“አዲሲቱ ዓለም ትርጉም”—ምሁራን እውነተኛ ሆኖ አግኝተውታል
“በሐሰት የተሞላ!” ይህ ቃል በ16ኛው መቶ ዘመን ስለ ማርቲን ሉተር የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱስ ትርጉም ተቃዋሚዎቹ የተናገሩት ነበር። የሉተር መጽሐፍ ቅዱስ “1,400 መናፍቃዊ ስሕተቶችንና ውሸቶችን” እንደያዘ ማሳየት እንችላለን ብለው ያምኑ ነበር። በዛሬው ጊዜ የሉተር መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ግሩም ትርጉም ተደርጎ ይታያል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም የተባለው መጽሐፍ “ታላቅ ችሎታ የተንጸባረቀበት የትርጉም ሥራ” በማለት ይጠራዋል።
በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን አዲሲቱ ዓለም ትርጉም በሐሰተኝነት ተከሷል። ለምን? ምክንያቱም ትርጉሙ ከብዙ የቀድሞ ትርጉም ጥቅሶች ስለተለዬና ይሖዋ የሚባለውን የአምላክ ስም መጠቀምን ጠበቅ ስለሚያደርግ ነው። ስለዚህ ከተለመደው አተረጓጐም የተለየ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሐሰት ያደርገዋልን? አያደርገውም። በብዙ ጥንቃቄና ለዝርዝሮች ትኩረት በመስጠት የተዘጋጀ ነው። ያልተለመደ የሚመስለውም እንኳ የመጀመሪያውን የግሪክኛ ቋንቋ ጥቃቅን የትርጉም ልዩነቶችን በጥንቃቄ ለማቅረብ የተደረገን ልባዊ ጥረት ያመለክታል። የቲዮሎጂ ምሁር የሆኑት ሲሆትማን አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ከተለመደው የአተረጓጐም ዘዴ የተለየበትን ምክንያት ሲያብራሩ፦ “በተቻለ መጠን አንባቢው እንዲገባው ሲባል ከመጀመሪያው ጽሑፍ አስፈላጊ አባባሎችን የተለያዩ የቆዩ (የተለመዱ) ትርጉሞች አስቀርተዋል” ብለዋል። የዚህን አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት።
የተለየ ነው፤ ቢሆንም ስሕተት አይደለም
በመጀመሪያ ደረጃ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪውን የተለያዩና በጣም ጥቃቅን የትርጉም ልዩነቶች እንዳሉ ለማንቃት የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ተዛማጅ ቃላት በተቻለ መጠን በተለያዩ የእንግሊዝኛ ቃላት ተተርጉመዋል። በመሆኑም ‘ሲንተሊያ’ የሚለው የግሪክኛ ቃል ‘conclusion (መደምደሚያ)’ ተብሎ ሲተረጐም ‘ቴሎስ’ የሚለው ቃል ደግሞ ‘end (ፍጻሜ)’ ተብሎ ተተርጉሟል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ቃላት በሌሎች ትርጉሞች ‘ፍጻሜ’ ብቻ ተብለው ተተርጉመዋል። (ማቴዎስ 24:3, 13) ‘ኮስሞስ’ የሚለው ቃል ‘world’ (ዓለም)’ ተብሎ ሲተረጐም ‘አይየን’ የሚለው “system of things (የነገሮች ሥርዓት)” ተብሎ ተተርጉሞአል። እንደዚሁም ‘አይኮሜን’ የሚለው ቃል “inhabited earth” (ሰው የሚኖርባት ምድር)” ተብሎ ተተርጉሟል። እዚህም ላይ ቢሆን በእነዚህ ቃሎች መካከል ልዩነት ቢኖርም ሌሎች ትርጉሞች አሁንም ከሦስቱ ውስጥ ሁለቱን ወይም ሦስቱን ለማመልከት “ዓለም” የሚለውን ቃል ብቻ ተጠቅመዋል።—ማቴዎስ 13:38, 39፤ 24:14
