የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 10—2 ሳሙኤል
ጸሐፊዎቹ:- ጋድ እና ናታን
የተጻፈበት ቦታ:- እስራኤል
ተጽፎ ያለቀው:- ከዘአበ በ1040 ገደማ
የሚሸፍነው ጊዜ:- 1077-1040 ከዘአበ ገደማ
የእስራኤል ብሔር ጊልቦዓ ላይ በደረሰው ሽንፈትና ያንን ተከትሎ በመጣው የድል አድራጊዎቹ የፍልስጥኤማውያን ወረራ ምክንያት ተስፋ ቆርጧል። የእስራኤል መሪዎችና ለጋ ወጣቶቻቸው በሜዳ ላይ ወድቀው ቀሩ። ‘በይሖዋ የተቀባው’ የእሴይ ልጅ ወጣቱ ዳዊት ሙሉ በሙሉ ወደ መድረክ ብቅ ያለው በዚህ ወቅት ነበር። (2 ሳሙ. 19:21) የይሖዋና የዳዊት መጽሐፍ ሊባል የሚችለው ሁለተኛ ሳሙኤል ትረካውን የሚጀምረው በዚህ መንገድ ነው። ታሪኩ የተለያዩ ክንውኖችን ያካተተ ነው። ታሪኩ ከታላቅ ሽንፈት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ድል፣ በጦርነት ከታመሰ ብሔር አንስቶ ብልጽግና እስካገኘ አንድነት ያለው መንግሥት፣ ከወጣትነት ጉልበት በኋለኛው ዕድሜ እስከሚገኘው ጥበብ ድረስ ያለውን ሁኔታ ይተርካል። ይሖዋን በፍጹም ልቡ ለመከተል ጥረት ያደረገው የዳዊት የሕይወት ታሪክ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀርቧል። ታሪኩ እያንዳንዱ አንባቢ ከፈጣሪው ጋር ያለውን ዝምድናና አቋም ማጠናከር ይችል ዘንድ ልቡን እንዲመረምር የሚያነሳሳው ሊሆን ይገባል።
2 እርግጥ ነው፣ በሁለተኛው ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ የሳሙኤል ስም አይገኝም። መጽሐፉ በዚህ ስም የተጠራበት ምክንያት መጀመሪያ ላይ ከአንደኛ ሳሙኤል ጋር አንድ ጥቅል ወይም ጥራዝ ስለነበረ ሊሆን ይችላል። አንደኛ ሳሙኤልን ያጠናቀቁት ነቢዩ ናታንና ነቢዩ ጋድ የሁለተኛ ሳሙኤልን ሙሉውን ክፍል ጽፈዋል። (1 ዜና 29:29) ይህን ተግባር ለመፈጸም ሁለቱም ብቁ ነበሩ። ዳዊት በእስራኤል እንደ ሽፍታ ይታደን በነበረባቸው ጊዜያት ሁሉ ጋድ አብሮት የነበረ ከመሆኑም በላይ በዳዊት የ40 ዓመት የግዛት ዘመን መገባደጃ አካባቢም ከንጉሡ ጋር በቅርብ ይሠራ ነበር። ዳዊት እስራኤልን በመቁጠር ስንፍና ባደረገ ጊዜ ይሖዋ አለመደሰቱን ለዳዊት የነገረው ጋድ ነበር። (1 ሳሙ. 22:5፤ 2 ሳሙ. 24:1-25) በጋድ የሕይወት ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ሥራውን ያከናውን የነበረው ነቢዩ ናታንም የዳዊት የቅርብ ወዳጅ ነበር። ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባውን ልዩ ቃል ኪዳን ማለትም የዘላለሙን ቃል ኪዳን የማሳወቅ ልዩ መብት አግኝቶ ነበር። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመውን ከባድ ኃጢአትና በዚህም ምክንያት የደረሰበትን ቅጣት በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ በድፍረት የተናገረው እርሱ ነው። (2 ሳሙ. 7:1-17፤ 12:1-15) በዚህም የተነሳ ይሖዋ በሁለተኛ ሳሙኤል ውስጥ የሚገኘውን በመንፈስ አነሳሽነት የሰፈረ ጠቃሚ መረጃ “[አምላክ] ሰጥቷል” የሚል ትርጉም የሚያስተላልፍ ስም ያለው ናታን እና “መልካም ዕድል” የሚል ትርጉም የሚያስተላልፍ ስም ያለው ጋድ እንዲመዘግቡ አድርጓል። ስለ ትውልድ ሐረጋቸው ወይም ስለ ግል ሕይወታቸው የሚገልጽ ምንም ዓይነት መረጃ አለመኖሩ እነዚህ ትሑት ታሪክ ጸሐፊዎች የራሳቸውን መታሰቢያ ለማስቀረት ምንም ፍላጎት እንዳልነበራቸው ያሳያል። ወደፊት ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎችን ለመጥቀም ሲሉ የአምላክ መንፈስ እንዲጽፉ ያነሳሳቸውን ታሪክ ብቻ አስፍረዋል።
