በሐዋርያት ዘመን የፈነጠቁ የብርሃን ብልጭታዎች
“ብርሃን ለጻድቃን፣ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ።”—መዝሙር 97:11
1. በአሁኑ ወቅት ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች የጥንት ክርስቲያኖችን የሚመስሉት እንዴት ነው?
እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን የመዝሙር 97:11ን ቃላት ምንኛ እናደንቃለን! ለእኛ በተደጋጋሚ ‘ብርሃን ወጥቶልናል።’ በእርግጥም አንዳንዶቻችን የይሖዋን እውቀት ሰጪ ብርሃን ለአሥርተ ዓመታት ተመልክተናል። ይህ ሁሉ “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል” የሚሉትን የምሳሌ 4:18 ቃላት ያስታውሰናል። እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ከወግ ይልቅ ለቅዱሳን ጽሑፎች ከፍተኛ ግምት ስለምንሰጥ የጥንት ክርስቲያኖችን እንመስላለን። የጥንት ክርስቲያኖች የነበራቸውን አመለካከት በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት ከተጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ታሪካዊ መጻሕፍትና ከመልእክቶቻቸው በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
2. የኢየሱስ ተከታዮች መጀመሪያ ከፈነጠቁላቸው የብርሃን ብልጭታዎች አንዱ ምን ነበር?
2 የጥንት የኢየሱስ ተከታዮች ከፈነጠቁላቸው የመጀመሪያዎቹ የብርሃን ብልጭታዎች መካከል ስለ መሢሑ ያገኙት ብርሃን ይገኝበታል። እንድርያስ ለወንድሙ ለስምዖን ጴጥሮስ “መሢሕን አግኝተናል” ሲል ነግሮት ነበር። (ዮሐንስ 1:42) ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስን “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ባለው ጊዜ በሰማይ ያለው አባት ይህን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ምሥክርነት እንዲሰጥ አስችሎታል።—ማቴዎስ 16:16, 17፤ ዮሐንስ 6:68, 69
የስብከት ተልእኳቸውን በተመለከተ የፈነጠቀ ብርሃን
3, 4. ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ የወደፊቱን ሥራቸውን በተመለከተ ለተከታዮቹ ምን የእውቀት ብርሃን ፈንጥቆላቸው ነበር?
3 ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በተከታዮቹ ላይ የተጣለባቸውን ግዴታ በተመለከተ ብርሃን ፈንጥቆላቸው ነበር። “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ያለው በገሊላ ተሰብስበው ለነበሩት 500 ደቀ መዛሙርት ሳይሆን አይቀርም። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:6) ከዚያ በኋላ የክርስቶስ ተከታዮች በሙሉ ሰባኪዎች መሆን ነበረባቸው፤ የስብከት ተልእኳቸውም ‘ለጠፉት የእስራኤል ቤት በጎች’ ብቻ መወሰን አልነበረበትም። (ማቴዎስ 10:6) ሰዎች የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ንስሐ መግባታቸውን የሚያመለክተውን የዮሐንስን ጥምቀትም አያጠምቁም ነበር። ከዚህ ይልቅ ሰዎችን “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” ማጥመቅ ነበረባቸው።
4 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት 11 ታማኝ ሐዋርያቱ “ጌታ ሆይ፣ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ ይህን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት ስለ ስብከት ተልእኳቸው ተጨማሪ መመሪያዎችን ሰጣቸው። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሆነው ቆይተዋል፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ግን የክርስቶስም ምሥክሮች ይሆናሉ።—ሥራ 1:6–8
5, 6. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በጰንጠቆስጤ ዕለት ምን የብርሃን ብልጭታዎች ፈንጥቀውላቸው ነበር?
