በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኩት የተባረከ፣ አስደሳች ሕይወት
ሊዮ ካልዮ እንደተናገረው
ጊዜው 1914 ነው። በፊንላንድ ተርኩ ተብላ በምትጠራው ከተማ ዳር በሚገኘው አካባቢያችን ውብ የሆነ አንድ የበጋ ቀን ወደ መገባደዱ ተቃርቧል። ጦርነት መነሣቱን በሚገልጸው ዜና በድንገት የአካባቢው ሰላም ተበጠበጠ። ወዲያው ጎዳናዎቹ ሁሉ በተከሰቱት ሁኔታዎች ምክንያት በሐሳብ በተዋጡ ሰዎች ተሞሉ። እኛ ልጆች የትልልቅ ሰዎችን በጭንቀት የተዋጠ ፊት በማየት ምን ሊመጣ ይሆን እያልን እናስብ ነበር። በዚያን ጊዜ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበርኩ። ሰላማዊው የልጆች ጨዋታ ወደ ጦርነት ጨዋታ ሲለወጥ ትዝ ይለኛል።
ፊንላንድ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት (1914–18) ገለልተኛ ሆና ብትቆይም በ1918 በተነሣው የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ደርሶባታል። ዘመዳሞች እንዲሁም ቀድሞ ጓደኛሞች የነበሩ ሰዎች ባላቸው የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት የተነሳ እርስ በርሳቸው ተጨፋጭፈዋል። ሰባት አባላት ያሉት የእኛ ቤተሰብም የእንዲህ ዓይነቱ ጥላቻ ገፈት ቀማሽ ሆኗል። የተሰማውን ፊት ለፊት የሚናገረው አባቴ ተያዘና የሰባት ዓመት እሥራት ተፈረደበት። ከጊዜ በኋላ በነፃ ተለቀቀ። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ ጤንነቱ ተቃውሶ ነበር።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ቤተሰባችን በረሀብና በበሽታ ተሠቃይቷል። ሦስት ታናናሽ እኅቶቼ ሞቱ። በታምፐር ከተማ የሚኖረው የአባቴ ታላቅ ወንድም የደረሰብንን አሳዛኝ ሁኔታ ሲሰማ አባትና እናቴ እንዲሁም የቀረነው ሁለት ልጆች አብረነው እንድንቀመጥ ጠራን።
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በታምፐር እያለን ሲልቪያ ከምትባል ከአንዲት ቆንጆ ልጃገረድ ጋር ተዋወቅሁ። እሷም ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አስተዳደግ አላት። አባቷ በእርስ በርሱ ጦርነት ተገድሏል፤ ከዚያም የቤተሰቧ የቅርብ ወዳጅ የሆነው ካርሎ (ካል) ቬሳንቶ እሷን፣ ታላቅ እኅቷንና እናቷን ከፖሪ ከተማ እሱ ጋ እንዲቀመጡ ወሰዳቸው። የሲልቪያ እናት ሥራ እንድታገኝና ሁለቱ ሴቶች ልጆች ደግሞ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ዝግጅት አደረገ። ከጊዜ በኋላ ሲልቪያ ሥራ ለማግኘት ወደ ታምፐር መጣች። እዚያም ከእኔ ጋር ተገናኘን።
ሕይወቴን የለወጠው ምሽት
