የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 11/1 ገጽ 26-29
  • ‘ይሖዋን ከሀብትህ አክብር’—እንዴት?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ይሖዋን ከሀብትህ አክብር’—እንዴት?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “እግዚአብሔርን አክብር”
  • “ሀብትህ” የተባሉት ነገሮች ምንድን ናቸው?
  • ጥንታዊ ምሳሌዎች
  • በጊዜያችን ‘በፈቃደኝነት የሚደረጉ መዋጮዎች’
  • ይሖዋ የሚያከብሩትን ሰዎች ይባርካል
  • ለይሖዋ የምንሰጠው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • “ገንዘቡ የሚገኘው ከየት ነው?”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • አንዳንዶች ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ እርዳታ የሚሰጡበት መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የ“በጎ ስጦታ ሁሉ” ሰጭ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 11/1 ገጽ 26-29

‘ይሖዋን ከሀብትህ አክብር’—እንዴት?

‘ይሖዋን ከሀብትህ አክብር፣ ከፍሬህም ሁሉ በኩራት።’ ከ2,600 ዓመታት በፊት በመለኮታዊ ኃይል አነሳሽነት በተጻፉት በእነዚህ የጥበብ ቃላት ውስጥ የተትረፈረፈ የይሖዋ በረከት የሚገኝበት ቁልፍ ተጠቅሷል። ምክንያቱም ጸሐፊው በመቀጠል “ጎተራህም እህልን ይሞላል፣ መጥመቂያህም በወይን ጠጅ ሞልታ ትትረፈረፋለች” ብሏል።​—⁠ምሳሌ 3:​9, 10

ይሁን እንጂ አምላክን ማክበር ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋን ልናከብርበት የሚያስችለን ሀብት ምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

“እግዚአብሔርን አክብር”

በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ማክበር ለሚለው ቃል የገባው የዕብራይስጥ ቃል ካቮድ የሚል ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “መክበድ” ማለት ነው። ስለዚህ አንድን ሰው ማክበር ማለት እሱን ወይም እሷን ከባድ፣ ግዙፍና ከፍተኛ ዋጋ ያለው አድርጎ መመልከት ማለት ነው። ማክበር ተብሎ የተሠራበት ሌላው የዕብራይስጥ ቃል ደግሞ ዬቃር ሲሆን “ውድ” እና “ውድ ነገሮች” ተብሎ ተተርጉሟል። በተመሳሳይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ማክበር” ተብሎ የተተረጎመው ታይሚ የሚለው የግሪክኛ ቃል በአክብሮት መመልከት፣ ትልቅ ግምት መስጠትና እንደ ክቡር ነገር አድርጎ መያዝ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ስለዚህ አንድ ሰው ሌላውን የሚያከብረው ለዚያ ሰው ጥልቅ አክብሮት በማሳየትና ከፍ አድርጎ በመመልከት ነው።

አክብሮት መስጠት ሌላም ነገር ይጨምራል። በአንድ ወቅት የጥንቱን የፋርስ ንጉሥ አርጤክስስን ለመግደል ተጠንስሶ የነበረውን ሴራ ስላጋለጠው አይሁዳዊ ስለ መርዶክዮስ የሚናገረውን ታሪክ ተመልከቱ። ከጊዜ በኋላ ንጉሡ፣ መርዶክዮስ ላደረገው ነገር ምንም ክብር እንዳልተሰጠው በተረዳ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበረውን ሐማን ጠርቶ ንጉሡ የተደሰተበትን ሰው ለማክበር ምን ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ ጠየቀው። ሐማ ይህን የመሰለው ክብር ለእሱ እንደሚሆን አስቦ ነበር፤ ነገር ግን በጣም ተሳስቷል! የሆኖ ሆኖ ሐማ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ‘የንጉሡን የክብር ልብስ’ መልበስና “ንጉሡ የተቀመጠበት ፈረስ” ላይ መቀመጥ አለበት አለ። ሲያጠቃልልም “በፈረሱ ላይ አስቀምጠውት በከተማይቱ አደባባይ ያሳልፉት፤ በፊቱም:- ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ተብሎ አዋጅ ይነገር” አለ። (አስቴር 6:​1-9) በዚህ ሁኔታ ላይ እንደታየው ለአንድ ሰው ክብር መስጠት ሁሉም ሰዎች ከፍ ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት ሲባል ሰውየውን በሕዝብ ፊት ማወደስን ይጨምር ነበር።

