ኤውንቄና ሎይድ በአርዓያነት የሚጠቀሱ አስተማሪዎች
የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ለልጆቻችን ውጤታማ የሆነ ሃይማኖታዊ ትምህርት መስጠት ከባድ ኃላፊነት መሆኑን እንገነዘባለን። አመቺ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እያሉም ይህን ኃላፊነት መወጣት የተለያዩ እንቅፋቶችና ችግሮች ሊገጥሙት ይችላል። በተለይ ደግሞ አንድ ክርስቲያን ወላጅ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖር ከሆነ ሁኔታው ይበልጥ ተፈታታኝ ይሆናል። እንዲህ ያለው ሁኔታ አዲስ አይደለም። ቅዱሳን ጽሑፎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ትኖር ስለነበር አንዲት ወላጅ ይነግሩናል።
የኤውንቄ ቤተሰብ በትንሿ እስያ ማዕከላዊ ደቡብ ባለችው በሊቃኦንያ ከተማ በልስጥራ ይኖር ነበር። ልስጥራ እምብዛም ጉልህ ሥፍራ ያልነበራት የገጠር ከተማ ነበረች። ይህች የሮማ ቅኝ ግዛት ዩልያ ፌሊክስ ጌሚና ሉስትራ ተብላ የምትጠራ ስትሆን አውግስጦስ ቄሣር በአካባቢው የነበረውን የሽፍቶች እንቅስቃሴ ለመከላከል ሲል የቆረቆራት ከተማ ነበረች። ኤውንቄ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ከግሪካዊው ባሏ፣ ከወንድ ልጅዋ ከጢሞቴዎስና ከእናቷ ከሎይድ ጋር የምትኖር አይሁዳዊ ክርስቲያን ነበረች።—ሥራ 16:1-3
መጽሐፍ ቅዱስ በልስጥራን ምኩራብ መኖሩን ስለማይገልጽ በከተማዋ የነበሩት አይሁዶች ቁጥር አነስተኛ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በኢቆንዮን የአይሁድ ማኅበረሰብ ይገኝ ነበር። (ሥራ 14:19) ስለዚህ ኤውንቄ አምልኮዋን ለማከናወን ተቸግራ መሆን አለበት። ጢሞቴዎስ በሕፃንነቱ ያልተገረዘው አንዳንድ ምሁራን የኤውንቄ ባል ሐሳቡን ቢቃወመው ነው ወደሚል መደምደሚያ እንዲያዘነብሉ አድርጓቸዋል።
ይሁን እንጂ ኤውንቄ የእምነት አጋር አላጣችም። ጢሞቴዎስ “ቅዱሳን መጻሕፍትን” የተማረው ከእናቱና በእናቱ በኩል አያቱ ከሆነችው ከሎይድ ነበር።a ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል አጥብቆ መክሮታል:- “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት [“እንድታምን በተደረግህበት፣” NW] ነገር ጸንተህ ኑር፣ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፣ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15
‘ከሕፃንነት ጀምሮ’ የተሰጠ ትምህርት
ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ “ቅዱሳን መጻሕፍትን” የተማረው ከሕፃንነቱ ጀምሮ መሆኑን ሲናገር ትንሽ ልጅ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ማለቱ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ አዲስ የተወለደ ሕፃንን የሚያመለክት የግሪክኛ ቃል (ብሬፎስ) መጠቀሙ ይህን የሚያሳይ ነው። (ከሉቃስ 2:12, 16 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ ኤውንቄ ከአምላክ የተሰጣትን ኃላፊነት በቁም ነገር በመመልከት ጢሞቴዎስ ሲያድግ ለአምላክ ያደረ አገልጋይ እንዲሆን የሚያስችለውን ማሠልጠኛ ከሕፃንነቱ ጀምራ ለመስጠት ዛሬ ነገ አላለችም።—ዘዳግም 6:6-9፤ ምሳሌ 1:8
