የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ”
    የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
    • “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ”

      8. ሰይጣን በሦስተኛው ፈተና ላይ በእርግጥ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው?

      8 ማቴዎስ 4:8-11⁠ን አንብብ። ሰይጣን በሦስተኛው ፈተና ላይ ስውር ዘዴ መጠቀሙን ትቶ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ተናገረ። ሰይጣን ለኢየሱስ (በራእይ አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም) “የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው”፤ የሚፈጽሙትን መጥፎ ድርጊት ግን አላሳየውም። ከዚያም ኢየሱስን “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው።b አዎ፣ ሰይጣን የፈለገው ዋናው ነገር አምልኮ ነበር! የሰይጣን ዓላማ ኢየሱስ ለአባቱ ጀርባውን እንዲሰጥና እሱን እንደ አምላኩ እንዲመለከተው ማድረግ ነበር። ሰይጣን ለኢየሱስ ያቀረበለት ግብዣ አቋራጭ መንገድ ሊመስል ይችላል። የእሾህ አክሊል ሳይደረግበት፣ ሳይገረፍ እንዲሁም በእንጨት ላይ ተሰቅሎ መሠቃየት ሳያስፈልገው የመንግሥታትን ሥልጣንና ሀብት በሙሉ ማግኘት እንደሚችል በተዘዋዋሪ መንገድ ገለጸለት። ሰይጣን ያቀረበው ግብዣ በእርግጥም የሚፈትን ነበር፤ ምክንያቱም እነዚህ መንግሥታት በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ናቸው። ኢየሱስም ቢሆን ሰይጣን በዓለም መንግሥታት ላይ ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ ጥያቄ አላነሳም! (ዮሐ. 12:31፤ 1 ዮሐ. 5:19) ደግሞም ሰይጣን፣ ኢየሱስ ለአባቱ ንጹሕ አምልኮ ጀርባውን እንዲሰጥ ማድረግ የሚያስችለው እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም ነገር ከመስጠት አይመለስም ነበር።

      አንድ ቤተሰብ የቤተሰብ አምልኮ ሲያደርግ።

      ሣጥን 1ሀ፦ አምልኮ ምንድን ነው?

      9. (ሀ) ሰይጣን ከአምላክ አገልጋዮች የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው? ሊፈትነን የሚሞክረውስ እንዴት ነው? (ለ) የምናቀርበው አምልኮ ምን ነገሮችን ይጨምራል? (“አምልኮ ምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

      9 በዛሬው ጊዜም ሰይጣን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እሱን እንድናመልከው ይፈልጋል። “የዚህ ሥርዓት አምላክ” እንደመሆኑ መጠን በታላቂቱ ባቢሎን የተወከሉት የሐሰት ሃይማኖቶች የሚያቀርቡት አምልኮ በሙሉ ዞሮ ዞሮ የሚቀርበው ለእሱ ነው። (2 ቆሮ. 4:4) ሆኖም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች የሚያቀርቡለት አምልኮ አልበቃው ብሎ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮችም ለአምላክ ፈቃድ ጀርባቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ይፈልጋል። ‘ለጽድቅ ሲሉ መከራ መቀበልን’ የሚጠይቀውን የክርስትና ጎዳና ከመከተል ይልቅ በዚህ ዓለም ውስጥ ሀብትና ሥልጣን ለማግኘት እንድንሯሯጥ ሊያባብለን ይሞክራል። (1 ጴጥ. 3:14) ንጹሕ አምልኮን እንድንተውና የሰይጣን ዓለም ክፍል እንድንሆን በሚቀርብልን ፈተና ከተሸነፍን ሰይጣንን እንደ አምላካችን አድርገን በመቀበል ተደፍተን እንዳመለክነው ይቆጠራል። ታዲያ እንዲህ ያለውን ፈተና መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

      10. ኢየሱስ ለሦስተኛው ፈተና ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? ለምንስ?

      10 ኢየሱስ ለሦስተኛው ፈተና ምላሽ የሰጠው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። ፈታኙን ወዲያውኑ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” በማለት ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። ከዚያም የመጀመሪያዎቹ ሁለት ፈተናዎች በቀረቡለት ወቅት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም መለኮታዊውን ስም የያዘ አንድ ጥቅስ ጠቀሰ፤ ከዘዳግም መጽሐፍ ላይ በመጥቀስ “‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏልና” አለው። (ማቴ. 4:10፤ ዘዳ. 6:13) በዚህ መንገድ ኢየሱስ መከራ የሌለበትና የተደላደለ ሕይወት ለመምራት እንዲሁም ከፍ ያለ ሥልጣን ለማግኘት የሚያስችል ሆኖም ለረጅም ጊዜ የማይዘልቅ አካሄድ እንዲከተል የቀረበለትን ግብዣ ውድቅ አድርጓል። ኢየሱስ፣ ሊመለክ የሚገባው አባቱ ብቻ እንደሆነና ሰይጣንን አንድ ጊዜም እንኳ ‘ተደፍቶ ማምለክ’ የእሱ ተገዢ ከመሆን ተለይቶ እንደማይታይ ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ ከአቋሙ ፍንክች ባለማለት መሠሪ የሆነውን ይህን ፈታኝ አምላኩ አድርጎ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን አሳይቷል። ዲያብሎስም ዕቅዱ እንዳልተሳካለት ሲያይ ኢየሱስን “ትቶት ሄደ።”c

