቃስ ዘገባን ያህል . . . ምስል ከሳች የአጻጻፍ ስልት የተንጸባረቀባቸው ዘገባዎች ብዙ አይደሉም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበረው የባሕር ጉዞም ሆነ በምሥራቃዊው የሜድትራንያን ባሕር ላይ ስላለው ሁኔታ በዝርዝር የጻፋቸው ነገሮች በጣም ትክክለኛ ናቸው”፤ ከዚህ አንጻር ዘገባዎቹ የተመሠረቱት በዕለት ውሎ ማስታወሻዎች ላይ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ሉቃስ ከሐዋርያው ጋር በሚጓዝበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ማስታወሻዎችን ይዞ ሊሆን ይችላል። በቀጣዩ ጉዟቸው ላይ ደግሞ ገና ብዙ የሚጽፈው ነገር ያገኛል። በመጨረሻ ሮም ሲደርሱ ጳውሎስ ምን ያጋጥመው ይሆን? እስቲ እንመልከት።
a ነዋሪዎቹ እፉኝቷን ማወቃቸው በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ ላይ እንዲህ ዓይነት እባቦች እንደነበሩ ይጠቁማል። ዛሬ በማልታ ደሴት ላይ እፉኝት አይገኝም። ለዚህ አንዱ ምክንያት ባለፉት በርካታ ዘመናት በአካባቢው ሥነ ምህዳር ላይ የተከሰተው ለውጥ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ደሴቲቱ ላይ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ መሄዱ እፉኝቶች እንዲጠፉ አድርጎ ይሆናል።
-
-
“በሚገባ . . . መመሥከር”‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
-
-
ምዕራፍ 27
“በሚገባ . . . መመሥከር”
ጳውሎስ በሮም ታስሮ እያለም መስበኩን አላቆመም
በሐዋርያት ሥራ 28:11-31 ላይ የተመሠረተ
1. ጳውሎስና አብረውት ያሉት ክርስቲያኖች ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ናቸው? ለምንስ?
ጊዜው 59 ዓ.ም. ገደማ ነው። አንድ ትልቅ መርከብ በሜድትራንያን ባሕር ላይ ጉዞ ጀምሯል፤ መነሻው የማልታ ደሴት፣ መድረሻው ደግሞ ጣሊያን ነው፤ መርከቡ እህል የጫነ ሳይሆን አይቀርም። የመርከቡ ዓርማ “የዙስ ልጆች” የሚል ነው። እስረኛው ሐዋርያው ጳውሎስና ጠባቂው እንዲሁም ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሉቃስና አርስጥሮኮስ በዚህ መርከብ ላይ ተሳፍረዋል። (ሥራ 27:2) መርከበኞቹ፣ ካስተርና ፖለክስ ከተባሉት የዙስ መንትያ ልጆች ጥበቃ ማግኘት ይፈልጋሉ፤ ወንጌላውያኑ ግን የግሪካውያኑ አማልክት ጥበቃ አላስፈለጋቸውም። (የሥራ 28:11ን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት፣ nwtsty-E) ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ፣ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው፤ ይሖዋ ደግሞ በሮም ስለ እውነት እንደሚመሠክርና በቄሳር ፊት እንደሚቆም ለጳውሎስ ነግሮታል።—ሥራ 23:11፤ 27:24
2, 3. ጳውሎስ የተሳፈረበት መርከብ የተጓዘው በየት በኩል ነው? ጳውሎስ ከመጀመሪያው አንስቶ የማን ድጋፍ አልተለየውም?