በተመሳሳይም አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ‘ግኖሲስ’ (‘እውቀት’) እና ‘ኤፒግኖሲስ’ (ትክክለኛ ዕውቀት ተብሎ የተተረጐመው) በተባሉት ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት በጥንቃቄ ያስገነዝባል። ይህ ልዩነት ግን በሌሎች ትርጉሞች ሁሉ ችላ ተብሏል። (ፊልጵስዩስ 1:9፤ 3:8) እንዲሁም ‘ቴፎስ’ (‘መቃብር’ የግል መቀበሪያ ጉድጓድ) ‘ምኔምየን’ (‘መቃብር’) እና ‘ሔይዴስ’ (‘ሐዴስ’ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰው ልጆችን የጋራ መቃብር የሚያመለክተው የሚሉትን ቃላት ትርጉሞች ለይቶ ያሳያል። (ማቴዎስ 27:60, 61፤ ዮሐንስ 5:28፤ ሥራ 2:29, 31) አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በማቴዎስ 23:29 ላይ ብቻ ‘ቴፎስ’ እና ‘ምኔምየን’ የሚሉትን ብቻ በተለያዩ መንገዶች ይተርጉሙ እንጂ እስከ መጨረሻው በዚሁ አይቀጥሉበትም።—ማቴዎስ 27:60, 61 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን
የግሶቹ ጊዜያት (ግሶቹ ከነጊዜ አመልካቾቻቸው) በጥንቃቄና በትክክል ተተርጉመዋል። ለምሳሌ ያህል በሪቫይዝድ እስታንዳርድ ቨርሽን 1 ዮሐንስ 2:1 እንዲህ ይነበባል፦ “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፣ እርሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” ይኸውም ትርጉም ወዲያውም በ1 ዮሐንስ 3:6 ላይ “በኢየሱስም የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም” ይላል። ታዲያ ማንም የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ኃጢአት የማያደርግ ከሆነ 1 ዮሐንስ 2:1 እንዴት ይሠራል?
ይህንን የሚቃረን የሚመስል ጉዳይ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም እንደሚከተለው በማለት ይፈታዋል። 1 ዮሐንስ 2:1 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ኃጢአት እንዳትፈጽሙ (commit) ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ግን ኃጢአት ቢፈጽም (commit) ከአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ” ነው። ዮሐንስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ግሥ የሚያመለክተው ፍጹማን ባለመሆናችን ሁላችንም አልፎ አልፎ የምናደርገውን ዓይነት አንድን ተደጋጋሚ ያልሆነ ነጠላ ኃጢአትን ነው። ይሁን እንጂ 1 ዮሐንስ 3:6 እንዲህ ይነበባል፦ “በእርሱ የሚኖር ኃጢአትን ልማድ አያደርግም። ማንም ኃጢአትን ልማድ የሚያደርግ አላየውም፤ አላወቀውምም።” እዚህ ላይ ዮሐንስ የተጠቀመበት ግሥ ያንድን ሰው ክርስቲያን ነኝ ብሎ መናገር ዋጋ የሚያሳጣው ቀጣይና ልማደኛ የኃጢአተኝነትን መንገድ ያሁኑን ጊዜም የሚያመለክት ነው።
ሌሎች ምሁራንም ይስማማሉ
የይሖዋ ምሥክሮች የፈለሰፉአቸው ናቸው የተባሉ አንዳንድ ያልተለመዱ አባባሎችም በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ወይም በማመሳከሪያ መጻሕፍት ድጋፍ አግኝተዋል። በሉቃስ 23:43 ላይ ከኢየሱስ ጋር ሞት ለተፈረደበት ወንጀለኛ ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት አዲሲቱ ዓለም ትርጉም እንደሚከተለው አስፍሯቸዋል፦ “ዛሬ እውነት እልሃለሁ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።” በመጀመሪያ ግሪክኛ እንደ ነጠላ ሰረዝ የመሳሰሉ ሥርዓተ ነጥቦች አልነበሩትም። ይሁን እንጂ ሲነበብ ለመረዳት እንዲቻል