ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
አእምሮዬ በአንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
“ከስብሰባዎች የሚገባኝን ያህል ጥቅም ሳላገኝ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። አእምሮዬ ሽርሽር ይሄዳል።”—ማቲው
በአንድ ትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለህ ወይም ደግሞ በአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ ድንገት ከሐሳብህ ብንን ስትል ስለ ምን ነገር እየተነገረ እንዳለ ግራ ተጋብተህ ታውቃለህ? አእምሮህ አንዳንድ ጊዜ ሽርሽር የሚሄድ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ያለብህ አንተ ብቻ አይደለህም። ቀደም ሲል በወጣው ርዕስ ላይ እንደተጠቆመው አብዛኞቹ ወጣቶች አንድን ነገር ረዘም ላለ ጊዜ በትኩረት የመከታተል ችግር አለባቸው።a ይሁን እንጂ ትንሽ ጥረት በማድረግና በተወሰነ መጠን አመለካከትን በማስተካከል በትኩረት የመከታተል ችሎታህን ማጎልበት ትችላለህ።
ፍላጎቱ ይኑርህ
ጥሩ ሥልጠና ስላገኘ ስለ አንድ አትሌት አስብ። “የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል” ሲል ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሯል። አንድ አትሌት ለትንሽ ጊዜ እንኳ ሐሳቡ እንዲከፋፈል ከፈቀደ ለሽንፈት ሊዳረግ ይችላል። ማሸነፍ እንዲችል ለሕዝቡ ጩኸት ትኩረት ባለመስጠት፣ የሚሰማውን ሕመምና ድካም ችላ በማለትና የመሸነፍን ሐሳብ ከአእምሮው በማውጣት እንዴት ሐሳቡን ማሰባሰብ እንደሚችል መማር አለበት። ይሁን እንጂ አትሌቶች እንዲህ ዓይነቱን ለየት ያለ ጥረት እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ይህን የሚያደርጉት “የሚጠፋውን አክሊል” ማለትም ለአሸናፊዎች የሚሰጠውን ዋንጫና ሽልማት ለማግኘት ሲሉ ነው።—1 ቆሮንቶስ 9:25
በተመሳሳይ አንተም በአንድ ነገር ላይ ትኩረት እንድታደርግ ከበስተጀርባ የሚገፋፋህ ነገር ሊኖር ይገባል! በዊልያም ኤች አርምስትሮንግ የተዘጋጀው ስተዲ ኢዝ ሀርድ ወርክ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ፍላጎቱ ሊኖረው የሚገባው ተማሪው ራሱ ነው። ማንም ሰው ይህን ሊያደርግልህ አይችልም፤ እንዲሁም አንተ እስካልፈለግህ ድረስ ማንም ሰው ፍላጎትህን ሊያሳድግልህ አይችልም።” በዙሪያህ ስላለው ዓለም ጥሩ ግንዛቤ እንድታገኝ የሚረዳህ ዋነኛው ነገር እውቀት ነው። ብዙ ባወቅኽ መጠን ብዙ ነገር ትማራለህ። ምሳሌ 14:6 “ለአስተዋይ ግን እውቀትን ማግኘት አያስቸግረውም” ይላል። በትምህርት ቤት የተማርካቸውን ነገሮች ሁሉ አታስታውስ ይሆናል፤ ሆኖም ቢያንስ ቢያንስ የምትማረው ትምህርት የማሰብ ችሎታህን እንድታሳድግና እንድታዳብር ይረዳሃል። (ከምሳሌ 1:4 ጋር አወዳድር።) አእምሮህን ገስጸህ ሐሳብህን ማሰባሰብ መቻልህ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ይጠቅምሃል።
የተሰላቹና የሚያሰለቹ አስተማሪዎች
አንዳንድ ወጣቶች አስተማሪዎቻቸውም እንኳ ሳይቀር የተሰላቹ እንደሆኑ በመግለጽ ቅሬታቸውን ያሰማሉ። ጄሲ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “መምህራን ፊታችሁ ቆመው የሆነ ነገር ሲናገሩ ይቆዩና የቤት ሥራ ሰጥተዋችሁ ይሄዳሉ። ግዴለሾች የሆኑ ይመስለኛል። መምህራኑ ራሳቸው ለትምህርቱ ክብደት የሚሰጡት አይመስሉም፤ ስለዚህ እኛም በትኩረት መከታተሉ ይህን ያህል አስፈላጊ ሆኖ አይታየንም።”
ታዲያ በዚህ ጊዜ በትኩረት መከታተሉ ጊዜ ማባከን እንደሆነ አድርገህ ማሰብ ይኖርብሃል? እንደዚያ ማለት አይቻልም። ብዙዎቹ አስተማሪዎች ሥራው ራሱ አሰልቺ ሊሆንባቸው ይችላል። ኮለን የተባለ ወጣት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “አስተማሪዎቹን በጥሞና የሚያዳምጥ የለም፤ ስለዚህ አስተማሪዎቹ መማር የሚፈልግ እንደሌለ ሆኖ ይሰማቸዋል። በመሆኑም በግለትና በስሜት ለማስተማር አይነሳሱም።”
