እነዚህን ጋሬጣዎች ማለፍ ትችላለህ!
አንድ ግዙፍ አውሮፕላን በመቶ የሚቆጠሩ መንገደኞችንና ብዙ ቶን የሚመዝን ዕቃ ጭኖ ወደ ሌላ አገር መጓዝ ይችላል። እንዲህ ያለ ግዙፍ አውሮፕላን ምድርን ለቅቆ በአየር ላይ ሊንሳፈፍ የሚችለው እንዴት ነው? ሊፍት በሚል የኤሮዳይናሚክ ኃይል አማካኝነት የስበትን ኃይል ተቋቁሞ አውሮፕላኑ ምድርን ለቅቆ በአየር ላይ ስለሚንሳፈፍ ነው።
አውይሮፕላኑ በመንደርደሪያው ላይ በፍጥነት በሚጓዝበት ጊዜ ጎበጥ ባሉት ክንፎች ላይና ታች አየር በፍጥነት ያልፋል። ይህም ሊፍት የሚባለውን ወደ ላይ የሚገፋ ኃይል ይፈጥራል። አውሮፕላኑ በቂ የሆነ ሊፍት ሲያገኝ ምድርን ለቅቆ መብረር ይችላል። እርግጥ ነው ከአቅሙ በላይ የጫነ አውሮፕላን በአየር ላይ እንዲንሳፈፍ የሚያደርገውን በቂ ሊፍት ሊያገኝ አይችልም።
እኛም ሸክማችን ከአቅማችን በላይ ሊሆን ይችላል። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ንጉሥ ዳዊት ‘ኃጢአቱ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ከብዶት እንደነበረ’ ተናግሯል። (መዝሙር 38:4) በተመሳሳይም ኢየሱስ ክርስቶስ የኑሮ ጭንቀቶች ከባድ ሸክም እንዳይሆኑብን አስጠንቅቋል። (ሉቃስ 21:34) አፍራሽ አስተሳሰቦችና ስሜቶች “መንሳፈፍ” የማይቻል እስኪመስለን ድረስ ሊከብዱን ይችላሉ። አንተም በተመሳሳይ መንገድ ሸክምህ ከብዶብሃልን? ወይም ተጨማሪ መንፈሳዊ እድገት እንዳታደርግ አንዳንድ መሰናክሎች ገጥመውሃልን? ገጥሞህ ከሆነ ለማስወገድ ምን ሊረዳህ ይችላል?
ሰልችቶሃልን?
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ስልችት ብሎኛል ሲሉ ይሰማል። ይህ ደግሞ ለአንዳንድ የይሖዋ ሕዝቦችም ጭምር የአእምሮ ውስጥ ጋሬጣ ሊሆንባቸው ይችላል። በተለይ ወጣቶች አንዳንድ ሥራዎችን አሰልቺ አድርገው ስለሚቆጥሯቸው ወደ ጎን ገሸሽ የማድረግ ዝንባሌ አላቸው። አንተም አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንደዚያ ሆነው ይታዩሃልን? ከሆነ በስብሰባ ላይ መገኘትህ ስሜትህን የሚቀሰቅስ እንዲሆንልህ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
ቁልፉ በስብሰባዎቹ ላይ መሳተፍ ነው። ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ “እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ። ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” በማለት ጽፎለታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:7, 8) መጽሐፉ የሚያዛቸውን እንቅስቃሴዎች አንድ በአንድ ተከታትለን ካልሠራን ስለ አካል ብቃት የሚናገረው መጽሐፍ አሰልቺ ወይም ዋጋ ቢስ ይሆናል። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም አእምሯችንን ለማንቀሳቀስ የተዘጋጁ ናቸው። ይህ የሚሆነው ግን ስንዘጋጅና ስንሳተፍ ነው። መዘጋጀታችንና መሳተፋችን ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የበለጠ ዋጋማና የሚያስደስቱ እንዲሆኑልን ያደርጋል።