2 መርከቡ ማረፊያውን በውቧ የሲሲሊ ከተማ በስራኩስ አደረገ፤ ስራኩስ ከአቴንስና ከሮም ጋር የምትፎካከር ከተማ ናት። ከሦስት ቀናት ቆይታ በኋላ መርከቡ በደቡባዊ ጣሊያን ጫፍ ወደምትገኘው ወደ ሬጊዩም አመራ። ቀጥሎ ደግሞ 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ፑቲዮሉስ አቀና፤ ከደቡብ በኩል በሚመጣ ነፋስ እየታገዘ ገና በሁለተኛው ቀን እዚያ ደረሰ፤ ፑቲዮሉስ የጣሊያን የወደብ ከተማ ስትሆን በዛሬዋ ኔፕልስ አጠገብ ትገኛለች።—ሥራ 28:12, 13
3 ጳውሎስ በንጉሠ ነገሥት ኔሮ ፊት ለመቅረብ ወደ ሮም የሚያደርገውን ጉዞ እያገባደደ ነው። “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ጉዞው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ከጳውሎስ ጋር ነበር። (2 ቆሮ. 1:3) ቀጥሎ እንደምንመለከተው ይሖዋ ለጳውሎስ ድጋፍ መስጠቱን አያቋርጥም፤ ጳውሎስም ቢሆን የሚስዮናዊነት ቅንዓቱ አይበርድም።
“ጳውሎስ . . . አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ” (የሐዋርያት ሥራ 28:14, 15)
4, 5. (ሀ) ጳውሎስና ጓደኞቹ ፑቲዮሉስ ሲደርሱ ምን ዓይነት መስተንግዶ ተደረገላቸው? ጳውሎስ ይህን ያህል ነፃነት ያገኘው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ክርስቲያኖች እስር ቤት እያሉም እንኳ መልካም ባሕርይ ማሳየታቸው እንዴት ሊጠቅማቸው ይችላል?
4 ጳውሎስና ጓደኞቹ ፑቲዮሉስ ሲደርሱ ምን አጋጠማቸው? ዘገባው “በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነሱም ሰባት ቀን አብረናቸው እንድንቆይ ለመኑን” ይላል። (ሥራ 28:14) እንዴት ያለ ግሩም የእንግዳ ተቀባይነት ምሳሌ ነው! እነዚህ ደግ ወንድሞች ከጳውሎስና ከጓደኞቹ መንፈሳዊ ማበረታቻ በማግኘታቸው በብዙ እጥፍ እንደተካሱ ምንም ጥያቄ የለውም። ይሁንና በጥበቃ ሥር ያለ አንድ እስረኛ ይህን ያህል ነፃነት ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ይህን መብት ያገኘው የሮማውያን ጠባቂዎቹን እምነት ስላተረፈ ይሆናል።
5 በዘመናችንም በተደጋጋሚ እንደታየው የይሖዋ አገልጋዮች በእስር ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ለየት ያለ ነፃነት ተሰጥቷቸዋል፤ ይህ የሆነው በክርስቲያናዊ ባሕርያቸው የተነሳ ነው። አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ሩማኒያ ውስጥ በዝርፊያ ወንጀል 75 ዓመት ተፈርዶበት የታሰረ አንድ ሰው የአምላክን ቃል ማጥናት ከጀመረ በኋላ በባሕርዩ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አደረገ። በዚህም የተነሳ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች፣ ያለምንም አጃቢ ከተማ ሄዶ ለእስር ቤቱ የሚያስፈልጉትን ዕቃዎች ገዝቶ እንዲመጣ ይልኩት ጀመር! እርግጥ ነው፣ የምናሳየው መልካም ባሕርይ ከሁሉ በላይ የሚያስከብረው ይሖዋን ነው።—1 ጴጥ. 2:12
6, 7. የሮም ወንድሞች ልዩ ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?
