ያወጣሁት ግብ ላይ ለመድረስ በቁርጠኝነት መታገል
ማርታ ቻቬዝ ሴርና እንደተናገረችው
የ16 ዓመት ልጅ እያለሁ፣ አንድ ቀን ቤት ውስጥ ሥራ እየሠራሁ ሳለ በድንገት ራሴን ስቼ ወደቅሁ። ስነቃ አልጋ ላይ ነበርኩ። ነገሮች ምስቅልቅል አሉብኝ፤ ራሴን በኃይል እያመመኝ ከመሆኑም ሌላ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ምንም ነገር መስማትም ሆነ ማየት አልቻልኩም። ፍርሃት ውርር አደረገኝ። ምን ሆኜ ነበር?
በሁኔታው ግራ የተጋቡት ወላጆቼ ወደ አንዲት ሐኪም የወሰዱኝ ሲሆን ሐኪሟም የቫይታሚን እንክብሎች እንድወስድ አዘዘችልኝ። የችግሬም መንስኤ በቂ እንቅልፍ አለመተኛቴ እንደሆነ ነገረቻቸው። ከሁለት ወራት በኋላ በተመሳሳይ ሰውነቴ እየተንዘፈዘፈ ራሴን ስቼ ወደቅሁ፤ በዚህ ሳያበቃ ለሦስተኛ ጊዜም እንዲሁ አደረገኝ። ስለዚህም ሌላ ሐኪም አማከርን፤ እርሱም የነርቭ ሕመም እንደያዘኝ ስላሰበ የሚያረጋጉ መድኃኒቶች ሰጠኝ።
ይሁን እንጂ ይህ የሚያንዘፈዝፈኝና የሚጥለኝ በሽታ ቶሎ ቶሎ ይመላለስብኝ ጀመር። በተደጋጋሚ ራሴን ስቼ ስለምወድቅ ሰውነቴ ይጎዳ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ምላሴንና የአፌን ውስጠኛ ክፍል እነክስ ነበር። ስነቃ ደግሞ ራሴን በጣም ያመኛል እንዲሁም ያቅለሸልሸኛል። መላ አካላቴን የሚያመኝ ከመሆኑም በተጨማሪ ራሴን ስቼ ከመውደቄ በፊት ምን ነገሮች ተከስተው እንደነበር ማስታወስ ይሳነኛል። አብዛኛውን ጊዜ ከሕመሙ ለማገገም አንድ ወይም ሁለት ቀን ተኝቼ ማረፍ አለብኝ። ያም ሆኖ ግን ይህ ችግር ጊዜያዊ እንደሆነና በቅርቡ እንደምድን ይሰማኝ ነበር።
ሕመሜ ባወጣሁት ግብ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ
ትንሽ ልጅ እያለሁ ወላጆቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ያስጠኑን የነበሩት ባልና ሚስት ልዩ አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሲሆኑ በወር ውስጥ በርካታ ሰዓታት ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ያሳልፋሉ። እነዚህ አቅኚዎች በአገልግሎታቸው ደስታ እንደሚያገኙ ማስተዋል ችዬ ነበር። እኔም ለመምህሬና ለክፍል ጓደኞቼ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ተስፋ በነገርኳቸው ወቅት ያን ደስታ ማጣጣም ችያለሁ።
በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ብዙዎቹ የቤተሰባችን አባላት የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ምሥራቹን መስበክ በጣም ያስደስተኝ ነበር! የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ፣ እኔም ልዩ አቅኚ ለመሆን ግብ አወጣሁ። በ16 ዓመቴ ስጠመቅ እዚህ ግቤ ላይ ለመድረስ አንድ ትልቅ እርምጃ ወሰድሁ። ይህ ሕመም የጀመረኝ ከዚያ በኋላ ነበር።
የአቅኚነት አገልግሎት
