የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • “የፍርድ ምርመራ” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ነውን?
    መጠበቂያ ግንብ—1997 | ሐምሌ 15
    • ይህን መሠረተ ትምህርት ለመደገፍ የሚጠቀሰው ዋነኛ ጥቅስ ዳንኤል 8:​14 ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እርሱም:- እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጠዋት ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነጻል አለኝ።” ብዙ አድቬንቲስቶች “ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነጻል” ከሚለው የጥቅሱ ክፍል በመነሳት ይህንን ጥቅስ ከዘሌዋውያን ምዕራፍ 16 ጋር ያያይዙታል። የዘሌዋውያን ጥቅስ በስርየት ቀን በአይሁዳውያን ሊቀ ካህናት አማካኝነት ስለሚከናወነው የቤተ መቅደሱ መንጻት ይናገራል። በተጨማሪም በዳንኤል ላይ ያሉትን ቃላት ኢየሱስ በሰማይ የሚገኝ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስለመሆኑ ከሚናገረው ከዕብራውያን ምዕራፍ 9 ጋር ያያይዟቸዋል። አንድ የኤስ ዲ ኤ ምሁር ይህ ማስረጃ “በጥቅስ የተደገፈ” ነው ብለዋል። አንድ ሰው “መቅደስ እንደሚለው ያለ አንድ ቃል ከዳን. 8:​14” ይወስድና “ይኸንኑ ቃል በዘሌ. 16ና በዕብ. 7, 8, 9 ላይ ካለው ጋር በማዛመድ ሁሉም ጥቅሶች የሚናገሩት ስለ አንድ ነገር ነው” ወደሚል መደምደሚያ ይደርሳል።

      አድቬንቲስቶች እንደሚከተለው በማለት ያስረዳሉ:- የጥንቷ እስራኤል ካህናት ቅድስት ተብሎ በሚጠራው የቤተ መቅደሱ ክፍል በየዕለቱ የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኝ ሥርዓት ያከናውኑ ነበር። በስርየት ቀን ደግሞ ሊቀ ካህናቱ በዓመት አንድ ጊዜ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ (በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል) የሕዝቡ ኃጢአት እንዲደመሰስ የሚያደርግ አገልግሎት ያከናውን ነበር። ስለሆነም የክርስቶስ ሰማያዊ የሊቀ ክህነት አገልግሎት ሁለት ምዕራፍ አለው ብለው ደምድመዋል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ካረገበት ከአንደኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በ1884 ያበቃ ሲሆን የኃጢአት ይቅርታ አስገኝቷል። ሁለተኛው ወይም “የፍርዱ ምዕራፍ” ደግሞ የጀመረው ጥቅምት 22, 1884 ሲሆን እስካሁንም ድረስ በመቀጠል የሰዎች ኃጢአት እንዲደመሰስ ያደርጋል። ይህ የሚከናወነው እንዴት ነው?

      ኢየሱስ ከ1844 አንስቶ አማኝ ነን የሚሉትን ሰዎች የሕይወት መዝገብ በሙሉ (በመጀመሪያ የሙታንን ከዚያም የሕያዋንን) እያየ ለዘላለም ሕይወት ይበቁ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመፍረድ እየመረመረ ነው ይላሉ። “የፍርድ ምርመራ” ተብሎ የሚጠራው ይህ ምርመራ ነው። በዚህ መንገድ ከተገመገሙ በኋላ ከፈተናው ያለፉት ሰዎች ኃጢአታቸው ከመዝገቡ ላይ ይደመሰስላቸዋል። ይሁን እንጂ ትላለች ኤለን ዋይት ይህን ፈተና የማያልፉት ሰዎች ‘ስማቸው ከሕይወት መጽሐፍ ይደመሰሳል።’ በዚህ መንገድ “የእያንዳንዱ ሰው ዕጣ ፋንታ ለሕይወት ይሁን ወይም ለሞት ይወሰናል።” ያኔ የሰማዩ መቅደስ ስለሚነጻ ዳንኤል 8:​14 ፍጻሜውን ያገኛል። የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ትምህርት ይህ ነው። ይሁን እንጂ አድቬንቲስት ሪቪው የተባለው የኤስ ዲ ኤ ጽሑፍ “የፍርድ ምርመራ የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም” ሲል አምኗል።