ማራ የተባለች አንዲት ክርስቲያን ወጣት ይህን በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “ሳልዘጋጅ ወደ ስብሰባዎች ከሄድኩ ደስ አይለኝም፤ ቀደም ብዬ ከተዘጋጀሁ ግን አእምሮዬና ልቤ የበለጠ ተቀባይ ይሆናሉ። ስብሰባዎቹ የበለጠ ትርጉም ያላቸው ይሆኑልኛል። ሐሳብ ለመስጠትም እጓጓለሁ።”
በተጨማሪም ጥሩ አድማጭ ለመሆን መጣር ጠቃሚ ነው። ጣእም ያለው ሙዚቃ መስማት ምንም የማያስቸግር ከመሆኑም በላይ ወዲያውኑ የደስታ ስሜት ይቀሰቅሳል። ይሁን እንጂ ሁሉም ደስታዎች በቅጽበት የሚፈጠሩ አይደሉም። ከስብሰባ ፕሮግራም ደስታ የምናገኘውም የሚነገረውን በጥሞና ስናዳምጥ ብቻ ነው። ራሄል የተባለች አንዲት ክርስቲያን “ተናጋሪው የሚያቀርበውን ንግግር ሕያው አድርጎ ካላቀረበ በንግግሩ ላይ ለማተኮር እቸገራለሁ። የእኔ መመሪያ ‘ንግግሩ የማይመስጥ ከሆነ በአንክሮ ለማዳመጥ ይበልጥ ራሴን ማስገደድ’ የሚል ነው። . . . ከጥቅሶች የሚቻለውን ቁም ነገር ለመቅሰም ስል ልዩ ትኩረት እሰጣቸዋለሁ።” ለማዳመጥ እንደ ራሄል ራሳችንን መገሰጽ ይኖርብናል። የምሳሌ መጽሐፍ “ልጄ ሆይ፣ ወደ ጥበቤ አድምጥ፤ ጆሮህን ወደ ትምህርቴ መልስ” ይላል።—ምሳሌ 5:1
በስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡት አንዳንድ ትምህርቶች ድግግሞሽ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ መደረጉ ግን አስፈላጊ ነው! ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ደካማ የማስታወስ ችሎታና ያሻውን የማድረግ ዝንባሌዎች ያሉት ፍጹም ያልሆነው ሥጋ በየጊዜው ተደጋጋሚ የሆኑ ማሳሰቢያዎች ማግኘት ያስፈልገዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘እነዚህን ነገሮች ምንም ቢያውቁ በእነርሱም ዘንድ ባለ እውነት ምንም ቢጸኑ፣ ስለ እነዚህ ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አላለም’ ነበር። (2 ጴጥሮስ 1:12) በተጨማሪም ኢየሱስ “ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል” በማለት አብራርቷል። (ማቴዎስ 13:52) ስለዚህ በስብሰባችን ላይ የምናውቃቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች ወይም ‘አሮጌ መዝገቦች’ ቢቀርቡም እኛን የሚያስደስቱ አንዳንድ ‘አዳዲስ መዝገቦችም’ ምን ጊዜም አይጠፉም።
ከስብሰባዎች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ከቆረጥን በውጤቱ እውነተኛ መንፈሳዊ ማበረታቻ ሊያስገኝልን ይችላል። “ለሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ምግብ ንቁ የሆኑ [መንፈስ ለማግኘት የሚለምኑ] ደስተኞች ናቸው” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3 አዓት የግርጌ ማስታወሻ) በስብሰባዎች ላይ ለሚቀርበው ጠቃሚ መንፈሳዊ ምግብ እንዲህ ያለ አመለካከት መያዝ መሰልቸትን ያስወግዳል።—ማቴዎስ 24:45–47
ጥሩ ምሳሌ የማይሆን ሰው ቅር አሰኝቶሃልን?