5 ከአሥር ቀናት በኋላ የኢየሱስ ተከታዮች ደማቅ የብርሃን ብልጭታ ፈንጥቆላቸዋል። በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት በኢዩኤል 2:28, 29 ላይ ያለውን የሚከተለውን ትንቢት ትርጉም ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ አስተዋሉ፦ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ።” የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ በእ ሳት ነበልባል መልክ በሁሉም ማለትም በኢየሩሳሌም ውስጥ በተሰበሰቡት 120 ወንዶችና ሴቶች ራስ ላይ ሲወርድባቸው ተመለከቱ።—ሥራ 1:12–15፤ 2:1–4
6 በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ መዝሙር 16:10 ከሞት በተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደተፈጸመ ለመጀመሪያ ጊዜ በጰንጠቆስጤ ዕለት አስተዋሉ። መዝሙራዊው “[ይሖዋ አምላክ ሆይ] ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም” ብሎ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ እነዚህ ቃላት በንጉሥ ዳዊት ላይ ሊፈጸሙ እንደማይችሉ ተገንዝበው ነበር፤ ምክንያቱም መቃብሩ እስከዚያን ቀን ድረስ በእነሱ ዘንድ ነበር። ይህ አዲስ ብርሃን ሲብራራ የሰሙ 3,000 የሚያህሉ ሰዎች ሙሉ እምነት ስላደረባቸው በዚያው ቀን መጠመቃቸው አያስደንቅም!—ሥራ 2:14–41
7. ሐዋርያው ጴጥሮስ ሮማዊውን መቶ አለቃ ቆርኔሌዎስን ሲጎበኝ ምን ደማቅ ብርሃን ፈንጥቆለት ነበር?
7 እስራኤላውያን ለብዙ መቶ ዘመናት አምላክ “እኔ ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ” በማለት ስለ እነሱ የተናገረውን ቃል ያውቁ ነበር። (አሞጽ 3:2) ስለዚህ ሐዋርያው ጴጥሮስና ወደ ሮማዊው የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ቤት ከእሱ ጋር አብረውት የሄዱት ሌሎች ሰዎች መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ባልተገረዙ አሕዛብ አማኞች ላይ ሲወርድ በተመለከቱ ጊዜ የፈነጠቀላቸው የብርሃን ብልጭታ በእርግጥም ደማቅ ነበር። ከጥምቀት በፊት መንፈስ ቅዱስ የተሰጠበት ጊዜ ይህ ብቻ እንደነበረ ሊስተዋል ይገባል። ይሁን እንጂ ይህ መሆን ነበረበት። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ጴጥሮስ እነዚህ ያልተገረዙ አሕዛብ ለጥምቀት ብቁ ስለመሆናቸው አያውቅም ነበር። ጴጥሮስ የዚህን ክስተት ትርጉም ሙሉ በሙሉ በመገንዘብ “እነዚህ [አሕዛብ] እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማነው?” ሲል ጠየቀ። በእርግጥም በቦታው የነበረ ማንም ሰው ሊቃወም ስላልቻለ እነዚህ አሕዛብ ተጠመቁ።—ሥራ 10:44–48፤ ከሥራ 8:14–17 ጋር አወዳድር።
ግርዘት ቀረ
8. አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች የግርዘትን ትምህርት መተው የከበዳቸው ለምን ነበር?
8 ሌላው የእውነት ደማቅ ብርሃን የፈነጠቀው ከግርዘት ጥያቄ ጋር በተያያዘ መልኩ ነው። የግርዘት ልማድ የጀመረው ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ባደረገበት በ1919 ከዘአበ ነበር። በዚያን ወቅት አምላክ እሱና በቤቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች ወንዶች በሙሉ እንዲገረዙ አብርሃምን አዘዘው። (ዘፍጥረት 17:9–14, 23–27) ስለዚህ ግርዘት የአብርሃም ዘሮች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ሆኖ ነበር። በግርዘት በጣም ይኩራሩ ነበር! በዚህም ምክንያት “ያልተገረዘ” የሚለው ቃል የንቀት መግለጫ ሆኖ ነበር። (ኢሳይያስ 52:1፤ 1 ሳሙኤል 17:26, 27) አንዳንድ የጥንት አይሁድ ክርስቲያኖች ይህ መለያ ምልክት እንዳለ እንዲቀጥል የፈለጉበትን ምክንያት መረዳት አያስቸግርም። አንዳንዶቹ በዚህ ጉዳይ ላይ ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ብዙ ተከራክረው ነበር። ከክርስቲያን ጉባኤ የአስተዳደር አካል ጋር በጉዳዩ ላይ ተነጋግሮ ችግሩን ለመፍታት ጳውሎስና ሌሎች ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ።—ሥራ 15:1, 2
9. በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ላይ እንደተመዘገበው የመጀመሪያው አስተዳደር አካል የተገለጠለት ብርሃን ምን ነበር?
