ከእነዚህ እንደ አንዱ ነህን?
‘መቶ ዓመት በግ ሆኖ ከመኖር አንድ ቀን አንበሳ ሆኖ መሞት ይሻላል።’ እነዚህን ቃላት እንደተናገረ የሚነገርለት በአንድ ወቅት የኢጣልያ አምባገነን ገዥ የነበረው ቤኒቶ ሙሶሎኒ ነው።
ብዙ ሰዎች እንደ ሙሶሎኒ በበግ ቢመሰሉ አይወዱም። ይሁን እንጂ የጥንትዋ እሥራኤል መዝሙራዊና ንጉሥ የነበረው ዳዊት “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] እረኛዬ ነው፣ . . . በለመለመ መስክ ያሳድረኛል ብሎአል።” (መዝሙር 23:1, 2) አዎ፣ ሕዝቦቹን ምንም ጉዳት እንደማያስከትሉ በጎች በጥንቃቄና በርህራሄ የሚጠብቃቸው ታላቅ እረኛ ይሖዋ ነው።
የአምላክ ሕዝቦች በመዝሙር 95:7 ላይ ምሳሌያዊ በጎች እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል። እንዲህ እናነባለን:- “እርሱ [ይሖዋ] አምላካችን ነውና፣ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነን።” አንዳንድ ሰዎች መዝሙራዊው “የማሰማርያው በጎች” እና “የእጁ ሕዝብ” ማለት ነበረበት ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ በተገላቢጦሽ የይሖዋ ሕዝቦች ራሳቸው በጎች እንደሆኑ ተገልጾአል። ከአምላክ ማሰማሪያ በሚያገኙት ጥቅም ይደሰታሉ። በፍቅራዊ እጁም ይመራሉ።
የይሖዋ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም መልካም እረኛ ነው። እርሱም ብዙ ጊዜ ሰዎችን በበግ መስሎአል። ለምሳሌ ያህል ስለ “ታናሽ መንጋ” እና ስለ “ሌሎች በጎች” ተናግሮአል። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 10:14–16) ኢየሱስ ትሁታን ስለሆኑት በግ መሰል ደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፣ እኔም አውቃቸዋለሁ፣ ይከተሉኝማል። እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፣ ለዘላለምም አይጠፉም። ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም” ብሏል። (ዮሐንስ 10:27, 28) በጎ አድራጊ ገዥ ሲኖር ተገዥዎቹ ከእጁ ማለትም ከሥልጣኑ፣ ከሞገሱ፣ ከአመራሩና ከጥበቃው ብዙ ጥቅም ያገኛሉ። — ራዕይ 1:16, 20፤ 2:1
በግ መሰል ሰዎችን ከኢየሱስ እጅ ጥበቃ ሊነጥቅ የሚችል የለም። በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ ሰዎችን ሞገሱን በማያገኙ “ፍየሎች” እና በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የዘላለም ሕይወት በሚያገኙ “በጎች” መካከል በመለየት ላይ ነው። (ማቴዎስ 25:31–46) አንተስ ከእነዚህ የተባረኩ በጎች መካከል ትሆናለህን?
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Garo Nalbandian