በ1928 ሲልቪያ እጮኛዬ ሆነች። ከዚያም አንድ ቀን እኔና ሲልቪያ ካል ቬሳንቶንና ቤተሰቡን ለመጠየቅ ወደ ፖሪ ሄድን። እንደዚያ አድርጎ ሕይወቴን በጣም የነካኝ ወሳኝ አጋጣሚ የለም። ካል የሰጋር ፈረሶች ባለቤትና የፈረስ ግልቢያ ተወዳዳሪ ነበር። ይሁን እንጂ ካል ይህን ሥራ ተወና እሱና ሚስቱ የመንግሥቱ ምሥራች ቀናተኛ አስፋፊዎች ሆኑ። ካል “አሁን በሕይወት ከሚኖሩት መካከል በፍጹም ሞትን የማያዩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይኖራሉ።” የሚሉትን ቃላት ሁለት ፎቅ ባለው መኖሪያ ቤቱ በውጭ ግድግዳው ላይ በትልቁ እንዲጽፉለት ሰዎችን እንደቀጠረ የ1990 የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ ይገልጻል። ጥቅሱ በትልቁ ስለተጻፈ በፍጥነት አልፈው ከሚሄዱት ባቡሮች ላይ ሆኖ በቀላሉ ይነበባል።
በዚያ ምሽት ካልና እኔ እስኪነጋ ድረስ ተነጋገርን። እኔ “ለምን? ለምን? ለምን?” እያልኩ እጠይቅና ካል ደግሞ ያብራራ ነበር። በአንድ ሌሊት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ እውነቶች ተማርኩ። የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያብራሩትን ጥቅሶች ጻፍኳቸው። ከዚያም ወደ ቤት እንደተመለስኩ የማስታወሻ ደብተር አመጣሁና እነዚያን ጥቅሶች በሙሉ አንድ በአንድ ገለበጥኳቸው። እኔ ራሴ ለመጽሐፍ ቅዱስ ገና አዲስ ስለሆንኩ በምሠራበት የግንባታ ቦታ ለሚሠሩት ሰዎች ለመመስከር በዚህ የማስታወሻ ደብተር እጠቀም ነበር። የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን በማጋልጥበት ጊዜ “ጓደኞቼ በእርግጥ ተታልላችሁ ነበር” በማለት የካልን ቃላት ብዙ ጊዜ እደጋግም ነበር።
ካል በታምፐር ከተማ ወደ 30 የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የሚሰበሰቡባትን የአንዲት ጎጆ አድራሻ ሰጠኝ። እዚያም የጎጆ ቤቷ ባለቤት ከሆነው ከወንድም አንደርሰን ቀጥሎ በሩ አጠገብ አንድ ማዕዘን አጠገብ ቁጢጥ ብዬ ተቀመጥሁ። በስብሰባ ላይ የምገኘው አልፎ አልፎ ነበር። ይሁን እንጂ ጸሎት በጣም ጠቃሚ ሆኖ አገኘሁት። አንድ ጊዜ በሥራ ቦታ ችግር አጋጠመኝና “እባክህ አምላኬ ይህን ችግር እንድወጣው ከረዳኸኝ እያንዳንዱን ስብሰባ አዘውትሬ ለመካፈል ቃል እገባለሁ” ስል ጸለይኩ። ይሁን እንጂ ነገሮች ይበልጥ ተባባሱ። ከዚያም ይሖዋን እንዲህ ካደረግክልኝ እንዲህ አደርጋለሁ እያልኩት እንደሆነ ተገነዘብኩ። ስለዚህ እንደሚከተለው በማለት መጸለይ ጀመርኩ፦ “የፈለገው ነገር ቢሆን ከእያንዳንዱ ስብሰባ ላለመቅረት ቃል እገባለሁ።” በዚህ ጊዜ ችግሮቼ ሁሉ ተቃለሉልኝ፤ እኔም አዘውትሬ መሰብሰብ ጀመርኩ።—1 ዮሐንስ 5:14
አገልግሎታችንን የጀመርንባቸው ዓመታት
በ1929 ሲልቪያና እኔ ተጋባን። ሁለታችንም በ19 34 ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንን በውኃ ጥምቀት አሳየን። በዚያን ጊዜ የነበረው አገልግሎታችን የሸክላ ማጫወቻዎችንና ንግግር የተቀረጸባቸውን ሸክላዎች ወደ ሰዎች ቤት ይዞ በመሄድ ከክፍያ ነፃ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ልናሰማቸው እንደምንችል በደግነት መጠየቅን ይጨምር ነበር። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ወዲያው ወደ ቤት እንድንገባ ይጋብዙናል። ከዚያም በሸክላ የተቀዳውን ንግግር ካዳመጡ በኋላ ያወያዩንና አንዳንድ ጽሑፎቻችንን ይወስዱ ነበር።