9 በዚህ ወቅት እነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች ግርዘት የይሖዋ አገልጋዮች የሚፈለግባቸው አንዱ ብቃት መሆኑ ያበቃለት ነገር እንደሆነ የሚገልጸውን ብርሃን ያገኙት በተአምር አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እየጨመረ የመጣውን ብርሃን የተቀበሉት ቅዱሳን ጽሑፎችን በመመርመር፣ በመንፈስ ቅዱስ አመራር በመታመንና ያልተገረዙ አሕዛብ ወደ ክርስትና ስለ መለወጣቸው የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ከጴጥሮስና ከጳውሎስ በመስማት ነበር። (ሥራ 15:6–21) በወቅቱ በደብዳቤ የተላለፈው ውሳኔ በከፊል እንዲህ ይነበባል፦ “ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል።” (ሥራ 15:28, 29) በዚህ መንገድ የጥንት ክርስቲያኖች ከግርዘት ትእዛዝና የሙሴ ሕግ ከሚያዛቸው ሌሎች ብቃቶች ነጻ ሆኑ። ስለሆነም ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን” በማለት ሊናገር ችሏል።—ገላትያ 5:1
በወንጌሎች ውስጥ የሚገኝ ብርሃን
10. በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ የተገለጡት አንዳንድ የብርሃን ብልጭታዎች የትኞቹ ናቸው?
10 በ41 እዘአ የተጻፈው የማቴዎስ ወንጌል አንባብያኑን የሚጠቅሙ ብዙ የብርሃን ብልጭታዎች እንዳቀፈ አያጠራጥርም። አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ ሲታይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል ኢየሱስ ሲያስተምር በግለሰብ ደረጃ በቀጥታ ያዳመጡት ጥቂቶች ነበሩ። በተለይ የማቴዎስ ወንጌል የኢየሱስ ስብከት አጠቃላይ መልእክት መንግሥቱ እንደነበር ያጎላል። በተጨማሪም ኢየሱስ ትክክለኛ ዝንባሌ የመያዝን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቶት ነበር። በተራራ ስብከቱ፣ (በምዕራፍ 13 ላይ እንደተመዘገቡት ባሉ) ምሳሌዎቹ እና በምዕራፍ 24 እና 25 ላይ ባለው ታላቅ ትንቢት ምንኛ ደማቅ የሆነ የብርሃን ብልጭታ ፈንጥቋል! በ33 እዘአ የዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ካለፈ ከስምንት ዓመታት በኋላ ገደማ የጥንት ክርስቲያኖች በማቴዎስ ወንጌል ዘገባ አማካኝነት እነዚህን ሐሳቦች በሙሉ እንዲያስቡባቸው ተደርጓል።
11. የሉቃስና የማርቆስ ወንጌሎችን ይዘት በተመለከተ ምን ሊባል ይቻላል?
11 ማቴዎስ ወንጌሉን ከጻፈ 15 ዓመታት ያህል ካለፉ በኋላ ሉቃስ ወንጌሉን ጻፈ። አብዛኛው የወንጌሉ ክፍል ከማቴዎስ ዘገባ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም 59 በመቶው ተጨማሪ ነገሮችን ያካተተ ነው። ሉቃስ በመጽሐፉ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ስድስት የኢየሱስ ተአምራትን የመዘገበ ሲሆን ሌሎች የወንጌል ጸሐፊዎች ከጠቀሷቸው ምሳሌዎቹ በእጥፍ ያህል የሚበልጡ ምሳሌዎችን ዘግቧል። ማርቆስ ኢየሱስ ክርስቶስ የተግባር ሰውና ተአምር ሠሪ መሆኑን በማጉላት ወንጌሉን የጻፈው፣ ሉቃስ ወንጌሉን ከጻፈ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ማርቆስ በአብዛኛው የተረከው ቀደም ሲል ማቴዎስና ሉቃስ የተረኳቸውን ክንውኖች ቢሆንም እነሱ ያልመዘገቡትን አንድ ምሳሌ ጽፏል። ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ላይ መንግሥተ ሰማያትን ቀስ በቀስ ከሚበቅል፣ ከሚያድግና ፍሬ ከሚያፈራ ዘር ጋር አመሳስሏታል።a—ማርቆስ 4:26–29
12. የዮሐንስ ወንጌል ተጨማሪ የእውቀት ብርሃን የሚሰጠው ምን ያህል ነው?