ብታምንም ባታምንም ይህን ሁኔታ መለወጥ ትችላለህ። እንዴት? በጥሞና በማዳመጥ። አንድ የተሰላቸ አስተማሪ ፍላጎት ያለው አንድ ተማሪ ማግኘቱ ብቻ ለሥራው ያለውን ፍቅር ሊያድስለት ይችል ይሆናል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ አስተማሪዎች የተማሪዎቻቸውን ስሜት ማርኮ የመያዝ ችሎታ ላይኖራቸው ይችላል። ሆኖም በሌላ ሐሳብ ጭልጥ ብለህ ከመወሰድህ በፊት ‘ይህ ሰው የሚያስተምረውን ነገር በሚገባ ያውቀዋል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እንደዚያ ከሆነ አንድ ነገር ከእሱ ለመማር አእምሮህን አዘጋጅ። በጥሞና አዳምጥ፤ ሐሳብህን አሰባስበህ ተከታተል! በክፍል ውስጥ በሚደረጉ ውይይቶች ተሳተፍ። በቀጥታ ነጥቡን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ጠይቅ። ሀው ቱ ስተዲ ኢን ሃይ ስኩል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ብዙ ተማሪዎች አስተማሪው ሰሌዳው ላይ የሚያሰፍራቸውን ወይም ደግሞ በአጽንኦት የሚገልጻቸውን ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ ቃላት፣ ካርታዎች፣ ፍቺዎችና ዋና ዋና ሐሳቦች በማስታወሻ መያዙ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።”
“ከወትሮው የበለጠ ትኩረት” መስጠት
ይሁን እንጂ በክርስቲያን ስብሰባዎች የሚሰጠውን ትምህርት ማዳመጥን በተመለከተ የሚገኘው ጥቅምም ሆነ ሊከተል የሚችለው ኪሳራ በጣም ከፍተኛ ነው። ጄሲ እንዲህ ሲል ሐቁን በግልጽ ተናግሯል:- “አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች ስብሰባዎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ስለማይገነዘቡ እንደ ስብሰባ ላሉ ነገሮች ተገቢውን ትኩረት አይሰጡም።” በዕብራውያን 2:1 (NW) ላይ “ምናልባት እንዳንወሰድ ለሰማናቸው ነገሮች ከወትሮው የበለጠ ትኩረት” እንድንሰጥ ታዝዘናል። በአንድ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ከተገኘህ በኋላ ከእያንዳንዱ ክፍል የሆነ ነገር ማስታወስ ትችላለህን? ወይስ አንዳንድ ጊዜ ክፍሉን ማን እንዳቀረበ እንኳን ማስታወስ ይሳንሃል?
አሁንም ቢሆን ለዚህ ወሳኙ የምትማረውን ነገር ጠቃሚነት ማጤንህ ነው። ሕይወትህን በቀጥታ የሚመለከት ጉዳይ ነው! (ዮሐንስ 17:3) ሌላም ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ አለ:- ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስትማር እንደ አምላክ ማሰብን እየተማርክ ነው ማለት ነው! (ኢሳይያስ 55:8, 9) የተማርከውን ነገር በሥራ ላይ ስታውል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አዲስ ሰው’ ብሎ የሚጠራውን እየለበስክ ነው ማለት ነው። (ቆላስይስ 3:9, 10) በሌላ በኩል ደግሞ ትኩረት የማትሰጥ ከሆነ በሕይወትህ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን ማሻሻያዎች ሳታደርግ ልትቀር ትችላለህ፤ የራስህን መንፈሳዊ ዕድገት ታጫጫለህ። ይሖዋ ሐሳባችንን የሚሰርቁ ነገሮች እንዳሉ ያውቃል። በመሆኑም እንዲህ ሲል ተማጽኗል:- “አድምጡኝ . . . ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች።”—ኢሳይያስ 55:2, 3
ከስብሰባዎች የተሻለ ጥቅም ማግኘት የሚቻልበት መንገድ
እርግጥ ነው፣ በስብሰባዎች ላይ በጥሞና ማዳመጥ መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሐሳባችንን አሰባስበን ለማዳመጥ ይበልጥ ጥረት ባደረግን መጠን አእምሯችን የዚያኑ ያህል እየተለማመደው እንደሚሄድ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ማቲው በስብሰባዎች ላይ ሐሳብን አሰባስቦ በማዳመጥ ረገድ የነበረበትን ችግር ማሸነፍ ችሏል። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በትኩረት ማዳመጥ እንድችል ራሴን መገሰጽ እንዳለብኝ ተረዳሁ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እየተሻሻላችሁ ትሄዱና ረዘም ላለ ጊዜ በትኩረት የማዳመጥ ልማድ ታዳብራላችሁ።” በተጨማሪም ማቲው ስብሰባዎች አስደሳች እንዲሆኑለት በእጅጉ የረዳውን ብቸኛ ነገር ጠቅሷል። “አስቀድሜ እዘጋጃለሁ” ሲል ተናግሯል። በተመሳሳይም ሸሪስ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “ተዘጋጅቼ ስሄድ እኔም የስብሰባው አካል እንደሆንኩ ይበልጥ ይሰማኛል። ንግግሮቹ ትኩረቴን ይበልጥ የሚስቡት ከመሆናቸውም በላይ የበለጠ ትርጉም ያላቸው ይሆኑልኛል።”
