-
ክርስትና ወደ ብዙ አገሮች ተስፋፋከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 98
ክርስትና ወደ ብዙ አገሮች ተስፋፋ
የኢየሱስ ሐዋርያት ምሥራቹን በመላው ምድር እንዲያስፋፉ ኢየሱስ የሰጣቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋል። በ47 ዓ.ም. በአንጾኪያ የሚኖሩ ወንድሞች ጳውሎስንና በርናባስን ወደተለያዩ ቦታዎች ሄደው እንዲሰብኩ ላኳቸው። እነዚህ ሁለት ቀናተኛ ሰባኪዎች ደርቤን፣ ልስጥራንና ኢቆንዮንን ጨምሮ በትንሿ እስያ ውስጥ ወደሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ሄዱ።
ጳውሎስና በርናባስ ሀብታም፣ ድሃ፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳይሉ ለሁሉም ሰው ይሰብኩ ነበር። ብዙ ሰዎች ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውነት ተቀበሉ። ጳውሎስና በርናባስ የቆጵሮስ አገረ ገዢ ለሆነው ለሰርግዮስ ጳውሎስ በሰበኩበት ወቅት አንድ ጠንቋይ ሊያስቆማቸው ሞከረ። ጳውሎስ ግን ጠንቋዩን ‘ይሖዋ ይቀጣሃል’ አለው። ወዲያውኑም ጠንቋዩ ዓይኑ ታወረ። አገረ ገዢው ሰርግዮስ ጳውሎስም ይህን ሲያይ አማኝ ሆነ።
ጳውሎስና በርናባስ በሁሉም ቦታ ማለትም ከቤት ወደ ቤት፣ በገበያ ቦታዎች፣ በመንገድ ላይና በምኩራቦች ውስጥ ይሰብኩ ነበር። ልስጥራ ውስጥ አንድን ሽባ ሰው በፈወሱ ጊዜ ይህን ተአምር ሲፈጽሙ ያዩ ሰዎች ጳውሎስና በርናባስ አማልክት ስለመሰሏቸው እነሱን ለማምለክ ተነሳሱ። ጳውሎስና በርናባስ ግን ‘አምላክን ብቻ አምልኩ! እኛ እንደ እናንተው ሰዎች ነን’ በማለት ከለከሏቸው። ከዚያም አንዳንድ አይሁዳውያን መጥተው ሕዝቡ በጳውሎስ ላይ እንዲያምፅ አደረጉ። ሰዎቹም ጳውሎስን በድንጋይ ወገሩት። ከዚያም ከከተማዋ ጎትተው አወጡት፤ የሞተ ስለመሰላቸውም ጥለውት ሄዱ። ጳውሎስ ግን አልሞተም ነበር! ወዲያውኑ ወንድሞች መጥተው ጳውሎስን ይዘውት ወደ ከተማዋ ገቡ። በኋላም ጳውሎስ ወደ አንጾኪያ ተመለሰ።
በ49 ዓ.ም. ጳውሎስ በተለያዩ ቦታዎች ለመስበክ እንደገና ተጓዘ። በትንሿ እስያ ወደሚገኙት ወንድሞች በድጋሚ ከሄደ በኋላ ምሥራቹን ርቀው በሚገኙት የአውሮፓ ከተሞች ሰበከ። ወደ አቴንስ፣ ኤፌሶን፣ ፊልጵስዩስ፣ ተሰሎንቄና ሌሎች ቦታዎች ሄዷል። ሲላስ፣ ሉቃስ እንዲሁም ጢሞቴዎስ የተባለ አንድ ወጣት ከጳውሎስ ጋር አብረው ተጉዘዋል። ጉባኤዎችን በማቋቋምና በማጠናከር አብረው ሠርተዋል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያሉትን ወንድሞች በማበረታታት ለአንድ ዓመት ከግማሽ ያህል በዚያ ቆየ። በዚህ ወቅት ምሥራቹን ይሰብክና ሰዎችን ያስተምር ነበር፤ እንዲሁም ለተለያዩ ጉባኤዎች ደብዳቤ ጽፏል። በተጨማሪም ድንኳን ይሠራ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጳውሎስ ወደ አንጾኪያ ተመለሰ።
በ52 ዓ.ም. ጳውሎስ በተለያዩ ቦታዎች ለመስበክ ለሦስተኛ ጊዜ ተጓዘ፤ መጀመሪያ የተጓዘው ወደ ትንሿ እስያ ነበር። በስተ ሰሜን እስከ ፊልጵስዩስ ድረስ የሄደ ሲሆን ከዚያም ወደ ቆሮንቶስ ተጓዘ። ጳውሎስ እያስተማረ፣ የታመሙትን እየፈወሰና ጉባኤውን እየረዳ ለተወሰኑ ዓመታት በኤፌሶን ቆየ። በተጨማሪም በየቀኑ በአንድ ትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ ንግግር ይሰጥ ነበር። ብዙ ሰዎች የሚያስተምረውን ትምህርት በመስማት ሕይወታቸውን መለወጥ ችለዋል። ጳውሎስ በብዙ አገሮች ምሥራቹን ከሰበከ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ።
“ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።”—ማቴዎስ 28:19
-
-
አንድ የእስር ቤት ጠባቂ ክርስቲያን ሆነከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 99
አንድ የእስር ቤት ጠባቂ ክርስቲያን ሆነ
በፊልጵስዩስ የምትኖር ጋኔን የያዛት አንዲት አገልጋይ ነበረች። እሷም ጋኔኑ እንድትጠነቁል ወይም ወደፊት ስለሚሆነው ነገር እንድትናገር ያደርጋት ስለነበር ለጌቶቿ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው ነበር። ጳውሎስና ሲላስ ወደ ፊልጵስዩስ ከመጡ በኋላ ለብዙ ቀናት ትከተላቸው ነበር። ‘እነዚህ ሰዎች የልዑሉ አምላክ ባሪያዎች ናቸው’ እያለች ትጮኽ ነበር። በመጨረሻም ጳውሎስ ጋኔኑን ‘ከእሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ስም አዝሃለሁ!’ አለው። በዚህ ጊዜ ጋኔኑ ከእሷ ወጣ።
የዚህች አገልጋይ ጌቶች ከዚያ በኋላ እየጠነቆለች ገንዘብ እንደማታመጣላቸው ሲያውቁ በጣም ተናደዱ። በመሆኑም ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ወሰዷቸውና እንዲህ አሉ፦ ‘እነዚህ ሰዎች ሕግ አያከብሩም፤ ደግሞም መላ ከተማዋን እየረበሹ ነው።’ የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎችም ጳውሎስና ሲላስ እንዲገረፉና እስር ቤት እንዲገቡ አዘዙ። የእስር ቤቱ ጠባቂም ጨለማ ወደሆነው የእስር ቤቱ ውስጠኛ ክፍል ወስዶ በእግር ግንድ አሰራቸው።
ጳውሎስና ሲላስ ግን ሌሎቹ እስረኞች እየሰሟቸው ይሖዋን በመዝሙር ያወድሱ ነበር። እኩለ ሌሊት ላይ በድንገት ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ እስር ቤቱን ከላይ እስከ ታች አናወጠው። የእስር ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ እስረኞቹ የታሰሩባቸው ሰንሰለቶችም ተፈቱ። የእስር ቤቱ ጠባቂ ወደ እስር ቤቱ ውስጠኛ ክፍል እየሮጠ ሲመጣ በሮቹ መከፈታቸውን አየ። እስረኞቹ በሙሉ ያመለጡ ስለመሰለው ራሱን ለመግደል ሰይፍ መዘዘ።
በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ‘በራስህ ላይ ጉዳት አታድርስ! ሁላችንም አለን!’ አለው። የእስር ቤቱ ጠባቂም በፍጥነት ሄዶ በጳውሎስና በሲላስ ፊት ተንበረከከ። ከዚያም “ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” በማለት ጠየቃቸው። እነሱም ‘አንተም ሆንክ ቤተሰብህ በኢየሱስ ማመን አለባችሁ’ አሉት። ከዚያም ጳውሎስና ሲላስ ለእስር ቤቱ ጠባቂና ለቤተሰቦቹ የይሖዋን ቃል አስተማሯቸው፤ እነሱም ወዲያውኑ ተጠመቁ።
“ሰዎች ይይዟችኋል፤ ስደት ያደርሱባችኋል እንዲሁም ለምኩራብና ለወህኒ ቤት አሳልፈው ይሰጧችኋል። በስሜም ምክንያት በነገሥታትና በገዢዎች ፊት ያቀርቧችኋል። ይህም ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትላችኋል።”—ሉቃስ 21:12, 13
-
-
ጳውሎስና ጢሞቴዎስከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 100
ጳውሎስና ጢሞቴዎስ
በልስጥራ በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ወጣት ወንድም ነበር። አባቱ ግሪካዊ ሲሆን እናቱ ደግሞ አይሁዳዊት ነበረች። እናቱ ኤውንቄና አያቱ ሎይድ ጢሞቴዎስን ሕፃን ልጅ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ስለ ይሖዋ አስተምረውታል።