      የቋንቋ ተዛምዶ ይጎድለዋል

      ይህ ትምህርት አንዳንድ አድቬንቲስቶችን ከንክኗቸዋል። አንድ ታዛቢ “በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉ ታማኝ መሪዎች ሲወርድ ሲዋረድ ስለመጣው የፍርድ ምርመራ ትምህርት ማሰቡ ነፍሳቸውን እረፍት እንደነሳው ታሪክ ያረጋግጣል” ካሉ በኋላ አክለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምሁራኑ “እስካሁን ድረስ ስለ መቅደሱ ለማብራራት ማስረጃ ብለን የያዝናቸው ዓምዶች ጥያቄ ላይ መውደቃቸው” ጭንቀቱን ወደ ጥርጣሬ ለውጦታል ብለዋል። እስቲ እንደ ዓምድ ከታዩት ማስረጃዎች መካከል ሁለቱን እንመርምር።

      አንደኛው ዓምድ:- ዳንኤል ምዕራፍ 8 ከዘሌዋውያን ምዕራፍ 16 ጋር መዛመዱ ነው። ይህ ማስረጃ ደካማ ሆኖ የተገኘው በሁለት ዋና ዋና ችግሮች የተነሣ ሲሆን እነዚህም ቋንቋውና የጥቅሱ አገባብ ናቸው። በመጀመሪያ ቋንቋውን ተመልከት። አድቬንቲስቶች በዘሌዋውያን ምዕራፍ 16 ላይ የተገለጸው ‘የመቅደስ መንጻት’ በዳንኤል ምዕራፍ 8 ላይ ለተገለጸው ‘የመቅደስ መንጻት’ ጥላ እንደሆነ ያምናሉ። ተርጓሚዎች በኪንግ ጀምስ ቨርሽን ላይ “መንጻት” ተብሎ በስህተት የተተረጎመው በዳንኤል 8:​14 ላይ የሚገኘው ጻድሃቅ (ትርጉሙ “ጻድቅ መሆን”) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል መሆኑን እስከተረዱበት ጊዜ ድረስ እነዚህን ጥቅሶች ለማመሳሰል የተደረገው ጥረት ተቀባይነት ያለው ይመስል ነበር። የሃይማኖታዊ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት አንቶኒ ኤ ሆክማ እንዲህ ብለዋል:- “እዚህ ላይ የተሠራበት የዕብራይስጥ ግሥ ብዙውን ጊዜ መንጻትን ለማመልከት የሚያገለግለው [ጣሄር ] ባለመሆኑ ቃሉ መንጻት ተብሎ መተርጎሙ ተገቢ አይደለም።”a ይህ ቃል በዘሌዋውያን ምዕራፍ 16 ላይ የተሠራበት ሲሆን የኪንግ ጀምስ ቨርሽን ጣሄር የሚለውን ቃል እርባታዎች “ማንጻት” እና “መንጻት” እያለ ተርጉሟቸዋል። (ዘሌዋውያን 16:​19, 30) በመሆኑም ዶክተር ሆክማ “ዳንኤል በስርየት ቀን ይፈጸም የነበረውን ዓይነት መንጻት መናገሩ ከነበረ ጻዳቅ [ጻድሃቅ] ከሚለው ይልቅ ጣሂር [ጣሄር] የሚለውን ቃል ይጠቀም ነበር” በማለት በትክክል ደምድመዋል። ይሁንና ጻድሃቅ የሚለው ቃል በዘሌዋውያን መጽሐፍ ላይ አይገኝም፤ ጣሄር የሚለው ደግሞ በዳንኤል መጽሐፍ ላይ አይገኝም። በጥቅሶቹ መካከል የቋንቋ ተዛምዶ የለም።

      የጥቅሱ አገባብ ምን ይጠቁማል?