ሐሳብን የሚከፋፍሉ ነገሮችንም ማስወገዱ በጣም አስፈላጊ ነው። እርግጥ ነው፣ በአእምሮህ ውስጥ እየተመላለሱ የሚያስጨንቁህ በቂ ምክንያቶች ይኖሩህ ይሆናል፤ በመጪው ሳምንት ፈተና ይኖርህ ይሆናል፤ ከሌላ ሰው ጋር በተፈጠረ የባሕርይ አለመጣጣም ተጨንቀህ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ልትሸፍነው የሚገባ ወጪ እያሳሰበህ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።” (ማቴዎስ 6:27, 34) ትኩረትህን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ማሳረፍህ ችግሮቹን ባያስወግዳቸውም እንኳ መንፈሳዊነትህ እንዲታደስ ስለሚረዳህ ችግሮቹን በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ትችላለህ።—ከ2 ቆሮንቶስ 4:16 ጋር አወዳድር።
በተጨማሪም በጥሞና ማዳመጥ ሐሳብህ ወደ ሌላ እንዳይሄድ ሊረዳህ ይችላል። ማቲው “ተናጋሪው ምን ምን ነጥቦችን ሊጠቅስ እንደሚችል አስቀድሜ ለማሰብ እሞክርና ንግግሩን በሚሰጥበት ጊዜ በምን መልኩ ነጥቦቹን እንደሚጠቅስ እከታተላለሁ” ሲል ተናግሯል። እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘እየተብራሩ ያሉት ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ናቸው? እየተሰጠ ያለውን ትምህርት እንዴት ልጠቀምበት እችላለሁ?’ ተናጋሪው ቀጥሎ ምን ነጥብ ሊጠቅስ እንደሚችል ለማሰብ መሞከርህም ሐሳብህ ወደ ሌላ እንዳይሄድ ሊረዳህ ይችላል። አንድ በአንድ እያያያዘ የሚጠቅሳቸውን ነጥቦች ለመከታተል ሞክር። የሚያቀርባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች ልብ በል። የዘረዘራቸውን ዋና ዋና ነጥቦች በማሰላሰል ጠቅለል ለማድረግ ሞክር። ግልጽ የሆነ አጭር ማስታወሻ ያዝ። የአድማጮችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ክፍል ሲኖር ተሳትፎ አድርግ! እንዲህ ማድረግህ አእምሮህ እንዲያዝና ሐሳብህ ወደ ሌላ እንዳይሄድ ሊረዳህ ይችላል።
አንድ ተናጋሪ ግለት የሚጎድለው ወይም ንግግሩን በማይስብ መንገድ የሚያቀርብ ከሆነ በትኩረት ማዳመጥ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ስለ ሐዋርያው ጳውሎስ የንግግር ችሎታ የነበራቸውን አመለካከት በተመለከተ ምን ብለው እንደነበር አስታውስ:- “ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፣ ንግግሩም የተናቀ ነው።” (2 ቆሮንቶስ 10:10) ሆኖም ጳውሎስ “በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፣ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም” በማለት ለተሰነዘረበት ትችት ምላሽ ሰጥቷል። (2 ቆሮንቶስ 11:6) አዎን፣ አድማጮቹ ከጳውሎስ የንግግር ችሎታ ባሻገር በመመልከት በሚናገረው ነገር ላይ ትኩረት አድርገው ቢሆን ኖሮ “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” መማር በቻሉ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 2:10) በተመሳሳይም ሐሳብህን አሰባስበህ በጥሞና የምታዳምጥ ከሆነ “ከማይስብ” ተናጋሪም እንኳ ትምህርት መቅሰም ትችላለህ። ማን ያውቃል? ትንሽ ለየት ያለ ማብራሪያ ሊሰጥ ወይም ደግሞ አንድን ጥቅስ አንተ ከዚህ ቀደም አስበኸው በማታውቀው መንገድ ሊጠቀምበት ይችላል።
በሉቃስ 8:18 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ሁኔታውን በጥሩ ሁኔታ ጠቅለል አድርገው ይገልጹታል:- “እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ።” እርግጥ ነው፣ ሐሳብን አሰባስቦ በትኩረት ማዳመጥ ጥረትና ልምድ ይጠይቃል። ሆኖም ውሎ አድሮ በረከቱን ማጨድህ አይቀርም። ሐሳብን አሰባስቦ የማዳመጥ ልማድ ማዳበር የተሻለ ውጤት ከሁሉም በላይ ደግሞ መንፈሳዊ እድገት ያስገኛል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በጥቅምት 1998 የንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ሐሳቤን ማሰባሰብ የማልችለው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለምትሰማው ነገር ፍላጎት ማዳበር በትኩረት ለማዳመጥ የሚያስችል ቁልፍ ነው