የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 10/8 ገጽ 3-4
  • ልጆቻችሁ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ልጆቻችሁ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው!
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከጥንት ዘመን ጀምሮ የኖረ ችግር
  • አስቸኳይ እልባት የሚያሻው ችግር
  • በቤት ውስጥ እንዳይከሰት መከላከል
    ንቁ!—1997
  • ልጆችን ለወሲብ መጠቀሚያ ማድረግ ዓለም አቀፍ ችግር ሆኗል
    ንቁ!—1998
  • በልጅነታቸው የወሲባዊ በደል ሰለባ የሆኑ ሰዎች
    ንቁ!—1999
  • በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ በደል የሚያስከትለው ስውር ቁስል
    ንቁ!—1999
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1997
g97 10/8 ገጽ 3-4

ልጆቻችሁ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው!

በልጆች ላይ የሚፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት የዚህ በሽተኛ ዓለም አንዱ አስከፊ ገጽታ ነው። ሊርስ የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ከካንሰር የበለጠ፣ ከልብ በሽታ የበለጠ፣ ከኤድስም የበለጠ ብዙዎቻችንን ያጠቃል።” በመሆኑም ንቁ! መጽሔት አንባቢዎቹ ከዚህ አደጋ እንዲጠበቁ የማስጠንቀቅና ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን ማድረግ እንደሚቻል የመጠቆም ግዴታ እንዳለበት ይሰማዋል።—ከሕዝቅኤል 3:17-21 እና ከሮሜ 13:11-13 ጋር አወዳድር።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በልጆች ላይ በሚፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት ላይ ዓለም አቀፋዊ ተቃውሞ ማስተጋባት ጀምሯል። ሆኖም የመገናኛ ብዙሃን በልጅነታቸው የተፈጸመባቸውን በጾታ የማስነወር ወንጀል በይፋ የተናገሩ ዝነኛ ሰዎችን በማቅረብ በጉዳዩ ላይ በስፋት ማተታቸው በብዙዎች ዘንድ አንዳንድ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች አሳድሯል። አንዳንዶች በልጆች ላይ ስለሚፈጸመው ጥቃት የሚነገረው ነገር ሁሉ እንዲሁ የአንድ ሰሞን ትኩስ ወሬ ብቻ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውታል። እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው፤ እንዲህ ዓይነቱ ወሲባዊ ጥቃት ዘመን አመጣሽ አይደለም። ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር እኩል የኖረ ችግር ነው ማለት ይቻላል።

ከጥንት ዘመን ጀምሮ የኖረ ችግር

ከዛሬ 4,000 ዓመት ገደማ በፊት ልቅ በሆነ ሥነ ምግባር የታወቁ ሰዶምና ገሞራ የሚባሉ ከተሞች ነበሩ። በእነዚህ ከተሞች ውስጥ ይፈጸሙ ከነበሩት ብልግናዎች አንዱ ሕፃናትን የማስነወር ድርጊት እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ሰዶማውያን “ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ” በጾታ ስሜት ናውዘው፣ ወደ ሎጥ ቤት በእንግድነት የመጡትን ሁለት ወንዶች አስገድደው ለመድፈር ፈልገው እንደነበረ ዘፍጥረት 19:4 ይገልጻል። እስቲ አስበው:- ገና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ወንዶች ልጆች ወንዶችን አስገድዶ የመድፈር ስሜት በውስጣቸው የተቀጣጠለው ለምንድን ነው? እነዚህ ልጆች አስቀድሞ ከተፈጥሮ ውጪ በሆነው የግብረ ሰዶም ልማድ ተካፍለው እንደነበረ ለመረዳት አያዳግትም።

ይህ ከሆነ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ የእስራኤል ሕዝብ በከነዓን ምድር መኖር ጀመረ። በከነዓን ምድር በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት፣ ግብረ ሰዶም፣ ከእንስሳት ጋር የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት፣ ዝሙት አዳሪነትና አልፎ ተርፎም ትንንሽ ልጆችን ለአጋንንታዊ አማልክት መሥዋዕት አድርጎ የማቅረብ ሃይማኖታዊ ልማድ በጣም ተስፋፍቶ ስለነበረ እነዚህ ጸያፍ የብልግና ድርጊቶች በሙሉ በሙሴ ሕግ ውስጥ በግልጽ መወገዝ አስፈልጓቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 18:6, 21-23፤ 19:29፤ ኤርምያስ 32:35) መለኮታዊ ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተው የነበረ ቢሆንም እንኳ አንዳንድ አለቆቻቸውን ጨምሮ ዓመፀኞቹ እስራኤላውያን እነዚህን ርካሽ የሆኑ ልማዶች ተከትለዋል።—መዝሙር 106:35-38

