‘የሰላም አምላክ’ መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች ያስባል
በጥንት ዘመን ይኖር ለነበረው ለዳዊት መከራ አዲስ ነገር እንዳልነበር መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ክፉና ግትር የሆነ አንድ ንጉሥ ሊገድለው ቆርጦ በመነሣት ሌት ተቀን ያሳድደው ስለነበር ለበርካታ ዓመታት ሲሸሽ ኖሯል። ዳዊት በዚህ የመከራ ወቅት ሰው በማይደርስበት አካባቢ ተደብቆ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከመደበቅም የበለጠ ነገር አድርጓል። የደረሰበትን መከራ በሚመለከት ከልቡ ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር። ይህን አስመልክቶ ከጊዜ በኋላ “በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፤ ልመናዬን በፊቱ አፈስሳለሁ፤ መከራዬንም በፊቱ እናገራለሁ” ሲል ጽፏል።— መዝሙር 142:1, 2
ዛሬ አንዳንዶች ዳዊት ባሳየው በአምላክ የመታመን ዝንባሌ ያፌዙ ይሆናል። ጸሎት ጊዜ ከማጥፋት ሌላ ምንም ቁም ነገር የሌለው ሥነ ልቦናዊ ዘዴ ነው ይሉ ይሆናል። ይሁንና የኋላ ኋላ የዳዊት ጠላቶች መሸነፋቸው በአምላክ ላይ ያሳየው ትምክህት መና እንዳልቀረ ያረጋግጣል። ዳዊት ያሳለፈውን ነገር ወደኋላ መለስ ብሎ በመመልከት “ይህ ችግረኛ ጮኸ፣ እግዚአብሔርም ሰማው፣ ከመከራውም ሁሉ አዳነው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 34:6) ዳዊት ለእርዳታ የጠራው እውነተኛ አምላክ በሌሎች ቦታዎች ‘የሰላም አምላክ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ፊልጵስዩስ 4:9፤ ዕብራውያን 13:20) አምላክ ከመከራ እንድንገላገል በማድረግ ሰላም ይሰጠን ይሆን?
ይሖዋ ስለ አንተ ያስባል
ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ የሚደርሱትን መከራዎች በቸልታ አይመለከትም። (መዝሙር 34:15) አገልጋዮቹ በቡድን ደረጃ የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት ብቻ ሳይወሰን በግለሰብ ደረጃም እርሱን የሚፈራ እያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር በትኩረት ይከታተላል። ሰሎሞን በጥንቷ ኢየሩሳሌም የተሠራውን ቤተ መቅደስ ለአምላክ ለመወሰን ባቀረበው ጸሎት ‘ማንም ሰው ወይም ሕዝቡ እስራኤል ሁሉ፣ ማናቸውም ሰው ችግሩንና መከራውን ተገንዝቦ ጸሎትና ልመና ቢያደርግ’ ይሖዋ እንዲሰማው ተማጽኗል። (2 ዜና መዋዕል 6:29) ሰሎሞን እንደገለጸው እያንዳንዱ ሰው ራሱን የቻለ ጽናት የሚጠይቅ መከራ ይገጥመዋል። የአንዱ መከራ አካላዊ ሕመም ሊሆን ይችላል። የሌላው ደግሞ በስሜት ላይ የሚደርስ ጉዳት ይሆናል። አንዳንዶችም የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ምክንያት ይሠቃያሉ። ሥራ ማጣት፣ የኑሮ ውድነትና በቤተሰብ የሚከሰቱ ችግሮች በእነዚህ አስጨናቂ ቀናት በሰፊው የሚታዩ ችግሮች ናቸው።
እስቲ ጥቂት ቆም ብለህ ስለ ራስህ ‘ችግርና መከራ’ አስብ። አንዳንድ ጊዜ “አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም፣ የሚያጽናናኝም አጣሁ” ሲል እንደጻፈው መዝሙራዊው ዳዊት ሊሰማህ ይችላል። ይሁንና አምላክ ስለ አንተ እንደሚያስብ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ፤ ምክንያቱም እዚሁ መዝሙር ላይ ዳዊት “እግዚአብሔር ችግረኞችን ሰምቶአልና፣ እስረኞቹንም አልናቀም” በማለት ጽፏል።— መዝሙር 69:20, 33
የዳዊትን ቃላት ሰፋ አድርገን ከተመለከትናቸው የሰው ዘር ፈጣሪ በሚደርስባቸው መከራ የታሠሩ ሰዎች የሚያሰሙትን ጸሎት እንደሚያዳምጥ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ከዚህም በላይ በመከራቸው ይረዳቸዋል። ይሖዋ መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች እንደሚራራ የሚያሳዩትን እነዚህን ሐሳቦች ልብ በል።