      አሁን ደግሞ የጥቅሱን አገባብ ተመልከት። አድቬንቲስቶች ዳንኤል 8:​14 ከላይ ካሉት ቁጥሮች ሐሳብ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ‘እንደ ደሴት’ መሐል ላይ ቁጭ ያለ ሐሳብ ነው ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ በዚህ ርዕስ ላይ ከቀረበው “በዳንኤል 8:​14 ዙሪያ ያለው ሐሳብ” ከሚለው ሣጥን ዳንኤል 8:​9-14ን ስታነብ የምታገኘው መልእክት ይህ ነውን? ቁጥር 9 ጠበኛ ስለሆነ አንድ ትንሽ ቀንድ ይናገራል። ከቁጥር 10-12 ላይ ይህ ጠበኛ ቀንድ በመቅደሱ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር ይገልጻል። ቁጥር 13 ይህ ‘ጠብ አጫሪነት እስከመቼ ድረስ ይዘልቅ ይሆን’ የሚል ጥያቄ ያቀርባል። ቁጥር 14 እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል:- “እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጠዋት ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነጻል።” በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ቁጥር 14 መልስ የሚሰጠው በቁጥር 13 ላይ ለተነሣው ጥያቄ ነው። የሃይማኖታዊ ትምህርት ምሁር የሆኑት ዴዝመንድ ፎርድ እንዲህ ብለዋል:- “ዳንኤል 8:​14ን ከዚህ ጩኸት [በቁጥር 13 ላይ ከሚገኘው “እስከ መቼ?” ከሚለው ጩኸት] ለመነጠል መሞከር መርከብን ያለ መልሕቅ ባሕር ላይ ለማቆም እንደ መሞከር ነው።”b

      አድቬንቲስቶች በቁጥር 14 ያለውን ጥቅስ በዙሪያው ካለው ሐሳብ የሚነጥሉት ለምንድን ነው? በኋላ ማጠፊያው እንዳያጥራቸው ሲሉ ነው። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ በቁጥር 14 ላይ የተጠቀሰው ቤተ መቅደስ በትንሹ ቀንድ ተግባር መርከሱን የሚገልጽ ነው። “የፍርድ ምርመራ” የሚለው መሠረተ ትምህርት ግን የቤተ መቅደሱን መርከስ ክርስቶስ ከሚያደርገው ነገር ጋር ያያይዘዋል። ኢየሱስ የአማኞችን ኃጢአት ወደ ሰማያዊ ቤተ መቅደስ ያዛውራል ይላሉ። ታዲያ አድቬንቲስቶች መሠረተ ትምህርቱንም በጥቅሱ ዙሪያ ያለውንም ሐሳብ ከተቀበሉ ውጤቱ ምን ይሆናል? የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን አባልና ቀደም ሲል የኤስ ዲ ኤ ባይብል ኮሜንታሪ ተባባሪ አዘጋጅ የነበሩት ዶክተር ሬይመንድ ኤፍ ኮትሬል እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ኤስ ዲ ኤ ለዳንኤል 8:​14 የሚሰጠው ማብራሪያ ከጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ እንዳገናዘበ አስመስለን መቅረብ ትንሹ ቀንድ ኢየሱስ ነው ማለት ይሆንብናል።” ዶክተር ኮትሬል በሐቀኝነት እንዲህ ሲሉ አምነዋል:- “በጥቅሱ ዙሪያ ያለውንም ሐሳብ፣ አድቬንቲስት ለጥቅሱ የምትሰጠውንም ፍቺ መቀበል የማይሆን ነገር ነው።” በመሆኑም የአድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን “የፍርድ ምርመራ” የሚለውን ትምህርት በሚመለከት ወይ መሠረተ ትምህርቱን አለዚያም ከዳንኤል 8:​14 ዙሪያ ያለውን ሐሳብ መቀበል ይኖርባታል። የሚያሳዝነው ግን መሠረተ ትምህርቱን የሙጢኝ ብላ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ሳትቀበል ቀርታለች። ዶክተር ኮትሬል ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች መጠነኛ እውቀት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አድቬንቲስቶች “ለቅዱስ ጽሑፉ የሌለ” ትርጉም “ለመስጠት ይሞክራሉ” በማለት መውቀሳቸው ምንም አያስገርምም ብለዋል።