በባለ ሥልጣኖች ፈቃድ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች በድምፅ ማጉያ በየመናፈሻዎቹ እናሰማ ነበር። ከተማ ዳር ባሉት አካባቢዎች ደግሞ የድምፅ ማጉያውን ጣሪያ ላይ ወይም ጭስ ማውጫው ላይ እንሰቅለዋለን። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የከተማው ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡበት ሐይቅ አካባቢ እነዚህን ንግግሮች እናሰማለን። በጀልባ ላይ ድምፅ ማጉያ እንይዝና በሐይቁ ዳር በዝግታ እየቀዘፍን እንሄዳለን። እሁድ እሁድ በገጠር አካባቢዎች ለመስበክ ውድ የሆኑ ድምፅ ማጉያዎቻችንና ብዙ ጽሑፎችን ይዘን በአውቶቡስ እንጓዛለን።
እምነታችንን የሚፈትን ለውጥ
በ1938 አቅኚ በመሆን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባሁ። ይሁን እንጂ የጡብ ግንባታ ሥራዬንም ቀጥዬ ነበር። ቀጥሎ ባለው የጸደይ ወቅት ተጓዥ አገልጋይ እንድሆን ከማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ አንድ ጥሪ ቀረበልኝ። ይህም አሁን የክልል የበላይ ተመልካች ተብሎ የሚጠራው ነው። ይህን ግብዣ ለመቀበል መወሰኑ በጣም ከባድ ነበር። ምክንያቱም በታምፐር በሚገኘው ጉባኤያችን ውስጥ ማገልገል በጣም ደስ ይለኝ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ እኛ የራሳችን ቤትና በቅርቡ ትምህርት የሚጀምር አርቶ የሚባል የስድስት ዓመት ልጅ ነበረን። እንዲሁም ሲልቪያ በሱቅ ውስጥ የአሻሻጭነት ሥራዋን ትወደው ነበር። ይሁን እንጂ አብረን ከተመካከርን በኋላ ይህን የመንግሥቱን ተጨማሪ የአገልግሎት መብት ተቀበልኩ።—ማቴዎስ 6:33
ከዚያም ሌላ አስቸጋሪ የሆነ ወቅት ጀመረ። የሶቪዬት ወታደሮች ፊንላንድን በመውረራቸው ኅዳር 30, 1939 ጦርነት ተነሣ። የቀዝቃዛው ክረምት ጦርነት እየተባለ የሚጠራው ይህ ጦርነት ፊንላንድ የሰላም ውል ስምምነት ለማድረግ እስከተገደደችበት እስከ መጋቢት 1940 ድረስ ቀጥሎ ነበር። ትዝ ይለኛል፤ በዚያን ጊዜ የነበረው ክረምት እጅግ በጣም ቀዝቃዛ ስለነበረ ተፈጥሮም ለውጊያው የተዘጋጀ ይመስል ነበር። የቅዝቃዜው መጠን ከዜሮ በታች 30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ቢሆንም በብስክሌት ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው ጉባኤ እጓዝ ነበር።
በ1940 በፊንላንድ የይሖዋ ምስክሮች ሥራ ታገደ። ከዚያም ብዙ የፊንላንድ ወጣት ምስክሮች ታሰሩና ሰብአዊነት በሌለባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ይማቅቁ ነበር። ከ1939 እስከ 1945 ድረስ በተደረገው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሁሉ ጉባኤዎችን ለማገልገል ቻልሁ። ይህም ለብዙ ወራት ከሲልቪያና ከአርቶ ተለይቼ እንድቆይ ያደርገኝ ነበር። ከዚህም በላይ ሕጋዊ ያልሆነ ሥራ ትሠራለህ በሚል እያዛለሁ የሚል የማያቋርጥ ስጋት ነበረብኝ።