በተመሳሳይም ለይሖዋ አክብሮት መስጠት ሁለት ነገሮችን ያካትታል፤ በግል እሱን ከፍ አድርጎ መመልከትና ስሙን ለሕዝብ በማወጁ ሥራ በመካፈልና ሥራውን በመደገፍ እሱን በሰዎች ፊት ማወደስ ናቸው።

“ሀብትህ” የተባሉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሀብት ተብለው የተገለጹት ነገሮች ሕይወታችንን፣ ጊዜያችንን፣ ተሰጥዎቻችንንና ጉልበታችንን እንደሚያጠቃልሉ የተረጋገጠ ነው። ስለ ቁሳዊ ንብረቶቻችንስ ምን ለማለት ይቻላል? ኢየሱስ አንዲት ድሀ መበለት አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን ሁለት ሳንቲሞች በቤተ መቅደሱ መዋጮ ሣጥን ውስጥ ስትጥል ባየበት ጊዜ የተናገራቸውን ቃላት ልብ በል። ኢየሱስ “ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጒድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ።” (ሉቃስ 21:​1-4) ይህች መበለት የይሖዋን አምልኮ ለማራመድ ስትል ያላትን ቁሳዊ ንብረት በመጠቀሟ ኢየሱስ አወድሷታል።

ስለዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሰሎሞን የጠቀሰው ሀብት ያለንን ማንኛውንም ዓይነት ንብረት ያጠቃልላል። እንዲሁም “ከፍሬህም ሁሉ በኩራት” የሚለው አገላለጽ ካለን ሀብት ውስጥ ምርጡን ለይሖዋ መስጠትን ያመለክታል።

ይሁን እንጂ ቁሳዊ ነገሮችን በመስጠት አምላክን ማክበር የሚቻለው እንዴት ነው? ቀድሞውኑስ ቢሆን ሁሉ ነገር የእሱ አይደለምን? (መዝሙር 50:​10፤ 95:​3-5) ንጉሥ ዳዊት “ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና” ሲል ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ይህን አረጋግጧል። እንዲሁም ቤተ መቅደሱን ለመገንባት እሱና ሕዝቡ ስላደረጉት መዋጮ ሲናገር “ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና” ብሏል። (1 ዜና መዋዕል 29:​14) ስለዚህ ለይሖዋ ስጦታ ስንሰጥ እሱ በደግነት የሰጠንን ነገር መልሰን መስጠታችን ነው። (1 ቆሮንቶስ 4:​7) ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ይሖዋን ማክበር እሱን በሌሎች ሰዎች ፊት ማወደስንም ይጨምራል። በተጨማሪም እውነተኛውን አምልኮ ለማራመድ የሚያገለግሉ ቁሳዊ ስጦታዎች አምላክ እንዲከበር ያደርጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ መንገድ ይሖዋን ስለማክበር የሚናገሩ በጣም ጥሩ ምሳሌዎችን ይዟል።

ጥንታዊ ምሳሌዎች

ከ3,500 ዓመታት በፊት ይሖዋ ለእስራኤላውያን በምድረ በዳ የመገናኛ ድንኳኑን የአምልኮ ቦታ አድርጎ የሚሰጥበት ጊዜ ሲደርስ መለኮታዊውን ንድፍ ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ውድ እቃዎች አስፈልገው ነበር። ‘የልብ ፈቃድ ያለው ሁሉ የይሖዋን መዋጮ እንዲያመጣ’ ለሕዝቡ ይነግር ዘንድ ይሖዋ ሙሴን አዘዘው። (ዘጸአት 35:​5) ታሪኩ ሲቀጥል እንዲህ ይላል:- “ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ።” (ዘጸአት 35:​21) ሕዝቡ በፈቃዳቸው ያመጡት መዋጮ ለሥራው ከሚያስፈልገው በላይ ከመሆኑ የተነሣ ‘ሕዝቡ እንዳያመጡ መከልከል’ ነበረባቸው!​—⁠ዘጸአት 36:​5, 6