ጳውሎስ ምሥራቹን በተለያዩ ቦታዎች ለመስበክ ለሁለተኛ ጊዜ በተጓዘበት ወቅት ልስጥራን ጎብኝቶ ነበር፤ እዚያ በቆየበት ወቅት ጢሞቴዎስ ወንድሞችን በጣም እንደሚወድና እነሱን መርዳት እንደሚያስደስተው አስተዋለ። በመሆኑም ጳውሎስ ጢሞቴዎስን አብሮት እንዲጓዝ ጠየቀው። ከዚያም ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ጎበዝ የምሥራቹ ሰባኪና አስተማሪ እንዲሆን አሠለጠነው።
ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በሄዱበት ቦታ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ይመራቸው ነበር። አንድ ቀን ጳውሎስ፣ አንድ የመቄዶንያ ሰው ወደ እነሱ መጥቶ እንዲረዳቸው ሲለምነው በራእይ አየ። ስለዚህ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ፣ ሲላስና ሉቃስ ምሥራቹን ለመስበክና ጉባኤዎችን ለማቋቋም ወደ መቄዶንያ ሄዱ።
መቄዶንያ ውስጥ በምትገኘው በተሰሎንቄ ከተማ የሚኖሩ በርካታ ወንዶችና ሴቶች ክርስቲያኖች ሆኑ። ሆኖም አንዳንድ አይሁዳውያን በጳውሎስና በጓደኞቹ ቀኑ። ስለዚህ ሕዝቡን አነሳስተው ወንድሞችን እየጎተቱ ወደ ከተማዋ ገዢዎች ወሰዷቸውና እንዲህ አሉ፦ ‘እነዚህ ሰዎች የሮም መንግሥት ጠላቶች ናቸው!’ በዚህ ጊዜ ወንድሞች፣ አይሁዳውያን ጳውሎስንና ጢሞቴዎስን እንዳይገድሏቸው ስለፈሩ በሌሊት ወደ ቤርያ ላኳቸው።
በቤርያ የሚኖሩት ሰዎች ምሥራቹን ለመስማት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፤ በመሆኑም በዚያ ከሚኖሩት ግሪካውያንና አይሁዳውያን መካከል ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ሆኑ። ሆኖም አንዳንድ አይሁዳውያን ከተሰሎንቄ መጥተው ችግር መፍጠር ሲጀምሩ ጳውሎስ ወደ አቴንስ ሄደ። ጢሞቴዎስና ሲላስ ግን በቤርያ የሚገኙትን ወንድሞች ለማጠናከር ሲሉ እዚያው ቀሩ። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ወደ ተሰሎንቄ ላከው፤ ይህን ያደረገው በተሰሎንቄ የሚገኙ ወንድሞች የሚደርስባቸውን ከባድ ስደት መቋቋም እንዲችሉ ማበረታቻ እንዲሰጣቸው ነው። በኋላም ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ወንድሞችን እንዲያበረታታ ወደተለያዩ ጉባኤዎች ልኮታል።
ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‘ይሖዋን ማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች ይሰደዳሉ’ ብሎት ነበር። ጢሞቴዎስ በእምነቱ ምክንያት ስደት ደርሶበታል እንዲሁም ታስሯል። ሆኖም ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት የሚያሳይበት አጋጣሚ በማግኘቱ ተደስቷል።
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የሚገኙ ክርስቲያኖችን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ ‘ጢሞቴዎስን ወደ እናንተ እልከዋለሁ። እሱም ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ መኖር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ያስተምራችኋል፤ እንዲሁም ለአገልግሎት ያሠለጥናችኋል።’ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ ይተማመን ነበር። ምክንያቱም ለብዙ ዓመታት ጓደኛሞች ነበሩ፤ እንዲሁም ይሖዋን አብረው አገልግለዋል።
“ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝምና። ሌሎቹ ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯጣሉ።”—ፊልጵስዩስ 2:20, 21
-
-
ጳውሎስ ወደ ሮም ተወሰደከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 101
ጳውሎስ ወደ ሮም ተወሰደ
ጳውሎስ ምሥራቹን ለመስበክ ለሦስተኛ ጊዜ ያደረገው ጉዞ ኢየሩሳሌም ላይ ተደመደመ። በኢየሩሳሌም ሳለ ተይዞ እስር ቤት ገባ። ሌሊት ላይ ኢየሱስ በራእይ ተገልጦ ‘ወደ ሮም ሄደህ በዚያ ትሰብካለህ’ አለው። ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም ወደ ቂሳርያ ተወሰደ፤ በዚያም ሁለት ዓመት ያህል በእስር ቤት ቆየ። በኋላም የአውራጃ ገዢ በሆነው በፊስጦስ ፊት ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ጳውሎስ ‘ቄሳር ፍርድ እንዲሰጠኝ ወደ ሮም መሄድ እፈልጋለሁ’ አለ። ፊስጦስም ‘ቄሳር እንዲፈርድልኝ እፈልጋለሁ ስላልክ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ’ አለው። በመሆኑም ጳውሎስን ወደ ሮም በሚሄድ መርከብ አሳፍረው ላኩት፤ ሁለት ክርስቲያን ወንድሞቹ ማለትም ሉቃስና አርስጥሮኮስ አብረውት ሄዱ።
በባሕር ላይ ሳሉ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተነሳ። አውሎ ነፋሱ ለብዙ ቀናት ስለቆየ በመርከቡ ውስጥ የነበሩት ሰዎች በሙሉ የሚሞቱ መስሏቸው ነበር። ሆኖም ጳውሎስ እንዲህ አላቸው፦ ‘እናንተ ሰዎች፣ አንድ መልአክ በሕልም ተገልጦ እንዲህ ብሎኛል፦ “ጳውሎስ፣ አትፍራ። በሰላም ሮም ትደርሳለህ፤ አብረውህ በመርከቡ ውስጥ ያሉት ሰዎችም በሙሉ ይተርፋሉ።” ስለዚህ አይዟችሁ! ማናችንም አንሞትም።’
አውሎ ነፋሱ ለ14 ቀናት ያህል ቆየ። በመጨረሻም አሸዋማ የሆነ ደረቅ መሬት ተመለከቱ፤ ማልታ ወደምትባለው ደሴት ተቃርበው ነበር። በዚህ ጊዜ መርከቡ ከመሬት ጋር ተጋጭቶ ተሰባበረ፤ ሆኖም በመርከቡ ላይ የነበሩት 276 ሰዎች በሙሉ በሰላም ከውኃው ውስጥ ወጡ። አንዳንዶቹ እየዋኙ ሌሎቹ ደግሞ በመርከቡ ስብርባሪዎች ላይ እየተንጠላጠሉ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ደረሱ። በማልታ የሚኖሩት ሰዎችም ተንከባከቧቸው፤ እንዲሁም እንዲሞቃቸው እሳት አነደዱላቸው።
ከሦስት ወር በኋላ ወታደሮቹ ጳውሎስን በሌላ መርከብ ወደ ሮም ወሰዱት። ሮም ሲደርስ በዚያ ያሉ ወንድሞች ሊቀበሉት መጡ። ጳውሎስም እነሱን ሲያይ ይሖዋን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ። ጳውሎስ እስረኛ የነበረ ቢሆንም በተከራየው ቤት ውስጥ አንድ ወታደር እየጠበቀው እንዲኖር ተፈቅዶለት ነበር። ለሁለት ዓመት ያህል በዚያ ቆየ። ሰዎች ሊጠይቁት ይመጡ የነበረ ሲሆን ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸውና ስለ ኢየሱስ ያስተምራቸው ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ በዚያ ሆኖ በትንሿ እስያና በይሁዳ ለሚገኙ ጉባኤዎች ደብዳቤ ጽፏል። በእርግጥም ይሖዋ ጳውሎስን በመጠቀም ምሥራቹ ለብዙ አገር ሰዎች እንዲዳረስ አድርጓል።
“በሁሉም ነገር ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን፤ ይህን የምናደርገው በብዙ ነገር በመጽናት፣ በመከራ፣ በእጦት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች [ነው]።”—2 ቆሮንቶስ 6:4
-