የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ይቅር ባይነት ለመዳን መንገድ ይከፍታል
በግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ፊት የቆሙት አሥሩ የያዕቆብ ልጆች በመካከላቸው አንድ ከባድ ምሥጢር ደብቀው ይዘው ነበር። ከብዙ ዓመታት በፊት ግማሽ ወንድማቸውን ዮሴፍን ለባርነት ከሸጡ በኋላ ዮሴፍ በአውሬ እንደተበላ አድርገው ለአባታቸው ለመንገር ተማከሩ።—ዘፍጥረት 37:18–35
ከ20 ዓመት ገደማ በኋላ የተከሰተ አስከፊ ረሃብ እነዚህን አሥር ሰዎች እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ እንዲሄዱ አስገደዳቸው። ሆኖም በቀላሉ ሸምተው መመለስ አልቻሉም። የእህል ተቆጣጣሪም ሆኖ የሚሠራው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላዮች ናችሁ ሲል ወነጀላቸው። ከመካከላቸው አንዱን ካሰረው በኋላ ሌሎቹ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱና ታናሽ ወንድማቸው ብንያምን ይዘው እንዲመጡ አዘዛቸው። እንደታዘዙት ወንድማቸውን ይዘውት ሲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብንያም እንዲታሰር ለማድረግ እቅድ አወጣ።—ዘፍጥረት 42:1–44:12
ከያዕቆብ ልጆች አንዱ የሆነው ይሁዳ በዚህ ሐሳብ አልተስማማም። ‘ብንያምን ሳንይዝ ወደ ቤት ከተመለስን አባታችን ይሞታል’ ሲል ተናገረ። ከዚያም ይሁዳም ሆነ ከጉዞ ጓደኞቹ መካከል አንዳቸውም ቢሆን ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከያዕቆብ ልጆች በስተቀር ሁሉም ሰው ክፍሉን ለቅቆ እንዲወጣ ካዘዘ በኋላ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። ከዚያም ራሱን አረጋጋና “እኔ ዮሴፍ ነኝ” ሲል ማንነቱን ገለጸላቸው።—ዘፍጥረት 44:18–45:3
ምሕረትና ከመከራ መዳን
ዮሴፍ “አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን?” ሲል ግማሽ ወንድሞቹን ጠየቃቸው። ምንም መልስ አልሰጡትም። በእርግጥም የዮሴፍ ወንድሞች የሚሉት ጠፍቷቸው ነበር። በደስታ መፈንደቅ ነው ያለባቸው ወይስ በፍርሃት መዋጥ? ያም ሆነ ይህ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ይህን ሰው ለባርነት ሸጠውታል። ዮሴፍ እነሱን የማሰር፣ ምግብ ከልክሎ ወደ አገራቸው የመስደድ ወይም አልፎ ተርፎም የመግደል ሥልጣን አለው! የዮሴፍ ግማሽ ወንድሞች ‘በፊቱ ከመደንገጣቸው የተነሳ ይመልሱለት ዘንድ አለመቻላቸው’ ያለ ምክንያት አልነበረም።—ዘፍጥረት 45:3
ዮሴፍ ወዲያውኑ እነዚህን ሰዎች ዘና እንዲሉ አደረጋቸው። “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። ወደ እርሱ በቀረቡ ጊዜ “ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፣ አትቆርቆሩም፤ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና” አላቸው።—ዘፍጥረት 45:4, 5
ዮሴፍ ምሕረት ያደረገላቸው እንዲሁ ያለ ምክንያት አልነበረም። አስቀድሞም ንስሐ መግባታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ተመልክቶ ነበር። ለምሳሌ ያህል ዮሴፍ ግማሽ ወንድሞቹን ሰላዮች ናችሁ ብሎ በወነጀላቸው ጊዜ እርስ በርሳቸው “በእውነት ወንድማችንን በድለናል፣ . . . ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን” ብለው ሲነጋገሩ ሰምቷቸዋል። (ዘፍጥረት 42:21) በተጨማሪም ብንያም ወደ አባቱ ተመልሶ መሄድ እንዲችል ይሁዳ በእርሱ ፋንታ ባሪያ ለመሆን ራሱን አቅርቧል።—ዘፍጥረት 44:33, 34
