የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ለምንሠራቸው ኃጢአቶች ሰይጣንን ተጠያቂ ማድረግ ይገባናልን?
የሰው ልጅ ለሠራው የመጀመሪያ ኃጢአት የተወነጀለው ሰይጣን ነበር። “እባብ አሳተኝና በላሁ” ስትል ሔዋን ተናግራለች። (ዘፍጥረት 3:13) ከዚያ ጊዜ አንስቶ “ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው . . . እርሱም የቀደመው እባብ” ሰዎችን ‘በማሳወር’ እና ‘ዓለሙን ሁሉ በማሳት’ የሰውን ዘር ለጥፋት እየዳረገ ይገኛል። (ራእይ 12:9፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) ከእሱ ተጽዕኖ ሊያመልጥ የሚችል ሰው የለም፤ ታዲያ ይህ ማለት ተጽዕኖውን መቋቋም አንችልም ማለት ነው? ኃጢአት በሠራን ቁጥር ተጠያቂው ሰይጣን ነው ማለት ነው?
እርግጥ ነው፣ ሔዋንን ያሳታት ሰይጣን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 2:14) የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ የአምላክ ዓይነት ማስተዋልና በራስ ፈቃድ የመመራት ነፃነት ልታገኝ እንደምትችል አድርጋ በማሰብ ተታለለች። (ዘፍጥረት 3:4, 5) ይህን በማሰብ ኃጢአት ሠራች። ይሁን እንጂ አምላክ እሷን ተጠያቂ በማድረግ ሞት ፈረደባት። ለምን? ምክንያቱም ሰይጣን ቢዋሽም እንኳ የአምላክን ትእዛዝ በሚገባ ታውቅ ነበር። ትእዛዙን እንድትጥስ ያስገደዳት የለም፤ ከዚህ ይልቅ ድርጊቷን በሙሉ የምትቆጣጠረው ራሷ ነበረች፤ የሰይጣንን ተጽዕኖ መቋቋም የምትችልበት የተሟላ ብቃት ነበራት።
ዲያብሎስን ተቋቋሙ
ሰዎች ዲያብሎስን መቋቋም ይችላሉ። በኤፌሶን 6:12 ላይ “በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር” ‘ትግል’ እንዳለብን ተነግሮናል። ስለዚህ አምላክ የሰይጣንን ተጽዕኖ እንድንቋቋም ይጠብቅብናል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ከአቅሙ በላይ የሆነውን የሰይጣንንና የአጋንንቱን ኃይል እንዴት መቋቋም ይችላል? የተጠየቅነው ልናሸንፈው በማንችለው ባልተመጣጠነ ውጊያ እንድንካፈል ነው? አይደለም፤ ምክንያቱም አምላክ ዲያብሎስን በራሳችን ኃይል እንድንጋፈጠው አይጠብቅብንም። ይሖዋ የዲያብሎስን ማታለያዎች ተቋቁመን በድል አድራጊነት መወጣት የምንችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ጠቁሞናል። መጽሐፍ ቅዱስ ዲያብሎስ ማን እንደሆነ፣ እንዴት ጥቃት እንደሚሰነዝርና ራሳችንን ከእሱ ጥቃት እንዴት መጠበቅ እንደምንችል ይነግረናል።—ዮሐንስ 8:44፤ 2 ቆሮንቶስ 2:11፤ 11:14
‘ዲያብሎስን መቃወም’ የምንችልበት መንገድ
ቅዱሳን ጽሑፎች ዲያብሎስን መቋቋም የሚቻልበት ሁለት እርምጃዎች ያቀፈ ሐሳብ ያቀርባሉ። የሚከተለው ጥብቅ ምክር ተሰጥቶናል:- “እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል።” (ያዕቆብ 4:7) ራስን ለአምላክ በማስገዛት የምንወስደው የመጀመሪያው እርምጃ ትእዛዛቱን ማክበር ይጨምራል። የአምላክን ሕልውና፣ ጥሩነቱን፣ አስፈሪ ኃይሉንና ሥልጣኑን እንዲሁም ከፍተኛ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ሁልጊዜ ማሰባችን ሰይጣንን ለመቃወም የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። ዘወትር ወደ አምላክ መጸለይም በጣም አስፈላጊ ነው።—ኤፌሶን 6:18
ኢየሱስ በዲያብሎስ የተፈተነበትን ጊዜ አስብ። ኢየሱስ የተለያዩ የአምላክ ትእዛዛትን በማስታወስ መጥቀሱ ፈተናውን ለመቋቋም እንደረዳው አያጠራጥርም። ሰይጣን ኢየሱስን አባብሎ ኃጢአት እንዲሠራ ማድረግ ባለመቻሉ ትቶት ሄደ። ኢየሱስ ይህን ፈታኝ ሁኔታ ካሳለፈ በኋላ ይሖዋ በመላእክቱ አማካኝነት ይበልጥ አበረታው። (ማቴዎስ 4:1–11) በመሆኑም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘ከክፉው እንዲያድናቸው’ አምላክን እንዲጠይቁ በእርግጠኝነት አበረታቷቸዋል።—ማቴዎስ 6:13
አምላክ ያድነናል ማለት በዙሪያችን መከላከያ ጋሻ ያኖራል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንደ እውነት፣ ጽድቅ፣ ሰላምና እምነት ያሉ አምላካዊ ባሕርያትን እንድንከታተል ይመክረናል። እነዚህ ባሕርያት ‘የዲያብሎስን ሽንገላ መቃወም’ እንድንችል በመርዳት እንደ “ዕቃ ጦር” ሆነው ያገለግሉናል። (ኤፌሶን 6:11, 13–18) ስለዚህ በአምላክ እርዳታ የዲያብሎስን ፈተናዎች ማጨናገፍ ይቻላል።
