-
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ” ናቸው?መጠበቂያ ግንብ—2011 | ነሐሴ 1
-
-
ጴጥሮስ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ነበር?
ካቶሊኮች ቤተ ክርስቲያናቸው በጴጥሮስ ላይ እንደተመሠረተች ለማስረዳት ኢየሱስ በማቴዎስ 16:18 ላይ የተናገረውን “አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚች ዐለት ላይ ጉባኤዬን እገነባለሁ” የሚለውን ሐሳብ ለረዥም ጊዜ ሲጠቅሱ ኖረዋል። እንዲያውም እነዚህ ቃላት በሮም በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ጣሪያ ላይ ከሥር በኩል በላቲን ቋንቋ ተቀርጸዋል።
የተከበረ የቤተ ክርስቲያን አባት የነበረው ኦገስቲን ጉባኤው በጴጥሮስ ላይ እንደተመሠረተ በአንድ ወቅት ያምን ነበር። ይሁን እንጂ በሕይወቱ መገባደጃ ላይ፣ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ የተረዳበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ተገንዘቦ ነበር። ሪትራክቴሽንስ በመባል የሚታወቅ አንድ መጽሐፍ ኦገስቲን ቤተ ክርስቲያን ማለትም የክርስቲያን ጉባኤ የተመሠረተው በጴጥሮስ ላይ ሳይሆን በኢየሱስ ላይ ነው የሚል ሐሳብ አቅርቦ እንደነበር ገልጿል።a
እውነት ነው፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ከሌሎቹ ሐዋርያት ይበልጥ ጎላ ተደርጎ ተጠቅሷል። ኢየሱስ ለየት ባሉ ጥቂት አጋጣሚዎች አብረውት እንዲሆኑ ከሐዋርያቱ መካከል ሦስቱን ማለትም ዮሐንስን፣ ያዕቆብንና ጴጥሮስን ነጥሎ ወስዷቸዋል። (ማርቆስ 5:37, 38፤ 9:2፤ 14:33) ጴጥሮስ፣ በመጀመሪያ ለአይሁድና ወደ ይሁዲነት ለተለወጡ ከዚያም ለሳምራውያን በመጨረሻም ለአሕዛብ ወደ አምላክ መንግሥት የሚያስገባውን በር ለመክፈት የተጠቀመባቸውን “የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች” ከኢየሱስ በአደራ ተቀብሏል። (ማቴዎስ 16:19፤ የሐዋርያት ሥራ 2:5, 41፤ 8:14-17፤ 10:45) ጴጥሮስ ቀልጠፍ ያለ ሰው ከመሆኑ አንጻር ሐዋርያቱን ወክሎ የተናገረባቸው ወቅቶች ነበሩ። (የሐዋርያት ሥራ 1:15፤ 2:14) ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች ጴጥሮስን በዘመኑ የነበረው ጉባኤ ራስ ያደርጉታል?
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ “ለተገረዙት ሐዋርያ ሆኖ እንዲያገለግል” ኃላፊነት እንደተሰጠው ጽፎ ነበር። (ገላትያ 2:8) ይሁን እንጂ በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ጳውሎስ ይህን ሲል ጉባኤው በጴጥሮስ አመራር ሥር እንደሆነ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ጴጥሮስ ለአይሁዳውያን እንዲሰብክ የተሰጠውን የሥራ ድርሻ እየገለጸ ነበር።
ምንም እንኳ ጴጥሮስ ትልቅ ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም የጉባኤው ራስ እንደሆነ አድርጎ መናገሩን የሚያሳይ እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱን ወክሎ ውሳኔ እንዳስተላለፈ የሚጠቁም ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ አናገኝም። ጴጥሮስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ራሱን “ሐዋርያ” እንዲሁም “ሽማግሌ” በማለት ከመጥራት በስተቀር ለየት ባለ የማዕረግ ስም አልተጠቀመም።—1 ጴጥሮስ 1:1፤ 5:1
-
-
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ” ናቸው?መጠበቂያ ግንብ—2011 | ነሐሴ 1
-
-
a ኢየሱስ ከጴጥሮስ ጋር ያደረገው ውይይት ያተኮረው በክርስቶስ ማንነትና በሚጫወተው ሚና ላይ እንጂ ጴጥሮስ በሚኖረው የሥራ ድርሻ ላይ አልነበረም። (ማቴዎስ 16:13-17) ቆየት ብሎም ራሱ ጴጥሮስ ጉባኤው የተገነባበት ድንጋይ ኢየሱስ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 2:4-8) ሐዋርያው ጳውሎስም የክርስቲያን ጉባኤ “የማዕዘኑ የመሠረት ድንጋይ” ጴጥሮስ ሳይሆን ኢየሱስ እንደሆነ አረጋግጧል።—ኤፌሶን 2:20
-