6 ጳውሎስና ጓደኞቹ ከዚህ ቀጥሎ ወደ ካፑዋ በእግር የተጓዙ ይመስላል፤ ከፑቲዮሉስ 50 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ያለችው ካፑዋ በአፒያን ጎዳና ላይ ትገኛለች። ወደ ሮም የሚያመራው ይህ ታዋቂ አውራ ጎዳና ትላልቅና ጠፍጣፋ የእሳተ ገሞራ ድንጋዮች ተነጥፈውበታል፤ በዚህ መንገድ ላይ የሚጓዝ ሰው ውቡን የጣሊያን ገጠራማ አካባቢ፣ አለፍ አለፍ እያለ ደግሞ የሜድትራንያንን ባሕር መቃኘት ይችላል። ፖንታይን ማርሽስ የተባለውን ረግረጋማ ቦታም አቋርጦ ያልፋል፤ ይህ ቦታ የሚገኘው ለሮም 60 ኪሎ ሜትር ገደማ ሲቀረው ነው፤ የአፍዩስ የገበያ ስፍራም ያለው እዚሁ ነው። ሉቃስ እንደዘገበው የሮም ወንድሞች ‘ስለ እነሱ በሰሙ ጊዜ’ አንዳንዶቹ እስከ ገበያ ስፍራው ድረስ መጡ፤ ሌሎቹ ደግሞ ሦስት ማደሪያ የሚባለው ቦታ ላይ ጠበቋቸው፤ ይህ ማረፊያ ቦታ ያለው ከሮም 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ነው። እንዴት ያለ ልዩ ፍቅር ነው!—ሥራ 28:15
7 የአፍዩስ የገበያ ስፍራ፣ ከአድካሚው ጉዞ አረፍ ማለት ለሚፈልግ መንገደኛ የሚመች ቦታ አይደለም። ሮማዊው ባለቅኔ ሆራስ እንደገለጸው የገበያ ስፍራው “በመርከበኞችና ሥነ ሥርዓት በሌላቸው የማረፊያ ቤት ባለቤቶች የተጨናነቀ” ነው። በተጨማሪም “ውኃው በጣም ያስጠላል” ሲል ጽፏል። ሆራስ በዚያ ምግብ ለመብላት እንኳ አልፈለገም! ከሮም የመጡት ወንድሞች ግን ጳውሎስንና ጓደኞቹን የጠበቁት እንዲህ ባለ መጥፎ ቦታ ሆነው ነው፤ ወንድሞችን ለመቀበልና ሮም ድረስ አጅበው ለመሄድ ሲሉ ምቾት የሚነሳ ብዙ ነገር ተቋቁመዋል።
8. ጳውሎስ ወንድሞቹን “ባያቸው ጊዜ” አምላክን ያመሰገነው ለምንድን ነው?
8 ዘገባው፣ ጳውሎስ ወንድሞቹን “ባያቸው ጊዜ አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ” ይላል። (ሥራ 28:15) አዎ፣ ሐዋርያው እነዚህን ውድ ወንድሞች በማየቱ ብቻ እንኳ ተበረታቷል እንዲሁም ተጽናንቷል፤ ምናልባትም ከመካከላቸው አንዳንዶቹን በቅርበት ያውቃቸው ይሆናል። ታዲያ ጳውሎስ አምላክን ያመሰገነው ለምንድን ነው? ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ገጽታ እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። (ገላ. 5:22) በዛሬው ጊዜም ክርስቲያኖች ለራሳቸው ቅንጣት ሳይሳሱ ወንድሞቻቸውን የሚረዱትና የሚያጽናኑት በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስተው ነው።—1 ተሰ. 5:11, 14
9. ጳውሎስን የተቀበሉት ወንድሞች ያሳዩት ዓይነት መንፈስ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?
9 ለምሳሌ ያህል፣ መንፈስ ቅዱስ ለጋስ የሆኑ ወንድሞች ለወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ ለሚስዮናውያንና ለሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያሳዩ ይገፋፋቸዋል፤ እነዚህ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ለማድረግ ሲሉ ብዙ መሥዋዕት ከፍለዋል። እንግዲያው ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ጉብኝት ለመደገፍ ማድረግ የምችለው ተጨማሪ ነገር ይኖራል? እሱንም ሆነ ያገባ ከሆነ ሚስቱን በእንግድነት መቀበል እችላለሁ? አብሬያቸው ለማገልገል ሁኔታዎቼን ማመቻቸት እችላለሁ?’ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ብዙ በረከት ታገኛለህ። በሮም ያሉት ወንድሞች ጳውሎስና ጓደኞቹ ያገኟቸውን የሚያንጹ ተሞክሮዎች ሲሰሙ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን አስበው።—ሥራ 15:3, 4
‘በየቦታው መጥፎ ነገር ይወራበታል’ (የሐዋርያት ሥራ 28:16-22)
10. ጳውሎስ ሮም ውስጥ የነበረበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ሐዋርያው እዚያ ከደረሰ ብዙም ሳይቆይ ምን አደረገ?