“መበለቲቱንና ድሀ አደጎቹን አታስጨንቋቸው። ብታስጨንቋቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ እኔ ጩኸታቸውን ፈጽሞ እሰማለሁ፤ ቁጣዬም ይጸናባችኋል።”— ዘጸአት 22:22-24
“እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?”— ሉቃስ 18:7
“ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውን ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው [“ደማቸው፣” NW] በፊቱ ክቡር ነው።”— መዝሙር 72:12-14
“የሚነካችሁ [በምድር ላይ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች] የዓይኔን ብሌን የሚነካ ነውና።”— ዘካርያስ 2:8
እነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች ፈጣሪያችን ስለ ሕዝቡ ደህንነት አጥብቆ እንደሚያስብ ይገልጻሉ። እንግዲያውስ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” የሚለውን የሐዋርያው ጴጥሮስ ማሳሰቢያ የምንከተልበት በቂ ምክንያት አለን። (1 ጴጥሮስ 5:7) ይሁን እንጂ አምላክ በመከራ ወቅት የሚረዳን እንዴት ነው?
አምላክ መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች የሚረዳበት መንገድ
ቀደም ሲል እንዳየነው ዳዊት መከራ በደረሰበት ጊዜ ከአምላክ መመሪያ ለማግኘት ከልብ የመነጨ ጸሎት አቅርቧል። ዳዊት በዚህ ብቻ አልተወሰነም፤ ከአሳዳጆቹ እጅ የሚያመልጥበትን ዘዴ በመፍጠር ችግሩን ለማቃለል የበኩሉን አድርጓል። በመሆኑም በይሖዋ ላይ ያሳደረው ትምክህት ከግል ጥረቱ ጋር ተዳምሮ የደረሰበትን መከራ በጽናት ለመቋቋም አስችሎታል። ከዚህ ምን ልንማር እንችላለን?
መከራ ሲደርስብን ችግሩን ለመፍታት ምክንያታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የበኩላችንን ማድረጋችን ስህተት አይደለም። ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን ከሥራ ሲባረር ሥራ ለማግኘት ጥረት አያደርግምን? ወይም ደግሞ ሲታመም ሕክምና ለማግኘት አይጥርምን? ሁሉንም ዓይነት በሽታ የመፈወስ ችሎታ የነበረው ኢየሱስ እንኳ ሳይቀር ‘የታመመ ሰው ሐኪም እንደሚያስፈልገው’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 9:12፤ ከ1 ጢሞቴዎስ 5:23 ጋር አወዳድር።) እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቹ መከራዎች ሊወገዱ የማይችሉ በመሆናቸው በጽናት ከመቻል ሌላ አማራጭ አይኖርም። ሆኖም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት መከራን እንደ በጎ ስጦታ በጸጋ አይቀበልም። (ከ1 ነገሥት 18:28 ጋር አወዳድር።) ከዚያ ይልቅ መከራውን ለመወጣት የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል።
ይሁን እንጂ ጉዳዩን ለይሖዋ በጸሎት ማሳወቁ ምክንያታዊ ነው። ለምን? በመጀመሪያ ደረጃ በአምላክ ላይ መደገፋችን ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተን እንድናውቅ’ ያስችለናል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ለምሳሌ ያህል ሥራ በምንፈልግበት ጊዜ በጸሎት በአምላክ ላይ መደገፋችን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረን ሥራ ውስጥ እንዳንገባ ይረዳናል። በተጨማሪም ገንዘብን በመውደድ ‘ከእምነት እንዳንስት’ ይጠብቀናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) በእርግጥም ሥራ መቀጠርን የሚመለከት ወይም ሌሎች የሕይወታችንን ዘርፎች የሚነኩ ከባድ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ ዳዊት የሰጠውን የሚከተለውን ማሳሰቢያ መከተል ይኖርብናል:- “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።”— መዝሙር 55:22