ሌላም ምሳሌ ተመልከት። የመገናኛው ድንኳን ለታቀደለት ዓላማ ካገለገለ በኋላ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ዳዊት ልጁ ሰሎሞን ለሚገነባው ለዚህ ቤተ መቅደስ መሥሪያ በግሉ ከፍተኛ መዋጮ አድርጓል። በተጨማሪም ሌሎች ሰዎች እንዲተባበሩት ጥሪ ሲያቀርብ ለይሖዋ ውድ የሆኑ ስጦታዎችን በማምጣት ሕዝቡ ለጥሪው ምላሽ ሰጥቷል። ብሩና ወርቁ ብቻ ዛሬ ባለው ዋጋ ቢተመን 50 ቢልዮን ዶላር ይሆናል። “ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፣ ደስ አላቸው።”​—⁠1 ዜና መዋዕል 29:​3-9፤ 2 ዜና መዋዕል 5:​1

በጊዜያችን ‘በፈቃደኝነት የሚደረጉ መዋጮዎች’

በጊዜያችን በፈቃደኝነት መዋጮ ከማድረግ በሚገኘው ደስታ ተካፋዮች ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ዘመን በዓለም ላይ እየተካሄደ ያለው በጣም አስፈላጊ ሥራ መንግሥቱን መስበክና ደቀ መዛሙርት ማድረግ ነው። (ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20፤ ሥራ 1:​8) በተጨማሪም ይሖዋ የመንግሥቱን ምድራዊ ፍላጎቶች ለምሥክሮቹ በአደራ መስጠትን ተገቢ ሆኖ አግኝቶታል።​—⁠ኢሳይያስ 43:​10

ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች እያከናወኑት ላለው ሥራ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። የመንግሥት አዳራሾችን፣ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን፣ ፋብሪካዎችንና የቤቴል ቤቶችን መሥራትና መጠገን ገንዘብ ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማተምና ማሰራጨትም ወጪዎች አሉት። እነዚህን የመሳሰሉ ድርጅታዊ ወጪዎች የሚሸፈኑት እንዴት ነው? ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት በሚሰጡ መዋጮዎች አማካኝነት ነው!

አብዛኛዎቹ መዋጮዎች የሚገኙት ኢየሱስ እንደተመለከታት መበለት መጠነኛ ገቢ ካላቸው ግለሰቦች ነው። ይሖዋን በዚህ መስክ ማክበሩ እንዲያመልጣቸው ስለማይፈልጉ “እንደ ዓቅማቸው መጠን” እንዲሁም አንዳንዴ “ከዓቅማቸውም የሚያልፍ” የተወሰነ መዋጮ ያደርጋሉ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 8:​3, 4

ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 9:​7) በደስታ ለመስጠት ጥሩ የሆነ እቅድ ማውጣት ያስፈልጋል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች “እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያን ጊዜ እንዳይሆን፣ ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ” ብሏቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 16:​2) በተመሳሳይም ዛሬ የመንግሥቱን ሥራ ለማራመድ በግልና በፈቃደኝነት መዋጮ ለማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ ለዚህ ዓላማ የሚውል ገንዘብ ከገቢያቸው የተወሰነ መጠን ሊያስቀምጡ ይችላሉ።

ይሖዋ የሚያከብሩትን ሰዎች ይባርካል

ቁሳዊ ብልጽግና በራሱ ወደ መንፈሳዊ ብልጽግና ባይመራም ያለንን ሀብት ማለትም ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ቁሳዊ ሀብታችንን ይሖዋን ለማክበር በልግስና መስጠታችን በረከት ያስገኛል። ይህ የሚሆንበት ምክንያት “ለጋስ ነፍስ መልሳ ራስዋ ትጠግባለች፣ በነፃ ውኃ የሚያጠጣም ራሱ መልሶ በነፃ ይጠጣል” በማለት የሁሉም ነገር ባለቤት የሆነው አምላክ ዋስትና ስለሚሰጠን ነው።​—⁠ምሳሌ 11:​25 NW

ንጉሥ ዳዊት ከሞተ በኋላ ልጁ ሰሎሞን አባቱ የሰበሰበውን በፈቃደኝነት የተደረገ መዋጮ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ታላቅ የሆነ ቤተ መቅደስ ለመገንባት ተጠቅሞበታል። እንዲሁም ሰሎሞን አምላክን በማምለክ ታማኝ ሆኖ እስከቀጠለበት ጊዜ ድረስ “በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ . . . ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።” (1 ነገሥት 4:​25) እስራኤላውያን ‘ባላቸው ሀብት ይሖዋን ማክበራቸውን’ እስከ ቀጠሉ ድረስ ጎተራቸው አይጎድልም ነበር፤ እንዲሁም የወይን መጥመቂያዎቻቸው ጢም ብለው ይሞሉ ነበር።