ሲባል ተርጓሚዎች አንዳንድ ሥርዓት ነጥቦችን ማስገባታቸው የተለመደ ነው። ሆኖም አብዛኞቹ (ትርጉሞች) ሉቃስ 23:43 ኢየሱስና ወንጀለኛው ያንኑ ዕለት ወደ ገነት ሄዱ የሚል ትርጉም እንደሚሰጥ ሆኖ እንዲነበብ አድርገውታል። ኒው ኢንግሊሽ ባይብል እንዲህ ይነበባል፦ “ይህን እልሃለሁ፣ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ።” ይሁን እንጂ ሁሉም ይህን አስተሳሰብ አያስተላልፉም። ፕሮፌሰር ዊልሄልም ሚካኤሊስ ይህን ቁጥር እንዲህ ተርጉመውታል፦ “በእውነት ዛሬውኑ ይህን ዋስትና እሰጥሃለሁ፦ (አንድ ቀን) ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።” ይህ ትርጉም ከኒው ኢንግሊሽ ባይብል ትርጉም ይበልጥ ትክክል ነው። ያን ቀን የሞተው ወንጀለኛ ከኢየሱስ ጋር ወደ ገነት ያንኑ ዕለት ልሄድ አይችልም ነበር። ኢየሱስ ከሞቱ በኋላ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ አልተነሣም ነበር። እስከዚያ ድረስ በሐዴስ ማለትም በሰው ልጆች የጋራ መቃብር ውስጥ ነበር።—ሥራ 2:27, 31፤ 10:39, 40
በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መሠረት ኢየሱስ የጌታን እራት በዓል ሲያቋቁም ለደቀ መዛሙርቱ ስላሳለፈው ቂጣ ማቴዎስ 26:26 እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሥጋዬ ማለት ነው።” አብዛኞቹ ሌሎች ትርጉሞች ግን ይህን ቁጥር “ይህ ሥጋዬ ነው” በማለት ተርጉመውታል። ይህም በጌታ እራት በዓል ወቅት ቂጣው ቃል በቃል ክርስቶስ ሥጋ ይሆናል ብሎ የሚያስተምረውን መሠረተ ትምህርት ለመደገፍ እየተሠራበት ነው። በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ‘ማለት’ ተብሎ የተተረጐመው ቃል (ኤስቲን ኤሜይ የሚለው ቃል ዓይነት ወይም ዝርያ) የመጣው ትርጉሙ ‘መሆን’ ከሚል የግሪክ ቃል ሲሆን ‘ማለት’ የሚል ትርጉም ያመለክታል። በመሆኑም የታየር ግሪክ ሌክሲኮን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ይህ ግሥ ምን ከማለት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ በመግለጽ ትርጉማቸው ‘ማመልከት’ የሆነ ሦስት የተለያዩ የእንግሊዝና ቃላትን ማለትም (to denote, signify, import) ተጠቅመዋል። በእርግጥም እዚህ ላይ ተገቢው ትርጉም ‘ማለት’ የሚለው ቃል ነው። ኢየሱስ የመጨረሻውን እራት በዓል ሲያቋቁም ሥጋው ገና በአጥንቱ ላይ ነበር። ታዲያ እንዴት አድርጐ ነው ቂጣው ቃል በቃል የእርሱ ሥጋ ሊሆን የሚችለው?a
በዮሐንስ 1:1 ላይ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም እንዲህ ይነበባል፦ “ቃልም አምላክ ነበረ።” (እዚህ ላይ አምላክ ለማለት የገባው የእንግሊዝኛው ቃል ‘a god’ ነው።) በብዙ ሌሎች ትርጉሞች ግን ይህ ጥቅስ የተተረጐመው “The Word was God” (“ቃልም እግዚአብሔር ነበር”) ተብሎ ነው። ይህም የስላሴን ትምህርት ለመደገፍ ይሠራበታል። እንግዲያውስ የስላሴ ደጋፊዎች የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምን ቢጠሉት አያስደንቅም። ይሁን እንጂ ዮሐንስ 1:1 ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ አለመሆኑን ለማሳየት ተብሎ በሐሰት ተጣሞ የተተረጐመ አይደለም። የመጀመሪያውን ቋንቋ በትክክል ለመተርጎም የሚጥረው አዓት ገና ከመውጣቱ በፊትም የይሖዋ ምሥክሮች ‘god’ የሚለውን ቃል በትልቁ መጻፍ ትክክል አይደለም ብለው ሲከራከሩ ነበር። አምስት የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችም በተመሳሳይ በዚያ ጥቅስ ላይ ‘a god’ የሚለውን አባባል ተጠቅመዋል።