10 መንገደኞቹ በመጨረሻ ሮም ደረሱ፤ በዚያም “ጳውሎስ አንድ ወታደር እየጠበቀው ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት።” (ሥራ 28:16) የቁም እስረኛ የሆነ ሰው እንዳያመልጥ በአብዛኛው ከጠባቂው ጋር በሰንሰለት እንዲቆራኝ ይደረግ ነበር። ጳውሎስ ግን ቀናተኛ ሰባኪ ነው፤ በሰንሰለት መታሰሩ ስለ መንግሥቱ ከመስበክ አያግደውም። በመሆኑም ከጉዞው ድካም ለሦስት ቀን ብቻ ካረፈ በኋላ በሮም ያሉትን የአይሁዳውያን ታላላቅ ሰዎች ጠራ፤ ይህን ያደረገው ራሱን ለማስተዋወቅና ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን ለመንገር ነው።
11, 12. ጳውሎስ አይሁዳውያን ወገኖቹን ሲያነጋግር ስለ እሱ የሚኖራቸውን የተሳሳተ አመለካከት ለማስወገድ ጥረት ያደረገው እንዴት ነው?
11 ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ወንድሞች፣ ምንም እንኳ ሕዝቡን ወይም የአባቶቻችንን ልማድ የሚጻረር ነገር ያልፈጸምኩ ቢሆንም በኢየሩሳሌም አስረው ለሮማውያን አሳልፈው ሰጥተውኛል። እነሱም ከመረመሩኝ በኋላ ለሞት የሚያበቃ ምንም ጥፋት ስላላገኙብኝ ሊፈቱኝ ፈልገው ነበር። ሆኖም አይሁዳውያን ይህን በተቃወሙ ጊዜ ለቄሳር ይግባኝ ለማለት ተገደድኩ፤ ይህን ያደረግኩት ግን ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም።”—ሥራ 28:17-19
12 ጳውሎስ አይሁዳውያን አድማጮቹን “ወንድሞች” ብሎ በመጥራት ከእነሱ ጋር ለመግባባት የሚያስችል መሠረት ጥሏል፤ ስለ እሱ የተሳሳተ አመለካከት ከነበራቸውም ይህን ማለቱ ሁኔታውን ለማለዘብ ይረዳል። (1 ቆሮ. 9:20) በተጨማሪም ወደ ሮም የመጣው ወገኖቹ የሆኑትን አይሁዳውያን ለመክሰስ ሳይሆን ለቄሳር ይግባኝ ለማለት እንደሆነ በግልጽ ተናገረ። ይሁን እንጂ በዚያ የሚኖሩት አይሁዳውያን ጳውሎስ ይግባኝ ስለመጠየቁ የሰሙት ነገር የለም። (ሥራ 28:21) በይሁዳ ከሚኖሩት አይሁዳውያን ይህ መረጃ ያልደረሳቸው ለምንድን ነው? አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ የተሳፈረበት መርከብ፣ ከክረምቱ በኋላ መጀመሪያ ጣሊያን ከደረሱት መርከቦች መካከል ሳይሆን አይቀርም፤ በመሆኑም በኢየሩሳሌም ከሚገኙት አይሁዳውያን ባለሥልጣኖች የተላኩ ሰዎችም ሆኑ ጉዳዩን በተመለከተ የተጻፈ ደብዳቤ ከዚህ ቀድሞ ሮም ሊደርስ አይችልም።”
13, 14. ጳውሎስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ጭብጥ ያስተዋወቀው እንዴት ነው? የእሱን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለውስ በምን መንገድ ነው?
