የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 1/1 ገጽ 27-31
  • ድክመትን፣ ክፋትንና ንስሐን ለይቶ ማወቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ድክመትን፣ ክፋትንና ንስሐን ለይቶ ማወቅ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ድክመትን፣ ክፋትንና ንስሐን መመዘን
  • ኃላፊነቱን መውሰድና ንስሐ መግባት
  • መጥፎ ድርጊትን ማዘውተር
  • በትዕቢት ለይሖዋ ንቀት ማሳየት
  • ሌሎችን መጉዳት
  • አምላካዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅሞ ሁኔታውን ማመዛዘን
  • ምንጊዜም የይሖዋን ተግሣጽ ተቀበል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ከባድ ኃጢአት ብትፈጽም ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 1/1 ገጽ 27-31

ድክመትን፣ ክፋትንና ንስሐን ለይቶ ማወቅ

ኃጢአት ክርስቲያኖች የሚጠሉት ነገር ሲሆን የይሖዋን የጽድቅ ደረጃዎች ሳያሟሉ መቅረት ማለት ነው። (ዕብራውያን 1:9) የሚያሳዝነው ደግሞ ሁላችንም በየጊዜው ኃጢአት የምንሠራ መሆናችን ነው። ሁላችንም በዘር ከወረስነው ድክመትና አለፍጽምና ጋር እንታገላለን። ይሁን እንጂ በአብዛኛው ኃጢአቶቻችንን ለይሖዋ ከተናዘዝንና ላለመድገም ከልብ ጥረት የምናደርግ ከሆነ በንጹሕ ሕሊና ልንቀርበው እንችላለን። (ሮሜ 7:21–24፤ 1 ዮሐንስ 1:8, 9፤ 2:1, 2) ድክመቶች ቢኖሩብንም እንኳ በቤዛው መሥዋዕት አማካኝነት ቅዱስ አገልግሎታችንን ስለሚቀበለን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።

አንድ ሰው በሥጋዊ ድክመት ሳቢያ ከባድ ኃጢአት ከሠራ በያዕቆብ 5:14–16 ላይ ከተገለጸው ሥርዓት ጋር በመስማማት ወዲያውኑ እረኝነት ማግኘት ያስፈልገዋል፦ “ከእናንተ [በመንፈሳዊ] የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ . . . ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል። እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ፣ ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ።”

በመሆኑም አንድ ራሱን ለአምላክ የወሰነ ክርስቲያን ከባድ የሆነ ኃጢአት ከሠራ ኃጢአቱን በግል ለይሖዋ ከመናዘዙ በተጨማሪ ሌላም ነገር ማድረግ ያስፈልገዋል። የጉባኤው ንጽሕና ወይም ሰላም አደጋ ላይ ስለወደቀ ሽማግሌዎች አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው። (ማቴዎስ 18:15–17፤ 1 ቆሮንቶስ 5:9–11፤ 6:9, 10) ሽማግሌዎች የሚከተሉትን ነገሮች ለይተው ማወቅ ያስፈልጋቸው ይሆናል፦ ግለሰቡ ንስሐ ገብቷልን? ኃጢአቱን ለመፈጸም ያበቃው ነገር ምንድን ነው? በድንገተኛ ድክመት ሳቢያ የተከሰተ ነገር ነውን? የተዘወተረ ኃጢአት ነውን? የጥያቄዎቹን ትክክለኛ መልስ ማግኘት ሁልጊዜ ቀላል ወይም ግልጽ አይሆንም፤ ትልቅ ማስተዋል የሚጠይቅ ነው።

ይሁንና ኃጢአቱ የተፈጸመው መጥፎ ድርጊትንና ክፉ አኗኗርን በመከተል የተነሣ ከሆነስ? በዚህ ጊዜ የሽማግሌዎቹ ኃላፊነት ምንም አያሻማም። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ተከስቶ የነበረን አንድ ከባድ ጉዳይ እንዴት መያዝ እንደሚገባ መመሪያ ሲሰጥ “ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት” ብሎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 5:13) ክፉ ሰዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቦታ የላቸውም።

