የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በሐዘን ለተደቆሱ ግዞተኞች የተላከ ተስፋ ሰጭ መልእክት
    የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
    • ‘ለወገኖች አዛዥ’

      13. ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅትም ሆነ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ “ለአሕዛብ ምስክር” የሆነው እንዴት ነው?

      13 በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጠው ይህ ንጉሥ ምን ያከናውናል? ይሖዋ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እነሆ፣ ለአሕዛብ ምስክር፣ ለወገኖችም አለቃና [“መሪ፣” አ.መ.ት ] አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ።” (ኢሳይያስ 55:4) ኢየሱስ ካደገ በኋላ የይሖዋ ምድራዊ ወኪል ማለትም ለአሕዛብ የአምላክ ምስክር ሆኖ አገልግሏል። ኢየሱስ ሰው ሆኖ በኖረበት ዘመን አገልግሎቱ ያተኮረው ‘የጠፉትን የእስራኤል ቤት በጎች’ በመፈለጉ ሥራ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ተከታዮቹን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 10:​5, 6፤ 15:​24፤ 28:​19, 20) በመሆኑም ውሎ አድሮ የመንግሥቱ መልእክት አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች መነገር የጀመረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባው ቃል ኪዳን ፍጻሜ ተካፋዮች ሆነዋል። (ሥራ 13:​46) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላም ‘ለአሕዛብ የይሖዋ ምስክር’ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል።

      14, 15. (ሀ) ኢየሱስ “መሪና አዛዥ” መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች ምን ተስፋ አግኝተዋል?

      14 በተጨማሪም ኢየሱስ “መሪና አዛዥ” እንደሚሆን ተነግሯል። በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከዚህ ትንቢታዊ መግለጫ ጋር በሚስማማ መንገድ የራስነት ሥልጣኑ የሚያስከትልበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የተቀበለ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ወደ እሱ በመሳብ፣ የእውነትን ቃል በማስተማርና አመራሩን የሚከተሉ ሁሉ የሚያገኟቸውን ጥቅሞች በመግለጽ በሁሉም ዘርፍ ግንባር ቀደም ሆኖ አገልግሏል። (ማቴዎስ 4:​24፤ 7:​28, 29፤ 11:​5) ደቀ መዛሙርቱን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው የስብከት ዘመቻ በሚገባ በማዘጋጀት ውጤታማ በሆነ መንገድ አሠልጥኗቸዋል። (ሉቃስ 10:​1-12፤ ሥራ 1:​8፤ ቆላስይስ 1:​23) ኢየሱስ በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የጣለው መሠረት ከተለያዩ ዘሮች የተውጣጡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አባላትን ያቀፈ አንድነት ያለው ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ እንዲቋቋም አስችሏል! እንዲህ ያለ ታላቅ ሥራ ማከናወን የሚችለው እውነተኛ “መሪና አዛዥ” ብቻ ነው።b

      15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ሥር የተሰባሰቡት ሰዎች በአምላክ ቅዱስ መንፈስ የተቀቡ ሲሆን በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች የመሆን ተስፋ አግኝተዋል። (ራእይ 14:​1) ይሁን እንጂ የኢሳይያስ ትንቢት ከጥንቱ የክርስትና ዘመን ባሻገር ያለውንም ሁኔታ ይዳስሳል። ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ 1914 ድረስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት እንዳልጀመረ ማስረጃዎቹ ያመለክታሉ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በምድር ባሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ የተፈጠረው ሁኔታ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በግዞት የነበሩት አይሁዳውያን ገጥሟቸው ከነበረው ሁኔታ ጋር በብዙ መልኩ ይመሳሰላል። እንዲያውም የኢሳይያስ ትንቢት የላቀ ፍጻሜውን ያገኘው በእነዚህ ክርስቲያኖች ላይ ነው።

      ዘመናዊ ግዞትና ነፃነት

      16. በ1914 ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ ምን መከራ ተከሰተ?