የጤና እክል ቢኖርብኝም አንድ ቀን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እካፈላለሁ ብዬ አስብ ነበር። ነገር ግን በሽታው በሳምንት ሁለት ጊዜ ያህል ይጥለኝ ስለነበር አንዳንድ በጉባኤያችን ያሉ ወንድሞች ይህንን ከባድ ኃላፊነት ለመቀበል እንደሚከብደኝ ነገሩኝ። ይህ ያሳዘነኝ ከመሆኑም በላይ ተስፋ እንድቆርጥ አደረገኝ። ከጊዜ በኋላ፣ ሜክሲኮ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግሉ ባልና ሚስት ወደ እኛ ጉባኤ መጡ። አቅኚ ለመሆን ያለኝን ጉጉት ሲያውቁ ብዙ ማበረታቻ ሰጡኝ። በሽታዬ ከአቅኚነት ግቤ ወደኋላ እንድል ሊያደርገኝ እንደማይገባ አሳመኑኝ።
ስለዚህ መስከረም 1, 1988 በሜክሲኮ በምትገኘው የትውልድ ከተማዬ፣ በሳን አንድራስ ቺአውትላ የዘወትር አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። በእያንዳንዱ ወር ምሥራቹን በመስበክ ብዙ ሰዓታት አሳልፍ ነበር። አንዳንዴ በጤንነቴ ምክንያት ውጪ ወጥቼ መስበክ ሳልችል ስቀር ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆኑ ርዕሶች ላይ ተመርኩዤ ደብዳቤ በመጻፍ በአቅራቢያዬ ያሉ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ አበረታታቸዋለሁ።
ችግሬ ታወቀ
በዚህ ወቅት ቤተሰቦቼ ከፍተኛ ወጪ ቢጠይቅባቸውም ወደ አንድ የነርቭ ስፔሻሊስት ወሰዱኝ። ዶክተሩም የያዘኝ የሚጥል በሽታ እንደሆነ ነገረን። ያን ጊዜ በወሰድኩት ሕክምና ምክንያት በሽታዬን ለአራት ዓመታት ያህል መቆጣጠር ተቻለ። በዚህ መሃል በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት ተካፈልኩ፤ እዚያም ያገኘሁት ማበረታቻ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ለማገልገል የነበረኝን ፍላጎት ይበልጥ አነሳሳው።
ወላጆቼ አገልግሎቴን ከፍ ለማድረግ በጣም እንደምፈልግ ያውቁ ነበር። ስለዚህም በሽታዬ ከሞላ ጎደል በቁጥጥር ሥር በመዋሉ ቤተሰቦቼ ከቤታችን 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና በሚቾካን ግዛት ውስጥ ባለችው በሴታከዋሮ ከተማ እንዳገለግል ፈቀዱልኝ። በዚያ ተመድበው ከነበሩት አቅኚዎች ጋር ጊዜዬን ማሳለፌ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ይበልጥ ከፍ አድርጌ እንድመለከተው አደረገኝ።
በሴታከዋሮ ለሁለት ዓመታት ያህል ካገለገልኩ በኋላ የሚጥለኝ በሽታ እንደገና አገረሸብኝ። በጣም አዝኜና ተስፋ ቆርጬ ሕክምና ለመከታተል ወደ ቤተሰቦቼ ቤት ተመለስኩ። ከዚያም የነርቭ ሐኪሙ እየወሰድኩት ያለው ሕክምና ጉበቴን እንደጎዳው ነገረኝ። ስፔሻሊስቱ የሚጠይቀው ክፍያ ስለከበደን ሌላ የሕክምና አማራጭ ፈለግሁ። ሁኔታዬ እየተባባሰ በመሄዱ አቅኚነትን አቋረጥኩ። በሽታው በተመላለሰብኝ ቁጥር ጤንነቴ እያሽቆለቆለ ነበር። ይሁን እንጂ የመዝሙር መጽሐፍን ሳነብና በጸሎት ወደ ይሖዋ ስቀርብ መጽናናትና ጥንካሬ አገኛለሁ።— መዝሙር 94:17-19