በጉባኤህ ውስጥ ያለ አንድ ሰው በሚያሳየው ጠባይ ተበሳጭተህ ታውቃለህን? ‘አንድ ወንድም በእንዲህ ዓይነት ምግባር እየተመላለሰ እንዴት ጥሩ አቋም ሊኖረው ይችላል?’ በማለት ትገረም ይሆናል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ እንቅፋት ሊሆንብንና ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ሊኖረን የሚችለው አስደሳች ጓደኝነት ጥቅሙ እንዳይታየን ሊያደርገን ይችላል።—መዝሙር 133:1
በቆላስይስ የነበሩ አንዳንድ የጉባኤ አባሎች ተመሳሳይ የሆነ ችግር ሳይኖርባቸው አይቀርም። ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ” በማለት አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ቆላስይስ 3:13) በቆላስይስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የሚያሳዩት መጥፎ ባሕርይ ሌሎችን ሊያስከፋቸው እንደሚችል ጳውሎስ ተገንዝቧል። እንደዚሁም ከወንድሞቻችን ወይም ከእህቶቻችን መካከል አንዱ ወይም አንዷ አልፎ አልፎ አንዳንድ ክርስቲያናዊ ባሕርያት ቢጎድሏቸው ከልክ በላይ መገረም አይገባንም። ኢየሱስ ከባድ አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ጥሩ ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 5:23, 24፤ 18:15–17) ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የእምነት ወንድሞቻችን የሚሠሯቸውን ስህተቶች ችለን ማለፍና ይቅር ማለት እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 4:8) እርግጥ ነው እንዲህ ያለው አቋም ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ይጠቅማል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
ምሳሌ 19:11 “ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቁጣ ያዘገየዋል፣ ለበደለኛውም ይቅር ይል ዘንድ ክብር ይሆንለታል” በማለት ይናገራል። ቁጣንና ቅሬታን አምቆ ከመያዝ ይልቅ ይቅር ማለት ምንኛ የተሻለ ነው! በአፍቃሪ ባሕርዩ የታወቀ አንድ ሳልቫዶር የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ “አንድ ወንድም ሲያጣጥለኝ ወይም በክፉ ቃል ሲናገረኝ ‘ወንድሜን እንዴት ልረዳው እችላለሁ? ከእርሱ ጋር የነበረኝ ውድ ዝምድና እንዳይበላሽ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። የተሳሳተ ነገር መናገር እንዴት ቀላል እንደሆነ አሳምሬ አውቃለሁ። አንድ ሰው በግዴለሽነት ሲናገር ዓይነተኛው መፍትሔ ያ ሰው የተናገረውን ወደ ጎን መተውና እንደገና አዲስ ግንኙነት መጀመር ነው። ይሁን እንጂ ይህ የማይቻል ከሆነ የሚቀጥለውን ከሁሉ የተሻለ መንገድ በመከተል የተናገረውን ነገር ችላ ብዬ አልፋለሁ። ይህ ነገር የወንድሜ እውነተኛ ስብዕና ነጸብራቅ ሳይሆን ፍጹም ባልሆነው ሥጋው ምክንያት የተከሰተ ነገር እንደሆነ አድርጌ እመለከተዋለሁ።”
እንዲህ ብሎ መናገሩማ ቀላል ነው፤ ማድረጉ ነው እንጂ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ አብዛኛው የሚመካው በአስተሳሰባችን ላይ ነው። “ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ . . . እነዚህን አስቡ” በማለት ጳውሎስ ምክር ይሰጣል። (ፊልጵስዩስ 4:8) “ፍቅር ያለበት” የሚለው ቃል በቃል ሲተረጎም “የሚወደድ” ማለት ነው። ይሖዋ ቅሬታ በሚፈጥሩ ሳይሆን በሚወደዱ ባሕርያት ላይ በማተኮር ሰዎች ያላቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንድንመለከት ይፈልግብናል። በዚህ በኩል ይሖዋ ራሱ ትልቅ ምሳሌ ይሆነናል። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል?” በማለት ያስታውሰናል።—መዝሙር 103:12፤ 130:3
እውነት ነው አንዳንድ ጊዜ የአንድ ክርስቲያን ጠባይ ሊያሳዝነን ቢችልም አብዛኞቹ መሰል አማኞች ግን በክርስቲያናዊ አኗኗራቸው ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ይህን የምናስታውስ ከሆነ እንደ ዳዊት ‘ይሖዋን በአፋችን እጅግ በማመስገንና በብዙዎችም መካከል እርሱን በማወደስ’ ደስታ እናገኛለን።—መዝሙር 109:30
የይሖዋ ምሥክር መሆን አስቸጋሪ ሆኖ ይታይሃልን?