12 ከዚያም ማርቆስ ዘገባውን ከጻፈ ከ30 ዓመታት በላይ ካለፉ በኋላ የዮሐንስ ወንጌል ተጻፈ። ዮሐንስ በኢየሱስ አገልግሎት ላይ በተለይም ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረውን ሕልውና በተመለከተ በጠቀሳቸው መረጃዎች አማካኝነት እንዴት ያለ ብርሃን ፈንጥቋል! ስለ አልዓዛር ትንሣኤ የሚናገረውን ታሪክ የጻፈው ዮሐንስ ብቻ ነበር፣ ከምዕራፍ 13 እስከ ምዕራፍ 17 ባሉት ምዕራፎች ላይ የሰፈሩትን ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ የሰጣቸውን ግሩም ምክሮችም ሆነ አሳልፎ በተሰጠበት ሌሊት የጸለየውን ልብ የሚነካ ጸሎት የገለጸልን እሱ ብቻ ነው። እንዲያውም ከዮሐንስ ወንጌል ውስጥ 92 በመቶው በሌሎች ወንጌሎች ውስጥ አይገኝም ተብሏል።
በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ የሚገኙ የብርሃን ብልጭታዎች
13. አንዳንዶች ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች የላከላቸውን መልእክት እንደ ወንጌል አድርገው የተመለከቱት ለምንድን ነው?
13 በሐዋርያት ዘመን በክርስቲያናዊ ሕይወት ላይ ብርሃን ለመፈንጠቅ በይበልጥ ያገለገለው ሐዋርያው ጳውሎስ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሉቃስ ወንጌሉን በጻፈበት በ56 እዘአ ገደማ ጳውሎስ ለሮማውያን መልእክት ጽፎላቸው ነበር። ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ላይ ጽድቅ የሚገኘው ይገባናል በማንለው የአምላክ ደግነትና በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መሆኑን አጉልቷል። ጳውሎስ ይህን የምሥራቹን ገጽታ ማጉላቱ አንዳንዶች ለሮም ሰዎች የጻፈላቸውን መልእክት እንደ አምስተኛ ወንጌል አድርገው እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል።
14–16. (ሀ) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው የመጀመሪያ መልእክቱ ላይ የአንድነትን አስፈላጊነት በተመለከተ ምን ብርሃን ፈንጥቆ ነበር? (ለ) አንደኛ ቆሮንቶስ ጠባይን በተመለከተ ምን ተጨማሪ ብርሃን ይዟል?
14 ጳውሎስ በቆሮንቶስ ውስጥ የነበሩ ክርስቲያኖች ያስቸግሯቸው የነበሩ አንዳንድ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጽፏል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈላቸው መልእክት እስከ ዘመናችን ድረስ ለክርስቲያኖች ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘ በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ብዙ ምክር ይዟል። በመጀመሪያ ደረጃ በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ እያተኮሩ በቡድን በመከፋፈላቸው የሠሩትን ስሕተት አሳውቋቸዋል። ሐዋርያው “ወንድሞች ሆይ፣ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ” ሲል በድፍረት በመናገር አመለካከታቸውን አስተካክሏል።—1 ቆሮንቶስ 1:10–15
15 በቆሮንቶስ በሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከባድ የጾታ ብልግና በቸልታ ታልፎ ነበር። አንድ ሰው የአባቱን ሚስት አግብቶ ስለ ነበር ‘በአሕዛብ እንኳ የማይገኝ ዝሙት’ ተፈጽሞ ነበር። ጳውሎስ በግልጽ “ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 5:1, 11–13) ይህ ነገር ማለትም ውገዳ ለክርስቲያን ጉባኤ አዲስ ነበር። የቆሮንቶስ ጉባኤ ማስተዋል ያስፈልገው የነበረው ሌላው ጉዳይ ደግሞ አንዳንድ የጉባኤው አባላት ያለባቸውን ቅሬታ ለመፍታት መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውን በዓለማዊ ፍርድ ቤቶች ከማቅረባቸው ጋር የተያያዘ ነበር። ጳውሎስ ይህን በማድረጋቸው በጣም ወቅሷቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 6:5–8