አንድ የጠበቃ ቦርሳ፣ አንድ ጽሑፎችን የያዘ ቦርሳ እንዲሁም የሸክላ ማጫዎቻና የሸክላ ክሮችን ጭኜ በብስክሌት ስሄድ እንግዳ ነገር ሳልመስል አልቀርም። ሸክላዎችን ይዤ የምሄድበት አንዱ ምክንያት ድንገት ብያዝ እንኳን አካባቢውን ለመቃኘት ከአውሮፕላን በጥላ የወረድኩ የሩሲያውያን ሰላይ እንዳልሆንኩ ለማረጋገጥ ነው። በጥላ የዘለልኩ ሰላይ ብሆን ኖሮ በምዘልበት ጊዜ ሸክላዎቹ ይሰባበሩ ነበር ብዬ ለመከራከር እችላለሁ።
ሆኖም አንድ ጊዜ አንድ ሰላይ አለ የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው በነበሩ አካባቢዎች ያሉ ሰዎችን እየጠየቅሁ ሳለ አንድ የይሖዋ ምስክሮች ቤተሰብ ሰላይ መሰልኳቸው። ጭልም ባለው የክረምት ምሽት በራቸውን አንኳኳሁ፤ እነሱ ግን ለመክፈት በጣም ፈሩ። ስለዚህ የከብቶች በረት ውስጥ አደርኩ። እንዲሞቀኝ ለማድረግ ድርቆሽ ውስጥ ገብቼ ተኛሁ። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ማንነቱ ሳይታወቅ የቀረው ሰው ማንነት ታወቀ። ከዚያ በኋላ ልጠይቃቸው በሄድኩ ቁጥር ቤተሰቡ በሙሉ በጣም የተለየ መስተንግዶ ያደርግልኛል።
በጦርነቱ ወቅት በሰሜናዊና በመካከለኛው ፊንላንድ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ የምናገለግለው ወንድም ዮሐንስ ኮስኪነንና እኔ ብቻ ነበርን። እያንዳንዳችን እንድናገለግልበት የተሰጠን ክልል በጣም ሰፊ ነበር። ርዝመቱ ወደ 600 ኪሎ ሜትር ይደርስ ነበር። በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ ለሁለት ወይም ለሦስት ቀን ብቻ በመቆየት ጉብኝት የምናደርግላቸው በጣም ብዙ ጉባኤዎች ነበሩን። ባቡሮች ብዙውን ጊዜ በሰዓቱ አይገኙም፤ ያሉት አውቶቡሶች ደግሞ ጥቂት ስለነበሩና ሰው በጣም ስለሚበዛባቸው የምንፈልገው ቦታ መድረሳችን አስደናቂ ነበር።
ለትንሽ ከአደጋ አመለጥን
አንድ ጊዜ የቀዝቃዛው ክረምት ጦርነት እንደጀመረ አካባቢ በሄልሲንኪ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ሄድኩና በባቡር ይዤ በመሄድ ለጉባኤዎች ለማድረስ የታገዱ ጽሑፎችን የያዙ አራት ከባድ ካርቶኖችን ወሰድኩ። በሪሂማኪ ባቡር ጣቢያ ሳለሁ ከአውሮፕላን ላይ የቦምብ ድብደባ ሊጀምር መሆኑን የሚያስጠነቅቅ ድምፅ አስተጋባ። በባቡሩ ውስጥ የነበሩት ወታደሮች የበረዶ ልብሳቸውን ለበሱ፤ መንገደኞችም በፍጥነት ከባቡሩ እንዲወጡና ከጣቢያው ፊት ለፊት ወዳለው ባዶ ሜዳ እንዲሄዱ ተነገራቸው።
እኔ የያዝኳቸው ካርቶኖች በጣም ውድ ዕቃ ይዘዋል በማለት ወታደሮቹ እንዲይዙልኝ ጠየቅኋቸው። አራቱም ወታደሮች አንዳንድ ካርቶን ያዙልኝና በበረዶ ወደተሸፈነው ሜዳ 200 ሜትር ያህል ሮጥን። ከዚያም መሬት ላይ ለጥ አልን። “ስማ አንተ ሲቪል እንዳትንቀሳቀስ! ቦምብ የሚጥሉት አውሮፕላኖች እቅስቃሴ ካዩ በቦምብ ይደበድቡናል” ሲል አንድ ሰው ወደ እኔ ተጣራ። ወደ ሰማይ ለማየት በጣም ጓጉቼ ስለነበረ በጥንቃቄ ቀና ብዬ ስመለከት 28 አውሮፕላኖችን ቆጠርኩ!