በሌላ የአእምሮ ውስጥ ጋሬጣ ምክንያት አንዳንዶች ገና አሁንም ይሖዋን ማወደስ አለመጀመራቸው የሚያሳዝን ነው። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ አንዳንድ ወንዶች ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡና አልፎ ተርፎም ሚስቶቻቸው በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንዲሳተፉ ድጋፋቸውን የሚሰጡ ናቸው። የወዳጅነት መንፈስ የሚያሳዩና በጉባኤ ስብሰባ የሚገኙ ቢሆንም ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ አገልጋዮች ለመሆን ግን አይቃጡም። ወደ ኋላ የሚጎትታቸው ምንድን ነው?
አንዱ ምክንያት ሚስቶቻቸው በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዳቸውን ስለሚመለከቱና የይሖዋ ምሥክር መሆን ብዙ ነገር የሚጠይቅባቸው ስለሚመስላቸው ሊሆን ይችላል። ወይም ከቤት ወደ ቤት ሄዶ መስበክ በጣም የሚያስፈራ ሆኖ ስለሚታያቸው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው አመለካከታቸው ሊገኙ የሚችሉት በረከቶች ከክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቹ በጣም ያነሱ ሆነው እንዲታዩአቸው ያደርጋል። ይህ የአእምሮ ውስጥ ጋሬጣ የሆነባቸው ለምንድን ነው? አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እውነትን የተማሩትና በሥራ ላይ ያዋሉት ቀስ በቀስ ነው። የማያምኑ ባሎች ግን እውነትን ለመቀበል የሚገፋፋቸውን ስሜት ከመገንባታቸው በፊት ሁሉንም ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች ጠንቅቀው ያውቃሉ።
በዚህ ሁኔታ ሥር የነበረው ማንዌል እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ለአሥር ዓመታት ያህል ወደ ትልልቅ ስብሰባዎችና ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ከባለቤቴ ጋር ሄጃለሁ። ሐቁን ለመናገር በዓለም ካሉ ሰዎች ይልቅ የምሥክሮቹን ጓደኝነት እመርጣለሁ። በምችለው ሁሉ እነርሱን መርዳት ያስደስተኝ ነበር። በመካከላቸው በነበረው ፍቅር በጣም ተማርኬ ነበር። ይሁን እንጂ ከቤት ወደ ቤት የመሄዱ ሐሳብ ትልቅ እንቅፋት ሆኖብኝ ነበር። በተጨማሪም የሥራ ባልደረቦቼ ይሳለቁብኝ ይሆናል ብዬ ፈራሁ።
“ባለቤቴ በጣም በትዕግሥት ትይዘኝ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና በጭራሽ ተጭናኝ አታውቅም። እርሷም ሆነች ልጆቹ ይበልጥ ‘የሰበኩልኝ’ ጥሩ ምሳሌ በመሆን ነበር። በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ የነበረው ሆሴዕ ቀርቦ አነጋገረኝ። በጨረሻም ከልቤ ጥናት እንድጀምር ያደረገኝ የእርሱ ማበረታቻ ይመስለኛል። ከተጠመቅሁ በኋላ ከሁሉ የበለጠ እንቅፋት የሆነብኝ የራሴ አስተሳሰብ እንደነበር ተገነዘብኩ። ይሖዋን ለማገልገል አንድ ጊዜ ከቆረጥሁኝ በኋላ ፍርሃቴን ለማሸነፍ የእርሱን እርዳታ አግኝቻለሁ።”
ባሎች እንደ ማንዌል የአእምሮ ውስጥ ጋሬጣ እንዲያሸንፉ ሚስቶችና ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አድናቆትንና የአምላክን ፈቃድ የማድረግ ምኞትን ሊገነባ ይችላል። እርግጥ ነው የተሟላ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት ማግኘት እምነት ለማዳበርና በወደፊቱ ተስፋ ላይ ትምክህት ለመጣል መሠረት ነው።—ሮሜ 15:13