16 ከዚህም ሌላ በጉባኤው ውስጥ የጾታ ብልግና በጣም ተስፋፍቶ ነበር። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 7 ላይ የጾታ ብልግና በመስፋፋቱ ምክንያት እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ቢኖረውና እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ቢኖራት ጥሩ እንደሆነ ጠቁሟል። በተጨማሪም ጳውሎስ ነጠላ የሆነ ሰው ሐሳቡ ብዙም ሳይከፋፈል ይሖዋን ማገልገል የሚችል ቢሆንም ሁሉም ሰው ነጠላ የመሆን ስጦታ እንደሌለው አሳይቷል። ከዚህም ሌላ አንዲት ሴት ባሏ ቢሞትባት “በጌታ ይሁን እንጂ” እንደገና ለማግባት ትችላለች።—1 ቆሮንቶስ 7:39
17. ጳውሎስ በትንሣኤ ትምህርት ላይ ምን ብርሃን ፈንጥቆ ነበር?
17 ጌታ ትንሣኤን በተመለከተ በጣም አስደናቂ የሆኑ የብርሃን ብልጭታዎችን እንዲፈነጥቅ ጳውሎስን ተጠቅሞበታል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚነሡት ምን ዓይነት አካል ይዘው ነው? ጳውሎስ “ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፣ መንፈሳዊ አካል ይነሣል” ሲል ጽፏል። ‘ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ስለማይወርሱ’ ሥጋዊ አካል ወደ ሰማይ አይሄድም። ጳውሎስ ቅቡዓን በሙሉ በሞት እንደማያንቀላፉ ሆኖም በኢየሱስ መገኘት ወቅት የሚሞቱ በቅጽበት ዓይን የማይጠፋ ሕይወት ይዘው እንደሚነሡ አክሎ ተናገረ።—1 ቆሮንቶስ 15:43–53
18. ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች የጻፈላቸው የመጀመሪያ መልእክት የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ምን ብርሃን ይዟል?
18 ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብርሃን ለመፈንጠቅ አገልግሏል። የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ በሌሊት ይመጣል። በተጨማሪም ጳውሎስ “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም” ሲል ገልጿል።—1 ተሰሎንቄ 5:2, 3
19, 20. በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የነበሩ ክርስቲያኖች ጳውሎስ ለዕብራውያን ከጻፈላቸው መልእክት ምን የብርሃን ብልጭታዎችን አግኝተው ነበር?
19 ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን በጻፈው መልእክቱ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ለሚገኙ የጥንት ክርስቲያኖች የብርሃን ብልጭታዎችን ፈንጥቆላቸዋል። የክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት ከሙሴ የአምልኮ ሥርዓት የላቀ መሆኑን በጣም አሳማኝ በሆነ መንገድ ጠቁሟል። ክርስቲያኖች በመላእክት አማካኝነት የተሰጠውን ሕግ ከመከተል ይልቅ ከእነዚህ መላእክታዊ መልእክተኞች በላቀው በአምላክ ልጅ በተነገረው መዳን ላይ እምነት አላቸው። (ዕብራውያን 2:2–4) ሙሴ በአምላክ ቤት ውስጥ አገልጋይ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ በቤቱ ሁሉ ላይ መሪ ነው። ክርስቶስ ከአሮናዊው ክህነት የላቀ ቦታ ያለው እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት ሊቀ ካህን ነው። በተጨማሪም ጳውሎስ እስራኤላውያን እምነትና ታዛዥነት ስላላሳዩ ወደ አምላክ እረፍት እንዳልገቡ ሆኖም ክርስቲያኖች በታማኝነታቸውና በታዛዥነታቸው ምክንያት ወደ እረፍቱ እንደሚገቡ ጠቁሟል።—ዕብራውያን 3:1 እስከ 4:11