ግቤ ላይ መድረስ
በሽታዬ በጣም ሲብስብኝ በቀን ሁለት ጊዜ ይጥለኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሁኔታዎች ተለወጡ። አንድ ሐኪም ለሚጥል በሽታ ልዩ ሕክምና ስላደረገልኝ ረዘም ላሉ ጊዜያት ሳያመኝ መቆየት ቻልኩ። ስለዚህም ከመስከረም 1, 1995 ጀምሮ እንደገና የአቅኚነት አገልግሎቴን ጀመርኩ። ጤንነቴ በጣም ስለተስተካከለና ለሁለት ዓመታት ያህል አንድ ጊዜም ሳያመኝ መቆየት በመቻሌ ልዩ አቅኚ ለመሆን አመለከትኩ። ይህ ደግሞ በአገልግሎቱ ረጅም ሰዓታት ማሳለፍንና በተፈለግሁበት በየትኛውም ቦታ ማገልገልን ይጨምራል። ልዩ አቅኚ ሆኜ ስመደብ ምን እንደተሰማኝ ልትገምቱ ትችላላችሁ! ልጅ ሆኜ ያወጣሁት ግብ ላይ ደረስኩ።
በሚያዝያ 1, 2001 አዲሱን ምድቤን ተቀብዬ ሂዳልጎ ወደተባለው ተራራማ ግዛት ሄድኩ። አሁን በጉዋናጁዋቶ ግዛት በምትገኝ አንዲት ትንሽ ከተማ እያገለገልኩኝ እገኛለሁ። በቂ እረፍት አደርጋለሁ እንዲሁም መድኃኒቴን ያለ ማቋረጥ እወስዳለሁ። በአመጋገብ ረገድም ቢሆን በተለይ ስብ፣ ካፌይንና የታሸጉ ምግቦችን በተመለከተ እጠነቀቃለሁ። በተጨማሪም እንደ ቁጣና ከልክ ያለፈ ጭንቀት ያሉ ስሜቶችን ለማስወገድ እጥራለሁ። አዘውትሬ እንዲህ ዓይነት ጥንቃቄ ማድረጌ ጠቅሞኛል። ልዩ አቅኚ ሆኜ ባሳለፍኳቸው ጊዜያት ራሴን ስቼ የወደቅሁት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ያላገባሁና የቤተሰብ ኃላፊነት የሌለኝ እንደመሆኔ መጠን ልዩ አቅኚ ሆኜ በመቀጠሌ ደስተኛ ነኝ። ይሖዋ ‘ዐመፀኛ ስላይደለ ሥራችንንና ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር እንደማይረሳ’ ማወቄ ያጽናናኛል። ከአቅማችን በላይ እንድንሰጠው ባለመፈለጉ እንዴት ያለ አፍቃሪ አምላክ ነው! ይህንን እውነታ መቀበሌ አስተሳሰቤን ለማስተካከል የረዳኝ ከመሆኑም ባሻገር ወደፊት የጤናዬ ሁኔታ በአቅኚነት እንዳልቀጥል እንቅፋት ቢሆንብኝ እንኳ ይሖዋ በሙሉ ነፍስ በማቀርበው አገልግሎቴ እንደሚደሰት እርግጠኛ እንድሆን ረድቶኛል።—ዕብራውያን 6:10፤ ቈላስይስ 3:23
በየዕለቱ እምነቴን ለሌሎች ማካፈሌ እንድጠነክር እንደረዳኝ ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም አምላክ ወደፊት ያዘጋጀውን በረከት በአእምሮዬ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንድሰጠው አድርጎኛል። መጽሐፍ ቅዱስ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ምንም ዓይነት በሽታ፣ “ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና” በማለት ተስፋ ይሰጣል።—ራእይ 21:3, 4፤ ኢሳይያስ 33:24፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰባት ዓመቴ ገደማ (ከላይ)፤ በ16 ዓመቴ እንደ ተጠመቅሁ አካባቢ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጓደኛዬ ጋር ስሰብክ