      16 ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ በዙፋን ላይ ሲቀመጥ በዓለም ላይ ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ መከራ ተከስቷል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ሲነግሥ ሰይጣንንና ሌሎቹን ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ከሰማይ አባርሯል። ሰይጣን እንቅስቃሴው በምድር ብቻ እንዲወሰን ሲደረግ በምድር ላይ በቀሩት ቅዱሳን ማለትም በቅቡዓን ቀሪዎች ላይ ጦርነት ከፈተ። (ራእይ 12:​7-12, 17) በቅቡዓኑ ላይ የተከፈተው ይህ ውጊያ በ1918 በከፍተኛ ሁኔታ በመፋፋሙ የስብከቱ ሥራ የተዳፈነ ያህል ሆኖ የነበረ ሲሆን በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሠሩ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አባላትም በመንግሥት ላይ ዓመፅ ለማነሳሳት ሞክራችኋል በሚል ክስ ተወንጅለው ታሠሩ። በዚህ መንገድ ዘመናዊዎቹ የይሖዋ አገልጋዮች በጥንት ዘመን ቃል በቃል በግዞት ተይዘው ከነበሩት አይሁዳውያን ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ በመንፈሳዊ ግዞተኞች ሆኑ። በዚህም ሳቢያ ለከፍተኛ ነቀፋና ትችት ተጋልጠው ነበር።

      17. ቅቡዓን ቀሪዎቹ ገጥሟቸው የነበረው ሁኔታ በ1919 የተለወጠው እንዴት ነው? በዚያን ጊዜ የተጠናከሩትስ እንዴት ነው?

      17 ይሁን እንጂ የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች በመንፈሳዊ ግዞት የቆዩት ለረጅም ጊዜ አልነበረም። ታስረው የነበሩት ወንድሞች መጋቢት 26, 1919 የተፈቱ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ ተመሥርቶባቸው ከነበረው ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆኑ። ይሖዋ ነፃ በወጡት ሕዝቦቹ ላይ ቅዱስ መንፈሱን በማፍሰስ ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሥራ አበረታቸው። ‘የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲወስዱ’ የቀረበላቸውን ጥሪ በደስታ ተቀበሉ። (ራእይ 22:​17) ‘የወይን ጠጅና ወተት ያለ ገንዘብና ያለ ዋጋ’ ከመግዛታቸውም በላይ ብዙም ሳይቆይ የተገኘውንና ቅቡዓን ቀሪዎቹ ፈጽሞ ያልጠበቁትን እጅግ አስደናቂ የሆነ እድገት ለማስተናገድ የሚያስችል መንፈሳዊ ጥንካሬ አግኝተዋል።

      እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ ቅቡዓን ይሮጣሉ

      18. ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከተሉት ሁለት ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? በአሁኑ ጊዜስ ምን ሆነዋል?

      18 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሁለት ዓይነት ተስፋ አላቸው። በመጀመሪያ 144, 000 ቁጥር ያላቸው ‘የታናሹ መንጋ’ ማለትም ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ አባላት የሆኑ ከአይሁድና ከአሕዛብ የተውጣጡ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተሰባሰቡ ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር የመግዛት ተስፋ አላቸው። (ሉቃስ 12:​32፤ ገላትያ 6:​16፤ ራእይ 14:​1) በመጨረሻዎቹ ቀናት ደግሞ ‘የሌሎች በጎች’ አባላት የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ብቅ ብለዋል። እነዚህ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። አስቀድሞ የተወሰነ ቁጥር የሌላቸው እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ታላቁ መከራ ከመምጣቱ በፊት ከታናሹ መንጋ ጎን ተሰልፈው የሚያገለግሉ ሲሆን እነዚህ ሁለት ቡድኖች ‘በአንድ እረኛ’ የሚመራ ‘አንድ መንጋ’ ሆነዋል።​—⁠ራእይ 7:​9, 10፤ ዮሐንስ 10:​16

  • በሐዘን ለተደቆሱ ግዞተኞች የተላከ ተስፋ ሰጭ መልእክት
    የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
    • b ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በበላይነት መቆጣጠሩን ቀጥሏል። (ራእይ 14:​14-16) በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ኢየሱስን የጉባኤው ራስ አድርገው ያዩታል። (1 ቆሮንቶስ 11:​3) ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ኢየሱስ በአርማጌዶን በአምላክ ጠላቶች ላይ የሚከፈተውን ወሳኝ የሆነ ውጊያ በመምራት ለየት ባለ መንገድ “መሪና አዛዥ” ሆኖ እርምጃ ይወስዳል።​—⁠ራእይ 19:​19-21

  • በሐዘን ለተደቆሱ ግዞተኞች የተላከ ተስፋ ሰጭ መልእክት
    የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
    • [በገጽ 239 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ኢየሱስ ለወገኖች “መሪና አዛዥ” መሆኑን አስመስክሯል

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