“ጤዛን ያስገኘ ማን ነው?”
አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ጋዜጠኛ ስለ ጤዛ ሲናገር “ከአየር የተሠራ ፈሳሽ የምድር ጌጥ” በማለት ገልጾታል። ፈጣሪያችን ከጥንት አባቶች አንዱ የሆነውን ኢዮብን “ጤዛን ያስገኘ ማን ነው?” ሲል ጠይቆታል። (ኢዮብ 38:28 የ1980 ትርጉም) አምላክ ውድ የሆነው ጤዛ መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው ኢዮብን አስገንዝቦታል።
ጤዛ ካለው አንጸባራቂ ጌጥ መሰል ውበት በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከበረከት፣ ከልምላሜ፣ ከብልጽግናና ሕይወትን ጠብቆ ከማቆየት ጋር ተያይዞ ተገልጿል። (ዘፍጥረት 27:28፤ ዘዳግም 33:13, 28፤ ዘካርያስ 8:12) በእስራኤል ሞቃታማ የበጋ ወራት ወቅት ‘የአርሞንዔም ጠል’ በምድሪቱ ላይ ያለው ዕፅዋት በሕይወት እንዲቀጥል በማስቻሉ በተዘዋዋሪ መንገድ ሕዝቡን በሕይወት ማቆየት ችሏል። አናቱ በደን እና በበረዶ የተሸፈነው የአርሞንዔም ተራራ በአሁኑ ጊዜም ምሽት ላይ ወደ ውኃነት የሚቀየር ተን ስለሚያመነጭ መስኩ በጤዛ ይሸፈናል። መዝሙራዊው ዳዊት ይህን የመሰለው ጤዛ የሚያስገኘውን ልምላሜ ይሖዋን ከሚያመልኩ የእምነት ጓደኞቻችን ጋር በኅብረት ስንቀመጥ ከሚኖረው አስደሳች ሁኔታ ጋር አመሳስሎታል።—መዝሙር 133:3
ነቢዩ ሙሴ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው መመሪያዎች ልክ እንደ ጤዛ ተስማሚና መንፈስን የሚያድሱ ነበሩ። “ነገሬ እንደ ጠል ትንጠባጠባለች፤ በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፣ በሣርም ላይ እንደ ካፊያ” ሲል ተናግሯል። (ዘዳግም 32:2) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወት ሰጪ የሆነውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች እስከ ምድር ዳር ድረስ በማወጅ ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 24:14) አምላክ “የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” በማለት ግብዣ በማቅረብ ላይ ነው። (ራእይ 22:17) ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወትን ለዘላለም ለማቆየት የሚያስችለውን አምላክ ያቀረበውን ይህን በመንፈሳዊ የሚያድስ ግብዣ እየተቀበሉ ናቸው።