b ቢያንስ 13 ሌሎች ትርጉሞች ‘መለኰት መሳይ’ ወይም ‘አምላክ መሳይ’ በመሳሰሉት አገላለጾች ተጠቅመዋል። እነዚህ አተረጓጐሞች ከሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ይስማማሉ። በሰማይ ሳለ ኢየሱስ ‘a god’ ነው ለማለት ይቻላል ምክንያቱም መለኰታዊ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋና ኢየሱስ አንድ ሕላዌ ወይም አካል ወይም አንድ አምላክ አይደሉም።—ዮሐንስ 14:28፤ 20:17
የአምላክ የግል ስም
በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መሠረት በሉቃስ 4:18 ላይ ኢየሱስ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው” በማለት የኢሳይያስን ትንቢት ጠቅሶ በእሱ ላይ እንደተፈጸመ ገልጾአል። (ኢሳይያስ 61:1) ብዙዎች እዚህ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም መጠቀሱን ይቃወማሉ። ይሁን እንጂ ይህ አዲስ ኪዳን በሚባለው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያ ስም ከሰፈረባቸው ከ200 ከሚበልጡ ቦታዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው። እውነት ነው አሁን በእጅ ካሉት የቀድሞ ‘የአዲስ ኪዳን’ የግሪክኛ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ በማንኛቸውም ላይ የአምላክ የግል ስም አይገኝም። ይሁን እንጂ ምክንያታዊ ባልሆነ ድንገት ደራሽ ፍላጎት ሳይሆን በጠንካራ ምክንያቶች ስሙ በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ገብቷል። ሌሎችም ተመሳሳይ መንገድ ተከትለዋል። በጀርመንኛ ቋንቋ ብቻ 11 ትርጉሞች “ይሖዋ” የሚለውን ስም ወይም “በአዲስ ኪዳን” ጽሑፎች ውስጥ የዕብራይስጡን “ያህዌህ” ቃል በቃል ትርጉም ሲጠቀሙ ሌሎች አራት ትርጉሞች ግን “ጌታ” ከሚለው (የማዕረግ ስም) በማስከተል በቅንፍ ውስጥ ስሙን ይጨምራሉ።c ከ70 በላይ የጀርመንኛ ትርጉሞች በግርጌ ማስታወሻዎቻቸው ወይም ሐተታዎቻቸው ውስጥ ስሙን ተጠቅመውበታል።
በእሥራኤል አገር የአምላክ ስም ያላንዳች ዕገዳ ከሺህ ለሚበልጡ ዓመታት ሰዎች እየጠሩ ሲጠቀሙበት ነበር። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች (በብሉይ ኪዳን) ውስጥ የዚህን ስም ያህል ተደጋግሞ የተጠቀሰ የለም። ሕዝቡ በአጠቃላይ ስሙን አያውቅም ነበር ብሎ ለመከራከር ወይም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የ“አዲስ ኪዳን”), መጻሕፍትን በመንፈስ አነሳሽነትና መሪነት በጻፉበት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የስሙ አጠራር ተረስቶ ነበር ብሎ ለመከራከር አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም።—ሩት 2:4