በመሆኑም ዮሴፍ ምሕረት ለማሳየት በቂ ምክንያት ነበረው። በእርግጥም እንዲህ ማድረጉ መላ ቤተሰቡ ደኅንነት እንዲያገኝ እንደሚያስችል ተገንዝቧል። ስለዚህ ዮሴፍ ግማሽ ወንድሞቹ ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ተመልሰው ሄደው እንዲህ እንዲሉት ነገራቸው:- “ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው:- እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፤ ወደ እኔ ና፣ አትዘግይ፤ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ፣ ወደ እኔም ትቀርባለህ፣ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፣ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ። በዚያም . . . እመግብሃለሁ።”—ዘፍጥረት 45:9–11
ታላቁ ዮሴፍ
በኢየሱስና በዮሴፍ መካከል አስደናቂ የሆኑ ተመሳሳይነቶች ስላሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቁ ዮሴፍ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ኢየሱስ ልክ እንደ ዮሴፍ ወንድሞቹ በሆኑት የአብርሃም ዝርያዎች በደል ደርሶበታል። (ከሥራ 2:14, 29, 37 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ሁለቱም ሰዎች ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ነገር ገጥሟቸዋል። ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ከነበረበት የባርነት ደረጃ ተነስቶ ከፈርዖን ቀጥሎ ያለውን ቦታ በመያዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኗል። በተመሳሳይ ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት አስነስቶ “በእግዚአብሔር ቀኝ” የመሆን የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አድርጎታል።—ሥራ 2:33፤ ፊልጵስዩስ 2:9–11
ዮሴፍ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደመሆኑ መጠን እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ለሚመጡት ሰዎች ሁሉ እህል ያከፋፍል ነበር። ዛሬ ታላቁ ዮሴፍ በምድር ላይ ታማኝና ልባም ባሪያ ቡድን አለው፤ በዚህ ቡድን አማካኝነት “በጊዜው” መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበ ነው። (ማቴዎስ 24:45–47፤ ሉቃስ 12:42–44) በእርግጥም ወደ ኢየሱስ የሚመጡ ሰዎች “ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፣ ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሙም፣ . . . በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፣ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና።”—ራእይ 7:16, 17
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
ዮሴፍ ምሕረት በማሳየት ረገድ በጣም ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ፍትሕን በጥብቅ ቢከተል ኖሮ ወደ ባርነት የሸጡትን ሰዎች ለመቅጣት ይገደድ ነበር። በአንፃሩ ደግሞ ስሜታዊ ቢሆን ኃጢአታቸውን በቀላሉ ችላ ብሎ እንዲያልፍ ይገፋፋ ነበር። ዮሴፍ ሁለቱንም አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ግማሽ ወንድሞቹ ባደረጉት ነገር መጸጸት አለመጸጸታቸውን ፈትኗል። ከዚያም ከልብ መጸጸታቸውን ሲረዳ ይቅር አላቸው።
እኛም የዮሴፍን አርአያ መኮረጅ እንችላለን። በደል የፈጸመብን ሰው እውነተኛ የልብ መለወጥ ሲያሳይ ይቅር ልንለው ይገባል። እርግጥ ነው ስሜታዊነት ከባድ ኃጢአቶችን ችላ ብለን እንድናልፍ ሊጋርደን አይገባም። በአንፃሩ ደግሞ የቂመኛነት ዝንባሌ እውነተኛ የንስሐ ድርጊቶችን ከማየት እንዲያግደን መፍቀድ የለብንም። ስለዚህ ‘እርስ በርሳችን ትዕግሥት ማሳየታችንንና በነፃ ይቅር መባባላችንን እንቀጥል።’ (ቆላስይስ 3:13) እንዲህ በማድረግ “ይቅር ባይ” የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን እንመስለዋለን።—መዝሙር 86:5፤ ሚክያስ 7:18, 19