በድንገት ከቦምቡ ፍንዳታ የተነሳ መሬቱ ተነቃነቀ። ምንም እንኳን የባቡር ጣቢያው በቦምብ ከመደብደብ ቢያመልጥም እኛን ይዞን የመጣው ባቡር ተመታ። እንክትክቱ የወጣውን ባቡርና ውልግድግድ ያሉትን የባቡር ሐዲዶች ማየት በጣም ያሳዝናል። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ካርቶኖቹን ይዤ ጉዞዬን ለመቀጠል ቻልኩ። ወታደሮቹ ደግሞ በሌላ ባቡር ጉዟቸውን ቀጠሉ። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ከወታደሮቹ አንዱ የይሖዋ ምስክር ሆነ። ወታደሮቹ ካርቶኖችን ይዞ አብሯቸው ስለነበረው ሲቪል ሰው በመገረም እንደተነጋገሩ ነገረኝ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወንድም ኮስኪነን በሰሜናዊ ፊንላንድ በሮቫኒሚ ከተማ በሚገኘው አነስተኛ ጉባኤ ለማገልገል ሲሄድ ከባቡሩ ከመውረዱ በፊት ተይዞ ወደ እስር ቤት ተወሰደ። በዚያም ከባድ ሥቃይ ደረሰበት። እኔ በዚሁ ጉባኤ ለማገልገል በሄድኩበት ጊዜ ኮይቩ በምትባለው አነስተኛ የባቡር ጣቢያ ስደርስ ከባቡሩ ለመውረድ ዝግጅት አደረግሁ። እዚያም እንደደረስኩ እኅት ሄልሚ ፓላሪ በወተት ማመላለሻ ጋሪ የቀረውን መንገድ እንድቀጥል ዝግጅት አደረገችልኝ። የሮቫኒሚ ጉባኤ ጉብኝቴ ተሳካ። ይሁን እንጂ ጉብኝቴን ጨርሼ ስመለስ ችግር አጋጠመኝ።
ከእኔ ጋር የነበረው የጉዞ ጓደኛዬና እኔ ወደ ባቡር ጣቢያው እየሄድን ሳለን የመንገደኞችን መታወቂያ እየመረመሩ ያሉ ሁለት ወታደሮች አጋጠሙን። “ወደ እነሱ አትመልከት። ቀጥ ብለህ ፊት ለፊት እያየህ ሂድ” አልኩ። በፍጹም እዚያ እንደሌሉ ያህል ዝም ብለን በመሐከላቸው አልፈን ሄድን። ከዚያም ያባርሩን ጀመር። ይሁን እንጂ ባቡር ጣቢያው ውስጥ ካለው ሕዝብ ጋር ተደባልቄ አመለጥኳቸውና በመንቀሳቀስ ላይ ያለ አንድ ባቡር ውስጥ ዘልዬ ገባሁ። የተጓዥነት ሥራ ባከናወንኩባቸው በእነዚያ ጊዜያት ብዙ አስደንጋጭ ነገሮች ያጋጥሙኝ ነበር።
አንድ ጊዜ ተያዝኩና ሲቪሎች ለወታደራዊ አገልግሎት ወደሚመለመሉበት ቦታ ተወሰድኩ። ዓላማው እኔን ወደ ጦር ግንባር ለመላክ ነበር። ሆኖም ስልኩ ጮኸና ጥያቄዎችን ሊያቀርብልኝ ተዘጋጅቶ የነበረው መኮንን ስልኩን አነሣ። “እነዚህን በሽተኛ የሆኑ የማይረቡ ሰዎች የምትልኩልን ለምንድን ነው? መልሰን እንልካቸዋለን። እኛ የምንፈልገው ለሥራ ብቁ የሆኑ ሰዎችን ነው” ብሎ ስልኩን የደወለው ሰው ሲጮኽ ይሰማኛል። እንደ አጋጣሚ ደግሞ የጤና ችግር እንዳለብኝ የሚገልጸውን የሐኪም ማስረጃዬን ይዤ ነበር። ይህን ማስረጃ ሳቀርብ በነፃ ተለቀቅሁ፤ ስለዚህ በጉባኤዎች መካከል የምሠራው ሥራ ሳይቋረጥ ቀጠለ።
በመከራ ወቅት መርዳት
ጦርነቱ እየተፋፋመና በጣም እየከፋ ሄደ። አህቲ ላኤስት የሚባለው ጓደኛዬ ተያዘ። ሚስቱ ስልክ ደወለችልኝና ቤታቸው ስሄድ አህቲ በከተማው የሕዝብ መናፈሻ ቦታዎች የተቀዱ ንግግሮችን እንዲያቀርብ ከአካባቢው ፖሊስ ፈቃድ እንደተሰጠው የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ከሌሎች ማስረጃዎቹ መካከል አገኘሁ። ማስረጃውን ይዘን ፍርድ ቤት ቀረብን። ዳኛው ክሱን አንብበው ከጨረሱ በኋላ እኔ ማስረጃውን ለወንድም ላኤስት ሰጠሁት። ዳኛው አንዱ ወታደር የሸክላ ማጫዎቻ እንዲያመጣና አብዛኞቹ በሸክላ የተቀረጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች ለፍርድ ቤቱ እንዲሰሙ አደረጉ። ዳኛው እያንዳንዱን ንግግር ከሰሙ በኋላ በንግግሩ ውስጥ ምንም ጥፋት እንዳላገኙበት ተናገሩ።
