ሰው አምላክን ሊመስል የሚችለው እንዴት ነው?
“እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው ታሪክ ከላይ ያለውን ይላል፤ ይሁን እንጂ ይህ ምን ማለት ነው? የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት በአምላክ መልክ የተፈጠሩት እንዴት ነው?—ዘፍጥረት 1:27
በአካላዊ መልካቸው አምላክን ይመስሉ ነበርን? አይደለም። ይህማ ሊሆን አይችልም። ሰው ሰብአዊ ፍጡር፣ ሥጋዊና በምድር ላይ ለመኖር እንዲችል ሆኖ የተፈጠረ ነው። አምላክ መንፈስ ነው፤ ማንም ሰው ሊደርስበት በማይችል በጣም ከፍተኛ በሆነ ሰማያዊ ክብር ይኖራል። (ዘጸአት 33:18–20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50) ታዲያ ሰው በአምላክ መልክ የተፈጠረው እንዴት ነው? ይህ ሲባል ሰው እንደ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ኃይል ያሉትን ጎላ ያሉ የአምላክ ባሕርያትና ሌሎቹን ጭምር እንዲያንጸባርቅ ችሎታ ተሰጥቶታል ማለት ነው።
የይሖዋ ባሕርያት
የይሖዋ አምላክ ባሕርያት በሁሉም የፍጥረት ሥራዎቹ ተንጸባርቀዋል፤ ይሁን እንጂ ከመጀ መሪያዎቹ ሁለት ሰዎች ከአዳምና ከሔዋን ጋር ባደረገው ግንኙነት ግን ይበልጥ አስደናቂ በሆነ መንገድ ታይተዋል። (ሮሜ 1:20) ይሖዋ ምድርን ለሰው መኖሪያ ፍጹም ተስማሚ እንድትሆን አድርጎ በመፍጠሩ ፍቅሩ ታይቷል። ይሖዋ ለአዳም ጓደኛና የልጆቹ እናት የምትሆንለት ፍጹም የሆነች ሚስት ፈጠረለት። ሁለቱንም በጣም ውብ በሆነች ገነት ውስጥ አስቀመጣቸውና በሕይወት ለመቀጠልና ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ አትረፍርፎ ሰጣቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ አምላክ ለዘላለም የመኖር ግሩም አጋጣሚ ሰጥቷቸው ነበር።—ዘፍጥረት 2:7–9, 15–24
የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሰዎች በመፈተኑ የአምላክ ጥበብ ታይቷል። የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባሎች ሆነው ለመቀጠልና የሰብዓዊው ዘር ወላጆች በመሆን ለዘላለም ለመኖር በታማኝነትና በእውነተኛ አምልኮ ምሳሌዎች መሆን ነበረባቸው። ስለዚህ ይሖዋ ተገቢ በሆነ ፈተና የልብ ሁኔታቸውን እንዲያሳዩ አጋጣሚ ሰጣቸው። መልካሙንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብሉ ብሎ ነገራቸው። ይሖዋ ለሰዎች ሊሰጥ አስቦ የነበረውን አስደናቂ መብት ከመስጠቱ በፊት ሰዎች ለእሱ ያላቸውን ታዛዥነትና ፍቅር በዚህ መንገድ እንዲያረጋግጡ መፍቀዱ እንዴት ጥበብ ነው!
