የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 5/15 ገጽ 4-6
  • ሀብት ደስተኛ ሊያደርግህ ይችላልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሀብት ደስተኛ ሊያደርግህ ይችላልን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ገንዘብን መውደድ ደስታ አያስገኝም
  • ባለን ነገር መርካት
  • ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ
  • ባለን መርካትና ለጋስ መሆን
    ንቁ!—2018
  • ለገንዘብ ሊኖረን የሚገባው ተገቢ አመለካከት ምንድን ነው?
    ንቁ!—2007
  • ሀብታምና ጠቢብ የነበረ ንጉሥ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ እውነተኛ ብልጽግና
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 5/15 ገጽ 4-6

ሀብት ደስተኛ ሊያደርግህ ይችላልን?

ንጉሥ ሰሎሞን ገንዘብ ያለውን ዋጋ ያውቅ ነበር። “እንጀራን ለሳቅ የወይን ጠጅንም ለሕይወት ደስታ ያደርጉታል፣ ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል” ሲል ጽፏል። (መክብብ 10:​19) ከጓደኞችህ ጋር መብላትና መጠጣት ሊያስደስትህ ይችላል። ይሁን እንጂ እንጀራ ወይም ወይን ለመግዛት ገንዘብ ያስፈልግሃል። ገንዘብ ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚያስችል ነገር በመሆኑ “ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል።”

ሰሎሞን እጅግ ባለጠጋ ሰው የነበረ ቢሆንም ሀብት ገደብ እንዳለው ያውቅ ነበር። በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ አኗኗር ለደስታ በር ከፋች እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። “ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም” ሲል ጽፏል።​—⁠መክብብ 5:​10

አንድ ባለጠጋ ሰው ተጨማሪ ሀብት አገኘ እንበል። ሰሎሞን “ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ” ብሏል። (መክብብ 5:​11) የአንድ ሰው “ሀብት” ወይም ያሉት ነገሮች ሲጨምሩ እነዚህን ነገሮች የሚቆጣጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ያስፈልጋሉ። የጥገና ሠራተኞች፣ ተወ​ካዮች፣ አገልጋዮች፣ የጥበቃ ሠራተኞችና ሌሎችም ለሚሰጡት አገልግሎት ክፍያ ይጠይቃሉ። ይህ ደግሞ ከበፊቱ የበለጠ ተጨማሪ ገንዘብ ያስወጣል።

እንዲህ ያለው ሁኔታ በአንድ ሰው ደስታ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያሳድራል። በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ዜኖፎን፣ ድሃ የነበረ አንድ ሰው ሀብታም ከሆነ በኋላ የተናገረውን ጽፏል:-

“ብዙ ሀብት ባገኘሁ ቁጥር ይበልጥ ደስተኛ የምሆን . . . ይመስላችኋል? ዛሬ የምበላውና፣ የምጠጣው ነገርም ሆነ የምተኛው እንቅልፍ በድህነቴ ወቅት በነበረኝ ደስታ ላይ ቅንጣት ታክል እንኳ እንዳልጨመረልኝ አላወቃችሁም። ብዙ ሀብት በማግኘቴ ያተረፍኩት ነገር ቢኖር ብዙ ሰዎችን መንከባከብን፣ ለሌሎች ብዙ መስጠትንና በፊት ከነበሩኝ የበለጡ ብዙ ነገሮችን መከታተሉ የሚያስከትለውን ችግር ብቻ ነው። በአሁኑ ጊዜ በቤቴ ውስጥ የሚኖሩት ብዙ ሰዎች የሚመገቡትን፣ የሚጠጡትንና የሚለብሱትን ማቅረብ ያለብኝ እኔ ነኝ። አንዳንዶቹ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል፤ አንዱ መጥቶ በጎች በቀበሮዎች ተበሉ ወይም በሬዎች ገደል ገብተው ሞቱ ወይም በከብቶች መሃል በሽታ ተነሥቷል ይለኛል። ስለዚህ ጥቂት ነገር ከነበረኝ ጊዜ ይልቅ አሁን ብዙ ስላለኝ ችግሩም የዚያኑ ያህል የበረከተብኝ . . . ይመስለኛል።”

ሰዎች ተጨማሪ ሀብት ለማግኘት የሚጥሩበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ “የባለጠግነት መታለል” ብሎ በጠራው ነገር በመታለላቸው ነው። (ማቴዎስ 13:​22) ከዚህ ወገባቸውን ታጥቀው ከሚያሳድዱት ሀብት የጠበቁትን እርካታ ወይም ደስታ ሊያገኙ ስለማይችሉ ይታለላሉ። አነስተኛ መጠን ያለው ሀብት ማከናወን የማይችለውን ነገር ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ሊያደርገው ይችላል ብለው ያስባሉ። ስለዚህ የበለጠ ሀብት ለማካበት ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ።

ገንዘብን መውደድ ደስታ አያስገኝም

አንድ ሀብታም ሰው ስለ ንብረቶቹ የሚጨነቅ ከሆነ ሰላማዊ እንቅልፍ አግኝቶ ሊያድር አይችልም። ሰሎሞን “እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ [“ሀብቱ፣” የ1980 ትርጉም] ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል” ሲል ጽፏል።​—⁠መክብብ 5:​12