በተጨማሪም ጸሎት በደረሰብን መከራ ከልክ በላይ እንዳናዝን የአስተሳሰብ ሚዛናችንን ለመጠበቅ ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ” ሲል ጽፏል። ይህስ ምን ውጤት አለው? “አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አዎን፣ ሰላም ያውም የአምላክ ሰላም እናገኛለን። ይህ ሰላም ‘አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ’ በመሆኑ በሐዘን ስሜት ስንደቆስ ሊያረጋጋን ይችላል። ‘ልባችንንና ሐሳባችንን ስለሚጠብቅልን’ ተቻኩለን ጥበብ የጎደለው እርምጃ በመውሰድ በችግራችን ላይ ችግር እንዳንጨምር ይጠብቀናል።— መክብብ 7:7
ጸሎት ከዚህም የበለጠ ነገር ሊያከናውን ይችላል። በሁኔታዎች ላይ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ተመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ጊዜ መሰል ክርስቲያኖችን እንዲጸልዩለት አበረታቷቸዋል። ለምን? “ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ” ሲል ጽፎላቸዋል። (ዕብራውያን 13:19) ጳውሎስ የእምነት አጋሮቹ ሳያቋርጡ መጸለያቸው ከእስር በሚለቀቅበት ጊዜ ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር።— ፊልሞና 22
ጸሎት በደረሰብህ መከራ ረገድ ለውጥ ሊያመጣ ይችላልን? ሊያመጣ ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠው ሁል ጊዜ እኛ በጠበቅነው መንገድ ላይሆን እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ‘የሥጋ መውጊያውን’ በተመለከተ በተደጋጋሚ ጸልዮአል፤ ይህ ምናልባት ከነበረበት የዓይን ችግር ጋር የተያያዘ ሕመም ሊሆን ይችላል። አምላክ የነበረበትን መከራ ከማስወገድ ይልቅ “ጸጋዬ ይበቃሃል፣ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና” ሲል ነግሮታል።— 2 ቆሮንቶስ 12:7-9
በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ የደረሰብን መከራ አይወገድ ይሆናል። ነገር ግን በፈጣሪያችን ላይ የምንታመን መሆናችንን የምናሳይበት አጋጣሚ እናገኛለን። (ሥራ 14:22) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የደረሰብንን መከራ ባያስወግድልንም እንኳ ‘መታገሥ እንችል ዘንድ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ እንደሚያደርግልን’ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 10:13) አዎን፣ ይሖዋ ‘በመከራችን ሁሉ የሚያጽናናን የመጽናናት ሁሉ አባት’ መባሉ ያለ ምክንያት አይደለም። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ለመጽናት የሚያስፈልገንን ነገር ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የማይገመት ሰላምም ይሰጠናል።
በቅርቡ መከራ የሌለበት ዓለም ይመጣል!
በቅርቡ ፈጣሪ በመንግሥቱ አማካኝነት በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱትን መከራዎች በሙሉ ጠራርጎ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል። ይህንን የሚያደርገው እንዴት ነው? ዋነኛ የመከራ ጠንሳሽና ቀንደኛ የሰላም ጠላት የሆነውንና መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም አምላክ” በማለት የሚጠራውን ሰይጣን ዲያብሎስን በማስወገድ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ይሁን እንጂ በቅርቡ በሰው ልጆች ላይ ያለው ሥልጣን ያከትማል። የሰይጣን መጥፋት አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው በረከቶችን እንዲያገኙ በር ይከፍታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ሲል ይሖዋ ስለሚያከናውነው ነገር ተስፋ ይሰጣል:- “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”— ራእይ 21:1-4