ይሁን እንጂ የጥንቶቹ ግሪክና ሮም በዚህ ረገድ ከእስራኤል እጅግ የከፉ ነበሩ። በሁለቱም አገሮች ውስጥ ሕፃናትን መግደል የተለመደ ነገር የነበረ ከመሆኑም በላይ በግሪክ ውስጥ ትልልቅ ወንዶች ከትንንሽ ወንዶች ልጆች ጋር የሚፈጽሙት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ልማድ ነበር። በጥንታዊዎቹ የግሪክ ከተሞች በሙሉ በዝሙት አዳሪነት የተሰማሩ ትንንሽ ወንዶች ልጆች የሚገኙባቸው ቦታዎች ተስፋፍተው ነበር። በሮማ ግዛት በዝሙት አዳሪነት የተሰማሩ በጣም ብዙ ልጆች ስለነበሩ በዚህ ንግድ ላይ ልዩ ቀረጥ ተጥሎ የነበረ ሲሆን ለዚህ ንግድ ተብለው የተቋቋሙ በዓላትም ነበሩ። በትግል መወዳደሪያ ሥፍራዎች ልጃገረዶች ተገደው ይደፈሩ ነበር፤ ከእንስሳትም ጋር የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ያስገድዷቸው ነበር። እንዲህ ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊቶች በሌሎች ብዙ የጥንት አገሮች ውስጥም ተስፋፍተው ይገኙ ነበር።

ዛሬስ? የሰው ልጅ ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ በመድረሱ እንደዚህ ዓይነቶቹ ዘግናኝ የጾታ ድርጊቶች እንኳ የማይታሰቡ ናቸው ሊባል ይቻላልን? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚህ አባባል አይስማሙም። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ያለንበትን ዘመን “የሚያስጨንቅ ዘመን” ብሎ እንደጠራው ያውቃሉ። እጅግ የተስፋፋውን ራስ ወዳድነትና ለሥጋዊ እርካታ ያደሩ መሆንን እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ባለው ኅብረተሰብ ላይ በስፋት እየተንጸባረቀ ያለውን ተፈጥሮአዊ የቤተሰብ ፍቅር መጥፋት ከዘረዘረ በኋላ “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች . . . በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” ሲል አክሎ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13፤ ራእይ 12:7-12) ብዙውን ጊዜ ‘ክፉዎችና አታላዮች’ በሆኑ ሰዎች የሚፈጸመው በልጆች ላይ የሚደርሰው ወሲባዊ ጥቃት እየተባባሰ ሄዷልን?

አስቸኳይ እልባት የሚያሻው ችግር

ብዙውን ጊዜ በልጆች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በምሥጢር ይያዛል፤ እንዲያውም ለፖሊስ ሪፖርት ከማይደረጉት ወንጀሎች ውስጥ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የሚይዘው ይህ በልጆች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆኖ ግን እንዲህ ዓይነቱ ወንጀል ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ እንዳለ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ሎስ አንጀለስ ታይምስ በዚህ ጉዳይ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንድ ጥናት አካሂዶ ነበር። በተደረገው ጥናት መሠረት 27 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና 16 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች በልጅነታቸው በጾታ የተነወሩ መሆናቸው ተረጋግጧል። እነዚህ አኃዛዊ መረጃዎች የሚያስደነግጡ ቢሆኑም በዚያው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ በተካሄዱ ጥናቶች ላይ የተመሠረቱ ሌሎች መረጃዎች ከላይ ከተጠቀሰው ቁጥር በልጠው ተገኝተዋል።