      ሥዕሎች፦ ኢየሱስ የሰይጣንን ፈተና ሲቋቋም። 1. ኢየሱስ በይሁዳ ምድረ በዳ ውስጥ በድንጋዮች መካከል ቁጭ ብሎ ሲያሰላስል። 2. ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አናት ላይ ቆሞ። 3. ኢየሱስ ሰይጣንን በቆራጥነት ‘ከፊቴ ራቅ!’ ሲለው።

      “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

      11. ሰይጣንን መቃወምና የሚያቀርባቸውን ፈተናዎች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

      11 እኛም ሰይጣንን መቃወምና እሱ የሚቆጣጠረው ክፉ ዓለም የሚያቀርብልንን ፈተናዎች መቋቋም እንችላለን። ምክንያቱም እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም የመምረጥ ነፃነት አለን። ይሖዋ ውድ የሆነውን ይህን ስጦታ ሰጥቶናል። በመሆኑም የትኛውም አካል ሌላው ቀርቶ ኃያልና ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ፈታኙ ሰይጣንም እንኳ ንጹሕ አምልኮን እንድንተው ሊያስገድደን አይችልም። ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ‘በእምነት ጸንተን በመቆም ሰይጣንን ስንቃወም’ እኛም “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” እንዳልነው ይቆጠራል። (1 ጴጥ. 5:9) ኢየሱስ በጥብቅ በተቃወመው ጊዜ ሰይጣን ትቶት እንደሄደ አስታውስ። ለእኛም መጽሐፍ ቅዱስ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ያዕ. 4:7

      ፎቶግራፎች፦ ፈተናን መቋቋም። 1. የሆቴል መኝታ ክፍል እያጸዳች ያለች እህት የክፍሉ እንግዶች ጠረጴዛ ላይ የተዉትን ጌጣጌጥ ስታይ። 2. አንድ ወጣት ወንድም ትምህርት ቤት ውስጥ ሁለት ወጣት ሴቶች እያዩት አልፎ ሲሄድ። 3. አንድ ወንድም የቀድሞ ጓደኞቹ አብሯቸው እንዲጠጣ፣ እንዲያጨስና ቁማር እንዲጫወት ጋብዘውት ግብዣቸውን ለመቀበል እንቢ ሲል።

      የሰይጣን ዓለም የሚያቀርባቸውን ፈተናዎች መቋቋም እንችላለን (አንቀጽ 11, 19⁠ን ተመልከት)

      የንጹሕ አምልኮ ጠላት

      12. በኤደን ገነት ውስጥ ሰይጣን የንጹሕ አምልኮ ጠላት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

      12 ሰይጣን ለኢየሱስ ያቀረበለት የመጨረሻው ፈተና የንጹሕ አምልኮ የመጀመሪያ ጠላት እሱ መሆኑን አረጋግጧል። ሰይጣን ለይሖዋ አምልኮ ያለውን ጥላቻ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየው በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በኤደን ገነት ውስጥ ነበር። ሰይጣን ሔዋንን ያታለላት ሲሆን እሷ ደግሞ አዳምን በማግባባት የይሖዋን ትእዛዝ እንዲጥስ አደረገችው፤ በዚህ መንገድ ሰይጣን ሁለቱም በእሱ አገዛዝና ቁጥጥር ሥር እንዲወድቁ አደረገ። (ዘፍጥረት 3:1-5⁠ን አንብብ፤ 2 ቆሮ. 11:3፤ ራእይ 12:9) አዳምና ሔዋን ወደዚህ የተሳሳተ ውሳኔ የመራቸውን አካል ትክክለኛ ማንነት ላያውቁ ቢችሉም ይህ አካል አምላካቸው ሆኗል፤ እነሱም አምላኪዎቹ ሆነዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን በኤደን ዓመፅ እንዲቀሰቀስ በማድረግ የይሖዋን ሉዓላዊነት ማለትም የመግዛት መብት ከመገዳደር አልፎ በንጹሕ አምልኮ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል። እንዴት?

  • “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ”
    የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
    • b አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ሰይጣን የተናገራቸውን ቃላት በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ጥያቄው አዳምና ሔዋን እንደወደቁበት እንደ መጀመሪያው ፈተና . . . ከሰይጣን ፈቃድና ከአምላክ ፈቃድ አንዱን የመምረጥ ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ወይ ለዚህ ወይ ለዚያ አምልኮ ከማቅረብ ጋር የተያያዘ ነው። ሰይጣን ራሱን በእውነተኛው አምላክ ቦታ አድርጎ መመለክ ይፈልጋል።”

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