ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
ኢየሱስ ሕያው ሆነ!
ሴቶቹ የኢየሱስን መቃብር ባዶ ሆኖ ሲያገኙት መግደላዊት ማርያም ለጴጥሮስና ለዮሐንስ ለመንገር ሮጠች። ሌሎቹ ሴቶች ግን እዚያው በመቃብሩ ቦታ እንደቀሩ ግልጽ ነው። ድንገት አንድ መልአክ ብቅ አለና ወደ ውስጥ ገብተው እንዲያዩ ይጋብዛቸዋል።
ሲገቡ እዚያም ሌላ መልአክ ያያሉ። ከመላእክቱ አንዱም ለሴቶቹ “እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና እንደተናገረ ተነሥቷልና በዚህ የለም። የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ከሙታን ተነሣ፤ እነሆም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩ” ይላቸዋል። ስለዚህ በፍርሃትና በታላቅ ደስታም እነዚህ ሴቶች ጭምር ሮጡ።
በዚህ ጊዜ ማርያም ጴጥሮስንና ዮሐንስን አገኘችና፦ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፤ ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም” ብላቸው ነበር። ወዲያውኑ ሁለቱ ሐዋርያት ሮጡ። ዮሐንስ ከጴጥሮስ ጋር ሲወዳደር በዕድሜው ገና ወጣት መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህም መሆን አለበት ቀድሞ ወደ መቃብሩ ስፍራ ደረሰ። እሱ በደረሰበት ሰዓት ሴቶቹ ሄደው ስለነበር ባካባቢው ማንንም አላገኘም። ጎንበስ ብሎም ወደ መቃብሩ ውስጥ ሲመለከት የተልባ እግሩን ልብስ (የኢየሱስ አስከሬን የተጠቀለለበትን) ተመለከተ። ወደ ውስጥ ግን አልገባም።
ጴጥሮስ ሲደርስ ወደ ውስጥ ለመግባት አላመነታም። የተልባ እግር ልብሱንና የኢየሱስ ራስ የተጠቀለለበትን ጨርቅ ያያል። ባንድ ላይ ተጠቅልሎ ተቀምጧል። አሁን ዮሐንስም ወደ መቃብሩ ይገባና ማርያም የነገረቻቸው እውነት መሆኑን ያምናል። ከዚህ በፊት ኢየሱስ ከሙታን እንደሚነሣ አዘውትሮ ይነግራቸው የነበረ ቢሆንም ጴጥሮስም ሆነ ዮሐንስ ኢየሱስ የመነሣቱ ጉዳይ ሊገባቸው አልቻለም። ሁለቱም ግራ ተጋብተው ወደ ቤት ተመለሱ። ማርያምም ወደ መቃብሩ ተመልሳ ስለነበር እዚያው ቆየች።
በዚያኑ ሰዓት ሌሎቹ ሴቶች መላእክቱ እንዳዘዟቸው ኢየሱስ መነሣቱን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየተቻኮሉ ሄደዋል። የሚችሉትን ያህል በፍጥነት ሲሄዱ ሳሉ ኢየሱስ ያገኛቸውና “እንዴት ዋላችሁ” ይላቸዋል። እነርሱም እግሩ ላይ ወድቀው ሰገዱለት። እርሱም “አትፍሩ። ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፤ በዚያም ያዩኛል” አላቸው።
ቀደም ሲል የምድር መናወጥ በሆነና መላእክት በተገለጡ ጊዜ ጠባቂዎቹ ወታደሮች ደንግጠው እንደሞቱ ያህል ሆነው ነበር። ያ ሁኔታ ሲለቃቸው ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች ነገሯቸው። ከአይሁድ ሽማግሌዎች ጋር ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮቹ ጉቦ በመስጠት ጉዳዩን ለማለባበስ ውሳኔ ተደረገ። ወታደሮቹም “እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ” ተባሉ።
የሮማ ወታደሮች በጥበቃ ሥራቸው ላይ እያሉ ተኝተው ከተገኙ በሞት ስለሚቀጡ ካህናቱ “ይህም [መተኛታችሁን የሚገልጸው ሪፖርት] በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደሆነ እኛ እናስረዳዋለን፤ እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን” ብለው ቃል ገቡላቸው። የጉቦው መጠን ከፍተኛ ስለሆነ ጠባቂዎቹ እንደተነገራቸው አደረጉ። በዚህም የተነሣ የኢየሱስ ሥጋ ተሰረቀ የሚለው ወሬ በአይሁዳውያን መካከል በሰፊው ተሰራጨ።
በመቃብሩ ቦታ የቀረችው መግደላዊት ማርያም በኀዘን ተዋጠች። ኢየሱስ የት ይሆን? ወደ መቃብሩ ስታጎነብስ ለሁለተኛ ጊዜ የተገለጡትን ነጭ የለበሱ መላእክት ትመለከታለች። የኢየሱስ ሥጋ ተቀምጦበት በነበረው ስፍራ አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠዋል። “አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት።
ማርያምም “ጌታዬን ወስደውታል። ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም” ብላ መለሰች። ከዚያም ዘወር ስትል “አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ?” ብሎ በድጋሚ የሚጠይቃት ሌላ ሰው ታያለች። ይኸኛው ሰው ደግሞ “ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” ይላታል።
ይህ ሰው መቃብሩ የሚገኝበትን የአትክልት ስፍራ የሚጠብቅ መስሏት “ጌታ ሆይ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ። እኔም እወስደዋለሁ” አለችው።
“ማርያም!” አላት ሰውየው። ወዲያውም ባነጋገሩ ኢየሱስ መሆኑን አወቀች። “ረቡኒ!” (ትርጓሜው መምህር ማለት ነው) ብላ ጮኸች። ወሰን በሌለው ደስታ ተውጣ ልትይዘው እጅዋን ትዘረጋለች። ኢየሱስ ግን “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ [አትጠምጠሚብኝ (አዓት)] ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው” አላት።
አሁን ማርያም ሐዋርያትና ሌሎች ደቀ መዛሙርት ወደ ተሰበሰቡበት ቦታ እየሮጠች ሄደች። ቀደም ሲል ሌሎቹ ሴቶች ኢየሱስን ከሙታን ተነሥቶ እንዳዩት በተናገሩት ትረካ ላይ እሷም የራሷን ቃል ጨመረችበት። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዋን ሴት ወሬ ያላመኑት ደቀ መዛሙርት ማርያምንም ያመኗት አይመስልም። ማቴዎስ 28:3-15፤ ማርቆስ 16:5-8፤ ሉቃስ 24:4-12፤ ዮሐንስ 20:2-18
◆ መቃብሩን ባዶውን ስታገኘው መግደላዊት ማርያም ምን አደረገች? ሌሎች ሴቶችስ ምን አጋጠማቸው?
◆ ጴጥሮስና ዮሐንስ መቃብሩን ባዶውን ሲያገኙት ምን አሉ?
◆ ሌሎቹ ሴቶች የኢየሱስን መነሣት ለደቀ መዛሙርቱ ሊነግሩ ሲሄዱ በመንገዳቸው ላይ ምን አጋጠማቸው?
◆ ጠባቂ ወታደሮቹ ምን አጋጠማቸው? የሆነውን ለካህናቱ ሲነግሩአቸውስ ምን ተደረገ?
◆ መግደላዊት ማርያም ብቻዋን በመቃብሩ ቀርታ ሳለች ምን ሆነ? ደቀ መዛሙርቱ ሴቶቹ የነገሩአቸውን ሪፖርት ከሰሙ በኋላ ምን አሉ?