      ዶክተር ኮትሬል በ1967 በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የተመረኮዘ በሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚሰጥ ትምህርት አዘጋጅተው የነበረ ሲሆን ይህም በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የኤስ ዲ ኤ አብያተ ክርስቲያናት ተሠራጭቷል። ትምህርቱ ዳንኤል 8:​14 በዙሪያው ካለው ሐሳብ ጋር የሚዛመድ መሆኑንና ‘መንጻት’ የሚለውም አማኞችን እንደማያመለክት አስረድቷል። ይህ ትምህርት አንድም ጊዜ ቢሆን ስለ “ፍርድ ምርመራ” አለመጥቀሱ የሚያስገርም ነው።

      አንዳንድ የሚያስደንቁ ምላሾች

      አድቬንቲስቶች ይህ ዓምድ “የፍርድ ምርመራ” የሚባለውን መሠረተ ትምህርት ለመሸከም የማይችል ደካማ መሆኑን ምን ያህል ተገንዝበውታል? ዶክተር ኮትሬል ‘በዳንኤል ምዕራፍ 8 እና በዘሌዋውያን ምዕራፍ 16 መካከል ያለውን የቋንቋ ወይም የአገባብ ተዛምዶ በተመለከተ ምን ያገኛችሁት ነገር አለ?’ የሚለውን ጥያቄ ለ27 የታወቁ የአድቬንቲስት ሃይማኖታዊ ምሁራን አቅርበው ነበር። ምላሻቸው ምን ነበር?

      “ሃያ ሰባቱም ቢሆኑ ዳን. 8:​14ን ከታላቁ የስርየት ቀንና ከፍርድ ምርመራ ጋር ለማያያዝ የሚያስችል አንድም የቋንቋም ሆነ የሐሳብ ተዛምዶ እንደሌለ አረጋግጠዋል።” ‘ሐሳቡን በዚህ መንገድ ለማገናኘት የሚያስችል ሌላ ምክንያት አላችሁ?’ ሲሉ ጠየቋቸው። አብዛኞቹ የአድቬንቲስት ምሁራን ምንም ምክንያት እንደሌላቸው ሲገልጹ አምስቱ ሐሳቡን በዚህ መንገድ ያያያዙት ኤለን ዋይት ስላያያዘችው እንደሆነ ተናግረዋል፤ ሁለቱ ደግሞ ትምህርቱ የተመረኮዘው በትርጉም ሥራ በተፈጠረው “ድንገተኛ ገጠመኝ” ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። የሃይማኖታዊ ትምህርት ምሁር የሆኑት ፎርድ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል:- “ምርጥ በሆኑ ምሁራኖቻችን የተሰጠው ይህ መደምደሚያ በዳን. 8:​14 ላይ የተመሠረተው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ትምህርታችን ምንም ማስረጃ እንደሌለው ያረጋግጣል።”

      ከዕብራውያን መጽሐፍ ድጋፍ ይገኝ ይሆን?

      ሁለተኛው ዓምድ:- ዳንኤል 8:​14 ከዕብራውያን ምዕራፍ 9 ጋር መያያዙ ነው። የሃይማኖታዊ ትምህርት ምሁር የሆኑት ፎርድ “ካሁን ቀደም የሠራናቸው የጽሑፍ ሥራዎች በሙሉ ዳን. 8:​14ን ለማብራራት መሠረት የሚያደርጉት ዕብ. 9ን ነበር” ብለዋል። ጥቅሶቹን በዚህ መልኩ ማዛመድ የተጀመረው በ1844 ከተከሰተው ‘ቅስም የሚሰብር’ ሁኔታ በኋላ ነው። ከሚለራውያኑ አንዱ የሆነው ሂራም አድሰን መመሪያ ለማግኘት በማሰብ መጽሐፍ ቅዱሱ ራሱ በራሱ እንዲገለጥ በቁሙ ጠረጴዛ ላይ ይጥለዋል። ውጤቱስ ምን ሆነ? ዕብራውያን ምዕራፍ 8 እና 9 ላይ ተገለጠለት። ፎርድ እንዲህ ይላሉ:- “በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የ1844ንና የዳንኤል 8:​14ን ትርጉም ለመረዳት የሚያስችል ቁልፍ ሐሳብ ይገኛል ለሚለው የአድቬንቲስቶች አባባል ከዚህ ይበልጥ ተስማሚና ገላጭ የሆነ ሌላ ምን ነገር ይኖራል!”