ውልፍጋንግ ፌኔበርግ ኤንቱስክሉስ/ኦፍን በተባለ የኢየሱሳውያን መጽሔት ላይ (ሚያዝያ 1985) እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፦ “እሱ (ኢየሱስ) ዮድ ሄ ዋው ሄ በተባሉት የዕብራይስጥ ተነባቢያን ፊደላት የሚጻፈውን ያባቱን ስም ለእኛ ለመግለጽ ወደኋላ አላለም። እንዲያውም ለእኛም በአደራ ሰጥቶናል፤ አለበለዚያ ‘ስምህ ይቀደስ’ የሚለውን የጌታ ጸሎት የመጀመሪያውን ልመና ለምን እንዲህ እንደሚነበብ ማብራራት አይቻልም።” ፌኒበርግ ጨምረውም “ከክርስትና ዘመን በፊት በነበሩት የእጅ ጽሑፎች ለግሪክኛ ተናጋሪ አይሁዳውያን በተጻፈው (የዕብራይስጥ ቅዱስ ጽሑፎች) ውስጥ የአምላክ ስም ‘ኪሪዮስ’ (‘ጌታ’) በሚለው የግሪክኛ ቋንቋ አልተተረጐመም ነበር። ከዚህ ይልቅ በአራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት (יהוה) ይጻፍ ነበር። . . . የቤተ ክርስቲያን አበው በጽሑፎቻቸው ውስጥ ስለ ስሙ አውስተው እናገኛለን። ይሁን እንጂ ስለዚህ ስም አልተጨነቁም። ይህን ስም “ኪሪዮስ” (ጌታ) ብለው በመተርጎማቸው እነዚያ የቤተ ክርስቲያን አበው የኪሪዮስን ታላቅነትና ግርማ ለኢየሱስ ክርስቶስ መስጠት ነበር ፍላጎታቸው” በማለት ገልጸዋል። አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ጠንካራና ምሁራዊ በሆነ ምክንያት በመገፋፋት ስሙን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደሚገባው ቦታ መልሶታል።——በባለ ማጣቀሻው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጨማሪ መግለጫ 1Dን ተመልከቱ።
አንዳንዶች በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የአምላክን ስም የተረጐሙበትን በእንግሊዝኛ “ጅሆቫ” (Jehovah) የሚለውን አጠራር ይነቅፋሉ። በእጅ የተጻፉ የዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ ስሙ የተጻፈው በአራት ተነባቢያን ፊደላት ብቻ ስለሆነ (יהוה ዮድ ሄ ዋው ሄ) ብዙዎች ተገቢው አጠራር “ጅሆቫ” ሳይሆን “ያህዌህ” ነው ይላሉ። ስለዚህ “ጅሆቫ” የሚለውን ስም መጠቀም ስህተት ነው ይላሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ምሁራን “ያህዌህ” የመጀመሪያውን አጠራር ይወክላል በሚለው ሐሳብ ስምምነት ላይ አልደረሱም። እውነቱ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙን “ዮድ ሄ ዋው ሄ” በሚሉት ፊደላት ከ6,000 በላይ እንዲገኝ ሲጠብቀው ሙሴ በሲና ተራራ በሰማው መንገድ አጠራሩን ጠብቆ ያላቆየልን መሆኑ ነው። (ዘጸዓት 20:2) ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ትልቁ ነገር የስሙ አጠራር አይደለም ማለት ነው።
በአውሮፓ “ይሖዋ” (“Jehovah”) የሚለው አጠራር ለብዙ መቶ ዓመታት በሰፊው የታወቀና በብዙ መጽሐፍ ቅዱሶችም ውስጥ፣ በአይሁዳውያን ትርጉሞችም ጭምር የተሠራበት ነው። በሕንፃዎች፣ በሳንቲሞች፣ በሌሎች ዕቃዎች ላይ እንዲሁም በጽሑፎችና በብዙ የቤተክርስቲያን መዝሙሮች ላይ ቁጥር ሥፍር በሌለው መጠን ተቀርጾ ይገኛል። ስለዚህ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ስሙን በመጀመሪያው የዕብራይስጥ አጠራር ለማቅረብ ከመሞከር ይልቅ በተጻፈባቸው የተለያዩ ቋንቋዎች በታወቁና ተቀባይነት ባለው መንገድ የአምላክን ስም ተጠቅሟል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም ቢሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሉ ሌሎች ስሞች ላይ የሚያደርጉት ልክ እንዲሁ ነው።
ኃይለኛ ነቀፋው ታዲያ ለምንድን ነው?
