-
‘በፈጠርሁት ለዘላለም ደስ ይበላችሁ’የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
-
-
18. ከይሖዋ የራቁ ሰዎች ትተውት የሚያልፉት ነገር ምንድን ነው? ስማቸው በእርግማን መጠቀሱ ምን ነገርን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል?
18 ይሖዋ በመቀጠል እሱን የተዉትን ሰዎች እንዲህ አለ:- “ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፣ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፣ ባሪያዎቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል። እንዲሁም በምድር ላይ የተባረከ በእውነት አምላክ ይባረካል፣ በምድርም ላይ የማለ በእውነት አምላክ ይምላል፤ የቀድሞው ጭንቀት ተረስቶአልና፣ ከዓይኔም ተሰውሮአልና።” (ኢሳይያስ 65:15, 16) ይሖዋን የተዉት ሰዎች ትተውት የሚያልፉት ነገር ቢኖር በእርግማን ወቅት ብቻ የሚነሳውን ስማቸውን ይሆናል። በሌላ አነጋገር ሰዎች ‘የገባሁትን ቃል ባጥፍ በእነዚያ ከሃዲዎች ላይ የደረሰው ቅጣት በእኔም ላይ ይድረስ’ ይላሉ እንደ ማለት ነው። አልፎ ተርፎም ስማቸው ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ አምላክ በክፉዎች ላይ ለሚወስደው የቅጣት እርምጃ ተምሳሌት ሆኖ ያገለግላል ማለትም ሊሆን ይችላል።
19. የአምላክ አገልጋዮች በሌላ ስም መጠራታቸው ምን ያመለክታል? በእውነት አምላክ ላይ ሙሉ እምነታቸውን የሚጥሉትስ ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
19 የአምላክ አገልጋዮች የሚገጥማቸው ዕጣ ግን ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው! በሌላ ስም ይጠራሉ። ይህም ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ የሚያገኙትን በረከትና ክብር ያመለክታል። የሌላ የማንኛውንም የሐሰት አምላክ በረከት አይሹም ወይም በድን በሆነ ጣዖት አይምሉም። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን የሚባርኩት ወይም መሐላ የሚገቡት በእውነት አምላክ ይሆናል። ይሖዋ ቃሉን የሚጠብቅ አምላክ መሆኑን በተግባር ያሳየ በመሆኑ የምድሪቱ ነዋሪዎች በእሱ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑበት በቂ ምክንያት አላቸው።c በትውልድ አገራቸው ከስጋት ነፃ ሆነው ስለሚኖሩ የቀድሞውን መከራና ችግር ወዲያውኑ ይረሱታል።
-
-
‘በፈጠርሁት ለዘላለም ደስ ይበላችሁ’የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
-
-
c በዕብራይስጡ የማሶሬቲክ ጽሑፍ ላይ ኢሳይያስ 65:16 ይሖዋ “የአሜን አምላክ” እንደሆነ ይገልጻል። “አሜን” ማለት “ይሁን” ወይም “የሚያስተማምን” ማለት ሲሆን ይህም አንድ ነገር እውነተኛ እንደሆነ ወይም ፍጻሜውን ማግኘቱ እንደማይቀር የሚያረጋግጥ ዋስትና ነው። ይሖዋ ቃል የገባውን ሁሉ በመፈጸም የሚናገረው ነገር እውነት እንደሆነ ያሳያል።
-