      ዶክተር ፎርድ ዳንኤል 8:​14 የስርየት ቀንና የፍርድ ምርመራ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ በማለት አክለው ተናግረዋል:- “ይህ የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስቶች ትልቅ ግምት የሚሰጡት ማስረጃ ነው። ከፍ አድርገን የምንመለከተውን የመቅደሱ ትምህርት . . . ትርጉም ዝርዝር ማብራሪያ የሚገኘው . . . በዕብ. 9 ላይ ብቻ ነው።” አዎን፣ “በአዲስ ኪዳን” ውስጥ የዘሌዋውያን ምዕራፍ 16ን ትንቢታዊ ትርጉም የሚያብራራው ምዕራፍ ዕብራውያን ምዕራፍ 9 ነው። ይሁን እንጂ አድቬንቲስቶች “ከብሉይ ኪዳን” ውስጥ ይህን ዓይነት ማብራሪያ የያዘው የዳንኤል 8:​14 ጥቅስ ነው ይላሉ። እነዚህ ሁለት ሐሳቦች እውነት ከሆኑ በዕብራውያን ምዕራፍ 9 እና በዳንኤል ምዕራፍ 8 መካከልም ተዛምዶ ሊኖር ይገባል ማለት ነው።

      ዴስመንድ ፎርድ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል:- “አንድ ሰው ገና ዕብ. ምዕራፍ 9ን ሲያነብ ግልጽ ሆነው የሚታዩት አንዳንድ ነገሮች አሉ። የዳንኤል መጽሐፍን እንደሚጠቅስ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም፤ በተለይ ደግሞ ዳን. 8:​14ን። . . . ጠቅላላ ምዕራፉ የዘሌ. 16ን አፈጻጸም የሚገልጽ ነው። እኛ ስለ መቅደሱ የምናስተምረው ትምህርት የቤተ መቅደሱን አገልግሎት በሚያብራራው ብቸኛው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ አይገኝም። ይህ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የታወቁ የአድቬንቲስት ጸሐፊዎች በሙሉ ተረጋግጧል።” በመሆኑም ሁለተኛውም ዓምድ ቢሆን ፈተና የገጠመውን ይህን መሠረተ ትምህርት ለመሸከም አይችልም።

      ይሁን እንጂ ይህ መደምደሚያ አዲስ አይደለም። ዶክተር ኮትሬል እንዳሉት “የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ለዳንኤል ምዕራፍ 8:​14 እና ዕብራውያን 9 የምንሰጠው የተለምዶ ትርጉም ለማስረዳት የሚያስቸግር እንደሆነ በሚገባ ከተገነዘቡት” ብዙ ዓመታት አልፈዋል። ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ተከታይ ኢ ጄ ዋጎነር ከ80 ዓመታት በፊት እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር:- ‘ስለ መቅደሱና ‘የፍርድ ምርመራው’ የሚገልጸው የአድቬንቲስት ትምህርት . . . ስርየትን ከመካድ ተለይቶ አይታይም።” (ኮንፌሽን ኦቭ ፌዝ) ከ30 ዓመታት በፊት ይህ ችግር ለኤስ ዲ ኤ አብያተ ክርስቲያናት አመራር ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ ነበር።

      ችግሮችና መሰናክል

      ጠቅላላ ጉባኤው “በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ችግሮች የሚፈታ ኮሚቴ” አቋቋመ። የኮሚቴው ዓላማ በዳንኤል 8:​14 ዙሪያ ያለውን ችግር መፍታት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ሪፖርት ማቅረብ ነበር። አሥራ አራቱ የኮሚቴው አባላት ለአምስት ዓመታት ጥያቄውን ሲያጠኑ ቢቆዩም በአንድ ድምፅ ውሳኔ ማስተላለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። የኮሚቴው አባል የነበሩት ኮትሬል በ1980 እንደተናገሩት አብዛኞቹ የኮሚቴው አባላት አድቬንቲስት ለዳንኤል 8:​14 የምትሰጠው ትርጉም “አጥጋቢ ነው” ተብሎ ተቀባይነት የሚያገኘው “ግምታዊ ሐሳቦችን” እርስ በርስ በማቀጣጠልና ችግሮቹን “በመርሳት” እንደሆነ ይስማማሉ። አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “ኮሚቴው በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ችግሮች የሚፈታ ተብሎ እንደተሰየመ ልብ በሉ፤ ሆኖም አብዛኞቻቸው ችግሩን እንርሳው ስለ እርሱ ማንሳት አያስፈልግም የሚሉ ነበሩ።” ይህም “መልስ የለንም ብሎ እንደማመን” የሚቆጠር ነው። በመሆኑም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የብዙሐኑን ሐሳብ ለመደገፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሪፖርቱ በቅጡ ሳይቀርብ ቀረ። የመሠረተ ትምህርቱም ችግሮች እልባት ሳያገኙ ቀርተዋል።

