-
“መንግሥትህ ይምጣ”የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
-
-
15, 16. “ይህ ትውልድ” የሚለው አነጋገር እነማንን ያመለክታል?
15 ይሁንና የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ ነው? ኢየሱስ መንግሥቱ የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ ለይቶ አልተናገረም። (ማቴ. 24:36) ሆኖም ይህ ጊዜ በጣም መቅረቡን በእርግጠኝነት እንድናምን የሚያስችል ሐሳብ ሰንዝሯል። ኢየሱስ መንግሥቱ የሚመጣው “ይህ ትውልድ” የትንቢታዊውን ምልክት ፍጻሜ ካየ በኋላ መሆኑን አመልክቷል። (ማቴዎስ 24:32-34ን አንብብ።) “ይህ ትውልድ” የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው እነማንን ነው? ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ እስቲ በጥልቀት እንመርምር።
16 “ይህ ትውልድ።” ኢየሱስ ይህን ሲናገር በአእምሮው ይዞ የነበረው አማኝ ያልሆኑ ሰዎችን ነው? አይደለም። ያዳምጡት የነበሩት እነማን እንደነበሩ ተመልከት። ኢየሱስ ይህን ትንቢት የተናገረው “ለብቻቸው ወደ እሱ መጥተው” ለነበሩት ጥቂት ሐዋርያት ነበር። (ማቴ. 24:3) ሐዋርያቱ በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። ደግሞም የጥቅሱን አውድ ልብ በል። ኢየሱስ ስለዚህ “ትውልድ” ከመናገሩ በፊት የሚከተለውን ተናግሯል፦ “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ። በተመሳሳይ እናንተም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደ ደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።” ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ፍጻሜ የሚመለከቱትና ትርጉሙን ይኸውም ኢየሱስ “ደጃፍ ላይ እንደ ደረሰ” የሚገነዘቡት አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ሳይሆኑ ቅቡዓን ተከታዮቹ ናቸው። ስለሆነም ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ብሎ ሲናገር በአእምሮው ይዞ የነበረው ቅቡዓን ተከታዮቹን ነው።
17. “ትውልድ” እና “እነዚህ ነገሮች ሁሉ” የሚሉት አባባሎች ምን ትርጉም አላቸው?
17 “እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ . . . ፈጽሞ አያልፍም።” እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘት የምንችለው “ትውልድ” እና “እነዚህ ነገሮች ሁሉ” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም እንዳላቸው ስናውቅ ነው። “ትውልድ” የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሆኖም በተመሳሳይ ጊዜ ላይ በሕይወት የኖሩ ሰዎችን ነው። የአንድ ትውልድ የጊዜ ርዝመት በጣም ረጅም አይደለም፤ ደግሞም ማብቂያ አለው። (ዘፀ. 1:6) “እነዚህ ነገሮች ሁሉ” የሚለው አገላለጽ ከ1914 እስከ ‘ታላቁ መከራ’ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑትን ኢየሱስ በእሱ መገኘት ወቅት እንደሚፈጸሙ በትንቢት የተናገራቸውን ነገሮች በሙሉ ያካትታል።—ማቴ. 24:21
18, 19. ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ሲል የተናገረውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል? ምን ብለንስ መደምደም እንችላለን?
18 ታዲያ ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ይህ ትውልድ፣ በተመሳሳይ ወቅት የኖሩ ሁለት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድኖችን ያቀፈ ነው፤ የመጀመሪያው ቡድን አባላት በ1914 ምልክቱ መፈጸም ሲጀምር የተመለከቱት ቅቡዓን ሲሆኑ የሁለተኛው ቡድን አባላት ደግሞ ከመጀመሪያው ቡድን ጋር ለተወሰነ ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት የኖሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። ከሁለተኛው ቡድን አባላት መካከል ቢያንስ የተወሰኑት በሕይወት ቆይተው ታላቁ መከራ ሲጀምር ይመለከታሉ። የእነዚህ ሁለት ቡድኖች አባላት እንደ አንድ ትውልድ ሊቆጠሩ ይችላሉ፤ እንዲህ ሊባል የሚችለው በመንፈስ ከተቀቡ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት ላይ የኖሩ በመሆናቸው ነው።c
19 ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ መገኘቱን የሚጠቁመው ምልክት በዓለም ዙሪያ በግልጽ እንደታየ እናውቃለን። እንዲሁም የዚህ “ትውልድ” ክፍል የሆኑት በሕይወት ያሉ ቅቡዓን በዕድሜ እየገፉ እንደሆኑ እየተመለከትን ነው። ይሁንና ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ሁሉም ሞተው አያልቁም። እንግዲያው የአምላክ መንግሥት የሚመጣበትና መላዋን ምድር የሚገዛበት ጊዜ በጣም ቀርቧል ብለን መደምደም እንችላለን! ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ” ብለን እንድንጸልይ ያስተማረን ጸሎት ፍጻሜውን ሲያገኝ መመልከት ምንኛ አስደሳች ይሆን!
-