የአንባብያን ጥያቄዎች
በመጀመሪያ ሔዋን በኋላም አዳም የበሉት መልካሙንና ክፉውን የሚያስታውቀው ፍሬ ፖም ነበርን?
ፖም ይሁን አይሁን አናውቅም። ብዙ ሰዎች ‘የተከለከለው ፍሬ’ ፖም ነበር ብለው ያስባሉ፤ ሠዓሊዎችም ለብዙ መቶ ዘመናት በተደጋጋሚ ፖም አስመስለው ሲሥሉት ቆይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የዛፉንም ሆነ የፍሬውን ስም አይጠቅስም። ሔዋንም ‘በገነት መካከል ያለ የዛፍ ፍሬ’ ከማለት በስተቀር ምንነቱን በውል አልተናገረችም።—ዘፍጥረት 3:3
ይህን በተመለከተ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ ላይ በእንግሊዝኛ “አፕል” በሚል ርዕስ የተሰጠው የሚከተለው ማብራሪያ ትኩረትን የሚስብ ሆኖ እናገኘዋለን፦
“ታፑአክ በሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገለጸውን ዛፍና ፍሬ ምንነት በተመለከተ ብዙ ግምታዊ ሐሳቦች ይሰነዘራሉ። ቃሉ ራሱ አንድን በመዓዛው ወይም በጥሩ ጠረኑ የታወቀ ፍሬ ያመለክታል። ይህ ቃል ‘እፍ ማለት፤ ትንፋሽ ቁርጥ ቁርጥ ማለት፤ መቃተት’ የሚል ትርጉም ካለው ናፓክ ከሚለው ቃል በእርባታ የተገኘ ነው። (ዘፍጥረት 2:7፤ ኢዮብ 31:39 አዓት፤ ኤርምያስ 15:9 የ1980 ትርጉም) ኤም ሲ ፊሸር ይህን በተመለከተ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ ‘ከቃሉ ጋር ያለው ግንኙነት በመጀመሪያ ጊዜ ሲታይ ከአግባብ ውጭ ይመስላል፤ ነገር ግን “ትንፋሽ” እና “ጥሩ መዓዛ ወደ ውጭ መተንፈስ” የሚሉት ሐሳቦች ከቃሉ ጋር ግንኙነት አላቸው። ተመሳሳይ መልእክት ለማስተላለፍ የሚያገለግለው ፑዋህ የሚለው ቃል ትርጉሙ “(ንፋስ) ነፈሰ” እና “ጥሩ መዓዛ ወደ ውጭ መተንፈስ፣ ጣፋጭ መዓዛ ያለው መሆን” የሚል ነው።—በ1980 በአር ኤል ሐሪስ የታተመው ቲኦሎጂካል ዎርድቡክ ኦቭ ዘ ኦልድ ቴስታመንትም ጥራዝ 2 ገጽ 586
“ከፖም ሌላም እንደ ብርቱካን፣ ትርንጎና ኮምጣጤ የመሳሰሉትን ጨምሮ በርካታ ፍራፍሬዎች ይሆናሉ የሚል ግምት ሲሰጣቸው ቆይቷል። . . . ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር የሚዛመደው ቱፋክ የሚለው የአረብኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉም ‘ፖም’ ማለት ሲሆን ታፑሐ እና ቤትታፑሐ የሚሉት የዕብራይስጥ የቦታ ስሞች (ምናልባትም ይህን ስም ያገኙት በእነዚህ አካባቢዎች ይህ ፍሬ በብዛት ስለሚገኝ ሊሆን ይችላል) በዚህ ቃል በመጠቀም ከአረብኛው ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ያለውን ስማቸውን እንደያዙ ቆይተዋል። (ኢያሱ 12:17፤ 15:34, 53፤ 16:8፤ 17:8) እነዚህ ቦታዎች የሚገኙት በቆላማ አካባቢ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ መካከለኛ የአየር ጠባይ ባለው ኮረብታማ አካባቢ የሚገኙ ናቸው። በተጨማሪም ቀደም ሲል አንዳንድ የአየር ጠባይ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሙሉ በሙሉ መዘንጋት የለበትም። በዛሬው ጊዜም በእስራኤል ውስጥ የፖም ዛፍ ይበቅላል። በዚህ መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ጋር በአጥጋቢ ሁኔታ የሚስማማ ይመስላል። ባለፈው መቶ ዘመን በሶሪያና በፍልስጤም ውስጥ በርካታ ዓመታት ያሳለፉት ዊሊያም ቶምሰን በፍልስጤም ሜዳ በአስቀሎን የፖም ተክል እንዳገኙ ገልጸዋል።—በ1910 በጄ ግራንድ ተሻሽሎ የታተመው ዘ ላንድ ኤንድ ዘ ቡክ የተባለው መጽሐፍ ገጽ 545, 546
“የፖም ዛፍ (ፓይረስ ማሉስ) በይበልጥ የተጠቀሰው በሰለሞን መዝሙር ውስጥ ነው። የሱናማይቱ ልጃገረድ ፍቅረኛ የሆነው እረኛ ከፖም ዛፍ ጥላና ከፍሬው ጣፋጭነት ጋር ተነፃጽሯል። (መኃልየ መኃልይ 2:3, 5) እሱ ደግሞ በተራው ትንፋሿን ከፖም መዓዛ ጋር ያወዳድራል። (መኃልየ መኃልይ 7:8፤ በተጨማሪም 8:5ን ተመልከት።) በምሳሌ (25:11) ላይ ትክክለኛና በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ‘በብር ፃሕል ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም’ ተደርጎ ተገልጿል። በሌላ ቦታ ላይ ፖም በቀጥታ የተጠቀሰው በኢዮኤል 1:12 ላይ ብቻ ነው። የተከለከለው የኤደን ፍሬ ፖም ነው የሚለው በዘልማድ በሰፊው የተሠራጨው እምነት ምንም ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የለውም። (በመዝሙር 17:8፤ በምሳሌ 7:2 እና በሌሎች ጥቅሶች ላይ) በእንግሊዝኛው ኪንግ ጀምስ ቨርሽን ‘የዓይን ፖም’ የሚል አገላለጽ እናገኛለን። ይህ ግን የዕብራይስጡ አገላለጽ አይደለም። የዕብራይስጡ አገላለጽ በቀጥታ ሲተረጎም ‘የዓይን ብሌን’ ማለት ነው።”—በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1988 የታተመው ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 131–2