ድክመትን፣ ክፋትንና ንስሐን መመዘን

አንድ ሰው ንስሐ መግባቱን ሽማግሌዎች ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው?a ይህ ቀላል ጥያቄ አይደለም። ለምሳሌ የንጉሥ ዳዊትን ሁኔታ አስብ። ምንዝር ፈጸመ፤ ይህም የእጅ አዙር ነፍስ ግድያን አስከተለ። ሆኖም ይሖዋ በሕይወት እንዲቀጥል ፈቅዶለታል። (2 ሳሙኤል 11:2–24፤ 12:1–14) ስለ ሐናንያና ሰጲራ ደግሞ እስቲ አስብ። በግብዝነት ካደረጉት በላይ የቸሩ መስለው በመቅረብ በውሸት ሐዋርያቱን ለማታለል ሞከሩ። ከባድ ነገር ነበርን? በእርግጥ ነበር። የነፍስ ግድያንና የምንዝርን ያህል መጥፎ ነበርን? በፍጹም! ሆኖም ሐናንያና ሰጲራ ሕይወታቸውን እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል።—ሥራ 5:1–11

የተለያየ ዓይነት ፍርድ የተሰጠው ለምንድን ነው? ዳዊት ከባድ ኃጢአት ሊሠራ የቻለው በሥጋዊ ድክመት የተነሣ ነው። በሠራው ሥራ ሲወነጀል ንስሐ ገብቷል፤ ይሖዋም ይቅር ብሎታል፤ ቢሆንም በቤቱ ውስጥ በተነሱት ችግሮች ክፉኛ ተቀጥቷል። ሐናንያና ሰጲራ ኃጢአት የሠሩት የክርስቲያን ጉባኤን ለማታለል በመሞከር በግብዝነት በመዋሸት ነው። በዚህ መንገድ ‘መንፈስ ቅዱስንና አምላክን ዋሹ።’ ይህም ክፉ ልብ እንደነበራቸው አረጋግጧል። በመሆኑም የከፋ ፍርድ ተቀብለዋል።

በሁለቱም ሁኔታዎች ፍርዱን የፈረደው ይሖዋ ነው። ልብን መመርመር ስለሚችል ደግሞ የወሰነው ፍርድ ትክክለኛ ነበር። (ምሳሌ 17:3) ሰብዓዊ ሽማግሌዎች ይህን ማድረግ አይችሉም። ታዲያ ሽማግሌዎች አንድ ከባድ ኃጢአት ድክመትን የሚያሳይ ይሁን ወይ ክፋት ለይተው ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

እርግጥ ኃጢአት ሁሉ ክፋት ነው፤ ሁሉም ኃጢአተኞች ግን ክፉዎች አይደሉም። አንዱ ዓይነት ኃጢአት የአንዱን ሰው ድክመት ሲያሳይ የሌላውን ሰው ደግሞ ክፋት የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ኃጢአት መሥራት ብዙውን ጊዜ ኃጢአት የሠራው ሰው በተወሰነ ደረጃ ያለበትን ድክመትና ክፋት ያንጸባርቃል። አንዱ መመዘኛ ኃጢአተኛው ለሠራው ኃጢአት ያለው አመለካከትና የሠራውን ኃጢአት በተመለከተ ለማድረግ ያሰበው ነገር ነው። የንስሐ መንፈስ ያሳያልን? ሽማግሌዎች ይህን ለመረዳት ጠለቅ ብለው ማስተዋል ያስፈልጋቸዋል። ይህን ጥልቅ ማስተዋል ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል ቃል ገብቶለት ነበር፦ “የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ [“ይሰጥሃል” አዓት]።” (2 ጢሞቴዎስ 2:7) ሽማግሌዎች ትሑቶች በመሆን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን የጳውሎስንም ሆነ የሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን ቃላት ‘ዘወትር በጥሞና የሚመለከቱ’ ከሆነ በጉባኤው ውስጥ ኃጢአት የሚፈጽሙትን ሰዎች ተገቢ በሆነ መንገድ ለመመልከት የሚያስፈልገውን ማስተዋል ያገኛሉ። እንዲህ ሲያደርጉ ውሳኔያቸው የራሳቸውን ሳይሆን የይሖዋን ሐሳብ የሚያንጸባርቅ ይሆናል።—ምሳሌ 11:2፤ ማቴዎስ 18:18

ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ ሰዎችን እንዴት አድርጎ እንደሚገልጻቸው መመርመርና መግለጫው ጉዳዩን በመመልከት ላይ ባሉት ሰው ላይ ይሠራ እንደሆነና እንዳልሆነ መመልከት ነው።

ኃላፊነቱን መውሰድና ንስሐ መግባት

የክፋትን ጎዳና የመረጡት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን ናቸው። ፍጹም የነበሩና ስለ ይሖዋ ሕግ የተሟላ እውቀት የነበራቸው ቢሆኑም እንኳ በመለኮታዊ ሉዓላዊነት ላይ ዓመፁ። ይሖዋ ስለሠሩት ሥራ ሲያፋጥጣቸው ያሳዩት ምላሽ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር ነው፤ አዳም በሔዋን አላከከ፤ ሔዋን ደግሞ በእባቡ አላከከች! (ዘፍጥረት 3:12, 13) ይህን አድራጎት ከዳዊት የጠለቀ ትሕትና ጋር አወዳድረው። በፈጸማቸው ከባድ ኃጢአቶች ሲወነጀል ኃላፊነቱን ተቀብሎ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” በማለት ይቅር እንዲባል ተማጽኗል።—2 ሳሙኤል 12:13፤ መዝሙር 51:4, 9, 10

ሽማግሌዎች በተለይ ለአካለ መጠን የደረሰን ግለሰብ ከባድ ኃጢአት በሚመረምሩበት ጊዜ እነዚህን ሁለት ምሳሌዎች ማጤናቸው ጥሩ ነው። ኃጢአተኛው ኃጢአቱን እንዲያምን ሲደረግ እንደ ዳዊት ወዲያውኑ ወቀሳውን ተቀብሎ በመጸጸት ይሖዋ እንዲረዳውና ይቅር እንዲለው ይለምናል ወይስ የሠራውን ለማቃለልና ምናልባትም በሌላ ሰው ለማላከክ ይሞክራል? እውነት ነው፣ ኃጢአት የሠራው ሰው ድርጊቱን ለመፈጸም ያበቃውን ነገር ለመናገር ይፈልግ ይሆናል፤ እንዲሁም ሽማግሌዎች በምን መንገድ ሊረዱት እንደሚችሉ በሚወስኑበት ጊዜ ግምት ውስጥ ሊያስገቧቸው የሚገቡ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን የተከናወኑ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። (ከሆሴዕ 4:14 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ኃጢአት የሠራው እሱ መሆኑንና በይሖዋ ፊት ተጠያቂው እሱ መሆኑን መቀበል ይኖርበታል። “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” የሚለውን ቃል አስታውሱ።—መዝሙር 34:18

መጥፎ ድርጊትን ማዘውተር

በመዝሙራት መጽሐፍ ውስጥ ስለ ክፉ ሰዎች የሚናገሩ ብዙ ጥቅሶች አሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ጥቅሶች አንድ ሰው በመሠረቱ ክፉ ይሁን ደካማ ለይተው ለማወቅ ሽማግሌዎችን ይበልጥ ሊረዷቸው ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ንጉሥ ዳዊት በመንፈስ አነሳሽነት የጸለየውን ጸሎት ተመልከት፦ “ከኀጥአንና ከክፉ አድራጊዎች [“መጥፎ ድርጊትን አዘውትረው ከሚፈጽሙ” አዓት] ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፤ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ።” (መዝሙር 28:3) ክፉ ሰዎች “መጥፎ ድርጊትን አዘውትረው ከሚፈጽሙ” ሰዎች ጋር ጎን ለጎን እንደተጠቀሱ ልብ በል። በሥጋዊ ድክመት ምክንያት ኃጢአት የፈጸመ ሰው አድራጎቱን አውቆ ወደ ልቡ ሲመለስ ወዲያውኑ እንደሚያቆም የታወቀ ነው። ይሁንና አንድ ሰው መጥፎ ድርጊትን ‘የሚያዘወትር’ ወይም የሚቀጥልበት በመሆኑ ምክንያት ድርጊቱ አንዱ የኑሮው ክፍል ወደ መሆን ደረጃ ከደረሰ ይህ የክፉ ልብ ምልክት ሊሆን ይችላል።