ከዚያም አህቲ፣ ሚስቱና እኔ ኮሪዶር ውስጥ ሆነን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንድንጠብቅ ተደረገ። የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለመስማት ተጨንቀን እንጠባበቅ ነበር። በመጨረሻም “ተከሳሽ እባክህ ወደ ፍርድ ቤቱ ግባ” የሚል ድምፅ ሰማን። ወንድም ላኤስት በነፃ ተለቀቀ! ሥራችንን እንደገና በመቀጠላችን ይሖዋን ከልብ አመሰገነው። ወንድም ላኤስትና እኅት ላኤስት በጉባኤያቸው ውስጥ ማገልገላቸውን ቀጠሉ፤ እኔ ደግሞ የተጓዥነት ሥራዬን ቀጠልኩ።
ጦርነቱ አበቃ፤ አገልግሎታችን ቀጠለ
ጦርነት ሲያበቃ በስብከት ሥራችን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነሣ። ወንድሞችም ከእስር ቤት ተለቀቁ። ባሳለፍኳቸው ብዙ የአገልግሎት ዓመታት ክርስቲያን እኅቶች በመንግሥቱ ሥራና ባሎቻቸውን በመርዳት ረገድ በሚጫወቱት ሚና ልቤ በጣም ተነክቷል። በተለይም ሲልቪያ ለከፈለቻቸው መሥዋዕትነቶችና ለሰጠችኝ ድጋፍ አመስጋኝ ነኝ። ከዚህም የተነሳ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ያለማቋረጥ ለ33 ዓመት እንድቀጥልና ከዚያም በኋላ ልዩ አቅኚ ሆኜ ለማገልገል ችያለሁ።
እኔና ሲልቪያ አርቶ ትምህርቱን ሲጨርስ አቅኚነትን እንዲጀምር፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተምሮ በአሜሪካ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት እንዲሰለጥን እናበረታታው ነበር። በ1953 ከጊልያድ ትምህርት ቤት ተመረቀ። ከዚያም በኋላ ኢቫን አገባ። ሁለቱም የክልል የበላይ ተመልካችነትን ሥራ፣ የቤቴል አገልግሎትንና ልዩ አቅኚነትን ጨምሮ በተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቶች ተካፍለዋል። በ1988 ልዩ አቅኚዎች ሆነው ማገልገላቸውን በመቀጠል እኔንና ሲልቪያን ለመጦር እኛ ወደምንኖርባት ከተማ ወደ ታምፐር ተዛወሩ።
እኔና ሲልቪያ ምንም እንኳን አሁን አቅማችን በጣም እየተዳከመ ቢሄድም ብዙ የሚያበረታቱን ትዝታዎች ያሉበት አስደሳችና የተባረከ ሕይወት አሳልፈናል። በዓይናችን ያየነውን እድገት ማሰብ ራሱ በጣም የሚያስደስት ነው። በ1939 እኔ ጉባኤዎችን መጎብኘት ስጀምር በፊንላንድ 865 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነበሩ። አሁን ግን ከ18,000 በላይ አስፋፊዎች አሉ!
በ1938 የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ስጀምር ከ55 ዓመትም በኋላ በዚህ ሥራ ላይ እገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ምንም እንኳን ዕድሜያችን እየገፋ ቢሄድም ቃል የተገባልንን ሽልማታችንን በጉጉት በመጠባበቅ በይሖዋ ኃይል መመላለሳችንን እንቀጥላለን። “እግዚአብሔር ቸር፣ ምሕረቱም ለዘላለም፣ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነውና” በሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ላይ ሙሉ እምነት አለን።—መዝሙር 100:5
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሊዮና ሲልቪያ ካሊዮ በ1934 ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በጥምቀት አሳይተዋል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሊዮና ሲልቪያ ለ60 ዓመት ያህል ራሳቸውን ወስነው ካገለገሉ በኋላ በቅርብ ጊዜ የተነሱት ፎቶ ግራፍ