ጢሞቴዎስ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ‘እንዲያምን ተደርጎ’ ነበር። በአንድ የግሪክኛ መዝገበ ቃላት መሠረት ጳውሎስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ቃል አንድን ነገር “በጽኑ እንዲያምን ማድረግ፤ እርግጠኛ እንዲሆን ማድረግ” የሚል ትርጉም አለው። በጢሞቴዎስ ልብ ውስጥ እንዲህ ያለውን ጽኑ እምነት መትከልና ከአምላክ ቃል እያስረዱ በቃሉ ላይ እምነት እንዲኖረው ማድረግ ብዙ ጊዜና ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ እንደነበር አያጠራጥርም። ኤውንቄና ሎይድ ጢሞቴዎስን ከቅዱሳን ጽሑፎች ለማስተማር በጋራ ጠንከረው መሥራታቸውን ከዚህ መገንዘብ ይቻላል። እነዚህ አምላካዊ ሴቶች ምንኛ ተክሰዋል! ጳውሎስ ስለ ጢሞቴዎስ ሲጽፍ “በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፣ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ” ለማለት ችሎ ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 1:5
ኤውንቄና ሎይድ በጢሞቴዎስ ሕይወት ውስጥ የነበራቸው ሚና ምንኛ ጉልህ ነበር! ደራሲው ዴቪድ ሪድ ይህን አስመልክተው ሲናገሩ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ሐዋርያው በጢሞቴዎስ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወተው ነገር በግሉ ለመለወጥ ያደረገው ጥረት እንደሆነ ቢሰማው ኖሮ ቀጥታ ስለዚሁ በጠቀሰለት ነበር። ይሁን እንጂ ስለ ጢሞቴዎስ እምነት ሲናገር በመጀመሪያ የጠቀሰው ይህ እምነት ‘አስቀድሞ በሎይድና . . . በኤውንቄ’ መኖሩን ነው።” የሎይድን፣ የኤውንቄንና የጢሞቴዎስን እምነት አስመልክቶ ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ እንደሚያሳየው አያቶችን ጨምሮ ወላጆች ለልጆቻቸው ከሕፃንነታቸው አንስቶ በቤት ውስጥ የሚሰጡት ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት የአንድን ልጅ የወደፊት መንፈሳዊነት የሚወስን መሠረታዊ ነገር ነው። ይህ፣ የቤተሰብ አባላት ለአምላክም ሆነ ለልጆቻቸው ያለባቸውን ኃላፊነት ለማሟላት ምን በማድረግ ላይ እንዳሉ በጥሞና እንዲያስቡበት ሊያደርጋቸው አይገባምን?
ከዚህም ሌላ ሎይድና ኤውንቄ በቤታቸው እንዲሰፍን አድርገውት የነበረውን ጥሩ መንፈስም ጳውሎስ ሳያስብ አልቀረም። ሐዋርያው መጀመሪያ ወደ ልስጥራን በሄደበት በ47/48 እዘአ ገደማ ቤታቸውን ጎብኝቶት መሆን አለበት። ሁለቱ ሴቶች ወደ ክርስትና የተለወጡት በዚያን ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 14:8-20) ጳውሎስ በዚህ ቤት ውስጥ ያየው ሞቅ ያለና አስደሳች ግንኙነት፣ ሎይድ የጢሞቴዎስ “አያት” መሆኗን ለማመልከት የተጠቀመበትን ቃል በመምረጥ ረገድ ተጽእኖ ሳያሳድርበት አልቀረም። ሴስላ ስፒክ የተባሉት ምሁር እንደገለጹት ከሆነ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል (ማሜ፤ ይህ ቴቴ ከሚለው የቆየና አክብሮት የተሞላ ቃል የተለየ ነው) “አንድ ልጅ” ሴት አያቱን “የሚጠራበት የፍቅር ቃል” ሲሆን በዚህ አገባቡ “ቤተሰባዊነትንና የጠበቀ መዋደድን” ይገልጻል።
የጢሞቴዎስ ተለይቶ መሄድ
ጳውሎስ (በ50 እዘአ አካባቢ) ለሁለተኛ ጊዜ ልስጥራን ሲጎበኝ የኤውንቄ ትዳር ምን መልክ እንደነበረው በግልጽ አይታወቅም። ብዙ ምሁራን ባሏ ሳይሞትባት አይቀርም ብለው ይገምታሉ። በዚያም ሆነ በዚህ ጢሞቴዎስ በእናቱና በአያቱ አመራር ሥር በመሆን ጥሩ ወጣት ሆኗል። በዚህ ጊዜ 20 ዓመት ሳይሞላው አይቀርም። “ለእርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች መሰከሩለት።” (ሥራ 16:2) ጳውሎስ ከእርሱና ከሲላስ ጋር በሚስዮናዊ ጉዟቸው እንዲሄድ ያቀረበለትን ግብዣ መቀበሉ የመንግሥቱን ምሥራች የማስፋፋት ፍላጎት በጢሞቴዎስ ልብ ውስጥ ተተክሎ የነበረ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