ዳዊት በዚያው ቁጥር ላይ ሌላ የክፋት መለያ የሆነ ጠባይ ጠቅሷል። ክፉው ሰው ልክ እንደ ሐናንያና ሰጲራ በአፉ ጥሩ ነገሮችን ይናገራል፤ ሆኖም በልቡ ውስጥ መጥፎ ነገሮችን ይቋጥራል። ‘በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን የሚታዩትና በውስጣቸው ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት የሞላባቸው’ በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን እንደነበሩት ግብዝ ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 23:28፤ ሉቃስ 11:39) ይሖዋ ግብዝነትን ይጠላል። (ምሳሌ 6:16–19) አንድ ሰው ሌላው ቀርቶ በፍርድ ኮሚቴ ፊት ቀርቦ በሚናገርበት ጊዜም እንኳ የሠራቸውን ከባድ ኃጢአቶች በግብዝነት ለመካድ የሚሞክር ከሆነ ወይም በእምቢተኝነት ሙሉ በሙሉ ለመናዘዝ አሻፈረኝ በማለት ሌሎች ያወቁትን ድርጊት ብቻ አምኖ የሚቀበል ከሆነ ይህም የክፉ ልብ ምልክት ሊሆን ይችላል።

በትዕቢት ለይሖዋ ንቀት ማሳየት

አንድን ክፉ ሰው ለይተው የሚያሳውቁ ሌሎች ነገሮች በመዝሙር 10 ላይ ተዘርዝረዋል። እዚያ ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ክፉ ሰዎች ይታበያሉ፤ ድኾችንም ያሳድዳሉ፤ . . . እግዚአብሔርንም ይክዳል [“ይንቃል” አዓት]።” (መዝሙር 10:2, 3 የ19 80 ትርጉም) ትዕቢተኛ የሆነንና ይሖዋን የሚንቅን አንድ ራሱን ለአምላክ የወሰነ ክርስቲያን መመልከት ያለብን እንዴት ነው? እነዚህ ክፉ አስተሳሰቦች እንደሆኑ አያጠራጥርም። በድክመት የተነሳ ኃጢአት የፈጸመ ሰው አንዴ የሠራውን ኃጢአት ከተገነዘበ ወይም ካስተዋለ ንስሐ በመግባት አኗኗሩን ለመለወጥ ጠንክሮ ይሠራል። (2 ቆሮንቶስ 7:10, 11) በአንጻሩ አንድ ሰው በይሖዋ ላይ ባለው መሠረታዊ ንቀት የተነሣ ኃጢአት ቢሠራ በተደጋጋሚ ወደ ኃጢአተኝነት ተግባሩ ከመመለስ ምን ያግደዋል? በየዋህነት መንፈስ ምክር ቢሰጠውም እንኳ ትዕቢተኛ ከሆነ ከልቡ ተነሳስቶ እውነተኛ ንስሐ ለመግባት የሚያስፈልገው ትሕትና እንዴት ሊኖረው ይችላል?

ዳዊት በዚያው መዝሙር ውስጥ ትንሽ ወረድ ብሎ የተናገራቸውን ቃላት ተመልከት፦ “ኃጢአተኛ ሰው እግዚአብሔርን ስለምን ይንቃል? በአሳቡስ “እግዚአብሔር አይቀጣኝም” ለምን ይላል?” (መዝሙር 10:13 የ1980 ትርጉም) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ክፉው ሰው ትክክልና ስህተት በሆነው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት ያውቃል፤ ሆኖም ምንም እንደማይሆን አድርጎ ካሰበ ስህተት ለመፈጸም ምንም አያቅማማም። እጋለጣለሁ የሚል ፍራቻ እስከሌለበት ድረስ ለኃጢአት ዝንባሌዎቹ ሙሉ ነጻነት ይሰጣቸዋል። ከዳዊት በተለየ መልኩ ኃጢአቶቹ ገሃድ ከወጡ ከተግሣጽ የሚያመልጥበትን መንገድ ይሸርባል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ይሖዋን እጅግ የሚያቃልል ሰው ነው። “የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዓይኖቹ ፊት የለም። . . . ክፋትን አይንቃትም።”—መዝሙር 36:1, 4