የሉተር መጽሐፍ ቅዱስ የተነቀፈው በዘመኑ የነበረውን የተለመደውን ሃይማኖት ድክመቶች ባጋለጠ ሰው ስለተዘጋጀ ነበር። የሱ ትርጉም ተራዎቹ ሰዎች አብዛኛውን እሱ የተናገረውን ነገር እውነትነት እንዲረዱ መንገድ ከፍቶላቸዋል። በተመሳሳይም አዲሲቱ ዓለም ትርጉም የተነቀፈው ብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኙ በግልጽ በሚያስታውቁት በይሖዋ ምሥክሮች ስለታተሙ ነው። አዲሲቱ ዓለም ትርጉምም ሆነ ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ ያረጋግጣል።
እንደ እውነቱ ከሆነ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ምሁራን ያዘጋጁት የትርጉም ሥራ ነው። በ1989 የእሥራኤሉ ፕሮፌሰር ቤንጃሚን ኬዳር እንዲህ አሉ፦ “ከዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስና ትርጉሞች ጋራ በተያያዘ ባደረግሁት የቋንቋ ጥናቴ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም በመባል የሚታወቀውን የእንግሊዝኛ እትም አዘውትሬ እጠቅሳለሁ። እንዲህ ሳደርግም ይህ የትርጉም ሥራ በተቻለ መጠን ትክክለኛ የሆነውን የጽሑፍ መረዳት ለማግኘት የተደረገ ሐቀኛ ጥረት የሚያንጸባርቅ ለመሆኑ የሚሰማኝ ስሜት በተደጋጋሚ ሲረጋገጥ አገኘዋለሁ። ተርጓሚዎቹ የቀድሞው ቋንቋ ሰፊ ችሎታ እንዳላቸው በማሳየት አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ ከዕብራይስጡ ልዩ አቋም ባለመራቅ የቀድሞዎቹን ቃላት ሊገባ በሚችል መንገድ ወደ ሁለተኛ ቋንቋ ተርጉመዋል። . . . ማንኛውም የቋንቋ አነጋገር በተለያዩ መንገዶች ለመተርጎም ያስችላል። ስለዚህ ማንኛውም በቋንቋ የሚፈታ ነገር ክርክር ሊያስነሣ ይችላል። ይሁን እንጂ በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ አንድን የሌለ ነገር ያለአግባብ በጽሑፍ ውስጥ የማስገባት ዓላማ አግኝቼ አላውቅም።”
አዲሲቱ ዓለም ትርጉም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎቹን በዘመናዊ ቋንቋ በትክክል የሚተረጉም ስለሆነ በምድር በሚልዮን የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ይጠቀሙበታል። በአሁኑ ጊዜ መላው መጽሐፍ ቅዱስ በዘጠኝ ቋንቋዎች ሲገኝ ክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ብቻ ደግሞ በሁለት ተጨማሪ ቋንቋዎች ይገኛል። በሌሎች 20 ቋንቋዎች በመዘጋጀት ላይ ነው። ትክክለኛ ትርጉም ከፍተኛ ጥንቃቄ የታከለበት ዓመታት የሚወስድ ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም ገና ሌሎች ብዙዎች “የሕይወትን ቃል” የተሻለ መረዳት እንዲያገኙ ለመርዳት በእነዚህ የተለያዩ ቋንቋዎች ሁሉ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ወጥቶ ለማየት በጉጉት እንጠባበቃለን። (ፊልጵስዩስ 2:16) ይህ ትርጉም ከዚህ በፊት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “የሕይወትን ቃል” በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱት የረዳቸው ስለሆነ በእውነትም ሰዎች እንዲያነቡት ሐሳብ ልናቀርብላቸው እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በራእይ 1:20 ላይ የጀርመንኛ ተርጓሚ ኩርት እስቴጅ ይህንኑ ግሥ እንደሚከተለው ተርጉሞታል፦ “ሰባቱ መቅረዞች ማለት (ኤይንሲ) ሰባቱ ጉባኤዎች ናቸው።” ፍሪዝ ቲልማንና ሉድዊግ ቲምም በተመሳሳይ በማቴዎስ 12:7 ላይ ኤስቲንን ‘ማለት’ ብለው ተርጉመውታል።