አንድ ሰው ያለኝን ሀብት አጣለሁ ብሎ ከልክ በላይ መጨነቅ ከጀመረ በእንቅልፍ ማጣት ብቻ አያበቃም። ሰሎሞን ስለ አንድ ቆንቋና ሰው ሲናገር “ዘመኑን ሁሉ በጨለማ በኀዘን በብስጭት በደዌና በቁጣ ነው” ብሏል። (መክብብ 5:​17) በሀብቱ ከመደሰት ይልቅ ለሚበላው ምግብ እንኳ ያወጣው ገንዘብ ይቆጨው ይመስል “በኀዘን” ይመገባል። እንዲህ ያለው የተዛባ አስተሳሰብ የጤና መታወክ እንዲከሰት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ይህ የጤና መታወክ ደግሞ በተራው የበለጠ ሀብት እንዳያጋብስ እንቅፋት ስለሚሆንበት የዚያ ስግብግብ ሰው ጭንቀት ይጨምራል።

ይህ ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን ሳያስታውስህ አይቀርም:- “ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ . . . በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:​9, 10) ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ያታልላሉ፣ ይዋሻሉ፣ ይሠርቃሉ፣ ራሳቸውን ለዝሙት አዳሪነት ይሸጣሉ እንዲሁም የሰው ሕይወት እንኳን ሳይቀር ያጠፋሉ። አንድ ሰው ሀብት ለማግኘትና ይህንኑ ጠብቆ ለማቆየት የሚያደርገው ጥረት ውጤቱ በስሜታዊ፣ በአካላዊና በመንፈሳዊ ስቃይ መወጋት ነው። ታዲያ ይህ ወደ ደስታ የሚመራ ጎዳና ይመስላል? ሊሆን አይችልም!

ባለን ነገር መርካት

ለሀብት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝን በተመለከተ ሰሎሞን ብዙ ነገር ተናግሯል። “ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል፤ ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለውን ምንም አያገኝም። እነሆ፣ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና” ሲል ጽፏል።​—⁠መክብብ 5:​15, 18

ደስተኛ መሆናችን የተመካው በሕይወት ዘመናችን ተጠቅመን የማንጨርሰውን የሀብት ቁልል በማግበስበስ እንዳልሆነ እነዚህ ቃላት ያሳያሉ። ከዚህ ይልቅ ጠንክረን በመሥራት ባገኘነው ውጤት መርካትና መደሰት ይበልጥ የተሻለ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይም ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ ገልጿል:- “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​7, 8፤ ከሉቃስ 12:​16-21 ጋር አወዳድር።

ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ

ሰሎሞን ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብትም ሆነ አምላካዊ ጥበብ ነበረው። ይሁንና ደስታን ያያያዘው ከጥበብ እንጂ ከገንዘብ ጋር አይደለም። እንዲህ ብሏል:- “ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ከቀይ ዕንቁም ትከብራለች፣ የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም። በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፣ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር። መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፣ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርስዋ ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናት፣ የተመረኮዘባትም ሁሉ ምስጉን ነው።”​—⁠ምሳሌ 3:​13-18

ጥበብ ከቁሳዊ ንብረት የሚበልጠው ለምንድን ነው? ሰሎሞን “የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፤ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው” ሲል ጽፏል። (መክብብ 7:​12) ገንዘብ ባለቤቱ የሚያስፈልገውን ነገር እንዲገዛ በማስቻል በተወሰነ መጠን ጥላ ሆኖ ሲያገለግል ጥበብ ግን አንድ ሰው ሕይወቱን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነገር እንዳያደርግ ሊጠብቀው ይችላል። እውነተኛ ጥበብ ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት በማሳደር ላይ የተመሠረተ ስለሆነ አንድ ሰው ያለጊዜው እንዳይቀጭ ከመጠበቅም በተጨማሪ የዘላለም ሕይወት ወደ ማግኘት ይመራዋል።

አምላካዊ ጥበብ ወደ ደስታ የሚመራው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እውነተኛ ደስታ ሊገኝ የሚችለው ከይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። እውነተኛ ደስታ ሊገኝ የሚችለው የሁሉ የበላይ የሆነውን አምላክ በመታዘዝ ብቻ መሆኑን ከተሞክሮ መገንዘብ ተችሏል። ዘላቂ ደስታ ማግኘት የሚቻለው በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ይዞ በመመላለስ ነው። (ማቴዎስ 5:​3-10) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ያገኘነውን እውቀት በተግባር በመተርጎም ‘ላይኛይቱን ጥበብ’ እናዳብራለን። (ያዕቆብ 3:​17) ሀብት ፈጽሞ ሊያስገኝልን የማይችለውን ደስታ ይሰጠናል።

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሥ ሰሎሞን አንድን ሰው ደስተኛ የሚያደርገው ነገር ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር። አንተስ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