20 ከዚህም በላይ አዲሱ ቃል ኪዳን ከሕጉ ቃል ኪዳን የላቀ ነው። በኤርምያስ 31:31–34 ላይ ከ600 ዓመታት ቀደም ብሎ እንደተተነበየው በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የገቡ ሰዎች የአምላክ ሕግ በልባቸው የተጻፈና እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ ያገኙ ናቸው። ክርስቲያኖች ያላቸው ሊቀ ካህን በየዓመቱ ለራሱና ለሕዝቡ የኃጢአት መሥዋዕት የሚያቀርብ ሊቀ ካህን ሳይሆን ኃጢአት የሌለበትና ለአንዴና ለሁልጊዜ የኃጢአት መሥዋዕት ያቀረበው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ መሥዋዕቱን ለማቅረብ የገባው በሰው እጅ ወደ ተሠራች ቅድስት ሳይሆን በይሖዋ ፊት ለመቅረብ ወደ ሰማይ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በሙሴ ሕግ ሥር የነበሩ የእንስሳ መሥዋዕቶች ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ አይችሉም ነበር፤ ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ቢያስወግዱ ኖሮ በየዓመቱ ባልቀረቡ ነበር። ይሁን እንጂ ለአንዴና ለሁልጊዜው የቀረበው የኢየሱስ መሥዋዕት ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። ይህ ሁሉ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ እና ዛሬ ቅቡዓን ቀሪዎችና “ሌሎች በጎች” በሚያገለግሉበት አደባባይ ላይ ብርሃን ፈንጥቋል።—ዮሐንስ 10:16፤ ዕብራውያን 9:24–28
21. በሐዋርያት ዘመን መዝሙር 97:11 እና ምሳሌ 4:18 መፈጸማቸውን በተመለከተ ይህ ትምህርት የጠቆመው ነገር ምንድን ነው?
21 ሐዋርያው ጴጥሮስና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የነበሩት ያዕቆብና ይሁዳ በጻፏቸው መልእክቶች ውስጥ የሚገኙትን የብርሃን ብልጭታዎች የመሳሰሉ ተጨማሪ ምሳሌዎች ለመጥቀስ ቦታ አይበቃንም። ይሁን እንጂ መዝሙር 97:11 እና ምሳሌ 4:18 በሐዋርያት ዘመን አስደናቂ ተፈጻሚነት እንዳገኙ ለማሳየት ቀደም ሲል የተገለጸው ይበቃል። እውነት ከምሳሌነትና ጥላነት ተነሥቶ ፍጻሜ እያገኘና ተጨባጭ እውነታ እየሆነ ሄደ።—ገላትያ 3:23–25፤ 4:21–26
22. ከሐዋርያት ሞት በኋላ ምን ተከሰተ? የሚቀጥለው ርዕስ የሚጠቁመው ምንድን ነው?
22 ከኢየሱስ ሐዋርያት ሞትና አስቀድሞ የተነገረው ክህደት ከጀመረ በኋላ የእውነት ብርሃን እየደበዘዘ መጣ። (2 ተሰሎንቄ 2:1–11) ሆኖም ኢየሱስ በሰጠው ተስፋ መሠረት ጌታው ሲመለስ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለቤተ ሰዎቹ በተገቢው ጊዜ ምግብ ሲያቀርብ አገኘው። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያውን “ባለው ሁሉ ላይ” ሾመው። (ማቴዎስ 24:45–47) ከዚያ በኋላ የፈነጠቁት የብርሃን ብልጭታዎች የትኞቹ ናቸው? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እዚህ ላይ የተጠቀሰው መሬት ክርስቲያኑ ባሕሪውን ለመኮትኮት የሚመርጠውን አካባቢ ያመለክታል።—ሰኔ 15, 1980 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 18–19
ታስታውሳለህን?
◻ እውነትን መረዳት የሚቻለው ደረጃ በደረጃ መሆኑን የሚያሳዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
◻ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገቡት አንዳንድ የብርሃን ብልጭታዎች የትኞቹ ናቸው?
◻ በወንጌሎች ውስጥ ምን ብርሃን ይገኛል?
◻ የጳውሎስ መልእክቶች ምን የብርሃን ብልጭታዎችን ይዘዋል?