በያዕቆብ 4:7 ላይ የተጠቀሰው ሁለተኛው እርምጃ ደግሞ ‘ዲያብሎስን መቃወም’ ነው። ይህም ጎጂ ከሆነው የሰይጣን ተጽዕኖ በመሸሽ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድን ይጨምራል። አንድ ሰው አታላይ ለሆነው ኃይሉ እንዳይጋለጥ መጠንቀቅ ያለበት ከመሆኑም በላይ በዛሬው ዓለም በእጅጉ ተስፋፍተው የሚገኙትን ፍቅረ ነዋይና ብልሹ ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅባቸው ፍልስፍናዎች ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግ አለበት። ሕይወታችንን አምላክን በሚያስደስት መንገድ ለመምራት በመወሰን ዲያብሎስን በዚህ መንገድ መቃወማችን ከሰይጣን ጋር በምናደርገው ውጊያ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝልናል። ይሁን እንጂ ማንኛውንም ኃጢአት የምንሠራው ዲያብሎስ በቀጥታ በሚያሳድርብን ተጽዕኖ ነው?
ከውስጥ ያለብን ውጊያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች” ሲል ገልጿል። (ያዕቆብ 1:14, 15) የሚያሳዝነው፣ በዘር የወረስነውን ድክመትና አለፍጽምና ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ አንችልም። (ሮሜ 5:12) መጽሐፍ ቅዱስ “በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝም” ሲል ይናገራል።—መክብብ 7:20
ይህ ማለት ግን ማንኛውም ዓይነት ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥራችን ውጪ ነው ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በራሳችን የተሳሳቱ ምርጫዎች ሳቢያ በራሳችን ላይ ፈተና እናመጣለን። ስለዚህ ምንም እንኳ በራሳችን አለፍጽምና ወይም ደግሞ በሰይጣን ተጽዕኖ የተነሳ መጥፎ ምኞት ሊያድርብን ቢችልም ምኞቱን ማሳደጋችንም ሆነ ማስወገዳችን ሙሉ በሙሉ በእኛ ላይ የተመካ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” ብሎ መጻፉ ተገቢ ነው።—ገላትያ 6:7
ኃላፊነቱን ውሰድ
ብዙውን ጊዜ ሰዎች የራሳቸውን ድክመት፣ ስህተትና ጉድለት ማለትም የሠሩትን ኃጢአት አምኖ መቀበል ይከብዳቸዋል። (መዝሙር 36:2) ለሠራናቸው ኃጢአቶች ኃላፊነት እንድንወስድ ሊረዳን የሚችለው አንዱ ነገር አምላክ ፍጽምናን እንደማይጠብቅብን መገንዘባችን ነው። “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም” ሲል መዝሙራዊው ዳዊት ተናግሯል። (መዝሙር 103:10) አምላክ ይቅር ባይ ቢሆንም እንኳ ለዲያብሎስ ማባበያዎችና ለራሳችን የኃጢአት ዝንባሌዎች እንዳንሸነፍ ራሳችንን ለመገሰጽ ከፍተኛ ትግል እንድናደርግ ይጠብቅብናል።—1 ቆሮንቶስ 9:27
ዲያብሎስ በድርጊቶቻችን ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ እንደሚችልና የሰው ልጅ ላለበት የኃጢአተኝነት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂ እንደሆነ አምላክ የሚገነዘብ ቢሆንም እንኳ ይህ ከራሳችን የግል ተጠያቂነት ነፃ ሊያደርገን እንደማይችል መረዳት አለብን። በመሆኑም ሮሜ 14:12 “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ሲል ይናገራል።
ሆኖም ‘ክፉውን ነገር ከተጸየፍንና ከበጎ ነገር ጋር ከተባበርን’ ኃጢአትን ድል ማድረግ እንችላለን። (ሮሜ 12:9, 21) የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን ይህን ሳታደርግ በመቅረቷ ተቀጥታለች፤ ተጽዕኖውን መቋቋምና አምላክን መታዘዝ ትችል ነበር። (ዘፍጥረት 3:16) ይሁን እንጂ ዲያብሎስ እሷን በማታለል ረገድ የተጫወተውን ሚና አምላክ በቸልታ አላለፈውም። ዲያብሎስ ከመረገሙም በላይ ዘላለማዊ ጥፋት ተፈርዶበታል። (ዘፍጥረት 3:14, 15፤ ሮሜ 16:20፤ ዕብራውያን 2:14) እሱ ከሚያሳድርብን መጥፎ ተጽዕኖ ጋር የምናደርገው ትግል በቅርቡ ያከትማል።—ራእይ 20:1–3, 10
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Erich Lessing/Art Resource, NY