ኤውንቄና ሎይድ ጢሞቴዎስ ለመሄድ ሲዘጋጅ ምን እንደሚሰማቸው እስቲ አስቡት! ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተማቸውን ሲጎበኝ ሐዋርያው በድንጋይ እንደተወገረና ሞቷል ብለው እንደተዉት ያውቃሉ። (ሥራ 14:19) ስለዚህ ወጣቱ ጢሞቴዎስ እንዲሄድ መፍቀዱ ከብዷቸው መሆን አለበት። ለምን ያህል ጊዜ ይቆይ ይሆን? በደህና ይመለስ ይሆን? እያሉ ሳያስቡ አልቀሩም። እናቱና አያቱ እነዚህ ነገሮች ቢያስጨንቋቸውም ይህን ልዩ መብት ተቀብሎ ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መልኩ እንዲያገለግል ጢሞቴዎስን እንዳበረታቱት ምንም ጥርጥር የለውም።
ጠቃሚ ትምህርቶች
የኤውንቄንና የሎይድን ታሪክ በጥንቃቄ በመመርመር ብዙ ለመማር ይቻላል። ጢሞቴዎስን በመንፈሳዊ አንጸው እንዲያሳድጉት ያንቀሳቀሳቸው እምነት ነው። አያቶች ለልጅ ልጆቻቸውና ለሌሎችም ሊያሳዩ የሚችሉት ጉልምስናና የሰከነ አቋም የሚንጸባረቅበት ለአምላክ የማደር ባሕርይ ለጠቅላላው የክርስቲያን ጉባኤ በጣም ጠቃሚ ነው። (ቲቶ 2:3-5) በተመሳሳይም የኤውንቄ ምሳሌ የማያምኑ ባሎች ያሏቸውን እናቶች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ትምህርትን የማካፈል ኃላፊነት እንዳለባቸውና ይህን ማድረጋቸውም የሚክስ መሆኑን እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። በተለይ ባልየው የትዳር ጓደኛውን ሃይማኖታዊ እምነቶች በጥሩ ዓይን የማይመለከት ከሆነ ይህን ማድረግ ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። አንዲት ክርስቲያን ሚስት የባሏን ራስነት የማክበርም ግዴታ ስላለባት ዘዴኛ መሆንንም ይጠይቃል።
ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ እድገት አድርጎ የተዋጣለት ሚስዮናዊና የበላይ ተመልካች ለመሆን መብቃቱ ሎይድና ኤውንቄ ላሳዩት እምነት፣ ጥረትና የራስን ፍላጎት መሥዋዕት የማድረግ ባሕርይ ትልቅ ካሣ ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:19-22) ዛሬም በተመሳሳይ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ለልጆቻችን ማስተማር ጊዜ፣ ትዕግሥትና ቆራጥነትን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ የሚያስገኘው ውጤት ሲታይ ያደረግነው ጥረት ሁሉ ምንም አያስቆጭም። በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ‘ቅዱሳን ጽሑፎችን ከሕፃንነታቸው ጀምረው’ ተምረው ያደጉ በምሳሌነት የሚጠቀሱ በርካታ ክርስቲያን ወጣቶች አምላካዊ ለሆነው ወላጃቸው ትልቅ ደስታን ያመጣሉ። ‘ጠቢብን ልጅ የወለደች ደስታን ታገኛለች’ የሚለው ምሳሌ ምንኛ እውነት ነው!—ምሳሌ 23:23-25
ሐዋርያው ዮሐንስ መንፈሳዊ ልጆቹን አስመልክቶ ሲናገር “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም” ብሏል። (3 ዮሐንስ 4) እነዚህ ቃላት በአርዓያነት እንደሚጠቀሱት ሁለቱ አስተማሪዎች እንደ ኤውንቄና እንደ ሎይድ ኃላፊነታቸውን የተወጡ ወላጆች ስሜት የተንጸባረቀባቸው እንደሆኑ የተረጋገጠ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሲሪያክ ትርጉም በ2 ጢሞቴዎስ 1:5 ላይ “የእናትህ እናት” የሚል አገላለጽ መጠቀሙ ሎይድ ለጢሞቴዎስ አያት የሆነችው በአባቱ በኩል እንዳልሆነ ያመለክታል።