መከራ የሌለበት ዓለም ይመጣል የሚለው ሐሳብ ሊታመን የማይችል ነውን? መከራ ይቀራል የሚለውን ሐሳብ ለመቀበል እስኪከብደን ድረስ ከመከራ ጋር መኖርን ተለማምደናል። ይሁን እንጂ የአምላክ ዓላማ መጀመሪያውኑም ሰዎች ከፍርሃት፣ ከጭንቀትና ከችግር ነፃ ሆነው እንዲኖሩ ነበር፤ ዓላማው ደግሞ መፈጸሙ አይቀርም።— ኢሳይያስ 55:10, 11
በመጀመሪያው ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሶንያ፣ ፋቢያና እና አና ያገኙት ተስፋም ይኸው ነው። ሁለት ልጆቿ በኤድስ የሞቱባት ሶንያ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ትንሣኤ ያገኛሉ’ ሲል በሚሰጠው ተስፋ ትልቅ እፎይታ አግኝታለች። (ሥራ 24:15) “አንድ እርግጠኛ የሆነ ነገር አለ፤ ተስፋችን ማንኛውንም ዓይነት ሥቃይ እንድንቋቋም ይረዳናል” ብላለች።
አና ጓላሟታ ውስጥ እያለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር አነጋገረቻት። አና እንዲህ ትላለች:- “የይሖዋን ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስታሳየኝ በደስታ አለቀስኩ። ከፍተኛ እርዳታ ያስፈልገኝ ነበር፤ ስለ እኛ የሚያስብ አምላክ እንዳለ አወቅሁ።” አና ከጓላማታው ከወጣች በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ፈቃደኛ በመሆኗ ስለ ይሖዋ ተስፋዎች ተጨማሪ ነገሮችን ተማረች። ከዚያም ራሷን ለይሖዋ አምላክ መወሰኗን በማሳየት ተጠመቀች። “ከዚያን ጊዜ ወዲህ በጸሎት በይሖዋ ላይ ከመታመን ወደኋላ አላልኩም፤ እርሱ እንደሚረዳኝ እርግጠኛ መሆኔ አጽናንቶኛል።”
ፋቢያናም አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሰጠውን ተስፋ በማወቋ ከመከራዋ መጽናኛና የአእምሮ ሰላም አግኝታለች። “የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር በጣም ጨለማና ጭጋጋማ ከሆነ ቦታ ወጥቶ ጥርት ብሎ ወደሚታይበት፣ ብሩህና አስደሳች ቦታ የመግባት ያህል ነው።”— ከመዝሙር 118:5 ጋር አወዳድር።
ይሁን እንጂ በመላዋ ምድር ላይ ቃል በቃል ሰላም የሚሰፍነው እንዴትና መቼ ነው? ይህን ደግሞ በሚቀጥሉት ርዕሶች እንመለከታለን።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱ ልዩ ልዩ መከራዎች
▪ በግምት ሩብ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በከፍተኛ ድህነት ተቆራምዶ የሚኖር ሲሆን በሚልዮን የሚቆጠሩት ሌሎች ደግሞ ከሰውነት ተራ ወጥተው ለሕይወታቸው በሚያሰጋ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
▪ ከ200 ሚልዮን የሚበልጡ ሕፃናት ተመጣጣኝ ምግብ አያገኙም።
▪ የተቅማጥ በሽታ በየዓመቱ ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸውን ሦስት ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት ሕይወት ይቀጥፋል።
▪ በ1993 ብቻ ተላላፊ በሽታዎች 16.5 ሚልዮን ሰዎችን ገድለዋል። አንዳንድ አገሮች በሽታን ከሌላ መደብ ስለሚፈርጁት እንጂ ትክክለኛው አኃዝ ከዚህም እጅግ ሊበልጥ ይችላል።
▪ ወደ 500 ሚልዮን የሚገመቱ ሰዎች በሆነ መልኩ በአእምሮ ሕመም ይሠቃያሉ።
▪ ራስን መግደል ከሌሎች የዕድሜ ክልሎች ይበልጥ በወጣቱ ዘንድ በፍጥነት እየተስፋፋ ሄዷል።
▪ “ረሃብና ሥራ አጥነት የዓለማችን ነቀርሳ ሆነዋል” ሲል ዘ ዩኔስኮ ኩሪየር ዘግቧል። “በሰባቱ የዓለም ባለጠጋ ሀገሮች ውስጥ 35 ሚልዮን ሥራ የፈቱ ሰዎች ሲኖሩ በብራዚል ውስጥ ብቻ ሥራ ኖሯቸውም ጠግበው የማያድሩ 20 ሚልዮን ሠራተኞች ይገኛሉ።”
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጸሎት መከራ የሌለበት ዓለም እንደሚመጣ አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ እንድናተኩር ሊረዳን ይችላል