3 ሁለተኛ ሳሙኤል የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳዖል ከሞተ በኋላ ያለውን ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በመተረክ ይጀምርና እስከ ዳዊት 40ኛ የግዛት ዘመን መገባደጃ ድረስ ይዘልቃል። ይህም ከ1077 እስከ 1040 ከዘአበ አካባቢ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል ማለት ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ዳዊት እንደ ሞተ አለመጠቀሱ መጽሐፉ በ1040 ከዘአበ ገደማ ወይም ከዳዊት ሞት ጥቂት ቀደም ብሎ እንደተጻፈ ያረጋግጣል።
4 ለአንደኛ ሳሙኤል የቀረበው ማስረጃ የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አድርገን እንድንቀበል ግድ ይለናል። የመጽሐፉ ትክክለኛነት ምንም አያጠያይቅም። ንጉሥ ዳዊት የፈጸመው ኃጢአትና የሠራው ስህተት ሳይደበቅ በግልጽ መሥፈሩ የመጽሐፉን ትክክለኛነት የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።
5 ይሁን እንጂ ለሁለተኛ ሳሙኤል ትክክለኛነት ከሁሉ የበለጠው ጠንካራ ማስረጃ ለዳዊት ከተገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘ የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ነው። አምላክ “ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፣ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል” በማለት ለዳዊት ቃል ገብቶለታል። (7:16) ኤርምያስ ዘመኑ ለይሁዳ መንግሥት በጨለመበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር ለዳዊት ቤት የተገባው ይህ ቃል ኪዳን የሚቀጥል መሆኑን ሲገልጽ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና:- በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከዳዊት ዘንድ አይታጣም” በማለት ተናግሯል። (ኤር. 33:17) መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያመለክተው ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ከይሁዳ ነገድ ‘የዳዊት ልጅ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን’ በማስነሳት ትንቢቱ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል።—ማቴ. 1:1
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
28 በዛሬው ጊዜ ያለ አንድ አንባቢ ከሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ትምህርቶችን ማግኘት ይችላል! በገሃዱ ዓለም የሚታዩት ሁሉም ዓይነት ሰብዓዊ ስሜቶች እጅግ ማራኪ በሆነ መንገድ ተገልጸዋል። ስለሆነም የሥልጣን ጥምና በቀል (3:27-30)፣ የሌላን ሰው የትዳር ጓደኛ መመኘት (11:2-4, 15-17፤ 12:9, 10)፣ ከዳተኛ መሆን (15:12, 31፤ 17:23)፣ በጾታ ስሜት ላይ የተመሠረተ ፍቅር (13:10-15, 28, 29)፣ ሳያመዛዝኑ በችኮላ መፍረድ (16:3, 4፤ 19:25-30)፣ እንዲሁም አንድ ሰው ላለው የአምልኮ ፍቅር ንቀት ማሳየት (6:20-23) የመሳሰሉት ነገሮች አጥፊ ውጤት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ጠንከር ባለ መንገድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል።