ለፍጥረቶቹ ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎችን አውጥቶ እነዚህን የአቋም ደረጃዎች ባለማላላቱ የአምላክ ፍትሕ ታይቷል። አዳምና ሔዋን ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ማንኛውንም አጋጣሚ በመስጠቱ የአምላክ ፍትሕ ታይቷል። እንዲሁም አዳምና ሔዋን ይህን ሳያደርጉ ቀርተው ቢያምፁ ይደርስባቸዋል ብሎ የተናገረውን ቅጣት እንዲቀበሉ በመፍረዱ የአምላክ ፍትሕ ታይቷል።
በመጨረሻም ያስተላለፈውን ፍርድ ተከታትሎ በማስፈጸሙ የይሖዋ ኃይል ታይቷል። ቀንደኛው ዓመፀኛ ሰይጣን ይሖዋ ውሸታም ነው ብሎ ነበር፤ እንዲሁም ሔዋን አምላክን ባትታዘዝ ከፍ ያሉ ነገሮችን እንደሚሰጣት ሰይጣን ቃል ገብቶላት ነበር። (ዘፍጥረት 3:1–7) ይሁን እንጂ ሰይጣን ሔዋንን ከይሖዋ እጅ ሊያድናት አልቻለም። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከዔደን የአትክልት ቦታ እንዳያስወጣቸው ሰይጣን ሊከለክለው አልቻለም። እንዲሁም አምላክ “አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህና” ሲል ለአዳም የተናገራቸው ቃላት ሳይፈጸሙ እንዲቀሩ ለማድረግ አልቻለም። (ዘፍጥረት 3:19) ይሁን እንጂ ይሖዋ የሞት ቅጣቱ ወዲያው እንዲፈጸም አላደረገም፤ በዚህም ይበልጥ ፍቅሩን አሳይቷል። ለሰው ልጆች የነበረው የመጀመሪያ ዓላማው ውሎ አድሮ እንዲፈጸም ሲል አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ ጊዜ ሰጣቸው።—ዘፍጥረት 1:28
በመጨረሻም የሰይጣንን ሥራዎችና በመለኮታዊው አገዛዝ ላይ የተነሣው የመጀመሪያው ዓመፅ ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች የሚሽር ዘር ለመስጠት በገባው ቃል የይሖዋ አምላክ ፍትሕ፣ ፍቅር፣ ኃይልና ጥበብ ታይቷል። (ዘፍጥረት 3:15) እንዴት አስደናቂ የሆነ አምላክ አለን!
አምላክን ለመምሰል የሚደረጉ ጥረቶች
ምንም እንኳን ሰዎች ፍጹም ባይሆኑም አሁንም የአምላክን ባሕርያት ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። ስለሆነም ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን ክርስቲያኖች “እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትመስሉ ሁኑ” በማለት አበረታቷቸዋል። (ኤፌሶን 5:1) ይሁን እንጂ በታሪክ ሂደት እንደታየው አብዛኞቹ ሰዎች ለአምላክ ባሕርያት ከፍተኛ ንቀት አሳይተዋል። በኖኅ ዘመን ሰዎች በጣም ተበላሽተው ስለነበረ ይሖዋ ከኖኅና ከቤተሰቡ በስተቀር ሁሉንም የሰው ዘር ለማጥፋት ወሰነ። ኖኅ “በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም [የፍትሕ] ሰው” ነበረ። ኖኅ የአምላክን ትዕዛዝ በመፈጸም ለአምላክ ያለውን ፍቅር አሳይቷል።a “ኖኅም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:9, 22) ኖኅ ‘የጽድቅ ሰባኪ’ በመሆን ለሰዎች ያለውን ፍቅርና ምን ያህል ፍትሕን እንደሚወድ አሳይቷል። (2 ጴጥሮስ 2:5) ኖኅ የአምላክን መመሪያ ለመፈጸም አንድ ግዙፍ መርከብ በመሥራት፣ በመርከቡ ውስጥ ምግብ በማከማቸት፣ እንስሳትን ወደ መርከቡ በማስገባትና በይሖዋ ትዕዛዝ ወደ መርከቡ በመግባት አካላዊ ኃይሉን በተገቢው መንገድ ተጠቅሞበታል፤ እንዲሁም ጥበብ አሳይቷል። በተጨማሪም በአካባቢው የነበሩ ክፉ ሰዎች እንዲያበላሹት ባለመፍቀድ ለጽድቅ ያለውን ፍቅር አሳይቷል።
መጽሐፍ ቅዱስ በተመሳሳይ አምላካዊ ባሕርያትን ያንጸባረቁ ብዙ ሌሎች ሰዎችንም ይገልጻል። ከእነዚህም ዋነኛው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ፍጹም አምላክን ስለመሰለ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ለማለት ችሏል። (ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ ካሳያቸው ባሕርያት የላቀው ፍቅር ነው። ለአባቱና ለሰዎች የነበረው ፍቅር ሰማያዊ መኖሪያውን እንዲተውና ሰው ሆኖ በምድር ላይ እንዲኖር ገፋፍቶታል። ፍቅር በጽድቅ አኗኗሩ አባቱን ከፍ ከፍ እንዲያደርግና የመዳንን ምሥራች ለሰዎች እንዲሰብክ አነሳስቶታል። (ማቴዎስ 4:23፤ ዮሐንስ 13:31) ከዚያም ኢየሱስ ለሰው ልጆች መዳንና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለአምላክ ስም መቀደስ ሲል ፍጹም ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንዲሰጥ ያነሣሣው ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 13:1) አምላክን ለመምሰል በምናደርገው ጥረት ልንከተለው የሚገባ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሻለ ምሳሌ ይኖራልን?—1 ጴጥሮስ 2:21
ዛሬ አምላክን ይበልጥ ለመምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