13 ጳውሎስ የአይሁዳውያን እንግዶቹን ጉጉት በሚቀሰቅስ መንገድ የመልእክቱን ጭብጥ አስተዋወቀ፤ ስለ አምላክ መንግሥት አንድ ሐሳብ ጣል አደረገ። “[እናንተን] ለማየትና ለማነጋገር ጥያቄ ያቀረብኩት ለዚህ ነው፤ በዚህ ሰንሰለት የታሰርኩትም ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው” አላቸው። (ሥራ 28:20) የክርስቲያን ጉባኤ የሚያውጀው ይህ ተስፋ ከመሲሑና ከእሱ መንግሥት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። አይሁዳውያኑ ሽማግሌዎችም “ስለዚህ ኑፋቄ በየቦታው መጥፎ ነገር እንደሚወራ ስለምናውቅ የአንተን ሐሳብ ደግሞ መስማት ተገቢ ይመስለናል” አሉት።—ሥራ 28:22
14 እኛም ምሥራቹን የምንሰብክበት አጋጣሚ ስናገኝ ጳውሎስ እንዳደረገው ትኩረት የሚስቡ ሐሳቦችንና ጥያቄዎችን በማንሳት የአድማጮቻችንን ፍላጎት ማነሳሳት እንችላለን። ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር፣ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም እንዲሁም ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ የተባሉት ጽሑፎች ላይ ግሩም ሐሳቦች ማግኘት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚረዱት በእነዚህ መሣሪያዎች በሚገባ እየተጠቀምክ ነው?
“በሚገባ በመመሥከር” ግሩም አርዓያ ትቶልናል (የሐዋርያት ሥራ 28:23-29)
15. ጳውሎስ ከሰጠው ምሥክርነት የምናገኛቸው አራት ቁም ነገሮች ምንድን ናቸው?
15 የተቀጠረው ቀን ሲደርስ፣ አይሁዳውያኑ ጳውሎስ ወደሚኖርበት ስፍራ “ብዙ ሆነው” መጡ። ጳውሎስ “በኢየሱስ እንዲያምኑ ለማድረግ ከሙሴ ሕግና ከነቢያት እየጠቀሰ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ በመመሥከር ጉዳዩን አብራራላቸው።” (ሥራ 28:23) ጳውሎስ ምሥክርነት ከሰጠበት መንገድ የምናገኛቸው አራት ቁም ነገሮች አሉ። አንደኛ፣ ትኩረት ያደረገው በአምላክ መንግሥት ላይ ነው። ሁለተኛ፣ የአድማጮቹን ልብ ለመንካት የጣረው አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ ነው። ሦስተኛ፣ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ያስረዳ ነበር። አራተኛ፣ “ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ” በመመሥከር የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ አሳይቷል። በእርግጥም ልንከተለው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ውጤቱስ ምን ነበር? “አንዳንዶቹ የተናገረውን ነገር ሲያምኑ ሌሎቹ ግን አላመኑም።” ሉቃስ እንደዘገበው በመካከላቸው ክፍፍል ስለተፈጠረ “ለመሄድ ተነሱ።”—ሥራ 28:24, 25ሀ
16-18. በሮም የሚኖሩ አይሁዳውያን አሉታዊ ምላሽ መስጠታቸው ጳውሎስን ያላስገረመው ለምንድን ነው? ሰዎች መልእክታችንን ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑ ምን ሊሰማን አይገባም?
16 የሰዎቹ ምላሽ ጳውሎስን አላስገረመውም፤ ምላሻቸው መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ከተናገረው ትንቢት ጋር የሚስማማ ነው፤ እሱ ራሱም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ያውቃል። (ሥራ 13:42-47፤ 18:5, 6፤ 19:8, 9) በመሆኑም ጳውሎስ መልእክቱን መቀበል ያልፈለጉት ሰዎች ተነስተው ሲወጡ እንዲህ አላቸው፦ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ለአባቶቻችሁ እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል ትክክል ነበር፦ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሄደህ እንዲህ በላቸው፦ “መስማቱን ትሰማላችሁ፤ ግን በፍጹም አታስተውሉም፤ ማየቱን ታያላችሁ፤ ግን በፍጹም ልብ አትሉም። ምክንያቱም . . . የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗል።”’” (ሥራ 28:25ለ-27) “ደንድኗል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የወፈረ” ወይም “የሰባ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል፤ በመሆኑም የመንግሥቱ መልእክት ወደ ልባቸው ጠልቆ እንዳይገባ ስቡ አግዶታል ማለት ነው። እንዴት ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ነው!