ከጊዜ በኋላ ይሖዋ በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት እንዲህ ብሎ ነበር:- “የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፣ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” (ሚልክያስ 3:​10) ዛሬ የይሖዋ አገልጋዮች ያገኙት መንፈሳዊ ብልጽግና አምላክ የገባውን ቃል እንደሚጠብቅ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

ይሖዋ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስቀደም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ስናደርግ በእርግጥ ይደሰታል። (ዕብራውያን 13:​15, 16) እንዲሁም ‘መንግሥቱንና ጽድቁን አስቀድመን መፈለጋችንን ከቀጠልን’ ደግፎ እንደሚያቆመን ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 6:​33) ከልብ በመነጨ ደስታ ተነሳስተን ‘ይሖዋን ባለን ሀብት እናክብረው።’

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንዳንድ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ማድረግ የሚችሉባቸው መንገዶች

ብዙዎች “ለማኅበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ​—⁠ማቴዎስ 24:​14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩትን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ይመድባሉ ወይም ወጪ ያደርጋሉ። ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአካባቢው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ።

በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎች በቀጥታ Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-​2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገርህ ወደሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም በእርዳታ መስጠት ይቻላል። የተላከው ነገር ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ አብሮ መላክ ይኖርበታል።

ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት

አንድ ሰው ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሰጠውን ገንዘብ ሊጠቀምበት በሚፈልግበት ጊዜ ሊመለስለት የሚያስችል ልዩ ዝግጅት በማድረግ ለማኅበሩ ሊሰጥ ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።

በእቅድ የሚደረግ ስጦታ

ለማኅበሩ በቀጥታ የገንዘብ ስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም መስጠት የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ:-

ኢንሹራንስ:- የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ሲደረግ ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።

የባንክ ሒሳብ:- የአገሩ ባንክ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ማንኛውም ዝግጅት መደረጉን ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።

አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችና ቦንዶች እንዳለ በስጦታ መልክም ሆነ ገቢው ለሰጪው ያለማቋረጥ የሚከፈልበት ዝግጅት ተደርጎ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በእርዳታ መልክ መስጠት ይቻላል።

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች:- ሊሸጡ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እንዳለ በስጦታነት ወይም ሰጪው በሕይወት እስካለ ድረስ በንብረቱ በመተዳደር እንዲቀጥል መብቱን በማስጠበቅ ለማኅበሩ በእርዳታ መስጠት ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማኅበሩ ከማስተላለፉ በፊት ከማኅበሩ ጋር መገናኘት ይኖርበታል።

ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት። የኑዛዜው ወይም ንብረት በአደራ የተሰጠበት ስምምነት ቅጂ ለማኅበሩ ሊላክ ይገባል።

“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል በትንሹም ቢሆን እቅድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። ማኅበሩን በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደጎም ለሚፈልጉ ግለሰቦች የዓለም አቀፉን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ስጦታዎችን፣ ኑዛዜዎችንና አደራዎችን በተመለከተ ማኅበሩ ለቀረቡለት ብዛት ያላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ነው። ብሮሹሩ ንብረትን፣ የገንዘብ አጠቃቀምንና የቀረጥ ምጣኔን አስመልክቶ ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን የያዘ ከመሆኑም በተጨማሪ በዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩና በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የመንግሥቱን ፍላጎት ለመደጎም ፍላጎት ያላቸውን ግለሰቦች የቤተሰባቸውና የግል ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውን ጠቃሚና ውጤታማ ዘዴ ለመምረጥ እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ይህን ብሮሹር በማንበብና በእቅድ የሚደረግ ስጦታ ዴስክ ላይ ከሚሠሩት ወንድሞች ምክር በመጠየቅ ብዙዎች ማኅበሩን ለመርዳት ከመቻላቸውም በላይ ከቀረጥ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ችለዋል። በጽሑፍ ወይም በስልክ ጥያቄ በማቅረብ ብሮሹሩን ማግኘት ይቻላል።

በየትኛውም በእቅድ በሚደረጉት በእነዚህ የስጦታ ዝግጅቶች ለመካፈል የሚፈልጉ ሰዎች Planned Giving Desk, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 100 Watchtower Drive, Patterson, New York 12563-​9204, telephone (914) 878-​7000 ብለው መጻፍ ወይም በአገራቸው የሚገኘውን የማኅበሩን ቢሮ ማነጋገር ይገባቸዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