ሌሎችን መጉዳት

ብዙውን ጊዜ በአንድ ኃጢአት ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ይጎዳሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ አመንዝራ በአምላክ ላይ ኃጢአት ይሠራል፤ ሚስቱንና ልጆቹን ለሥቃይ ሰለባነት ይዳርጋቸዋል፤ በኃጢአቱ የተባበረችው ሴት ባለ ትዳር ከሆነች የእሷንም ቤተሰብ ለሥቃይ ሰለባነት ይዳርጋል፤ እንዲሁም የጉባኤውን መልካም ስም ያጎድፋል። ይህን ሁሉ የሚመለከተው እንዴት ነው? እውነተኛ ንስሐን ጨምሮ ልባዊ የሐዘን ስሜት ያሳያልን? ወይስ በመዝሙር 94 ላይ የተጠቀሰውን መንፈስ ያንጸባርቃል፦ “ዓመፃንም የሚያደርጉ ሁሉ ይናገራሉ። አቤቱ፣ ሕዝብህን አዋረዱ፣ ርስትህንም አስቸገሩ። ባልቴቲቱንና ድሀ አደጉን ገደሉ፣ ስደተኛውንም ገደሉ። እግዚአብሔር አያይም፣ የያዕቆብም አምላክ አያስተውልም አሉ”?—መዝሙር 94:4–7

በአንድ ጉባኤ የሚከሰቱ ኃጢአቶች ነፍስ ግድያንና ሕይወት ማጥፋትን የሚመለከቱ ላይሆኑ ይችላሉ። ሆኖም በዚህ ጊዜ የሚንጸባረቀው መንፈስ ይኸውም ለግል ጥቅም ሲባል ሌሎችን ለሥቃይ ለመዳረግ ዝግጁ የመሆን መንፈስ ሽማግሌዎች ኃጢአትን በሚመረምሩበት ጊዜ ገሃድ ሊወጣ ይችላል። ይህም የአንድ ክፉ ሰው መለያ ምልክት የሆነ የዕብሪት መንፈስ ነው። (ምሳሌ 21:4) ይህ ራሱን ለወንድሙ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ የሆነ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ካለው መንፈስ ፍጹም ተቃራኒ ነው።—ዮሐንስ 15:12, 13

አምላካዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅሞ ሁኔታውን ማመዛዘን

እነዚህ ጥቂት መምሪያዎች ደንቦችን ለመደንገግ የታለሙ አይደሉም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በትክክል ክፉ ናቸው ብሎ የሚመለከታቸውን አንዳንድ ነገሮች ይጠቁሙናል። የተሠራውን ጥፋት በኃላፊነት ለመቀበል አሻፈረኝ ይላልን? ኃጢአት የሠራው ሰው ቀደም ሲል በዚሁ ጉዳይ ላይ የተሰጠውን ምክር ያለ ምንም ሀፍረት ወደ ጎን ገሸሽ አድርጓልን? ከባድ የሆነ መጥፎ ድርጊት የመፈጸም ልማድ ክፉኛ ተጠናውቶታልን? መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ሰው ለይሖዋ ሕግ ግልጽ የሆነ ንቀት ያሳያልን? መጥፎውን ድርጊት ለመደበቅ፣ ምናልባትም እግረመንገዱን ሌሎች ሰዎችን ለመበከል ሆን ብሎ ጥረት አድርጓልን? (ይሁዳ 4) መጥፎው ድርጊት ገሃድ ሲወጣ እንዲህ ዓይነቶቹ ጥረቶች ጭራሹኑ ይበልጥ ይጠናከራሉን? መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ሰው በሌሎችና በይሖዋ ስም ላይ ላስከተለው ጉዳት ደንታ ቢስነት ያሳያልን? አቋሙስ ምንድን ነው? በደግነት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ከተሰጠውም በኋላ ትዕቢተኛ ወይም ዕብሪተኛ ነውን? መጥፎውን ድርጊት ላለመድገም ልባዊ ፍላጎት ይጎድለዋልን? ሽማግሌዎች የንስሐ ጉድለት እንዳለ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠቁሙትን እንዲህ ዓይነቶቹን ነገሮች ካስተዋሉ የተፈጸሙት ኃጢአቶች እንዲሁ የሥጋ ድክመትን ብቻ ሳይሆን ክፋትንም የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንደሆኑ አድርገው ሊደመድሙ ይችላሉ።

የክፋት ዝንባሌዎች ያሉት ከሚመስል ሰው ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜም እንኳ ሽማግሌዎች የጽድቅን መንገድ እንዲከታተል አጥብቀው ከማሳሰብ ወደኋላ አይሉም። (ዕብራውያን 3:12) ክፉ ግለሰቦች ንስሐ ሊገቡና ሊለወጡ ይችላሉ። እንዲህ ባይሆን ኖሮ ይሖዋ እስራኤላውያንን ለምን እንዲህ ብሎ አጥብቆ ያሳስባቸው ነበር፦ “ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፣ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ”? (ኢሳይያስ 55:7) ምናልባት ጉዳዩን የፍርድ ኮሚቴ በሚሰማበት ጊዜ ሽማግሌዎቹ የሚያነጋግሩት ሰው የንስሐ ዝንባሌና አመለካከት ሲያሳይ በልቡ ሁኔታ ላይ ግልጽ የሆነ ለውጥ ማድረጉን ሊያስተውሉ ይችሉ ይሆናል።

አንድ ግለሰብ በሚወገድበት ጊዜም እንኳ ሽማግሌዎቹ እረኞች እንደመሆናቸው መጠን ንስሐ እንዲገባና መንገዱን በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ወዳለው አቅጣጫ ለመመለስ እንዲሞክር አበክረው ያሳስቡታል። በቆሮንቶስ የነበረውን “ክፉውን” ሰው አስታውሱ። መንገዱን እንደለወጠ ግልጽ ነው፤ በኋላም ጳውሎስ ከውገዳ እንዲመልሱት ሐሳብ አቅርቦላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 2:7, 8) ንጉሥ ምናሴንም እንውሰድ። በእርግጥ በጣም ክፉ ነበር፤ ይሁን እንጂ በመጨረሻ ንስሐ ሲገባ ይሖዋ ንስሐውን ተቀብሎታል።—2 ነገሥት 21:10–16፤ 2 ዜና መዋዕል 33:9, 13, 19

እውነት ነው፣ ይቅር የማይባል ኃጢአት አለ፤ እሱም በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ነው። (ዕብራውያን 10:26, 27) ያ ኃጢአት መፈጸም አለመፈጸሙን የሚወስነው ይሖዋ ብቻ ነው። ሰዎች እዚህ ላይ ሥልጣን የላቸውም። የሽማግሌዎቹ ኃላፊነት የጉባኤውን ንጽሕና መጠበቅና ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች ወደ ቀድሞው ጥሩ ሁኔታቸው እንዲመለሱ መርዳት ነው። ሽማግሌዎች በማስተዋልና በትሕትና ይህን ካደረጉና ውሳኔያቸው የይሖዋን ጥበብ እንዲያንጸባርቅ ከተጠነቀቁ ይሖዋ ይህን የእረኝነታቸውን ዘርፍ ይባርክላቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ 9–102 ገጽ 5, 6 እንዲሁም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 2 ገጽ 772–4 ተመልከት።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐናንያና ሰጲራ የልባቸውን ክፋት በሚያሳይ ሁኔታ በግብዝነት መንፈስ ቅዱስን ዋሹ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