ዛሬ የአምላክን ባሕርያት ለማንጸባረቅና በአምላክ መልክ ለመመላለስ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ የፍቅርን ባሕርይ እንውሰድ። ኢየሱስ “ጌታ [ይሖዋ አዓት] አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” ብሏል። ለአምላክ ፍቅር የምናሳየው እንዴት ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።”—ማቴዎስ 22:37፤ 1 ዮሐንስ 5:3
እርግጥ ነው የይሖዋን ትእዛዛት ለማክበር ትእዛዛቱን ማወቅ አለብን። ይህም የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብ፣ ማጥናትና ማሰላሰልን ይጨምራል። “አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው” እንዳለው መዝሙራዊ ለማለት መቻል ይኖርብናል። (መዝሙር 119:97) የአምላክን ቃል ይበልጥ በጥልቀት እየተረዳነው በሄድን መጠን በአምላክ አስተሳሰብ እየተሞላን እንሄዳለን። ጽድቅን መውደድና ዓመፅን መጥላት እንጀምራለን። (መዝሙር 45:7) አዳም የተሳሳተው እዚህ ላይ ነበር። የይሖዋን ሕግ ያውቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሕጉን አጥብቆ ለመያዝ የሚያስችለው ለሕጉ በቂ ፍቅር አልነበረውም። የአምላክን ቃል በምናነብበት ጊዜ ዘወትር ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ አለብን ‘ይህ በእኔ ላይ ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው? ጠባዬ ከአምላክ ባሕርያት ጋር ይበልጥ እንዲስማማ ምን ላደርግ እችላለሁ?’
በተጨማሪም ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” ብሏል። (ማቴዎስ 22:39) ማንኛውም ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ራሱን ይወድዳል፤ እንዲሁም ለራሱ የተሻለውን ነገር ይፈልጋል። ይህ ስህተት አይደለም። ይሁን እንጂ ለባልንጀራችን ተመሳሳይ የሆነ ፍቅር እናሳያለንን? “ለተቸገረ ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፤ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ እንከተላለንን?—ምሳሌ 3:27፤ ገላትያ 6:10
የጥበብ ባሕርይን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? ይህን ባሕርይ ለማሳየት ያለን ፍላጎት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ማጥናት ይመራናል፤ ምክንያቱም የመለኮታዊ ጥበብ ጎተራ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መዝሙር 119:98–100 እንደሚከተለው ይነበባል፦ “ለዘላለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ።” በምሳሌ 3:18 ላይ ጥበብ እንደ ‘ሕይወት ዛፍ’ ተደርጋ ተገልጻለች። ጥበብ ካገኘንና ያገኘነውን ጥበብ ከሠራንበት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነትንና የዘላለም ሕይወት ሽልማትን እናገኛለን።—መክብብ 7:12
ፍትሕን በተመለከተስ? በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ አምላክን ለሚያስደስቱ ሰዎች ፍትሕ የግድ አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ጽድቅን (ፍትሕን) ይወድና ዓመፅን ይጠላ ነበር። (ዕብራውያን 1:9) ዛሬም ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ። ፍትሕ ትክክለኛ የሆኑ ባሕርያትን እንዲወዱ ይገፋፋቸዋል። ከዚህ ዓለም የዓመፅ መንገዶች ይርቃሉ። እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ በሕይወታቸው ውስጥ ዋናው ነገር እንዲሆን ያደርጋሉ።—1 ዮሐንስ 2:15–17
ኃይልን በተመለከተ ደግሞ ሁላችንም የተወሰነ ኃይል አለን። በተፈጥሯችን አካላዊና አእምሯዊ ኃይል አለን፤ ክርስቲያናዊ እድገት በምናደርግበት ጊዜ ደግሞ መንፈሳዊ ኃይል እናዳብራለን። ምንም እንኳን ደካማ ብንመስልም ፈቃዱን ለመፈጸም እንድንችል ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ኃይላችንን ከፍ ያደርገዋል። ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:13) እኛም የይሖዋ መንፈስ እንዲሰጠን ከጸለይን ተመሳሳይ ኃይል ማግኘት እንችላለን።
ምሥራቹን መስበክ
አራቱን የአምላክ ዋና ዋና ባሕርያት ማሳየታችን በሚገባ የሚታየው የሚከተለውን ትእዛዝ ስንፈጽም ነው፦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) እንዲህ ዓይነቱ የማስተማር ሥራ ለሚቀበሉት ሰዎች ሕይወት ያስገኝላቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ምንም ለማናውቃቸው ሰዎች እንዲህ ማድረጉ እንዴት ያለ ግሩም የሆነ የፍቅር መግለጫ ነው!
ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት የጥበብ መንገድ ነው። ጸንቶ የሚቆይ ፍሬ ያስገኛል። “ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና” ሊባልለት የሚችል ምን ሌላ ሥራ ይኖራል? (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚከስሩ ሰዎች የሉም። የሚሰሙትም ሆኑ የሚያስተምሩት ዘላለማዊ በረከቶችን ያገኛሉ።
ፍትሕን በተመለከተ ክርስቲያኖች ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸው ፍትሐዊና ጻድቅ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያስተምሯቸዋል። “የፍርድ [የፍትሕ] አምላክ” የሆነውን ይሖዋን እንዲያገለግሉ እየረዳናቸው ነው። (ሚልክያስ 2:17) ዛሬ ይሖዋን ለማገልገል ራሳቸውን የወሰኑና በታማኝነት የሚመላለሱ ሁሉ ይሖዋ እንደ ጻድቃን አድርጎ የሚቆጥራቸውና ከአርማጌዶን የሚተርፉ ይሆናሉ።—ሮሜ 3:24፤ ያዕቆብ 2:24–26
ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ መስበክና ማስተማር ከፍተኛ የሆነ የኃይል መግለጫ ነው። (ማቴዎስ 24:14) አብዛኛው ሰው መስማት በማይፈልግባቸው የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ያለማቋረጥ መስበክ ጽናትን ይጠይቀል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እስከ መጨረሻው ድረስ ለመጽናት የሚያስፈልገውን ኃይል ይሰጣል።—ኢሳይያስ 40:30, 31፤ ማቴዎስ 24:13፤ ሉቃስ 11:13
እውነት ነው፤ ፍጽምና የሌለን የአዳም ልጆች እንደመሆናችን መጠን እነዚህን ግሩም ባሕርያት በፍጽምና ደረጃ ለማንጸባረቅ አንችልም። ይሁን እንጂ ሰው በአምላክ መልክ እንደተሠራ አስታውስ። ይበልጥ አምላክን ለመምሰል ከጣርን የተፈጠርንበትን ዓላማ በከፊል እየፈጸምን ነው። (መክብብ 12:13) የተቻለንን ያህል መልካም ለማድረግ ጥረት ካደረግንና በምንሳሳትበት ጊዜ ይቅርታ ከጠየቅን ከጥፋት ተርፈን ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ወደምንደርስበት ወደ አምላክ አዲስ የጽድቅ ሥርዓት ለመግባት ተስፋ ልናደርግ እንችላለን። ከዚያ ሁሉም የይሖዋ አምላክን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ የሚያንጸባርቁ ፍጹም የሆኑ ሰዎች በሚኖሩባት ምድራዊ ገነት ውስጥ እንኖራለን። እንዴት የሚያስደስት ነው! በመጨረሻም ሰዎች አምላክን ሙሉ በሙሉ ይመስላሉ ብሎ መናገር ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ራይቸስ” እና “ጀስት” የሚሉት የእንግሊዝኛ ቃላት በጣም የተቀራረበ ትርጉም አላቸው። በግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ኪካይኦስ በሚለው ቃል ተገልጿል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋን መለኮታዊ ባሕርያት እንዴት መኮትኮት እንደሚቻል ኢየሱስ አሳይቶናል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጨረሻ ሰዎች ሙሉ በሙሉ አምላክን የሚመስሉ ይሆናሉ