29 ይሁን እንጂ ትክክለኛ ምግባርንና ድርጊትን በሚመለከት በውስጡ የሰፈሩትን ግሩም ምሳሌዎች በመከተል ከሁለተኛ ሳሙኤል አዎንታዊ ጎን የበለጠውን ጥቅም ማግኘት ይቻላል። ዳዊት ለአምላክ ብቻ የተወሰነ አምልኮ በማቅረብ (7:22)፣ በአምላክ ፊት በትሕትና በመመላለስ (7:18)፣ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ በማድረግ (7:23, 26)፣ ለደረሰበት መከራ ተገቢ አመለካከት በመያዝ (15:25)፣ ለኃጢአቱ ልባዊ ንስሐ በመግባት (12:13)፣ ለገባው ቃል ታማኝ በመሆን (9:1, 7)፣ መከራ በገጠመው ጊዜ ሚዛኑን በመጠበቅ (16:11, 12)፣ ያለ ማቋረጥ በይሖዋ በመደገፍ (5:12, 20) እንዲሁም ለይሖዋ ዝግጅትና ሹመት ጥልቅ አክብሮት በማሳየት (1:11, 12) በኩል ምሳሌ ይሆነናል። ዳዊት ‘ለእግዚአብሔር እንደ ልቡ’ የሆነ ሰው ተብሎ መጠራቱ ምንም አያስደንቅም።—1 ሳሙ. 13:14
30 በሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ በሥራ ላይ የዋሉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማግኘት ይቻላል። ከእነዚህ መካከል የማኅበረሰባዊ ተጠያቂነት እንዳለ (2 ሳሙ. 3:29፤ 24:11-15)፣ ድርጊቱ በቅንነት የተፈጸመ ቢሆንም የአምላክን የአቋም ደረጃ እንደማያስቀይር (6:6, 7)፣ በይሖዋ ቲኦክራሲያዊ ዝግጅት ውስጥ የራስነት ቦታ መከበር እንዳለበት (12:28)፣ ደምን እንደ ቅዱስ ነገር አድርጎ ማየት እንደሚገባ (23:17)፣ የደም ባለዕዳነት ስርየት እንደሚያስፈልገው (21:1-6, 9, 14)፣ ጠቢብ የሆነ ሰው በብዙዎች ላይ ጥፋት እንዳይደርስ ሊያደርግ እንደሚችል (2 ሳሙ. 20:21, 22፤ መክ. 9:15)፣ “በሞትም ቢሆን በሕይወት” ለይሖዋ ድርጅትና ለወኪሎቹ ታማኝነትን ማሳየት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ይገኙበታል።—2 ሳሙ. 15:18-22
31 ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁለተኛ ሳሙኤል “የዳዊት ልጅ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን የአምላክ መንግሥት አሻግረን እንድንመለከት ከማድረጉም በላይ ስለ መንግሥቱ ብሩህ የሆነ ፍንጭ ይሰጠናል። (ማቴ. 1:1) ይሖዋ መንግሥቱ ለዘለቄታው ጸንቶ እንደሚኖር ለዳዊት የገባው መሐላ (2 ሳሙ. 7:16) ከኢየሱስ ጋር ተያይዞ ሥራ 2:29-36 ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። “እኔም አባት እሆነዋለሁ፣ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” የሚለው ትንቢት (2 ሳሙ. 7:14) ኢየሱስን በትክክል እንደሚያመለክት ዕብራውያን 1:5 ላይ ተገልጿል። “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ከይሖዋ ዘንድ በመጣ ጊዜ ይህ ነገር ተረጋግጧል። (ማቴ. 3:17፤ 17:5) በመጨረሻም ገብርኤል ኢየሱስን በማስመልከት ለማርያም በተናገረው ቃል ውስጥ ለዳዊት የተገባውን የመንግሥት ቃል ኪዳን ጠቅሶ ተናግሯል:- “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:32, 33) ስለ መንግሥቱ ዘር የተነገረው የተስፋ ቃል ደረጃ በደረጃ እየተገለጠ ሄዶ መጨረሻ ላይ እውን ሲሆን ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው!