-
‘እንዴት ይህን ክፉ ድርጊት እፈጽማለሁ?’መጠበቂያ ግንብ—2014 | ኅዳር 1
-
-
እርግጥ ነው፣ ዮሴፍ እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎታል። የጲጥፋራ ሚስት ልትበቀለው ፈለገች። በመሆኑም ወዲያውኑ እየጮኸች አገልጋዮቹን መጣራት ጀመረች። ዮሴፍ ሊደፍራት እንደሞከረና እሷ ስትጮኽ ሸሽቶ እንዳመለጠ ነገረቻቸው። ዮሴፍን ለመወንጀል ባሏ እስኪመለስ ድረስ ልብሱን ይዛ ቆየች። ጲጥፋራ ወደ ቤት ተመልሶ ሲመጣ ያንኑ ውሸት ደግማ ተናገረች፤ ጲጥፋራ ይህን ባዕድ ሰው ወደ ቤት በማምጣቱ ለደረሰባት ነገር ተጠያቂው እሱ እንደሆነ በተዘዋዋሪ ገለጸች። የጲጥፋራ ምላሽ ምን ነበር? ታሪኩ በጣም ‘እንደተቆጣ’ ይናገራል። ከዚያም ዮሴፍን ወደ እስር ቤት አስገባው።—ዘፍጥረት 39:13-20
“እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ”
በዚያ ዘመን ስለነበሩት የግብፃውያን እስር ቤቶች ብዙ የምናውቀው ነገር የለም። የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የግብፃውያን እስር ቤቶችን ፍርስራሽ አግኝተዋል፤ እነዚህ እስር ቤቶች ከመሬት በታች ተቆፍረው የተሠሩ ጨለማ ክፍሎችና ሌሎች ጠባብ ክፍሎች ያሏቸው እንደ ምሽግ ያሉ ቦታዎች ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ የታሰረበትን ቦታ ለመግለጽ ቃል በቃል ሲተረጎም “ጉድጓድ” የሚል ፍቺ ያለው ቃል ተጠቅሟል፤ ይህም እስር ቤቱ ብርሃን የሌለውና በቀላሉ መውጣት የማይቻልበት ስፍራ እንደሆነ ይጠቁማል። (ዘፍጥረት 40:15 NW፣ የግርጌ ማስታወሻ) በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው “እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤ በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ” የሚለው ዘገባ ዮሴፍ ተጨማሪ ሥቃይ ደርሶበት እንደነበረ ያሳያል። (መዝሙር 105:17, 18) ግብፃውያን አንዳንድ ጊዜ የእስረኞችን እጅ በብረት የፊጥኝ ያስሩ ነበር፤ ሌሎቹን ደግሞ አንገታቸው ላይ የብረት ማነቆ ያስገቡባቸው ነበር። ዮሴፍ የደረሰበት እንግልት በጣም አሠቃይቶት መሆን አለበት፤ ይህ ሁሉ የደረሰበት ግን ምንም ጥፋት ሳይሠራ ነው።
ከዚህም በላይ ዮሴፍ እንዲህ ካለው መከራ ወዲያውኑ አልተገላገለም። ዘገባው “ዮሴፍም እዚያው እስር ቤት ውስጥ ቆየ” (NW) በማለት ይናገራል። ዮሴፍ በዚያ መጥፎ ሥፍራ ለዓመታት ቆይቷል!a ደግሞም ከእስር ቤት ይውጣ አይውጣ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ዮሴፍ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቀን ቀንን እየተካ ሳምንታት ብሎም ወራት ተቆጠሩ፤ ይሁን እንጂ ዮሴፍ ተስፋ አልቆረጠም፤ ለዚህ የረዳው ምንድን ነው?
-
-
‘እንዴት ይህን ክፉ ድርጊት እፈጽማለሁ?’መጠበቂያ ግንብ—2014 | ኅዳር 1
-
-
a ዮሴፍ ወደ ጲጥፋራ ቤት ሲመጣ 17 ወይም 18 ዓመት ገደማ እንደሚሆነው እንዲሁም በዚያ እያለ አድጎ ሙሉ ሰው እንደሆነ የሚጠቁም ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኛለን፤ ስለዚህ በጲጥፋራ ቤት ለተወሰኑ ዓመታት ቆይቶ ሊሆን ይችላል። ከእሥር ቤት ሲለቀቅ ደግሞ 30 ዓመት ሆኖት ነበር።—ዘፍጥረት 37:2፤ 39:6 NW፤ ዘፍጥረት 41:46
-