17 ጳውሎስ ንግግሩን ሲደመድም፣ ከእነዚህ አይሁዳውያን በተለየ “[አሕዛብ] በእርግጥ ይሰሙታል” ብሏል። (ሥራ 28:28፤ መዝ. 67:2፤ ኢሳ. 11:10) ሐዋርያው ስለዚህ ጉዳይ አፉን ሞልቶ መናገር ይችላል! ምክንያቱም በርካታ አሕዛብ የመንግሥቱን መልእክት ሲቀበሉ በገዛ ዓይኑ ተመልክቷል።—ሥራ 13:48፤ 14:27
18 ሰዎች ምሥራቹን ለመቀበል ፈቃደኛ በማይሆኑበት ጊዜ ቅር ባለመሰኘት የጳውሎስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ደግሞም ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ የሚያገኙት በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂቶች እንደሆኑ እናውቃለን። (ማቴ. 7:13, 14) ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ሲቆሙ ደግሞ ልንደሰትና ልባችንን ከፍተን ልንቀበላቸው ይገባል።—ሉቃስ 15:7
‘ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ’ (የሐዋርያት ሥራ 28:30, 31)
19. ጳውሎስ የነበረበትን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ የተጠቀመበት እንዴት ነው?
19 ሉቃስ ዘገባውን የሚደመድመው አዎንታዊና አስደሳች በሆነ መንገድ ነው፤ እንዲህ ብሏል፦ “ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ኖረ፤ ወደ እሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደግነት ያስተናግዳቸው ነበር፤ ያለምንም እንቅፋት በታላቅ የመናገር ነፃነት ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምራቸው ነበር።” (ሥራ 28:30, 31) በእርግጥም በእንግዳ ተቀባይነት፣ በእምነትና በቅንዓት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል!
20, 21. ጳውሎስ በሮም ካከናወነው አገልግሎት የተጠቀሙ አንዳንድ ሰዎችን ጥቀስ።
20 ጳውሎስ በደግነት ካስተናገዳቸው መካከል ከቆላስይስ ኮብልሎ የመጣ አናሲሞስ የተባለ ባሪያ ይገኝበታል። ጳውሎስ አናሲሞስን ወደ ክርስትና አምጥቶታል፤ አናሲሞስ ደግሞ ለጳውሎስ ‘ታማኝና የተወደደ ወንድም’ ሆኖለታል። እንዲያውም ጳውሎስ ስለ እሱ ሲናገር “እንደ አባት የሆንኩለትን ልጄን” የሚል መግለጫ ተጠቅሟል። (ቆላ. 4:9፤ ፊልሞና 10-12) አናሲሞስ ለጳውሎስ ምንኛ የብርታት ምንጭ ሆኖለት ይሆን!a
21 ጳውሎስ ከተወው ግሩም ምሳሌ ሌሎችም ተጠቅመዋል። ሐዋርያው ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔ ያጋጠመኝ ሁኔታ ምሥራቹ ይበልጥ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ [አድርጓል]፤ የታሰርኩት የክርስቶስ አገልጋይ በመሆኔ የተነሳ እንደሆነ በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ሁሉና በሌሎች ሰዎች ሁሉ ዘንድ በይፋ ታውቋል። ጌታን የሚያገለግሉ አብዛኞቹ ወንድሞች በእኔ መታሰር ምክንያት የልበ ሙሉነት ስሜት አድሮባቸው የአምላክን ቃል ያለፍርሃት ለመናገር ከቀድሞው የበለጠ ድፍረት እያሳዩ ነው።”—ፊልጵ. 1:12-14
22. ጳውሎስ በሮም ታስሮ ያሳለፈውን ጊዜ በጥሩ ሁኔታ የተጠቀመበት እንዴት ነው?
22 ጳውሎስ በሮም ታስሮ ያሳለፈውን ጊዜ፣ አሁን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑትን ጠቃሚ ደብዳቤዎች ለመጻፍ ተጠቅሞበታል።b እነዚህ ደብዳቤዎች የተላኩላቸው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንደተጠቀሙ ጥያቄ የለውም። እኛም ብንሆን ከጳውሎስ ደብዳቤዎች እንጠቀማለን፤ ምክንያቱም በመንፈስ መሪነት የጻፈው ምክር እንደ ያኔው ሁሉ ዛሬም አስፈላጊ ነው።—2 ጢሞ. 3:16, 17
23, 24. በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች በግፍ ቢታሰሩም እንኳ እንደ ጳውሎስ አዎንታዊ አመለካከት ያሳዩት እንዴት ነው?