በማሌዥያ አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ባለፈው አሥርተ ዓመት ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች ቁጥር በአራት እጥፍ አድጓል። በታይላንድ በተደረገ አንድ ጥናት ወደ 75 በመቶ የሚጠጉት ወንዶች በዝሙት አዳሪነት ከተሰማሩ ልጆች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንደፈጸሙ ተናግረዋል። መንግሥት ባወጣቸው ግምታዊ ዘገባዎች መሠረት ጀርመን ውስጥ እስከ 300,000 የሚደርሱ ልጆች በየዓመቱ በጾታ ይነወራሉ። በደቡብ አፍሪካ እየታተመ የሚወጣው ኬፕ ታይምስ እንዳለው ከሆነ እንዲህ ዓይነት ጥቃት መፈጸሙን የሚገልጹት ሪፖርቶች ቁጥር በቅርቡ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 175 በመቶ ጨምሯል። በኔዘርላንድና በካናዳ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት አንድ ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት ሴቶች በልጅነታቸው በጾታ የተነወሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ችለዋል። በፊንላንድ ደግሞ በዘጠነኛ ክፍል ከሚገኙት ተማሪዎች ውስጥ 18 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ልጆችና (15 ወይም 16 ዓመት ቢሆናቸው ነው) 7 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ልጆች ቢያንስ ቢያንስ ከእነሱ በአምስት ዓመት ከሚበልጥ ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዳደረጉ ተናግረዋል።

በተለያዩ አገሮች ውስጥ ልጆችን አሠቃቂ በሆኑ የጾታ ድርጊቶች ስለሚያስነውሩና ስለሚያሰቃዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የሚገልጹ የሚሰቀጥጡ ሪፖርቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ወንጀል እንደተፈጸመባቸው የሚናገሩ ሰዎች የሚያምናቸውም ሆነ የሚራራላቸው ሰው የለም።

ስለዚህ በልጆች ላይ የሚፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት ዘመን አመጣሽና ያልተለመደ ነገር አይደለም፤ ለረጅም ጊዜ የኖረ ችግር ከመሆኑም በላይ በዛሬው ጊዜ እንደ ወረርሽኝ ተዛምቶ ይገኛል። የሚያሳድረው ተጽእኖ የከፋ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ይህ ድርጊት የተፈጸመባቸው ብዙዎቹ ሰዎች ጥልቅ የሆነ የከንቱነትና የዋጋቢስነት ስሜት ያድርባቸዋል። በዚህ መስክ የሰለጠኑ ጠበብቶች፣ አንዲት ልጃገረድ በቅርብ ዘመዷ ከተነወረች ይህ ድርጊት በልጅቷ ላይ በአብዛኛው የሚያስከትላቸውን አንዳንድ ጠንቆች ዘርዝረዋል። ከቤት መኮብለል፣ አደገኛ መድኃኒቶችንና አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድ፣ የአልኮል መጠጦችን ከመጠን በላይ መጠጣት፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ ራስን የመግደል ሙከራ፣ ዓመፀኝነት፣ ሴሰኝነት፣ የእንቅልፍ ማጣትና የመማር ችግር ከሚጠቀሱት ጠንቆች አንዳንዶቹ ናቸው። ከረጅም ጊዜ ጠንቆቹ መካከል አንዳንዶቹ ደግሞ የወላጅነትን ኃላፊነት በብቃት መወጣት አለመቻል፣ የጾታ ስሜት ማጣት፣ ወንዶችን አለማመን፣ ልጆችን በጾታ የሚያስነውርን ሰው ማግባት፣ በሴቶች መካከል የሚፈጸም ግብረ ሰዶም፣ ዝሙት አዳሪነትና በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት መፈጸም ሊሆኑ ይችላሉ።

እነዚህ ነገሮች በጾታ የተነወረ ሰው ሁሉ ሊያስወግዳቸው የማይችላቸው ጠንቆች ናቸው ማለት አይደለም፤ በተጨማሪም ማንኛውም ሰው ለሚፈጽመው መጥፎ ምግባር ቀደም ሲል የተፈጸመበትን ወሲባዊ ጥቃት ምክንያት አድርጎ ሊያቀርብ አይችልም። ሰዎች በጾታ መነወራቸው የግድ ብልሹ ምግባር እንዲከተሉ ወይም ደግሞ ዓመፀኞች እንዲሆኑ አያደርጋቸውም፤ ወደፊት በቀሪው ሕይወታቸው ለሚያደርጉት ነገርም ከተጠያቂነት ነጻ ሊያደርጋቸው አይችልም። ሆኖም በልጅነታቸው በጾታ የተነወሩ ሰዎች ለእነዚህ የተለመዱ ጠንቆች የተጋለጡ ናቸው። ይህም ልጆችን ከወሲባዊ ጥቃት ልንጠብቃቸው የምንችለው እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄ አፋጣኝ መልስ እንድንሻ ያስገድደናል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