      ዶክተር ኮትሬል ስምምነት ላይ ስላልተደረሰበት ስለዚህ ጉዳይ ያላቸውን አስተያየት ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “እስከ ዛሬ ድረስ ትምህርቱን በማብራራት ረገድ ዓይኑን ያፈጠጠ ችግር መኖሩን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናችን ምክንያት አሁንም ከዳንኤል 8:​14 ጥያቄ አልተላቀቅንም። ምንም ችግር እንደሌለ ማስመሰላችንን እስከቀጠልንና ‘ግመል ሰርቆ አጎንብሶ’ እንደሚባለው በግለሰብ ደረጃም ይሁን በጥቅል ጭንቅላታችንን ብቻ ለመሰወር እስከጣርን ድረስ ችግሩ አብሮን ይዘልቃል።”​—⁠ስፔክትረም፣ በአድቬንቲስት ፎረሞች ማኅበር የሚዘጋጅ ጋዜጣ

      ዶክተር ኮትሬል “በአድቬንቲስት እምነት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ላለው ለዚህ ጥቅስ የምንሰጠው ትርጓሜ የተመረኮዘባቸውን መሠረታዊ ሐሳቦችና መሠረታዊ ማብራሪያዎች አድቬንቲስቶች እንደገና በጥንቃቄ ሊመረምሩ ይገባል” ሲሉ አጥብቀው አሳስበዋል። እኛም አድቬንቲስቶች “የፍርድ ምርመራ” የሚለው መሠረተ ትምህርት ዓምዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጠንካራ መሠረት ያላቸው ይሁኑ ወይም እንደ አሸዋ ባለ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ ሐሳብ ላይ ብቻ የቆሙ እንዲመረምሩ ልናበረታታቸው እንወዳለን።c ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ” ሲል ጥበብ የተሞላበት ምክር ሰጥቷል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:​21

  • “የፍርድ ምርመራ” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ነውን?
    መጠበቂያ ግንብ—1997 | ሐምሌ 15
    • በዳንኤል 8:​14 ዙሪያ ያለው ሐሳብ

      ዳንኤል 8:​9 “ከእነርሱም ከአንደኛው አንድ ታናሽ ቀንድ ወጣ፣ ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም ወደ መልካሚቱም ምድር እጅግ ከፍ አለ። 10 እስከ ሰማይም ሠራዊት ድረስ ከፍ አለ፤ ከሠራዊትና ከከዋክብትም አያሌዎችን ወደ ምድር ጣለ፣ ረገጣቸውም። 11 እስከ ሠራዊትም አለቃ ድረስ ራሱን ታላቅ አደረገ፤ ከእርሱም የተነሣ የዘወትሩ መሥዋዕት ተሻረ፣ የመቅደሱም ስፍራ ፈረሰ። 12 ሠራዊቱም ከኃጢአት የተነሣ ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ተሰጠው፤ እርሱም እውነትን ወደ ምድር ጣለ፣ አደረገም ተከናወነም።

      “13 ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ለተናገረው ለቅዱሱም ሁለተኛው ቅዱስ:- ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፣ መቅደሱና ሠራዊቱም ይረገጡ ዘንድ ስለሚሰጥና ስለሚያጠፋ ኃጢአት የሆነው ራእይ እስከ መቼ ይሆናል? አለው። 14 እርሱም:- እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጠዋት ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነጻል አለኝ።” (ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።)​—⁠የ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