b ጃርገን ቤከር፣ ጀረምያስ ፈልቢንገር፣ ኦስካር ሆልዝማን፣ ፍሬዴክ ሪትልሜየርና ሲግፍሬድ እስኩልዝ። ኤሚል ቦክ “መለኰታዊ አካል” ብሎታል። እንዲሁም የዛሬው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (Today’s English Version) አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (The New English Bible) የሞፋት፣ የጉድስፒድ የእንግሊዝኛ ትርጉሞችን ተመልከቱ።
c ጆሃን ባቦር፣ ካርል ኤፍ ባርድት፣ ፔትረስ ዶሽ፣ ዊልሄልም ኤም፣ ኤል ዴዌቴ፣ ጆርጅ ኤፍ ጊሪሲንገር፣ ሄይንሪክ ኤ ደብልዩ ሜዬር፣ ፍሬድሪክ ሙንተር፣ ሴባስትያን ማስቼል፣ ጆሃን ሲ ኤፍ እስኩልዝ፣ ጆሃን ጄ እስቶልዝ፣ እና ዶሚኒክስ ቮን ብሬንታኖ፣ ኦገስት ዳሼል፣ ፍሬድሪክ ሃውክ፣ ጆሃን ፒ ላንጅና ሉድዊግ ሬይን ሃርት ስሙን በቅንፍ ይዘዋል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በሌሎች 20 ቋንቋዎች በመተርጐም ላይ ነው
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ትርጉሙ ራሱን ያስመሰግናል
በጀርመን አገር የሚገኝ አንድ የይሖዋ ምስክር ከአንድ በዕድሜ የገፉ ሴት ጋር ሲነጋገር በዕንባቆም 1:12 ላይ ያለውን እንዲህ የሚለውን ጥቅስ አንብቡ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ከጥንት ጀምሮ አልነበርህምን? አምላኬ ሆይ፣ የእኔ ቅዱስ፣ አንተ አትሞትም።” የእርስዋ መጽሐፍ ቅዱስ “እኛ አንሞትም” ስለሚል ሴትዬዋ ይህን አባባል ተቃወሙ። ምስክሩም አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ከመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ጋር በጣም የሚስማማ እንደሆነ ጠበቅ አድርጐ ገለጸ። ሴትዬዋ ዕብራይስጥ ቋንቋ ይናገሩ ስለነበረ፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ፈልገው አወጡና የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ትክክል እንደሆነ እስኪደነቁ ድረስ እውነትነቱን አረጋገጡ። የአይሁድ ጸሐፊዎች የሆኑት ሶፈሪም የመጀመሪያው ምንባብ ለአምላክ አክብሮት አልሰጠም በሚል ስሜት ከብዙ ጊዜ በፊት ይህንን ጥቅስ ለውጠውት ነበር። ከጥቂቶቹ በስተቀር በጀርመን የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በዚህ ጥቅስ ላይ ማስተካከያ አላደረጉም። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ግን የጥንቱን ጥቅስ እቦታው ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዲሲቱ ዓለም ትርጉም በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በሚከተሉት ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል፦ ዳኒሽ፣ ዳች፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ጣልያንኛ፣ ጃፓንኛ፣ ፖርቹጊዝ እና ስፓኒሽ