እንደዚህ ያሉትን ባሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ማን ሊያበረታታቸው ይችላል? አብዛኛውን ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ተሞክሮ ያለው አንድ ወንድም ከእነርሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረቱ ውሳኔ እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይችላል። ምናልባት አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም ሌላ ተሞክሮ ያለው ወንድም ባልዬውን ሊተዋወቀው ይችላል። ጥሩ ግንኙነት ከተመሠረተ በኋላ የሚያስፈልገው ነገር ከሚያስጠናው ሰው ጋር ማገናኘት ብቻ ነው። (1 ቆሮንቶስ 9:19–23) እስከዚያ ድረስ ግን ልባም ክርስቲያን ሚስት ባሏን መጫን ጥሩ ውጤት እንደማይኖረው በመገንዘብ ለማያምነው ባሏ ቀለል ያሉ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ልታካፍለው ትችላለች።—ምሳሌ 19:14
ማንዌል በተሞክሮ እንደተገነዘበው አንድ ሰው መንፈሳዊ ጥንካሬ ካገኘ በኋላ ተራራ የሚያክሉት እንቅፋቶች ትንሽ የአፈር ቁልል ያህል ይሆኑለታል። ይሖዋ እርሱን የማገልገል ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ያበረታታቸዋል። (ኢሳይያስ 40:29–31) ከአምላክ በሚገኝ ጥንካሬና ከጎለመሱ ክርስቲያኖች በሚገኝ እርዳታ በማያምኑ ባሎች አእምሮ ውስጥ ያለው እንቅፋት ፈጽሞ ሊወገድ ይችላል። ከዚያም በሙሉ ልብ የሚከናወነው አገልግሎት አስደሳች ሲሆን ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው ሥራም ሆነ የሥራ ባልደረቦች ተስፋ የሚያስቆርጡ አይሆኑም።—ኢሳይያስ 51:12፤ ሮሜ 10:10
ሳያቋርጡ እድገት ማድረግ
እስከ አሁን እንዳየነው ሦስቱንም ዓይነት የአእምሮ ውስጥ ጋሬጣዎችን ማሸነፍ ይቻላል። አንድ አውሮፕላን ምድርን ለቅቆ በሚያኮበኩብበት ጊዜ ከሞተሩ የሚያገኘው ከፍተኛ ኃይልና የአብራሪው ያልተከፋፈለ ትኩረት ያስፈልገዋል። ምድርን ለመልቀቅ በሚንደረደርበት ጊዜ ሞተሩ በሌላ በማንኛውም በረራ ጊዜ ከሚያስፈልገው የበለጠ ነዳጅ ይወስዳል። በተመሳሳይም ከአፍራሽ አስተሳሰቦችና ስሜቶች ነፃ ለመሆን ከፍተኛ ጥረትና ትኩረት ያስፈልጋል። መጀመር ከሁሉ የበለጠ አስቸጋሪ ወቅት ሊሆን ይችላል፤ አንዴ ኃይል ከተገኘ ግን እድገት ለማድረግ እየቀለለ ይሄዳል።—ከ2 ጴጥሮስ 1:10 ጋር አወ ዳድር።
ቀጣይ እድገት የሚገኘው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻዎችን በትክክል በመከተል ነው። (መዝሙር 119:60) ጉባኤው ሊረዳን እንደሚፈልግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ገላትያ 6:2) ከሁሉም የሚበልጠው ግን የይሖዋ አምላክ ድጋፍ ነው። ዳዊት እንዳለው “ሸክማችንን በየቀኑ የሚያቀልልንና እኛን የሚያድን እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይሁን።” (መዝሙር 68:19) በጸሎት አማካኝነት ሸክማችንን ስናቃልል የተጫነን ክብደት ይቀንስ ልናል።
አንዳንድ ጊዜ የአየሩ ጠባይ ዝናባማና ደመናማ ሲሆን አንድ አውሮፕላን ደመናውን አቋርጦ ደማቅ የፀሐይ ብርሃን ወደፈነጠቀበት ሰማይ ይበራል። እኛም አፍራሽ አስተሳሰቦችን ወደ ኋላ ጥለን መሄድ እንችላለን። በመለኮታዊ እርዳታ አማካኝነት ምሳሌያዊ የደመና ክምሮችን አልፈን ብሩህና ደስተኛ ወደሆኑት ምድር አቀፍ የይሖዋ አምላኪዎች ቤተሰብ ከባቢ አየር መግባት እንችላለን።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በይሖዋ እርዳት የአእምሮ ውስጥ ጋሬጣዎችን ማስወገድ እንችላለን