23 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጳውሎስ መቼ እንደተፈታ ባይናገርም ነፃነቱን ለማግኘት አራት ዓመት ገደማ ወስዶበታል፤ በቂሳርያ ሁለት ዓመት፣ በሮምም ሁለት ዓመት ታስሮ ነበር።c (ሥራ 23:35፤ 24:27) ያም ቢሆን በአምላክ አገልግሎት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ቀጥሏል። ዛሬ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም በእምነታቸው ምክንያት በግፍ ቢታሰሩም ደስታቸውን አላጡም፤ መስበካቸውንም ቀጥለዋል። በክርስቲያናዊ ገለልተኝነቱ ምክንያት በስፔን ታስሮ የነበረውን አዶልፎን እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንድ መኮንን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “በጣም ነው የምታስገርመን። ሕይወት እንዲመርህ ያላደረግነው ነገር አልነበረም፤ እኛ ስናከብድብህ አንተ ፈገግታ አይለይህም፤ ደግ ቃል እንጂ ክፉ አይወጣህም።”
24 ከጊዜ በኋላ ጠባቂዎቹ አዶልፎን በጣም ስለተማመኑበት የታሰረበትን ክፍል ክፍት ይተዉት ጀመር። ወታደሮችም እየመጡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠይቁት ነበር። እንዲያውም ከጠባቂዎቹ አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ወደ አዶልፎ ክፍል ይገባ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሰው እንዳያየው አዶልፎ አካባቢውን ይቃኝለታል። እስረኛው የጠባቂው “ጠባቂ” ሆነ! እንዲህ ያሉ ታማኝ ምሥክሮች የተዉት ግሩም ምሳሌ እኛም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ “የአምላክን ቃል ያለፍርሃት ለመናገር ከቀድሞው የበለጠ ድፍረት” እንድናሳይ ያነሳሳናል።
25, 26. ጳውሎስ 30 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የትኛው አስደናቂ ትንቢት ሲፈጸም ተመልክቷል? ይህስ በዘመናችን ካለው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
25 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ምሥራቹን ለመስበክ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ስላደረጉ ክርስቲያኖች የሚገልጹ አስገራሚ ዘገባዎችን ይዟል፤ መጽሐፉ የሚደመደመውም እስረኛ የሆነው የክርስቶስ ሐዋርያ ሊጠይቁት ለመጡ ሁሉ “ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸው” እንደነበር በሚገልጽ የሚያበረታታ ሐሳብ ነው! በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸውን ተልእኮ እናነባለን፤ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) ይህን ከተናገረ 30 ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የመንግሥቱ መልእክት “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል።”d (ቆላ. 1:23) የአምላክ መንፈስ ያለውን ኃይል የሚያሳይ እንዴት ያለ ማስረጃ ነው!—ዘካ. 4:6
26 ዛሬም ቅቡዓን ቀሪዎችና “ሌሎች በጎች” “ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ [እንዲመሠክሩ]” ኃይል እየሰጣቸው ያለው ይኸው መንፈስ ነው፤ ምሥራቹን ከ240 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ይሰብካሉ! (ዮሐ. 10:16፤ ሥራ 28:23) አንተስ በዚህ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እያደረግክ ነው?
a ጳውሎስ፣ አናሲሞስን እሱ ጋር ሊያስቀረው ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ቢያደርግ የሮምን ሕግ መጣስ ይሆንበታል፤ የአናሲሞስ ጌታ የሆነውን ፊልሞና የተባለውን ክርስቲያን መብትም ይጋፋል። በመሆኑም አናሲሞስ፣ ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን ደብዳቤ ይዞ ወደ ጌታው ተመልሷል፤ ጳውሎስ በደብዳቤው ላይ ፊልሞና፣ ባሪያውን እንደ መንፈሳዊ ወንድም ቆጥሮ በደግነት እንዲቀበለው አበረታቶታል።—ፊልሞና 13-19
b “ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም ታስሮ ሳለ የጻፋቸው አምስት ደብዳቤዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
c “የጳውሎስ ሕይወት ከ61 ዓ.ም. በኋላ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
d “ምሥራቹ ‘ለፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል’” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
-